ይቅር የምትሉት እንደ ይሖዋ ነውን?
“ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፣ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።”—ማቴዎስ 6:14, 15
1, 2. ምን ዓይነት አምላክ እንዲኖረን እንፈልጋለን? ለምንስ?
“እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ሁል ጊዜም አይቀሥፍም፣ ለዘላለምም አይቆጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ [አፈር መሆናችንንም ያስታውሳል የ1980 ትርጉም]።”—መዝሙር 103:8–14
2 ሁል ጊዜ ለኃጢአት ሕግ ምርኮኛ እንድንሆን የሚገፋፋንን ከዘር የወረስነውን አለፍጽምና ጨምሮ በኃጢአት የተፀነስንና ከኃጢአት ጋር የተወለድን በመሆናችን ‘ከአፈር የተሠራን መሆናችንን የሚያስታውስ’ አምላክ በጣም እንፈልጋለን። ዳዊት በ103ኛው መዝሙር ላይ ይሖዋን እጅግ ማራኪ በሆነ መንገድ ከገለጸው ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሚክያስ አንዴ የተፈጸሙ ኃጢአቶችን ይቅር የሚል በመሆኑ ይህንኑ አምላክ በጣም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ አወድሶታል፦ “በደልን ይቅር የሚል፣ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቁጣውን ለዘላለም አይጠብቅም። ተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፣ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል።”—ሚክያስ 7:18, 19
3. ይቅር ማለት ምን ማለት ነው?
3 በግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ይቅር ማለት” ለሚለው የገባው ቃል “መተው” ማለት ነው። ከላይ የተጠቀሱት ዳዊትና ሚክያስ ይህንኑ ትርጉም ባማሩና ገላጭ በሆኑ ቃላት እንዳስቀመጡት ልብ በሉ። የይሖዋ ይቅር ባይነት ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ መገንዘብ እንድንችል ይቅር ባይነቱ በተግባር ከታየባቸው ብዙ ምሳሌዎች መካከል ጥቂቶቹን መለስ ብለን እንቃኛቸው። የመጀመሪያው ምሳሌ የይሖዋ አእምሮ ሊወስደው ያሰበውን የማጥፋት እርምጃ በመተው ወደ ይቅር ባይነት ሊለወጥ እንደሚችል ያሳያል።
ሙሴ ለሕዝቡ ማለደ፤ ይሖዋም ሰማው
4. እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት የፈሩት የትኞቹን የይሖዋ ኃይል የተገለጠባቸውን ትዕይንቶች ካዩም በኋላ ነበር?
4 ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ ደህንነታቸውን ጠብቆ ከግብፅ በማውጣት መኖሪያ ይሆናችኋል ብሎ ቃል ወደ ገባላቸው ምድር አቅራቢያ አደረሳቸው። እነርሱ ግን በከንዓን የነበሩትን ተራ ሰዎች በመፍራታቸው እግራችንን አናነሣም አሉ። ይሖዋ አውዳሚ የሆኑ አሥር መቅሰፍቶችን በማዝነብ ከግብፅ ሲያድናቸው፣ ቀይ ባሕርን ሰንጥቆ ማምለጥ የሚችሉበትን መንገድ ሲከፍትላቸው፣ ሊከተሏቸው የሞከሩትን የግብፃውያን ሠራዊት ሲደመስስ፣ የይሖዋ የተመረጡ ሕዝብ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን የሕጉን ቃል ኪዳን በሲና ተራራ ላይ ሲያቋቁምላቸውና እነርሱን ለመመገብ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በየዕለቱ ከሰማይ መናን ሲያዘንብላቸው ያዩ ሰዎች አንዳንድ ግዙፍ ከነዓናውያንን በመፍራት ወደ ተስፋይቱ ምድር አንገባም አሉ!—ዘኁልቁ 14:1–4
5. ሁለት ታማኝ ሰላዮች የእስራኤልን ሕዝብ ለማደፋፈር የሞከሩት እንዴት ነበር?
