“መንፈስ . . . የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል”
“መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል።”—1 ቆሮ. 2:10
1. በ1 ቆሮንቶስ 2:10 ላይ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የሚጫወተውን የትኛውን ሚና ጎላ አድርጎ ገልጿል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?
የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ለሚያከናውናቸው ተግባሮች ምንኛ አመስጋኞች ነን! ቅዱሳን መጻሕፍት መንፈስ ቅዱስ ረዳትና ስጦታ እንደሆነ እንዲሁም እንደሚመሠክርና ስለ እኛ እንደሚማልድ ይናገራሉ። (ዮሐ. 14:16፤ ሥራ 2:38፤ ሮም 8:16, 26, 27) ሐዋርያው ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ ሌላም ጠቃሚ ሚና እንደሚጫወት ሲያጎላ “መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል” ብሏል። (1 ቆሮ. 2:10) በእርግጥም ይሖዋ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለመግለጥ በመንፈስ ቅዱሱ ይጠቀማል። እንዲህ ያለ እርዳታ ባናገኝ ኖሮ የይሖዋን ዓላማዎች ምን ያህል መረዳት እንችል ነበር? (1 ቆሮንቶስ 2:9-12ን አንብብ።) ይሁንና አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሳሉ፦ ‘መንፈስ የአምላክን ጥልቅ ነገሮች የሚመረምረው’ እንዴት ነው? ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እነዚህን ነገሮች የገለጠው በማን በኩል ነው? በዘመናችንስ መንፈስ እነዚህን ጥልቅ ነገሮች የሚመረምረው እንዴትና በማን በኩል ነው?
2. መንፈስ ቅዱስ ምን ሁለት ተግባሮች ያከናውናል?
2 ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ የሚያከናውናቸውን ሁለት ተግባሮች ገልጿል። ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለሐዋርያቱ “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 14:26) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው መንፈስ ቅዱስ አስተማሪና አስታዋሽ የመሆን ሚና ይጫወታል። አስተማሪ የሚሆነው ክርስቲያኖች ከዚህ ቀደም የማያውቋቸውን ነገሮች እንዲረዱ ስለሚያስችላቸው ነው። አስታዋሽ የሚሆነው ደግሞ ቀደም ሲል የተብራራን ነገር እንዲያስታውሱና በትክክል በሥራ ላይ እንዲያውሉት ስለሚረዳቸው ነው።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን
3. ኢየሱስ የተናገረው ነገር ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ ደረጃ በደረጃ እንደሚገለጡ የሚጠቁመው እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙ አዳዲስ እውነቶችን አስተምሯቸው ነበር። ያም ሆኖ ሊማሩት የሚገባ በርካታ ነገር ይቀር ነበር። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። ይሁን እንጂ እሱ ይኸውም የእውነት መንፈስ ሲመጣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል።” (ዮሐ. 16:12, 13) ኢየሱስ ይህን ሲል መንፈስ ቅዱስ፣ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን ደረጃ በደረጃ እንደሚገልጥ መናገሩ ነበር።
4. በ33 በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የአስተማሪነትና የአስታዋሽነት ሚናውን የተጫወተው እንዴት ነው?
