-
ንጹሑ ልሳን አንድ ያድርጋችሁመጠበቂያ ግንብ—1991 | ግንቦት 1
-
-
ንጹሑ ልሳን አንድ ያድርጋችሁ
“በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው (ይሖዋን) ያገለግሉ ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሁን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።”—ሶፎንያስ 3:9
1. ሰዎች ይሖዋ አምላክ ሲናገር ሰምተውት ያውቃሉን?
የይሖዋ አምላክ ልሣን ንጹህ ነው። ግን እርሱ ሲናገር ሰዎች ሰምተውት ያውቃሉን? እንዴታ! ያም የሆነው ከ19 መቶ ዓመታት በፊት ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ አምላክ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ተሰምቷል። (ማቴዎስ 3:13-17) ያ ቃል በሰው ቋንቋ ለኢየሱስና ለዮሐንስ መጥምቁ የተሰማ የንጹህ እውነት መግለጫ ነው።
2. ሐዋርያው ጳውሎስ “የመላእክት ልሣን” ሲል የጠቀሰው ቃል ምን ያመለክታል?
2 ከጥቂት ዓመታት በኋላም ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ሰዎችና ስለ መላእክት “ልሣን” ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:1) ይህስ ምን ያመለክታል? ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራንም ቋንቋና ንግግር እንዳላቸው ያመለክታል! እርግጥ አምላክና መላእክቱ እርስ በርሳቸው የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉት ለእኛ በሚሰማንና በሚገባን ድምጽና ቋንቋ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ሰዎች የሚሰሙትና የሚረዱት የድምጽ ሞገድን ለማሠራጨት በምድር ዙሪያ እንዳለው ከባቢ አየር ስለሚያስፈልግ ነው።
3. ሰብዓዊ ቋንቋ እንዴት መጣ?
3 የሰው ቋንቋ እንዴት ተጀመረ? ቅድመ አያቶቻችን በማጓራትና በማቃሰት ዓይነት ድምጽ እርስ በርሳቸው ለመነጋገር ይታገሉ ነበር በማለት አንዳንዶች ይናገራሉ። ኢቮሉሽን (ላይፍ ኔቸር ላይብረሪ) የተሰኘው መጽሐፍ “ከአንድ ሚልዮን ዓመታት በፊት የነበረው ጦጣ መሰል ሰው ጥቂት የንግግር ድምጾችን ጠንቅቆ ሳያውቅ አልቀረም” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ የታወቁት መዝገበ ቃላት ጸሐፊ ሉዲዊግ ከውኽለር “የሰው ቋንቋ ምስጢር ነው፤ መለኰታዊ ስጦታና ተዓምርም ነው” ብለዋል። አዎ፤ አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም ቋንቋን ስለሰጠው ሰብዓዊ የንግግር ችሎታ መለኰታዊ ስጦታ ነው። ያም ቋንቋ በኋላ ዕብራይስጥ የተባለው እንደሆነ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ያ ቋንቋ አያቱ የመርከብ ሠሪው የኖህ ልጅ ሴም የሆነው ታማኝ አበው የ“ዕብራዊው አብርሃም” ዘሮች የእሥራኤላውያን መነጋገሪያ ቋንቋ ነበር። (ዘፍጥረት 11:10-26፤ 14:13፤ 17:3-6) አምላክ ሴምን ከባረከበት ትንቢታዊ በረከት አንጻር ሲታይ ቋንቋው ከ43 መቶ ዓመታት በፊት ይሖዋ በተዓምር ባደረገው ነገር አልተነካም ነበር ብሎ መናገር ምክንያታዊ ነው።—ዘፍጥረት 9:26
4. ናምሩድ ማን ነበር? ሰይጣን ዲያብሎስ የተጠቀመበትስ እንዴት ነው?
4 በዚያን ጊዜ “ምድር ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች።” (ዘፍጥረት 11:1) በዚያን ጊዜ “[ይሖዋን በመጻረር (አዓት)] ኃያል አዳኝ” የነበረ ናምሩድ የሚባል ሰው ነበረ። (ዘፍጥረት 10:8, 9) በዓይን የማይታየው የሰው ልጅ ቀንደኛ ጠላት ሰይጣን የራሱን ድርጅት ምድራዊ ክፍል እንዲያቋቁም ናምሩድን ተጠቀመበት። ናምሩድ ለራሱ ታላቅ ስም ለማትረፍ ፈለገ። የሱ የዕብሪት ዝንባሌ በሰናዖር ምድር ልዩ የግንባታ ሥራ በጀመሩት የእሱ ተከታዮች ዘንድም ተዛመተ። በዘፍጥረት 11:4 መሠረት “ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው” ተባባሉ። “ምድርን ሙሉ” የሚለውን የአምላክን ትዕዛዝ የሚቃወመው ያ ዕቅድ ይሖዋ የዐመጸኞቹን ቋንቋ በደባለቀ ጊዜ አከተመ። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ “እግዚአብሔር ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው። ከተማይቱንም መሥራት ተዉ” ይላል። (ዘፍጥረት 9:1፤ 11:2-9) ከተማዋም ባቤል ወይም ባቢሎን ተብላ ተጠራች፤ ትርጉሙም “መዘበራረቅ” “መደበላለቅ” ማለት ነው። ምክንያቱም “ይሖዋ በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና።”
5. (ሀ) አምላክ የሰው ልጆችን ቋንቋ በደባለቀ ጊዜ የታገደው ምን ነበር? (ለ) ስለ ኖህና ስለ ሴም ቋንቋ ምን ብለን መደምደም እንችላለን?
5 ያ ተአምር ማለትም አንዱን ሰብአዊ ቋንቋ ማደባለቁ አምላክ ለኖኅ ምድርን እንዲሞሉአት የሰጠውን ትእዛዝ ወደመፈጸም አምርቷል፤ ሰይጣንም የሰማይና የምድር ልዑል ጌታ በሆነው በይሖዋ ላይ ባመጹ ሰዎች አማካኝነት ለራሱ አንድነት ያለው እርኩስ አምልኮ ለማቋቋም የነበረው እቅድ ተደናቀፈ። እርግጥ ነው ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት በመያዛቸው ዞሮ ዞሮ የዲያብሎስ አምላኪዎች ከመሆን አላመለጡም። አማልክትን በተባዕታይና አነስታይ ጾታ ሠርተው በተለያዩ ቋንቋዎቻቸውም ስም ሰጥተው ባመለኩአቸው ጊዜ አጋንንትን ማምለካቸው ወይም ማገልገላቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:20) ይሁን እንጂ በባቢሎን ላይ በአንዱ እውነተኛ አምላክ የተወሰደው እርምጃ ሰይጣን በግልጽ ተመኝቶት የነበረውን አንድነት ያለው የሐሰት ሃይማኖት እንዳያቋቁም አግዷል። ጻድቁ ኖኅና ልጁ ሴም በሰናዖር ምድር በደረሰው ውድቀትና ምስቅልቅል ውስጥ አልገቡም። ስለዚህ ቋንቋቸው ቀጠለና የታማኙ የአብራም (አብርሃም) መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። ያው ቋንቋ ነበር አምላክ በዔድን ገነት ከአዳምና ከሔዋን ጋር የተነጋገረበት።
6. በ33 እዘአ የጰንጤቆስጤ ዕለት ይሖዋ በልሣናት መናገርን መስጠት እንደሚችል እንዴት አሳየ?