5 ሙሴና አሮን የሕዝቡ አድራጎት አሳፈራቸው፤ ምን እንደሚያደርጉም ግራ ገባቸው። ሁለቱ ታማኝ ሰላዮች፣ ኢያሱና ካሌብ ‘ምድሪቱ እጅግ መልካም ናት። ወተትና ማር የምታፈስስ ምድር ናት። ይሖዋ ከእኛ ጋር ነውና አትፍሩ!’ በማለት የእስራኤልን ሕዝብ ለማደፋፈር ሞከሩ። በእነዚህ ቃላት እንደመበረታታት በፍርሃት የተሸበሩት ዓመፀኛ ሰዎች ኢያሱንና ካሌብን በድንጋይ ለመውገር አሰቡ።—ዘኁልቁ 14:5–10
6, 7. (ሀ) የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመጓዝ አሻፈረኝ ባለ ጊዜ ይሖዋ ምን ለማድረግ ወስኖ ነበር? (ለ) ሙሴ ይሖዋ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የበየነውን ፍርድ የተቃወመው ለምንድን ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
6 ይሖዋ እጅግ ተቆጣ! “እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምንብኝም? ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተንም ከእነርሱ ለሚበዛና ለሚጠነክር ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፦ ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤ ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። . . . ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ፦ እግዚአብሔር ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው ብለው ይናገራሉ።”—ዘኁልቁ 14:11–16
7 ሙሴ ለይሖዋ ስም ሲል ይቅር እንዲላቸው ተማጽኗል፦ “ይህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፣ እባክህ፣ እንደ ምሕረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል። እግዚአብሔርም አለ፦ እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ።”—ዘኁልቁ 14:19, 20
የምናሴ የጣዖት አምልኮና ዳዊት የፈጸመው ምንዝር
8. የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ምናሴ ምን ዓይነት ታሪክ ሠርቷል?
8 የይሖዋ ይቅር ባይነት በግልጽ የተንጸባረቀበት ጉልህ ምሳሌ የመልካሙ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ በሆነው በምናሴ ላይ የታየው ሁኔታ ነው። ምናሴ በኢየሩሳሌም ላይ መግዛት ሲጀምር 12 ዓመቱ ነበር። የኮረብታ መስገጃዎችን ሠራ፤ ለበአሊም መሠዊያ አቆመ፤ የማምለኪያ ዐፀዶችን ተከለ፤ ለሰማይ ከዋክብትም ሰገደ፤ ሞራ ገላጭ ሆነ፤ አስማታዊ ድርጊት መፈጸም ጀመረ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ሰበሰበ፤ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የተቀረጸ ምስል ተከለ፤ በሄኖምም ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት አሳለፈ። “እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ።”—2 ዜና መዋዕል 33:1–9
9. ይሖዋ ፊቱ ለምናሴ የተፈታው እንዴት ነበር? ምን ውጤትስ ተገኘ?
9 በመጨረሻ ይሖዋ አሦራውያን ይሁዳን እንዲወሯት አደረገ፤ እነርሱም ምናሴን ያዙትና ወደ ባቢሎን ወሰዱት። “በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፣ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ። ወደ እርሱም ጸለየ፤ እርሱም ተለመነው፣ ጸሎቱንም ሰማው፣ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው።” (2 ዜና መዋዕል 33:11–13) ከዚያ በኋላ ምናሴ እንግዶቹን አማልክት፣ ጣዖታቱንና መሠዊያዎቹን አስወገደ፤ ከከተማይቱም ውጭ ጣላቸው። በይሖዋ መሠዊያ ላይ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ጀመረ፤ የይሁዳ ሰዎችም እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልኩ አደረገ። ይህ ሁኔታ ትሕትና፣ ጸሎትና የተፈጸሙትን ስሕተቶች ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት ለንስሐ የሚገቡ ፍሬዎችን በሚያፈሩበት ጊዜ ይሖዋ ይቅር ለማለት ያለውን ፈቃደኝነት የሚያሳይ አስገራሚ ትዕይንት ነው!—2 ዜና መዋዕል 33:15, 16
10. ዳዊት ከኦርዮ ሚስት ጋር የፈጸመውን ኃጢአት ለመሸፋፈን የሞከረው እንዴት ነው?
