-
‘እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ማግኘት’መጠበቂያ ግንብ—2005 | የካቲት 1
-
-
‘እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ማግኘት’
“መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት የሚጋደሉ ብዙዎች ናቸው፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ደግሞ ወራሽ ይሆናሉ።”—ማቴዎስ 11:12 Nw
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መንግሥተ ሰማይ ከተናገራቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ ምን ያልተለመደ ባሕርይ ጠቅሷል? (ለ) ኢየሱስ እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ በተናገረው ምሳሌ ላይ ምን ብሏል?
እጅግ ከፍተኛ ግምት የምትሰጠው ከመሆኑ የተነሳ አለኝ የምትለውን ነገር ሁሉ ሰጥተህ በእጅህ ልታስገባው የምትፈልገው ነገር አለ? ምንም እንኳ ሰዎች ገንዘብ፣ ታዋቂነት፣ ሥልጣን ወይም ማዕረግ ለማግኘት ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን ሲናገሩ መስማት የተለመደ ቢሆንም በጣም የሚፈልገውን ነገር አግኝቶ የራሱ ለማድረግ ሲል ያለውን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ግን እምብዛም አይገኝም። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አምላክ መንግሥት ከተናገራቸው አመራማሪ የሆኑ ምሳሌዎች መካከል በአንዱ ላይ ይህን ያልተለመደ ሆኖም የሚደነቅ ባሕርይ ጠቅሷል።
2 ምሳሌው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ብቻ የነገራቸው እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ የሚናገረው ታሪክ ነው። ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማይ ውብ ዕንቊ የሚፈልግ ነጋዴ ትመስላለች፤ እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ ባገኘም ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 13:36, 45, 46) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው አድማጮቹን ምን ለማስተማር ፈልጎ ነው? እኛስ ከዚህ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
ውድ ዋጋ ያላቸው ዕንቁዎች
3. በጥንት ዘመን ጥራት ያለው ዕንቁ በጣም ውድ የነበረው ለምንድን ነው?
3 ከጥንት ዘመን አንስቶ ዕንቁ ጌጣ ጌጥ ለመሥራት የሚያገለግል በጣም ተፈላጊ ማዕድን ሆኖ ቆይቷል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ፣ ሮማዊው ምሑር ትልቁ ፕሊኒ ዕንቁ “ውድ ዋጋ አላቸው ከሚባሉ ነገሮች ሁሉ የመጀመሪያውን ደረጃ” ይይዛል ብሎ መናገሩን ገልጿል። ከወርቅ፣ ከብርና ከሌሎች በርካታ ውድ ማዕድናት በተለየ ዕንቁ የሚገኘው ከሕያዋን ፍጥረታት ነው። ኦይስተር ተብለው ከሚጠሩት የዓሣ ዝርያዎች አንዳንዶቹ እንደ ጠጠር ያሉ የሚቆረቁሯቸውን ነገሮች ከሰውነታቸው በሚመነጭ ኔከር በሚባል ፈሳሽ በመሸፈን የሚያብረቀርቅ ዕንቁ የመሥራት ችሎታ እንዳላቸው በሰፊው ይታወቃል። በጥንት ዘመን ጥራት ያላቸው ዕንቁዎች በአብዛኛው የሚገኙት ከቀይ ባሕር፣ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤና ከሕንድ ውቅያኖስ ሲሆን እነዚህ ቦታዎች የሚገኙት ደግሞ ከእስራኤል ርቀው ነበር። ኢየሱስ “ውብ ዕንቊ የሚፈልግ ነጋዴ” በማለት የተናገረው ከዚህ የተነሳ እንደሚሆን ግልጽ ነው። እውነተኛ ዕንቁ ለማግኘት ብዙ ጥረት ይጠይቃል።
4. ኢየሱስ ዕንቁ ስለሚፈልግ ነጋዴ የተናገረው ምሳሌ የያዘው ዋና መልእክት ምንድን ነው?
4 ከረጅም ዘመን አንስቶ ውብ ዕንቁዎች ከፍተኛ ዋጋ የነበራቸው ቢሆንም ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው ከዋጋ አንጻር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ የአምላክን መንግሥት እንዲያው ውድ ዋጋ ካለው ዕንቁ ጋር አዛምዶ ብቻ አላለፈም፤ ከዚህ ይልቅ ‘ውብ ዕንቊ የሚፈልገው ነጋዴ’ ዕንቁውን ሲያገኝ የወሰደውን እርምጃ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ዕንቁ ከሚሸጥ ከአንድ ተራ ባለ ሱቅ በተለየ ዕንቁ ፍለጋ የሚጓዝ አንድ ነጋዴ በሙያው የተካነ እንደሆነ ይታመናል። ነጋዴው አንድን ዕንቁ በዓይነቱ ልዩ የሚያስብለውን ውበትና ጥራት መንጥሮ የማየት ችሎታ አለው። እውነተኛውን ዕንቁ ዓይቶ ማወቅ ስለሚችል ጥራት በሌለው ወይም አስመስለው በሠሩት የውሸት ዕንቁ አይታለልም።
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ ምን ለየት ያለ ባሕርይ አለው? (ለ) ስለተደበቀ ሀብት የሚናገረው ምሳሌ ስለ ነጋዴው ምን የሚገልጸው ነገር አለ?
