ተመልሰው የተቋቋሙት የይሖዋ ሕዝቦች በመላው ምድር ያወድሱታል
“አሕዛብ ሁሉ . . . እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።”—ሶፎንያስ 3:9
1. በይሁዳና በሌሎች ብሔራት ላይ የተነገሩ የጥፋት መልእክቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት ለምን ነበር?
ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት በሶፎንያስ በኩል ያስነገረው የፍርድ መልእክት ምንኛ ከባድ ነበር! እነዚህ የጥፋት መልእክቶች በይሁዳና በዋና ከተማዋ በኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸሙት መሪዎቹም ሆኑ ሕዝቡ በአጠቃላይ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ስላቆሙ ነበር። እንደ ፍልስጥኤም፣ ሞዓብና አሞን ያሉት አጎራባች ብሔራትም የአምላክን ቁጣ ይቀምሳሉ። ለምን? ለብዙ መቶ ዓመታት የይሖዋን ሕዝቦች በጭካኔ ስለ ጨቆኑ ነው። የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረችው አሦርም በዚህ ምክንያት የተነሳ ዳግመኛ ላትንሠራራ ትወድማለች።
2. በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ሶፎንያስ 3:8 የሚናገረው ስለ እነማን ነበር?
2 ይሁን እንጂ በጥንቷ ይሁዳ ትክክለኛ ዝንባሌ የነበራቸው አንዳንድ ግለሰቦች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በክፉዎች ላይ የሚወርደውን መለኮታዊ ፍርድ በናፍቆት ይጠብቁ ነበር። የሚከተሉት ቃላት የሚናገሩት ስለነዚህ ሰዎች እንደሆነ ግልጽ ነው:- “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፣ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፣ ይላል እግዚአብሔር።”—ሶፎንያስ 3:8
‘ንጹሕ ልሳን’ የሚመለሰው ለእነማን ነው?
3. ሶፎንያስ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲያደርስ የተደረገው የተስፋ መልእክት ምንድን ነው?
3 አዎን፣ ሶፎንያስ የይሖዋን የጥፋት መልእክት አድርሷል። ይሁን እንጂ ነቢዩ አስደናቂ የሆነ የተስፋ መልእክትም በመንፈስ አነሳሽነት ጨምሮ ተናግሯል። መልእክቱ ለይሖዋ ታማኝነታቸውን በመጠበቅ የጸኑትን የአምላክ ሕዝቦች በእጅጉ የሚያጽናና ይሆናል። ሶፎንያስ 3:9 ላይ እንደተመዘገበው ይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።”
4, 5. (ሀ) ጽድቅ ወዳድ ያልሆኑ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? (ለ) ከዚህስ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነማን ናቸው? ለምንስ?
4 ንጹሑ ልሳን የማይሰጣቸው ሰዎች ይኖራሉ። ትንቢቱ እነዚህን ሰዎች አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “እየታበዩ የሚፎክሩትን ከመካከልሽ አወጣለሁ።” (ሶፎንያስ 3:11) ስለዚህ የአምላክን ሕግጋት ተጋፍተው ከጽድቅ በራቀ ጎዳና የተመላለሱ ትዕቢተኛ ሰዎች ይወገዳሉ። ታዲያ ከዚህ የሚጠቀሙት እነማን ይሆናሉ? ሶፎንያስ 3:12, 13 እንዲህ ይላል:- “በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በእግዚአብሔርም ስም ይታመናሉ። የእስራኤል ቅሬታ ኃጢአትን አይሠሩም፣ ሐሰትንም አይናገሩም፣ በአፋቸውም ውስጥ ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፣ ይመሰጉማል፣ የሚያስፈራቸውም የለም።”
5 በጥንቷ ይሁዳ የነበሩ ታማኝ ቀሪዎች ይጠቀሙ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ቀጥሎ ካሉት ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላልሰዋል:- “እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”—ሶፎንያስ 2:3
6. በሶፎንያስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ የተከናወነው ምን ነበር?
