ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች
“እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:8
1. የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ለየትኞቹ ነገሮች ትኩረት እንሰጣለን? ለምንስ?
ጥሩ ችሎታ ያላቸው አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን ምን ማስተማር እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን እንዴት አድርገው ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ጭምር ያስባሉ። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ተመሳሳይ ነገር እናደርጋለን። ለምንሰብከው መልእክትም ሆነ ለምንጠቀምባቸው ዘዴዎች ትኩረት እንሰጣለን። መልእክታችን ማለትም የአምላክ መንግሥት ምሥራች ምንጊዜም አይለወጥም፤ የምንጠቀምባቸውን ዘዴዎች ግን እንደ ሁኔታው እንቀያይራለን። ለምን? ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ ስንል ነው።
2. የስብከት ዘዴዎቻችንን በመቀያየር የእነማንን አርዓያ እንኮርጃለን?
2 የስብከት ዘዴዎቻችንን በመቀያየር ጥንት የነበሩ የአምላክ አገልጋዮችን አርዓያ እንኮርጃለን። እስቲ ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ . . . ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ።” (1 ቆሮንቶስ 9:19-23) ጳውሎስ አቀራረቡን እንደየግለሰቦቹ ሁኔታ መቀያየሩ ጥሩ ውጤት አስገኝቶለታል። እኛም የምናነጋግራቸውን ሰዎች ሁኔታ በደግነት ከግምት ውስጥ በማስገባት አቀራረባችንን የምንለዋውጥ ከሆነ ተመሳሳይ ውጤት እናገኛለን።
እስከ “ምድር ዳርቻ”
3. (ሀ) በስብከት ሥራችን ላይ የሚያጋጥመን ፈታኝ ሁኔታ ምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ 45:22 በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
3 ምሥራቹን የሚሰብኩ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ትልቅ ፈታኝ ሁኔታ የአገልግሎት ክልሉ ስፋት ነው። ምሥራቹ “በዓለም ሁሉ” መሰበክ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 24:14) ባለፈው መቶ ዘመን በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ምሥራቹን ባልተዳረሰባቸው አገሮች ለማሰራጨት በትጋት ሠርተዋል። ይህስ ምን ውጤት አምጥቷል? አስደናቂ የሆነ ዓለም አቀፋዊ እድገት ተገኝቷል። በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የስብከቱ ሥራ ይካሄድ የነበረው በጥቂት አገሮች ውስጥ ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮች ውስጥ ያገለግላሉ! በእርግጥም የመንግሥቱ ምሥራች እስከ “ምድር ዳርቻ” ድረስ በመሰበክ ላይ ነው።—ኢሳይያስ 45:22
4, 5. (ሀ) ምሥራቹን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና የተጫወቱት እነማን ናቸው? (ለ) አንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በክልሎቻቸው ውስጥ በማገልገል ላይ ስለሚገኙ የውጭ አገር ምሥክሮች ምን አስተያየት ሰጥተዋል?