5 ከዚህ አስተዋይ ነጋዴ የምንማረው ሌላም ቁም ነገር አለ። አብዛኞቹ ነጋዴዎች ከዕንቁው ሽያጭ የሚያገኙትን ትርፍ ለማወቅ ዕንቁውን ከመግዛታቸው በፊት ገበያ ላይ ያለውን የመሸጫ ዋጋ ያጣራሉ። በተጨማሪም ወዲያውኑ መሸጥ ስለሚፈልጉ፣ የሚገዙት ዕንቁ ገበያ ላይ ተፈላጊ መሆን አለመሆኑን ያጤናሉ። በሌላ አባባል የነጋዴዎቹ ፍላጎት ዕንቁውን ይዞ መቀመጥ ሳይሆን የገዙትን ዕንቁ በቶሎ ሸጦ ትርፍ ማግኘት ነው። ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ነጋዴ አስተሳሰብ ግን የተለየ ነው። የእርሱ ፍላጎት ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም ማግኘት አይደለም። እንዲያውም ሲፈልገው የነበረውን ነገር በእጁ ለማስገባት ሲል “ያለውን ሁሉ” ማለትም የግል ንብረቱንና ሀብቱን በሙሉ ለመሠዋት ፈቃደኛ ነበር።
6 በአብዛኞቹ ነጋዴዎች አስተሳሰብ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ግለሰብ ያደረገው ነገር የቂል ሥራ ይመስል ይሆናል። አንድ ብልጥ ነጋዴ እንዲህ ዓይነት የማያዋጣ ነገር አያደርግም። በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ ግን ለሀብት ያለው አመለካከት የተለየ ነው። የእርሱ ፍላጎት ገንዘብ ማትረፍ ሳይሆን እጅግ የላቀ ዋጋ ያለውን ነገር እጁ በማስገባት ደስታና እርካታ ማግኘት ነው። ኢየሱስ በተናገረው በአንድ ተመሳሳይ ምሳሌ ላይ ይህን ነጥብ ግልጽ አድርጎታል። “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ ሄዶ፤ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያንን የዕርሻ ቦታ ገዛ” ብሏል። (ማቴዎስ 13:44) አዎ፣ ሰውየው ያንን ሀብት ማግኘቱና የግሉ ማድረጉ የሚያስገኝለት ደስታ ያለውን ሁሉ እንዲሸጥ አነሳስቶታል። በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ይገኛሉ? ደግሞስ እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት ሊከፈልለት የሚገባ ሀብት ይኖራል?
የአምላክን መንግሥት ዋጋማነት የተገነዘቡ ሰዎች
7. ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ያለውን የላቀ ዋጋ በሚገባ እንደተገነዘበ ያሳየው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው ስለ “መንግሥተ ሰማይ” ለማስረዳት ብሎ ሲሆን የአምላክ መንግሥት ትልቅ ዋጋ እንዳለውም በሚገባ ያውቅ ነበር። የወንጌል ዘገባዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አሳማኝ ምሥክርነት ይሰጣሉ። ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጠመቀ “‘ንስሓ ግቡ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና’ እያለ መስበክ ጀመረ።” ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ብዙ ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት አስተማረ። በመላው የይሁዳ ምድር እየተዘዋወረ “የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ አለፈ።”—ማቴዎስ 4:17፤ ሉቃስ 8:1
8. ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት የሚያከናውናቸውን ነገሮች ለማሳየት ምን አድርጓል?
8 ኢየሱስ የታመሙትን መፈወስን፣ የተራቡትን መመገብን፣ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠርንና ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተአምራት በመፈጸም የአምላክ መንግሥት የሚያከናውናቸውንም ነገሮች አሳይቷል። (ማቴዎስ 14:14-21፤ ማርቆስ 4:37-39፤ ሉቃስ 7:11-17) በመጨረሻም በመከራ እንጨት ላይ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት ለአምላክና በሰማይ ለተቋቋመው መንግሥት ያለውን ታማኝነት አረጋግጧል። ነጋዴው “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት ሲል ያለውን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ ሁሉ ኢየሱስም እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ድረስ ለአምላክ መንግሥት በታማኝነት ቆሟል።—ዮሐንስ 18:37
9. የቀድሞዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባሕርይ አሳይተዋል?
9 ኢየሱስ ሕይወቱ በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያተኩር ከማድረጉም ሌላ ጥቂት ተከታዮች አፍርቷል። እነርሱም ቢሆኑ ይህ መንግሥት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው በጥልቅ ተገንዝበው ነበር። ቀደም ሲል የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው እንድርያስ ከእነርሱ መካከል አንዱ ነው። እንድርያስና አንድ ሌላ የዮሐንስ ደቀ መዝሙር (ዮሐንስ የሚባለው የዘብዴዎስ ልጅ ሳይሆን አይቀርም) ኢየሱስ “የእግዚአብሔር በግ መሆኑን” መጥምቁ ዮሐንስ ሲመሰክር ሰምተው ወዲያውኑ ኢየሱስን መከተል ጀመሩ፤ በእርሱም አመኑ። ሆኖም ጉዳዩ በዚህ አላበቃም። እንድርያስ ምንም ጊዜ ሳያባክን የሥጋ ወንድሙ ስምዖን ጋር ሄዶ “መሲሑን አገኘነው” ብሎ ነገረው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ስምዖን (ኬፋ ወይም ጴጥሮስ በሚል ስያሜ የሚታወቀው) እንዲሁም ፊልጶስና ጓደኛው ናትናኤል ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ተገነዘቡ። እንዲያውም ናትናኤል ኢየሱስን “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” ብሎታል።—ዮሐንስ 1:35-49
ለተግባር ተነሳሱ
10. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በድጋሚ አግኝቶ እንዲከተሉት ሲነግራቸው ምን አደረጉ?
