ደፋሮች ሁኑ!
“ በድፍረት:- ጌታ ይረዳኛልና . . . እንላለን።” — ዕብራውያን 13:6
1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የአምላክን እውነት ሰምተው የተቀበሉ ሰዎች ያሳዩት ምን ዓይነት ድፍረት ነበር?
ጊዜው በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ነው። ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የኖረው መሲሕ መጥቶአል። ደቀ መዛሙርቱንም በጥሩ ሁኔታ አስተምሮ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የስብከት ሥራ አስጀምሮአል። ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች መስማት ያለባቸው ጊዜ ደርሶ ነበር። ስለዚህ እውነትን የተማሩ ወንዶችና ሴቶች ያንን አስደናቂ መልእክት በድፍረት አውጀዋል። — ማቴዎስ 28:19, 20
2. በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምስክሮች ድፍረት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
2 መንግሥቲቱ በዚያ ዘመን አልተቋቋመችም ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሊሆን የተቀባው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት በመንግሥታዊ ሥልጣኑ በማይታይ ሁኔታ ስለሚገኝበት ጊዜ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይህ የመገኘቱ ጊዜም ከዚያ ቀደም ተወዳዳሪ ባልነበረው ጦርነት፣ ረሀብ፣ ቸነፈሮች፣ የመሬት መንቀጥቀጦችና በዓለም አቀፍ የምሥራቹ ስብከት ተለይቶ የሚታወቅ ነበር። (ማቴዎስ 24:3–14፤ ሉቃስ 21:10, 11) የይሖዋ ምስክሮች እንደመሆናችን መጠን እነዚህን ሁኔታዎችና የሚያጋጥመንን ስደት ለመቋቋም ድፍረት ያስፈልገናል። ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ስለነበሩት ደፋር የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ታሪክ መመርመር ጠቃሚ ነው።
ክርስቶስን ለመምሰል ያሳዩት ድፍረት
3. ከሁሉ የበለጠ የድፍረት ምሳሌ የተወልን ማን ነው? ስለ እርሱስ በዕብራውያን 12:1–3 ላይ ምን ተብሏል?
3 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ የላቀ የድፍረት ምሳሌ ትቶልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቅድመ ክርስትና የነበሩትን የደፋር ምስክሮች ‘ታላቅ ደመና’ ከጠቀሰ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ትኩረቱን በኢየሱስ ላይ ያሳርፋል:- “እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፣ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።” — ዕብራውያን 12:1–3
4. ኢየሱስ በሰይጣን በተፈተነ ጊዜ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነበር?
4 ኢየሱስ ከተጠመቀና በማሰላሰል፣ በመጸለይና በመጾም 40 ቀናት በበረሃ ካሳለፈ በኋላ ሰይጣንን በቆራጥነት ተቃውሞታል። ኢየሱስ ድንጋዮቹን ወደ እንጀራ እንዲለውጥ በሰይጣን ፈተና በቀረበለት ጊዜ የግል ፍላጎትን ለማሟላት ተአምር መሥራት ትክክል ባለመሆኑ እምቢ ብሎአል። ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” አለው። ኢየሱስ ራሱን ከቤተ መቅደስ ጫፍ ላይ ወደታች እንዲወረውር ዲያብሎስ በተፈታተነው ጊዜ ራሱን ወደ መግደል ከሚያደርሰው ከዚህ ሁኔታ እንዲያድነው አምላክን መፈታተን ኃጢአት ስለሚሆን ኢየሱስ ይህንን ጥያቄም አልተቀበለም። ክርስቶስ “ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” በማለት ተናገረ። ሰይጣን ለአንድ ጊዜ ‘ስግደት’ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ሊሰጠው አቅርቦለት ነበር። ኢየሱስ ግን ዲያብሎስ ሰዎች ቢፈተኑ ለአምላክ ታማኝ አይሆኑም ብሎ ያቀረበውን ግድድር በመደገፍ የክህደት እርምጃ አልወሰደም። ስለዚህ ኢየሱስ “ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና” በማለት አስታወቀ። ከዚያ በኋላ ፈታኙ “እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ።” — ማቴዎስ 4:1–11፤ ሉቃስ 4:13
