“አንባቢው ያስተውል”
“የጥፋትን ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣. . . በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ።”—ማቴዎስ 24:15, 16
1. በሉቃስ 19:43, 44 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ምን ውጤት አስገኝቷል?
ከፊታችን እየቀረበ ስላለ አደጋ ማስጠንቀቂያ ማግኘታችን ከችግር ሊጠብቀን ይችላል። (ምሳሌ 22:3) ስለዚህ ሮማውያን በ66 እዘአ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ በኢየሩሳሌም የሚገኙ ክርስቲያኖች በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኙ እንደነበር አስቡ። ኢየሱስ ከተማዋ እንደምትከበብና እንደምትወድም አስጠንቅቆ ነበር። (ሉቃስ 19:43, 44) አብዛኞቹ አይሁዶች ማስጠንቀቂያውን ችላ ብለው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ግን ማስጠንቀቂያውን በመስማት እርምጃ ወስደዋል። በዚህም ምክንያት በ70 እዘአ ከደረሰው ጥፋት ሊድኑ ችለዋል።
2, 3. በማቴዎስ 24:15-21 ላይ ተመዝግቦ ስለሚገኘው የኢየሱስ ትንቢት ማወቅ ያለብን ለምንድን ነው?
2 ዛሬ ለምንገኘው ትልቅ ትርጉም ባለው አንድ ትንቢት ላይ ኢየሱስ ጦርነትን፣ የምግብ እጥረትን፣ የመሬት መንቀጥቀጥን፣ ወረርሽኝ በሽታዎችንና ስለ አምላክ መንግሥት በሚሰብኩ ክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ መከራን ስለሚያካትት ድርብ ተፈጻሚነት ያለው ምልክት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:4-14፤ ሉቃስ 21:10-19) በተጨማሪም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መጨረሻው መቅረቡን የሚያሳውቅ ፍንጭ የሰጣቸው ሲሆን ይህም ‘በተቀደሰ ስፍራ ስለሚቆም የጥፋት ርኩሰት’ የሚናገር ነው። (ማቴዎስ 24:15) እነዚህን ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ቃላት ደግመን በመመርመር የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ሕይወታችንን እንዴት እንደሚነኩት እንመልከት።
3 ኢየሱስ ስለ ምልክቱ ከተናገረ በኋላ እንዲህ አለ:- “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል፣ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፣ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።”—ማቴዎስ 24:15-21
4. ማቴዎስ 24:15 በአንደኛው መቶ ዘመን ተፈጻሚነት እንደነበረው የሚያመለክተው ምንድን ነው?
4 የማርቆስና የሉቃስ ዘገባዎች በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ። ማቴዎስ “በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ” ሲል ማርቆስ 13:14 ደግሞ “በማይገባው ስፍራ ቆሞ” ይላል። ሉቃስ 21:20 የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላት ያክላል:- “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።” ይህ ሐሳብ በ66 እዘአ ሮማውያን በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሷ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት የሚመለከተውን የመጀመሪያውን ፍጻሜ እንድናስተውል ይረዳናል። ይህ ቦታ ለአይሁዳውያን እንጂ በይሖዋ ፊት ቅዱስ መሆኑ አክትሞለት ነበር። ኢየሩሳሌም ሙሉ በሙሉ የጠፋችው ሮማውያን በ70 እዘአ ከተማዋንና ቤተ መቅደሱን ባወደሙ ጊዜ ነበር። በዚያን ጊዜ ‘ርኩስ’ የተባለው ነገር ምን ነበር? ‘በተቀደሰ ስፍራ የቆመውስ’ እንዴት ነበር? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምናገኘው መልስ ዘመናዊውን ፍጻሜ በግልጽ ለመረዳት ያስችላል።
5, 6. (ሀ) ዳንኤል ምዕራፍ 9ን የሚያነቡ ሰዎች ማስተዋል የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ‘ርኩስ’ ስለሆነው ነገር የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?