4 ለእድገቱ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ነገሮች ምንድን ናቸው? በርካታ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል። በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሠለጠኑ ሚስዮናውያን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ከ20,000 የሚበልጡ ወንድሞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የራሳቸውን ወጪ በመሸፈን የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሄደው የሚያገለግሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ያበረከቱት አስተዋጽኦም እንዲህ ቀላል አይደለም። እንዲህ ያለ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች፣ ወጣቶችና አረጋውያን፣ ያገቡና ያላገቡ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን መልእክት በምድር ዙሪያ በመስበኩ ሥራ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። (መዝሙር 110:3፤ ሮሜ 10:18) በእርግጥ ከፍተኛ አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። አንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ክልሎቻቸው ውስጥ ስለሚያገለግሉ የውጪ አገር ሰዎች የጻፉትን ሐሳብ ተመልከት።
5 “እነዚህ ውድ ምሥክሮች ነጠል ብለው በሚገኙ ክልሎች ውስጥ በመስበክ፣ አዳዲስ ጉባኤዎችን በማቋቋም እንዲሁም የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው ያገለግላሉ።” (ኢኳዶር) “በአገራችን የሚያገለግሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገር ወንድሞችና እህቶች ከዚህ ቢሄዱ ጉባኤዎች በጣም ይጎዳሉ። እነርሱ ከእኛ ጋር መሆናቸው ትልቅ በረከት ነው።” (ዶሚኒካን ሪፑብሊክ) “በብዙዎቹ ጉባኤዎቻችን ውስጥ የእህቶች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ እስከ 70 በመቶ ይደርሳል። (መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም) ከእነዚህ እህቶች መካከል አብዛኞቹ አዳዲሶች ናቸው። ሆኖም ከሌሎች አገሮች የመጡ ነጠላ አቅኚ እህቶች እነርሱን በማሠልጠን ረገድ ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከውጪ አገር የመጡት እነዚህ እህቶች ግሩም ስጦታ ሆነውልናል!” (በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኝ አገር) አንተስ ወደ ሌላ አገር ሄደህ ስለማገልገል አስበህ ታውቃለህ?a—የሐዋርያት ሥራ 16:9, 10
“ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች”
6. ዘካርያስ 8:23 ቋንቋ በስብከቱ ሥራችን ላይ ፈታኝ ሁኔታ እንደሚፈጥር የሚጠቁመው እንዴት ነው?
6 ምሥራቹን የሚሰብኩ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ሌላው ትልቁ ፈታኝ ሁኔታ ደግሞ በምድር ላይ የሚነገሩት ቋንቋዎች ብዛት ነው። የአምላክ ቃል “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ይሉታል” የሚል ትንቢት ይዟል። (ዘካርያስ 8:23) በዚህ ትንቢት ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት አሥሩ ሰዎች በራእይ 7:9 ላይ የተጠቀሱትን እጅግ ብዙ ሕዝቦች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ በዘካርያስ ትንቢት ላይ የተገለጹት “ዐሥር ሰዎች” የተውጣጡት ከየወገኑ ብቻ ሳይሆን “ከየቋንቋው” እንደሆነም ልብ በል። ታዲያ ይህ ታላቅ ትንቢት በዘመናችን ፍጻሜውን አግኝቷል? እንዴታ!
7. ሰዎች ‘በቋንቋቸው’ ምሥራቹን እንዲሰሙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚያሳዩት የትኞቹ አኃዛዊ መረጃዎች ናቸው?
7 እስቲ አንዳንድ አኃዛዊ መረጃዎችን እንመልከት። ከሃምሳ ዓመታት በፊት ጽሑፎቻችን የሚታተሙት በ90 ቋንቋዎች ነበር፤ በዛሬው ጊዜ ግን ጽሑፎቻቸን ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይታተማሉ። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ተናጋሪዎች ባሏቸው ቋንቋዎች ጭምር ጽሑፎች እንዲተረጎሙ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በግሪንላንድኛ (47,000 ተናጋሪዎች አሉት)፣ በፓላውኛ (15,000 ተናጋሪዎች አሉት) እንዲሁም በያፕኛ (7,000 ገደማ ተናጋሪዎች አሉት) ቋንቋዎች ይገኛሉ።
አዳዲስ አጋጣሚዎች የከፈተ “ታላቅ የሥራ በር”
8, 9. “ታላቅ የሥራ በር” የከፈተልን የትኛው ለውጥ ነው? በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ለውጥ በተመለከተ ምን እርምጃ ወስደዋል?
