የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የናሆም፣ የዕንባቆምና የሶፎንያስ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች
የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረው አሦር፣ አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ የሆነችውን ሰማርያን አጥፍቷታል። አሦር ይሁዳንም ቢሆን ስጋት ላይ ጥሏት ነበር። በይሁዳ ይኖር የነበረው ነቢዩ ናሆም የአሦር መዲና በሆነችው በነነዌ ላይ የሚያውጀው የፍርድ መልእክት አለው። በ632 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈው የናሆም መጽሐፍ ይህን መልእክት ይዟል።
ከአሦር ቀጥሎ የተነሳው የዓለም ኃያል መንግሥት፣ አልፎ አልፎ ከለዳውያን ነገሥታት ይገዙበት የነበረው የባቢሎን መንግሥት ነው። በ628 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ተጽፎ የተጠናቀቀው የዕንባቆም መጽሐፍ፣ ይሖዋ የጥፋት ፍርዱን ለማስፈጸም በዚህ የዓለም ኃያል መንግሥት የሚጠቀመው እንዴት እንደሆነና የባቢሎን አወዳደቅ ምን እንደሚመስል የሚገልጽ ትንቢት ይዟል።
በይሁዳ የሚኖረው ነቢዩ ሶፎንያስ ትንቢት መናገር የጀመረው ከናሆምም ሆነ ከዕንባቆም በፊት ነው። ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመጥፋቷ ከ40 ዓመት በፊት በይሁዳ ላይ የጥፋት ፍርድና ተስፋ ያዘለ መልእክት አውጇል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሶፎንያስ መጽሐፍ በሌሎች ብሔራት ላይ የተነገሩ የፍርድ መልእክቶችን አካትቷል።
“ለደም ከተማ ወዮላት!”
‘በነነዌ ላይ የጥፋት ንግር’ ያስነገረው “ለቍጣ የዘገየ በኀይሉም ታላቅ” የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ይሖዋ በእሱ ለሚታመኑ ሰዎች ‘በጭንቅ ጊዜ መሸሸጊያ’ የሚሆንላቸው ቢሆንም ነነዌ ግን መጥፋት ነበረባት።—ናሆም 1:1, 3, 7
ይሖዋ ‘የያዕቆብን ክብር መመለሱ’ አይቀርም። ያም ሆኖ አሦራውያን ‘እንደ አንበሳ’ የአምላክን ሕዝቦች ሲያሸብሯቸው ቆይተዋል። ይሖዋ ‘የነነዌን ሠረገሎች አቃጥሎ ያጨሳቸዋል፤ ደቦል አንበሶቻቸውንም ሰይፍ ይበላቸዋል።’ (ናሆም 2:2, 12, 13) ‘የደም ከተማ’ ለሆነችው ለነነዌ “ወዮላት!” ስለ እሷ ‘የሰማ ሁሉ፣ በውድቀቷ ደስ ብሎት ያጨበጭባል።’—ናሆም 3:1, 19
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:9—የነነዌ ሙሉ በሙሉ ‘መጥፋት’ ለይሁዳ ምን ትርጉም አለው? ይሁዳ ከአሦራውያን ስጋት ለዘለቄታው እፎይታ የምታገኝ ከመሆኑም በላይ “መከራም ዳግመኛ አይነሣም።” ናሆም ነነዌ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደምትጠፋ ሲናገር እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነሆ፤ የምሥራች የሚያመጣውን፣ ሰላምን የሚያውጀው ሰው እግር፣ በተራሮች ላይ ነው፤ ይሁዳ ሆይ፤ በዓላትህን አክብር።”
2:6—‘ወለል ብለው የተከፈቱት የወንዝ በሮች’ ምንድን ናቸው? እነዚህ በሮች የሚያመለክቱት የጤግሮስ ወንዝ የነነዌን ግንብ አፍርሶ ሲገባ የተፈጠሩትን ክፍተቶች ነው። ነነዌ በ632 ከክርስቶስ ልደት በፊት የባቢሎናውያንና የሜዶናውያን ጥምር ኃይል ሊወጋት ሲመጣ ምንም ፍርሃት አልተሰማትም ነበር። ነነዌ በትላልቅ ግንቦቿ በመመካት፣ ራሷን የማትበገር ከተማ እንደሆነች አድርጋ ትቆጥር ነበር። ይሁን እንጂ ከባድ ዝናብ በመዝነቡ ሳቢያ የጤግሮስ ወንዝ ሞልቶ ፈሰሰ። የታሪክ ጸሐፊው ዲዶረስ እንደዘገበው “ከተማዋ በከፊል የተጥለቀለቀች ሲሆን በግንቦቿ ላይም ሰፋፊ ክፍተቶች ተፈጥረው ነበር።” በመሆኑም የወንዞቹ በሮች ተከፈቱ፤ በትንቢት እንደተነገረው ሁሉ እሳት ገለባን እንደሚበላ ነነዌም ወዲያውኑ በጠላቶቿ ቁጥጥር ሥር ዋለች።—ናሆም 1:8-10
3:4—ነነዌ ዘማዊት የሆነችው በምን መንገድ ነው? ነነዌ ከሌሎች መንግሥታት ጋር መወዳጀትና እነሱን መርዳት የምትፈልግ መስላ በመቅረብ የኋላ ኋላ የጭቆና ቀንበሯን ትጭንባቸዋለች። ለምሳሌ ያህል፣ ሶርያና እስራኤል የይሁዳ ንጉሥ በነበረው በአካዝ ላይ ባሴሩ ጊዜ አሦር ለንጉሡ መጠነኛ ድጋፍ አድርጋ ነበር። ውሎ አድሮ ግን ‘የአሦር ንጉሥ ወደ እሱ [አካዝ] መጣ፤ ችግርም ፈጠረበት።’—2 ዜና መዋዕል 28:20
