ፍትሕንና ጽድቅን በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ
“ምሕረትንና ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር [ነኝ] . . . ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና።”—ኤርምያስ 9:24
1. ይሖዋ ምን ዓይነት አስደናቂ ተስፋ ሰጥቷል?
ይሖዋ ሁሉም ሰው እሱን የሚያውቅበት ቀን እንደሚመጣ ተናግሯል። በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” ብሏል። (ኢሳይያስ 11:9) ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው!
2. ይሖዋን ማወቅ ምንን ይጨምራል? ለምንስ?
2 ይሁንና ይሖዋን ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው? ይሖዋ ለኤርምያስ የላቀ ግምት የሚሰጠው ነገር ምን እንደሆነ ገልጾለታል:- “ምሕረትንና ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን [ማወቅና ማስተዋል]፤ . . . ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና።” (ኤርምያስ 9:24) ስለዚህ ይሖዋን ማወቅ ፍትሕና ጽድቅ የሚያሳይበትን መንገድ ማወቅን ይጨምራል። ከዚያም እነዚህን ባሕርያት የምናሳይ ከሆነ በእኛ ይደሰታል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ከጥንት ዘመን ጀምሮ አለፍጽምና ካለባቸው ሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተዘግቦ እንዲቆይ አድርጓል። ይህን በማጥናት የይሖዋን የፍትሕና የጽድቅ መንገድ ልናውቅ ብሎም እሱን ልንመስለው እንችላለን።—ሮሜ 15:4
ፍትሐዊ ግን ሩኅሩኅ
3, 4. ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ማጥፋቱ ፍትሐዊ የነበረው ለምንድን ነው?
3 በሰዶምና ገሞራ ላይ የደረሰው መለኮታዊ የቅጣት እርምጃ የይሖዋን ፍትሕ በርካታ ገጽታዎች የሚያሳይ በጣም ጥሩ ምሳሌ ነው። ይሖዋ ቅጣት የሚገባቸውን ሰዎች መቅጣት ብቻ ሳይሆን መዳን የሚገባቸውም ሊድኑ የሚችሉበትን መንገድ አዘጋጅቷል። የእነዚህ ከተሞች መጥፋት ፍትሐዊ ነበርን? አብርሃም በመጀመሪያ ላይ ፍትሐዊ አልመሰለውም ነበር። የሰዶም ክፋት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብዙም ያወቀ አይመስልም። ይሖዋ አሥር ጻድቅ ሰዎች ብቻ እንኳ ቢገኙ ከተማዋን እንደማያጠፋት ለአብርሃም አረጋግጦለት ነበር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የይሖዋ ፍትሕ ችኩልነት የሚንጸባረቅበት ወይም ምሕረት የለሽ አይደለም።—ዘፍጥረት 18:20-32
4 ሁለት መላእክት ያደረጉት ስለላ ሰዶም በሥነ ምግባር ለመበላሸቷ ጉልህ ማስረጃ ነበር። የከተማዋ ሰዎች ወደ ሎጥ ቤት የገቡ እንግዶች እንዳሉ ባወቁ ጊዜ እነዚህን ሰዎች አስገድደው ግብረሰዶም ሊፈጽሙባቸው ስለፈለጉ “ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ” የሎጥን ቤት ከብበው መደብደብ ጀመሩ። በእርግጥም በሥነ ምግባር አዘቅት ውስጥ ይገኙ ነበር! ይሖዋ በከተማዋ ላይ የወሰደው የቅጣት እርምጃ የጽድቅ እርምጃ እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም።—ዘፍጥረት 19:1-5, 24, 25
5. አምላክ ሎጥንና ቤተሰቡን ከሰዶም ያወጣቸው እንዴት ነበር?