5 ኢየሱስ አንባቢዎች እንዲያስተውሉ አጥብቆ አሳስቧል። የትኞቹን አንባቢዎች ማለቱ ነበር? የዳንኤል ምዕራፍ 9ን አንባቢዎች ለማመልከት የፈለገ ይመስላል። በዚህ ምዕራፍ ላይ መሲሑ የሚገኝበትን ጊዜ የሚያመለክትና ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ‘እንደሚገደል’ የሚናገር ትንቢት እናገኛለን። ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “በርኩሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቆረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።”—ዳንኤል 9:26, 27 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ በተጨማሪም ዳንኤል 11:31፤ 12:11ን ተመልከት።
6 አይሁዳውያኑ ይህ ትንቢት ከ200 ዓመታት ገደማ በፊት አንታይከስ አራተኛ ቤተ መቅደሱን ማርከሱን የሚያመለክት ነው ብለው ያስቡ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ርኩሰቱ በተቀደሰው ስፍራ ላይ ለመቆም የሚመጣበት ጊዜ ገና መሆኑን እንዲያስተውሉ በማሳሰብ ሁኔታው እነሱ እንደሚያስቡት አለመሆኑን ገልጿል። ኢየሱስ በትንቢቱ፣ በ66 እዘአ ልዩ የሆኑ አርማዎችን ይዞ የሚመጣውን የሮማውያኑን ሠራዊት ማመልከቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። እንደነዚህ ያሉት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋሉ አርማዎች ጣዖታት ተደርገው የሚታዩ ሲሆን ለአይሁዳውያኑም ርኩስ ነገሮች ነበሩ።a ሆኖም ‘በተቀደሰው ስፍራ ላይ የሚቆሙት’ መቼ ነው? ይህ የሆነው የሮማ ሠራዊት አርማዎቹን ይዞ በመምጣት አይሁዳውያን ቅዱስ አድርገው የሚመለከቷቸውን ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ባጠቃበት ጊዜ ነበር። ሮማውያኑ በቤተ መቅደሱ አካባቢ ያለውን ቅጥር ሳይቀር ማፍረስ ጀምረው ነበር። በእርግጥም ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ርኩስ ተደርጎ ይታይ የነበረው ነገር በተቀደሰው ስፍራ ላይ ቆመ!—ኢሳይያስ 52:1፤ ማቴዎስ 4:5፤ 27:53፤ ሥራ 6:13
ዘመናዊው “ርኩሰት”
7. በጊዜያችን በመፈጸም ላይ ያለው የትኛው የኢየሱስ ትንቢት ነው?
7 በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ምልክት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ከፍተኛ ፍጻሜውን ሲያገኝ ተመልክተናል። ይሁንና እንዲህ ሲል የተናገራቸውን ቃላት አስታውሱ:- “የጥፋትን ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ . . . በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ።” (ማቴዎስ 24:15, 16) ይህ የትንቢቱ ገጽታም በዘመናችን ተፈጻሚነት ሊኖረው ይገባል።
8. ባለፉት ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በጊዜያችን ያለውን “ርኩሰት” ለይተው ያሳወቁት እንዴት ነበር?
8 የጥር 1, 1921 መጠበቂያ ግንብ የይሖዋ አገልጋዮች ይህ ትንቢት እንደሚፈጸም ትምክህት እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ በመካከለኛው ምሥራቅ ከነበረው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ማብራሪያ አውጥቶ ነበር። ከጊዜ በኋላም መጠበቂያ ግንብ በታኅሣሥ 15, 1929 እትሙ በገጽ 374 ላይ በግልጽ እንዲህ ብሎ ነበር:- “የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ፍላጎት ሰዎችን ከአምላክ እና ከክርስቶስ ማራቅ ነው፤ በመሆኑም ርኩስ፣ ሰይጣን የመሠረተውና በአምላክ ፊት በጣም አስጸያፊ የሆነ ነገር ነው።” ስለዚህ በ1919 ‘ርኩሰቱ’ ታየ። ከጊዜ በኋላ የቃል ኪዳኑ ማኅበር ለተባበሩት መንግሥታት ቦታውን ለቀቀ። የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ሰብዓዊ የሰላም ድርጅቶች አምላክ ርኩስ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ከረዥም ጊዜ በፊት አጋልጠዋል።
9, 10. ቀደም ሲል ስለ ታላቁ መከራ የነበረን ግንዛቤ ‘ርኩሰቱ’ በተቀደሰው ስፍራ ላይ የሚቆምበትን ጊዜ በተመለከተ ባለን አመለካከት ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነበር?
