ምዕራፍ 14
የጉባኤውን ሰላምና ንጽሕና መጠበቅ
በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በየዓመቱ በርካታ ሰዎች የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ወደሆነው ወደ ይሖዋ ቤት እየጎረፉ ነው። (ሚክ. 4:1, 2) እነዚህ ሰዎች ወደ ‘አምላክ ጉባኤ’ በመምጣታቸው በጣም ደስተኞች ነን! (ሥራ 20:28) እነሱም ይሖዋን ከእኛ ጋር የማገልገል እንዲሁም ንጹሕ በሆነውና ሰላም በሰፈነበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የመኖር መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። የአምላክ ቅዱስ መንፈስና በቃሉ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ምክር የጉባኤውን ሰላምም ሆነ ንጽሕና ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል።—መዝ. 119:105፤ ዘካ. 4:6
2 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ “አዲሱን ስብዕና” እንለብሳለን። (ቆላ. 3:10) ቀላል ግጭቶችንና የግል አለመግባባቶችን ችላ ብለን እናልፋለን። ነገሮችን በይሖዋ ዓይን መመልከታችን፣ የሚከፋፍሉ ዓለማዊ ተጽዕኖዎችን እንድንቋቋም እንዲሁም በዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ በአንድነት ተባብረን እንድንሠራ ረድቶናል።—ሥራ 10:34, 35
3 ይሁን እንጂ የጉባኤውን ሰላምና አንድነት የሚያናጉ ችግሮች አልፎ አልፎ ሊከሰቱ ይችላሉ። የእነዚህ ችግሮች መንስኤ ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ አለማዋል ነው። ከሰብዓዊ አለፍጽምናችን ጋር የምናደርገው ትግል ገና አላበቃም። ከመካከላችን ኃጢአት የሌለበት ሰው የለም። (1 ዮሐ. 1:10) በመሆኑም አንድ ሰው በጉባኤው ላይ ሥነ ምግባራዊ ወይም መንፈሳዊ ርኩሰት ሊያስከትል የሚችል እርምጃ ሊወስድ ይችላል። በተጨማሪም በግድየለሽነት በተናገርነው ወይም ባደረግነው ነገር የተነሳ ሌሎችን ቅር ልናሰኝ ወይም እኛ ራሳችን ሌሎች ባደረጉት ወይም በተናገሩት ነገር ልንሰናከል እንችላለን። (ሮም 3:23) በዚህ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ምን ማድረግ እንችላለን?
4 አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ ያስገባል። ቃሉ ችግሮች ሲፈጠሩ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ ምክር ይዟል። አፍቃሪ የሆኑ መንፈሳዊ እረኞች ማለትም ሽማግሌዎች በግለሰብ ደረጃ ሊረዱን ይችላሉ። እነሱ የሚሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ከሌሎች ጋር የነበረንን ሰላማዊ ግንኙነት ልናድስና በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም ይዘን ልንቀጥል እንችላለን። መጥፎ ድርጊት በመፈጸማችን ምክንያት ተግሣጽ ወይም ወቀሳ ቢሰጠን እንዲህ ያለው እርማት በሰማይ የሚኖረው አባታችን ለእኛ ያለው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ምሳሌ 3:11, 12፤ ዕብ. 12:6
ቀላል አለመግባባቶችን መፍታት
5 በጉባኤው ውስጥ ባሉ ወንድሞችና እህቶች መካከል የግል ግጭቶች ወይም ቀላል አለመግባባቶች የሚከሰቱባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ችግሮች በወንድማማች ፍቅር ወዲያውኑ መፈታት አለባቸው። (ኤፌ. 4:26፤ ፊልጵ. 2:2-4፤ ቆላ. 3:12-14) በጉባኤው ውስጥ ካለ ሰው ጋር የተፈጠረ የግል አለመግባባት አብዛኛውን ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ “አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” በማለት የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል። (1 ጴጥ. 4:8) መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን” ይላል። (ያዕ. 3:2) ብዙውን ጊዜ፣ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው” የሚለውን ወርቃማ ሕግ ተግባራዊ በማድረግ የተፈጸሙብንን ቀላል በደሎች ይቅር ማለትና መርሳት እንችላለን።—ማቴ. 6:14, 15፤ 7:12
