ምዕራፍ 5
“አዲስ ኪዳን—ታሪክ ወይስ ተረት?
“ዛሬ አዲስ ኪዳን በዓለም ላይ ካሉት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ ጥልቅ ምርምር የተደረገበት መጽሐፍ ነው ሊባል ይችላል።” “ኦን ቢይንግ ኤ ክርስቺየን” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ይህን የተናገሩት ሃንስ ኩንግ ናቸው። ደግሞም ትክክል ናቸው። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ባለፉት ከ300 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ምርምር ብቻ ሳይሆን የተካሄደባቸው ከየትኛውም የጽሑፍ ሥራ በበለጠ መንገድ አንድ በአንድ እየተነጣጠሉ ተገምግመዋል።
1, 2. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) ባለፉት 300 ዓመታት ውስጥ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ምን ዓይነት ሁኔታዎች ገጥመውታል? (ለ) አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች ምን እንግዳ የሆነ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል?
አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች የደረሱባቸው መደምደሚያዎች ግራ ናቸው። በ19ኛው መቶ ዘመን በጀርመን የነበረው ሉድቪግ ኖአክ የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈው በ60 እዘአ ነው ብሎ የደመደመ ሲሆን እንደ እርሱ አባባል ከሆነ ጸሐፊው የተወደደው ደቀ መዝሙር ይሁዳ ነው! ፈረንሳዊው ጆሴፍ ኧርነስት ሬናን የአልዓዛርን ትንሣኤ በሚመለከት አስተያየቱን ሲሰጥ ተዓምር እሠራለሁ የሚለውን የኢየሱስ አባባል ለመደገፍ ሲል አልዓዛር ራሱ ያቀነባበረው ተንኮል ነው ብሏል። ጀርመናዊው የሃይማኖት ምሁር ጉስታቭ ቮልክማር ደግሞ በአንድ ወቅት በሕይወት እንደነበር ታሪክ የሚመሰክርለት ኢየሱስ መሲሐዊ ተልዕኮ አለኝ ብሎ መጥቶ ነበር ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው በማለት አጥብቆ ተከራክሯል።1
2 በሌላ በኩል ደግሞ ብሩኖ ቦዌር ኢየሱስ የሚባል ሰው ኖሮ አያውቅም በማለት ደምድሟል! “ክርስትና በጀመረባቸው ዓመታት በእርግጥ የነበሩ የታወቁ የፈጠራ ሰዎች ፊሎ፣ ሴኔካና ግኖስቲኮች ብቻ ናቸው ሲል ተከራክሯል። በመጨረሻም በታሪክ ኢየሱስ የሚባል ሰው ኖሮ እንደማያውቅ . . . የክርስትና ሃይማኖትም የተፈጠረው በሁለተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ሲሆን የኢስጦይኮች ፍልስፍና ከገነነበት የአይሁድ እምነት የወጣ መሆኑን ገልጿል።”2
3. ብዙዎች እስከ ዛሬም ድረስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው?
3 ዛሬ ይህ ዓይነቱ ጽንፈኛ አቋም ያላቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። ይሁን እንጂ የዘመናችን ምሁራን የሚያዘጋጁአቸውን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ስታነብ ዛሬም ቢሆን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች አፈታሪክ፣ ተረትና የተጋነነ ነገር ይዘዋል ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ትረዳለህ። ይህ ነገር እውነት ነውን?
የተጻፉት መቼ ነው?
4. (ሀ) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መቼ እንደተጻፉ ማወቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጻፉበትን ጊዜ በሚመለከት የሚሰነዘሩት አንዳንድ አመለካከቶች የትኞቹ ናቸው?
4 ተረቶችና አፈታሪኮች ለመስፋፋት ጊዜ ይወስዳሉ። በመሆኑም እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት መቼ ነው? የሚለው ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ይሆናል። ታሪክ ጸሐፊው ማይክል ግራንት፣ ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻፍ የጀመሩት “ኢየሱስ ከሞተ ከሠላሳ ወይም ከአርባ ዓመት በኋላ” ነው ብለዋል።4 ሲ ሲ ቶሬይ እንደሚከተለው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አርኪኦሎጂስት የሆኑት ዊልያም ፎክስዌል ኦልብራይት ገልጸዋል:- “ሁሉም ወንጌሎች የተጻፉት ከ70 ዓ.ም. በፊት ሲሆን ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ በነበሩት ሃያ ዓመታት ውስጥ ሊጻፍ አይችልም የምንለው አንድም ነገር አይገኝም።” ኦልብራይትም ራሳቸው የሚያስቡት ወንጌሎቹ ተጽፈው ያበቁት “ከ80 ዓ.ም. በፊት ነው” ብለው ነው። ሌሎች ከዚህ ትንሽ ለየት ያለ ግምት ይዘው ብቅ ይበሉ እንጂ አብዛኛዎቹ “አዲስ ኪዳን” ተጽፎ ያለቀው በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ ነው በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።
5, 6. የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጻፉት በውስጣቸው የያዙት ታሪክ ከተፈጸመ ብዙም ሳይቆይ በመሆኑ ምን መደምደሚያ ላይ ልንደርስ ይገባል?