6 የሰው ልጆችን የመጀመሪያ ቋንቋ የደባለቀው ይሖዋ በልሳናት የመናገርን ችሎታም ሊሰጥ ይችላል። በ33 እዘአ በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ያደረገውም ያንኑ ነው። በሥራ 2:1-11 መሠረት በዚያን ጊዜ 120 የሚያህሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በሰገነት ላይ ተሰብስበው ነበር። (ሥራ 1:13, 15) በድንገትም “እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ” ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ። “እሳት የመሰሉ ልሳኖች” ታዩና ተከፋፈሉ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” በነዚያ መለኮታዊ ስጦታ በሆኑ ቋንቋዎች “የእግዚአብሔርን አስደናቂ ነገሮች መናገር ጀመሩ።” እንደ ሜሴፖታሚያ፣ ግብፅ፣ ሊብያና ሮም ከመሳሰሉት የተለያዩ ሩቅ ቦታዎች የመጡ አይሁድና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ያን ሕይወት ሰጪ መልእክት መስማት ችለው ስለነበር ያ እንዴት ዓይነት ተአምር ነበር!
ዛሬም ከአምላክ የተሰጠ ቋንቋ አለ!
7. በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያውና መግባቢያው አንድ ቋንቋ ብቻ ቢሆን ኖሮ ምን ሁኔታዎች ይኖሩ ነበር?
7 አምላክ በተአምር የተለያዩ ልሳናትን ሊሰጥ የሚችል ስለሆነ በዓለም ዙሪያ አንድ ቋንቋ ብቻ እንዲነገርና መግባቢያ እንዲሆን ቢያደርግ ግሩም አይሆንምን? እንደዚያ ቢሆን በሰብአዊ ቤተሰብ መካከል የበለጠ መግባባት ሊኖር ይችል ነበር። ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደገለጸው “ሁሉም ሕዝቦች አንድ ቋንቋ ቢናገሩ ኖሮ ባሕላዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በጣም የበለጠ የተቀራረቡ ይሆኑ ነበር። በአገሮች መካከል መተማመን ይጨምር ነበር።” ባለፉት ዘመናት ቢያንስ 600 ዓይነት ቋንቋዎች ዓለም አቀፋዊ መግባቢያ እንዲሆኑ ሐሳብ ቀርቦ ነበር። ከእነዚህ መካከል ኢስቀራንቶ የተባለው ቋንቋ ከፍተኛ ኃይል ነበረው፤ ምክንያቱም በ1887 ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ 10,000,000 ያህል ሕዝብ ሊማረው ችሏል። ሆኖም በአንድ ዓለም አቀፍ ቋንቋ አማካኝነት የሰው ልጅን ለማስተባበር የተደረገው የሰው ጥረት ስኬታማ አልሆነም። እንዲያውም “ክፉ ሰዎች በክፋት እየባሱ” ሲሄዱ ተጨማሪ ችግሮች በዚህ ዓለም መከፋፈልን እያስከተሉ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:13
8. በአሁኑ ዓለም አንድ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ መምረጥና በሥራ ላይ ማዋል ቢቻልም ኖሮ እንኳን ገና ምን ይኖራል? ለምንስ?
8 በሃይማኖት ረገድ ከፍተኛ መዘበራረቅ አለ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ የዓለምን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት “ታላቂቱ ባቢሎን” ብሎ ስለሚጠራ ይህ መዘበራረቅ እንደሚኖር መጠበቅ አይገባንምን? (ራእይ 18:2) አዎን “ባቢሎን” ማለት “መዘበራረቅ” ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባናል። ባሁኑ ዓለም ሰው ሠራሽ ቋንቋ ወይም እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ ወይም ሩሲያኛ የመሳሰሉት ልሳኖች በዓለም አቀፋዊ መግባቢያነት ተመርጠው ቢያዙም ኖሮ በሃይማኖትና በሌላም መከፋፈል ይኖራል። ለምን? ምክንያቱም “ዓለምም በሞላው በክፉው [በሰይጣን ዲያብሎስ] ተይዟል።” (1 ዮሐንስ 5:19) እሱ ሁለንተናው ራስ ወዳድ ነው። ስለዚህ በናምሩድና በባቢሎን ግንብ ጊዜ እንዳደረገው በራስ ወዳድነት በሰው ልጅ ሁሉ እንዲመለክ ይመኛል። በኃጢአተኛ ሰዎች የሚነገር አንድ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ለሰይጣን አንድነት ያለው የዲያብሎስ አምልኮ ሊያስገኝለት ይችል ነበር። ይሖዋ ግን ያንን ፈጽሞ አይፈቅድም። እንዲያውም ማንኛውንም ዲያብሎሳዊ የሆነ የሐሰት ሃይማኖት በቅርቡ ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል።
9. ከሁሉም ሕዝቦችና ዘሮች የመጡ ሰዎች አሁን አንድ እየሆኑ ያሉት እንዴት ነው?
9 ሆኖም አስደናቂው ነገር ከሁሉም ብሔራትና ዘሮች የተውጣጡ ጥሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድነት የመጡ መሆናቸው ነው። ይህም እየተፈጸመ ያለው አምላክ በፈለገው መንገድና ለራሱ አምልኮ ሲባል ነው። ባሁኑ ጊዜ አምላክ የሰው ልጆችን በምድር ላይ አንዱን ብቸኛ ንጹሕ ልሳን እንዲማሩና እንዲናገሩ እያስቻላቸው ነው። እሱም በእርግጥ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው። በእርግጥም ይሖዋ ባሁኑ ጊዜ ይህን ንጹሕ ልሳን ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለተውጣጡ ሰዎች እያስተማራቸው ነው። ይህም አምላክ የራሱ ነቢይና ምስክር በሆነው በሶፎንያስ በኩል ያስነገረው ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜ ነው። “በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው [ይሖዋን (አዓት)] ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን [ቃል በቃል ሲተረጐም “ንጹሕ ከንፈር”] እመልስላቸዋለሁ። (ሶፎንያስ 3:9) ይህ ንጹሕ ልሳን ምንድን ነው?
ንጹሑ ልሳን ምን እንደሆነ ሲብራራ
10. ንጹሕ ልሣን ምንድን ነው?