5. ፈተናን እንድንቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
5 ኢየሱስ ለይሖዋ ይገዛ ስለነበረ ሰይጣንን ተቃውሞታል። እኛም እንደ እርሱ ‘ለአምላክ ከተገዛንና ዲያብሎስን ከተቃወምነው ከእኛ ይሸሻል።’ (ያዕቆብ 4:7) እኛም እንደ ኢየሱስ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሥራ የምንተረጉም ከሆነ፣ ምናልባትም አንድ ዓይነት ኃጢአት ለመፈጸም በምንፈተንበት ጊዜ [ለራሳችን] ልንጠቅሳቸው ከቻልን ፈተናዎችን በድፍረት ልንቋቋም እንችላለን። እንድንሰርቅ የሚፈታተን ሁኔታ ባጋጠመን ጊዜ “አትስረቅ” የሚለውን የአምላክ ሕግ ለራሳችን ደግመን ከጠቀስን ለዚህ ፈተና ልንሸነፍ እንችላለንን? ሁለት ክርስቲያኖች የጾታ ብልግና ለመፈጸም ፈተና ባጋጠማቸው ጊዜ ከሁለት አንዳቸው እንኳን “አታመንዝር” የሚለውን ቃል በድፍረት ቢጠቅስ በፈተናው ሊሸነፉ ይችላሉን? — ሮሜ 13:8–10፤ ዘጸአት 20:14, 15
6. ኢየሱስ ደፋር የዓለም ድል አድራጊ የነበረው እንዴት ነበር?
6 በዓለም የተጠላን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከዓለም መንፈስና ከኃጢአተኝነት ምግባሩ ልንርቅ እንችላለን። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” በማለት ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 16:33) እርሱ ዓለምን ድል ያደረገው ዓለምን ባለመምሰል ነው። የእርሱ የድል አድራጊነት ምሳሌና የፍጹም አቋም ጠባቂነት አካሄዱ ያስገኘው ውጤት እኛም በዚህ ዓለም ሳንበከል የተለየን ሆነን በመኖር እርሱን ለመምስል በድፍረት እንድንሞላ ሊያደርገን ይችላል። — ዮሐንስ 17:16
መስበካቸውን ለመቀጠል ያሳዩት ድፍረት
7, 8 ስደት ቢደርስብንም መስበካችንን እንድንቀጥል ምን ይረዳናል?
7 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ስደት ቢያጋጥማቸውም መስበካቸውን ለመቀጠል ድፍረት እንዲሰጣቸው በአምላክ ላይ ተማምነዋል። ክርስቶስ ስደት ቢያጋጥመውም እንኳን አገልግሎቱን በድፍረት ፈጽሟል። ስደት የደረሰባቸው ተከታዮቹ በ33 እዘአ ከዋለው ጴንጠ ቆስጠ በኋላ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች መስበካቸውን ሊያስተውአቸው ቢሞክሩም ምሥራቹን ማወጃቸውን ቀጥለው ነበር። (ሥራ 4:18–20፤ 5:29) ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ዛቻቸው ተመልከት . . . ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው” ብለው ጸለዩ። ከዚያስ ምን ሆነ? “ከጸለዩ በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሃት በድፍረት ተናገሩ” በማለት ዘገባው ይገልጽልናል። — ሥራ 4:24–31 የ1980 ትርጉም
8 በአሁኑ ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች የምሥራቹን ስለማይቀበሉ ለእነርሱ መስበካችንን ለመቀጠል ብዙውን ጊዜ ድፍረት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮች በሚሰደዱበት ጊዜ የተሟላ ምስክርነት እንዲሰጡ ከአምላክ የሚሰጠው ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። (ሥራ 2:40፤ 20:24) ስለዚህ የመንግሥቱ ደፋር አዋጅ ነጋሪ የነበረው ጳውሎስ ትንሽ ፍርሃት ለነበረበት የስብከት ባልደረባው እንደሚከተለው በማለት ነግሮታል:- “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፣ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል።” (2 ጢሞቴዎስ 1:7, 8) ድፍረት እንድናገኝ ከጸለይን መስበካችንን ለመቀጠል እንችላለን፤ ስደትም እንኳ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን የምናገኘውን ደስታ አይቀማንም። — ማቴዎስ 5:10–12
ከይሖዋ ጎን ለመሰለፍ ያሳዩት ድፍረት
9, 10. (ሀ) የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዶችና አሕዛብ የተጠመቁ የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን ሲሉ ምን አድርገዋል? (ለ) ክርስቲያን ለመሆን ድፍረት አስፈላጊ የነበረው ለምን ነበር?
