ክርስቲያናዊ እምነት ይፈተናል
‘እምነት ለሁሉም አይደለም።’—2 ተሰሎንቄ 3:2
1. እውነተኛ እምነት ያላቸው ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ ታሪክ ያሳየው እንዴት ነው?
በታሪክ ዘመናት ሁሉ እውነተኛ እምነት የነበራቸው ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ነበሩ። “እውነተኛ” የሚለው ቅጽል መግባቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ተጨባጭ የሆነ ምንም መሠረት ወይም ምክንያት የሌለውን ነገር አሜን ብለው ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን እምነት ብለው የሚጠሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች በመኖራቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱ እምነት ብዙውን ጊዜ ከሐሰት አማልክት ወይም ሁሉን ቻይ ከሆነው ከይሖዋና ከተገለጠው ቃሉ ጋር ከማይስማሙ የአምልኮ ዓይነቶች ጋር የተዛመደ ነው። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እምነት ለሁሉም አይደለም’ ሲል ጽፏል።—2 ተሰሎንቄ 3:2
2. የራሳችንን እምነት መመርመራችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ይሁን እንጂ የጳውሎስ አነጋገር በዚያን ጊዜም ሆነ ዛሬ አንዳንዶች እንዲህ ያለው እምነት እንዳላቸው የሚያመለክት ነው። አብዛኞቹ የዚህ መጽሔት አንባቢዎች ከመለኮታዊ እውነት ትክክለኛ እውቀት ጋር የሚስማማው እንዲህ ዓይነቱ እምነት እንዲኖራቸውና እንዲጎለብትላቸው ይፈልጋሉ። (ዮሐንስ 18:37፤ ዕብራውያን 11:6) የአንተም ፍላጎት ከዚህ ጋር የሚስማማ ነውን? እንደዚያ ከሆነ እምነትህ እንደሚፈተን መገንዘብህና ለዚያም ዝግጁ ሆነህ መጠበቅህ እጅግ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
3, 4. ስለ እምነት ፈተናዎች ስናስብ በኢየሱስ መተማመን የሚኖርብን ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ ክርስቶስ የእምነታችን መሠረት መሆኑን አምነን መቀበል ይኖርብናል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የእምነታችን ፈጻሚ እንደሆነ ይናገራል። ስለ ኢየሱስ እንዲህ ለማለት የሚያስችለው የተናገረውና ያደረገው ነገር በተለይም ደግሞ ትንቢትን የፈጸመበት ሁኔታ ነው። የሰው ልጆች እውነተኛ እምነት ሊገነቡበት የሚያስችላቸውን መሠረት አጠናክሯል። (ዕብራውያን 12:2፤ ራእይ 1:1, 2) ይሁንና ኢየሱስ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ” መሆኑን እናነባለን። (ዕብራውያን 4:15) አዎን፣ የኢየሱስ እምነት ተፈትኗል። ይህ ነገር ሊያጽናናን እንጂ ተስፋ ሊያስቆርጠን ወይም ፍርሃት ሊያሳድርብን አይግባም።
4 ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ እስከመገደል ድረስ የተለያዩ ከባድ ፈተናዎችን በማሳለፉ ‘መታዘዝን ተምሯል።’ (ዕብራውያን 5:8) ሰዎች ማንኛውም ዓይነት ፈተና ቢደርስባቸው እንኳ እውነተኛ እምነት ይዘው ለመኖር እንደሚችሉ አረጋግጧል። ኢየሱስ “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ” በማለት ስለ ተከታዮቹ የተናገረውን ነገር ስናስብ ይህ ሐሳብ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። (ዮሐንስ 15:20) እንዲያውም ኢየሱስ “ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት በዘመናችን ስላሉት ተከታዮቹ ትንቢት ተናግሮ ነበር።—ማቴዎስ 24:9
5. ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙን ቅዱሳን ጽሑፎች የሚጠቁሙት እንዴት ነው?