6 በሶፎንያስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ አምላክ እምነት የለሿን ይሁዳ በ607 ከዘአበ የወቅቱ የዓለም ኃያል መንግሥት በነበረው በባቢሎን እንድትጋዝ በመፍቀድ ቀጥቷታል። ነቢዩ ኤርምያስን ጨምሮ አንዳንድ ሰዎች ከደረሰው ጥፋት የዳኑ ሲሆን የቀሩት ደግሞ በግዞትም ሆነው ለይሖዋ ታማኝ እንደሆኑ ቀጠሉ። በ539 ከዘአበ ባቢሎን በንጉሥ ቂሮስ በሚመራው የሜዶ ፋርስ ግዛት ተገለበጠች። ከሁለት ዓመት አካባቢ በኋላ ቂሮስ አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚፈቅድ ሕግ አወጣ። ከጊዜ በኋላ ኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ዳግመኛ ተሠራ። በተጨማሪም የክህነት ሥርዓቱ ለሕዝቡ ሕጉን ለማስተማር እንደገና ተቋቋመ። (ሚልክያስ 2:7) ስለዚህ ይሖዋ ዳግመኛ የተቋቋሙትን ሕዝቦች ታማኝነታቸውን እስከጠበቁ ድረስ አበልጽጓቸው ነበር።
7, 8. የሶፎንያስ 3:14-17 ትንቢታዊ ቃላት ተፈጻሚነት የሚኖራቸው በእነማን ላይ ነው? እንዲህ ብለህ የመለስከውስ ለምንድን ነው?
7 ሶፎንያስ ከዚህ ተሐድሶ ተቋዳሽ የሚሆኑትን ሰዎች በተመለከተ የሚከተለውን ተንብዮአል:- “የጽዮን ልጅ ሆይ፣ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፣ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ በፍጹም ልብሽ ሐሤት አድርጊ ደስም ይበልሽ። እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፣ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፣ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም። በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም:- ጽዮን ሆይ፣ አትፍሪ፣ እጆችሽም አይዛሉ። አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፣ በፍቅሩም ያርፋል፣ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል።”—ሶፎንያስ 3:14-17
8 እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት የሚናገሩት ከባቢሎን ምርኮ ተሰባስበው ወደ አባቶቻቸው ምድር ስለተመለሱት ቀሪዎች ነው። ይህ ጉዳይ ሶፎንያስ 3:18-20 ላይ በግልጽ ተቀምጧል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ከጉባኤው ርቀው የሚያዝኑትን፣ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር። በዚያ ዘመን እነሆ፣ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፣ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ። በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፣ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።”
9. ይሖዋ ከይሁዳ ጋር በተያያዘ ለራሱ ስም ያተረፈው እንዴት ነው?
9 የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች የነበሩ አጎራባች ብሔራት እንዴት ያለ ድንጋጤ እንደሚወድቅባቸው ገምቱ! የይሁዳ ነዋሪዎች በኃያሏ ባቢሎን ወደ ግዞት ሲወሰዱ ነፃ እንደሚወጡ የሚጠቁም ግልጽ የሆነ ተስፋ አልነበረም። በተጨማሪም አገራቸው ባድማ ሆኗል። ይሁን እንጂ በአምላክ ኃይል ከ70 ዓመት በኋላ በገዛ አገራቸው በድጋሚ ሰፈሩ። ጠላቶቻቸው የነበሩት ብሔራት ግን ፍጹም ጥፋት ይጠብቃቸው ነበር። ይሖዋ እነዚህን ታማኝ ቀሪዎች መልሶ በማቋቋም ለራሱ ምንኛ ታላቅ ስም አተረፈ! “በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና” አድርጓቸዋል። ይህ ተሐድሶ ለይሖዋና በአሕዛብ ፊት ስሙን ለሚሸከሙ ሁሉ ምንኛ ታላቅ ውዳሴ አስገኘ!
የይሖዋ አምልኮ ከፍ ከፍ ተደረገ
10, 11. የሶፎንያስ የተሐድሶ ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ይሆናል? ይህንስ እንዴት ማወቅ እንችላለን?
10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ኢየሱስ ክርስቶስ እስራኤላውያን ቀሪዎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ በሰበሰበ ጊዜ ሌላ ተሐድሶ ተከናውኗል። ዋነኛው ተሐድሶ የሚከናወነው ገና ወደፊት በመሆኑ ይህ ወደፊት ለሚከናወኑ ነገሮች እንደ ናሙና ነበር። የሚክያስ ትንቢት እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጎርፋሉ።”—ሚክያስ 4:1
11 ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ትንቢቱ እንዳለው ‘በመጨረሻው ዘመን’ አዎን፣ “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህም ብሔራት የሐሰት አማልክትን እያመለኩ ባሉበት የአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት ይፈጸማል። ሚክያስ 4:5 “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል” ይላል። እውነተኛ አምላኪዎችስ ምን ያደርጋሉ? የሚክያስ ትንቢት እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- “እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።”
12. በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እውነተኛው አምልኮ የላቀ ደረጃ የያዘው እንዴት ነው?