5 ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰዶምንና የገሞራን ጥፋት የማስጠንቀቂያ ምሳሌ አድርጎ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን . . . ያውቃል።” (2 ጴጥሮስ 2:6-9) ጻድቁ ሎጥና ቤተሰቡ አምላካዊ ካልሆነው የሰዶም ሕዝብ ጋር በአንድ ላይ ቢጠፋ ኖሮ የተወሰደው የቅጣት እርምጃ ፍትሐዊ አይሆንም ነበር። ስለዚህ የይሖዋ መላእክት ሊመጣ ካለው ጥፋት እንዲያመልጥ ሎጥን አስጠንቅቀውታል። ሎጥ በዘገየ ጊዜ መላእክቱ ‘በይሖዋ ርኅራኄ’ የእሱን፣ የሚስቱንና የሴቶች ልጆቹን እጆች በመያዝ ከከተማዋ አወጧቸው። (ዘፍጥረት 19:12-16) ይሖዋ ጻድቅ የሆኑ ሰዎችን ወደፊት ከሚመጣው ከዚህ ክፉ ሥርዓት ጥፋት በማዳን ተመሳሳይ አሳቢነቱን እንደሚያሳያቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
6. ስለ መጪው የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት ከሚገባው በላይ መጨነቅ የሌለብን ለምንድን ነው?
6 የዚህ ሥርዓት ማብቂያ ‘ፍትሐዊ እርምጃ የሚወሰድበት’ ጊዜ ቢሆንም ከሚገባው በላይ ልንጨነቅ አይገባም። (ሉቃስ 21:22 NW) አምላክ በአርማጌዶን የሚወስደው የቅጣት እርምጃ ‘ሙሉ በሙሉ የጽድቅ እርምጃ’ ይሆናል። (መዝሙር 19:9 NW) አብርሃም እንደተገነዘበው እኛም በይሖዋ ፍትሕ ላይ ሙሉ ትምክህታችንን ልንጥል እንችላለን። የይሖዋ ፍትሕ ደግሞ ከእኛ ፍትሕ እጅግ የላቀ ነው። አብርሃም “የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” ሲል ጠይቋል። (ዘፍጥረት 18:25፤ ከኢዮብ 34:10 ጋር አወዳድር።) ወይም ደግሞ ኢሳይያስ በትክክል እንዳስቀመጠው “የፍርድንም [“የፍትሕንም፣” NW] መንገድ [ይሖዋን] ማን አስተማረው?”—ኢሳይያስ 40:14
የሰው ልጆችን ለማዳን የተወሰደ የጽድቅ እርምጃ
7. በአምላክ ፍትሕና በምሕረቱ መካከል ምን ግንኙነት አለ?
7 የአምላክ ፍትሕ የሚገለጠው መጥፎ የሠሩ ሰዎችን በሚቀጣበት ጊዜ ብቻ አይደለም። ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር “ጻድቅ አምላክና መድኃኒት” እንደሆነ ገልጿል። (ኢሳይያስ 45:21) በግልጽ እንደሚታየው በአምላክ ጽድቅ ወይም ፍትሕና የሰው ልጆችን ከኃጢአት ውጤቶች ለማዳን ባለው ፍላጎት መካከል የቅርብ ግንኙነት አለ። በ1982 የተዘጋጀው ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይከለፒዲያ የተባለው መጽሐፍ በዚህ ጥቅስ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ “የአምላክ ፍትሕ ምሕረቱን ለማሳየትና ማዳኑን ለመፈጸም የሚችልባቸውን ተጨባጭ መንገዶች ይፈልጋል።” ይህ የሆነው የአምላክ ፍትሕ በምሕረት መለዘብ ስለሚያስፈልገው ሳይሆን ምሕረት የአምላክ ፍትሕ መግለጫ ስለሆነ ነው። አምላክ ለሰው ልጆች መዳን ቤዛ ማዘጋጀቱ የዚህ መለኮታዊ ፍትሕ ገጽታ ታላቅ ምሳሌ ነው።
8, 9. (ሀ) “አንድ የጽድቅ ሥራ” በሚለው መግለጫ ውስጥ የተካተተው ነገር ምን ነበር? ለምን? (ለ) ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
8 ራሱ የቤዛው ዋጋ ማለትም የአምላክ አንድያ ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ውድ ሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነው፤ ምክንያቱም የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ለሁሉም የሚሠሩ ሲሆኑ ራሱ ይሖዋም በእነዚሁ ይመራል። (ማቴዎስ 20:28) ፍጹም የነበረው የአዳም ሕይወት በመጥፋቱ የአዳምን ተወላጆች ሕይወት ለመቤዠት ሌላ ፍጹም ሕይወት ያስፈልግ ነበር። (ሮሜ 5:19-21) ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ የከፈለውን