5 ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? ኦልብራይት እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “አንድ ማለት የምንችለው ነገር አለ። በሃያና በሃምሳ ዓመታት ውስጥ የጽሑፉን መሠረታዊ ይዘት የሚያዛባ ጉልህ ለውጥ ይቅርና ኢየሱስ ሐሳቡን ለመግለጽ በተጠቀመባቸው ቃላት ላይ እንኳ ለውጥ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።”5 ፕሮፌሰር ጋሪ ሃበርማስ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “የጥንት ታሪኮች ብዙውን ጊዜ የሚያወሱት ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ስለተፈጸሙ ነገሮች ሲሆን ወንጌሎቹ የተጻፉበትና የሚተርኩት ነገር ግን ከተፈጸሙበት ጊዜ ጋር ተቀራራቢ ናቸው። ይሁንና የዘመናችን ታሪክ ጸሐፊዎች በእነዚያ የጥንት ዘመናት ሳይቀር የተፈጸሙትን ነገሮች በሚገባ ማወቅ ችለዋል።”6
6 በሌላ አባባል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ትረካዎች ቢያንስ ቢያንስ ከዓለማዊ ታሪኮች ያላነሰ ተዓማኒነት ማግኘት ይገባቸዋል። በእርግጥም ደግሞ በክርስትና ዘመን መባቻ ላይ በተከናወኑት ነገሮችና እነዚህ ነገሮች በጽሑፍ በሰፈሩበት መካከል ባለው ጥቂት የጊዜ ልዩነት ተረቶችና አፈታሪኮች ተፈልስፈው ሰፊ ተቀባይነት ሊያገኙ አይችሉም።
የዓይን ምሥክሮች ማስረጃ
7, 8. (ሀ) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ተጽፈው በሚሠራጩበት ወቅት ሁሉ እነማን በሕይወት ነበሩ? (ለ) ከፕሮፌሰር ኤፍ ኤፍ ብሩስ አባባል በመነሳት ምን ብለን መደምደም ይገባናል?
7 ብዙዎቹ ዘገባዎች የዓይን ምሥክሮችን ማስረጃ የሚጠቅሱ በመሆናቸው ይህ አባባል እውነት ሆኖ እናገኘዋለን። የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ እንዲህ ብሏል:- “ስለ እነዚህም የመሰከረ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ [ኢየሱስ የሚወደው] ደቀ መዝሙር ነው።” (ዮሐንስ 21:24) የሉቃስ መጽሐፍ ጸሐፊ ደግሞ “ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት” አስተላለፉልን ብሏል። (ሉቃስ 1:1, 2) ሐዋርያው ጳውሎስ ለኢየሱስ ትንሣኤ የዓይን ምሥክር የሆኑትን ሰዎች በሚመለከት ሲናገር:- “ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 15:6
8 ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፕሮፌሰር ኤፍ ኤፍ ብሩስ ግሩም አስተያየት ሰጥተዋል:- “ምን እንደተፈጸመና ምን እንዳልተፈጸመ አሳምረው የሚያውቁት ብዙዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሕይወት በነበሩባቸው በእነዚያ የመጀመሪያ ዓመታት ኢየሱስ እንዲህ አደረገ፣ እንዲህ ተናገረ ብሎ የፈጠራ ሥራ መሥራት አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች የሚያስቡትን ያክል ፈጽሞ ቀላል ሊሆን አይችልም። . . . ደቀ መዛሙርቱ ስህተት ለመፈላለግ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ወገኖች በቀላሉ ሊያጋልጧቸው የሚችሉ የተዛቡ (ሆነ ተብሎ እውነታውን በማጣመም የተነገሩ) ነገሮችን በመሰንዘር ራሳቸውን ለችግር ለመዳረግ እንደማይቃጡ የታወቀ ነው። እንዲያውም በተቃራኒው የሐዋርያት ስብከት አንዱ ጠንካራ ጎን አድማጮቻቸው ስለጉዳዩ እንደሚያውቁ ሆነው በልበ ሙሉነት መቅረባቸው ነው። ‘እኛ ለዚህ ነገር የዓይን ምሥክሮች ነን’ ብቻ ከማለት ይልቅ ‘ራሳችሁ እንደምታውቁት’ ይሉም ነበር። (ሥራ 2:22)።”7
ይዘቱ አስተማማኝ ነውን?
9, 10. የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚመለከት ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
9 የዓይን ምሥክሮቹ ያቀረቧቸው ማስረጃዎች በትክክል ከተመዘገቡ ከጊዜ በኋላ ተበርዘው ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራልን? በሌላ አባባል የመጀመሪያው ቅጂ ተጽፎ ካለቀ በኋላ ተረትና አፈታሪክ ተጨምሮበት ሊሆን ይችላልን? የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ይዘት ከሌሎች ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ቀደም ብለን ተመልክተናል። የመጽሐፍ ቅዱስ የግሪክኛ ጽሑፎች ምሁር የሆኑት ኩርት እና ባርባራ ኦላንድ ከጥንት እስከ ዘመናችን ድረስ የቆዩ 5,000 የሚያክሉ ጥንታዊ ቅጂዎችን የዘረዘሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የተዘጋጁ ናቸው።8 እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች በአጠቃላይ የጽሑፉ መሠረታዊ ይዘት እንዳልተለወጠ የሚያረጋግጡ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የጽሑፎቹ ይዘት ትክክል እንደሆነ የሚያረጋግጡ ብዙ የጥንት ትርጉሞች አሉ። ከእነዚህ መካከል ጥንታዊ የሆነው በ180 እዘአ ገደማ የተዘጋጀ ነው።9
10 እንግዲያው በዚህም ሆነ በዚያ የመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አፈታሪክም ሆነ ተረት ወደ ክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ሾልኮ እንዳልገባ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ዛሬ በእጃችን ላይ ያለው ጽሑፍ ይዘትና የመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች የጻፉት ነገር ተመሳሳይ ነው። በዚያ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖችም ተቀብለውት ስለነበር ትክክለኝነቱ ምንም አያጠራጥርም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች ጥንታዊ ታሪኮች ጋር በማወዳደር ታሪካዊ ይዘቱን መፈተን እንችላለንን? በተወሰነ ደረጃ እንችላለን።
የጽሑፍ ማስረጃዎች
11. የሌሎች መዛግብት ማስረጃዎች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን የታሪክ ዘገባ የሚደግፉት ምን ያህል ነው?
