ምዕራፍ 11
ምድራዊቱ ኢየሩሳሌም ከሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ጋር ስትነጻጸር
1. (ሀ) የኢየሩሳሌም መጥፋት አዲስ ነገር ይሆናልን? (ለ) ኢየሩሳሌም ድጋሚ ጥፋት ቢደርስባት ለሁሉም የሰው ዘሮች ታላቅ ውድቀት የማይሆነው ለምንድን ነው?
በአሁኑ ጊዜ በሥጋ አይሁዳውያን የሆኑት በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኘው ኢየሩሳሌም ለዘላለም እንደምትጸና ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። የሕዝበ ክርስትና ሰዎችም እንኳን ሳይቀሩ ኢየሱስ አገልግሎቱን የፈጸመባትን ከተማ ከፍ አድርገው ይመለከቷታል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር የዚያች ከተማ ኅልውና ስለመቀጠሉ ዋስትና ይሰጣልን? ከተማዋ በመጀመሪያ በ607 ከዘአበ በባቢሎናውያን በኋላም በ70 እዘአ በሮማውያን ጠፍታ ነበር። አሁንም እንደገና ጥፋት ቢደርስባት በሁሉም የሰው ዘር ላይ መከራ ይሆናል ማለት ነውን? አይደለም፣ የአብርሃም ቃል ኪዳን በረከቶች ወደ ሰው ዘሮች አንዲፈሱ ከተማዋ አታስፈልግም። እንዲያውም ስለ አብርሃም እንዲህ ተጽፏል:- “[እውነተኛ (አዓት)] መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።”— ዕብራውያን 11:10
2. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ሌላ የምትበልጥ ኢየሩሳሌም እንዳለች ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የዚህች ኢየሩሳሌም ባል ወይም ባለቤት የሆነውስ ማን ነው? ከእርሷ የሚወልዳቸው ልጆቹስ እነማን ናቸው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ:- “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት” ብሎ ጽፏል። (ገላትያ 4:26) በዚሁ ላይ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ከሣራ ጋር እንደምትመሳሰልና የታላቁ አብርሃም የይሖዋ አምላክ ሚስት መሠል ድርጅት እንደሆነች አሳይቷል። በዚህ ምክንያት ‘የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ልጆች እንደ ጳውሎስ ያሉት በመንፈስ የተዋጁት ክርስቲያኖች ናቸው።
“ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ንጉሣዊ ከተማ ሆነች
3. (ሀ) ይሖዋ አምላክ ራሱ መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ለ) ኢየሱስ ክርስቶስ የነገሠው የት ነበር? ይህስ በይሖዋ ንግሥና ላይ ምን ውጤት አመጣ?
3 “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” በ1914 “የአሕዛብ ዘመናት” ካለቁበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥታዊ መልክ ይዛለች። (ሉቃስ 21:24) ከዚያን ጊዜ ወዲህ መዝሙር 97:1 ተግባራዊ ሆኗል:- “[ይሖዋ (አዓት)] ነገሠ፣ ምድር ሐሴትን ታድርግ።” በተመሳሳይም መዝሙር 99:1, 2 ተግባራዊ ሆኗል:- “[ይሖዋ (አዓት)] ነገሠ፣ . . . [ይሖዋ (አዓት)] በጽዮን ታላቅ ነው፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አለ።” በ1914 በአንድ ወቅት ንጉሣዊ ከተማ በነበረችው በኢየሩሳሌም ይወከል የነበረው የዳዊት ንጉሣዊ መስመር መረገጥ የሚያቆምበት ጊዜ መጣ። ስለዚህም እርሱ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ‘በላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ማለትም በሰማይቱ ኢየሩሳሌም በቀኙ እንደ ንጉሥ አድርጎ በማስቀመጥ አነገሠው፤ በዚህም መንገድ ይህችን ንጉሣዊ ከተማ አደረጋት። የራሱ የይሖዋ ንግሥና ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ንጉሥ ሆኖ በመሾሙ ተጠናከረ ወይም ተስፋፋ።
4. “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ከ1914 ወዲህ ንጉሣዊ ከተማ የሆነችው በምን ሁኔታዎች ነው?