9 ብዙ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁድና ያልተገረዙ አሕዛብ የተጠመቁ የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን ሲሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወግና ባሕሎቻቸውን በድፍረት እርግፍ አድርገው ትተዋል። በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠ ቆስጠ ዕለት በኋላ ወዲያውኑ “በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቁጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።” (ሥራ 6:7) እነዚያ አይሁዶች ከቀድሞ ሃይማኖታቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋርጠው ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመቀበል ድፍረት ነበራቸው።
10 ከ36 እዘአ ጀምሮ ብዙ አሕዛብ አማኞች ሆነዋል። ቆርኔሌዎስ፣ የቤተሰቡ አባሎችና ሌሎችም አሕዛብ የምሥራቹን በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ተቀበሉት፣ መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉና ‘በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ።’ (ሥራ 10:1–48) በፊልጵስዩስ ከአሕዛብ ወገን የሆነ አንድ የወህኒ ቤት ጠባቂና ቤተሰቦቹ ክርስትናን ባንዴ ተቀበሉና “ያንጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ።” (ሥራ 16:25–34) እንዲህ ዓይነቶቹን እርምጃዎች ለመውሰድ ድፍረት ይጠይቅ ነበር፤ ምክንያቱም ክርስቲያኖች የሚሰደዱና በሕዝብ ዘንድ የተጠሉ በቁጥር አነስተኛ ወገን ስለነበሩ ነው። እስካሁንም ድረስ እንደዚያው ናቸው። ታዲያ ራስህን ለአምላክ ያልወሰንክና ከይሖዋ ምስክሮች እንደ አንዱ በመሆን ያልተጠመቅህ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን የድፍረት እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን አይደለምን?
በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤተሰቦች ውስጥ ያሳዩት ድፍረት
11. ኤውንቄና ጢሞቴዎስ ምን የድፍረት መልካም ምሳሌ ትተውልናል?
11 ኤውንቄና ልጅዋ ጢሞቴዎስ በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤተሰቦች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ድፍረት ለተሞላበት እምነት ጥሩ ምሳሌ ትተዋል። ኤውንቄ አረማዊ ባል ቢኖራትም ልጅዋን ከሕፃንነቱ ጀምሮ “ቅዱሳን መጻሕፍትን” አስተምራዋለች። (2 ጢሞቴዎስ 3:14–17) ክርስቲያን በሆነች ጊዜም ‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’ አሳይታለች። (2 ጢሞቴዎስ 1:5) በተጨማሪም ለማያምነው ባሏ ራስነት አክብሮት እያሳየች ለጢሞቴዎስ የክርስትና ትምህርቶችን ለማካፈል የሚያስችል ድፍረት ነበራት። በጥሩ ሁኔታ ያስተማረችው ልጅዋ ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞው አብሮት እንዲሄድ በመረጠው ጊዜ እምነቷና ድፍረቷ ዋጋ እንዳስገኘ ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይ ሁኔታ ለሚገኙ ክርስቲያን ወላጆች ይህ እንዴት የሚያበረታታ ነው!
12. ጢሞቴዎስ ምን ዓይነት ሰው ሆነ? በአሁኑ ጊዜ እንደ እርሱ መሆናቸውን እያስመሰከሩ ያሉት እነማን ናቸው?
12 ጢሞቴዎስ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ቢኖርም ክርስትናን በድፍረት ተቀብሎ መንፈሳዊ ሰው ሊሆን በመቻሉ ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ሊናገርለት ችሎአል:- “ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እርሱ ያለ፣ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ ማንም የለኝምና፤ . . . ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ።” (ፊልጵስዩስ 2:19–22) በአሁኑ ጊዜ በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤቶች የሚኖሩ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እውነተኛውን ክርስትና በድፍረት እየተቀበሉ ነው። እነሱም እንደ ጢሞቴዎስ ምን ዓይነት አቋም እንዳላቸው እያስመሰከሩ ነው። ስለዚህ እነርሱም የይሖዋ ድርጅት ክፍል በመሆናቸው ምንኛ እንደሰታለን!