11 እንደ እውነቱ ከሆነ በኢየሱስና በሐዋርያቱ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሚገኙት የጽሑፍ ማስረጃዎች ውስን ናቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው አነስተኛ ቡድን ስለነበሩ ይህ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ይሁን እንጂ ሌሎች የታሪክ ምንጮች የሚሰጡትም ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናነበው ነገር ጋር የሚጣጣም ነው።
12. ጆሴፈስ መጥምቁ ዮሐንስን በሚመለከት ምን ብሏል?
12 ለምሳሌ ያህል ሄሮድስ አንጢጳስ ከባድ ወታደራዊ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ በ93 እዘአ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “አንዳንዶቹ አይሁዳውያን የሄሮድስ ሠራዊት መደምሰሱ መለኮታዊ የበቀል እርምጃ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል፤ ደግሞም መጥምቁ በሚል ቅጽል ስም ይታወቅ በነበረው በዮሐንስ ላይ ከፈጸመው ነገር አንጻር ሲታይ ተገቢ የበቀል እርምጃ ነበር። ዮሐንስ አይሁዳውያን በጽድቅ ጎዳና እንዲመላለሱ፣ ለመሰሎቻቸው ፍትሕን እንዲያደርጉ እንዲሁም ለአምላክ ያደሩ እንዲሆኑ የረዳ ጥሩ ሰው ቢሆንም አስገድሎታል።”10 በዚህ መንገድ ጆሴፈስ፣ አጥማቂው ዮሐንስ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ይሰብክ የነበረ ጻድቅ ሰው ስለመሆኑና ሄሮድስ እንዳስገደለው የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛነት አረጋግጧል።—ማቴዎስ 3:1-12፤ 14:11
13. ያዕቆብም ሆነ ኢየሱስ በታሪክ ውስጥ የኖሩ መሆናቸውን ጆሴፈስ የመሠከረው እንዴት ነው?
13 በመጀመሪያ ኢየሱስን እንዳልተከተለ የኋላ ኋላ ግን በኢየሩሳሌም ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ያለው ሽማግሌ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚናገርለት ስለ ኢየሱስ ግማሽ ወንድም ስለ ያዕቆብም ቢሆን ጠቅሷል። (ዮሐንስ 7:3-5፤ ገላትያ 1:18, 19) የያዕቆብን መታሰር በሚከተሉት ቃላት ገልጾታል:- “[ሊቀ ካህናቱ ሐና] የሳንሄድሪንን ዳኞች ሰብስቦ ክርስቶስ ይባል የነበረው የኢየሱስ ወንድም የሆነውን ያዕቆብ የተባለ ሰውና ሌሎችንም ወደ ፊታቸው አቀረበ።”11 ጆሴፈስ በዚህ አባባሉ “ክርስቶስ ይባል የነበረው ኢየሱስ” በገሃዱ ዓለም የነበረ በታሪክ የሚታወቅ ሰው መሆኑን ጨምሮ አረጋግጧል።
14, 15. ታሲተስ የመጽሐፍ ቅዱሱን ዘገባ የሚደግፍ ምን ነገር ጽፏል?
14 ሌሎችም የጥንት ጸሐፊዎች እንዲሁ በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱ ነገሮችን በሚመለከት ጽፈዋል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በፍልስጤም ምድር አካባቢ ያከናወነው ስብከት ሰፊ ተቀባይነት እንዳገኘ ወንጌሎች ይነግሩናል። ጴንጤናዊው ጲላጦስ ሞት በፈረደበት ጊዜም ተከታዮቹ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገብቷቸውና ቅስማቸው ስብር ብሎ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ግን እነዚሁ ደቀ መዛሙርት ጌታቸው ትንሣኤ እንዳገኘ የሚገልጸውን መልእክት በድፍረት በመስበክ ኢየሩሳሌምን በትምህርታቸው ሞሏት። ክርስትና በጥቂት ዓመታት ውስጥ በመላው የሮማ ግዛት ተስፋፋ።—ማቴዎስ 4:25፤ 26:31፤ 27:24-26፤ ሥራ 2:23, 24, 36፤ 5:28፤ 17:6
15 ይህ ነገር እውነት መሆኑን የክርስትና ወዳጅ ያልነበረው ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ መሥክሯል። ኔሮ በክርስቲያኖች ላይ ያደረሰውን ጭካኔ የሞላበት ስደት አስመልክቶ ከ100 እዘአ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሲጽፍ እንደሚከተለውም ብሎ ነበር:- “የስሙ መገኛ የሆነው ክሪስተስ በገዥው በጴንጤናዊው ጲላጦስ ቃል በጢባሪዮስ ዘመን በሞት እንዲቀጣ ከተደረገ በኋላ መርዘኛ የሆነው አጉል እምነት ለጊዜው ብቻ ተገትቶ ቆየ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የበሽታው ምንጭ የሆነችውን ይሁዳን ብቻ ሳይሆን ራሷን ዋና ከተማዋን [ሮምን] ሳይቀር አጥለቀለቃት።”12
16. ሱቶኒየስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ ስለሚገኘው ስለየትኛው ታሪካዊ ክስተት ተናግሯል?