9 ከዚህ በፊት ያለው ርዕስ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። ‘በተቀደሰው ስፍራ ላይ ስለ ቆመው ርኩሰት’ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት ያስፈልግ ይሆን? አዎን፣ የሚያስፈልግ ይመስላል። የኢየሱስ ትንቢት ‘በተቀደሰው ስፍራ መቆምን’ አስቀድሞ ከተነገረው “መከራ” መጀመር ጋር በቅርብ ያያይዘዋል። ከዚህ የተነሣ ‘ርኩሰቱ’ ሕልውና ያገኘው ከረዥም ጊዜ በፊት ቢሆንም ‘በተቀደሰው ስፍራ በመቆሙና’ በታላቁ መከራ መካከል ያለው ግንኙነት አስተሳሰባችንን ሊነካው ይገባል። ግን እንዴት?
10 በአንድ ወቅት የአምላክ ሕዝቦች የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ክፍል በ1914 ጀምሯል ብለው ያስቡ የነበረ ሲሆን የመጨረሻው ክፍል ደግሞ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ ይደመደማል የሚል ግንዛቤ ነበራቸው። (ራእይ 16:14, 16፤ ከሚያዝያ 1, 1939 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 110 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ከጊዜ በኋላ የሚመጣው “ርኩሰት” በተቀደሰው ስፍራ ላይ የቆመው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጥቂት ጊዜ በኋላ መሆን አለበት ተብሎ ይታሰብ የነበረው ለምን እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን።
11, 12. በ1969 ታላቁን መከራ የሚመለከት ምን የማስተካከያ ሐሳብ ተሰጥቶ ነበር?
11 ይሁን እንጂ በኋለኞቹ ዓመታት ላይ ነገሮችን ለየት ባለ መንገድ መመልከት ጀምረናል። “ሰላም በምድር ላይ” በተሰኘው ትልቅ ስብሰባ ላይ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበረው ኤፍ ደብልዩ ፍራንዝ ሐምሌ 10, 1969 ሐሙስ ቀን ቀስቃሽ የሆነ ንግግር ሰጥቶ ነበር። ወንድም ፍራንዝ ስለ ኢየሱስ ትንቢት ቀደም ሲል የነበረውን መረዳት በመከለስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “‘ታላቁ መከራ’ በ1914 እዘአ የጀመረ ቢሆንም አምላክ መከራው እስከ መጨረሻው እንዲቀጥል ባለ መፍቀድ አንደኛው የዓለም ጦርነትን በኅዳር 1918 እንዲቆም አድርጓል የሚል ማብራሪያ ተሰጥቶ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አምላክ ‘የታላቁ መከራ’ የመጨረሻ ክፍል በአርማጌዶን ጦርነት እንደገና እንዲጀምር ከመፍቀዱ በፊት የተመረጡት ቅቡዓን ክርስቲያን ቀሪዎቹ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት የተወሰነ ጊዜ ፈቅዷል።”
12 ከዚያም ጉልህ ማስተካከያ የተደረገበት ማብራሪያ ተሰጠ:- “በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከተፈጸሙት ክንውኖች ጋር እንዲስማማ ከተፈለገ . . . ‘የታላቁ መከራ’ ፍጻሜ የጀመረው በ1914 እዘአ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ በኢየሩሳሌም ዘመናዊ አምሳያ ላይ ከ1914-1918 የደረሰው ነገር ‘የምጥ ጣር መጀመሪያ’ ብቻ ነበር። . . . እንግዲህም ከቶ አይሆንም የተባለለት “ታላቅ መከራ” ገና ወደፊት የሚፈጸም ነው፤ ምክንያቱም ይህ መከራ (ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ) የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት መጥፋቷንና በአርማጌዶን የሚሆነው ‘ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ መጀመሩን የሚያመለክት ነው።” በዚህ መሠረት ታላቁ መከራ የሚጀምረው ገና ወደፊት ይሆናል ማለት ነው።