10 እንድርያስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ሌሎች መሲሑን ባገኙ ጊዜ የተሰማቸውን ደስታ ነጋዴው እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ከተሰማው ደስታ ጋር ማወዳደር ይቻላል። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? ለመጀመሪያ ጊዜ ኢየሱስን ካገኙት በኋላ ወዲያውኑ ምን እንዳደረጉ የወንጌል ዘገባዎች ብዙም የሚናገሩት ነገር የለም። አብዛኞቹ ወደ ወትሮ ኑሯቸው እንደተመለሱ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ እንድርያስን፣ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ወንድሙን ያዕቆብን በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ሲያጠምዱ አገኛቸው።a በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ታዲያ ምን አደረጉ? የማቴዎስ ዘገባ “ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት” በማለት ጴጥሮስና እንድርያስ ያደረጉትን ይገልጻል። ያዕቆብና ዮሐንስን በተመለከተ “ወዲያውኑ ጀልባቸውንም ሆነ አባታቸውን ትተው ተከተሉት” የሚል እናነባለን። ሉቃስ ያሰፈረው ዘገባ ደግሞ “ሁሉን ትተው ተከተሉት” የሚል ተጨማሪ ሐሳብ ይዟል።—ማቴዎስ 4:18-22፤ ሉቃስ 5:1-11
11. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እንዲከተሉት ሲጠራቸው አፋጣኝ ምላሽ የሰጡት ለምን ሊሆን ይችላል?
11 ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዓይነት ፈጣን ምላሽ የሰጡት በስሜት ተገፋፍተው ይሆን? በፍጹም! ምንም እንኳ ከኢየሱስ ጋር መጀመሪያ ከተገናኙ በኋላ በቤተሰብ መልክ ወደሚያከናውኑት ዓሣ የማጥመድ ሥራ የተመለሱ ቢሆንም በዚያን ጊዜ ያዩትና የሰሙት ነገር በልባቸውና በአእምሯቸው ላይ የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸው እንዳለፈ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ የነበረው ወደ አንድ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ በእነዚያ ጉዳዮች ላይ የሚያሰላስሉበት በቂ ጊዜ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። አሁን አንድ አቋም የሚወስዱበት ጊዜ ደርሷል። ደቀ መዛሙርቱ፣ ውድ የሆነ ዕንቁ ሲያገኝ ልቡ በደስታ ከመፈንደቁ የተነሳ ዕንቁውን ወዲያው “ሄዶ” ለመግዛት አስፈላጊውን ነገር እንዳደረገው ነጋዴ ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዱ ይሆን? ምን ጥያቄ አለው፤ ባዩትና በሰሙት ነገር ልባቸው ተነክቷል። እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ መድረሱን ተገንዝበዋል። በመሆኑም ዘገባው እንደሚለው ምንም ሳያቅማሙ ያላቸውን ሁሉ እርግፍ አድርገው በመተው ኢየሱስን መከተል ጀምረዋል።
12, 13. (ሀ) የኢየሱስን ስብከት ያዳመጡ ብዙ ሰዎች የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ ምን ብሏል? እንደዚያ ሲልስ ምን ማለቱ ነበር?
12 እነዚህ ታማኝ ሰዎች በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ከተጠቀሱ ሌሎች ሰዎች ፈጽሞ የተለየ አቋም ነበራቸው! ኢየሱስ የፈወሳቸውና የመገባቸው ሰዎች በጣም ብዙ ቢሆኑም ሁሉም ወደ ግል ጉዳያቸው ተመልሰዋል። (ሉቃስ 17:17, 18፤ ዮሐንስ 6:26) እንዲያውም አንዳንዶች ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሆኑ ሲጠራቸው መምጣት የማይችሉበትን ሰበብ አቅርበዋል። (ሉቃስ 9:59-62) ከእነዚህ ፍጹም በተለየ ኢየሱስ ስለ ታማኝ ተከታዮቹ በሌላ ጊዜ እንዲህ ብሏል:- “ከመጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ብዙዎች መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት ይጋደላሉ፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ወራሽ ይሆናሉ።”—ማቴዎስ 11:12 NW
13 ‘መጋደል’ እና ‘በተጋድሎ መጽናት’ የሚሉት ቃላት ምን ሐሳብ ያስተላልፋሉ? እነዚህ ቃላት የተገኙበትን የግሪክኛውን ግስ በተመለከተ ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት “ግሱ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ያመለክታል” ይላል። ይህን ጥቅስ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ሃይነሪክ ሜየር እንዲህ ብለዋል:- “መምጫው የተቃረበውን መሲሐዊውን መንግሥት ለማግኘት የነበራቸው ጉጉት፣ ከፍተኛ ፍላጎትና ጥሮሽ የተገለጸው በዚህ መንገድ ነው . . . መንግሥቱን ይጠባበቁ የነበሩት (በለዘብተኝነትና በጥርጣሬ ሳይሆን) በከፍተኛ ጉጉትና በሙሉ ልብ ነበር።” በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰው ነጋዴ ሁሉ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦችም እውነተኛ ዋጋ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ወዲያውኑ የተገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን መንግሥት ለማግኘት ሲሉ የነበራቸውን ሁሉ በፈቃደኝነት ሠውተዋል።—ማቴዎስ 19:27, 28፤ ፊልጵስዩስ 3:8
ሌሎችም በፍለጋው ተሰማሩ
14. ኢየሱስ ሐዋርያቱን ለስብከቱ ሥራ ያዘጋጃቸው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?