12 በዚህ የመጨረሻ ቀን “የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ [ቆሟል።]” ከፍተኛው የይሖዋ እውነተኛ አምልኮ ከማንኛውም ሃይማኖት በላይ ከፍ ብሎ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል፣ በጽኑ ተመሥርቷል እንዲሁም የሁሉ የበላይ ሆኗል። የሚክያስ ትንቢት እንደተነበየውም “አሕዛብም ወደ እርሱ ይጎርፋሉ።” እንዲሁም በእውነተኛው ሃይማኖት የሚመላለሱ ሁሉ “በአምላ[ካቸው] በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW ] ስም ለዘላለም [ይሄዳሉ]።”
13, 14. ይህ ዓለም ወደ ‘መጨረሻው ቀን’ የገባው መቼ ነው? ከዚያን ጊዜ አንስቶ እውነተኛውን አምልኮ በተመለከተ ምን ሲከናወን ቆይቷል?
13 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መሠረት የተከናወኑ ሁኔታዎች እንደሚያመለክቱት ይህ ዓለም ከ1914 ወዲህ ‘በመጨረሻው ዘመን’ ማለትም በመጨረሻው ቀን ውስጥ ይገኛል። (ማርቆስ 13:4-10) ይሖዋ ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን ታማኝ ቅቡዓን ቀሪዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ ማሰባሰብ እንደጀመረ ታሪክ ያመለክታል። ከዚህ ተከትሎም ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” መሰብሰብ ጀመሩ።—ራእይ 7:9
14 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ እስከ ዛሬ ጊዜ ድረስ የይሖዋን ስም የተሸከሙ ሕዝቦች የሚያከናውኑት አምልኮ በይሖዋ አመራር እየታገዘ ከፍተኛ ግስጋሴ አድርጓል። የይሖዋ አምላኪዎች ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ከነበሩት ጥቂት ሺህ አባላት ተነስተው ዛሬ ስድስት ሚልዮን ደርሰዋል። በ235 አገሮች በሚገኙ 91, 000 በሚያክሉ ጉባኤዎች ውስጥ ተሰባስበዋል። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በየዓመቱ ይሖዋን በሕዝብ ፊት በአደባባይ በማወደሱ ሥራ ከአንድ ቢልዮን የበለጠ ሰዓት ያሳልፋሉ። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ትንቢታዊ ቃላት እየፈጸሙ እንደሆኑ ግልጽ ነው:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
15. ሶፎንያስ 2:3 በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
15 ሶፎንያስ 3:17 “አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው” ይላል። የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ የመጨረሻ ቀን ያገኙት መንፈሳዊ ብልጽግና ይሖዋ ‘በመካከላቸው’ ያለ ኃያል አምላካቸው በመሆኑ ያገኙት ቀጥተኛ ውጤት ነው። የጥንቷ ይሁዳ በ537 ከዘአበ ዳግመኛ ስትቋቋም እንደሆነው ሁሉ ዛሬም የሆነው ይኸው ነው። በሶፎንያስ 2:3 ላይ “የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ” የሚለው በዘመናችን ዋነኛ ፍጻሜውን እንዴት እንደሚያገኝ ማየት እንችላለን። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በ537 ከዘአበ “ሁሉ” የተባሉት ከባቢሎን ግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን ቀሪዎች ነበሩ። ዛሬ ምድር አቀፉን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ተቀብለው ‘ወደ ይሖዋ ቤት ተራራ የሚጎርፉትን’ ከመላው የምድር ብሔራት የተውጣጡ ቅኖችን ያጠቃልላል።
እውነተኛው አምልኮ ተስፋፋ
16. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ላገኙት ብልጽግና ጠላቶቻችን የሚሰጡት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?