10 ንጉሥ ዳዊት ከኬጤያዊው ኦርዮ ሚስት ጋር የፈጸመው የምንዝር ኃጢአት በብዙዎች ዘንድ በደንብ የታወቀ ታሪክ ነው። ዳዊት ከእርሷ ጋር ምንዝር በመፈጸም አላበቃም። በፀነሰች ጊዜም ድርጊቱን ለመሸፈን አንድ የረቀቀ ውጥን አዘጋጅቶ ነበር። ወደ ቤቱ ሄዶ ከባለቤቱ ጋር የፆታ ግንኙነት ይፈጽማል ብሎ በማሰብ ኦርዮ ከጦር ግንባር እንዲመለስ ንጉሡ ፈቃድ ሰጠው። ሆኖም ኦርዮ በውጊያ ግንባር ለነበሩት እሱን መሰል ለሆኑት ወታደሮች በነበረው አክብሮት የተነሣ ወደ ቤቱ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያ በኋላ ዳዊት እንዲበላና ጠጥቶ እንዲሰክር ኦርዮን ጋበዘው። ያም ሆኖ ግን ኦርዮ ወደ ባለቤቱ አልሄደም። ከዚህ በኋላ ዳዊት ኦርዮ እንዲገደል የተጧጧፈ ውጊያ በሚካሄድበት ቦታ ላይ እንዲያሰልፈው ለጄኔራሉ መልእክት ላከለት። የተፈጸመውም ሁኔታ ይኸው ነበር።—2 ሳሙኤል 11:2–25
11. ዳዊት ለፈጸመው ኃጢአት ንስሐ ሊገባ የቻለው እንዴት ነው? ሆኖም ምን መከራ ደርሶበታል?
11 የንጉሡን ኃጢአት እንዲያጋልጥ ይሖዋ ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው። “ዳዊትም ናታንን፦ እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትም” አለው። (2 ሳሙኤል 12:13) ዳዊት በፈጸመው ኃጢአት ከባድ የጥፋተኛነት ስሜት ተሰምቶት ነበር። ንስሐ መግባቱንም ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ገልጿል፦ “መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” (መዝሙር 51:16, 17) ዳዊት በተሰበረ ልብ ያቀረበውን ጸሎት ይሖዋ አልናቀውም። ያም ሆኖ ግን በዘጸአት 34:6, 7 [አዓት] ላይ ከሰፈረው “ከመቅጣት ወደ ኋላ አይልም” ከሚለው የይሖዋ ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ዳዊት ከባድ ቅጣት ተቀብሏል።
ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሲመርቅ
12. ሰሎሞን በቤተ መቅደሱ ምረቃ ወቅት ምን ጠየቀ? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠ?
12 ሰሎሞን የይሖዋን ቤተ መቅደስ ግንባታ ሲጨርስ በምረቃው ወቅት ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።” ይሖዋ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፣ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፣ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፣ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፣ ፊቴንም ቢፈልጉ፣ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፣ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፣ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፣ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።”—2 ዜና መዋዕል 6:21፤ 7:13, 14
13. ይሖዋ ለሰው ስላለው አመለካከት ሕዝቅኤል 33:13–16 ምን ያሳያል?
13 ይሖዋ ወደ እናንተ በሚመለከትበት ጊዜ የሚቀበላችሁ አሁን ባላችሁ አቋም እንጂ ቀደም ሲል በነበራችሁ አቋም አይደለም። ሕዝቅኤል 33:13–16 እንደሚለው ይሆናል ማለት ነው፦ “እኔ ጻድቁን፦ በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፣ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። እኔም ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፣ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፣ ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፣ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።”
14. የይሖዋን ይቅር ባይነት ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?