6 አንድ ሰው አንተ በተናገርከው ወይም ባደረግከው ነገር ቅር እንደተሰኘ ካስተዋልክ ሳትውል ሳታድር ቅድሚያውን ወስደህ እርቅ ለመፍጠር ጥረት አድርግ። ይህ ጉዳይ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድናም እንደሚነካብህ አስታውስ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል፦ “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።” (ማቴ. 5:23, 24) ምናልባትም በመካከላችሁ አለመግባባት የተፈጠረው በተሳሳተ መንገድ የተረዳችሁት ነገር ስላለ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ስለ ጉዳዩ መነጋገራችሁ አለመግባባቱን ለመፍታት ይረዳችኋል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ በነፃነት መነጋገራቸው አለመግባባቶችን ለማስወገድ እንዲሁም ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
አስፈላጊውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መስጠት
7 አንዳንድ ጊዜ የበላይ ተመልካቾች የአንድን ሰው አስተሳሰብ ለማስተካከል ምክር መስጠት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “ወንድሞች፣ አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።”—ገላ. 6:1
8 የበላይ ተመልካቾች ለመንጋው እረኝነት በማድረግ ጉባኤውን ከብዙ መንፈሳዊ አደጋዎች ሊታደጉ እንዲሁም ከባድ ችግሮች እንዳይከሰቱ ሊከላከሉ ይችላሉ። ሽማግሌዎች ጉባኤውን በሚያገለግሉበት ጊዜ ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል በገባው ቃል ላይ የተገለጸውን የሚከተለውን መሥፈርት አሟልተው ለመገኘት ጥረት ያደርጋሉ፦ “እያንዳንዱም ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ፣ ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት፣ በደረቅ ምድርም እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል።”—ኢሳ. 32:2
በሥርዓት በማይሄዱት ላይ ምልክት ማድረግ
9 ጳውሎስ በጉባኤው ላይ ጤናማ ያልሆነ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አንዳንድ ሰዎችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ጳውሎስ “በሥርዓት ከማይሄድና ከእኛ የተቀበላችሁትን ወግ ከማይከተል ማንኛውም ወንድም እንድትርቁ . . . እናዛችኋለን” ብሏል። ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በዚህ ደብዳቤ አማካኝነት ላስተላለፍነው ቃል የማይታዘዝ ሰው ቢኖር ይህን ሰው ምልክት አድርጉበት፤ ያፍርም ዘንድ ከእሱ ጋር አትግጠሙ። ይሁን እንጂ እንደ ጠላት አትመልከቱት፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ወንድም አጥብቃችሁ መምከራችሁን ቀጥሉ።”—2 ተሰ. 3:6, 14, 15
10 አንድ ክርስቲያን ሊያስወግድ የሚችል ከባድ ኃጢአት ባይሠራም አምላክ ክርስቲያኖች እንዲመሩበት ለሰጣቸው መሥፈርት ንቀት እንዳለው በግልጽ የሚያሳይ ድርጊት ይፈጽም ይሆናል። ይህም ከልክ በላይ ሰነፍ ወይም ነቃፊ መሆንን አሊያም አካላዊ ንጽሕናን አለመጠበቅን ሊያካትት ይችላል። ግለሰቡ ‘በማይመለከተው ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ’ ሊሆን ይችላል። (2 ተሰ. 3:11) አሊያም ደግሞ ከሌሎች ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት የሚሞክር ወይም ፈጽሞ ተቀባይነት በሌለው መዝናኛ የሚካፈል ሰው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ከሥርዓት ውጭ የሆነ ምግባር የጉባኤውን ስም ሊያጎድፍና ወደ ሌሎች ክርስቲያኖች ሊዛመት የሚችል እንደ ቀላል የማይታይ ጉዳይ ነው።