14 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎችም መንግሥቱን ማግኘት እንዲችሉ ሥልጠናና ድጋፍ ሰጥቷቸዋል። በመጀመሪያ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል 12ቱን መርጦ ሐዋርያት (የተላኩ ማለት ነው) ብሎ ሾማቸው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ አገልግሎታቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ዝርዝር መመሪያ የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ወደፊት ስለሚጠብቃቸው አስቸጋሪ ሁኔታና መከራ አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴዎስ 10:1-42፤ ሉቃስ 6:12-16) በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ገደማ ኢየሱስ በመላው ይሁዳ እየተዘዋወረ ሲሰብክ አብረውት በመሄድ ከእርሱ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ችለዋል። የሰጣቸውን ትምህርቶች አዳምጠዋል፣ ተአምራዊ ሥራዎቹን አይተዋል እንዲሁም የተወውን ምሳሌ ተመልክተዋል። (ማቴዎስ 13:16, 17) እነዚህ ሁሉ ነገሮች በጥልቅ ስለነኳቸው እንደ ዕንቁ ነጋዴው እነርሱም የአምላክን መንግሥት ለማግኘት በቅንዓትና በሙሉ ልብ ተነሳስተዋል።
15. የኢየሱስን ተከታዮች ይበልጥ ደስ የሚያሰኛቸው እርሱ የተናገረው የትኛው ሐሳብ ነው?
15 ኢየሱስ ከ12ቱ ሐዋርያት በተጨማሪ “ሌሎች ሰባ . . . ሰዎችን መርጦ ሾመ፤ ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።” በተጨማሪም ወደፊት ስለሚጠብቃቸው ፈተናና መከራ የነገራቸው ከመሆኑም ሌላ ለሰዎች “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች” ብለው እንዲሰብኩ መመሪያ ሰጣቸው። (ሉቃስ 10:1-12) ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ በጣም ተደስተው የነበረ ሲሆን ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” በማለት ያጋጠማቸውን ሁኔታ ነገሩት። ይሁንና ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት በቅንዓት በመደገፋቸው የላቀ ደስታ እንደሚጠብቃቸው ሲነግራቸው ሳይገረሙ አይቀሩም። “መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ” አላቸው።—ሉቃስ 10:17, 20
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ምን ነገራቸው? (ለ) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ምን የሚያስደስትና የሚያበረታታ ነገር ነገራቸው?
16 በመጨረሻም ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፋት የመጨረሻ ምሽት የጌታ እራት የተባለውን በዓል ያቋቋመ ሲሆን ዕለቱን ለመታሰቢያው እንዲያከብሩለትም አዘዛቸው። በዚያ ምሽት ኢየሱስ አብረውት ለቆዩት ለአሥራ አንዱ ሐዋርያት እንዲህ አላቸው:- “እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።”—ሉቃስ 22:19, 20, 28-30
17 ኢየሱስ እንዲህ ሲላቸው ሐዋርያቱ በጣም ተደስተው መሆን አለበት! ማንኛውም ሰው ሊያገኘው ከሚችለው እጅግ የላቀ ክብርና መብት ተሰጣቸው። (ማቴዎስ 7:13, 14፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰው ዕንቁ ነጋዴ ሁሉ እነርሱም ኢየሱስን በመከተል መንግሥቱን ለማግኘት ባደረጉት ጥረት ብዙ ነገሮችን ሠውተዋል። ይሁንና እስከዚያን ጊዜ ድረስ የከፈሏቸው መሥዋዕቶች በከንቱ እንዳልቀሩ ማረጋገጫ ተሰጣቸው።
18. ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት በተጨማሪ ጊዜው ሲደርስ ከአምላክ መንግሥት ጥቅም የሚያገኙት እነማን ናቸው?
18 ከአምላክ መንግሥት ጥቅም የሚያገኙት በዚያ ምሽት ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ሐዋርያት ብቻ አይደሉም። ይሖዋ፣ በሰማይ በሚገኘው ክብራማ መንግሥት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች የሚሆኑና በመንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ የሚታቀፉ በጥቅሉ 144,000 ሰዎችን የመምረጥ ዓላማ ነበረው። ከዚህ በተጨማሪ ሐዋርያው ዮሐንስ “በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው . . . ‘ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣ የአምላካችንና የበጉ ነው’” ሲሉ በራእይ ተመልክቷል። እነዚህ በምድር ላይ የሚኖሩ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ናቸው።b—ራእይ 7:9, 10፤ 14:1, 4
19, 20. (ሀ) ለሕዝቦች ሁሉ ምን አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ የሚያገኘው ጥያቄ ምንድን ነው?
19 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ታማኝ ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አዟቸዋል:- “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) በመሆኑም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ ማለት ነው። እነዚህም ውርሻቸው በሰማይ መኖርም ሆነ በምድር ልባቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ ስለሚያኖሩ ነጋዴው ውብ ዕንቁ ሲያገኝ ያደረገውን ዓይነት እርምጃ ወስደዋል።
20 ይህ የኢየሱስ አነጋገር ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” እንደሚቀጥል ያሳያል። ታዲያ በዘመናችን የአምላክን መንግሥት ለማግኘት ሲሉ ያላቸውን ሁሉ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴውን የሚመስሉ ግለሰቦች አሉ? ይህ ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ ያገኛል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ ኢየሱስ ያከናወናቸውን ነገሮች በወንጌል ዘገባው ላይ በግልጽ እንዲያሰፍር ያስቻለው ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ለተወሰነ ወቅት ከእርሱ ጋር በመሆን ያደረጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ተመልክቶ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐንስ ምዕራፍ 2-5) ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲከተለው እስከጠራው ጊዜ ድረስ ወደ ዓሣ ማጥመድ ሥራው ተመልሷል።
b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 10ን ተመልከት።
-
-
በዛሬው ጊዜ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት የተደረገ ጥረትመጠበቂያ ግንብ—2005 | የካቲት 1
-
-
በዛሬው ጊዜ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት የተደረገ ጥረት
“ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።”—ማቴዎስ 24:14
1, 2. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ስለ አምላክ መንግሥት የነበራቸው ግንዛቤ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት በትክክል እንዲገባቸው ምን አድርጓል? ውጤቱስ ምን ነበር?