ቤዛና ፍጹም አቋም ጠባቂነቱን “አንድ የጽድቅ ሥራ” ሲል ጠርቶታል። (ሮሜ 5:18 NW፣ የግርጌ ማስታወሻ) እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? ምንም እንኳ ከፍተኛ ዋጋ መክፈል ቢጠይቅበትም በይሖዋ አመለካከት የሰው ልጆችን መቤዠት ትክክልና ፍትሐዊ ነበር። የአዳም ልጆች አምላክ ሊሰብረው እንዳልፈለገ ‘የተቀጠቀጠ ሸምበቆ’ ወይም ሊያጠፋው እንዳልፈለገ ‘የሚጤስ የጥዋፍ ክር’ ነበሩ። (ማቴዎስ 12:20) አምላክ ከአዳም ዘሮች መካከል ታማኞች የሆኑ ብዙ ወንዶችና ሴቶች እንደሚነሱ እርግጠኛ ነበር።—ከማቴዎስ 25:34 ጋር አወዳድር።
9 ለዚህ ከፍተኛ የፍቅርና የፍትሕ መግለጫ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለብን? ይሖዋ በምላሹ ‘ፍትሕን እንድናሳይ’ ይፈልጋል። (ሚክያስ 6:8 NW) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ፍትሕን ፈልጉ፣ ጽድቅን ተከታተሉ
10. (ሀ) ፍትሕን ልናሳይ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) አስቀድመን የአምላክን ጽድቅ ልንፈልግ የምንችለው እንዴት ነው?
10 በመጀመሪያ ደረጃ ከአምላክ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ጋር መስማማት አለብን። ምክንያቱም የአምላክ የአቋም ደረጃዎች ፍትሐዊና ትክክለኛ በመሆናቸው ከእነርሱ ጋር ተስማምተን ስንኖር ፍትሕን እናሳያለን። ይሖዋ ከሕዝቦቹ የሚጠብቀው ይህን ነው። ይሖዋ እስራኤላውያንን “መልካም መሥራትን ተማሩ፣ ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] ፈልጉ” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 1:17) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ እያዳመጡት የነበሩትን ሰዎች ‘አስቀድመው የአምላክን መንግሥት ጽድቁንም እንዲፈልጉ’ ባዘዛቸው ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ ምክር ለግሷል። (ማቴዎስ 6:33) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘ጽድቅን እንዲከታተል’ መክሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11) አምላክ ጠባይን በተመለከተ ካወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተን ስንኖርና አዲሱን ሰው ስንለብስ ትክክለኛ ፍትሕንና ጽድቅን እየተከታተልን ነው ማለት ነው። (ኤፌሶን 4:23, 24) በሌላ አባባል የምናደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ በአምላክ መንገድ በመሥራት ፍትሕ ለማሳየት እንጥራለን።
11. ኃጢአት ጌታችን እንዳይሆን መከላከል ያለብን ለምንና እንዴት ነው?
11 ሁላችንም እንደምናውቀው አለፍጽምና ላለባቸው ሰዎች ሁልጊዜ ፍትሕን ማሳየትና ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ቀላል አይደለም። (ሮሜ 7:14-20) ጳውሎስ በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖች ለአምላክ የወሰኑትን ሰውነት “የጽድቅ የጦር ዕቃ” አድርገው ማቅረብ ይችሉ ዘንድ ኃጢአት ጌታቸው እንዳይሆን አጥብቀው እንዲዋጉ አበረታቷቸዋል። ይህ ደግሞ አምላክ ዓላማውን እንዲያከናውን ያስችለዋል። (ሮሜ 6:12-14) በተመሳሳይም የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናትና ተግባራዊ በማድረግ ‘የይሖዋን ምክር’ ልንቀስምና ‘በጽድቅ መንገድ ልንታረም’ እንችላለን።—ኤፌሶን 6:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
12. ይሖዋ እኛን እንዲይዘን በምንፈልግበት መንገድ ሌሎችን ለመያዝ ከፈለግን ምን ነገር ማስወገድ አለብን?