14 ይሖዋ አምላክ የሚያሳየን ይቅር ባይነት ለየት ያለ ገጽታ አለው። ይሖዋ ይቅር ይላል፤ እንዲሁም በደሉን ይረሳዋል። ሰብዓዊ ፍጥረታት አንዳቸው ሌላውን ይቅር በሚሉበት ጊዜ ይህን ነገር ማድረግ በጣም ይቸግራቸዋል። አንዳንድ ሰዎች ‘ይቅር ልልህ እችላለሁ፤ የሠራኸኝን ሥራ ግን ልረሳው አልችልም (ወይም መቼም አልረሳውም)’ ይላሉ። በአንጻሩ ይሖዋ ምን እንደሚያደርግ የተናገረውን ልብ በሉ፦ “በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና [አላስታውሰውም አዓት።]”—ኤርምያስ 31:34
15. ይሖዋ ምን የይቅር ባይነት ታሪክ አለው?
15 ይሖዋ በምድር ላይ የኖሩ አምላኪዎቹን ለብዙ ሺህ ዓመታት ይቅር ሲላቸው ቆይቷል። ይሖዋ ኃጢአት መሥራታቸውን ያወቁትንም ሆነ ኃጢአት መሥራታቸውን ያላወቁ ብዙ ሰዎችን ይቅር ብሏል። የምሕረት፣ የትዕግሥትና የይቅር ባይነት ዝግጅቱ ማብቂያ የለውም። ኢሳይያስ 55:7 “ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።”
ይቅር ባይነት በክርስቲያን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ
16. ኢየሱስ ዘወትር ያሳየው ይቅር ባይነት ይሖዋ ከሚያሳየው ይቅር ባይነት ጋር የሚስማማ ነው ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
16 ስለ አምላክ ይቅር ባይነት የሚናገረው ታሪክ በክርስቲያን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ዘገባ ላይም በብዛት ተንጸባርቆ ይገኛል። ኢየሱስ በጉዳዩ ላይ ይሖዋ ካለው አስተሳሰብ ጋር እንደሚስማማ በማሳየት ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ተናግሯል። የኢየሱስ አስተሳሰብ ከይሖዋ የመነጨ ነው። ኢየሱስ ይሖዋን ያንጸባርቃል። ትክክለኛው የይሖዋ ባሕርይ ምሳሌ ነው። እሱን ማየት ማለት ይሖዋን ማየት ማለት ነው።—ዮሐንስ 12:45–50፤ 14:9፤ ዕብራውያን 1:3
17. ኢየሱስ የይሖዋ ይቅር ባይነት “ሰፊ” መሆኑን በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?
17 የይሖዋ ይቅር ባይነት ሰፊ መሆኑን ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች መካከል አንዱ ማለትም 10,000 መክሊት (ወደ 33, 000, 000 የሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር) ዕዳ የነበረበትን ባሪያውን ስለማረው አንድ ንጉሥ የሚናገረው ምሳሌ ያሳያል። ይሁን እንጂ ያ ባሪያ አንድ መቶ ዲናር (ወደ 60 የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ) ዕዳ የነበረበትን ባልንጀራው የሆነውን ባሪያ ሊምረው ባለመፍቀዱ ንጉሡ እጅግ ተቆጣ። “አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ጌታውም ተቆጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው።” ከዚያም ኢየሱስ ይህ ምሳሌ እንዴት እንደሚሠራ ተናገረ፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፣ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።”—ማቴዎስ 18:23–35
18. ጴጥሮስ ለይቅር ባይነት የነበረው አመለካከት ኢየሱስ ከነበረው አመለካከት ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ከላይ ያለውን ምሳሌ የሰጠው ጴጥሮስ የሚከተለውን ጥያቄ ከጠየቀው በኋላ ነበር፦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው።” ጴጥሮስ በጣም ቸር የሆነ መስሎት ነበር። ምንም እንኳ ጻፎችና ፈሪሳውያን ለይቅር ባይነት ገደብ ያወጡለት ቢሆንም ኢየሱስ ጴጥሮስን “እስከ ሰባ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም” አለው። (ማቴዎስ 18:21, 22 አዓት) ኢየሱስ እንዳለው ሰባት ጊዜ ይቅር ማለት ለአንድ ቀን እምብዛም በቂ ላይሆን ይችላል፦ “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፣ ቢጸጸትም ይቅር በለው። በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ፦ ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፣ ይቅር በለው።” (ሉቃስ 17:3, 4) ይሖዋ ይቅር ሲል ኃጢአታችንን የማይቆጥር መሆኑ ደስ የሚያሰኝ ነው።
19. የይሖዋን ይቅር ባይነት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?