5 በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ፍርድ ከአምላክ ቤት ጀምሯል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ በማለት ይተነብያሉ:- “ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?”—1 ጴጥሮስ 4:17, 18
እምነት ይፈተናል—ለምን?
6. የተፈተነ እምነት ይህ ነው የማይባል ዋጋ አለው የምንለው ለምንድን ነው?
6 ያልተፈተነ እምነት ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ፋይዳ የለውም ማለት ይቻላል። ጥንካሬው ገና ያልለየለት ነው። ገና ካልተመነዘረ የገንዘብ ቼክ ጋር ልታመሳስሉት ትችላላችሁ። ለሠራችሁት ሥራ፣ ላቀረባችሁት ዕቃ ወይም በስጦታ መልክ አንድ ቼክ አግኝታችሁ ይሆናል። ቼኩ ከውጭ ሲታይ ዋጋ ያለው ይመስላል። ይሁን እንጂ ዋጋ አለውን? በላዩ ላይ የሠፈረውን ገንዘብ ማስገኘቱና አለማስገኘቱ ታውቋልን? እምነታችንም በተመሳሳይ በውጭ ከሚታየው ወይም በአንደበታችን ከምንናገረው የበለጠ ጥራት ያለው መሆን ይኖርበታል። በእርግጥ ጥሩ መሠረትና ጥንካሬ ያለው መሆኑ እንዲረጋገጥ ከፈለግን መፈተን ይኖርበታል። እምነታችን በሚፈተንበት ጊዜ ጠንካራና ጥራት ያለው ሆኖ እናገኘው ይሆናል። በእምነታችን ላይ የሚደርሰው ፈተና እምነታችን በምን በኩል ገና መጥራት ወይም መጠንከር እንደሚያስፈልገው ሊያሳይ ይችላል።
7, 8. የእምነታችን ፈተናዎች ምንጫቸው ምንድን ነው?
7 አምላክ ስደትና ሌላ ዓይነት የእምነት ፈተናዎች እንዲደርሱብን ይፈቅዳል። እንዲህ እናነባለን:- “ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፣ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ታዲያ ለሚደርሱብን ፈተናዎች ተጠያቂው ማን ወይም ምንድን ነው? ሰይጣን፣ ዓለምና ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን ናቸው።
8 ሰይጣን በዚህ ዓለም እንዲሁም በዓለም አስተሳሰብና በመንገዶቹ ላይ ከባድ ተጽእኖ እንደሚያሳድር እናምን ይሆናል። (1 ዮሐንስ 5:19) እንዲሁም በክርስቲያኖች ላይ ስደት እንደሚያስነሳም እናውቅ ይሆናል። (ራእይ 12:17) ይሁን እንጂ የዚያኑ ያህል ሰይጣን ዓለማዊ ማታለያዎችን ከፊታችን በማስቀመጥ ወጥመዱ ውስጥ እንድንገባና ፍጹም ያልሆነውን የሥጋችንን ምኞት ተከትለን የአምላክን ትእዛዛት እንድንጥስ፣ በዚህም ምክንያት የይሖዋን ሞገስ እንድናጣ ለማድረግ እንደሚጥር እናምናለንን? እርግጥ፣ የሰይጣን ዘዴዎች እንደ አዲስ ሊያስደንቁን አይገባም። ኢየሱስን ለማሳት በሞከረበት ጊዜም በእነዚሁ ዘዴዎች ተጠቅሟል።—ማቴዎስ 4:1-11
9. ከእምነት ምሳሌዎች ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ በቃሉና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ልንመስላቸው የሚገቡንን ጥሩ የእምነት ምሳሌዎች ሰጥቶናል። ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ፣ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፣ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ” ሲል አጥብቆ መክሯል። (ፊልጵስዩስ 3:17) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች አንዱ እንደመሆኑ ብዙ ከባድ ፈተናዎች ቢደርሱበትም የእምነት ሥራዎችን በግንባር ቀደምትነት አከናውኗል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይም ተመሳሳይ የእምነት ምሳሌዎች የሚሆኑን አሉ። በዕብራውያን 13:7 ላይ የሚገኙት “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” የሚሉት የጳውሎስ ቃላት ያላቸው ኃይል ከተጻፉበት ጊዜ ያነሰ አይደለም።
10. የትኞቹ የቅርብ ጊዜያት ልዩ የእምነት ምሳሌዎች አሉን?