12 በሁለተኛ ደረጃ፣ ይሖዋ እኛን እንዲይዘን በምንፈልግበት መንገድ ሌሎችን የምንይዝ ከሆነ ፍትሕን እናሳያለን። ለራሳችን ላላ ያለ ለሌሎች ግን ጥብቅ የሆነ ሁለት ዓይነት መስፈርት ማውጣቱ ቀላል ነው። ለራሳችን ስህተቶች ምክንያት መደርደር የሚቀናን ሲሆን ሌሎች ሰዎች ከእኛ ጋር ሲተያዩ ከቁብ የማይቆጠሩ ስህተቶችን ሲሠሩ ግን ለመንቀፍ እንቸኩላለን። ኢየሱስ “በወንድምህም ዓይን ያለውን ጕድፍ ስለ ምን ታያለህ፣ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?” የሚል ጠንከር ያለ ጥያቄ አቅርቧል። (ማቴዎስ 7:1-3) ይሖዋ ጉድለቶቻችንን ቢመረምር አንዳችንም በፊቱ መቆም እንደማንችል በፍጹም መርሳት የለብንም። (መዝሙር 130:3, 4) የይሖዋ ፍትሕ የወንድሞቻችንን ድክመቶች እንዲያልፍ የሚያደርገው ከሆነ እኛ በእነርሱ ላይ የምንፈርደው ማን ነን?—ሮሜ 14:4, 10
13. ጻድቅ የሆነ ሰው ስለ መንግሥቱ ምሥራች መስበክ እንዳለበት ሆኖ የሚሰማው ለምንድን ነው?
13 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ስንካፈል አምላካዊ ፍትሕ እናሳያለን። ይሖዋ “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” በማለት ይመክረናል። (ምሳሌ 3:27) አምላክ በልግስና የሰጠንን ሕይወት ሰጪ እውቀት ለራሳችን ብቻ ማስቀረቱ ተገቢ አይደለም። እርግጥ ብዙ ሰዎች መልእክታችንን አይቀበሉት ይሆናል፤ ነገር ግን አምላክ ምሕረቱን እስከዘረጋላቸው ድረስ ‘ወደ ንስሐ መድረስ’ የሚችሉበትን አጋጣሚ መስጠታችንን ለመቀጠል ፈቃደኞች መሆን አለብን። (2 ጴጥሮስ 3:9) እንዲሁም ልክ እንደ ኢየሱስ አንድ ሰው ፊቱን ወደ ፍትሕና ጽድቅ እንዲመልስ መርዳት ስንችል እጅግ እንደሰታለን። (ሉቃስ 15:7) ‘በጽድቅ የምንዘራበት’ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ አሁን ነው።—ሆሴዕ 10:12
‘ለፍትሕ የቆሙ መሳፍንት’
14. ፍትሕን በሚመለከት ሽማግሌዎች ምን ሚና ይጫወታሉ?
14 ሁላችንም በጽድቅ መንገድ መጓዝ ቢኖርብንም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ልዩ ኃላፊነት አለባቸው። የኢየሱስ መስፍናዊ አገዛዝ ‘በፍትሕና በጽድቅ የጸና’ ነው። በተመሳሳይም ሽማግሌዎች መስፈርት አድርገው የሚጠቀሙት መለኮታዊውን ፍትሕ ነው። (ኢሳይያስ 9:7) በኢሳይያስ 32:1 ላይ በትንቢት የተገለጸውን ነገር በአእምሯቸው ያስቀምጣሉ:- “እነሆ፣ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፣ መሳፍንትም በፍርድ [“በፍትሕ” NW] ይገዛሉ።” ሽማግሌዎች በአምላክ መንፈስ የተቀቡ የበላይ ተመልካቾች ወይም ‘የአምላክ መጋቢዎች’ እንደመሆናቸው መጠን ነገሮችን በአምላክ መንገድ ማከናወን ይገባቸዋል።—ቲቶ 1:7
15, 16. (ሀ) ሽማግሌዎች በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰውን ታማኝ እረኛ ሊመስሉ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ስለ ጠፉ ሰዎች ምን ይሰማቸዋል?