4 “የእውነት መንፈስ” የመጣው በ33 በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም አንድ ላይ ተሰብስበው በነበሩ 120 ያህል ክርስቲያኖች ላይ በወረደበት ወቅት ነው። (ሥራ 1:4, 5, 15፤ 2:1-4) በወቅቱ የታየውና የተሰማው ነገር ለዚህ ማስረጃ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በልዩ ልዩ ልሳኖች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ተናገሩ። (ሥራ 2:5-11) አሁን አንድ አዲስ ነገር የሚገለጥበት ወቅት ነው። ነቢዩ ኢዩኤል፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚፈስስ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢዩ. 2:28-32) በአካባቢው የነበሩት ሰዎች ፈጽሞ ባልጠበቁት መንገድ ይህ ትንቢት ሲፈጸም ተመለከቱ፤ ሐዋርያው ጴጥሮስም ስለ ትንቢቱ አፈጻጸም አብራራላቸው። (የሐዋርያት ሥራ 2:14-18ን አንብብ።) ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ መሞላታቸው ኢዩኤል ከዘመናት በፊት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ጴጥሮስ እንዲገነዘብ በማድረግ መንፈስ ቅዱስ የአስተማሪነት ሚናውን ተጫውቷል። ጴጥሮስ፣ የኢዩኤልን ትንቢት ብቻ ሳይሆን የዳዊትን ሁለት መዝሙሮች ጭምር መጥቀሱ መንፈስ ቅዱስ የአስታዋሽነት ሚናም እንደተጫወተ ያሳያል። (መዝ. 16:8-11፤ 110:1፤ ሥራ 2:25-28, 34, 35) በቦታው የተሰበሰቡት ሰዎች ያዩትና የሰሙት በእርግጥም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ነበር።
5, 6. (ሀ) በ33 ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በኋላ አዲሱን ቃል ኪዳን በተመለከተ መልስ የሚያሻቸው ምን ጥያቄዎች ተነሱ? (ለ) እነዚህን ጉዳዮች ለውይይት ያቀረቡት እነማን ነበሩ? ውሳኔ ላይ የተደረሰውስ እንዴት ነበር?
5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች ግልጽ ያልሆኑላቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩ። ለምሳሌ በጴንጤቆስጤ ዕለት በሥራ ላይ መዋል ከጀመረው ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ። በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚታቀፉት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ብቻ ናቸው? አሕዛብም በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ሊታቀፉና በመንፈስ ቅዱስ ሊቀቡ ይችላሉ? (ሥራ 10:45) አሕዛብ የሆኑ ወንዶች መጀመሪያ መገረዝና ለሙሴ ሕግ መገዛት ያስፈልጋቸዋል? (ሥራ 15:1, 5) እነዚህ በጣም ወሳኝ ጥያቄዎች ነበሩ። እነዚህን ጥልቅ ነገሮች ለመመርመር የይሖዋ መንፈስ ያስፈልግ ነበር። ይሁንና ይህ መንፈስ የሚሠራው በማን በኩል ነው?
6 እያንዳንዱን ጉዳይ ለውይይት እንዲቀርብ ያደረጉት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ነበሩ። ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና በርናባስ የበላይ አካሉ ባደረገው ስብሰባ ላይ በመገኘት ይሖዋ ላልተገረዙ አሕዛብ ያደረገላቸውን ነገሮች ተረኩ። (ሥራ 15:7-12) የበላይ አካሉ ይህንን ማስረጃ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ ሐሳቦች ጋር ካገናዘበ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ። ከዚያም ስለ ውሳኔው ለጉባኤዎች በደብዳቤ አሳወቀ።—የሐዋርያት ሥራ 15:25-30ን እና ሥራ 16:4, 5ን አንብብ፤ ኤፌ. 3:5, 6
7. ጥልቅ እውነቶች የተገለጡት በምን መንገድ ነበር?
7 ዮሐንስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ጳውሎስ በመንፈስ ተመርተው የጻፏቸው ተጨማሪ ደብዳቤዎች ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ግልጽ አደረጉ። ሆኖም የክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት ተጽፈው ካበቁ በኋላ የመተንበይ ስጦታና በተአምር የሚገለጥ እውቀት ቀርቷል። (1 ቆሮ. 13:8) ታዲያ መንፈስ አስተማሪና አስታዋሽ በመሆን የሚጫወተው ሚና ይቀጥል ይሆን? ክርስቲያኖች የአምላክን ጥልቅ ነገሮች መመርመር እንዲችሉ መርዳቱን ይቀጥል ይሆን? ይህን ማድረጉን እንደሚቀጥል የሚያሳዩ ትንቢቶች አሉ።
በፍጻሜው ዘመን
8, 9. በፍጻሜው ዘመን መንፈሳዊ ጥበብ በማግኘት “ደምቀው” የሚያበሩት እነማን ናቸው?