8 ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን በየቋንቋው ለመስበክ የግድ ውጪ አገር መሄድ አያስፈልገንም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በስደትና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በኢኮኖሚ ወደበለጸጉት አገሮች መፍለሳቸው በእነዚህ አገሮች ውስጥ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ማኅበረሰቦች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል በፓሪስ፣ ፈረንሳይ ወደ 100 የሚጠጉ ቋንቋዎች ይነገራሉ። በቶሮንቶ፣ ካናዳ 125 እንዲሁም በለንደን፣ እንግሊዝ ከ300 የሚበልጡ የውጪ አገር ቋንቋዎች ይነገራሉ! በበርካታ ጉባኤዎች የአገልግሎት ክልል ውስጥ የውጭ አገር ሰዎች መኖራቸው ምሥራቹን ለሰዎች ሁሉ ለመስበክ የሚያስችል አዳዲስ አጋጣሚ ያስገኘ “ታላቅ የሥራ በር” እንዲከፈት አድርጓል።—1 ቆሮንቶስ 16:9
9 በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሌላ ቋንቋ በመማር ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። ለብዙዎቹ እንዲህ ማድረግ ቀላል አይደለም፤ ሆኖም ስደተኞችን ጨምሮ የውጪ አገር ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዲማሩ በመርዳት የሚያገኙት ደስታ ልፋታቸውን እጥፍ ድርብ ያካክስላቸዋል። በቅርቡ በአንድ የምዕራብ አውሮፓ አገር በተደረጉ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ከተጠመቁት ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚያህሉት ከሌላ አገር የመጡ ናቸው።
10. ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለውን ቡክሌት የተጠቀምክበት እንዴት ነው? (በገጽ 26 ላይ የሚገኘውን “ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለው ቡክሌት ገጽታዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
10 ብዙዎቻችን የውጪ አገር ቋንቋ ለመማር ሁኔታችን እንደማይፈቅድልን የታወቀ ነው። ቢሆንም አስደሳቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በተለያዩ ቋንቋዎች የያዘውን ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራችb የተባለ አዲስ ቡክሌት ጥሩ አድርገን በመጠቀም ከሌላ አገር የመጡ ሰዎችን በመርዳቱ ሥራ መካፈል እንችላለን። (ዮሐንስ 4:37) አንተስ ይህን ቡክሌት በአገልግሎት እየተጠቀምክበት ነው?
ሰዎች በጎ ምላሽ ባይሰጡ
11. በአንዳንድ ክልሎች ምን ሌላ ፈታኝ ሁኔታ ይታያል?
11 ሰይጣን በዓለም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እየጨመረ በመጣ መጠን ሌላም ፈታኝ ሁኔታ አዘውትሮ እየተከሰተ ነው፤ ይህም በአንዳንድ ክልሎች ለመንግሥቱ መልእክት በጎ ምላሽ የሚሰጡት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ እየሆነ መምጣቱ ነው። እርግጥ ኢየሱስ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንደሚኖር ትንቢት ስለተናገረ ይህ መሆኑ አያስደንቀንም። ዘመናችንን በሚመለከት “የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:12) በእርግጥም ብዙ ሰዎች በአምላክ ላይ የነበራቸው እምነትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው አክብሮት እየተዳከመ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) በመሆኑም በአንዳንድ የምድር ክፍሎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚሆኑት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በጣም ጥቂት ነው። እንዲህ ሲባል ግን ለመንግሥቱ መልእክት በጎ ምላሽ በማይገኝባቸው ክልሎች ውስጥ የሚያገለግሉ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚለፉት በከንቱ ነው ማለት አይደለም። (ዕብራውያን 6:10) ለምን? የሚከተለውን ሐሳብ እንመልከት።
12. የስብከት ሥራችን ሁለት ዓላማዎች የትኞቹ ናቸው?
12 የማቴዎስ ወንጌል የስብከት ሥራችንን ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ይናገራል። አንደኛው ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት ማድረግ’ ነው። (ማቴዎስ 28:19) በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥቱ መልእክት በሰዎች ላይ “ምስክር” ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልጿል። (ማቴዎስ 24:14) ሁለቱም ዓላማዎች አስፈላጊ ቢሆኑም በተለይ ሁለተኛው ለየት ያለ ትርጉም አለው። ለምን?