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2-6፦ ይሖዋ እሱን ብቻ ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆኑ ጠላቶቹን ተበቅሏቸዋል። ይህም ሕዝቦቹ እሱን ብቻ እንዲያመልኩት እንደሚጠብቅባቸው ያሳያል።—ዘፀአት 20:5
1:10፦ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማማዎች ያሏቸው ትላልቅ የሆኑት የነነዌ ግንቦች ይሖዋ በከተማዋ ላይ ያስነገረው የፍርድ መልእክት እንዳይፈጸም እንቅፋት አልሆኑም። በዛሬው ጊዜም ቢሆን የይሖዋ ሕዝብ ጠላቶች ከአምላክ የቅጣት ፍርድ አያመልጡም።—ምሳሌ 2:22፤ ዳንኤል 2:44
‘ጻድቅ በሕይወት ይኖራል’
የዕንባቆም መጽሐፍ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች በነቢዩና በይሖዋ መካከል የተደረገውን የቃላት ምልልስ ይዘዋል። ዕንባቆም በይሁዳ ያለው ሁኔታ በጣም ስላስጨነቀው አምላክን “ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ?” ሲል ጠየቀው። ይሖዋም “ምድርን ሁሉ የሚወሩትን፣ ጨካኝና ፈጣን የሆኑትን፣ ባቢሎናውያንን አስነሣለሁ” ሲል መለሰለት። ይህ ነቢይ፣ አምላክ ይሁዳን ለመቅጣት እነዚህን “አታላዮች” የሚጠቀም መሆኑ አስደንቆታል። (ዕንባቆም 1:3, 6, 13) ዕንባቆም ጻድቃን በሕይወት እንደሚኖሩና ጠላቶቻቸው ግን ከቅጣት እንደማያመልጡ እርግጠኛ ነበር። ከዚህም በላይ ዕንባቆም በከለዳውያን ላይ የሚደርሱባቸውን አምስት ወዮታዎች ዘግቧል።—ዕንባቆም 2:4 የ1954 ትርጉም
ዕንባቆም የአምላክን ምሕረት ለማግኘት በሐዘን እንጉርጉሮ መልክ ባቀረበው ጸሎት ላይ በጥንት ዘመን የይሖዋ ታላቅ ኃይል የታየባቸውን በቀይ ባሕር፣ በምድረ በዳና በኢያሪኮ የተፈጸሙ ክንውኖችን ተርኳል። በተጨማሪም ይሖዋ በአርሜዶን ስለሚያመጣው ጥፋት ተንብዮአል። ነቢዩ ጸሎቱን የደመደመው በሚከተሉት ቃላት ነው:- “ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ኀይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።”—ዕንባቆም 3:1, 19
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1:5, 6—ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ላይ ይነሳሉ የሚለው ሐሳብ ለአይሁዳውያን የማይታመን የሆነባቸው ለምንድን ነው? ነቢዩ ዕንባቆም ትንቢት መናገር በጀመረበት ወቅት ይሁዳ በግብጽ ተጽዕኖ ሥር ነበረች። (2 ነገሥት 23:29, 30, 34) በዚያን ወቅት ባቢሎናውያን ኃያል እየሆኑ ቢሄዱም ሠራዊታቸው የፈርዖን ኒካዑን ጦር ገና ድል አላደረገም ነበር። (ኤርምያስ 46:2) ከዚህም በላይ፣ የይሖዋ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረ ሲሆን መቀመጫውን በከተማ ውስጥ ያደረገው የዳዊት ሥርወ መንግሥትም መግዛቱን አላቆመም። በመሆኑም በጊዜው ለነበሩት አይሁዳውያን አምላክ በኢየሩሳሌም ላይ ‘አንድ ነገር ያደርጋል’ ይኸውም ከለዳውያን እንዲያጠፏት ይፈቅዳል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይታመን ነገር ነበር። አይሁዳውያን ዕንባቆም የተናገራቸውን ቃላት ለማመን አዳጋች ቢሆንባቸውም እንኳ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንደሚያጠፏት የተነገረው ትንቢት በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በእርግጥ ወደ ፍጻሜው ‘መጥቷል።’—ዕንባቆም 2:3
2:5 NW—እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ሰው” ማን ነው? “ከቶ አይሳካለትም” የተባለውስ ለምንድን ነው? በወታደራዊ ስልታቸው ተጠቅመው ሌሎች ብሔራትን ድል የሚያደርጉት ባቢሎናውያን ልክ እንደ አንድ “ሰው” ነበሩ። ይህ ሰው ድል ሲያደርግ በወይን ጠጅ የሰከረ ሰው ዓይነት ስሜት ይሰማዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሜዶናውያንን እና ፋርሳውያንን ተጠቅሞ ስለሚያጠፋው ሕዝቦችን ለራሱ ለመሰብሰብ የሚያደርገው ጥረት አይሳካለትም። በዘመናችን ያለው “ሰው” ደግሞ በፖለቲካ ኃይሎች የተገነባ ነው። እሱም በራስ በመመራትና በእብሪት መንፈስ የሰከረ ሲሆን ግዛቱን ይበልጥ የማስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ይሁን እንጂ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ለራሱ’ ለመሰብሰብ ያለው እቅድ አይሳካለትም። የሰው ልጆችን አንድ ማድረግ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:1-4፤ 1:12 እስከ 2:1፦ ዕንባቆም በቅንነት ተነሳስቶ ጥያቄዎችን ጠይቋል፤ ይሖዋም መልስ ሰጥቶታል። እውነተኛው አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል።