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአምላክ መንግሥት በእስራኤላውያን ዘንድ ዓቢይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር። (ማቴዎስ 3:1, 2፤ 4:23-25፤ ዮሐንስ 1:49) መጀመሪያ ላይ ግን አብዛኞቹ ሰዎች ግዛቱ ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረውና ምን ዓይነት አገዛዝ እንደሚሆን እንዲሁም በሰማይ ያለ መስተዳደር መሆኑን በሚገባ አልተረዱም ነበር። (ዮሐንስ 3:1-5) አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች እንኳ ሳይቀሩ የአምላክ መንግሥት ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች የመሆን መብት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በትክክል አልገባቸውም ነበር።—ማቴዎስ 20:20-22፤ ሉቃስ 19:11፤ የሐዋርያት ሥራ 1:6
2 በጊዜ ሂደት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በፊተኛው ርዕስ ላይ የተመለከትነውን እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ የሚናገረውን ምሳሌ ጨምሮ ብዙ ትምህርቶች በማስተማር መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ እንዳለባቸው ገለጸላቸው። (ማቴዎስ 6:33፤ 13:45, 46፤ ሉቃስ 13:23, 24) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በሰፊው እንደሚያሳየው በአጭር ጊዜ ውስጥ ትጉና ደፋር የመንግሥቱ ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን መልእክቱን እስከ ምድር ዳር ድረስ በማሰራጨታቸው ትምህርቱ ልባቸውን በጥልቅ እንደነካው መረዳት ይቻላል።—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ቈላስይስ 1:23
3. ኢየሱስ የእኛን ዘመን አስመልክቶ ስለ አምላክ መንግሥት ምን ብሏል?
3 ዛሬስ ሁኔታው ምን ይመስላል? በአምላክ መንግሥት ሥር ምድር ገነት ስትሆን የሚኖረው አስደሳች ሕይወት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እየተሰበከ ነው። ኢየሱስ ‘ስለ ዓለም መጨረሻ’ በተናገረው ትንቢት ላይ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 14፤ ማርቆስ 13:10) ከዚህ በተጨማሪ ይህ መጠነ ሰፊ ሥራ የሚከናወነው ከፍተኛ እንቅፋትና ፈተና ብሎም ስደት እያለ እንደሆነ ገልጿል። ይሁን እንጂ “እስከ መጨረሻ የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” የሚል ዋስትና ሰጥቷል። (ማቴዎስ 24:9-13) ይህ ሁሉ ነገር ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ ያሳየው ዓይነት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና የዓላማ ጽናት ይጠይቃል። በዛሬው ጊዜ መንግሥቱን ለማግኘት እንዲህ ዓይነት እምነትና ቅንዓት የሚያሳዩ ግለሰቦች ይገኛሉ?
እውነትን ማወቅ የሚያስገኘው ደስታ
4. የመንግሥቱ እውነት በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ምን የማድረግ ኃይል አለው?
4 ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ነጋዴ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ሲያገኝ በጣም ተደስቶ ነበር። እንዲያውም እጅግ ከመደሰቱ የተነሳ ዕንቁውን እጁ ለማስገባት ሲል የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል። (ዕብራውያን 12:1) ዛሬም ቢሆን ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ የሚነገረው እውነት ሰዎችን ይማርካቸዋል እንዲሁም ለተግባር ያነሳሳቸዋል። ይህ ደግሞ ወንድም አሌክሳንደር ማክሚላን ስለ አምላክና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ለማወቅ ያደረገውን ጥረት በሚመለከት ፌዝ ኦን ዘ ማርች በተባለው መጽሐፉ ላይ ያሰፈረውን ሐሳብ ያስታውሰናል:- “እኔ ያገኘሁትን ነገር በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማግኘት ላይ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከተለያየ ብሔር፣ ዘር፣ የኑሮ ደረጃና ዕድሜ የተውጣጡ በመሆናቸው እንደ እኔና እንደ እናንተ ያሉ ሰዎች ናቸው። እውነት ከሰው ሰው አይለይም። ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይስባል።”
5. የ2004 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው ምን ግሩም ውጤት ተገኝቷል?
5 በየዓመቱ ቅን ልብ ያላቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ሰምተው ሕይወታቸውን ለይሖዋ ለመወሰንና ፈቃዱን ለማድረግ መነሳሳታቸው የዚህን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል። በመስከረም 2003 ጀምሮ በነሐሴ 2004 የተደመደመው የ2004 የአገልግሎት ዓመትም ቢሆን ተመሳሳይ ውጤት ተገኝቶበታል። በእነዚያ 12 ወራት ውስጥ 262,416 ሰዎች በሕዝብ ፊት በውኃ በመጠመቅ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን አሳይተዋል። ይህ የተከናወነው በ235 አገሮች ውስጥ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ አገሮች ውስጥ የተለያየ የኑሮ ሁኔታ ያላቸው ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ የተውጣጡ 6,085,387 የሚያህሉ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሠፈረውንና ሕይወት የሚያሰጠውን እውነት እንዲያገኙ ለመርዳት በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናት ላይ ይገኛሉ።—ራእይ 7:9
6. ባለፉት ዓመታት ቀጣይ እድገት እንዲኖር ያስቻለው ምንድን ነው?