16 መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት መካከል አንዱ በሥራ 18:2 ላይ “አይሁድ ከሮሜ ይወጡ ዘንድ ቀላውዴዎስ አዞ” እንደነበር ጠቅሷል። በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበረው ሮማዊ ታሪክ ጸሐፊ ሱቶኒየስም እንዲሁ መባረራቸውን ጠቅሷል። ይህ ታሪክ ጸሐፊ ዘ ዲፋይድ ክላውዲየስ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ “አይሁዳውያኑ በክሬስተስ ቆስቋሽነት ያለማቋረጥ ረብሻ ይፈጥሩ ስለነበር እርሱ [ክላውዲየስ] ከሮም አስወጣቸው” ሲል ጽፏል።13 እዚህ ላይ የተጠቀሰው ክሬስተስ የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስን ከሆነና በሮም የታየው ሁኔታ በሌሎችም ከተሞች ይታይ የነበረ ነገር ከሆነ ረብሻዎቹ በክርስቶስ (በሌላ አባባል በክርስቶስ ተከታዮች) አነሳሽነት የተቀሰቀሱ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ግን ክርስቲያኖቹ በታማኝነት ያከናውኑት በነበረው የስብከት እንቅስቃሴ ምክንያት አይሁዳውያኑ ያነሳሱትን ዓመፅ የሚያመለክት ነው።
17. በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረው ሰማዕቱ ጀስቲን ኢየሱስ ስላከናወነው ትንሣኤና ስለ ሞቱ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚያረጋግጡ ምን ማስረጃዎች ነበሩት?
17 ሰማዕቱ ጀስቲን በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ሲጽፍ የኢየሱስን ሞት በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ከጴንጤናዊው ጲላጦስ ሥራ መጽሐፍ ማረጋገጥ ትችላላችሁ።”14 ከዚህም በላይ እንደ ሰማዕቱ ጀስቲን አባባል ከሆነ የተጠቀሱት እነዚሁ መዝገቦች ስለ ኢየሱስ ተዓምራትም የሚጠቅሱ ሲሆን ይህንን በሚመለከት ሲናገር “እነዚህን ነገሮች እንዳደረገ ከጴንጤናዊው ጲላጦስ ሥራ መጽሐፍ ልታነቡ ትችላላችሁ” ብሏል።15 እነዚህ ‘የሥራ’ መጻሕፍት ወይም ኦፊሴላዊ መዛግብት ዛሬ እንደማይገኙ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ መዛግብት በሁለተኛው መቶ ዘመን እንደነበሩ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። ሰማዕቱ ጀስቲንም የተናገረው ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን አንባቢዎቹ ራሳቸው ሄደው እንዲያረጋግጡ በልበ ሙሉነት የተገዳደራቸው ለዚህ ነበር።
አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ
18. ጴንጤናዊው ጲላጦስ በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑን አርኪኦሎጂ ያረጋገጠው እንዴት ነው?
18 አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶችም ቢሆኑ በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የምናነባቸው ነገሮች ይበልጥ ግልጽ እንዲሆኑ ከማድረጋቸውም ሌላ ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል በ1961 በቂሣሪያ በነበረው የሮማ የቲያትር አዳራሽ ፍርስራሽ ውስጥ በተገኘ አንድ ጽሑፍ ላይ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የሚለው ስም ተቀርጾ ተገኝቷል።16 ይህ ጽሑፍ እስከተገኘበት ጊዜ ድረስ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ይህ የሮማ ገዥ እንደነበር የሚገልጹት ማስረጃዎች በጣም ውስን ነበሩ።
19, 20. ሉቃስ (በሉቃስና በሥራ መጻሕፍት ውስጥ) ስለ ጠቀሳቸው ስለ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች በአርኪኦሎጂ ማረጋገጥ ተችሏል?