2:1 [NW]፦ ልክ እንደ ዕንባቆም በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መኖር አለብን። በተጨማሪም ከሚሰጠን ከማንኛውም “ተግሣጽ” ወይም እርማት ጋር አስተሳሰባችንን ለማስማማት ዝግጁ ልንሆን ይገባል።
2:3፤ 3:16፦ የይሖዋን ቀን መምጣት በእምነት ስንጠባበቅ የጥድፊያ ስሜታችን እንዳይጠፋ እንጠንቀቅ።
2:4፦ ከመጪው የይሖዋ የፍርድ ቀን ለመትረፍ በታማኝነት መጽናት ይኖርብናል።—ዕብራውያን 10:36-38
2:6, 7, 9, 12, 15, 19፦ ያለ አግባብ የሚገኝን ጥቅም የሚያሳድዱ፣ ዓመጽን የሚወዱ፣ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወዮታ እንደሚደርስባቸው እሙን ነው። እነዚህ ጎጂ ባሕርያትና ልማዶች እንዳይጠናወቱን መጠንቀቅ ይኖርብናል።
2:11፦ የዚህን ዓለም ክፋት ከማጋለጥ ወደኋላ የምንል ከሆነ ‘ድንጋይ ራሱ መጮኹ’ አይቀርም። የመንግሥቱን መልእክት ሳናሰልስ በድፍረት መስበካችን አስፈላጊ ነው!
3:6፦ ይሖዋ ፍርዱን ከማስፈጸም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ እንደ ተራራና እንደ ኮረብታ ጽኑ መስለው የሚታዩት ሰብዓዊ ድርጅቶች እንኳ ይህን ማድረግ አይችሉም።
3:13፦ አርማጌዶን ሁሉንም ሰው በጅምላ የሚያጠፋ ላለመሆኑ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ይታደጋቸዋል።
3:17-19፦ ከአርማጌዶን በፊትም ሆነ በዚያን ወቅት ችግሮች ሊያጋጥሙን ቢችሉም ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን እስከቀጠልን ድረስ የሚያስፈልገንን ‘ኃይል’ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን።
“የይሖዋ ቀን ቀርቧል”
የበኣል አምልኮ በይሁዳ እጅግ ተስፋፍቷል። ይሖዋ “እጄን በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አነሣለሁ” ሲል በነቢዩ ሶፎንያስ በኩል ተናገረ። ሶፎንያስም “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ቀርቧል” በማለት አስጠንቅቋል። (ሶፎንያስ 1:4, 7, 14) በዚያን ቀን ከጥፋት ‘የሚሰወሩት’ የአምላክን መሥፈርቶች የሚያሟሉ ብቻ ናቸው።—ሶፎንያስ 2:3
“ለጨቋኞች ከተማ [ለኢየሩሳሌም] ወዮላት! እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንዲህ ይላል፤ ‘ስለዚህ እስከምፈርድበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፤ አሕዛብን ላከማች፣ . . . መዓቴን . . . በላያቸው ላፈስ ወስኛለሁ።’” ይሁንና አምላክ “ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኮአችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል።—ሶፎንያስ 3:1, 8, 20
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
3:9 የ1954 ትርጉም—‘ንጹሕ ልሳን’ ምንድን ነው? የሚነገረውስ እንዴት ነው? ንጹሕ ልሳን የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ እውነት ነው። ይህ ልሳን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በሙሉ ያጠቃልላል። እውነትን በማመን፣ እውነትን ለሌሎች በትክክል በማስተማርና ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተን በመኖር ይህን ልሳን መናገር እንችላለን።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:8፦ በሶፎንያስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በዙሪያቸው ባሉት ብሔራት ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ‘እንግዳ ልብስ ይለብሱ’ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አምላኪዎችም በዓለም ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ተመሳሳይ ነገር ቢያደርጉ እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆናል!