4 ስለዚህ ሰማያዊው መንግሥት በ1914 ከተወለደ በኋላና ሰይጣንና አጋንንቱም ከሰማይ ከተጣሉ በኋላ እንደሚከተለው ተብሎ መታወጁ ተገቢ ነበር:- “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፣ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።” (ራእይ 12:1–10) “የክርስቶስም ሥልጣን” እንደ ንጉሥ በመሆን ‘በላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ላይ እንዲገዛ ያደርገዋል። በእርግጥም እርስዋ በዚያ በተባረከው ዓመት በ1914 ንጉሣዊ ከተማ ሆናለች።
‘የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ሴት ልጅ
5, 6. (ሀ) በራእይ 21:1, 2 ላይ ዮሐንስ የተመለከተው ምን ምሳሌያዊ ከተማን ነው? (ለ) በዘካርያስ 9:9, 10 ላይ እንደተገለጸው ንጉሣዊ አቀባበል ያደረጉት እነማን ናቸው? ምን በሚሉ ቃላትስ?
5 በ70 እዘአ ኢየሩሳሌም በሮማ ሠራዊት ከጠፋች ከሩብ ምዕተ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት አስደናቂ ራእዮች ተሰጥተውት ነበር። በራእይ 21:1, 2 ላይ ዮሐንስ ስለ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ይናገራል። በይሖዋ ስም የሚመጣውን አዲስ የተሾመ ንጉሥ በደስታ የሚቀበሉት “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” የሚሆኑት ሰዎች ናቸው፤ እነርሱም በዘካርያስ 9:9, 10 ላይ ባሉት በሚከተሉት ቃላት ጥሪ ቀርቦላቸዋል:-
6 “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፣ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ እልል በይ፣ እነሆ፣ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሁትም ሆኖ በአህያም . . . ተቀምጦ . . . ይመጣል። ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም አጠፋለሁ፤ የሰልፍም ቀስት ይሰበራል። ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፣ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፣ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሆናል።”
7. በዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ወቅት ይህ ትንቢት ተፈጻሚነትን ያገኘው በማን ነው? በምንስ መንገድ?
7 ይህ ትንቢት ኢየሱስ ክርስቶስ በ33 እዘአ ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው የድል ግልቢያ ከፊል ተፈጻሚነቱን አግኝቷል። ከ1919 ወዲህ ደግሞ በመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ላይ የመጨረሻ ፍጻሜውን አግኝቷል። በእነዚያ የቅቡዓን ቀሪዎች አባላት መካከል በጥንቶቹ በኤፍሬምና የሁለቱ ነገድ የይሁዳ መንግሥት ዋና ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌም መካከል እንደነበረው መለያየት ያለ መከፋፈል የለም። እነርሱ በማቴዎስ 24:14 እና በማርቆስ 13:10 ላይ ያለውን ትንቢት ለመፈጸሙ ዓላማ የመሲሐዊውን መንግሥት ፍላጎት አንድ ሆነው በማገልገል ድል አድራጊውን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን በምስጋና መቀበላቸውን ይቀጥላሉ። ሊበጠስ በማይችል አንድነትም በዚህ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ዘመን ውስጥ ለንጉሣዊ አገዛዙ በታማኝነት ይገዛሉ።— ማቴዎስ 24:3
8. (ሀ) ድል አድራጊውን ንጉሥ ሳይቀበሉ የቀሩት እነማን ናቸው? (ለ) እነዚህስ ወደየትና ወደምን እየተጓዙ ናቸው?
8 የሚያሳፍረው ግን በአጠቃላይ ሕዝበ ክርስትና የሚባሉት ብሔራትና በእስራኤል ሪፓብሊክ ውስጥ ያለችው ኢየሩሳሌም በይሖዋ ስም የመጣውን ድል አድራጊ ንጉሥ አይቀበሉትም። ሆኖም በሌላ በኩል አንድ በመሆን እርሱ በስሙ ለመጣለት አምላክ ምሥክሮች ሆነው በመቅደሱ በደስታ የሚያገለግሉት አሉ። (ኢሳይያስ 43:10–12) እነርሱም የእስራኤልን ሪፖብሊክና በተባበሩት መንግሥታት ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉትንና አሁን “በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ” በመጓዝ ላይ የሚገኙትን ሌሎች ብሔራት እንዲያዩ መንፈሳዊ ዓይናቸው ተከፍቷል። (ራእይ 16:16) ሁሉን የሚችለው አምላክ ጦርነት ቀርቧል።
9. የምድራዊቷ ኢየሩሳሌም የወደፊት ሁኔታ ከአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው?