13. ‘ርኩሰቱ’ ‘በተቀደሰ ቦታ ላይ የሚቆምበት’ ጊዜ ወደፊት ይመጣል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ይህ ጉዳይ ‘ርኩሰቱ’ በተቀደሰው ስፍራ ላይ የሚቆምበትን ጊዜ ከማስተዋል ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሆነውን ነገር አስታውስ። በ66 እዘአ ሮማውያን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ ይሁንና ሳይታሰብ ወደ ኋላ በማፈግፈጋቸው “ሥጋ የለበሱ” ክርስቲያኖች የሚድኑበት አጋጣሚ ተከፈተላቸው። (ማቴዎስ 24:22) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ታላቁ መከራ በቅርቡ እንደሚጀምር ብንጠብቅም ለአምላክ ምርጦች ሲባል ጊዜው እንዲያጥር ይደረጋል። ይህንን ቁልፍ ነጥብ ልብ በል:- በጥንቱ ፍጻሜ መሠረት ‘የርኩሰቱ በተቀደሰ ስፍራ መቆም’ በጄኔራል ጋለስ የሚመራው የሮማ ሠራዊት በ66 እዘአ ጥቃት ከመሰንዘሩ ጋር የተቆራኘ ነበር። የዚህ ጥቃት ዘመናዊ አምሳያ የሆነው ታላቅ መከራ የሚጀምረው ገና ወደፊት ነው። ስለዚህ ከ1919 ጀምሮ ሕልውና ያገኘው ‘የጥፋት ርኩሰት’ በተቀደሰው ስፍራ ላይ የሚቆመው ገና ወደፊት መሆኑን ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል።b ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህስ እኛን ሊነካን የሚችለው እንዴት ነው?
ወደፊት የሚሰነዘር ጥቃት
14, 15. ራእይ ምዕራፍ 17 ወደ አርማጌዶን የሚመሩ ክንውኖችን ለማስተዋል የሚረዳን እንዴት ነው?
14 የሐሰት ሃይማኖት ወደፊት ለጥፋት የሚዳርግ ጥቃት እንደሚሰነዘርበት የራእይ መጽሐፍ ይናገራል። ምዕራፍ 17 ‘የጋለሞታዎች እናት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን’ ማለትም በዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ላይ አምላክ ስለሚወስደው የቅጣት እርምጃ ይናገራል። በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን የታሠረ ዝምድና አለኝ የምትለው ሕዝበ ክርስትና ነች። (ከኤርምያስ 7:4 ጋር አወዳድር።) ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ የሐሰት ሃይማኖቶች በአጠቃላይ ከረዥም ጊዜ አንስቶ “ከምድር ነገሥታት” ጋር ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት ቢኖራቸውም እነዚህ ሃይማኖቶች በሚጠፉበት ጊዜ ግን ይህ ሁኔታ ያከትማል። (ራእይ 17:2, 5) የሚጠፉት በማን እጅ ነው?
15 የራእይ መጽሐፍ ለተወሰነ ጊዜ ስለሚኖር፣ ስለሚጠፋና ከዚያም ተመልሶ ስለሚመጣ ‘ቀይ አውሬ’ ይገልጻል። (ራእይ 17:3, 8) ይህ አውሬ በዓለም ገዥዎች የሚደገፍ ነው። ይህ ምሳሌያዊ አውሬ የሚያመለክተው በ1919 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር (“ርኩሰት”) ሆኖ ብቅ ያለውንና ዛሬ የተባበሩት መንግሥታት በመባል የሚታወቀውን የሰላም ድርጅት እንደሆነ በትንቢቱ ውስጥ የተገለጹት ዝርዝር ጉዳዮች ይጠቁሙናል። ራእይ 17:16, 17 አምላክ በዚህ “አውሬ” ውስጥ ከፍ ብለው በሚታዩ አንዳንድ ሰብዓዊ መሪዎች ልብ ውስጥ የሐሰት ሃይማኖትን ግዛት የማጥፋት ሐሳብ እንደሚያኖር ይናገራል። ይህ ጥቃት ታላቁ መከራ መጀመሩን ለይቶ የሚያሳውቅ ይሆናል።
16. ሃይማኖትን በተመለከተ ምን ትኩረትን የሚስቡ ነገሮች በመፈጸም ላይ ናቸው?