19 የሉቃስ ወንጌል አጥማቂው ዮሐንስ አገልግሎቱን የጀመረው “ሊሳኒዮስም በሳቢላኒስ የአራተኛው ክፍል ገዥ” በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ይነግረናል። (ሉቃስ 3:1) ጆሴፈስ ሊሳኒዮስ የተባለ ሰው ሳቢላኒስን ይገዛ እንደነበርና ዮሐንስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ማለትም በ34 ከዘአበ እንደሞተ ተናግሮ ስለነበር አንዳንዶች ይህንን አባባል ሲጠራጠሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ አርኪኦሎጂስቶች በሳቢላኒስ ያገኙት የተቀረጸ ጽሑፍ ጢባሪዮስ በሮም ቄሣር ሆኖ በሚያስተዳድርበትና ዮሐንስ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ ሌላ ሊሳንዮስ የተባለ ሰው የአራተኛው ክፍል ገዥ (የአውራጃው ገዥ) እንደነበር ይገልጻል።17 ሉቃስ የጠቀሰው ሊሳንዮስ ይህ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው።
20 በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ጳውሎስና በርናባስ ለሚስዮናዊነት ሥራ ወደ ቆጵሮስ እንደተላኩና በዚያም ሰርጊዮስ ጳውሎስ የተባለ “አስተዋይ” አገረ ገዥ እንዳገኙ እናነባለን። (ሥራ 13:7) በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ በቆጵሮስ በተደረጉት ቁፋሮዎች በ55 እዘአ የተዘጋጁና ስለዚህ ሰው የሚጠቅሱ የተቀረጹ ጽሑፎች ለመገኘት ተችሏል። አርኪኦሎጂስቱ ጂ ኧርነስት ራይት ይህንኑ አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ስለዚህ አገረ ገዥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ተጠቅሶ የተገኘበት አንድ ቦታ ቢኖር ይህ ነው። ሉቃስ ስሙንና ማዕረጉን በትክክል ማስፈሩ የሚያስገርም ነው።”18
21, 22. መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርላቸውና በአርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች የተረጋገጡት የትኞቹ ሃይማኖታዊ ልማዶች ናቸው?
21 ጳውሎስ በአቴንስ በነበረበት ጊዜ “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል መሠዊያ እንዳየ ተናግሮ ነበር። (ሥራ 17:23) በሮማ ግዛት ሥር በነበሩ ክልሎች ውስጥ ስም ለሌላቸው አማልክት የተሠሩ መሆናቸው በላቲን ቋንቋ የተጻፈባቸው መሠዊያዎች ተገኝተዋል። በአቴንስ ከነበረው ጋር ሊመሳሰል የሚችል አንድ በግሪክኛ የተጻፈበት መሠዊያ በጴርጋሞን ተገኝቷል።
22 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በኤፌሶን ሳለ የሴት አምላክ የሆነችውን የአርጤምስ የአምልኮ ዕቃዎችና ምስሎችን በመሥራት የሚተዳደሩት አንጥረኞች አጥብቀው ተቃውመውት ነበር። ኤፌሶን “ለታላቂቱ አርጤምስ . . . የመቅደስ ጠባቂ” ተብላ ተጠርታለች። (ሥራ 19:35) ከዚሁ ጋር በሚስማማ መንገድ የተወሰኑ የሸክላ ሥራዎችና በእብነ በረድ የተቀረጹ የአርጤምስ ምስሎች በጥንቷ ኤፌሶን ተገኝተዋል። ባለፈው መቶ ዘመን ደግሞ ግዙፍ የሆነው ቤተ መቅደስ ቅሪት ሳይቀር በቁፋሮ ተገኝቷል።
እውነተኝነት
23, 24. (ሀ) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ጠንካራ ማስረጃ የሚገኘው የት ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ተንጸባርቆ የሚገኘው የትኛው ባሕርይ የመጻሕፍቱን እውነተኝነት ይመሠክራል? በምሳሌ አስረዳ።
23 እንግዲያው ታሪክና አርኪኦሎጂ በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ነገሮች ይበልጥ ግልጽ እንዲሆኑ ከማድረጋቸውም ሌላ እውነት ለመሆናቸው በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማረጋገጫ ይሰጡናል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን እነዚህ ጽሑፎች እውነተኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ከሁሉ የበለጠው ጠንካራ ማስረጃ የሚገኘው በራሳቸው በመጻሕፍቱ ውስጥ ነው። ስታነባቸው ተረት እንደሆኑ አይሰማህም። የያዙት እውነትን ነው።
24 በመጀመሪያ ደረጃ ምንም የደባበቁት ነገር የለም። ለምሳሌ ስለ ጴጥሮስ ተመዝግቦ የሚገኘውን ነገር ተመልከት። በውኃ ላይ ለመሄድ ያደረገው መከራ አለመሳካቱ የሚያሳፍር ቢሆንም በግልጽ ሰፍሯል። ከዚያም ኢየሱስ ይህን ትልቅ ክብር የነበረው ሐዋርያ “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን” ብሎታል። (ማቴዎስ 14:28-31፤ 16:23) ከዚህም በተጨማሪ ሌሎቹ ሁሉ እንኳን ትተውት ቢሄዱ እርሱ ኢየሱስን ትቶ እንደማይሸሽ አፉን ሞልቶ ሲናገር የነበረው ጴጥሮስ ለአንድ ምሽት መጠበቅ አቅቶት በእንቅልፍ ከማሸለቡም ሌላ ጌታውን ሦስት ጊዜ ካደው።—ማቴዎስ 26:31-35, 37-45, 73-75
25. የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ ሐዋርያቱ የሠሯቸውን የትኞቹን ስህተቶች በግልጽ አስቀምጠዋል?