‘በነፍሳችን ለመቁረጥ’ ድፍረት ማሳየት
13. አቂላና ጵርስቅላ ድፍረት ያሳዩት በምን መንገድ ነው?
13 አቂላና ሚስቱ ጵርስቅላ ለእምነት ጓደኛቸው ሲሉ በድፍረት ‘በነፍሳቸው በመቁረጣቸው’ ጥሩ ምሳሌ ትተዋል። ጳውሎስን ወደ ቤታቸው ተቀብለው በድንኳን ሥራውም ከእርሱ ጋር አብረው የሠሩ ከመሆናቸውም በላይ በቆሮንቶስ አዲስ ጉባኤ ሲያቋቁም ረድተውታል። (ሥራ 18:1–4) ከጳውሎስ ጋር ባሳለፉት የ15 ዓመት ወዳጅነት ወቅት ሁሉ በግልጽ ባይነገረንም ለእርሱ ሲሉ ሕይወታቸውን በአደጋ ላይ ጥለው ነበር። ጳውሎስ በሮሜ ላሉት ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት በነገራቸው ጊዜ አቂላና ጵርስቅላ የሚኖሩት በሮም ነበር:- “በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፣ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም።” — ሮሜ 16:3, 4
14. አቂላና ጵርስቅላ ለጳውሎስ ሲሉ ራሳቸውን ለሞት በማቅረባቸው ከየትኛው ትእዛዝ ጋር የሚስማማ ተግባር ፈጽመዋል?
14 አቂላና ጵርስቅላ ለጳውሎስ ሲሉ ነፍሳቸውን ለሞት በማቅረባቸው ከሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስደዋል:- “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።” (ዮሐንስ 13:34) ይህ ትእዛዝ “አዲስ” የነበረው ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድን ከሚጠይቀው የሙሴ ሕግ አልፎ የሚሄድ በመሆኑ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:18) ኢየሱስ እንዳደረገው የራስን ሕይወት ለሌሎች እስከ መስጠት የሚያደርስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅርን የሚጠይቅ ነው። የሁለተኛውና የሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ አቆጣጠር ጸሐፊ የነበረው ተርቱሊያን ዓለማውያን ሰዎች ክርስቲያኖችን በተመለከተ እንደሚከተለው እያሉ ይናገሩ እንደነበረ ጽፏል:- “‘ተመልከቱ’ ይላሉ፣ ‘[ክርስቲያኖች] እንዴት እርስ በርሳቸው እንደሚዋደዱ . . . አንዱ ለሌላው ለመሞትም እንኳን ምን ያህል ዝግጁዎች እንደሆኑ [እዩ።]’” (አፖሎጂ ምዕራፍ 39 አንቀጽ 7) በተለይ ደግሞ ስደት ሲያጋጥም መሰል አማኞች በጭካኔ እንዲሰቃዩ ወይም እንዲሞቱ በጠላት እጅ አሳልፈን ላለመስጠት ነፍሳችንን ስለነፍሳቸው በድፍረት በማቅረብ የጠበቀ ወንድማዊ ፍቅርን ለማሳየት እንገደድ ይሆናል። — 1 ዮሐንስ 3:16
ድፍረት ደስታ ያመጣል
15, 16. በሥራ ምዕራፍ 16 ላይ እንደታየው ድፍረትና ደስታ ሊያያዙ የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ጳውሎስና ሲላስ በመከራ ጊዜ ድፍረት ማሳየት ደስታ ሊያመጣ እንደሚችል ማስረጃ ይሆኑናል። በፊልጵስዩስ ከተማ በሕዝባዊ ባለ ሥልጣኖች ትእዛዝ ባደባባይ በዱላ ተደብድበውና እሥር ቤት ገብተው በእግር ብረት ታስረው ነበር። ሆኖም በኀዘን ተቆራምደው በፍርሃት አልተሸማቀቁም። የሚፈትን ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ከአምላክ የሚሰጠው ድፍረትና ይህ ድፍረትም ለታማኝ ክርስቲያኖች የሚያመጣላቸው ደስታ በዚያም ወቅት ነበራቸው።
16 እኩለ ሌሊት አካባቢ ላይ ጳውሎስና ሲላስ ይጸልዩና አምላክን በመዝሙር ያወድሱ ነበር። በድንገትም የምድር መንቀጥቀጥ የእሥር ቤቱን መሠረት አናወጠውና እግር ብረቱ ተፈታላቸው፣ በሮቹም ተበረገዱ። በፍርሃት የተዋጠው ዘብ ጠባቂና ቤተሰቦቹ የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ወደመሆን ያደረሳቸው ምስክርነት በድፍረት ተሰጣቸው። እርሱ ራሱም “በእግዚአብሔር ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሴት አደረገ።” (ሥራ 16:16–34) ይህ ለጳውሎስና ለሲላስ እንዴት ያለ ደስታ አምጥቶላቸው መሆን አለበት! ይህንንና ሌሎችንም ቅዱስ ጽሑፋዊ የድፍረት ምሳሌዎችን በመመርመር የይሖዋ ደፋር አገልጋዮች ሆነን ለመቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
ደፋሮች በመሆን ቀጥሉ
17. በመዝሙር 27 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋን ተስፋ ማድረግ ከድፍረት ጋር የተገናኘው እንዴት ነው?