8 የፍጻሜውን ዘመን አስመልክቶ አንድ መልአክ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሯል፦ “ጥበበኞች እንደ ሰማይ ጸዳል፣ ብዙዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። . . . ዕውቀትም ይበዛል።” (ዳን. 12:3, 4) ጥበበኞች የተባሉትና እንደሚደምቁ የተነገረላቸው እነማን ናቸው? ኢየሱስ የስንዴውንና የእንክርዳዱን ምሳሌ በተናገረበት ወቅት ፍንጭ ሰጥቷል። ስለዚህ “ሥርዓት መደምደሚያ” ሲናገር “በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ” ብሏል። (ማቴ. 13:39, 43) ኢየሱስ የምሳሌውን ትርጉም ባብራራበት ወቅት “ጻድቃን” የተባሉት “የመንግሥቱ ልጆች” ይኸውም ቅቡዓን ክርስቲያኖች መሆናቸውን ግልጽ አድርጓል።—ማቴ. 13:38
9 ታዲያ “ደምቀው” የሚያበሩት ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአጠቃላይ በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስለሚካፈሉ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ አንዳቸው ሌላውን ስለሚያንጹ “ደምቀው” የሚያበሩት ሁሉም ቅቡዓን ናቸው ሊባል ይችላል። ቅቡዓኑ በዚህ ረገድ ለሌሎች ክርስቲያኖች ምሳሌ ይሆናሉ። (ዘካ. 8:23) ከዚህም በተጨማሪ ጥልቅ ነገሮች የሚገለጡት በፍጻሜው ዘመን እንደሆነ ተነግሮ ነበር። ዳንኤል የተናገረው ትንቢት እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ “የታተመ” ነበር። (ዳን. 12:9) ታዲያ መንፈስ እነዚህን ጥልቅ ነገሮች የሚመረምረው እንዴትና በማን በኩል ነው?
10. (ሀ) በመጨረሻው ዘመን መንፈስ ጥልቅ እውነቶችን የሚገልጠው በማን በኩል ነው? (ለ) የይሖዋን ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የተመለከቱ እውነቶች የተብራሩት እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
10 በዘመናችን አንድ መንፈሳዊ ጉዳይ የሚብራራበት ጊዜ ሲደርስ “ታማኝና ልባም [ባሪያን]” በመወከል በኃላፊነት ቦታ ላይ ሆነው በዋናው መሥሪያ ቤት የሚሠሩት ወንድሞች ቀደም ሲል ያልተረዷቸውን ጥልቅ የሆኑ እውነቶች እንዲያስተውሉ መንፈስ ቅዱስ ይረዳቸዋል። (ማቴ. 24:45፤ 1 ቆሮ. 2:13) የበላይ አካሉ አባላት ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በሚኖሩበት ጊዜ በአንድ ላይ ሆነው ጉዳዩን በመመርመር ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። (ሥራ 15:6) ከዚያም ከትምህርቱ ሁሉም ሰው ጥቅም እንዲያገኝ ሲባል ማስተካከያ የተደረገበት ማብራሪያ አስፈላጊ ከሆነ በጽሑፍ ታትሞ እንዲወጣ ያደርጋሉ። (ማቴ. 10:27) ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ያስፈልጉ ይሆናል፤ ባሪያው ይህንንም በሐቀኝነት ያቀርበዋል።—“መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምን ትርጉም እንዳለው መንፈስ የገለጠው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
መንፈስ በዘመናችን ከሚጫወተው ሚና ጥቅም ማግኘት
11. በዛሬው ጊዜ ያሉ ሁሉም ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ የአምላክን ጥልቅ ነገሮች በመግለጥ ረገድ ከሚጫወተው ሚና መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው?