1:12 [የ1954 ትርጉም]፤ 3:5, 16፦ ይሖዋ ስለ መለኮታዊ ፍርድ በመናገር ሕዝቦቹን እንዲያስጠነቅቋቸው ነቢያቱን በየጊዜው ይልክ ነበር። ምንም እንኳ በርካታ አይሁዳውያን በወይን ጠጅ ጋን ውስጥ እንደሚገኝ አተላ ተደላድለው የተቀመጡና ለመልእክቱ ግዴለሾች ቢሆኑም ይሖዋ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አላለም። ታላቁ የይሖዋ ቀን በቀረበ መጠን የሰዎች ግዴለሽነት ተስፋ አስቆርጦን ‘እጃችን እንዲዝል’ ከመፍቀድ ይልቅ የመንግሥቱን መልእክት ያለማሰለስ ማወጅ ይኖርብናል።
2:3፦ ከይሖዋ የቁጣ ቀን ሊያድነን የሚችለው እሱ ብቻ ነው። የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘን መቀጠል ከፈለግን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ በጸሎት አማካኝነት መመሪያውን በመጠየቅና ይበልጥ ወደ እሱ በመቅረብ ይሖዋን ‘መሻት’ ይገባናል። በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነን በመኖር ‘ጽድቅን መፈለግ’ ይኖርብናል። በተጨማሪም ትሑት በመሆን እንዲሁም የታዛዥነትን መንፈስ በማዳበር ‘ትሕትናን መፈለግ’ አለብን።
2:4-15፤ 3:1-5፦ የአምላክን ሕዝቦች ሲጨቁኑ የኖሩት ሕዝበ ክርስትና እና ሁሉም ብሔራት ይሖዋ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ቀን የጥንቷ ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ የነበሩት ብሔራት ዓይነት ዕጣ ይደርስባቸዋል። (ራእይ 16:14, 16፤ 18:4-8) የአምላክን የፍርድ መልእክት በድፍረት ማወጃችንን መቀጠል አለብን።
3:8, 9 [የ1954 ትርጉም]፦ የይሖዋን ቀን በምንጠባበቅበት በዚህ ወቅት ‘ንጹሑን ልሳን’ በመማርና ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ‘ስሙን በመጥራት’ ከቁጣው ለመዳን መዘጋጀት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ‘ተስማምተን’ እሱን እናገለግላለን እንዲሁም “የምስጋናን መሥዋዕት” እናቀርብለታለን።—ዕብራውያን 13:15
“ፈጥኖም ይመጣል”
መዝሙራዊው “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 37:10) የናሆም መጽሐፍ ስለ ነነዌ፣ የዕንባቆም መጽሐፍ ደግሞ ስለ ባቢሎንና ስለ ከሃዲዋ ይሁዳ በተናገሯቸው ትንቢቶች ላይ ስናሰላስል የመዝሙራዊው ቃላት በእርግጥ እውነት መሆናቸውን እንረዳለን። ይሁንና የመዝሙራዊው ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት መቼ ነው?
ሶፎንያስ 1:14 [NW] “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል፤ ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል” ይላል። በተጨማሪም የሶፎንያስ መጽሐፍ ከዚያ ቀን መሰወር የምንችለው እንዴት እንደሆነና ለመዳን አሁን ምን ማድረግ እንዳለብን ይጠቁመናል። በእርግጥም የአምላክ “ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።”—ዕብራውያን 4:12
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የነነዌ ትላልቅ ግንቦች የናሆም ትንቢት ፍጻሜውን እንዳያገኝ አላገዱትም
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Randy Olson/National Geographic Image Collection