10 ዛሬ የቅቡዓን ቀሪዎች አካሄድ ምን ፍሬ እንዳስገኘ በምንመለከትበት ጊዜ ከላይ ያለው ምክር ልዩ የሆነ ኃይል ይኖረዋል። ምሳሌያቸውን ተመልክተን እምነታቸውን ልንኮርጅ እንችላለን። እምነታቸው በፈተናዎች አማካኝነት የተጣራ እውነተኛ እምነት ነው። በ1870ዎቹ ዓመታት ከነበረው አነስተኛ ጅምር ተነስቶ ዛሬ ዓለም አቀፍ የሆነ የክርስቲያናዊ ወንድማማቾች ማኅበር ሊገኝ ችሏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቅቡዓኑ ያሳዩት እምነትና ጽናት በአሁኑ ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ የተሠማሩ ከአምስት ሚልዮን ተኩል የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችን አፍርቷል። ዛሬ ያለው ቀናተኛ የሆኑ እውነተኛ አምላኪዎችን የያዘው ዓለም አቀፍ ጉባኤ የተፈተነ እምነት ሕያው ማረጋገጫ ነው።—ቲቶ 2:14
1914ን በተመለከተ የተነሣ የእምነት ፈተና
11. ለሲ ቲ ራስልና ለተባባሪዎቹ 1914 ልዩ ዓመት የነበረው እንዴት ነው?
11 ቀሪዎቹ የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ከበርካታ ዓመታት በፊት አንስተው 1914 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ዓመት እንደሚሆን ሲያውጁ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ይፈጸማሉ ብለው የጠበቋቸው አንዳንድ ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜ ገና ስለነበር ግምታቸው ሙሉ በሙሉ ትክክል አልነበረም። ለምሳሌ ያህል የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ሲ ቲ ራስልና ተባባሪዎቹ ሰፊ የስብከት ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተገንዝበው ነበር። “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” የሚለውን አንብበዋል። (ማቴዎስ 24:14) ይሁንና በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ የነበረው ቡድናቸው ይህን ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው?
12. ከራስል ተባባሪዎች አንዱ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?
12 ይህ ጉዳይ የራስል ተባባሪ የነበረውን ኤ ኤች ማክሚላንን እንዴት እንደነካው ተመልከት። በካናዳ የተወለደው ማክሚላን ዘ ፕላን ኦቭ ዚ ኤጅስ (1886) የተባለውን የራስል መጽሐፍ ሲያገኝ 20 ዓመት አልሞላውም ነበር። (ይህ መጽሐፍ ዘ ዲቫይን ፕላን ኦቭ ዚ ኤጅስ ተብሎም የሚጠራ ሲሆን በስፋት በተሰራጨውና ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ ተብለው ከሚጠሩት ጥራዞች ውስጥ የመጀመሪያው ጥራዝ ነው። ዘ ታይም ኢዝ አት ሃንድ [1889] የተባለው ሁለተኛው ጥራዝ “የአሕዛብ ዘመናት” የሚያበቁት በ1914 መሆኑን አመልክቶ ነበር። [ሉቃስ 21:24]) ማክሚላን መጽሐፉን ማንበብ በጀመረበት በዚያኑ ዕለት ምሽት “ይህ እውነት መሆን አለበት!” ሲል አሰበ። በ1900 የክረምት ወቅት በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከራስል ጋር ተገናኘ። ማክሚላን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተጠመቀና ኒው ዮርክ በሚገኘው የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ከወንድም ራስል ጋር መሥራት ጀመረ።
13. በማቴዎስ 24:14 ፍጻሜ ረገድ ማክሚላንና ሌሎችም የታያቸው ችግር ምን ነበር?