13, 14. (ሀ) ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን ከሚያሳዩ ጎላ ያሉ ገጽታዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው? (ለ) እምብዛም በጎ ምላሽ በማይገኝባቸው ክልሎች ውስጥ ስንሰብክ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
13 ሐዋርያቱ ኢየሱስን “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውት እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ ዘግቧል። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስም ከምልክቱ ጎላ ያሉ ገጽታዎች መካከል አንዱ ዓለም አቀፋዊው የስብከት ሥራ እንደሆነ ተናገረ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለማድረጉ ሥራ መግለጹ ነበር? አልነበረም። ከዚህ ይልቅ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) በዚህ መንገድ ኢየሱስ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በራሱ የምልክቱ አንድ ወሳኝ ገጽታ እንደሆነ ገልጿል።
14 ስለሆነም የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበክን ደቀ መዛሙርት በማድረግ ረገድ ሁልጊዜ ባይቀናንም እንኳ ‘ምስክርነት’ በመስጠት በኩል ስኬታማ እንደምንሆን ማስታወስ ይኖርብናል። ሰዎች ለመልእክታችን የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን እያደረግን ስላለው ነገር ያውቃሉ፤ በዚህ መንገድ የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረጉ ሥራ ላይ እንካፈላለን። (ኢሳይያስ 52:7፤ ራእይ 14:6, 7) በምዕራብ አውሮፓ የሚኖር ጆርዲ የተባለ ወጣት ወንድም “ይሖዋ፣ ማቴዎስ 24:14 ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረጉ ሥራ ላይ ድርሻ እንዲኖረኝ እየተጠቀመብኝ መሆኑን ማወቄ በጣም ያስደስተኛል” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 2:15-17) አንተም እንደዚህ እንደሚሰማህ ምንም ጥርጥር የለውም።
ሰዎች መልእክታችንን ሲቃወሙ
15. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር? (ለ) ተቃውሞ እያለም መስበካችንን እንድንቀጥል የሚረዳን ምንድን ነው?
15 የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ላይ የተደቀነው ሌላው ተፈታታኝ ሁኔታ ደግሞ ተቃውሞ ነው። ኢየሱስ “በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት ለተከታዮቹ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:9) እንደ ጥንት ክርስቲያኖች ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የኢየሱስ ተከታዮችም ከሌሎች ጥላቻ፣ ተቃውሞና ስደት ደርሶባቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:17, 18, 40፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ ራእይ 12:12, 17) በአሁኑ ጊዜም እንኳ በአንዳንድ አገሮች መንግሥት እገዳ ጥሎባቸዋል። የሆነ ሆኖ በእነዚህ አገሮች የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን መታዘዝ ስለሚፈልጉ የመንግሥቱን ምሥራች መስበካቸውን ቀጥለዋል። (አሞጽ 3:8፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) እነዚህም ሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ እንዲያደርጉ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ኃይል ስለሰጣቸው ነው።—ዘካርያስ 4:6፤ ኤፌሶን 3:16፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:17
16. ኢየሱስ በስብከቱ ሥራና በአምላክ መንፈስ መካከል ያለውን ግንኙነት የገለጸው እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ ለተከታዮቹ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ . . . እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎ በነገራቸው ጊዜ በአምላክ መንፈስና በስብከቱ ሥራ መካከል ጥብቅ ግንኙነት እንዳለ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ራእይ 22:17) በዚህ ጥቅስ ላይ ክንውኖቹ የተቀመጡበት ቅደም ተከተል ትልቅ ትርጉም አለው። በቅድሚያ ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ ከዚያ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ማከናወን ጀመሩ። ‘ለሕዝብ ሁሉ ምስክርነት’ በመስጠቱ ሥራ ለመጽናት የሚያስችላቸውን ብርታት የሚያገኙት በአምላክ መንፈስ እርዳታ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 24:13, 14፤ ኢሳይያስ 61:1, 2) በእርግጥም ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን “ረዳት” ብሎ መጥቀሱ ተገቢ ነው። (ዮሐንስ 15:26 NW) የአምላክ መንፈስ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚያስተምራቸውና እንደሚመራቸው ተናግሯል።—ዮሐንስ 14:16, 26፤ 16:13
17. ከባድ ተቃውሞ ሲገጥመን መንፈስ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት ነው?