16 ከ537 ከዘአበ በኋላ በአጎራባች አገሮች ይኖሩ የነበሩ ብዙ ሰዎች የአምላክ አገልጋዮች በአገራቸው ወደሚገኘው እውነተኛ አምልኮ በመመለሳቸው በጣም ተደንቀው ነበር። ይሁን እንጂ የዚያ ዘመኑ ተሐድሶ የተከናወነው በአንጻራዊ ሁኔታ በአነስተኛ መጠን ነበር። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች፣ የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች ሳይቀሩ በዘመናችን የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮች ያገኙትን አስደናቂ እድገት፣ ብልጽግናና የወደፊት ግስጋሴ ሲመለከቱ ምን እንደሚሉ ለመገመት ትችላለህ? ከእነዚህ ጠላቶች አንዳንዶቹ ፈሪሳውያን ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ሲጎርፉ ባዩ ጊዜ የተሰማቸው ዓይነት ስሜት ሳያድርባቸው አይቀርም። “እነሆ፣ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ።”—ዮሐንስ 12:19
17. አንድ ጸሐፊ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለዋል? ምን እድገትስ አግኝተዋል?
17 ፕሮፌሰር ቻርለስ ኤስ ብራደን ዚዝ ኦልሶ ብሊቭ በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራቸው መላውን ምድር ቃል በቃል አዳርሰዋል። የመንግሥቱን ምሥራች በማሠራጨት ረገድ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያክል ቅንዓትና ጽናት ያሳየ አንድም የሃይማኖት ቡድን የለም ለማለት ይቻላል። ይህ እንቅስቃሴ ከጥንካሬ ወደ ጥንካሬ እየተሸጋገረ መቀጠሉ አይቀርም።” እኚህ ሰው ምንኛ ትክክል ነበሩ! እነዚህን ቃላት የጻፉት በዓለም ዙሪያ በስብከቱ ሥራ የተሰማሩት ምሥክሮች ቁጥር ገና ከ300, 000 ባልበለጠበት ከ50 ዓመታት በፊት ነበር። የሰባኪዎች ቁጥር በ20 እጥፍ አድጎ ስድስት ሚልዮን በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ ስላለው የሥራችን ስፋት ምን ይሉ ይሆን?
18. ንጹሑ ልሳን ምንድን ነው? አምላክ የሰጠውስ ለእነማን ነው?
18 አምላክ በነቢዩ በኩል እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።” (ሶፎንያስ 3:9) በዚህ የመጨረሻ ቀን የይሖዋን ስም የሚጠሩት፣ ሊበጠስ በማይችል የፍቅር ሰንሰለት ተሳስረው፣ አዎን፣ “አንድ ሆነው” ይሖዋን በማገልገል ላይ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ይሖዋ ንጹሑን ልሳን የሰጠው ለእነዚህ ሰዎች ነው። ይህ ንጹሕ ልሳን ስለ አምላክና ስለ ዓላማው የሚገልጸውን እውነት በተገቢ ሁኔታ መረዳትን ይጨምራል። በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይህን መረዳት ሊሰጥ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:10) ይሖዋ መንፈሱን የሰጠው ለእነማን ነው? ‘እርሱን እንደ ገዢ አድረገው ለሚታዘዙት ብቻ ነው።’ (ሥራ 5:32 NW ) የአምላክን ገዥነት ተቀብለው በሁሉም ነገር ሊታዘዙት ፈቃደኛ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። የአምላክን መንፈስ ያገኙትና ስለ ይሖዋና ስለ አስደናቂ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እውነት ማለትም ንጹሑን ልሳን የሚናገሩት በዚህ ምክንያት ነው። ንጹሑን ልሳን ይሖዋን በመላው ምድር እያደገ በሚሄድ ከፍተኛ መጠን ለማወደስ ይጠቀሙበታል።
19. ንጹሑን ልሳን መናገር ምን ያጠቃልላል?
19 በንጹሑ ልሳን መናገር እውነትን በማመንና ለሌሎች በማስተማር ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን አንድ ሰው ባሕርዩን ከአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ማስማማቱን የሚጨምር ነው። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋን በመፈለግና ንጹሑን ልሳን በመናገር ረገድ ግንባር ቀደም ሆነዋል። ምን ያህል ከፍተኛ ውጤት እንዳገኙ አስብ! የቅቡዓኑ ቁጥር እየተመናመነ ሄዶ ከ8, 700 ያነሱ ቢሆንም ስድስት ሚልዮን የሚያክሉ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች የእነርሱን አርዓያ በመከተል ይሖዋን በመፈለግና ንጹሑን ልሳን በመናገር ላይ ናቸው። እነዚህ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ያላቸው፣ በአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ላይ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡ እንዲሁም በቅርቡ በዚህ ከጽድቅ በራቀ ዓለም ላይ ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት የሚተርፉ ቁጥራቸው እያደገ የሚሄድ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ናቸው።—ራእይ 7:9, 14, 15
20. ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?