6 ይህ እድገት እንዴት ሊገኝ ቻለ? ይሖዋ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን እነዚህን ሰዎች ወደ ራሱ እንደሳባቸው ምንም ጥያቄ የለውም። (ዮሐንስ 6:65፤ የሐዋርያት ሥራ 13:48) ይሁንና መንግሥቱን ለመውረስ በሚያደርጉት ጥረት ራሳቸውን ምንም ሳይቆጥቡ ያቀረቡና ያለ አንዳች መታከት በሥራው የተሳተፉ ክርስቲያኖች ያከናወኑት ተግባር ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። ወንድም ማክሚላን በ79 ዓመት ዕድሜው እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “ታማሚና ሟች ለሆነው የሰው ዘር የተዘረጋለትን ተስፋ መጀመሪያ ከሰማሁበት ጊዜ አንስቶ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በዚህ ትምህርት ላይ ያለኝ እምነት ፈጽሞ አልተዳከመም። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሁሉን ቻይ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክና ለሰው ልጆች ስላለው በጎ ዓላማ እንደ እኔ ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች መንገር እንድችል መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ነገር ይበልጥ ለማወቅ ቆርጬ ተነሳሁ።”
7. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያገኙ ሰዎች የሚሰማቸውን ደስታና ጉጉት የሚያሳየው የትኛው ተሞክሮ ነው?
7 በዛሬው ጊዜ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ዘንድ ተመሳሳይ ግለት ይታያል። ለምሳሌ ያህል በኦስትሪያ፣ ቬይና የምትኖረውን የዳንየላን ተሞክሮ ተመልከት። እንዲህ ትላለች:- “ከልጅነቴ አንስቶ አምላክ የቅርብ ወዳጄ ሆኖ ቆይቷል። ‘አምላክ’ የሚለው ስም ፈጣሪ እውን ሆኖ እንዲታየኝ ስለማያደርግ ስሙን የማወቅ ጉጉት ነበረኝ። ይሁንና በ17 ዓመቴ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ ስሙን ሳላውቅ ቆየሁ። ከእነርሱ ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ስለ አምላክ ማወቅ የምፈልገውን ነገር ሁሉ ነገሩኝ። በመጨረሻ እውነትን አገኘሁ፤ እውነትን ማወቅ በጣም ያስደስታል! እንዲያውም ከደስታዬ የተነሳ ላገኘሁት ሰው ሁሉ መስበክ ጀመርኩ።” ዳንየላ በጋለ ስሜት መስበኳ ብዙም ሳይቆይ ከትምህርት ቤት ጓደኞቿ ፌዝ አስከተለባት። በመቀጠል እንዲህ ትላለች:- “እኔ ግን ኢየሱስ ተከታዮቹ ለስሙ ሲሉ እንደሚጠሉና እንደሚሰደዱ እንደተናገረ ቀደም ብዬ ስለተማርኩ ነገሩን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ አድርጌ ቆጠርኩት። ከፍተኛ በሆነ የደስታና የመገረም ስሜት ተዋጥሁ።” ዳንየላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወቷን ለይሖዋ ወስና የተጠመቀች ከመሆኑም ሌላ ሚስዮናዊ ለመሆን ጥረት ማድረግ ጀመረች። ትዳር ከመሠረተች በኋላ ከባለቤቷ ከሄልሙት ጋር ሆና ቬይና ውስጥ ለሚኖሩ አፍሪካውያን፣ ቻይናውያን፣ ፊሊፒናውያንና ሕንዶች ምሥራቹን መስበክ ጀመረች። በአሁኑ ጊዜ ዳንየላና ሄልሙት በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ሚስዮናዊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ተስፋ አልቆረጡም
8. ብዙዎች ለአምላክ ያላቸውን ፍቅርና ለመንግሥቱ ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩበት አንድ አስደሳች መንገድ የትኛው ነው?
8 በእርግጥም የሚስዮናዊነት አገልግሎት በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ለአምላክ ያላቸውን ፍቅርና ለመንግሥቱ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳዩበት አንደኛው መንገድ ነው። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ነጋዴ ሚስዮናዊ የሚሆኑ ክርስቲያኖችም ለአምላክ መንግሥት ሲሉ ሩቅ ወደሆኑ ቦታዎች ለመጓዝ ፈቃደኛ ናቸው። እርግጥ ነው፣ ሚስዮናውያኑ የሚጓዙት የመንግሥቱን ምሥራች ለማግኘት ብለው ሳይሆን ርቀው በሚገኙ የምድር ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለማስተማርና ለመርዳት ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) በብዙ አገሮች ውስጥ አይተው የማያውቁትን ችግር ለመቋቋም ይገደዳሉ። ሆኖም ጽናታቸው ከፍተኛ በረከት ያስገኝላቸዋል።
9, 10. ሚስዮናውያን እንደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ በመሳሰሉ ርቀው በሚገኙ አገሮች ምን አስደሳች ተሞክሮዎች አግኝተዋል?
9 ለምሳሌ ያህል፣ ባለፈው ዓመት በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ በአገሪቱ ካሉት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ወደ ሰባት እጥፍ ገደማ ማለትም 16,184 ሰዎች የተገኙባትን የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክን ተመልከት። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ መብራት ስለማይገኝ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን የሚያከናውኑት ከቤት ውጪ ዛፍ ጥላ ሥር ሆነው ነው። በመሆኑም ሚስዮናውያኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸውን የሚያስጠኑት ከቤት ውጪ ዛፍ ሥር ተቀምጠው ነው። ውጪ ማጥናታቸው የተሻለ ብርሃንና ቀዝቀዝ ያለ አየር የሚያስገኝላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ሌላም ጥቅም አለው። ሕዝቡ በተፈጥሮው ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር አለው፤ እንዲሁም በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየት በአንዳንድ አገሮች ስለ ስፖርትና ስለ አየር ጠባይ የማውራት ያህል የተለመደ ነገር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጥናት ሲካሄድ የሚመለከቱ መንገደኞች ከፈለጉ መጥተው ያዳምጣሉ።
10 በመሆኑም አንድ ሚስዮናዊ ውጪ መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠና ሳለ ከመንገዱ ባሻገር የሚኖር አንድ ወጣት ቀረብ ብሎ እርሱን ቤቱ መጥቶ ያነጋገረው ሰው ስለሌለ ሚስዮናዊው እርሱ ጋር መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናው እንደሚፈልግ ነገረው። እንደሚጠበቀው ሁሉ ሚስዮናዊው ለማስጠናት ደስተኛ መሆኑን ገለጸለት፤ ወጣቱም ፈጣን እድገት በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚያ አገር ብዙ ጊዜ ፖሊሶች የይሖዋ ምሥክሮችን መንገድ ላይ ያስቆሟቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉት ግን የክስ ወይም የቅጣት ወረቀት ሊሰጧቸው ሳይሆን በቅርብ የወጡ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት እንዲሰጧቸው ለመጠየቅ አሊያም ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን ርዕስ በተመለከተ ምስጋናቸውን ለመግለጽ ነው።
11. የተለያዩ ፈተናዎች ቢኖሩም ለረጅም ጊዜ በሚስዮናዊነት ያገለገሉ ወንድሞች ስለ አገልግሎታቸው ምን ይሰማቸዋል?