17 በዛሬው ጊዜ የአምላክ መንፈስ ምሥራቹን እንዳንሰብክ የሚያጋጥመንን ከባድ ተቃውሞ እንድንቋቋም የሚረዳን በምን መንገዶች ነው? የአምላክ መንፈስ ብርታት የሚሰጠን ከመሆኑም ባሻገር አሳዳጆቻችንን ይቃወማቸዋል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ንጉሥ ሳኦል አጋጥሞት የነበረውን ሁኔታ እንመልከት።
የአምላክ መንፈስ ይቃወማቸዋል
18. (ሀ) የሳኦል ባሕርይ የተለወጠው እንዴት ነው? (ለ) ሳኦል ዳዊትን ለማሳደድ ምን ዘዴዎች ተጠቅሟል?
18 ሳኦል የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ ሆኖ በተሾመ ጊዜ ጥሩ ባሕርይ ነበረው፤ እያደር ግን ይሖዋን ከመታዘዝ ወደኋላ ማለት ጀመረ። (1 ሳሙኤል 10:1, 24፤ 11:14, 15፤ 15:17-23) በዚህ የተነሳ የአምላክ መንፈስ ለእርሱ የሚሰጠውን ድጋፍ አቆመ። ሳኦል ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን በተቀባውና የአምላክን መንፈስ እርዳታ አግኝቶ በነበረው በዳዊት ላይ ከመበሳጨቱ የተነሳ አደጋ ሊያደርስበት ሙከራ ማድረግ ጀመረ። (1 ሳሙኤል 16:1, 13, 14) ዳዊት በቀላሉ ሊጠቃ የሚችል ይመስል ነበር። ደግሞም ዳዊት ከበገና በስተቀር ምንም መሣሪያ አልነበረውም፤ ሳኦል ግን ጦር ይይዝ ነበር። አንድ ቀን ዳዊት በገና እየተጫወተ ሳለ ሳኦል “‘ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ’ ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ።” (1 ሳሙኤል 18:10, 11) በኋላ ላይ ደግሞ ሳኦል የዳዊት ጓደኛ የነበረው ልጁ ዮናታን የሰጠውን ምክር ሰምቶ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ሆኖም በሌላ ጊዜ ሳኦል ዳዊትን “ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር በግድግዳው ላይ ተሰካ።” በዚህ ምክንያት ዳዊት የሸሸ ሲሆን ሳኦል ግን ያሳድደው ጀመር። በዚህ አደገኛ ጊዜ የአምላክ መንፈስ የሳኦል ተቃዋሚ ሆነ። እንዴት?—1 ሳሙኤል 19:6, 10
19. የአምላክ መንፈስ ዳዊትን ከጥቃት የጠበቀው እንዴት ነው?
19 ዳዊት ሸሽቶ ወደ ነቢዩ ሳሙኤል ሄደ፤ ሳኦል ግን ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎችን ወደዚያ ላከ። ይሁን እንጂ መልእክተኞቹ ዳዊት ወደተሸሸገበት ቦታ ሲደርሱ “የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ወረደ፤ እነርሱም . . . ትንቢት ተናገሩ።” የአምላክ መንፈስ እጅግ ስላየለባቸው የተላኩበትን ዓላማ ጨርሶ ዘንግተውት ነበር። ሳኦል ከዚያ በኋላ ዳዊትን ይዘው እንዲመጡ ሁለት ጊዜ መልእክተኞች የላከ ቢሆንም ሁለቱንም ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ተፈጸመ። በመጨረሻ ንጉሥ ሳኦል ራሱ ወደ ዳዊት ሄደ፤ ሆኖም የአምላክን መንፈስ ሊቋቋም አልቻለም። እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ ሳኦል “ቀኑንና ሌሊቱን በሙሉ” እንዳይንቀሳቀስ ስላገደው ዳዊት ለመሸሽ የሚያስችለውን በቂ ጊዜ አገኘ።—1 ሳሙኤል 19:20-24
20. ሳኦል ዳዊትን እንዳሳደደው ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
20 ስለ ሳኦልና ስለ ዳዊት የሚናገረው ይህ ዘገባ የሚያበረታታ ትምህርት ይዟል። የአምላክ አገልጋዮችን የሚያሳድዱ ሰዎች የአምላክ መንፈስ ከተቃወማቸው ፈጽሞ ሊሳካላቸው አይችልም። (መዝሙር 46:11፤ 125:2) ይሖዋ ዳዊትን በእስራኤል ላይ የማንገሥ ዓላማ ነበረው። ማንም ቢሆን ይህን ዓላማውን ማስቀየር አይችልም። በዘመናችንም ይሖዋ ‘የመንግሥቱ ወንጌል እንዲሰበክ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ማንም ይህ እንዳይፈጸም ማገድ አይችልም።—የሐዋርያት ሥራ 5:40, 42
21. (ሀ) በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ምን እርምጃ ይወስዳሉ? (ለ) ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ነን?