11 ሁሉም ታማኝ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ የአምላክን ጥልቅ ነገሮች በመግለጥ ረገድ ከሚጫወተው ሚና ጥቅም ያገኛሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም መንፈስ ቅዱስ እንድንረዳው ያደረገንን ትምህርት እናጠናለን እንዲሁም በሌላ ጊዜ አስታውሰን ተግባራዊ እናደርገዋለን። (ሉቃስ 12:11, 12) በጽሑፍ ታትመው የሚወጡትን ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶች ለመረዳት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መማር አያስፈልገንም። (ሥራ 4:13) የአምላክን ጥልቅ ነገሮች በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ምን ማድረግ እንችላለን? ከዚህ በታች አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።
12. መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ ያለብን መቼ ነው?
12 መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልይ። መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለማጥናት በምንዘጋጅበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን በቅድሚያ በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል። ብቻችንን ብንሆን ወይም የምናጠናው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው። እንዲህ ያለው በትሕትና የቀረበ ልመና በሰማይ ያለውን አባታችንን ልብ ደስ ያሰኛል። ኢየሱስ እንደገለጸው ይሖዋ ከልብ የምናቀርበውን ልመና በመስማት መንፈሱን በነፃ ይሰጠናል።—ሉቃስ 11:13
13, 14. የአምላክን ጥልቅ ነገሮች በመረዳት ረገድ ለስብሰባዎች የምናደርገው ዝግጅት ምን ሚና አለው?
13 ለስብሰባዎች ተዘጋጅ። በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት “በተገቢው ጊዜ” ምግብ እናገኛለን። ‘ባሪያው’ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማቅረብ እንዲሁም የጥናትና የስብሰባ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። ባሪያው “መላው የወንድማማች ማኅበር” አንዳንድ ትምህርቶችን እንዲያጠና የሚጠይቀው ጉዳዩን በደንብ ስላሰበበት ነው። (1 ጴጥ. 2:17፤ ቆላ. 4:16፤ ይሁዳ 3) የቀረበልንን ሐሳብ በተግባር ለማዋል የተቻለንን ሁሉ ስናደርግ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንተባበራለን።—ራእይ 2:29
14 ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ስንዘጋጅ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥተን መመልከታችንና እያንዳንዱ ጥቅስ ከቀረበው ትምህርት ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ለማስተዋል መሞከራችን ጠቃሚ ነው። ይህን ልማድ ማድረጋችን በጊዜ ሂደት ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንድናዳብር ይረዳናል። (ሥራ 17:11, 12) ጥቅሱን አውጥተን መመልከታችን ሐሳቡ በአእምሯችን ውስጥ እንዲቀረጽ የሚያደርግ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በሌላ ጊዜ ልናስታውሰው እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ጥቅሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝበትን ቦታ መመልከታችን የጥቅሱ አቀማመጥ በጭንቅላታችን ውስጥ እንዲቀረጽ ስለሚያደርግ በሌላ ጊዜ ስንፈልገው ቦታውን በቀላሉ እንድናገኘው ሊረዳን ይችላል።
15. አዳዲስ ጽሑፎችን ተከታትለን ማንበብ ያለብን ለምንድን ነው? አንተ ይህን የምታደርገው እንዴት ነው?
15 አዳዲስ የሚወጡ ጽሑፎችን ተከታትለህ አንብብ። ከሚወጡት ጽሑፎች አንዳንዶቹ በስብሰባ ላይ ባይጠኑም የተዘጋጁት ለእኛው ጥቅም ነው። ለሕዝብ የምናሰራጫቸው መጽሔቶችም እንኳ የሚዘጋጁት እኛንም ታሳቢ በማድረግ ነው። በውጥረት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ በአብዛኛው አንድን ሰው ወይም አንድን ነገር ስንጠብቅ ጊዜ ማለፉ አይቀርም። ያላነበብነውን ወይም ያልጨረስነውን ጽሑፍ ይዘን ከሄድን አጋጣሚውን በመጠቀም የተወሰነ ነገር ማንበብ እንችላለን። አንዳንዶች በእግራቸው ወይም በመኪና በሚሄዱበት ጊዜ በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎቻችንን በማዳመጥ አዳዲስ የሚወጡት ትምህርቶች እንዳያመልጧቸው ያደርጋሉ። በጥንቃቄ ምርምር ተደርጎባቸውና አብዛኛው ሰው በቀላሉ እንዲረዳቸው ታስበው የሚዘጋጁት ሁሉም ጽሑፎች እውቀታችንን የሚያሰፉልን ከመሆኑም በላይ ለእውነት ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋሉ።—ዕን. 2:2
16. በአእምሯችን ውስጥ የተፈጠሩትን ጥያቄዎች በማስታወሻችን ላይ በመጻፍ ምርምር ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኛል?