16 ታላቁ መከራ የሚጀምረው ወደፊት በመሆኑ ርኩሰቱ “በተቀደሰው ስፍራ ላይ ቆሞ” የምንመለከተው ገና ወደፊት ይሆናል ማለት ነው? ሁኔታው እንደዚያ ይመስላል። ‘ርኩሰቱ’ በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሕልውና ያገኘና ላለፉት አሥርተ ዓመታት ሕያው ሆኖ የቆየ ቢሆንም በቅርቡ ለየት ባለ መንገድ ‘በተቀደሰው ስፍራ ላይ ይቆማል።’ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች ርኩሰቱ ‘በተቀደሰው ስፍራ ላይ የሚቆመው’ እንዴት እንደሆነ ለመመልከት በጉጉት ይጠባበቁ እንደነበረ ሁሉ በዘመናችን የሚገኙ ክርስቲያኖችም የትንቢቱን ፍጻሜ ለማየት ይጓጓሉ። የአፈጻጸሙን ዝርዝር ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ለማወቅ በቀጥታ ትንቢቱ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ መጠበቅ እንዳለብን የተረጋገጠ ነው። ይሁንና በአንዳንድ አገሮች በሃይማኖት ላይ እየጨመረ የመጣ ጥላቻ መኖሩ ትኩረትን የሚስብ ነው። አንዳንድ ፖለቲካዊ አካላት እውነተኛውን አምልኮ ትተው ከወጡ ክርስቲያኖች ጋር በማበር በአጠቃላይ በሃይማኖትና በተለይም ደግሞ በእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ላይ ጥላቻ እያስፋፉ ነው። (መዝሙር 94:20, 21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) በመሆኑም ፖለቲካዊ ኃይላት አሁን እንኳ ‘ከበጉ ጋር በመዋጋት’ ላይ ሲሆኑ ራእይ 17:14 በሚናገረው መሠረት ደግሞ ውጊያው እየተፋፋመ ይሄዳል። ከፍ ባለ ክብራማ ቦታ ላይ ከሚገኘው ከአምላክ በግ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ቃል በቃል ውጊያ ባይገጥሙም ተቃውሟቸውን በአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ላይ በተለይም ደግሞ በ“ቅዱሳኑ” ላይ ያደርጋሉ። (ዳንኤል 7:25፤ ከሮሜ 8:27፤ ቆላስይስ 1:2፤ ራእይ 12:17 ጋር አወዳድር።) በጉና ከእሱ ጋር ያሉት ድል እንደሚቀዳጁ መለኮታዊ ማረጋገጫ አለን።—ራእይ 19:1-21
17. ድርቅ ያለ ሐሳብ ባንሰጥም ‘ርኩሰቱ’ በተቀደሰው ስፍራ ስለሚቆምበት ሁኔታ ምን ለማለት እንችላለን?
17 የሐሰት ሃይማኖት ጥፋት እንደሚጠብቀው እናውቃለን። ታላቂቱ ባቢሎን ‘በቅዱሳን ደም የሰከረችና’ እንደ ንግሥት ሆና የምትታይ ብትሆንም መጥፋትዋ አይቀሬ ነው። ‘አሥር ቀንዶች ካሉት አውሬ’ ጋር የነበራት ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ጥላቻ ሲቀየር በምድር ነገሥታት ላይ የነበራት መጥፎ ተጽእኖ በሚያስደንቅ ሁኔታ ይለወጣል። (ራእይ 17:6, 16፤ 18:7, 8) ‘ቀዩ አውሬ’ በሃይማኖታዊ ጋለሞታዋ ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ‘ርኩሰቱ’ ሕዝበ ክርስትና ቅዱስ ብላ በምትጠራው ስፍራ ላይ አስጊ በሆነ ሁኔታ ይቆማል።c ስለዚህ ጥፋቱ የሚጀምረው ራሷን ቅዱስ አድርጋ በምታቀርበው እምነት የለሿ ሕዝበ ክርስትና ነው።
‘የምንሸሸው’ እንዴት ነው?