15 ኢየሱስ የይሖዋ ፍትሕ ሩኅሩኅ፣ መሐሪና ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግር ያለባቸውን ለመርዳት እንዲሁም ‘የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን’ ጥሯል። (ሉቃስ 19:10) በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው እረኛ የጠፋውን በግ እስኪያገኘው ድረስ ያለመታከት እንደፈለገው ሁሉ ሽማግሌዎችም በመንፈሳዊ የጠፉትን ይፈልጋሉ እንዲሁም ወደ መንጋው እንዲመለሱ ለማድረግ ይጥራሉ።—ማቴዎስ 18:12, 13
16 ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችን ከመኮነን ይልቅ የሚቻል ከሆነ እነሱን ለመፈወስና ንስሐ እንዲገቡ ለመርዳት ይሻሉ። አንድን የባዘነ ሰው ለመርዳት ሲችሉ ይደሰታሉ። ይሁንና በደለኛ ሰው ንስሐ ሳይገባ ሲቀር ያዝናሉ። በዚህ ጊዜ የአምላክ የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ንስሐ ያልገባውን ሰው እንዲያስወግዱት ይጠብቁባቸዋል። ያም ሆኖ ግን እንደ ኮብላዩ ልጅ አባት ይህ በደለኛ አንድ ቀን ‘ወደ አእምሮው ሊመለስ’ እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ። (ሉቃስ 15:17, 18) ስለዚህ ሽማግሌዎች ራሳቸው ቅድሚያውን በመውሰድ አንዳንድ የተወገዱ ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት ሊመለሱ የሚችሉበትን መንገድ እንዲያስቡበት ለማድረግ ሲሉ ሄደው ያነጋግሯቸዋል።a
17. ሽማግሌዎች ስህተት የሠሩ ሰዎችን ጉዳይ የሚመለከቱት ምንን ግብ በማድረግ ነው? ወደዚህ ግብ ለመድረስስ የትኛውን ባሕርይ ማዳበራቸው ይረዳቸዋል?
17 ሽማግሌዎች በተለይ መጥፎ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎችን ጉዳይ በሚመለከቱበት ጊዜ የይሖዋን ፍትሕ ሊኮርጁ ይገባል። ኃጢአተኞች፣ ያለባቸውን ችግር ኢየሱስ እንደሚገነዘብና እንደሚረዳቸው ስለ ተሰማቸው “ወደ እርሱ ይቀርቡ” ነበር። (ሉቃስ 15:1፤ ማቴዎስ 9:12, 13) እርግጥ ኢየሱስ ክፋትን ችላ ብሎ ያልፍ ነበር ማለት አይደለም። የሕዝቡን ገንዘብ በመበዝበዝ መጥፎ ስም አትርፎ የነበረው ዘኬዎስ በአንድ ግብዣ ላይ ከኢየሱስ ጋር የተወሰነ ጊዜ በማሳለፉ ብቻ ንስሐ ለመግባትና በሌሎች ላይ ላደረሰው ሥቃይ ማካካሻ የሚሆን ነገር ለማድረግ ተገፋፍቷል። (ሉቃስ 19:8-10) ዛሬም ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን በሚሰሙበት ጊዜ ዋናው ግባቸው ስህተት የፈጸመው ሰው ንስሐ እንዲገባ መርዳት ነው። ሽማግሌዎች እንደ ኢየሱስ የሚቀረቡ ከሆኑ ጥፋት የፈጸሙ ብዙ ሰዎች እርዳታቸውን ለመጠየቅ ቀላል ይሆንላቸዋል።
18. ሽማግሌዎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” እንዲሆኑ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
18 ሽማግሌዎች የሰውን ሐሳብና ስሜት ከልብ ለመረዳት መጣራቸው መለኮታዊውን ፍትሕ ተግባራዊ ለማድረግ ስለሚረዳቸው ውሳኔያቸው አሳቢነትና ርኅራኄ የጎደለው አይሆንም። ዕዝራ እስራኤላውያንን ፍትሕ ለማስተማር አእምሮውን ብቻ ሳይሆን ልቡንም ዝግጁ ማድረጉ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዕዝራ 7:10) ሽማግሌዎች አስተዋይ ልብ ካላቸው ተገቢውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግና የእያንዳንዱን ግለሰብ ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይችላሉ። ኢየሱስ ደም ይፈሳት የነበረችውን ሴት በፈወሰበት ጊዜ የይሖዋ ፍትሕ የሕጉን መንፈስም ሆነ የሕጉን ፊደላት መረዳት የሚጠይቅ እንደሆነ አሳይቷል። (ሉቃስ 8:43-48) በራሳቸው ድክመት ወይም በምንኖርበት በዚህ ክፉ ሥርዓት ምክንያት ለተንገላቱ ሰዎች በደግነት ፍትሕን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሽማግሌዎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” ይሆናሉ።—ኢሳይያስ 32:2
19. አንዲት እህት ለመለኮታዊ ፍትሕ አሠራር ምን ምላሽ ሰጠች?