9 የምድራዊቷ ኢየሩሳሌም የወደፊት ሁኔታ ጨለማ ነው፤ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ተስፋ ግን ብሩኅ ነው። ውሎ አድሮ የፖለቲካዊው “አውሬ” “አሥር ቀንዶች” እና “አውሬው” ራሱ በጋለሞታው ሥርዓት ላይ ማለትም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ በጥላቻ ይነሡባታል። ሃይማኖታዊ ክብር በሚሰጣት በምድራዊት ኢየሩሳሌም ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ጥላቻ ኃይል በመጠቀም ይገልጻሉ፣ በእሳት እንደምትጠፋ ያህል ያጠፏታል። (ራእይ 17:16) ይሁን እንጂ ሰማያዊ የሆነችውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ፍጹም ሊነኳት አይችሉም።
10. ምድራዊት ኢየሩሳሌም በመንፈስ የተዋጁት ክርስቲያኖችና “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት ጓደኞቻቸው ከተከተሉት የተለየ መንገድ የተከተለችው እንዴት ነው?
10 የሰማይቱ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክፍል ለመሆን የሚጠባበቁት በመንፈስ የተዋጁ ክርስቲያኖች ቀሪዎች “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከሆኑት ከሌሎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመሆን ሙሽራውን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን በምስጋና መቀበላቸውን ይቀጥላሉ። በዚህ የታማኝነት እርምጃቸው ከፊተኛዋ ኢየሩሳሌም አንፃር ይቆማሉ። የእስራኤል ሪፖብሊክ ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ አሁን የአይሁዶች ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተከተሉትን መንገድ ትከተላለች። በሚያሳውር ሃይማኖታዊ ሽፋን ስር በመሆንዋም በሰማያዊው መንግሥት ለመግዛት መብትና ኃይል ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን አልቀበልም ማለቷን ትቀጥልበታለች።
11, 12. (ሀ) በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው የኢየሱስ ትንቢት ጉልህ ፍጻሜ የተከናወነው በተለይ በእነማን ነው? (ለ) እነርሱ በሥራ የሚደግፉት ድርጅት ዛሬ በእስራኤል ሪፓብሊክ ውስጥ ምን አለው?
11 የአሕዛብ ዘመናት በ1914 ካለቁበት ጊዜ ጀምሮ ‘የሰላሙ መስፍን’ ለሰው ዓይኖች በማይታይ ሁኔታ በሰማያት ውስጥ ሲገዛ መቆየቱ እውነት ነው። ዳሩ ግን ኢየሩሳሌም በአንደኛው የዓለም ጦርነት በእንግሊዝ ከተያዘችበትና በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ውሳኔ በእንግሊዝ ሞግዚትነት እንድትተዳደር ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በንጉሥ ዳዊት ልጅ እጅ የሚመራው የሰማያዊው መንግሥት የምሥራች ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደተነበየው:- “ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን . . . በዓለም ሁሉ” ሲሰበክ ቆይቷል።— ማቴዎስ 24:14
12 ይህ ደማቅ የትንቢቱ ፍጻሜ በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትንንሽ ጽሁፎች ማኅበር ሥር በይሖዋ ምሥክሮች ሲከናወን ቆይቷል። ይህ ማኅበር በእስራኤል ውስጥ ያሉትን የይሖዋ ምስክሮች የሥራ እንቅስቃሴ የሚመራ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ በቴልአቪቭ ውስጥ አለው። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በዚያ አገር ውስጥ የመንግሥቱን ወንጌል የሚሰብኩ ንቁ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉባቸው ጉባኤዎች አሉ።
13. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ምሥራች ስብከት ሙሉ በሙሉ ከተከናወነ በኋላ ምን ይመጣል? (ለ) በትንሣኤ ዳዊትን ለመቀበል ሌላ ምድራዊት ኢየሩሳሌም ታስፈልጋለችን?