10 ንጹሑ ልሳን የአምላክ ቃል በሆኑት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው የአምላክ እውነት ነው። በተለይም ደግሞ ለሰው ልጆች ሰላምና ሌሎች በረከቶች የሚያመጣውን የአምላክን መንግሥት የሚመለከተው እውነት ነው። ንጹሑ ልሳን ሃይማኖታዊ ስሕተትንና የሐሰት አምልኮን ያስወግዳል። ይህ ቋንቋ ተናጋሪዎቹን ሁሉ በሕያውና በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ የጠራ፣ ንጹሕና ጤናማ አምልኮ ያስተባብራቸዋል። ባሁኑ ጊዜ 3,000 የሚሆኑ ቋንቋዎች ለመግባባት መሰናክል ሆነዋል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች ደግሞ የሰው ልጆችን ግራ አጋብተዋል። ስለዚህ አምላክ ወደ ግሩምና ንጹሕ ልሳን የመለወጥን ዕድል ለሰዎች እየሰጠ በመሆኑ ምን ያህል ደስተኞች ነን!
11. ንጹሕ ልሣን ለሁሉም ሕዝቦችና ዘሮች ምን አድርጎላቸዋል?
11 አዎን፣ ንጹሑን ቋንቋ ከሁሉም ብሔራትና ዘሮች የተውጣጡ ሰዎች በደንብ አጣርተው እየተናገሩት ነው። በምድር ላይ ያለ ብቸኛ መንፈሳዊ ንጹሕ ልሳን እንደመሆኑ ኃይለኛ አስተባባሪ ኃይል ሆኖ ያገለግላል። በሱ የሚጠቀሙትን ሁሉ “የይሖዋን ስም እንዲጠሩና” “አንድ ሆነው” ወይም ቃል በቃሉ “በአንድ ትከሻ” እንዲያገለግሉት እያስቻላቸው ነው። ስለዚህ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብልና ዘ አምፕሊፋይድ ባይብል እንዳቀረቡት “ባንድ ድምፅ ወይም ሐሳብ” እና “ባንድ ሙሉ ድምፅ” ወይም ሐሳብ ወይም ስምምነትና በአንድ የተባበረ ትከሻ ወይም ክንድ” እያገለገሉት ነው። የእስቴቬን ቲ ባይንግተን ትርጉም እንዲህ ይነበባል፦ “በዚያን ጊዜ እኔ [ይሖዋ አምላክ] ሁሉም ሕዝቦች የይሖዋን ስም ይጠሩና በአገልግሎቱ አንድ ይሆኑ ዘንድ ልሳናቸውን ንጹሕ አደርጋለሁ።” በብዙ ቋንቋዎች በአምላክ አገልግሎት ይህን መሳይ አንድነት ያለው በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ብቻ ነው። ባሁኑ ጊዜ ከአራት ሚልዮን በላይ የሆኑ እነዚህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በ212 አገሮች የምሥራቹን በብዙ ቋንቋዎች እየሰበኩት ነው። ሆኖም ምስክሮቹ የሚናገሩት “በስምምነት” እና “በአንድ ልብና በአንድ አሳብ የተባበሩ” በመሆን ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት በምድር በየትኛውም ቦታ ቢኖሩም ሁሉም የይሖዋ ምስክሮች ለሰማያዊ አባታቸው ምስጋናና ክብር አንዱን ንጹሕ ልሳን ስለሚናገሩ ነው።
ንጹሑን ልሳን አሁንኑ ተማር
12, 13. (ሀ) ንጹሕ ልሣን የመናገሩ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድነው? (ለ) የሶፎንያስ 3:8, 9 ቃላት በዛሬው ጊዜ ትልቅ ቁም ነገር ያላቸው ለምንድነው?
12 ንጹሑን ልሳን የመናገሩ ጉዳይ ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው? መጀመሪያ ነገር ሕይወትህ የተመካው ይህን ቋንቋ በመማርህና በመናገርህ ላይ ስለሆነ ነው። አምላክ ለአሕዛብ ወደ ንጹሑ ልሳን የመለወጥን ዕድል እንደሚሰጥ ተስፋ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ ይላል [ይሖዋ (አዓት)]።”—ሶፎንያስ 3:8
13 እነዚያ የሁሉም የበላይ ገዥ የሆነው የይሖዋ ቃላት የተነገሩት መናገሻዋ ኢየሩሳሌም በነበረው በይሁዳ ውስጥ ከ26 መቶ ዘመናት በፊት ነው። ይሁን እንጂ እነዚያ ቃላት የተነገሩት በተለይ ለዘመናችን ነው። ምክንያቱም ኢየሩሳሌም የሕዝበ ክርስትና ምሳሌ ስለሆነች ነው። እንደዚሁም የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በ1914 ስለተቋቋመች ዘመናችን አምላክ አሕዛብን የሚሰበስብበትና መንግሥታትንም የሚያከማችበት የይሖዋ ቀን ነው። በታላቅ ምስክርነት የመስጠት ሥራ አማካኝነት ሁሉንም አሰባስቦ በትኩረቱ ሥር እያደረጋቸው ነው። ይህ ደግሞ ዓላማውን በመፃረር እንዲነሱ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በምሕረቱ ከነዚህ ብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ንጹሑን ልሳን በመናገር እንዲተባበሩ እያስቻላቸው ነው። ሁሉም አሕዛብ አርማጌዶን በመባል በሚታወቀው “በታላቁ ሁሉን በሚችለው አምላክ ጦርነት” ቀን በእሳታማው የመለኮታዊ ቁጣ መግለጫ ከመቃጠላቸው በፊት አምላክ ተስፋ በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በዚህ ቋንቋ አማካኝነት እንደ አንድ ሆነው ያገለግሉታል። (ራእይ 16:14, 16፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) የሚያስደስተው ነገር ንጹሑን ልሳን የሚናገሩና እውነተኛ አምላኪዎቹ በመሆን በእምነት ስሙን የሚጠሩ ሁሉ በዚያ ዓለም አቀፍ የትኩሳት መዓት ወቅት መለኮታዊ ጥበቃ የሚያገኙ መሆናቸው ነው። አምላክ ከዚያ ጠብቆ ወደ አዲሱ ዓለም ያስገባቸዋል። በዚያም ውስጥ በሁሉም የሰው ዘር ከንፈሮች የሚነገረው ንጹሑ ልሳን ብቻ ይሆናል።
14. የዚህን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ማለፉ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድን እንደሚጠይቅ አምላክ በሶፎንያስ በኩል ያሳየው እንዴት ነው?