17 በይሖዋ ተስፋ ማድረግ ደፋሮች ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። ዳዊት “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፣ ልብህም ይጽና፤ [አዎን]፣ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 27:14) ዳዊት ይሖዋን የሕይወቱ “ጠንካራ ምሽግ [አዓት]” በማድረግ እንደተማመነበት መዝሙር 27 ያሳያል። (ቁጥር 1) ዳዊት ከዚያ በፊት ይሖዋ ጠላቶቹን ምን እንዳደረጋቸው ማየቱ ድፍረት ሰጥቶታል። (ቁጥር 2, 3) ድፍረት የሰጠው ሌላው ነገር ደግሞ ለይሖዋ የአምልኮ ሥፍራ የነበረው አድናቆት ነበር። (ቁጥር 4) በይሖዋ እርዳታ፣ ጥበቃና ማዳን መተማመንም የዳዊትን ድፍረት አሳድጎለታል። (ቁጥር ከ5–10) የይሖዋን የጽድቅ መንገዶች በሚገልጹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የማያቋርጥ መመሪያ ማግኘቱም ረድቶታል። (ቁጥር 11) ከጠላቶቹ እንዲያድነው በልበ ሙሉነት ይጸልይ የነበረ መሆኑ እምነትና ተስፋ ታክሎበት ዳዊትን ደፋር እንዲሆን ረድቶታል። (ቁጥር 12–14) እኛም በተመሳሳይ መንገዶች ድፍረታችንን ልናሳድግ እንችላለን። እንዲህ በማድረግም በእርግጥ ‘ይሖዋን ተስፋ እንደምናደርግ’ እናሳያለን።
18. (ሀ) ይሖዋን ከሚያመልኩት ጋር አዘውትሮ ጊዜ ማሳለፍ ደፋሮች ሆነን እንድንቀጥል እንደሚረዳን የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ድፍረትን ለማሳደግ ምን ሚና ይጫወታሉ?
18 ከመሰል የይሖዋ አምላኪዎች ጋር ዘወትር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ደፋሮች ሆነን እንድንቀጥል ሊረዳን ይቸላል። ጳውሎስ ለቄሣር ይግባኝ ብሎ ወደ ሮሜ በሄደ ጊዜ መሰል አማኞች አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ ይባሉ በነበሩት የገበያ ሥፍራዎች ተቀበሉት። “ጳውሎስ ባያቸው ጊዜ” ይለናል ታሪኩ፣ “እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።” (ሥራ 28:15) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አዘውትረን ስንገኝ ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ እናውላለን:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን [እንበረታታ (የ1980 ትርጉም )] እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:24, 25) እርስ በርስ መበረታታት ማለት ምን ማለት ነው? ማበረታታት ተብሎ የተተረጎመው ቱ ኢንካሬጅ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “የሌላውን ድፍረት፣ መንፈስ፣ ወይም ተስፋ ማነሳሳት” ማለት ነው። (ዌብስተርስ ናይንዝ ኮሌጂየት ዲክሽነሪ) የሌሎችን ክርስቲያኖች ድፍረት ለማነሳሳት ማድረግ የምንችለው ብዙ ነገር አለ። የእነርሱ ማበረታቻም እንደዚሁ ይህን ባሕሪ በውስጣችን ሊያሳድግልን ይችላል።
19. ቅዱሳን ጽሑፎችና ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ደፋሮች ሆነን ከመቀጠላችን ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?