16 አሰላስል። መጽሐፍ ቅዱስን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ስታነብ ጊዜ ወስደህ ስለምታነበው ነገር አስብ። የምታነበው ነገር እንዴት እንደሚያያዝ በቁም ነገር ስታስብ በአእምሮህ ውስጥ ጥያቄዎች መፈጠራቸው አይቀርም። እነዚህን ጥያቄዎች በማስታወሻህ ላይ በመጻፍ በሌላ ጊዜ ምርምር ልታደርግባቸው ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ ጥልቀት ያለው ጥናት የምናደርገው ጥያቄ በፈጠሩብን ነገሮች ላይ ምርምር ስናደርግ ነው። በዚህ መንገድ ያከማቸነው እውቀት በሚያስፈልገን ጊዜ ልንጠቀምበት የምንችል የከበረ ሀብት ይሆንልናል።—ማቴ. 13:52
17. የቤተሰብ ወይም የግል ጥናት ፕሮግራምህ ምን ይመስላል?
17 ለቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም አውጣ። የበላይ አካሉ በሳምንት አንድ ቀን ምሽት ላይ ወይም በሌላ በማንኛውም ሰዓት ጊዜ በመመደብ የግል ወይም የቤተሰብ ጥናት እንድናደርግ ሁላችንንም አበረታቶናል። በስብሰባ ፕሮግራም ላይ ማስተካከያ መደረጉ ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልናል። በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ምን እያጠናችሁ ነው? አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሲሆን በዚህ ወቅት በአእምሯቸው ውስጥ ጥያቄ በፈጠሩባቸው ጥቅሶች ላይ ምርምር ያደርጋሉ፤ ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ አጠር ያለ ማስታወሻ ይጽፋሉ። ብዙ ቤተሰቦች ያጠኑትን ትምህርት በቤተሰባቸው ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ይወያያሉ። አንዳንድ የቤተሰብ ራሶች፣ ቤተሰባቸው ያስፈልገዋል ብለው ባሰቡት ትምህርት አሊያም ቤተሰቡ ባቀረበው ጥያቄ ወይም ርዕስ ጉዳይ ላይ ይወያዩበታል። አንተም በቤተሰብ አምልኮ ላይ ልታጠኗቸው የምትችሏቸውን ሌሎች ርዕሶች ማግኘትህ አይቀርም።a
18. በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ እውነቶች ከማጥናት ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?
18 ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ ረዳት እንደሚሆንልን መናገሩን አስታውስ። ስለዚህ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ እውነቶች ከማጥናት ወደኋላ ማለት የለብንም። እነዚህ እውነቶች ውድ የሆነው ‘ስለ አምላክ የሚገልጸው እውቀት’ ክፍል ሲሆኑ ይህን እውቀት እንድንፈልገው ተጋብዘናል። (ምሳሌ 2:1-5ን አንብብ።) እነዚህ እውነቶች “አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጃቸውን ነገሮች” በተመለከተ ብዙ የሚገልጹልን ነገር አለ። ስለ ይሖዋ ቃል ይበልጥ ለመማር ጥረት የምናደርግ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል፤ ምክንያቱም “መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል።”—1 ቆሮ. 2:9, 10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በተጨማሪም የጥቅምት 2008 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 4ን ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• መንፈስ “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” ለመመርመር የሚረዳን በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ነው?