25 ይሁን እንጂ በግልጽ የተጻፈው የጴጥሮስ ድክመት ብቻ አልነበረም። በግልጽ የተቀመጠው ዘገባ ሐዋርያቱ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እያሉ ይናቆሩ እንደነበር አልሸሸገም። (ማቴዎስ 18:1፤ ማርቆስ 9:34፤ ሉቃስ 22:24) የሐዋርያቱ የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ኢየሱስ በመንግሥቱ ለሁለቱ ልጆቿ ከሁሉ የተሻለውን ቦታ እንዲሰጣቸው ስላቀረበችውም ጥያቄ ቢሆን ሳይነግረን አላለፈም። (ማቴዎስ 20:20-23) በበርናባስና በጳውሎስ መካከል የነበረውም “መከፋፋት” በሐቀኝነት ተመዝግቦ ይገኛል።—ሥራ 15:36-39
26. እውነት ባይሆን ኖሮ አይጠቀስም ነበር የምንለው ከኢየሱስ ትንሣኤ ጋር ተያይዞ የተጠቀሰው ሁኔታ የትኛው ነው?
26 የሉቃስ መጽሐፍ ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱን በመጀመሪያ ያወቁት ‘ከገሊላ ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች’ መሆናቸውን መናገሩም ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ነው። የወንድ የበላይነት በገነነበት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኅብረተሰብ ዘንድ እንዲህ ያለው ዝርዝር መግለጫ ፈጽሞ ያልተለመደ ነበር። እንዲያውም እንደ ዘገባው አገላለጽ ከሆነ ይህ የሴቶቹ ወሬ ለሐዋርያቱ “ቅዠት መስሎ” ታይቷቸው ነበር። (ሉቃስ 23:55–24:11) በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው ታሪክ እውነተኛ አይደለም ከተባለ ፈጠራ ነው ማለት ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንደነዚህ ያሉትን የተከበሩ ሰዎች የሚነቅፍ ታሪክ የሚፈጠርበት ምን ምክንያት ይኖራል? እነዚህ ዝርዝር ሁኔታዎች የሠፈሩት እውነት ቢሆኑ ነው።
ኢየሱስ—በውን የነበረ ሰው
27. አንድ ታሪክ ጸሐፊ ኢየሱስ በታሪክ የነበረ ሰው መሆኑን የመሠከሩት እንዴት ነው?
27 ብዙ ሰዎች ታሪኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ኢየሱስን ልብ ወለድ ሰው እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል። ይሁን እንጂ ታሪክ ጸሐፊው ማይክል ግራንት እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ታሪክን ለሚዘግቡ ሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች የምንጠቀመውን ዓይነት መመዘኛ ለአዲስ ኪዳን የምንጠቀም ከሆነ፣ ደግሞም ልንጠቀም ይገባናል፣ በታሪክ ኖረዋል የሚባሉትንና ምንም ጥያቄ ተነሥቶባቸው የማያውቁትን ዓረማዊ ግለሰቦች ሕልውና ተቀብለን የኢየሱስን ሕልውና አንቀበልም የምንልበት ምንም ምክንያት አይኖርም።”19
28, 29. አራቱም ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ ባሕርይ ስምም የሆነ ነገር መግለጻቸው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር የሆነው ለምንድን ነው?
28 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ በሕይወት እንደነበር ብቻ ሳይሆን ምን ዓይነት ባሕርይ እንደነበረውም ሳይቀር እውነቱ በማያሻማ መንገድ ተገልጿል። አንድ እንግዳ የሆነ ገጸ ባሕርይ ፈጥሮ አንድ መጽሐፍ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ስለእርሱ ወጥ የሆነ ነገር ማስቀመጥ ቀላል ነገር አይሆንም። ባለ ታሪኩ በገሃዱ ዓለም ኖሮ የማያውቅ ከሆነ አራት የተለያዩ ጸሐፊዎች ስለዚያው ባለ ታሪክ ሲጽፉ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሊገልጹት ይችላሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። በአራቱም ወንጌሎች ውስጥ ስለ ኢየሱስ የተገለጸው ነገር በማያሻማ መንገድ ስለ እርሱ እንደሚናገሩ የሚያሳይ መሆኑ የወንጌሎቹን እውነተኝነት የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ ነው።
29 ማይክል ግራንት አንድ ተገቢ ጥያቄ አንስተዋል:- “በመጥፎ ስም የሚታወቁትን ጨምሮ ከሁሉም ዓይነት ሴቶች ጋር መልካም ግንኙነት የነበረው ውብ ጎልማሳ፣ አንዳችም የስሜታዊነት፣ መስሎ የማደር ወይም አጉል ተብለጭልጮ የመታየት ዝንባሌ የማይንጸባረቅበት፣ ነገር ግን በሁሉም አጋጣሚ ራሱን ሆኖ የሚመላለስ ጠንካራ ስብዕና ያለው ሰው ስለመሆኑ ሁሉም ወንጌሎች ያለምንም የሐሳብ መዘበራረቅ እንዴት ሊናገሩ ይችላሉ?”20 መልሱ እንዲህ ዓይነት ሰው በእርግጥ ስለነበርና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ስለተመላለሰ ነው የሚል ነው።
የማያምኑት ለምንድን ነው?
30, 31. ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም ብዙ ሰዎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ታሪካዊ ይዘት እውነተኛ እንደሆነ አድርገው የማይቀበሉት ለምንድን ነው?