19 ከባድ ኃጢአት ፈጽማ የነበረች አንዲት እህት መለኮታዊውን ፍትሕ በራሷ ላይ ከደረሰው ሁኔታ በሚገባ ልትገነዘብ ችላለች። “በእውነት ለመናገር ሽማግሌዎቹን ለማነጋገር ፈርቼ ነበር” ስትል ተናግራለች። “ይሁን እንጂ በርኅራኄና በአክብሮት መንፈስ ነበር ያነጋገሩኝ። ሽማግሌዎቹ እንደ ኃይለኛ ዳኛ ሳይሆን ልክ እንደ አፍቃሪ አባት ነበሩ። መንገዴን ለማስተካከል ቁርጥ ውሳኔ ካደረኩ ይሖዋ እንደማይተወኝ እንዳስተውል ረድተውኛል። ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት እንዴት እንደሚገስጸን በራሴ ላይ ከደረሰው ሁኔታ በሚገባ ተምሬአለሁ። ልመናዬን እንደሚሰማ በመተማመን ልቤን ለይሖዋ ለመክፈት ችዬ ነበር። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ከሽማግሌዎቹ ጋር ያደረግሁት ያ ውይይት ከይሖዋ የተገኘ በረከት ነው ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእሱ ጋር ያለኝ ዝምድና ይበልጥ ጠንክሯል።”
ፍትሕን ጠብቁ፣ ጽድቅ የሆነውንም አድርጉ
20. ፍትሕንና ጽድቅን ማስተዋልና ማሳየት ምን ጥቅሞች ያስገኛል?
20 መለኮታዊ ፍትሕ ማለት ለእያንዳንዱ ሰው የሚገባውን መስጠት ማለት ብቻ አለመሆኑ የሚያስደስት ነው። የይሖዋ ፍትሕ እምነት ለሚያሳዩ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ገፋፍቶታል። (መዝሙር 103:10፤ ሮሜ 5:15, 18) አምላክ እኛን በዚህ መንገድ የሚይዝበት ምክንያት ፍትሑ ሁኔታዎቻችንን ከግምት ውስጥ ስለሚያስገባና ሊኮንነን ሳይሆን ሊያድነን ስለሚፈልግ ነው። በእርግጥም የይሖዋ ፍትሕ ስላለው ስፋት የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታችን ይበልጥ ወደ እርሱ ያቀርበናል። እንዲሁም ይህን የባሕርዩን ገጽታ ለመኮረጅ ስንጥር የእኛም ሆነ የሌሎች ሰዎች ሕይወት በእጅጉ ይባረካል። የሰማዩ አባታችን ፍትሕን ለመከታተል የምናደርገውን ጥረት ይመለከተዋል። ይሖዋ “ማዳኔ ሊመጣ ጽድቄም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] ጠብቁ ጽድቅንም አድርጉ። ይህን የሚያደርግ ሰው . . . ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” ሲል ቃል ገብቶልናል።—ኢሳይያስ 56:1, 2
[የግርጌ ማስታወሻ]
[ታስታውሳለህን?]
◻ የሰዶምና ገሞራ መጥፋት ስለ ይሖዋ ፍትሕ ምን ያስተምረናል?
◻ ቤዛው የአምላክ ፍትሕና ፍቅር ታላቅ መግለጫ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ፍትሕ ልናሳይ የምንችልባቸው ሦስት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
◻ ሽማግሌዎች መለኮታዊውን ፍትሕ ሊኮርጁ የሚችሉት በየትኛው ልዩ መንገድ ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በስብከት እንቅስቃሴያችን አምላካዊ ፍትሕ እናሳያለን
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች አምላካዊ ፍትሕ የሚያሳዩ ከሆነ ችግር ያለባቸው ሰዎች እርዳታቸውን ለመጠየቅ ቀላል ይሆንላቸዋል