11 ሽማግሌዎች በሥርዓት የማይሄድን አንድ ክርስቲያን በመጀመሪያ ደረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር በመስጠት ሊረዱት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ግለሰቡ ተደጋጋሚ ምክር ቢሰጠውም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ማለቱን ከገፋበት ሽማግሌዎች ለጉባኤው የማስጠንቀቂያ ንግግር እንዲቀርብ ሊወስኑ ይችላሉ። ሽማግሌዎች ጉዳዩ የማስጠንቀቂያ ንግግር መስጠት እስኪያስፈልግ ድረስ ሌሎችን የሚረብሽ መሆን አለመሆኑን በጥንቃቄና በማስተዋል መወሰን ይኖርባቸዋል። ንግግር እንዲያቀርብ የተመደበው ወንድም ከሥርዓት ውጭ የሆነውን ምግባር በተመለከተ ተገቢውን ምክር ይሰጣል፤ ይሁንና በሥርዓት የማይመላለሰውን ግለሰብ ስም አይጠቀስም። በመሆኑም በንግግሩ ላይ የተጠቀሰውን ጉዳይ የሚያውቁ ክርስቲያኖች እንዲህ ካለው ግለሰብ ጋር ቅርርብ ከመፍጠር ይቆጠባሉ፤ ሆኖም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ግንኙነታቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን ግለሰቡን ‘እንደ ወንድም አጥብቀው ይመክሩታል።’
12 ታማኝ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች የሚወስዱት ጥብቅ አቋም በሥርዓት የማይሄደው ግለሰብ አካሄዱ እንዲያሳፍረውና ለውጥ ለማድረግ እንዲነሳሳ ይረዳው ይሆናል። ግለሰቡ አካሄዱን እንዳስተካከለ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ካለ ይህን ግለሰብ ምልክት እንደተደረገበት ሰው አድርጎ ማየቱ አስፈላጊ አይሆንም።
ከበድ ላሉ በደሎች እልባት መሻት
13 ቅር የተሰኘንበትን ነገር ለመተውና የበደለንን ሰው ይቅር ለማለት ፈቃደኞች እንሆናለን ሲባል ኃጢአትን አቅልለን እንመለከታለን ወይም ድርጊቱን እንቀበለዋለን ማለት አይደለም። መጥፎ ድርጊቶችን ሁሉ በወረስነው አለፍጽምና ማሳበብ አይቻልም፤ በተጨማሪም ከባድ በደሎችን ችላ ብሎ ማለፍ ተገቢ አይደለም። (ዘሌ. 19:17፤ መዝ. 141:5) የሕጉ ቃል ኪዳን አንዳንድ ኃጢአቶች ከሌሎች ኃጢአቶች የበለጠ ክብደት እንዳላቸው ያሳያል፤ ክርስቲያኖችም ይህን እውነታ ይገነዘባሉ።—1 ዮሐ. 5:16, 17
14 ኢየሱስ በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠሩ ከባድ ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ገልጿል። በቅደም ተከተል የዘረዘራቸውን እርምጃዎች ተመልከት፦ “ወንድምህ ቢበድልህ [1] አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው። ከሰማህ ወንድምህን ታተርፋለህ። የማይሰማህ ከሆነ ግን [2] ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ስለሚጸና አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ። እነሱንም ካልሰማ [3] ለጉባኤ ተናገር። ጉባኤውንም እንኳ የማይሰማ ከሆነ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ አድርገህ ቁጠረው።”—ማቴ. 18:15-17
15 በማቴዎስ 18:23-35 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረው ምሳሌ እንደሚጠቁመው በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የተጠቀሰው በደል ከገንዘብ ወይም ከንብረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለምሳሌ፣ የተበደሩትን ገንዘብ መልሶ አለመክፈልን ወይም ማጭበርበርን የሚመለከት ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ የተፈጸመው በደል የአንድን ሰው መልካም ስም የሚያጎድፍ ድርጊት ማለትም ስም ማጥፋት ሊሆን ይችላል።