30 በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች እውነተኛ መሆናቸውን ለመቀበል የሚያስችል በቂ ማስረጃ እያለ አንዳንድ ሰዎች እነዚህ ታሪኮች እውነተኛ አይደሉም የሚሉት ለምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች የተወሰነው ክፍል እውነተኛ መሆኑን እየተናገሩ በመጻሕፍቱ ውስጥ ያለውን በሙሉ ለመቀበል አሻፈረን የሚሉት ለምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ያሉ ምሁራን ሊያምኑባቸው የማይፈልጓቸውን ነገሮች መያዙ ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ትንቢቶችን እንዳስፈጸመና እርሱ ራሱም ትንቢቶችን እንደተናገረ ይገልጻል። እንዲሁም ተዓምራትን እንደሠራና ከሞተም በኋላ ትንሣኤ እንዳገኘ ይነግረናል።
31 የጥርጣሬ መንፈስ በነገሠበት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን እንዲህ ያሉት ነገሮች ፈጽሞ ሊታመኑ የማይችሉ ናቸው። ተዓምራትን በሚመለከት ፕሮፌሰር ኤዝራ ፒ ጎልድ እንዲህ ብለዋል:- “ተቺዎች እነርሱ ትክክል እንደሆኑ አድርገው እንዲያስቡ ያደረጋቸው የተቃውሞ ነጥብ አለ . . . ይኸውም ተዓምራት አይፈጸሙም የሚለው ነው።”21 አንዳንዶች ኢየሱስ ፈውስ አከናውኖ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ከአእምሮ ጋር የተያያዙ ስሜታዊ ችግሮችን ከመፈወስ ያለፈ አይሆንም ይላሉ። ሌሎቹን ተዓምራት በተመለከተ ግን አብዛኞቹ ሰዎች ፈጠራ ናቸው አለዚያም በእርግጥ የተፈጸሙት ነገሮች ከጊዜ በኋላ ተጋንነውና መልካቸውን ቀይረው ቀርበዋል ብለው ያስባሉ።
32, 33. አንዳንዶች ኢየሱስ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በተዓምር እንዳልመገበ ለማስረዳት የሞከሩት እንዴት ነው? ይሁን እንጂ ይህ ምክንያታዊ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
32 ለዚህ እንደምሳሌ እንዲሆነን ኢየሱስ በጥቂት እንጀራና በሁለት ዓሣ ከ5,000 የሚበልጡ ሰዎችን የመገበበትን ሁኔታ እንመልከት። (ማቴዎስ 14:14-22) የ19ኛው መቶ ዘመን ምሁር ሄንሪክ ፓውለስ የተከናወነው ነገር ይህን ይመስላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- በኢየሱስና በሐዋርያቱ ዙሪያ ብዙ ሰዎች ተሰብስበዋል። እነዚህ ሰዎች እርቧቸዋል። ስለዚህ ኢየሱስ በመካከላቸው ለነበሩት ሀብታሞች ምሳሌ ለመሆን ፈልጎ እርሱና ሐዋርያቱ የነበራቸውን ጥቂት ምግብ በመውሰድ ለእነዚያ ሁሉ ሰዎች አከፋፈለው። ከዚያ ወዲያው ምግብ አምጥተው የነበሩት ሌሎች ሰዎችም የእርሱን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች ማካፈል ጀመሩ። በመጨረሻ ያ ሁሉ ሕዝብ ተመግቦ ሄደ።22
33 በእርግጥ የተፈጸመው ነገር ይህ ነው ብንል እንኳ ይህ ራሱ መልካም ምሳሌነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ድንቅ ማረጋገጫ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለው አስደሳችና ትርጉም ያለው ታሪክ ከሰው በላይ በሆነ ኃይል የተከናወነ ተዓምር እንዲመስል ሲባል የሚቀየርበት ምን ምክንያት ይኖራል? እንደ እውነቱ ከሆነ ተዓምራቱ ተዓምራት አይደሉም ብሎ ለማስረዳት መሞከር ከሚፈታው ችግር ይልቅ የሚፈጥረው ችግር ይበልጣል። ደግሞም ሁሉም መሠረታቸው ሐሰት ነው። ተዓምር ሊፈጸም የማይችል ነገር ነው በሚል ግምታዊ ሐሳብ ይጀምራሉ። ይሁን እንጂ ለምን እንደዚያ ይሆናል?
34. በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ትክክለኛ ትንቢቶችንና በትክክል የተፈጸሙ ተዓምራትን ከሆነ ይህ ምን ማለት ይሆናል?
34 የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ከሁሉ የተሻሉ ሚዛናዊ ናቸው በሚባሉት መለኪያዎች ሲመዘኑ የያዙት ታሪክ እውነተኛ ሆኖ ይገኛል። ይሁንና ሁለቱም ክፍሎች ትንቢቶችንና ተዓምራትንም አካትተዋል። (ከ2 ነገሥት 4:42-44 ጋር አወዳድር።) ትንቢቶቹ እውነተኛ ሆነው ቢገኙስ? ተዓምራቱ በእርግጥ ተፈጽመው ከሆነስ? የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እንዲጻፉ ያደረገው አምላክ ስለሚሆን ቃሉ የእርሱ እንጂ የሰው አይደለም ማለት ይሆናል። ከሚቀጥሉት ምዕራፎች በአንዱ ውስጥ ትንቢትን በሚመለከት እንወያያለን። መጀመሪያ ግን እስቲ ስለ ተዓምራት እንነጋገር። ቀደም ባሉት መቶ ዘመናት ውስጥ ተዓምራት ተፈጽመው ነበር ብሎ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ማመን ምክንያታዊ ይሆናልን?