14 ከአሁኑ ክፉ ሥርዓት በሕይወት ለመትረፍ ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች አጣዳፊ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ይሖዋ በነቢዩ በሶፎንያስ በኩል ግልጽ አድርጎላቸዋል። በሶፎንያስ 2:1-3 መሠረት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ እፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፣ ትእዛዝ ሳይወጣ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ የይሖዋም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ የይሖዋም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፤ ተከማቹም። እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ [ይሖዋን (አዓት)] ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፤ ትሕትናንም ፈልጉ። ምናልባት በ[ይሖዋ (አዓት)] ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”
15. (ሀ) የሶፎንያስ 2:1-3 የመጀመሪያ ፍጻሜ ምን ነበር? (ለ) በይሁዳ ላይ ከመጣው የአምላክ የጥፋት ፍርድ ያመለጡት እነማን ነበሩ? በዘመናችን ይህን መዳን የሚመሳሰለውስ ምንድን ነው?
15 እነዚያ ቃላት የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በጥንቷ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ላይ ነው። የይሁዳ ኃጢአተኛ ሕዝብ ለይሖዋ ጥሪ እሺ የሚል ምላሽ አልሰጡም ምክንያቱም በ607 ከዘአበ በባቢሎናውያን እጅ ፍርዱን አስፈጽሞባቸዋል። ይሁዳ በአምላክ ፊት “እፍረት የሌለው” እንደነበረ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም በይሖዋ ፊት ሐፍረተ ቢስ “ሕዝብ” ሆናለች። ሆኖም የይሖዋን ታማኝ ነቢይ ኤርምያስን ጨምሮ አንዳንድ አይሁዳውያን የአምላክን ቃል በመስማታቸው ምክንያት ከጥፋቱ ሊተርፉ ችለዋል። ሌሎቹ ተራፊዎች ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክና የኢዮናዳብ ዘሮች ናቸው። (ኤርምያስ 35:18, 19፤ 39:11, 12, 16-18) ባሁኑ ጊዜም በተመሳሳይ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከአርማጌዶን ጥፋት ተርፈው ወደ አዲሱ የአምላክ ዓለም ይገባሉ። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:14-16) ንጹሑን ልሳን የሚማሩና የሚናገሩ ብቻ ናቸው የዚያ ጥፋት ደስተኛ ተራፊዎች የሚሆኑት።
16. “በይሖዋ የቁጣ ቀን” ለመሰወር አንድ ሰው ምን ማድረግ አለበት?
16 ይሁዳና ኢየሩሳሌም እንዲጠፉ የይሖዋ ብያኔ እንደነበረ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም መጥፋት አለባት። እንዲያውም የሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ጥፋት ቀርቧል። ስለዚህ ከጥፋቱ ሊተርፉ የሚፈልጉ ሁሉ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ይህንንም ማድረግ ያለባቸው ልክ በአውድማ ላይ እህል ከገለባው እንዲለይ ወደ ሰማይ ሲወረወር ገለባው በነፋስ ተጠርጎ እንደሚወስደው ዓይነት “ቀኑ እንደ ገለባ ከማለፉ” በፊት መሆን አለበት። ከአምላክ ቁጣ እንድንሰወር ከፈለግን የሚያቃጥለው የይሖዋ የቁጣ ቀን ሳይመጣብን ንጹሑን ልሳን መናገርና አምላክ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተን አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት አለብን። በሶፎንያስ ዘመንና ባሁኑ ጊዜም ትሑታን ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን ይፈልጋሉ። ይሖዋን መፈለግ ማለትም በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ አእምሮአችንና ጉልበታችን እሱን ማፍቀር ማለት ነው። (ማርቆስ 12:29, 30) እንዲህ የሚያደርጉም “ምናልባት በይሖዋ ቁጣ ቀን ይሰወሩ ይሆናል።” ታዲያ ለምንድን ነው ትንቢቱ “ምናልባት” የሚለው? ምክንያቱም መዳን በታማኝነትና በጽናት ላይ የተመካ በመሆኑ ነው። (ማቴዎስ 24:13) ከአምላክ የጽድቅ ደረጃዎች ጋር የሚስማሙና ንጹሑን ልሳን በመናገር የሚቀጥሉ ከይሖዋ ቁጣ ቀን ይሰወራሉ።
17. ልንመለከታቸው የሚገቡ ምን ጥያቄዎች ይቀራሉ?
17 የይሖዋ የቁጣ ቀን ቅርብ ስለሆነና መዳንም የተመካው ንጹሑን ልሳን በመማርና በመጠቀም ላይ በመሆኑ እሱን በማጥናትና በመናገር የምንዋጥበት ጊዜ አሁን ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ንጹሑን ልሳን ሊማር የሚችለው እንዴት ነው? እሱን በመናገርስ ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?
እንዴት ትመልሳለህ?
◻ የሰው ንግግር እንዴት መጣ?
◻ ንጹሑ ልሳን ምንድን ነው?
◻ በሶፎንያስ 3:8, 9 ላይ ያሉት ቃላት ላሁኑ ጊዜ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ለምንድን ነው?
◻ “በይሖዋ የቁጣ ቀን” ለመሰወር ምን ማድረግ አለብን?
-
-
ንጹሑን ልሳን ተናገርና ለዘላለም ኑር!መጠበቂያ ግንብ—1991 | ግንቦት 1
-
-
ንጹሑን ልሳን ተናገርና ለዘላለም ኑር!
“[ይሖዋን (አዓት)] ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ። ምናልባት [በይሖዋ (አዓት)] ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”—ሶፎንያስ 2:3
1. (ሀ) ተማሪዎች የውጭ ቋንቋን ለመማር በምን ዘዴዎች ይጠቀማሉ? (ለ) ንጹሑን ልሣን መናገር ያለብን ለምንድነው?
ተማሪዎች አንድን አዲስ ቋንቋ የሰዋሰውን ሥርዓት በማጥናት ወይም ሰዎች ሲናገሩ በመስማት ሊማሩት ይችላሉ። በሰዋስው ሥርዓት ሲማሩት ባጠቃላይ የመማሪያ መጻሕፍትን በመጠቀም የሰዋሰው ሕጎችን ይማራሉ። በመስማት በሚማሩበት ጊዜም በመምህራቸው የተነገሩ ድምፆችንና የንግግር ፈሊጦችን በመቅዳት ወይም በመኮረጅ ይማራሉ። “ንጹሑን ልሳን” ለመማር ሁለቱም ዘዴዎች ያገለግላሉ። “በይሖዋ የቁጣ ቀን ለመሰወር” የምንሻ ከሆነም ይህን ቋንቋ መናገራችን አስፈላጊ ነው።—ሶፎንያስ 2:1-3፤ 3:8, 9
2. የንጹሑ ቋንቋ የሰዋሰው ሕግ ሊባል የሚችለውን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
2 ንጹሑን ልሳን ለመማር አስፈላጊ የሆነው የመማሪያ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እሱንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በትጋት በማጥናት ለንጹሑ ልሳን የሰዋስው ሕግ የሚባሉትን ልትማሩ ትችላላችሁ። ከይሖዋ ምስክሮች ባንዱ የሚመራ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጥሩ ጅምር ነው። ከዚህ ቀደም ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎችም ዘወትር በትጋት ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናታቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ንጹሑን ልሳን ለመማር ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የተለዩ መንገዶች አሉን? ንጹሑን ልሳን በመናገርስ ምን ጥቅሞች ይመጣሉ?