11 ከዛሬ 40 ወይም 50 ዓመታት በፊት የሚስዮናዊነት አገልግሎት የጀመሩ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም በታማኝነት እያገለገሉ ናቸው። በእምነትና በጽናት ረገድ ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል! አንድ ባልና ሚስት ላለፉት 42 ዓመታት በሦስት አገሮች ውስጥ በሚስዮናዊነት አገልግለዋል። ባልየው እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ችግሮች ለመጋፈጥ ተገድደናል። ለምሳሌ ያህል፣ ለ35 ዓመታት ከወባ በሽታ ጋር ስንታገል ቆይተናል። ሆኖም ሚስዮናዊ ለመሆን ባደረግነው ውሳኔ ፈጽሞ ተቆጭተን አናውቅም።” ባለቤቱ ደግሞ እንዲህ ትላለች:- “ምንጊዜም አመስጋኝ እንድንሆን የሚያስችሉ ብዙ ነገሮች ያጋጥሙናል። አገልግሎት በጣም ያስደስታል፤ ደግሞም በቀላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸው ሰዎች ወደ ስብሰባ ሲመጡና አንዳቸው ከሌላው ጋር ሲተዋወቁ ማየት ዘመድ አዝማድ የተሰባሰበ ነው የሚመስለው።”
“ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት” ይቆጥራሉ
12. አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት እንደ ውድ ሀብት እንደሚቆጥር ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?
12 ነጋዴው እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ “ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው።” (ማቴዎስ 13:46) ነጋዴው የሚጠቅመውን ነገር መሥዋዕት ለማድረግ ያሳየው ይህ ዓይነቱ የፈቃደኝነት መንፈስ የአምላክን መንግሥት ዋጋማነት ከልብ የሚያደንቁ ሰዎች የሚታወቁበት ባሕርይ ነው። ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ክብር የመካፈል አጋጣሚ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጒድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለእርሱ ስል ሁሉን አጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ።”—ፊልጵስዩስ 3:8
13. በቼክ ሪፑብሊክ የሚኖሩ አንድ ግለሰብ ለአምላክ መንግሥት ያላቸውን ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?
13 በተመሳሳይ በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የአምላክ መንግሥት የሚያመጣውን በረከት ለማግኘት ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ መሠረታዊ ለውጦች ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥቅምት 2003 ቼክ ሪፑብሊክ ውስጥ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑ የ60 ዓመት ሰው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተዘጋጀ መጽሐፍ አገኙ። መጽሐፉን አንብበው ከጨረሱ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናቸው ሰው ለማግኘት ወዲያውኑ በአካባቢያቸው ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኙ። ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ታዲያ ለከተማው ከንቲባነት ከዚያም አልፎ ለምክር ቤት አባልነት ለመወዳደር የነበራቸውን ዕቅድ ምን አደረጉት? ይህን ትተው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን የሕይወትን ሩጫ ለመጀመር ወሰኑ። “ለተማሪዎቼ ብዙ ጽሑፎች ማበርከት ችያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። በሐምሌ 2004 በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት አሳዩ።
14. (ሀ) የመንግሥቱ ምሥራች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል? (ለ) እያንዳንዳችን ራሳችንን የትኞቹን አሳሳቢ ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን?
14 በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል። ከክፉው ዓለም ወጥተዋል፣ አሮጌውን ሰው አስወግደዋል፣ የቀድሞ ባልንጀሮቻቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል እንዲሁም ዓለማዊ ግቦችን ማሳደድ አቁመዋል። (ዮሐንስ 15:19፤ ኤፌሶን 4:22-24፤ ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) ይህን ሁሉ ያደረጉት ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት የሚያመጣላቸውን በረከት ይህ ሥርዓት ሊሰጣቸው ከሚችለው ከማንኛውም ጥቅም እጅግ አስበልጠው ስለተመለከቱ ነው። አንተስ ለአምላክ መንግሥት ምሥራች ተመሳሳይ አመለካከት አለህ? አኗኗርህን፣ በሕይወትህ ውስጥ ከፍተኛ ግምት የምትሰጣቸውን ነገሮችና ግቦችህን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ለማስማማት አስፈላጊውን ለውጥ እንድታደርግ ያነሳሳሃል? እንዲህ ማድረግህ አሁንም ሆነ ለዘላለም ብዙ በረከት እንድታገኝ ያስችልሃል።
መከሩ ወደ ፍጻሜው ተዳርሷል
15. በፍጻሜው ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ምን እንደሚያደርጉ በትንቢት ተነግሯል?