13 ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸው ባገኙት እውቀት መሠረት እነዚያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች 1914 በአምላክ ዓላማ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ዓመት እንደሚሆን አመልክተው ነበር። ይሁን እንጂ ማክሚላንና ሌሎችም በማቴዎስ 24:14 ላይ አስቀድሞ የተነገረው ለአሕዛብ የሚሰጠው ምሥክርነት በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ሊከናወን እንደሚችል ግራ ገብቷቸው ነበር። ማክሚላን ከጊዜ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ከወንድም ራስል ጋር ይህን ጉዳይ በተደጋጋሚ እያነሳን እንወያይ እንደነበር አስታውሳለሁ። እሱም ‘ወንድም፣ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት የሚበልጡ አይሁዶች በዚህ በኒው ዮርክ ይገኛሉ። በደብሊን ከሚገኙት የሚበልጡ አየርላንዳውያን እዚህ አሉ። እንዲሁም በሮም ካሉት የሚበልጡ ጣሊያናውያን ይገኛሉ። ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች ሰበክን ማለት ዓለምን በመልእክቱ አዳረስን ማለት ነው።’ ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ አእምሯችንን አላረካውም። ‘ፎቶ-ድራማ’ የተባለውን ፊልም ለማዘጋጀት የታሰበው ከዚህ በኋላ ነበር።”
14. ከ1914 በፊት ምን ልዩ ነገር ተከናውኗል?
14 “የፍጥረት ፎቶ-ድራማ” እንዴት ያለ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ክንውን ነበረ! ተንቀሳቃሽ ሥዕሎችንና የተለያዩ ባለ ቀለም የስላይድ ፊልሞችን ያካተተና በሸክላ ላይ ከተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችና ሙዚቃ ጋር ተቀነባብሮ የተቀረጸ ነበር። በዩ ኤስ ኤ በአርካንሳስ የተካሄደን አንድ የአውራጃ ስብሰባ አስመልክቶ መጠበቂያ ግንብ በ1913 እንዲህ ብሎ ነበር:- “የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ በአንድ ድምፅ ተወሰነ። . . . [ራስል] ለሦስት ዓመታት ያህል በዚህ እቅድ ላይ ሲሠራ እንደነበርና በመቶ የሚቆጠሩ የሚያማምሩ ሥዕሎች መዘጋጀታቸውን ከገለጸ በኋላ ያለ ምንም ጥርጥር እነዚህ ሥዕሎች የብዙ ሰዎችን ትኩረት የሚስቡ፣ ወንጌልን የሚያስፋፉና ሰዎች በአምላክ ላይ እምነት የሚያሳድሩ እንደሚሆኑ ተናግሮ ነበር።”
15. “ፎቶ-ድራማው” ምን ዓይነት ውጤቶች አስገኝቶ ነበር?
15 “ፎቶ-ድራማው” በጥር 1914 ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየ ጀምሮ ይህንኑ ዓላማ ሲያሳካ ቆይቷል። ቀጥሎ የቀረቡት ከ1914 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች የተገኙ ሪፖርቶች ናቸው:-