16 በጉባኤው ውስጥ ያለ ሰው በአንተ ላይ እንዲህ ያለ ከባድ በደል እንደፈጸመብህ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ቢኖርህም እንኳ ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተው እንዲረዱህ ለመጠየቅ አትቸኩል። ኢየሱስ በሰጠው ምክር መሠረት በመጀመሪያ፣ በደል ፈጽሞብኛል የምትለውን ሰው አንተ ራስህ አነጋግረው። ሌላ ሰው በመካከላችሁ ሳይገባ ሁለታችሁ ብቻ ሆናችሁ ችግሩን ለመፍታት ሞክሩ። ኢየሱስ ‘አንድ ጊዜ ብቻ ሄደህ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው’ እንዳላለ አስታውስ። ስለዚህ ግለሰቡ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ካልጠየቀ በድጋሚ ለማነጋገር መሞከርህ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ችግሩ በዚህ መንገድ ከተፈታ በደል የፈጸመው ግለሰብ ስለ ድርጊቱ ለሌሎች ስላልተናገርክበት ወይም በጉባኤው ውስጥ ያለውን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነገር ስላላደረግክ አመስጋኝ መሆኑ አይቀርም። በዚህ መንገድ “ወንድምህን ታተርፋለህ።”
17 በደሉን የፈጸመው ሰው ጥፋቱን ካመነ፣ ይቅርታ ከጠየቀና ጥፋቱን ለማካካስ ጥረት ካደረገ ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ አይደለም። ምንም እንኳ የተፈጸመው በደል ከባድ ቢሆንም እንዲህ ያለውን በደል፣ የሚመለከታቸው ግለሰቦች ተነጋግረው ሊፈቱት ይችላሉ።
18 “አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ” ጥፋቱን በመንገር ወንድምህን ማትረፍ ካልቻልክ ኢየሱስ እንዳለው ‘አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ በመሄድ’ ወንድምህን እንደገና ልታነጋግረው ትችላለህ። የምትወስዳቸው ሰዎችም ዓላማቸው ወንድምህን ማትረፍ እንድትችል መርዳት መሆን ይኖርበታል። ተፈጽሟል ለተባለው ድርጊት የዓይን ምሥክር የሆኑ ሰዎችን ብትወስድ ይመረጣል፤ የዓይን ምሥክሮች ከሌሉ ግን ውይይታችሁን የሚከታተሉ አንድ ወይም ሁለት ምሥክሮች ይዘህ መሄድ ትችላለህ። በተለይ ደግሞ እነዚህ ሰዎች መፍትሔ የሚያሻውን ጉዳይ በተመለከተ ልምድ ያላቸው ከሆኑ በእርግጥ በደል ተፈጽሟል አልተፈጸመም የሚለውን መለየት ይችሉ ይሆናል። ምሥክር እንዲሆኑ የተመረጡት ሰዎች ሽማግሌዎች ከሆኑ ጉባኤውን እንደሚወክሉ ተደርገው መታየት የለባቸውም፤ ምክንያቱም ይህን እንዲያደርጉ የወከላቸው የሽማግሌዎች አካል አይደለም።
19 በመጀመሪያ ብቻህን ከዚያም አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ይዘህ ሄደህ ግለሰቡን በማነጋገር ችግሩን ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም ጉዳዩ መፍትሔ ሊያገኝ ካልቻለና አንተም ጉዳዩን እንዲሁ ልትተወው እንደማትችል ከተሰማህ ለጉባኤው የበላይ ተመልካቾች ማሳወቅ ይኖርብሃል። የእነሱም ዓላማ የጉባኤውን ሰላምና ንጽሕና መጠበቅ እንደሆነ አስታውስ። ሽማግሌዎቹን ካናገርክ በኋላ ጉዳዩን ለእነሱ መተውና በይሖዋ መታመን ይኖርብሃል። የአንድ ሰው ምግባር እንዲያደናቅፍህ ወይም በይሖዋ አገልግሎት የምታገኘውን ደስታ እንዲያሳጣህ ፈጽሞ አትፍቀድ።—መዝ. 119:165
20 የመንጋው እረኞች ጉዳዩን ያጣራሉ። ግለሰቡ በአንተ ላይ ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመና ንስሐ እንዳልገባ እንዲሁም ምክንያታዊ የሆነና አግባብነት ያለው ማካካሻ ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በግልጽ ከተረጋገጠ የተወሰኑ የበላይ ተመልካቾችን ያቀፈ አንድ ኮሚቴ ጥፋተኛው ከጉባኤ እንዲወገድ ሊወስን ይችላል። በዚህ መንገድ ሽማግሌዎች መንጋውን ከአደጋ የሚታደጉ ከመሆኑም በላይ የጉባኤውን ንጽሕና ይጠብቃሉ።—ማቴ. 18:17
ከባድ ኃጢአት ሲፈጸም ጉዳዩ የሚታይበት መንገድ
21 እንደ ፆታ ብልግና፣ ምንዝር፣ ግብረ ሰዶም፣ አምላክን መሳደብ፣ ክህደትና ጣዖት አምልኮ ያሉ ከባድ ኃጢአቶች የተበደለው ግለሰብ ይቅር በማለቱ ብቻ የሚያበቁ ጉዳዮች አይደሉም። (1 ቆሮ. 6:9, 10፤ ገላ. 5:19-21) እንዲህ ያሉት ኃጢአቶች በጉባኤው መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ላይ አደጋ ስለሚያስከትሉ እነዚህን ኃጢአቶች ለሽማግሌዎች መናገርና እነሱ እንዲይዟቸው ማድረግ ይገባል። (1 ቆሮ. 5:6፤ ያዕ. 5:14, 15) አንዳንድ ግለሰቦች ወደ ሽማግሌዎች ቀርበው ኃጢአታቸውን ሊናዘዙ ወይም ሌሎች ስለሠሩት ኃጢአት የሚያውቁትን ነገር ሊናገሩ ይችላሉ። (ዘሌ. 5:1፤ ያዕ. 5:16) ሽማግሌዎቹ አንድ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ስለፈጸመው ከባድ ኃጢአት የሰሙበት መንገድ ምንም ይሁን ምን በመጀመሪያ ሁለት ሽማግሌዎች ጉዳዩን እንዲያጣሩ መደረግ አለበት። ሪፖርት የተደረገው ነገር ተጨባጭ መሠረት ያለው ከሆነና ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከተገኘ የጉባኤው የሽማግሌዎች አካል ጉዳዩን የሚያይ ቢያንስ ሦስት ሽማግሌዎችን ያቀፈ የፍርድ ኮሚቴ ያቋቁማል።