18, 19. ‘ወደ ተራራዎች መሸሽ’ ማለት ሃይማኖትን መቀየር ማለት እንዳልሆነ ለማሳየት ምን ምክንያቶች ተሰጥተዋል?
18 ኢየሱስ ‘ርኩሰቱ በተቀደሰው ስፍራ ላይ ስለ መቆሙ’ ከተናገረ በኋላ አስተዋይ ሰዎች እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል። ኢየሱስ ‘ርኩሰቱ በተቀደሰው ስፍራ በሚቆምበት’ በዚያ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ብዙዎች ከሐሰት ሃይማኖት ሸሽተው ወደ እውነተኛው አምልኮ ይመጣሉ ማለቱ ነበርን? በፍጹም። የመጀመሪያ ፍጻሜውን ተመልከት። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፣ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፣ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ።”—ማርቆስ 13:14-18 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
19 ኢየሱስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ከአይሁድ የአምልኮ ማዕከል መውጣትን የሚመለከት ይመስል መውጣት የሚያስፈልጋቸው በኢየሩሳሌም ያሉ ብቻ ናቸው አላለም፤ ወይም ደግሞ ማስጠንቀቂያው ሃይማኖትን ስለ መቀየር ማለትም ከሐሰተኛው ሸሽቶ በመውጣት እውነተኛውን ስለ መያዝ የሚናገር አይደለም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቀድሞውንም ቢሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ከአንድ ሃይማኖት ወጥተው ወደ ሌላ ሃይማኖት እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ እንደማያስፈልጋቸው የተረጋገጠ ነው። እንዲሁም በ66 እዘአ የተሰነዘረው ጥቃት በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ ውስጥ የሚገኙ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ክርስትናን እንዲቀበሉ አላነሳሳቸውም። ፕሮፌሰር ሃይንሪሽ ግሬትስ ሮማውያኑን ያሳድዱ የነበሩት ሰዎች ወደ ከተማው መመለሳቸውን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “ዜለትስ ተብለው የሚጠሩት ቀናኢ አይሁዶች እየሸለሉና እያቅራሩ፣ ነፃ የመውጣት ተስፋ ይዘው (ጥቅምት 8 ቀን) ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። . . . አምላክ የቀድሞ አባቶቻቸውን በደግነት እንደረዳቸው ሁሉ እነሱንም የረዳቸው መሆኑን የሚያሳይ አይደለምን? ዜለትስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ፍርሃት አላደረባቸውም።”
20. የቀድሞዎቹ ደቀ መዛሙርት ወደ ተራራዎች እንዲሸሹ ኢየሱስ ለሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነበር?
20 ታዲያ በወቅቱ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት ቁጥር የነበራቸው ምርጦች የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ ያደረጉት እንዴት ነበር? ይሁዳን ትተው በመውጣትና ዮርዳኖስን አቋርጠው ወደ ተራራዎች በመሸሽ በፖለቲካም ይሁን በሃይማኖት የአይሁድ ሥርዓት ክፍል አለመሆናቸውን አሳይተዋል። እርሻቸውንና ቤታቸውን የተዉ ሲሆን ንብረታቸውን ለመሰብሰብ ሲሉ እንኳ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። በይሖዋ ጥበቃና ድጋፍ በመታመን ጠቃሚ ከሚመስል ከማንኛውም ነገር ሁሉ በፊት የእሱን አምልኮ አስቀድመዋል።—ማርቆስ 10:29, 30፤ ሉቃስ 9:57-62
21. ‘ርኩሰቱ’ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ምን ነገር መጠበቅ አያስፈልገንም?
21 አሁን ደግሞ ከፍተኛውን ