‘እጆቻችሁ አይዛሉ’
“እጆችሽም አይዛሉ። አምላክሽ ይሖዋ በመካከልሽ ነው።እርሱ ኃያል እንደመሆኑ መጠን ይታደጋል።”—ሶፎንያስ 3:16, 17 አዓት
1. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሶፎንያስን ትንቢት በተመለከተ ምን ብለዋል?
የሶፎንያስ ትንቢት በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ያገኘው ፍጻሜ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አልነበረም። ፕሮፌሰር ሲ ኤፍ ኬይል የሶፎንያስን መጽሐፍ በተመለከተ በሰጡት ትንተና እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የሶፎንያስ ትንቢት . . . ይሁዳ በኃጢአቷ ምክንያት የሚደርስባትን ቅጣትና ብሔራት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ በጥላቻ ተነሳስተው በፈጸሙት በደል የሚመጣባቸውን ጥፋት ያካተተ ዓለም አቀፋዊ ፍርድ እንደሚኖር ብቻ ሳይሆን አስፈሪ በሆነው በታላቁ የይሖዋ ቀን የሚፈጸመውን ሁኔታ በዝርዝር ይናገራል።”
2. በሶፎንያስ ዘመን በነበረው ሁኔታና በዛሬው ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ባለው ሁኔታ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
2 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ከሶፎንያስ ዘመን የበለጠ ስፋት ባለው ሁኔታ ብሔራትን ለጥፋት ለመሰብሰብ ወስኗል። (ሶፎንያስ 3:8) በተለይ ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩት ብሔራት በአምላክ ዘንድ ርኩስ ናቸው። ኢየሩሳሌም ለይሖዋ ታማኝ ሆና ባለመገኘቷ የተነሳ ከባድ ቅጣት እንደደረሰባት ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም ልቅ ለሆነው ምግባሯ አምላክ ተገቢውን ቅጣት ያከናንባታል። በሶፎንያስ ዘመን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፉት መለኮታዊ የፍርድ መልእክቶች ከዚያን ጊዜ በበለጠ ሁኔታ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትና መናፍቃን ቡድኖች ላይ ይሠራሉ። አምላክን በሚያዋርዱ መሠረተ ትምህርቶች ንጹሑን አምልኮ በክለዋል። ከእነዚህ መሠረተ ትምህርቶች መካከል ብዙዎቹ ከአረማውያን የመጡ ናቸው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ጤናማ ልጆቻቸውን በዘመናዊው መሠዊያ በጦርነት ላይ ሠዉተዋቸዋል። በተጨማሪም የምሳሌያዊቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ስመ ክርስትናን ከኮከብ ቆጠራ፣ ከመናፍስታዊ ተግባራትና ከበኣል አምልኮ ጋር ከሚመሳሰለው ርካሽ የጾታ ብልግና ጋር ቀላቅለዋል።—ሶፎንያስ 1:4, 5
3. በዛሬው ጊዜ ስለሚገኙት ዓለማዊ መሪዎችና ፖለቲካዊ መንግሥታት ምን ለማለት ይቻላል? ሶፎንያስ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን ትንቢት ተናግሯል?
3 በአብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና አገሮች የሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጎላ ብለው ለመታየት ይፈልጋሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ከይሁዳ “አለቆች” ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ “እንደሚያገሡ አንበሶች” እና በጣም እንደተራቡ “ተኩላዎች” ሕዝቡን ይበዘብዛሉ። (ሶፎንያስ 3:1-3) የእነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ባለሟሎች ‘የጌቶቻቸውን ቤት በዓመፃና በሽንገላ ይሞላሉ።’ (ሶፎንያስ 1:9) ጉቦና ምግባረ ብልሹነት የተለመዱ ነገሮች ናቸው። አብዛኞቹ በሕዝበ ክርስትና አገሮችና በሌሎች አገሮች ያሉ መንግሥታት የይሖዋ ምሥክሮችን ከንቱ “መናፍቃን” እንደሆኑ አድርገው በመመልከት በሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሕዝቦች ላይ ‘ታብየዋል።’ (ሶፎንያስ 2:8፤ ሥራ 24:5, 14) ሶፎንያስ እንደነዚህ ስላሉት የፖለቲካ መሪዎችና ተከታዮቻቸው እንዲህ በማለት ተንብዮአል፦ “በእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥኖ ይጨርሳቸዋልና ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች።”—ሶፎንያስ 1:18
‘ከይሖዋ የቁጣ ቀን መሰወር’
4. ከታላቁ የይሖዋ ቀን የሚተርፉ ሰዎች እንዳሉ የሚያሳየው ምንድን ነው? ሆኖም እነዚህ ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው?
4 በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የጠፉት ሁሉም የይሁዳ ነዋሪዎች አልነበሩም። በተመሳሳይም ከታላቁ የይሖዋ ቀን የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ። ይሖዋ እነዚህን ሰዎች በተመለከተ በነቢዩ ሶፎንያስ አማካኝነት እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ትእዛዝ ሳይወጣ፣ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፣ ተከማቹም። እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”—ሶፎንያስ 2:2, 3
5. በዚህ የመጨረሻ ዘመን የሶፎንያስን ማስጠንቀቂያ በቅድሚያ የተቀበሉት እነማን ናቸው? ይሖዋስ የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?
5 የዓለም መጨረሻ በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ ትንቢታዊውን ጥሪ በቅድሚያ የተቀበሉት የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። (ሮሜ 2:28, 29፤ 9:6፤ ገላትያ 6:16) በ1919 ጽድቅንና ትሕትናን በመፈለግ እንዲሁም ለይሖዋ የፍርድ ውሳኔዎች አክብሮት በማሳየት የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ታላቂቷ ባቢሎን ወጥተዋል፤ መለኮታዊ ሞገስም አግኝተዋል። እነዚህ ታማኝ ቀሪዎች ከዚያን ጊዜ ወዲህ በተለይም ከ1922 ጀምሮ ይሖዋ በአብያተ ክርስቲያናትና በሕዝበ ክርስትና መናፍቃን ቡድኖች እንዲሁም በፖለቲካ መንግሥታት ላይ የሚያመጣውን ቅጣት በድፍረት አውጀዋል።
6. (ሀ) ሶፎንያስ ታማኝ ስለሆኑት ቀሪዎች ምን ተንብዮአል? (ለ) ይህ ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው?
6 ሶፎንያስ እነዚህን ታማኝ ቀሪዎች በተመለከተ እንዲህ በማለት ተንብዮአል፦ “በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በእግዚአብሔርም [“በይሖዋ፣” አዓት] ስም ይታመናሉ። የእስራኤል ቅሬታ ኃጢአትን አይሠሩም፣ ሐሰትንም አይናገሩም፣ በአፋቸውም ውስጥ ተንኮለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፣ ይመሰጉማል፣ የሚያስፈራቸውም የለም።” (ሶፎንያስ 3:12, 13) እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምንጊዜም ለይሖዋ ስም ከፍተኛ ቦታ ሲሰጡ ቆይተዋል። በተለይ ግን በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መጠቀም ሲጀምሩ ይህንን ስም ይበልጥ ከፍ ከፍ አድርገውታል። (ኢሳይያስ 43:10-12) በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳውን ግድድር ጎላ አድርገው በመግለጽ ለመለኮታዊው ስም ክብር የሰጡ ሲሆን ስሙ መሸሸጊያ እንደሆነላቸው ታይቷል። (ምሳሌ 18:10) ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበላቸው ሲሆን በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ያለ ፍርሃት ይኖራሉ።—ሶፎንያስ 3:16, 17
‘በአሕዛብ ሁሉ መካከል የከበረ ስምና ምስጋና’
7, 8. (ሀ) በመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ላይ የተፈጸመው ሌላው ትንቢት ምንድን ነው? (ለ) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተገነዘቡት ነገር ምንድን ነው? አንተ በዚህ ረገድ ምን ይሰማሃል?
7 ቅቡዓኑ የይሖዋን ስምና የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን የሙጥኝ ማለታቸው የሌሎችን ትኩረት ስቧል። ልበ ቅን ሰዎች በቅቡዓኑ ምግባርና የዚህ ዓለም ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መሪዎች በሚያሳዩት ምግባረ ብልሹነትና ግብዝነት መካከል ያለውን ልዩነት ተገንዝበዋል። ይሖዋ ‘[የመንፈሳዊ] እስራኤል ቀሪዎችን’ ባርኳል። ስሙን እንዲሸከሙና በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎች መካከል መልካም ስም እንዲያተርፉ በማድረግ ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል። ይህን በተመለከተ ሶፎንያስ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር፦ “በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፣ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ።”—ሶፎንያስ 3:20
8 ከ1935 ጀምሮ ቃል በቃል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቅቡዓኑ የይሖዋን በረከት እያገኙ እንዳሉ ተገንዝበዋል። “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” በማለት እነዚህን መንፈሳዊ አይሁዳውያን ወይም እስራኤላውያን በደስታ ተከትለዋቸዋል። (ዘካርያስ 8:23) እነዚህ “ሌሎች በጎች” ቅቡዓን ቀሪዎችን ክርስቶስ “[በምድር] ባለው ሁሉ ላይ የሾመው” “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። የባሪያው ክፍል “በጊዜው” የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ በደስታ ይመገባሉ።—ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 24:45-47
9. በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የትኛውን ‘ቋንቋ’ ተምረዋል? ሌሎች በጎች ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር “አንድ ሆነው” የሚያገለግሉት በየትኛው ታላቅ ሥራ ነው?
9 እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች በጎች ከቅቡዓኑ ጎን በመሆን አኗኗራቸውንና ንግግራቸውን ‘ከንጹሕ ልሳን’ ጋር እንዴት ማስማማት እንደሚችሉ እየተማሩ ናቸው።a ይሖዋ በሶፎንያስ በኩል “በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ” በማለት ተንብዮአል። (ሶፎንያስ 3:9) አዎን፣ ሌሎች በጎች ‘ከታናሹ መንጋ’ ቅቡዓን አባላት ጋር “አንድ ሆነው” አጣዳፊ በሆነው ‘ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበኩ ሥራ በመካፈል ይሖዋን ያገለግላሉ።—ሉቃስ 12:32፤ ማቴዎስ 24:14
‘የይሖዋ ቀን ይመጣል’
10. ቅቡዓን ቀሪዎች ምን የጸና እምነት ይዘው ኖረዋል? በቡድን ደረጃ በሕይወት ቆይተው የሚመለከቱትስ ምንድን ነው?
10 ቅቡዓን ቀሪዎች ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ተገፋፍቶ የተናገረውን የሚከተለውን ነገር ፈጽሞ ችላ አይሉትም፦ “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9, 10) የታማኙ ባሪያ ክፍል አባላት የይሖዋ ቀን በዚህ ባለንበት ዘመን እንደሚመጣ ጥርጣሬ ገብቷቸው አያውቅም። ይህ ታላቅ ቀን የሚጀምረው አምላክ የኢየሩሳሌም አምሳያ በሆነችው በሕዝበ ክርስትና እና በተቀረው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ላይ የወሰነውን ቅጣት ሲፈጽም ነው።—ሶፎንያስ 1:2-4፤ ራእይ 17:1, 5፤ 19:1, 2
11, 12. (ሀ) በቀሪዎቹ ላይ የተፈጸመው ሌላው የሶፎንያስ ትንቢት ምንድን ነው? (ለ) ቅቡዓን ቀሪዎች ‘እጆቻችሁ አይዛሉ’ የሚለውን ትእዛዝ የተከተሉት እንዴት ነው?
11 ታማኝ የሆኑት ቅቡዓን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ከነበሩበት መንፈሳዊ ግዞት በ1919 ነፃ ሲወጡ ተደስተዋል። ሶፎንያስ የተነበየው የሚከተለው ትንቢት በራሳቸው ላይ ሲፈጸም ተመልክተዋል፦ “የጽዮን ልጅ ሆይ፣ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፣ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ በፍጹም ልብሽ ሐሤት አድርጊ ደስም ይበልሽ። እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፣ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፣ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም። በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም፦ ጽዮን ሆይ፣ አትፍሪ፣ እጆችሽም አይዛሉ። አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው . . . ይባላል።”—ሶፎንያስ 3:14-17
12 ቅቡዓን ቀሪዎች ይሖዋ በመካከላቸው እንዳለ ጽኑ እምነት ስላላቸውና ይህንንም የሚያሳዩ ብዙ ማረጋገጫዎች ስለተመለከቱ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ተልዕኮ በማከናወን በድፍረት ወደፊት ገፍተዋል። የመንግሥቱን ምሥራች ከመስበካቸውም በላይ ይሖዋ በሕዝበ ክርስትና፣ በተቀረው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍልና በመላው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ላይ የወሰነውን ፍርድ አሳውቀዋል። ከ1919 ወዲህ ባሉት አሥርተ ዓመታት የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም “ጽዮን ሆይ፣ አትፍሪ፣ እጆችሽም አይዛሉ” የሚለውን መለኮታዊ ትእዛዝ ተከትለዋል። የይሖዋን መንግሥት የሚያውጁ በቢልዮን የሚቆጠሩ ትራክቶችን፣ መጽሔቶችን፣ መጽሐፎችንና ቡክሌቶችን በትጋት አሰራጭተዋል። ከ1935 ጀምሮ ወደ እነርሱ በመጉረፍ ከጎናቸው ለቆሙት ሌሎች በጎች እምነት የሚያጠነክሩ ምሳሌዎች ሆነዋል።
‘እጆቻችሁ አይዛሉ’
13, 14. (ሀ) አንዳንድ አይሁዶች ይሖዋን ከማገልገል ወደ ኋላ ያሉት ለምንድን ነው? ይህስ የታየው እንዴት ነው? (ለ) ምን ብሎ ማሰብ ጥበብ አይሆንም? እጆቻችን መዛል የሌለባቸው በየትኛው ሥራ ነው?
13 ታላቁን የይሖዋ ቀን ‘በጉጉት እየተጠባበቅን ባለንበት’ በአሁኑ ጊዜ ከሶፎንያስ ትንቢት ተግባራዊ እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የይሖዋ ቀን ቅርብ መሆኑን በመጠራጠራቸው የተነሳ ይሖዋን ከመከተል ወደኋላ እንዳሉት አይሁዶች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። እነዚህ አይሁዶች ያደረባቸውን ጥርጣሬ አፍ አውጥተው በግልጽ አልተናገሩት ይሆናል፤ ሆኖም ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ መሆኑን ከልባቸው እንደማያምኑበት አኗኗራቸው ያሳይ ነበር። ይሖዋን በጉጉት ከመጠባበቅ ይልቅ ያተኮሩት ሀብት በማግበስበስ ላይ ነበር።—ሶፎንያስ 1:12, 13፤ 3:8
14 ዛሬ በልባችን ውስጥ ጥርጣሬዎች እንዲተከሉ የምንፈቅድበት ጊዜ አይደለም። በአእምሯችንም ሆነ በልባችን የይሖዋ ቀን ገና ነው ብለን የምናስብ ከሆነ በጣም ሞኝነት ነው። (2 ጴጥሮስ 3:1-4, 10) ይሖዋን ከመከተል ወደ ኋላ ማለት ወይም በይሖዋ አገልግሎት ‘እጆቻችን እንዲዝሉ መፍቀድ’ የለብንም። ይህም ‘ምሥራቹን’ በመስበኩ ሥራ ‘ያለመታከት’ መካፈልን ያካትታል።—ምሳሌ 10:4፤ ማርቆስ 13:10
ሰዎች የሚያሳዩትን ግድ የለሽነት መቋቋም
15. በይሖዋ አገልግሎት እንድንታክት ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው? ይህ ችግር በሶፎንያስ ትንቢት ውስጥ አስቀድሞ የተነገረው እንዴት ነው?
15 በሁለተኛ ደረጃ ሰዎች የሚያሳዩን ግድ የለሽነት እንዳያዳክመን መጠንቀቅ አለብን። በአብዛኞቹ ምዕራባውያን አገሮች ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ግድ የለሽ መሆናቸው አንዳንዶቹን የምሥራቹ ሰባኪዎች ተስፋ አስቆርጧቸዋል። ይህ ዓይነቱ ግድ የለሽነት በሶፎንያስም ዘመን ነበር። ይሖዋ በነቢዩ በኩል “እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ” ብሏል። (ሶፎንያስ 1:12) ኤ ቢ ዴቪድሰን ካምብሪጅ ባይብል ፎር ስኩልስ ኤንድ ኮሌጅ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ይህ ጥቅስ “ግድ የለሽ የሆኑ ወይም አምላክ በሰዎች ጉዳይ በምንም ዓይነት ጣልቃ አይገባም” የሚሉ ሰዎችን እንደሚያመለክት ተናግረዋል።
16. አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባላት ምን አስተሳሰብ አላቸው? ሆኖም ይሖዋ ምን ማበረታቻ ይሰጠናል?
16 በዛሬው ጊዜ ግድ የለሽነት በብዙ የምድር ክፍሎች በተለይም በበለጸጉት አገሮች ውስጥ በእጅጉ ተስፋፍቷል። ሌላው ቀርቶ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባላት እንኳ ይሖዋ አምላክ በአሁኑ ጊዜ በሰዎች ጉዳይ እጁን ያስገባል ብለው አያምኑም። እነዚህ ሰዎች በማፌዝ ወይም “አልፈልግም” የሚል አጭር መልስ በመስጠት የመንግሥቱን ምሥራች ለማድረስ የምናደርገውን ጥረት መና ለማስቀረት ይሞክራሉ። እነዚህ ሁኔታዎች እያሉ በምስክርነቱ ሥራ መጽናት ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ያለንን ጽናት ይፈትነዋል። ሆኖም ይሖዋ በሶፎንያስ ትንቢት አማካኝነት እንደሚከተለው በማለት ታማኝ ሕዝቦቹን ያበረታታል፦ “እጆችሽም አይዛሉ። አምላክሽ ይሖዋ በመካከልሽ ነው። እርሱ ኃያል እንደመሆኑ መጠን ይታደጋል። በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፣ በፍቅሩም ያርፋል፣ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል።”—ሶፎንያስ 3:16, 17 አዓት
17. አዳዲስ የሆኑ የሌሎች በጎች አባላት ሊከተሉት የሚገባቸው ግሩም ምሳሌ ምንድን ነው? እንዴትስ?