• በመጀመሪያው መቶ ዘመን መንፈስ ቅዱስ ጥልቅ እውነቶችን የገለጠው በማን በኩል ነበር?
• መንፈስ ቅዱስ በዘመናችን መንፈሳዊ ጉዳዮችን ግልጽ የሚያደርገው እንዴት ነው?
• መንፈስ ከሚጫወተው ሚና ለመጠቀም ምን ማድረግ ትችላለህ?
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምን ትርጉም እንዳለው መንፈስ የገለጠው እንዴት ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከተገለጡት ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ አንዱ የመገናኛው ድንኳንና በኋላ የተሠሩት ቤተ መቅደሶች እጅግ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ እውነታን የሚያመለክቱ መሆናቸው ነው። ጳውሎስ ይህንን እውነታ “እውነተኛው ድንኳን” በማለት የጠራው ሲሆን ይህ ድንኳን “በሰው ሳይሆን በይሖዋ የተተከለ” እንደሆነ ገልጿል። (ዕብ. 8:2) ይህ ድንኳን ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነው፤ ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕትና የክህነት አገልግሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችል ዝግጅት ነው።
“እውነተኛው ድንኳን” ወደ ሕልውና የመጣው በ29 ዓ.ም. ኢየሱስ በተጠመቀበትና ፍጹም መሥዋዕት የሚሆነው እሱ መሆኑን ይሖዋ በተቀበለበት ወቅት ነው። (ዕብ. 10:5-10) ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት የመሥዋዕቱን ዋጋ “በአምላክ ፊት” አቅርቧል።—ዕብ. 9:11, 12, 24
በሌላ ቦታ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “የይሖዋ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን በማደግ ላይ” እንዳሉ ጽፏል። (ኤፌ. 2:20-22) ይህ ቤተ መቅደስ ጳውሎስ በኋላ ላይ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከገለጸው “እውነተኛው ድንኳን” ጋር አንድ ነው? የይሖዋ አገልጋዮች ለበርካታ ዓመታት ሁለቱ ነገሮች አንድ እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማይ የሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ “ድንጋዮች” ለመሆን በምድር ላይ እየተዘጋጁ ያሉ ይመስል ነበር።—1 ጴጥ. 2:5
በ1971 መገባደጃ አካባቢ ግን በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉት የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት ጳውሎስ በኤፌሶን ላይ የገለጸው ቤተ መቅደስ የይሖዋን ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሊያመለክት እንደማይችል ማስተዋል ጀመሩ። “እውነተኛው ድንኳን” የሚዋቀረው ትንሣኤ ባገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሆነ ይህ “ድንኳን” ወደ ሕልውና የሚመጣው የቅቡዓኑ ትንሣኤ ከጀመረ በኋላ ማለትም ‘ጌታ በሚገኝበት ጊዜ’ ሊሆን ነው ማለት ነው። (1 ተሰ. 4:15-17) ይሁንና ጳውሎስ የመገናኛውን ድንኳን አስመልክቶ ሲጽፍ “ይህ ድንኳን አስቀድሞ ተወስኖ ለነበረው አሁን ላለው ዘመን ምሳሌ” መሆኑን ገልጾ ነበር።—ዕብ. 9:9
እነዚህና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በጥንቃቄ ሲወዳደሩ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ በመገንባት ላይ አለመሆኑ እንዲሁም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የቤተ መቅደሱ ክፍል ለመሆን በምድር ላይ እየተዘጋጁ ያሉ “ድንጋዮች” እንዳልሆኑ ግልጽ ሆነ። ከዚህ በተቃራኒ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ አደባባይና ቅድስት ውስጥ እያገለገሉ ሲሆን ለአምላክ በየዕለቱ “የምስጋና መሥዋዕት” ያቀርባሉ።—ዕብ. 13:15
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ምን ማድረግ እንችላለን?