21 አንዳንድ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች የስብከት ሥራችንን ለማስተጓጎል የሐሰት ወሬ ያናፍሱብናል፤ አልፎ ተርፎም የኃይል እርምጃዎችን ይወስዳሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ዳዊትን በመንፈሳዊ እንደጠበቀው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሕዝቦቹንም ይጠብቃቸዋል። (ሚልክያስ 3:6) በመሆኑም እንደ ዳዊት በእርግጠኝነት “በአምላክ ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን። (መዝሙር 56:11፤ 121:1-8፤ ሮሜ 8:31) እኛም የመንግሥቱን ምሥራች ለሰዎች ሁሉ እንድንሰብክ የተሰጠንን መለኮታዊ ተልእኮ ስንፈጽም የሚያጋጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች በሙሉ በይሖዋ እርዳታ መጋፈጣችንን እንቀጥል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በገጽ 22 ላይ የሚገኘውን “ከፍተኛ የእርካታ ስሜት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
ታስታውሳለህ?
• የስብከት ዘዴያችንን የምንቀያይረው ለምንድን ነው?
• ‘ታላቁ የሥራ በር’ ምን አዳዲስ አጋጣሚዎችን ከፍቷል?
• እምብዛም በጎ ምላሽ በማይገኝባቸው የአገልግሎት ክልሎች ጭምር በስብከት ሥራችን አማካኝነት ምን ዓላማ እየተከናወነ ነው?
• ተቃዋሚዎች የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ሥራችንን ማስቆም የማይችሉት ለምንድን ነው?
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከፍተኛ የእርካታ ስሜት
“አንድ ሆነው ይሖዋን ማገልገላቸው ደስታና እርካታ አስገኝቶላቸዋል።” እንዲህ የተባለው ከስፔን ወደ ቦሊቪያ ተዛውሮ ለነበረ አንድ ቤተሰብ ነው። ከዚህ ቤተሰብ መካከል አንደኛው ልጅ በገለልተኛ ክልል የሚገኝ ቡድን ለመርዳት ወደ ቦሊቪያ ሄዶ ነበር። ወላጆቹ ልጁ ባገኘው ደስታ በጣም በመደነቃቸው ከ14 እስከ 25 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አራት ወንዶች ልጆቻቸውን ይዘው ወደዚያ ተዛወሩ። በአሁኑ ጊዜ ሦስቱ ልጆች አቅኚ ሆነው እያገለገሉ ሲሆን መጀመሪያ ወደ ቦሊቪያ የሄደው ልጅ በቅርቡ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተካፍሏል።
በምሥራቅ አውሮፓ በማገልገል ላይ የምትገኘውና ከካናዳ የመጣችው የ30 ዓመቷ አንጀሊካ እንዲህ ብላለች:- “በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉ። ሆኖም በአገልግሎት አማካኝነት ሰዎችን መርዳት እርካታ አስገኝቶልኛል። በተጨማሪም የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች እነርሱን ለመርዳት በመምጣቴ ምስጋናቸውን ለመግለጽ ሲሉ በየጊዜው የሚሰጡኝ የአድናቆት መግለጫ በእጅጉ ያበረታታኛል።”
በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የሚያገለግሉ በ20ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኙ ሁለት አሜሪካውያን እህትማማቾች እንዲህ ብለዋል:- “ብዙ ባሕሎችንና ልማዶችን መልመድ ነበረብን። ይሁን እንጂ በተመደብንበት ቦታ ጸንተን ቆይተናል። አሁን ሰባት የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረዋል።” እነዚህ ሁለት እህቶች ምንም ጉባኤ በሌለበት አንድ ትንሽ ከተማ ውስጥ ያሉ ጥቂት አስፋፊዎችን በማደራጀት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በ20ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የምትገኝ ሎራ የምትባል አንዲት እህት ከአራት ለሚበልጡ ዓመታት ከአገሯ ውጪ ስታገለግል ቆይታለች። እንዲህ ትላለች:- “ሆነ ብዬ አኗኗሬን ቀላል ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ። ይህ ደግሞ አስፋፊዎች እንዲህ ያለው ኑሮ የምርጫና የአስተሳሰብ ጉዳይ እንጂ ድሃ የመሆን ጉዳይ እንዳልሆነ እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። ሌሎችን በተለይም ወጣቶችን መርዳቴ በውጪ አገር ማገልገል የሚያስከትላቸውን ከባድ ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል ደስታ አስገኝቶልኛል። እዚህ የማከናውነውን አገልግሎት በምንም ነገር ልለውጠው አልፈልግም፤ ይሖዋ እስከፈቀደ ጊዜ ድረስ እዚሁ እቆያለሁ።”
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለው ቡክሌት ገጽታዎች
ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለው ቡክሌት እስከ 92 በሚደርሱ ቋንቋዎች የአንድ ገጽ መልእክት ይዟል። መልእክቱ የቀረበው ግለሰቡ አንተው ራስህ እያነጋገርከው እንዳለህ እንዲሰማው በሚያደርግ መንገድ ነው። ቡክሌቱ ሌሎች ጠቃሚ ገጽታዎችም አሉት።
በሽፋኑ የውስጠኛ ገጽ ላይ የዓለም ካርታ ይገኛል። ይህንን ካርታ ከቤቱ ባለቤት ጋር ለመግባባት ልትጠቀምበት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል አንተ የምትኖርበትን አገር በካርታው ላይ ካሳየኸው በኋላ እርሱ የየት አገር ሰው እንደሆነ ማወቅ እንደምትፈልግ ልትጠቁመው ትችላለህ። በዚህ መንገድ እንዲናገር ልታደርገውና በመካከላችሁ ወዳጃዊና ዘና ያለ መንፈስ እንዲፈጠር ማድረግ ትችላለህ።
የቡክሌቱ መቅድም የማናውቀውን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመርዳት ልንወስዳቸው የሚገቡንን በርካታ እርምጃዎች ይዘረዝራል። እባክህ እነዚህን ነጥቦች በሚገባ አንብበህ ተግባራዊ ለማድረግ ጣር፤ በሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ወሳኝ ነገር ነው።
የቡክሌቱ ማውጫ ቋንቋዎቹን ብቻ ሳይሆን ቋንቋዎቹን የሚወክሉ ፊደላትንም ጭምር በዝርዝር ይዟል። ይህም በትራክቶችና በሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ የሰፈሩትን ቋንቋውን የሚያመለክቱ ፊደላትን ለመረዳት ያስችልሃል።
[ሥዕል]
ይህን ቡክሌት በአገልግሎት እየተጠቀምክበት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት ጽሑፎቻችን በአሁኑ ጊዜ ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛሉ
ጋና
ፊሊፒንስ
ላፕላንድ (ስዊድን)
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደህ ማገልገል ትችላለህ?
ኢኳዶር
ዶሚኒካን ሪፑብሊክ