ሚያዝያ 1:- “አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሁለት ክፍሎችን ብቻ ከተመለከተ በኋላ ‘የፍጥረት ፎቶ-ድራማ ከተባለው ፊልም ያየሁት ከፊሉን ብቻ ቢሆንም በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያክል ከተማርኩት ይበልጥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተምሬበታለሁ’ ብሏል። አንድ አይሁዳዊ ‘ድራማውን ካየሁት በኋላ የተሻልኩ አይሁዳዊ ሆኛለሁ’ ብሏል። በርካታ የካቶሊክ ቀሳውስትና መነኮሳት ድራማውን የተመለከቱት ሲሆን ልባዊ አድናቆታቸውንም ገልጸዋል። . . . እስከ አሁን ድረስ የተዘጋጁት የድራማው ቅጂዎች አሥራ ሁለት ብቻ ናቸው። . . . ያም ሆኖ እንኳ ሠላሳ አንድ ከተማዎችን አዳርሰናል። . . . ከሠላሳ አምስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በየቀኑ ድራማውን እያዩ፣ እየሰሙ፣ እያደነቁ፣ እያሰቡበትና እየተባረኩበትም ነው።”
ሰኔ 15:- “ሥዕሎቹ እውነትን በበለጠ ቅንዓት እንዳስፋፋ እንዲሁም ለሰማያዊው አባታችንና ለውዱ ታላቅ ወንድማችን ለኢየሱስ ያለኝን ፍቅር እንዳሳድግ ረድተውኛል። የአምላክ የተትረፈረፈ በረከት በፍጥረት ፎቶ-ድራማ እና በዝግጅቱ በተሳተፉት ሁሉ ላይ እንዲሆን የዘወትር ጸሎቴ ነው። . . . በእርሱ አገልጋያችሁ የሆንሁ ኤፍ ደብልዩ ኖች።—አይወ”
ሐምሌ 15:- “በዚህ ከተማ ውስጥ ሥዕሎቹ ያሳደሩትን መልካም ተጽእኖ ለማየት በመቻላችን ተደስተናል። ለዓለም የሚሰጠው ይህ ምሥክርነት ጌታ ራሱ የመረጣቸው እንቁዎች መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ብዙ ሰዎች ለመሰብሰብም እንደሚረዳ እንተማመናለን። በፎቶ ድራማው አማካኝነት አሁን ከቡድኑ ጋር መተባበር የጀመሩ ብዙ ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን እናውቃለን። . . . በጌታ እህታችሁ የሆንኩ ኤማ ኤል ብሪከር።”
ኅዳር 15:- “ኪንግስዌይ በሚገኘው ዘ ለንደን ኦፔራ ሃውስ ውስጥ በመታየት ላይ ባለው የፍጥረት ፎቶ-ድራማ አማካኝነት እየተሰጠ ስላለው ግሩም ምሥክርነት መስማት እንደሚያስደስታችሁ እርግጠኞች ነን። እያንዳንዱ ዝርዝር የጌታ አመራር በሚያስደንቅ ሁኔታ የተንጸባረቀበት ሲሆን ወንድሞችም እጅግ ተደስተዋል። . . . አድማጮቻችን ከሁሉም የኑሮ መስክና ከሁሉም ዓይነት ሰዎች የተውጣጡ ናቸው። ብዙ ቀሳውስት መገኘታቸውንም ተመልክተናል። አንድ ገበዝ . . . እሱና ሚስቱ ድራማውን በድጋሚ ለማየት የሚያስችላቸውን ቲኬት ለማግኘት ጠይቀዋል። አንድ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መሪ ድራማውን ደጋግመው ከመመልከታቸውም በላይ . . . ድራማውን እንዲመለከቱ ብዙ ጓደኞቻቸውን አምጥተው ነበር። በተጨማሪም ሁለት ጳጳሳትና በርካታ የታወቁ ሰዎች ተገኝተው ነበር።”
ታኅሣሥ 1:- “ሚስቴና እኔ በአንተ መሣሪያነት ላገኘነው ታላቅና በዋጋ የማይተመን በረከት ሰማያዊውን አባታችንን እጅግ እናመሰግነዋለን። እውነትን ለማየትና ለመቀበል ያበቃን ውብ አድርገህ ያዘጋጀኸው ፎቶ-ድራማ ነበር። . . . የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባለው መጽሐፍህ ስድስቱም ጥራዞች አሉን። ትልቅ እርዳታ እያበረከቱልን ነው።”
በዚያን ጊዜ ለተነሡት ፈተናዎች የተሰጠው ምላሽ
16. ቅቡዓኑ 1914ን በተመለከተ ምን የእምነት ፈተና ገጥሟቸው ነበር?
16 ይሁን እንጂ እነዚህ ቅንና ለአምላክ ያደሩ ክርስቲያኖች እንደጠበቁት በ1914 ወደ ጌታ ሳይሄዱ ሲቀሩ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? እነዚያ ቅቡዓን እጅግ ፈታኝ የሆነ ጊዜ ገጥሟቸው ነበር። የኅዳር 1, 1914 መጠበቂያ ግንብ “በፈተና ወቅት ላይ እንዳለን እናስታውስ” ብሎ ነበር። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (የእንግሊዝኛ) (1993) የተባለው መጽሐፍ ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር “በእርግጥም ከ1914 እስከ 1918 የነበሩት ዓመታት ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ‘የፈተና ወቅት’ ሆነውባቸው ነበር” ብሏል። ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ታላቅ ሥራ ለማከናወን እምነታቸው እንዲጣራና አስተሳሰባቸው እንዲስተካከል ይፈቅዱ ይሆን?
17. ታማኞቹ ቅቡዓን 1914 ካለፈ በኋላ በምድር ላይ በመቆየታቸው ምን ተሰማቸው?
17 የመስከረም 1, 1916 መጠበቂያ ግንብ እንደሚከተለው ብሏል:- “ቤተ ክርስቲያንን [ቅቡዓኑን] የመሰብሰቡ የመከር ሥራ የአሕዛብ ዘመን ከመፈጸሙ በፊት ይጠናቀቃል ብለን ገምተን ነበር፤ ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህን የሚያመለክት ነገር አይገኝም። . . . የመከሩ ሥራ በመቀጠሉ እንቆጫለንን? . . . ውድ ወንድሞች፣ በአሁኑ ጊዜ ለአምላክ አመስጋኝ መሆን፣ አምላክ እንድናስተውለውና በእርሱም ተለይተን እንድንታወቅ መብት ለሰጠን ለእውነት ያለንን አድናቆት መጨመር፣ እንዲሁም ይህንን እውነት ሌሎች እንዲያውቁ በመርዳት ረገድ ያለንን ቅንዓት ማሳደግ ይኖርብናል።” እምነታቸው ፈተና ቢደርስበትም ፈተናውን በመጋፈጥ በተሳካ ሁኔታ ተወጥተውታል። እኛ ክርስቲያኖች ግን የእምነት ፈተናዎች ብዙና የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ልንገነዘብ ይገባናል።
18, 19. ወንድም ራስል ከሞተ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ምን ሌሎች የእምነት ፈተናዎች ገጥሟቸዋል?
18 ለምሳሌ ያህል ወንድም ቻርልስ ቲ ራስል ከሞተ በኋላ ወዲያው ቀሪዎቹ ሌላ ዓይነት ፈተና ገጥሟቸዋል። ታማኝነታቸውንና እምነታቸውን የሚመዝን ፈተና ነበር። በማቴዎስ 24:45 ላይ የተጠቀሰው ‘ታማኙ ባሪያ’ ማን ነው? አንዳንዶች ወንድም ራስል ራሱ ነው ብለው ያምኑ ስለነበረ ከአዲሱ ድርጅታዊ መዋቅር ጋር ተባብሮ መሥራት አቃታቸው። ታማኙ ባሪያ ወንድም ራስል ከሆነ እርሱ ከሞተ በኋላ ወንድሞች ምን ሊያደርጉ ነው? አዲስ የሚሾም አንድ ግለሰብ ሊከተሉ ነው ወይስ ይሖዋ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው አንድን ግለሰብ ሳይሆን መላውን የክርስቲያኖች ቡድን ወይም የባሪያውን ቡድን መሆኑን የሚገነዘቡበት ጊዜ ደርሶ ነበር?
19 በ1918 ደግሞ ዓለማዊ ባለሥልጣኖች በሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ተገፋፍተው በይሖዋ ድርጅት ላይ ‘በሕግ ሳቢያ ተንኮል በጠነሰሱ’ ጊዜ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ተጨማሪ ፈተና መጣ። (መዝሙር 94:20) በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ላይ በሰሜን አሜሪካም ሆነ በአውሮፓ የስደት ዘመቻ መካሄድ ጀመረ። ግንቦት 7, 1918 የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል ፍርድ ቤት በጄ ኤፍ ራዘርፎርድ፣ በኤ ኤች ማክሚላንና በሌሎች የቅርብ ባልደረቦቹ ላይ የእስራት ማዘዣ ባወጣ ጊዜ በቀሳውስት አራጋቢነት ይካሄድ የነበረው የስደት እሳት ይበልጥ ተፋፋመ። እነዚህ ወንድሞች በመንግሥት ላይ ዓመፅ ለማነሳሳት ሞክረዋል ተብለው የተከሰሱ ሲሆን ምንም ዓይነት ወንጀል ያልሠሩ መሆናቸውን በመግለጽ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
20, 21. በሚልክያስ 3:1-3 በተተነበየው መሠረት በቅቡዓኑ ላይ ምን ሥራ ተከናውኗል?
20 በጊዜው አልተገነዘቡትም እንጂ በሚልክያስ 3:1-3 በተገለጸው መሠረት የማጥራት ሥራ በመካሄድ ላይ ነበር:- “ነገር ግን [የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ] እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው? እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፣ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፣ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።”
21 አንደኛው የዓለም ጦርነት ወደ ፍጻሜው በተቃረበበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በዓለማዊ የውትድርና ጉዳዮች ረገድ ቁርጥ ያለ የገለልተኝነት አቋም መያዝ አለመያዛቸውን የሚመለከት ሌላ የእምነት ፈተና አጋጠማቸው። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) አንዳንዶች ቁርጥ ያለ አቋም አልነበራቸውም። ስለዚህ ይሖዋ በ1918 አነስተኛ የነበረውን የአምላኪዎች ቡድን ከዚህ ዓለም እድፍ ለማንጻት ‘የቃል ኪዳኑን መልእክተኛ’ ክርስቶስ ኢየሱስን ወደ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ዝግጅት ላከ። እነዚያ እውነተኛ እምነት ለማሳየት ቆርጠው የተነሡት ከተሞክሮ በመማር በቅንዓት መስበካቸውን በመቀጠል ወደፊት ገፍተዋል።
22. የእምነት ፈተናዎችን በተመለከተ ገና ልንመረምራቸው የሚገቡ ምን ነገሮች አሉ?
22 እስከ አሁን ስንመለከተው የነበረው ነገር እንዲሁ ያለፈ ታሪክ ብቻ አይደለም። በዛሬው ጊዜ ከሚገኘው ከይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ መንፈሳዊ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ርዕስ በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚደርሱትን አንዳንድ የእምነት ፈተናዎች በመመልከት እንዴት አድርገን በተሳካ ሁኔታ ልንወጣቸው እንደምንችል እንመርምር።
ታስታውሳለህ?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች እምነታቸው እንደሚፈተን መጠበቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
◻ ከ1914 በፊት የአምላክን መልእክት ለማሰራጨት ምን ዓይነት ጥረቶች ተደርገዋል?
◻ “ፎቶ-ድራማ” ምንድን ነበር? ምን ውጤትስ አስገኝቷል?
◻ ከ1914-18 ባለው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ነገሮች ቅቡዓኑን ለመፈተን ያገለገሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ በብዙ አገሮች የሚገኙ ሰዎች “ሚሌኒያል ዶውን” በተባለው ተከታታይ መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ነበር። ይህ መጽሐፍ በኋላ “የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት” ተብሏል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲ ቲ ራስል እንደ መግቢያ ሆኖ እንዲያገለግል በማሰብ ለቅጂ ያዘጋጀውን የሚከተለውን መልእክት ያዘለ ደብዳቤ:- “‘የፍጥረት ፎቶ-ድራማ’ የቀረበው በዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ነው። ዓላማውም በሃይማኖትና በሳይንስ የጋራ መስክ ሕዝቡን ለማስተማርና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስረዳት ነው”
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ድሜትሪየስ ፓፓጆርጅ “የፍጥረት ፎቶ-ድራማ”ን እያሳየ ወደ ብዙ ቦታዎች ተጉዟል። ከጊዜ በኋላ በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት ታስሮ ነበር