20 እጅግ ብዙ ሰዎች አምላክ ወዳዘጋጀው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ይገባሉ። (2 ጴጥሮስ 3:13) ኢየሱስ ክርስቶስና ከእሱ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው ለማገልገል ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ የሚያገኙ 144, 000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች አዲሱን የምድር መስተዳድር ይመሠርታሉ። (ሮሜ 8:16, 17፤ ራእይ 7:4፤ 20:6) ከታላቁ መከራ የሚተርፉ ሰዎች ምድርን ገነት ለማድረግ የሚሠሩ ከመሆኑም በተጨማሪ አምላክ የሰጣቸውን ንጹሕ ልሳን መናገራቸውን ይቀጥላሉ። በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ቀጥሎ ያሉት ቃላት ተፈጻሚነታቸውን የሚያገኙት በእነርሱ ላይ ነው:- “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። በጽድቅ ትታነጺያለሽ።”—ኢሳይያስ 54:13, 14
በታሪክ የታየ ታላቅ የማስተማር ሥራ
21, 22. (ሀ) ሥራ 24:15 ላይ እንደተገለጸው ንጹሑን ልሳን መማር የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው? (ለ) በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ በዓይነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ምን የማስተማር ሥራ ይከናወናል?
21 በአዲሱ ዓለም ውስጥ ንጹሑን ልሳን የመማር አጋጣሚ የሚሰጣቸው ሌሎች ብዙ ሰዎች ይኖራሉ። ሥራ 24:15 ስለ እነዚህ ሰዎች ሲናገር:- ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሣሉ’ ይላል። በቀደሙት ዘመናት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትክክለኛውን የይሖዋ እውቀት ሳያገኙ ኖረው ሞተዋል። እነዚህን ሰዎች ሥርዓታማ በሆነ መንገድ ወደ ሕይወት ይመልሳል። እንደነዚህ ያሉ ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ንጹሑን ልሳን መማር ያስፈልጋቸዋል።
22 በዚህ ታላቅ የማስተማር ሥራ መካፈል መቻል እንዴት ያለ መብት ነው! በሰው ልጅ ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ታላቅ የማስተማር ሥራ ይሆናል። ሥራው ባጠቃላይ በመልካሙ የክርስቶስ ኢየሱስ ንግሥና ሥር የሚከናወን ይሆናል። ከዚህ የተነሳ በመጨረሻ የሰው ልጅ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW ] በማወቅ ትሞላለች” የሚለው የኢሳይያስ 11:9 ትንቢት ሲፈጸም ይመለከታል።
23. የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን እጅግ ታድለናል የምትልበት ምክንያት ምንድን ነው?
23 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በእርግጥ ምድር ይሖዋን በማወቅ ለምትሞላበት ከፊታችን ለሚጠብቀን አስደናቂ ጊዜ በመዘጋጀት ላይ መሆናችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እንዲሁም ዛሬም ቢሆን በሶፎንያስ 3:20 ላይ የሚገኘው ትንቢታዊ ቃል ታላቅ ፍጻሜውን ሲያገኝ ከሚያዩት የአምላክ ሕዝቦች መካከል በመሆናችን ምንኛ ታድለናል! በዚህ ላይ ይሖዋ “በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ” ሲል የሰጠውን ማረጋገጫ እናገኛለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የሶፎንያስ የተሐድሶ ትንቢት ምን ፍጻሜዎች አግኝቷል?
• እውነተኛው አምልኮ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የተስፋፋው እንዴት ነው?
• በአዲሱ ዓለም ምን ታላቅ የማስተማር ሥራ ይከናወናል?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ሕዝቦች እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል። ይህ በዛሬው ጊዜ ምን ትርጉም እንዳለው ታውቃለህ?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ‘ንጹሑን ልሳን’ በመናገር ለሰዎች አጽናኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ያደርሳሉ