ንጹሑን ልሳን እንዴት መማር እንደሚቻል
3. ንጹሑን ልሣን ለመማር ብቸኛው መንገድ ምንድነው?
3 አንድን ቋንቋ በማጥናት ላይ ያለ ሰው ልዩ ልዩ የሰዋሰው ሕጎችን ለማዛመድ እንደሚሞክር ሁሉ ንጹሑን ልሳን ለመማር የሚረዳው አንዱ መንገድ እየተማርክ ያለኸውን እውነት ከዚህ በፊት ከምታውቃቸው ነጥቦች ጋር ማገናዘብ ነው። ለምሳሌ ባንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ አውቀህ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ተግባሮቹን በሚመለከት የምታውቀው ጥቂት ኖሮ ይሆናል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥ በመሆን አሁን እንደሚገዛና በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅትም የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ እስኪደርሱ እንደሚረዳቸው አስተምሮሃል። (ራእይ 20:5, 6) አዎን አዲስ ሐሳቦችን ከዚህ በፊት ከምታውቃቸው ጋር ማገናዘብ ንጹሑን ቋንቋ የመረዳት ችሎታህን ያሻሽለዋል።
4. (ሀ) የንጹሑን ልሣን ‘ሰዋሰዋዊ ሕግ’ ለመማር ሌላው መንገድ ምንድነው? ይህንን በምሳሌ ለማስረዳትስ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ተጠቅሷል? (ለ) ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሦስት መቶ ሰዎች እርምጃ ሲወስዱ ምን ሆነ? የጌዴዎን ታሪክ ምን ትምህርት ያስተምራል?
4 የንጹሕ ልሳንን ‘ሰዋስዋዊ’ ሕጎች ለመማር ሌላው መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ድርጊቶችን በዓይነት ሕሊና ማየት ነው። ለምሳሌ ያህል በመሳፍንት 7:15-23 ላይ የተመዘገበውን ታሪክ “ለማየትና ለማዳመጥ” ሞክር። ተመልከት። እስራኤላዊው መስፍን ጌዴዎን ሠራዊቱን እያንዳንዱ ሦስት መቶ ጓዶች ያሉት ሦስት ቦታ ከፋፈላቸው። በጨለማ ከጊልቦአ ተራራ ወርደው ተኝተው ያሉትን ምድያማውያን ሠፈር ይከብባሉ። እነዚህ ሦስት መቶ ሰዎች በደንብ የታጠቁ ናቸውን? ወታደራዊ ጦር መሣሪያ አልታጠቁም። ትዕቢተኛ ወታደራዊ ጠበብት እንዴት በሳቁባቸው! እያንዳንዱ ሰው የያዘው መለከት፣ ትልቅ ማሰሮና በማሰሮው ውስጥ ችቦ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እስቲ አዳምጥ! ምልክት ሲሰጣቸው ከጌዴዎን ጋር ያሉት መቶ ሰዎች መለከታቸውን ነፉ፤ ማሰሮዎቻቸውንም ሰባበሩ። ሌሎቹ ሁለት መቶ ወታደሮችም እንደዚያው አደረጉ። ሁሉም የሚንበለበሉ ችቦዎቻቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመያዝ “የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ!” ብለው ሲጮኹ ትሰማለህ። ይህ ምድያማውያንን እንዴት የሚያሸብር ነው! ከድንኳኖቻቸው እየተንገዳገዱ ሲወጡ በእንቅልፍ የከበዱ ዓይኖቻቸው ደግሞ ፍርሃት የሚያሳድር ጥላ የፈጠሩትን የሚንቦገቦጉ የሚፈነጣጠሩ ችቦዎችን በፍርሃት ፈጥጠው ይመለከታሉ። ምድያማውያን መሸሽ ሲጀምሩ የጌዴዎን ሰዎች መለከቶቻቸውን መንፋታቸውን ይቀጥላሉ። አምላክም ጠላቶቻቸውን አንዱን በሌላው ላይ ያስነሣቸዋል። ይህስ በንጹሑ ልሳን የሚገኝ እንዴት ትልቅ ትምህርት ነው! አምላክ አገልጋዮቹን ያለ ሰብአዊ ጦር ኃይል ሊያድን ወይም ነፃ ሊያወጣ ይችላል። ከዚህም በላይ “ይሖዋ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል ሕዝቡን አይተውም።”—1 ሳሙኤል 12:22
5. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ንግግራችንን ለማጥራት ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ተማሪዎች አንድን የባዕድ ቋንቋ በመስማት ዘዴ በሚማሩበት ጊዜ የመምህሩን ድምፅና አነጋገር በትክክል ለመድገም ወይም ለመኮረጅ ይሞክራሉ። ንጹሑን ልሳን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመናገር እንዴት መልካም አጋጣሚዎች አሉ! እዚያም ሌሎች በዚያ የቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ቋንቋ ሐሳባቸውን ሲገልጹ እንሰማለን፤ እኛም ራሳችን ሐሳባችንን ለመግለጽ መብት እናገኛለን። የተሳሳተ ነገር እንዳንናገር እንፈራለንን? ያ አያሳስበን፤ ምክንያቱም እንደ ሳምንታዊው መጠበቂያ ግንብ በመሳሰሉት ስብሰባዎች ላይ የሚመራው ሽማግሌ በደግነት ሲያርመን ንግግራችንን የተጣራ ሊያደርግልን ይችላል። ስለዚህ አዘውትረህ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ተገኝ፤ ተሳተፍም።—ዕብራውያን 10:24, 25
የቆሸሸ አነጋገር ሰርጎ ገባ
6. በይሖዋ ምሥክሮችና በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች መካከል ይህን ያህል ጉልህ ልዩነት ያለው ለምንድነው?