15 መዝሙራዊው “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል” ሲል ጽፏል። ራሳቸውን በፈቃደኝነት ካቀረቡት መካከል ‘እንደ ጠል ያሉ ጎልማሶች’ እና ‘ዜናውን የሚያሰራጩ ብዙ ሴቶች’ ይገኙበታል። (መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም፤ 110:3) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲሁም ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት ትጋትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ምን አስገኝቷል?
16. የአምላክ አገልጋዮች ሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት እንዲማሩ ለመርዳት ምን ጥረት እያደረጉ እንዳሉ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገር።
16 በሕንድ የምትኖር አንዲት አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በአገሪቱ የሚኖሩት ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ምሥራቹን እንዲያውቁ እንዴት ሊረዱ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ያሳስባት ነበር። (ኢሳይያስ 35:5) የምልክት ቋንቋ ለመማር ወደ አንድ ተቋም ሄዳ ለመመዝገብ ወሰነች። በዚያም መስማት ለተሳናቸው ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች መመሥከር ቻለች። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖች ተቋቋሙ። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከአሥራ ሁለት የሚበልጡ ሰዎች በመንግሥት አዳራሹ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ በአንድ የሠርግ ግብዣ ላይ አቅኚዋ ከካልካታ ከመጣ መስማት የተሳነው ወጣት ጋር ተገናኘች። ይህ ወጣት በርካታ ጥያቄዎች የነበሩት ከመሆኑም ሌላ ስለ ይሖዋ ተጨማሪ እውቀት የማግኘት ከፍተኛ ጉጉት አደረበት። ይሁንና መፍትሄ የሚያሻው አንድ ችግር ነበር። ወጣቱ ኮሌጅ ለመግባት 1,600 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደ ካልካታ መመለስ የነበረበት ሲሆን በዚያ ደግሞ የምልክት ቋንቋ የሚችሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን መቀጠል ስለፈለገ በባንጋሎር ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ለመግባት እንዲፈቅድለት አባቱን እንደ ምንም ብሎ አሳመነው። ግሩም መንፈሳዊ እድገት አድርጎ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ሕይወቱን ለይሖዋ ወሰነ። እርሱ ደግሞ በተራው የልጅነት ጓደኛውን ጨምሮ በርከት ያሉ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ላይ ይገኛል። በሕንድ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ አቅኚዎች በዚህ የአገልግሎት መስክ መካፈል እንዲችሉ የምልክት ቋንቋ እንዲማሩ ዝግጅት እያደረገ ነው።
17. ከገጽ 19 እስከ 22 ካለው የ2004 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት በጣም አበረታች ሆኖ ያገኘኸውን ነጥብ ተናገር።
17 በዚህ መጽሔት ከገጽ 19 እስከ 22 ላይ የይሖዋ ምሥክሮች በ2004 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ ያደረጉትን የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ሪፖርት ወጥቷል። ጥቂት ጊዜ ወስደህ ሪፖርቱን በማጤን በምድር ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች በዛሬው ጊዜ “እጅግ ውድ የሆነ ዕንቊ” ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ለመሆናቸው ማስረጃውን ተመልከት።
‘አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት እሹ’
18. ኢየሱስ ስለ ነጋዴው በተናገረው ምሳሌ ላይ ያልጠቀሰው ሐሳብ ምንድን ነው? ለምንስ?
18 ከዚህ በፊት የተጠቀሰውን ኢየሱስ ስለ ነጋዴው የተናገረውን ምሳሌ በድጋሚ ካነሳን ነጋዴው ያለውን ሁሉ ከሸጠ በኋላ በምን እንደሚተዳደር ኢየሱስ የተናገረው ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን። አንዳንዶች ‘ነጋዴው ለክፉ ቀን ያስቀመጠው ምንም ነገር ስለሌለ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከየት ያገኛል? በውድ ዋጋ የገዛው ዕንቁ ምን ሊያደርግለት ይችላል?’ ብለው መጠየቃቸው አይቀርም። ጉዳዩን በሥጋዊ ዓይን ከተመለከትነው ጥያቄዎቹ አግባብነት ያላቸው ይመስላሉ። ሆኖም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ከሁሉ አስቀድማችሁ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” በማለት አሳስቧቸው አልነበረም? (ማቴዎስ 6:31-33) የምሳሌው ዋና መልእክት ለአምላክ በሙሉ ልብ የማደርንና መንግሥቱን በቅንዓት የመደገፍን አስፈላጊነት ማስገንዘብ ነው። እኛ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ይኖራል?
19. ኢየሱስ እጅግ ውድ ስለሆነ ዕንቁ ከተናገረው ምሳሌ ምን ዓቢይ ትምህርት እናገኛለን?
19 አስደናቂውን ምሥራች የሰማነው በቅርቡም ሆነ የአምላክን መንግሥት በመጠባበቅና የሚያመጣቸውን በረከቶች ለሌሎች በመንገር በርካታ አሥርተ ዓመታት ያሳለፍን ቢሆን ልባችንና ትኩረታችን በመንግሥቱ ላይ እንዳነጣጠረ መቀጠል ይኖርብናል። ያለንበት ዘመን በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ይሁንና ለማግኘት የምንጣጣረው ነገር እውነተኛና ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሀብት እንደሆነ የሚያሳምነን ጠንካራ ምክንያት አለን። እንዲያውም ነጋዴው ባገኘው ዕንቁ ልንመስለው እንችላለን። በዓለም ላይ የሚታዩ ክስተቶችና ፍጻሜያቸውን ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የምንኖረው ‘በዓለም መጨረሻ’ ላይ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ ይሰጡናል። (ማቴዎስ 24:3) እንደ ነጋዴው ሁሉ እኛም የአምላክን መንግሥት በሙሉ ልባችን እንደምንደግፍ እናሳይ፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለማወጅ ባገኘነው መብት እንደሰት።—መዝሙር 9:1, 2
-