19 ደፋሮች ሆነን ለመቀጠል የአምላክን ቃል አዘውትረን ማጥናትና ምክሩንም በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል አለብን። (ዘዳግም 31:9–12፤ ኢያሱ 1:8) ዘወትር የምናደርገው ጥናት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ማጥናትንም መጨመር ይኖርበታል፤ ምክንያቱም በዚህ መንገድ የቀረበልን ጥሩ ምክር የእምነት ፈተናዎችን አምላክ በሚሰጠን ድፍረት እንድንቋቋም ስለሚረዳን ነው። የይሖዋ አገልጋዮች በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር እንዴት ደፋሮች እንደነበሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ተመልክተናል። በአሁኑ ሰዓት እንዲህ ዓይነቱ ዕውቀት ምን ያህል ሊረዳን እንደሚችል ላናውቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ኃይል አለው፤ ከእርሱ የምንማረውም ነገር ምንጊዜም ሊጠቅመን ይችላል። (ዕብራውያን 4:12) ለምሳሌ ያህል ሰውን መፍራት አገልግሎታችንን ሊነካብን ከጀመረ ሄኖክ የአምላክን መልእክት ለአምላክ ደንታ ላልነበራቸው ሰዎች ለማድረስ ድፍረት እንዴት እንዳገኘ ልናስታውስ እንችላለን። — ይሁዳ 14, 15
20. የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን ደፋሮች ሆነን እንድንቀጥል ከተፈለገ ጸሎት የግድ አስፈላጊ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
20 የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን ደፋሮች ሆነን ለመቀጠል በጸሎት መጽናት አለብን። (ሮሜ 12:12) ኢየሱስ የደረሰበትን መከራ በድፍረት ችሎ የጸናበት ምክንያት “ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን [በማቅረቡና] እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ [ስለተሰማለት]” ነበር። (ዕብራውያን 5:7) በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ተቀራርበን በመኖር ትንሣኤ የሌለው “ሁለተኛ ሞት” እንደተጠበቀላቸው ፈሪዎች እንደሆኑት የዓለም ሰዎች አንሆንም። (ራእይ 21:8) መለኮታዊ ጥበቃና በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት የሚያገኙት ደፋር አገልጋዮቹ ናቸው።
21. የይሖዋ ታማኝ ምስክሮች ደፋሮች ሊሆኑ የሚችሉት ለምንድን ነው?
21 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን አጋንንታዊና ሰብአዊ ጠላቶችን መፍራት አያስፈልገንም። ምክንያቱም የአምላክን ድጋፍ ስለምናገኝና ኢየሱስ ዓለምን በማሸነፍ ረገድ የተወልን የደፋርነት ምሳሌ ስላለን ነው። ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር በመንፈሳዊ ገንቢ የሆነ ግንኙነት ማድረግም እንደዚሁ ደፋሮች እንድንሆን ይረዳናል። በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎችና ክርስቲያናዊ ጽሑፎች በሚሰጡት መመሪያና ምክር አማካኝነት ድፍረታችን ይገነባል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን የቀድሞዎቹ የአምላክ አገልጋዮች ታሪክም በመንገዶቹ በድፍረት እንድንመላለስ ይረዳናል። እንግዲያውስ በእነዚህ የመጨረሻ አስጨናቂ ቀኖች በቅዱስ አገልግሎታችን በድፍረት ወደፊት እንግፋ። አዎን፣ የይሖዋ ሕዝቦች ሁሉ ደፋሮች ሁኑ!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የኢየሱስ ምሳሌነት ድፍረት የሚያሳድርብን እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ድፍረት የሰጣቸው ምን ነበር?
◻ አይሁድና አረማውያን ከይሖዋ ጎን ለመሰለፍ ድፍረት ያስፈለጋቸው ለምን ነበር?
◻ ኤውንቄና ጢሞቴዎስ የድፍረት ምሳሌ የሆኑልን እንዴት ነው?
◻ በስደት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ድፍረት ደስታን እንደሚያመጣ ምን ማስረጃ አለ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅዱሳን ጽሑፎችን የምንሠራባቸውና የምንጠቅሳቸው ከሆነ እኛም እንደ ኢየሱስ ፈተናን ልንቋቋም እንችላለን