17 ዘመናዊው የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ እንደሚያሳየው ቅቡዓኑና ረጅም ዕድሜ ያሳለፉ የሌሎች በጎች አባላት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ አስደናቂ የመሰብሰብ ሥራ አከናውነዋል። እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ለአያሌ አሥርተ ዓመታት ጸንተዋል። በሕዝበ ክርስትና ሥር ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች የሚያሳዩአቸው ግድ የለሽነት ተስፋ እንዲያስቆርጣቸው አልፈቀዱም። ከሌሎች በጎች መካከል የሆኑ አዳዲስ ሰዎችም ቢሆኑ በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች በተስፋፋው ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች በሚያሳዩት ግድ የለሽነት ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም። ‘እጆቻቸው ሊዝሉ’ ወይም ሊታክቱ አይገባም። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም በግ መሰል ሰዎችን ስለ ይሖዋ ቀንና ከዚያ በኋላ ስለሚመጡ በረከቶች እውነተኛውን እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት የተዘጋጁ ሌሎች ጽሑፎችን ለማበርከት እያንዳንዱን አጋጣሚ መጠቀም ይገባቸዋል።
ታላቁን ቀን እየጠበቃችሁ ወደ ፊት ግፉ!
18, 19. (ሀ) በማቴዎስ 24:13 እና በኢሳይያስ 35:3, 4 ላይ ለመጽናት የሚያስችል ምን ማበረታቻ ተሰጥቷል? (ለ) በይሖዋ አገልግሎት በአንድነት ወደ ፊት ከገፋን የምንባረከው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:13) ስለዚህ ታላቁን የይሖዋ ቀን ስንጠብቅ ‘እጆቻችን ሊደክሙ’ ወይም ‘ጉልበቶቻችን ሊላሉ’ አይገባም! (ኢሳይያስ 35:3, 4) የሶፎንያስ ትንቢት ስለ ይሖዋ ሲናገር “ኃያል እንደመሆኑ መጠን ይታደጋል” በማለት ያረጋግጥልናል። (ሶፎንያስ 3:17 አዓት) አዎን፣ ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ ‘የታበዩትን’ የፖለቲካ መንግሥታት እንዲያደቃቸው ለልጁ ትእዛዝ በመስጠት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘የታላቁን መከራ’ የመጨረሻ ምዕራፍ በሕይወት እንዲያልፉ ያደርጋል።—ራእይ 7:9, 14፤ ሶፎንያስ 2:10, 11፤ መዝሙር 2:7-9
19 ታላቁ የይሖዋ ቀን እየቀረበ ሲሄድ ‘አንድ ሆነን’ ይሖዋን በቅንዓት በማገልገል ወደፊት እንግፋ! (ሶፎንያስ 3:9) እንዲህ ካደረግን እኛና ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ‘ከእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ለመሰወርና’ የይሖዋ ስም ሲቀደስ ለማየት እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ‘ንጹሕ ልሳንን’ በተመለከተ ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት የሚያዝያ 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-5 እና የግንቦት 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10-20 ተመልከት።
ለክለሳ ያህል
◻ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ በሶፎንያስ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?
◻ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙዎቹ የፖለቲካ መሪዎች በሶፎንያስ ዘመን ከነበሩት የሕዝብ “አለቆች” ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
◻ በቀሪዎቹ ላይ የተፈጸሙት ሶፎንያስ የተናገራቸው ተስፋዎች የትኞቹ ናቸው?
◻ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተገነዘቡት ነገር ምንድን ነው?
◻ በይሖዋ አገልግሎት እጆቻችን እንዲዝሉ መፍቀድ የሌለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ታማኝ የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎች ልክ እንደ ሶፎንያስ ይሖዋ የሚያመጣቸውን ቅጣቶች ያለ ፍርሃት አውጀዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“ሌሎች በጎች” የሰዎች ግድ የለሽነት ተስፋ እንዲያስቆርጣቸው አልፈቀዱም