22 ሽማግሌዎቹ መንጋውን በመንፈሳዊ ሊጎዱ ከሚችሉ ነገሮች ለመጠበቅ በንቃት ይከታተላሉ። በተጨማሪም የአምላክን ቃል በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም ስህተት የሠራውን ሰው ለመገሠጽና በመንፈሳዊ እንዲያገግም ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። (ይሁዳ 21-23) ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በመጻፍ ለጢሞቴዎስ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚስማማ ነው፦ “በአምላክ ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ላይ በሚፈርደው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አጥብቄ አሳስብሃለሁ፤ . . . በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ውቀስ፣ ገሥጽ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር።” (2 ጢሞ. 4:1, 2) እንዲህ ማድረግ ጊዜን መሠዋት የሚጠይቅ ቢሆንም ሽማግሌዎች በትጋት እንዲያከናውኑ ከሚጠበቅባቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ነው። ጉባኤው ሥራቸውን የሚያደንቅ ከመሆኑም በላይ “እጥፍ ክብር [ይሰጣቸዋል]።”—1 ጢሞ. 5:17
23 አንድ ግለሰብ ኃጢአት እንደፈጸመ ቢረጋገጥም እንኳ ምንጊዜም ቢሆን የሽማግሌዎቹ ዋነኛ ዓላማ ግለሰቡ በመንፈሳዊ እንዲያገግም መርዳት ነው። ግለሰቡ ከልቡ ንስሐ ከገባና ሽማግሌዎች ሊረዱት የሚችሉ ከሆነ ለብቻው ወይም የፍርድ ጉዳዩ በተሰማበት ወቅት ለምሥክርነት በተገኙት ሰዎች ፊት ወቀሳ ይሰጡታል፤ ይህም ግለሰቡን ለመገሠጽና ጉዳዩን የሚያውቁት ሰዎች ጤናማ ፍርሃት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ያስችላል። (2 ሳሙ. 12:13፤ 1 ጢሞ. 5:20) ምንጊዜም ቢሆን አንድ ሰው በፍርድ ኮሚቴ ወቀሳ ከተሰጠው እገዳዎች ይጣሉበታል። ይህም ኃጢአት የሠራው ግለሰብ ለወደፊቱ እግሩ “ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ” ለማድረግ ሊረዳው ይችላል። (ዕብ. 12:13) ግለሰቡ በመንፈሳዊ ማገገሙ በግልጽ እየታየ ሲመጣ ቀስ በቀስ እገዳዎቹ ይነሱለታል።
ወቀሳን የሚመለከት ማስታወቂያ
24 የፍርድ ኮሚቴው ግለሰቡ ንስሐ ገብቷል ብሎ ቢወስንም ጉዳዩ በጉባኤው ወይም በማኅበረሰቡ ዘንድ መታወቁ የማይቀር ከሆነ አሊያም የጉባኤው አስፋፊዎች ንስሐ ከገባው ኃጢአተኛ ጋር ባላቸው ግንኙነት ጠንቃቃ እንዲሆኑ ማስጠንቀቅ ካስፈለገ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ አጭር ማስታወቂያ እንዲነገር ይደረጋል። ማስታወቂያው “[እገሌ] ወቀሳ ተሰጥቶታል” የሚል ይሆናል።
ውሳኔው ውገዳ በሚሆንበት ጊዜ
25 አንዳንድ ጊዜ ግለሰቡ የኃጢአት ድርጊቱን ልማድ ሊያደርገውና እሱን ለመርዳት ለሚደረገው ጥረት በጎ ምላሽ ላይሰጥ ይችላል። የፍርድ ኮሚቴው ጉዳዩን በሰማበት ወቅት ግለሰቡ “ለንስሐ የሚገባ ሥራ” እንደሠራ በበቂ መጠን አላሳየ ይሆናል። (ሥራ 26:20) ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ይደረጋል? ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆነውን ኃጢአተኛ ከጉባኤው በማስወገድ ንጹሕ ከሆነው የይሖዋ ሕዝብ ጋር እንዳይቀላቀል ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም ግለሰቡ በጉባኤው ላይ መጥፎ ተጽዕኖ እንዳያሳድር፣ የጉባኤው ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እንዲሁም የጉባኤው መልካም ስም እንዳይጎድፍ ያደርጋል። (ዘዳ. 21:20, 21፤ 22:23, 24) ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ያለ ሰው አሳፋሪ ድርጊት እንደፈጸመ በሰማ ጊዜ ሽማግሌዎቹን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል፦ “እንዲህ ያለውን ሰው ለሰይጣን አሳልፋችሁ ልትሰጡት ይገባል፤ ይህም . . . የጉባኤው መንፈስ በጌታ ቀን ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል [ያስችላል]።” (1 ቆሮ. 5:5, 11-13) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በእውነት ላይ በማመፃቸው ከጉባኤው ስለተወገዱ ሌሎች ሰዎችም ገልጿል።—1 ጢሞ. 1:20
26 አንድ ንስሐ ያልገባ ኃጢአተኛ መወገድ እንዳለበት በሚወሰንበት ጊዜ የፍርድ ኮሚቴው የውገዳ እርምጃ የተወሰደበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት(ቶች) በግልጽ በመንገር ውሳኔውን ለግለሰቡ ሊያሳውቀው ይገባል። የፍርድ ኮሚቴው ውሳኔውን ለግለሰቡ በሚያሳውቅበት ጊዜ ግለሰቡ በፍርዱ ላይ ከባድ ስህተት ተፈጽሟል ብሎ የሚያምንና ይግባኝ መጠየቅ የሚፈልግ ከሆነ ምክንያቶቹን በግልጽ በማስፈር ይግባኙን በደብዳቤ ማቅረብ እንዳለበት ይነግረዋል። ግለሰቡ የኮሚቴውን ውሳኔ ከሰማበት ጊዜ አንስቶ በሰባት ቀን ውስጥ ይግባኝ መጠየቅ ይችላል። የሽማግሌዎች አካል የይግባኝ ጥያቄው ሲደርሰው የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ያነጋግራል፤ የወረዳ የበላይ ተመልካቹም ጉዳዩን እንደገና የሚሰሙ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች መርጦ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያቋቁማል። ሽማግሌዎቹ ደብዳቤው ከደረሳቸው ዕለት አንስቶ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይግባኙን ለመስማት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይግባኝ ከተጠየቀ የውገዳ ማስታወቂያው ለሌላ ጊዜ ይተላለፋል። እስከዚያው ድረስ ግን ክስ የተመሠረተበት ሰው በስብሰባ ላይ ሐሳብ ከመስጠትም ሆነ ከመጸለይ እንዲሁም በሌሎች መብቶች ከማገልገል ይታገዳል።
27 ግለሰቡ ይግባኝ ማለት የሚችልበት ዝግጅት መደረጉ አሳቢነትን የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ግለሰቡ ሐሳቡን መግለጽ የሚችልበት ተጨማሪ አጋጣሚ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ይሁንና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ጉዳዩን ለመስማት በሚሰበሰብበት ወቅት ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ሆን ብሎ በቀጠሮው ካልተገኘ እሱን ለማግኘት ተገቢው ጥረት ከተደረገ በኋላ የውገዳ ማስታወቂያው ይነገራል።
28 ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ይግባኝ መጠየቅ ካልፈለገ የፍርድ ኮሚቴው ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነት እንዲሁም ወደፊት ውገዳው እንዲነሳለት ከፈለገ ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችል ይገልጽለታል። ይህ ጠቃሚና ደግነት የሚንጸባረቅበት ዝግጅት እንደመሆኑ መጠን ሽማግሌዎች ግለሰቡ ወደፊት አካሄዱን አስተካክሎ ወደ ይሖዋ ድርጅት ለመመለስ ብቁ ይሆናል የሚል መንፈስ ይዘው ሊያነጋግሩት ይገባል።—2 ቆሮ. 2:6, 7
የውገዳ ማስታወቂያ
29 ንስሐ ያልገባን አንድ ኃጢአተኛ ከጉባኤው ማስወገድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ “[እገሌ] ከእንግዲህ የይሖዋ ምሥክር አይደለም” የሚል አጭር ማስታወቂያ ይነበባል። ማስታወቂያው መነገሩ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ታማኝ ክርስቲያኖች ከግለሰቡ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንዲያቆሙ ያደርጋቸዋል።—1 ቆሮ. 5:11
ራስን ማግለል
30 “ራስን ማግለል” የሚለው አገላለጽ አንድ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ሆን ብሎ ክርስቲያናዊ አቋሙን በመካድና ከዚህ በኋላ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደማይፈልግ በመግለጽ የሚወስደውን እርምጃ ያመለክታል። አንድ ሰው በሚያደርገውም ነገር የክርስቲያን ጉባኤ ክፍል መሆን እንደማይፈልግ ሊያሳይ ይችላል፤ ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት የሚጻረር ዓላማ በማራመዱ ምክንያት ይሖዋ አምላክ ጥፋት የፈረደበት አንድ ዓለማዊ ድርጅት ክፍል ሊሆን ይችላል።—ኢሳ. 2:4፤ ራእይ 19:17-21
31 ሐዋርያው ዮሐንስ እሱ በነበረበት ዘመን ክርስቲያናዊ እምነታቸውን ስለካዱ ሰዎች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “በእኛ መካከል ነበሩ፤ ሆኖም ከእኛ ወገን ስላልነበሩ ትተውን ሄደዋል። ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር።”—1 ዮሐ. 2:19
32 ይሖዋ፣ ራሱን ያገለለን ግለሰብ የሚያይበት መንገድ የቀዘቀዘን ማለትም በመስክ አገልግሎት መካፈል ያቆመን ክርስቲያን ከሚያይበት መንገድ ፈጽሞ የተለየ ነው። አንድ ሰው የሚቀዘቅዘው የአምላክን ቃል አዘውትሮ ባለማጥናቱ ሊሆን ይችላል። ወይም ባጋጠሙት የግል ችግሮች አሊያም በደረሰበት ስደት ሳቢያ ለይሖዋ አገልግሎት የነበረው ቅንዓት ጠፍቶ ይሆናል። ሽማግሌዎችም ሆኑ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች አንድን የቀዘቀዘ ክርስቲያን ለመርዳት ሲሉ አስፈላጊውን መንፈሳዊ ድጋፍ መስጠታቸውን ይቀጥላሉ።—ሮም 15:1፤ 1 ተሰ. 5:14፤ ዕብ. 12:12
33 በአንጻሩ ግን ክርስቲያን የሆነ አንድ ሰው ራሱን ለማግለል ከመረጠ “[እገሌ] ከእንግዲህ የይሖዋ ምሥክር አይደለም” የሚል አጭር ማስታወቂያ ለጉባኤው ይነበባል። እንዲህ ያለው ግለሰብ የሚታየው ልክ እንደተወገደ ሰው ነው።
ውገዳ ማንሳት
34 አንድ የተወገደ ወይም ራሱን ከጉባኤ ያገለለ ግለሰብ የውገዳ ውሳኔው ተነስቶለት ወደ ጉባኤው መመለስ የሚችለው ንስሐ መግባቱን በግልጽ ሲያሳይና የኃጢአት መንገዱን እንደተወ ምክንያታዊ በሆነ የጊዜ ርዝመት ሲያረጋግጥ ነው። ግለሰቡ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረው እንደሚፈልግ ማሳየት ይኖርበታል። ሽማግሌዎቹ ግለሰቡ ከልብ ንስሐ መግባቱን ማረጋገጥ እንዲችሉ በቂ ጊዜ እንዲያልፍ መፍቀድ ይኖርባቸዋል፤ ይህ የጊዜ ርዝመት እንደ ሁኔታው ሊለያይ የሚችል ሲሆን በርከት ያሉ ወራት፣ አንድ ዓመት አሊያም ከዚያ የበለጠ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። አንድ ግለሰብ ውገዳው እንዲነሳለት ለሽማግሌዎች አካል በደብዳቤ ጥያቄ ሲያቀርብ ውገዳ አንሺ ኮሚቴ ግለሰቡን እንዲያነጋግረው ይደረጋል። ኮሚቴው፣ ግለሰቡ “ለንስሐ የሚገባ ሥራ” ማሳየቱን ካመዛዘነ በኋላ፣ በዚህ ጊዜ ውገዳው ሊነሳለት ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን ጉዳይ ይወስናል።—ሥራ 26:20
35 ውገዳው እንዲነሳለት ጥያቄ ያቀረበው ግለሰብ የተወገደው በሌላ ጉባኤ ከሆነ አሁን ያለበት ጉባኤ ውገዳ አንሺ ኮሚቴ ከግለሰቡ ጋር ተገናኝቶ ጉዳዩን ያያል። አሁን ባለበት ጉባኤ ውስጥ ያለው የውገዳ አንሺ ኮሚቴ አባላት ግለሰቡ ውገዳው ሊነሳለት ይገባል ብለው ካመኑ ጉዳዩን መጀመሪያ ላየው ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል የድጋፍ ሐሳብ ይልካሉ። ሁለቱም ኮሚቴዎች ትክክለኛው ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ለማሰባሰብ ተባብረው መሥራት ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ እንዲመለስ የሚወስነው ጉዳዩን መጀመሪያ ባየው ጉባኤ ውስጥ ያለው ውገዳ አንሺ ኮሚቴ ነው።
ውገዳ መነሳቱን የሚገልጽ ማስታወቂያ
36 ውገዳ አንሺ ኮሚቴው የተወገደው ወይም ራሱን ያገለለው ሰው ልባዊ ንስሐ እንደገባ ካመነበትና ውገዳው ሊነሳለት ይገባል ብሎ ከወሰነ ይህን የሚገልጽ ማስታወቂያ የግለሰቡ ጉዳይ በተያዘበት ጉባኤ ይነበባል። በወቅቱ ግለሰቡ የሚገኘው በሌላ ጉባኤ ከሆነ በዚያም ማስታወቂያው ሊነበብ ይገባል። ማስታወቂያው በአጭሩ “[እገሌ] ተመልሶ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል” የሚል መሆን ይኖርበታል።
ለአካለ መጠን ያልደረሱ የተጠመቁ ልጆችን የሚመለከቱ የፍርድ ጉዳዮች
37 ለአካለ መጠን ያልደረሰ የተጠመቀ ልጅ ከባድ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች ማሳወቅ ያስፈልጋል። ሽማግሌዎች ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ የፈጸመውን ከባድ ኃጢአት በሚያዩበት ጊዜ የልጁ የተጠመቁ ወላጆች በቦታው ቢገኙ ይመረጣል። ወላጆቹ ጥፋት የሠራው ልጅ አስፈላጊው ተግሣጽ እንዳይሰጠው ለመከላከል ጥረት ከማድረግ ይልቅ ከፍርድ ኮሚቴው ጋር ተባብረው መሥራት ይኖርባቸዋል። የፍርድ ኮሚቴው አንድ አዋቂ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ ጥፋት የሠራውን ልጅ ለማረምና ለማስተካከል ጥረት ያደርጋል። ያም ሆኖ ልጁ ንስሐ ካልገባ የውገዳ እርምጃ ይወሰዳል።
ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ
38 ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ከባድ ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ ምን መደረግ ይኖርበታል? የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ስላልሆኑ ከጉባኤው ሊወገዱ አይችሉም። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በተመለከተ የተሟላ ግንዛቤ ላይኖራቸው ስለሚችል በደግነት የሚሰጣቸው ምክር ለእግራቸው ‘ቀና የሆነ መንገድ’ እንዲያበጁ ሊረዳቸው ይችላል።—ዕብ. 12:13
39 ኃጢአት የሠራ አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሁለት ሽማግሌዎች ካነጋገሩትና እሱን ለመርዳት ጥረት ካደረጉ በኋላም ንስሐ የማይገባ ከሆነ ለጉባኤው ማስታወቂያ መነገር ይኖርበታል። “[እገሌ] ከእንግዲህ ያልተጠመቀ አስፋፊ አይደለም” የሚል አጭር ማስታወቂያ ይነበባል። ከዚያ በኋላ ጉባኤው ግለሰቡን እንደ ዓለማዊ ሰው ይቆጥረዋል። ግለሰቡ ባይወገድም እንኳ ክርስቲያኖች ከእሱ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት በተመለከተ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። (1 ቆሮ. 15:33) በተጨማሪም ግለሰቡ የመስክ አገልግሎት ሪፖርት መመለስ አይችልም።
40 የአስፋፊነት መብቱን ያጣ አንድ ያልተጠመቀ ግለሰብ ዳግመኛ አስፋፊ መሆን ይፈልግ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሁለት ሽማግሌዎች ግለሰቡን በማነጋገር መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አለማድረጉን ለማጣራት ይሞክራሉ። ብቃቱን የሚያሟላ ከሆነ “[እገሌ] ዳግመኛ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኗል” የሚል አጭር ማስታወቂያ ይነበባል።
ይሖዋ ንጹሕና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያመልኩትን ሰዎች ይባርካል
41 በዛሬው ጊዜ በአምላክ ጉባኤ ውስጥ የታቀፉ ሁሉ ይሖዋ ለሕዝቡ በሰጠው የበለጸገ መንፈሳዊ ርስት ሊደሰቱ ይችላሉ። መንፈሳዊው የግጦሽ መስካችን እጅግ የለመለመ ነው፤ ደግሞም መንፈስን የሚያድስ የእውነት ውኃ በገፍ አግኝተናል። በተጨማሪም ይሖዋ በክርስቶስ ራስነት ሥር ባለው ቲኦክራሲያዊ ዝግጅት አማካኝነት ጥበቃ አድርጎልናል። (መዝ. 23፤ ኢሳ. 32:1, 2) ሁከት በነገሠበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ መሆናችን ደህንነት እንዲሰማን አድርጓል።
የጉባኤውን ሰላምና ንጽሕና በመጠበቅ የመንግሥቱን የእውነት ብርሃን ማብራታችንን እንቀጥላለን
42 የጉባኤውን ሰላምና ንጽሕና በመጠበቅ የመንግሥቱን የእውነት ብርሃን ማብራታችንን እንቀጥላለን። (ማቴ. 5:16፤ ያዕ. 3:18) አምላክ በሚሰጠን በረከት ብዙ ሰዎች ይሖዋን ሲያውቁና ፈቃዱን በማድረግ ከጎናችን ሲሰለፉ የማየት አጋጣሚ እናገኛለን።