13 የዚህ “የመንግሥት ወንጌል” ስብከት ሙሉ በሙሉ ከተከናወነ በኋላ በዚህ ዓለማዊ “የነገሮች ሥርዓት” ላይ “መጨረሻው” እንደሚመጣ ኢየሱስ ክርስቶስ ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ አሁን የምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ፍጻሜ መታየት ጀምሯል። ባሁኑ ጊዜ በእርሱ ንጉሣዊ ዝርያ በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥት ስር በሚከናወነው ትንሣኤ ከሞት ሲነሳ በአንድ ወቅት የኢየሩሳሌም ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን ለመቀበል በጥንቱ ቦታ ላይ ሌላ ኢየሩሳሌም መሥራት የሚያስፈልግ አይመስልም። (ዮሐንስ 5:28, 29) ሆኖም ዳዊት ይሖዋ አምላክን አስቀድሞ ያገለግልበት በነበረው አካባቢ ሳይነሳ አይቀርም።
የደስታ ጊዜ
14, 15. (ሀ) ሐዋርያው ዮሐንስ ክብራማዋን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምንና የሰውን ዘር ለመባረክ ከሰማይ መውረዷን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ጊዜያችን የደስታ ጊዜ የሚሆንልን ለምንድን ነው? አጽናፈ ዓለማዊ ደስታ ለማግኘት ምን አጋጣሚ ቀርቧል?
14 አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክብራማው አዲስ የነገሮች ሥርዓት ጋር ተያይዛለች። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ይላል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደፊት የለም። ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፣ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምጽ ከሰማይ:- እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል።” (ራእይ 21:1–3) በዚህ መንገድ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለሁሉም የሰው ዘር በረከት ትሆናለች።
15 በዚህ ምክንያት ጊዜያችን የደስታ ጊዜ ይሆናል። በዚህ ደስታ ላይ ተጨምሮ አጽናፈ ዓለማዊ ጥቅምና አጽናፈ ዓለማዊ ደስታ የሚገኝበት ጊዜ እየቀረበ ነው። ይህም ቁጥሯ የተሟላው የሙሽራዋ ክፍል ማለትም አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከንጉሡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምታደርገው ጋብቻ ነው። በራእይ 19:6–9 ላይ እንደተጻፈውም:- “እንደ ብዙ ሕዝብም ድምጽ፣ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምጽ እንደ ብርቱም ነጎድጓድ ድምጽ ያለ ድምጽ ሰማሁ። እንዲህ ሲል:- [ያህን አመስግኑ (አዓት)] ሁሉን የሚገዛ [ይሖዋ (አዓት)] አምላካችን ነግሦአልና። የበጉ (የኢየሱስ ክርስቶስ) ሰርግ ስለደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሴትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ። ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና። እርሱም:- ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁአን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ።”
16. (ሀ) ከበጉ ጋር በምታደርገው ሰማያዊ ጋብቻ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የማን እናት ትሆናለች? (ለ) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በረከት የምትሆነው ከምን ጋር ሙሉ በሙሉ በመስማማት ነው?
16 ይህ ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚደረግ የጋብቻ አንድነት በሰማይ ላይ ለምትገኘው ለምሳሌያዊቱ ኢየሩሳሌም ሊገለጽ የማይቻል ደስታ ያመጣላታል። በዚህም አንድነት አማካኝነት “ደስ የተሰኘች የልጆች እናት” ትሆናለች። (መዝሙር 113:9) አዎን፣ አፍቃሪው ባልዋ ከ19 መቶ ዘመናት በፊት ፍጹም ሰብዓዊ መስዋዕት በማቅረብ ለዋጃቸው ለሁሉም ሰዎች ለሕያዋን ሆነ ለሙታን ሰማያዊት እናት ትሆናለች። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ከገባው ቃል ኪዳን ጋር ሙሉ በሙሉ በመስማማት አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለሁሉም የምድር ቤተሰቦች በረከት ትሆናለች።
[በገጽ 96 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአዲሱ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሰውን ዘር በሙሉ ትባርካለች