6 የይሖዋን ዓላማ የሚያውጁና ሰማያዊ መንግሥቱንም የሚያስታውቁ ሁሉ ምስክሮቹ በመሆን ንጹሕ ልሳን ይናገራሉ። ስሙን ያስታውቃሉ። “ትከሻ ለትከሻ” ወይም ስምም ሆነውም ያገለግሉታል። (ሶፎንያስ 3:9) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖራቸውም ንጹሑን ልሳን አይናገሩም፤ ወይም በእምነት በስሙ አይጠሩም። (ኢዩኤል 2:32) በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ እርስ በርሱ የሚስማማ መልእክት የላቸውም። ለምን? ምክንያቱም ሃይማኖታዊ ወጎችን፣ ዓለማዊ ፍልስፍናዎችንና ፖለቲካዊ ድጋፍ ሰጭነትን ከአምላክ ቃል በላይ አድርገው ስለያዙ ነው። ዓላማቸው፣ ተስፋቸውም ሆነ ዘዴያቸው ሁሉ የዚህ ክፉ ዓለም ነው።
7. በ1 ዮሐንስ 4:4-6 ላይ በይሖዋ ምሥክሮችና በሐሰት ሃይማኖቶች መካከል ምን ልዩነት እንዳለ ነው የሚያመለክተው?
7 ሕዝበ ክርስትና እንዲያውም ጠቅላላው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የይሖዋ ምስክሮች የሚናገሩትን ዓይነት ቋንቋ አይናገሩም። ለዚህም ነው ሐዋርያው ዮሐንስ ንጹሑን ልሳን ለሚናገሩት እንደሚከተለው የጻፈው፦ “እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችሁማል [ምክንያቱም] በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ይበልጣልና። እነሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ። ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ግን ከእግዚአብሔር ነን እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል። ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም።” (1 ዮሐንስ 4:4-6) የይሖዋ አገልጋዮች የሐሰት አስተማሪዎችን አሸንፈዋል። ምክንያቱም ከሕዝቡ ጋር የሆነው አምላክ “በዓለም ካለው [ከዓለም ማለትም ከዓመፀኛው ሰብአዊ ኅብረተሰብ ጋር ካለው ከዲያብሎስ] ይበልጣልና።” ከሐዲዎች “ከዓለም ስለሆኑ” እና የሱ ክፉ መንፈስም ስላላቸው “ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ፤ ዓለሙም ይሰማቸዋል።” በግ መሰል ግለሰቦች ግን የይሖዋ ሕዝቦች በድርጅቱ በኩል የሚቀርበውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ንጹሕ ልሳን እንደሚናገሩ በመገንዘብ የሚሰሙት ከአምላክ የሆኑትን ነው።
8. የዐመጽ ሰው መታወቂያው ወይም መለያው ምንድነው?
8 ታላቅ ክህደት እንደሚመጣ በትንቢት ተነግሮ ነበር። “የዓመፅ ምሥጢርም” ገና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቅ ማለት ጀምሮ ነበር። ከጊዜ በኋላ በጉባኤ ውስጥ የማስተማርን ቦታ የተቀበሉ ወይም የያዙ ሰዎች ብዙ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን አስተማሩ። ቋንቋቸው ንጹሕ ከመሆን በጣም የራቀ ነበር። ስለዚህ ከሐሰት ሃይማኖታዊ ወጎች፣ ከዓለማዊ ፍልስፍናዎችና ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ ትምህርቶች ጋር የተሳሰረው “የዓመፅ ሰው” የተባለው የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ቡድን መጣ።—2 ተሰሎንቄ 2:3, 7
ንጹሑ ልሳን በዓለም ዙሪያ ሲነገር ይሰማል
9. በ19ኛው መቶ ዘመን ምን ሃይማኖታዊ ሁኔታዎች በመከሰት ላይ ነበሩ?
9 “ለቅዱሳን ስለተሰጠ እምነት የሚጋደሉት” በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። (ይሁዳ 3) እነዚህ አማኞች ሊገኙ የሚችሉት የት ነው? የሐሰት ሃይማኖት ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሕዝቦች ለብዙ መቶ ዓመታት በመንፈሳዊ ጨለማ አቆይቷቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ የሱ ድጋፍ ወይም ሞገስ ያላቸውን ሰዎች ያውቅ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 2:19) ከዚያም የንግድ፣ የኢንዱስትሪና ማኅበራዊ ለውጦች ይደረጉ በነበረበት በ19ኛው መቶ ዘመን ከአጠቃላዩ የሐሰት ሃይማኖት ዝብርቅ ባቤል የተለዩ ድምፆች መሰማት ጀመሩ። አነስተኛ ቡድኖች የዘመኑን ምልክቶች ለማንበብና የክርስቶስን ዳግማዊ ምፅዓት ለመተንበይ ሞከሩ፤ ይሁን እንጂ ሁሉም ንጹሑን ልሳን ተናጋሪዎቹ አልሆኑም።
10. “ዳግም መምጣትን” ይጠባበቁ ከነበሩት መካከል አምላክ ንጹሑን ልሣን እንዲናገር የመረጠው የትኛውን ቡድን ነው? የይሖዋ እጅ ከእነሱ ጋር እንደነበረ በግልጽ የሚታየውስ እንዴት ነው?
10 ይሁን እንጂ በ1879 ምስክሮቹ በመሆን ንጹሑን ልሳን እንዲናገር በይሖዋ የተመረጠው የትኛው “የዳግም ምፅዓት” ድምፅ እንደሆነ ግልጽ ሆነ። በዚያን ጊዜ በቻርልስ ቴዝ ራስል የሚመራ አንድ ንዑስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ውስጥ ፒትስበርግ ፔንሲልቫንያ መሰብሰብ ጀምሮ ነበር። እነሱም የኢየሱስ የማይታይ መገኘቱ በዳግም ምፅዓቱ እንደሚጀምር፣ የዓለም የመከራ ዘመን በመምጣት ላይ እንደነበረ፣ ይህንንም ተከታትሎ የሚመጣው ለታዛዥ ሰዎች ከዘላለም ሕይወት ጋር በምድር ላይ ገነትን የሚመልሰው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መሆኑን እርግጠኞች ሆኑ። በ1879 ሐምሌ ወር ላይ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አሁን መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀውን መጽሔት ማተም ጀመሩ። ከመጀመሪያው እትም ለሰዎች የታደሉት 6,000 ቅጂዎች ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ “የይሖዋ እጅ” ከነዚያ ምስክሮቹ ጋር ነበር፤ ምክንያቱም ባሁኑ ጊዜ ይህ መጽሔት በ111 ቋንቋዎች በያንዳንዱ እትም ባማካይ ከ15,000,000 በላይ ቅጂዎች እየታተመ ነው።—ከሥራ 11:19-21 ጋር አወዳድር
11, 12. ንጹሑን ልሣን የሚናገሩት የተረዱአቸው አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ምንድናቸው?