19 ንስሐ ለመግባትና ኃጢአታችንን ለመናዘዝ የሚያስችል ትሕትና ካለን ይሖዋ ቀና ምላሽ ለመስጠት ምንም አያቅማማም፦ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” —1 ዮሐንስ 1:9
20. እስጢፋኖስ ኃጢአትን ይቅር ለማለት ምን ዓይነት ፈቃደኝነት አሳይቷል?
20 የኢየሱስ ተከታይ የሆነው እስጢፋኖስ በንዴት የጦፉ ሰዎች ተሰብስበው የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱበት አስገራሚ በሆነ የይቅር ባይነት መንፈስ ይህን ልመና አሰማ፦ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ መንፈሴን ተቀበል። ተንበርክኮም፦ ይሖዋ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ።”—ሥራ 7:59, 60 አዓት
21. ኢየሱስ የሮማ ወታደሮችን ይቅር ለማለት ያሳየው ፈቃደኝነት እጅግ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?
21 ኢየሱስ ከዚህም ይበልጥ አስገራሚ የሆነ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የመሆን ምሳሌ ትቷል። ጠላቶቹ ያዙት፤ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በችሎት ፊት አቀረቡት፤ ጥፋተኛ ነህ ብለው ፈረዱበት፤ ዘበቱበት፤ ተፉበት፤ ብዛት ባላቸው ጠፍሮቹ ላይ የአጥንትና የብረት ስብርባሪዎች በተሰኩበት ጅራፍ ገረፉት፤ በመጨረሻም በእንጨት ላይ ቸንክረው ለሰዓታት አቆዩት። ሆኖም ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ሆኖ ሊሞት ሲያጣጥር የሰቀሉትን ወታደሮች በተመለከተ ለሰማያዊ አባቱ እንዲህ ብሏል፦ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።”—ሉቃስ 23:34
22. በተራራው ስብከት ላይ የተጠቀሱትን የትኞቹን ቃላት ተግባራዊ ለማድረግ መጣር አለብን?
22 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ . . . ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” ብሏል። እስከ ምድራዊ አገልግሎቱ ፍጻሜ ድረስ ኢየሱስ ራሱ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ታዟል። ከውዳቂው ሥጋችን ድክመቶች ጋር የምንታገለው እኛ እንዲህ ማድረጉ ከአቅም በላይ የሆነ ጥረት ይጠይቅብናልን? ቢያንስ ቢያንስ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የጸሎት ሞዴል ከሰጣቸው በኋላ ያስተማራቸውን ቀጥሎ ያለውን ትምህርት በተግባር ለማዋል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፦ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፣ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴዎስ 5:44፤ 6:14, 15) ይቅር የምንለው እንደ ይሖዋ ከሆነ፣ ይቅር ከማለትም አልፈን በደሉን እንሳዋለን።
ታስታውሳለህን?
◻ ይሖዋ ኃጢአታችንን በተመለከተ ምን ያደርጋል? ለምንስ?
◻ ምናሴ ወደ ንግሥናው የተመለሰው ለምንድን ነው?
◻ ሰዎች ፈተና የሚሆንባቸው የትኛውን ለየት ያለ የይሖዋ የይቅር ባይነት ገጽታ መኮረጅ ነው?
◻ ኢየሱስ ይቅር ለማለት ያሳየው ፈቃደኝነት እጅግ አስገራሚ የሆነው እንዴት ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት የአምላክን ይቅርታ ማግኘት እንደሚያስፈልገው እንዲያስተውል ናታን ረድቶታል