[በገጽ 66 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ካልሆነ በስተቀር ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱን በመጀመሪያ ያወቁት ሴቶች ናቸው ብሎ ለምን ይናገራል?
[በገጽ 56 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የዘመናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ሰንካላ ሆኖ ተገኝቷል
የዘመናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ተለዋዋጭ ባሕርይ ያለው መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ሬይሞንድ ኢ ብራውን የዮሐንስን ወንጌል አስመልክተው የሰነዘሩትን ሐሳብ እንመልከት:- “ምሁራኑ ባለፈው መቶ ዘመን መጨረሻና በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይህን ወንጌል በሚመለከት ያላቸው ሐሳብ በእጅጉ በጥርጣሬ የተሞላ ነበር። የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈው በ2ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በኋላ ያውም ወደ መገባደጃው ላይ ነው። በግሪካውያኑ ዓለም የተዘጋጀ እንደመሆኑ መጠን ምንም ታሪካዊ ጠቀሜታ እንደሌለውና የናዝሬቱ ኢየሱስ ከኖረባት ፍልስጤም ጋር ምንም የሚያዛምደው ነገር እንደሌለ ይታሰብ ነበር። . . .
“ያልተጠበቁ የአርኪኦሎጂ፣ የመዛግብት እንዲሁም ከጽሑፉ ይዘት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግኝቶች በመጉረፋቸው ዛሬ ከእነዚህ አመለካከቶች መካከል በማስረጃዎቹ ያልተነካ የለም። እነዚህ ግኝቶች ተቀባይነት ያላቸው ይመስሉ የነበሩትን የተቺዎች ሐሳብ በማስረጃ ለመቃወምና የዮሐንስ ወንጌል የተገመገመባቸው በጥርጣሬ የተሞሉ መሠረቶች በቀላሉ ፍርክርካቸው እንደሚወጣ ለመገንዘብ አስችለውናል። . . .
“ትንሽ ማሻሻያ ተደርጎ ወንጌሉ የተጻፈው በአንደኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ወይም ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው ተብሏል። . . . ምናልባትም ከዚህ ሁሉ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ አንዳንድ ምሁራን እንደገና የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ ከወንጌሉ ጋር የተወሰነ ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም ለማለት መድፈራቸው ነው”!3
እርሱ እንደጻፈው የሚታመነውን መጽሐፍ እርሱ ጽፎታል ማለት የሚያስገርም የሆነው ለምንድን ነው? ተቺዎቹ አስቀድመው በአእምሮአቸው ውስጥ ካስቀመጡት ሐሳብ ጋር ሳይስማማ በመቅረቱ ካልሆነ በቀር ሌላ ምክንያት የለውም።
[በገጽ 70 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰነዘረ ሌላ ጥቃት
ቲሞቲ ፒ ዌበር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ውጤቶች ተራው ሕዝብ [በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ] የሚገኘውን ማንኛውንም ነገር ለመረዳት ያለውን ችሎታ እንዲጠራጠር አድርገዋል። . . . ኤ ቲ ፒርሰን እንደ ሮማ ካቶሊክ ሁሉ [የመጽሐፍ ቅዱስ ትችትም] ለአምላክ ቃል ትርጓሜ ሊሰጡ የሚችሉት ምሁራኑ ብቻ ናቸው በማለቱ ቃሉ ከተራው ሕዝብ እንዲርቅ አድርጓል በማለት ብዙዎቹ ሰባኪዎች ያደረባቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። ሮም በቃሉና በሰዎች መካከል ቀሳውስትን ስታስቀምጥ ሥነ ጽሑፋዊው ትችት ደግሞ የተማሩት ተንታኞች በአማኞቹና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል እንዲገቡ አድርጓል።”23 በመሆኑም የዘመናችን ሥነ ጽሑፋዊ ትችት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰነዘረ ሌላ ጥቃት መሆኑ ግልጽ ሆኖ ታይቷል።
[በገጽ 62 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጴርጋሞን የሚገኘው ይህ መሠዊያ ‘ለማይታወቁ አማልክት’ የተወሰነ ነበር
[በገጽ 63 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድ ወቅት በጣም ገናና የነበረውና የኤፌሶን ሰዎች የሚኩራሩበት የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ
[በገጽ 64 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ እንደካደ መጽሐፍ ቅዱስ ሐቁን ሳይሸሽግ ይተርካል
[በገጽ 67 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ በጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተፈጠረውን “መከፋፋት” በሐቀኝነት መዝግቦ ይገኛል
[በገጽ 68 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአራቱም ወንጌሎች ውስጥ ስለ ኢየሱስ የተሰጠው መግለጫ ስምም መሆኑ የወንጌሎቹን እውነተኝነት የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው
[በገጽ 69 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኞቹ የዘመናችን ተቺዎች ተዓምር ሊፈጸም የሚችል ነገር አይደለም ብለው ያስባሉ