11 በመጽሐፍ ቅዱስና በይሖዋ ምስክሮች ጽሑፎች አማካኝነት በተለይ ደግሞ እነዚህ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ምሥራቹን ለማስታወቅ በሚያደርጉት ጥረት አማካኝነት ንጹሑ ልሳን በምድር ዙሪያ የታወቀ ሆኗል። ንጹሑን ልሳን የሚናገሩትስ እንዴት ያሉ ታላቅ ጥቅሞችን እያገኙ ነው! ምሥጢራዊውን የሥላሴ ቅንብር ተከትለው “እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነው፤ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው” በማለት ፋንታ ይሖዋ ከሁሉ በላይ የሆነ ሉዓላዊ ገዥ፣ ኢየሱስ ደግሞ ከሱ ያነሰ ሆኖ ልጁ መሆኑንና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ አስገራሚ አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገልጸው አቋም ጋር ይስማማሉ። (ዘፍጥረት 1:2፤ መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 3:16, 17) የንጹሑ ልሳን ተናጋሪዎች ሰው ከአነስተኛ የሕይወት ዓይነት ተነስቶ በመሻሻል የመጣ ሳይሆን በአፍቃሪ አምላክ የተፈጠረ መሆኑን ያውቃሉ። (ዘፍጥረት 1:27፤ 2:7) ሙታንን ከመፍራት የሚያድነውን እውነት ይኸውም የነፍስ ሕላዌ በሞት እንደሚያቆም ይገነዘባሉ። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ሲኦልን የተረዱት በአንድ ጨካኝ አምላክ የተፈጠረ የእሳታማ ሥቃይ ቦታ እንደሆነ አድርገው ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ መቃብር እንደሆነ ነው። (ኢዮብ 14:13) እንደዚሁም አምላክ ለሙታን የሰጠው ተስፋ ትንሣኤ መሆኑን ያውቃሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:25፤ ሥራ 24:15
12 ንጹሑን ልሳን የሚናገሩት ሁሉ ለደምና ለሕይወት አክብሮት ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ሥራ 15:28, 29) ለታዛዥ ሰዎች የተከፈለው የቤዛ ዋጋ የክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት መሆኑን ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 20:28፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) ጸሎታቸው መቅረብ ያለበት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለይሖዋ አምላክ ብቻ መሆኑን ስለሚያውቁ ወደ “ቅዱሳን” አይጸልዩም። (ዮሐንስ 14:6, 13, 14) የአምላክ ቃል ጣዖት ማምለክን ስለሚያወግዝ በአምልኮታቸው በምስሎች አይጠቀሙም። (ዘፀአት 20:4-6፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) ከዚህም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዘውን መናፍስትነትን ስለማይቀበሉ ከአጋንንት ጋር የተያያዘ ማንኛውም ነገር ከሚያመጣው አደጋ ይጠበቃሉ።—ዘዳግም 18:10-12፤ ገላትያ 5:19-21
13. ንጹሑን ልሣን የሚናገሩት ግራ የማይጋቡት ለምንድነው?
13 ንጹሑን ልሳን የሚናገሩ የይሖዋ አገልጋዮች በጊዜ ሂደት ውስጥ የትኛው ነጥብ ላይ ስለመድረሳቸው ግራ አይጋቡም። ኢየሱስ ክብር የተሞላ የማይታይ መንፈስ ሆኖ በተገኘበት “የፍጻሜ ዘመን” ላይ እንደሚኖሩ ይሖዋ አስተምሯቸዋል። (ዳንኤል 12:4፤ ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) ክርስቶስ ኃያላን ሰማያዊ ሠራዊቶችን ከኋላው አስከትሎ የአምላክን ፍርድ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ ለማስፈጸም ወደ ጦርነት ሜዳ ሊገባ ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 16:14, 16፤ 18:1-8፤ 19:11-21) አዎን፣ ንጹሑን ልሳን የሚናገሩትንም በክርስቶስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ለታዛዥ የሰው ልጆች በሙሉ በምድራዊ ገነት ታላላቅ በረከቶችን እንደምታመጣ የሚገልጸውን የምሥራች በማወጅ እየተጣደፉ ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14፤ ሉቃስ 23:43) ይህ ሁሉ አለ፤ እንዲያውም ከላይ ከላይ ብቻ ጨረፍ ስናደርግለት ነው። በእርግጥም ንጹሑ ልሳን በምድር ላይ ካሉት ቋንቋዎች ሁሉ ይበልጥ የበለጸገና ውድ የሆነ ቋንቋ ነው!
14. ንጹሑን ልሣን የሚናገሩት ያገኙአቸው ሌሎች ጥቅሞች ምንድናቸው?
14 ንጹሑን ልሳን የሚናገሩ ሰዎች የሚያገኙአቸው ጥቅሞች ልብንና አእምሮን የሚጠብቀውን “የአምላክን ሰላምም” ይጨምራሉ። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ጤንነትን፣ ደስታንና ይሖዋን ከማስደሰት የሚመጣውን እርካታ የሚያመጡትን የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጎች ይታዘዛሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አዎን፤ የንጹሑን ልሳን ተናጋሪዎች አምላክ ተስፋ በገባው አዲስ ዓለም ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—2 ጴጥሮስ 3:13
ተጠቀምበት አለዚያ ትረሳዋለህ
15. ንጹሑን ልሣን በጥሩ ሁኔታ በመረዳትህ ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?
15 ወደ አዲሱ ዓለም ገብተህ ንጹሑን ቋንቋ እንድትናገር ከፈለግህ የምታስበውም በዚሁ ቋንቋ እስኪሆን ድረስ በደንብ ልታውቀው ይገባሃል። አንድ ሰው አንድን ቋንቋ በሚማርበት ጊዜ መጀመሪያ ላይ የሚያስበው በትውልድ ቦታው ቋንቋ ሆኖ ሐሳቦቹን ወደ አዲሱ ቋንቋ ይተረጉማል። በአዲሱ ቋንቋ በደንብ እየሠለጠነ በሄደ ቁጥር ግን የመተርጐሙ ሂደት ሳያስፈልገው በሱው ማሰብ ይጀምራል። በተመሳሳይም በትጋት በማጥናት የንጹሑን ልሳን ጥልቅ እውቀት ከማግኘትህ የተነሣ ችግሮችህን ለመፍታትና “በሕይወት መንገድ” ጸንተህ ለመኖር እንዲረዳህ የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጎችና ሥርዓቶች በሥራ እንዴት እንደምታውላቸው ታውቃለህ።—መዝሙር 16:11
16. ንጹሑን ልሣን አዘውትረህ ካልተጠቀምክበት ምን ሊደርስብህ ይችላል?
16 በንጹሑ ልሳን አዘውትረህ መጠቀም አለብህ። አለዚያ አጥርተህ የመናገር ችሎታው ይጠፋብሃል። ለማስረዳት ያህል ከአያሌ ዓመታት ቀደም ብሎ አንዳንዶቻችን የውጭ ቋንቋ ተማርን። አሁን የዚያን ቋንቋ አንዳንድ ቃላት እናስታውስ ይሆናል። ግን አዘውትረን ስለማንጠቀምበት የመናገር ችሎታችንን አጥተን ይሆናል። በንጹሑ ልሳን ረገድም ያው ነገር ሊደርስ ይችላል። አዘውትረን የማንጠቀምበት ከሆነ ችሎታችንን ልናጣ እንችላለን። ያ ደግሞ በመንፈሳዊነታችን ላይ አሳዛኝ ውጤት ያስከትላል። ስለዚህ በስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ንጹሑን ቋንቋ አዘውትረን እንናገረው። እንዲህ ማድረጋችን ከግል ጥናት ጋር ተጣምሮ ነገሮችን በንጹሑ ቋንቋ በትክክል እንድንናገር ያስችለናል። ያስ እንዴት አስፈላጊ ነው!
17. ንግግር ሕይወት አንድን ወይም ሞት የሚያስከትል ሊሆን እንደሚችል ለማስረዳት ምን መጥቀስ ይቻላል?
17 ንግግር ሕይወት አድን ሊሆን ወይም ሞት ሊያስከትል ይችላል። ይህም በእስራኤላዊው በኤፍሬም ነገድና በጊልያዱ መስፍን በዮፍታሔ መካከል ግጭት በተነሣበት ወቅት ታይቷል። የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ይሸሹ የነበሩትን ኤፍሬማውያን ለይቶ ለማወቅ ጊልያዳውያን “ሺቦሌት” የሚለውን የመለያ ቃል ተጠቀሙ። የኤፍሬም ሰዎችም የቃሉን የመጀመሪያ ድምፅ (‘ሽ’) አሳስተው በመጥራት “ሲቦሌት” በማለት በዮርዳኖስ መልካዎች ላይ ለቆሙት የጊልያድ ዘቦች ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ። በዚህም ምክንያት 42,000 ኤፍሬማውያን ታረዱ። (መሳፍንት 12:5, 6) በተመሳሳይም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በደንብ ለማይተዋወቁ ሰዎች የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የሚያስተምሩት ከንጹሑ ልሳን ጋር የሚቀራረብ ድምፅ ያለው ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ በሐሰት ሃይማኖታዊ መንገድ መናገር በይሖዋ የቁጣ ቀን ሞት የሚያስከትል ይሆናል።
አንድነታችንን እንደጠበቅን እንኖራለን
18, 19. የሶፎንያስ 3:1-5 ትርጉም ምንድነው?
18 የጥንቷን እምነተ ቢስ ኢየሩሳሌምንና የሷን ዘመናዊ እኩያ ሕዝበ ክርስትናን በማስመልከት በሶፎንያስ 3:1-5 ላይ እንዲህ ተብሏል፦ “ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱ ከተማ ወዮላት! ድምፅን አልሰማችም። ተግሣጽንም አልተቀበለችም። [በይሖዋም (አዓት)] አልታመነችም። ወደ አምላኳም አልቀረበችም። በውስጧ ያሉ አለቆቿ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው። ፈራጆቿም እስከ ነገ ድረስ ምንም እንደማያስቀሩ እንደ ማታ ተኩላዎች ናቸው። ነቢያቶቿ ቅሌታሞችና ተንኰለኞች ሰዎች ናቸው። ካህናቶቿም መቅደሱን (ቅዱስ የነበረውን ነገር) አርክሰዋል። በሕግም ላይ ግፍ ሠርተዋል። [ይሖዋ (አዓት)] በውስጧ ጻድቅ ነው። ክፋትን አያደርግም። ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል። ሳያወጣውም አይቀርም። ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም።” የእነዚህ ቃላት ቁም ነገር ምንድን ነው?
19 የጥንቷ ኢየሩሳሌምም ሆነች ዘመናዊቷ ሕዝበ ክርስትና በይሖዋ ላይ ዓምፀዋል። በሐሰት አምልኮ ረክሰዋል። የመሪዎቻቸው መጥፎ ድርጊት ጭቆናን አስከትሏል። አምላክ በተደጋጋሚ ቢያስጠነቅቃቸውም ሰምተው ወደሱ አልቀረቡም። መሳፍንቶቻቸውም በዕብሪት ጽድቅን የሚንቁ እንደሚያደቡ አንበሶች ናቸው። እንደ ነጣቂ ተኩላዎችም በመሆን ፍትሕን ቦጫጭቀው ጥለውታል። ካህናቶቻቸው “ቅዱስ የሆነውን ነገር አርክሰዋል፤ በአምላክ ሕግ ላይም ግፍ (ዓመፅ) ሠርተዋል።” ስለዚህ ይሖዋ “የቁጣውን ትኩሳት ሁሉ ያፈስስባቸው ዘንድ አሕዛብን ሊሰበስብ መንግሥታትንም ሊያከማች” ነው።—ሶፎንያስ 3:8
20. (ሀ) በይሖዋ የቁጣ ቀን ለመዳን ምን መደረግ አለበት? (ለ) ከአምላክ የሚመጡትን ዘላለማዊ በረከቶች ለማግኘት ተስፋ ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው?
20 የይሖዋ የቁጣ ቀን በፍጥነት እየቀረበ ነው። ከዚያ ተርፎ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት እንግዲያውስ ሳትዘገይ ንጹሑን ልሳን ተማርና ተናገር። እንዲህ ካደረግህ ብቻ ነው ባሁኑ ጊዜ ከመንፈሳዊ ታላቅ ውድቀትና በፍጥነት እየቀረበ ካለው ዓለም አቀፍ መዓት ጥበቃ ልታገኝ የምትችለው። የይሖዋ ምስክሮች የአምላክን የቁጣ ቀንና ልብን የሚያበረታታውን የመንግሥቱን መልእክት እያወጁ ነው። ስለ መንግሥቱ ክብር መናገር ምን ያህል ያስደስታቸዋል! (መዝሙር 145:10-13) ከነሱ ጋር ተባበርና የንጹሑ ቋንቋ ምንጭ ከሆነው ከልዑል የበላይ ገዥ ከይሖዋ የሚመጡትን የዘላለም ሕይወትና ሌሎች በረከቶችን ለማግኘት ተስፋ ልታደርግ ትችላለህ።
እንዴት ትመልሳለህ?
◻ ንጹሑን ልሳን ለመማር የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ ንጹሑን ልሳን መናገር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ንጹሑን ልሳን አዘውትረህ የማትጠቀምበት ከሆነ ምን ሊያጋጥም ይችላል?
◻ አንድ ሰው የይሖዋን የቁጣ ቀን በሕይወት በማለፍ የዘላለም በረከቶችን ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች መለከታቸውን ነፉ፤ ችቦአቸውንም ከፍ አድርገው ያዙት
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቻርልስ ራስልና ተባባሪዎቹ አምላክ ንጹሑን ልሳን ለማስፋፋት እየተጠቀመባቸው እንዳለ ከ1879 ጀምሮ ግልጽ ሆነ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ንጹሑን ልሳን በመናገር በኩል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አንድ ሆነሃልን?
-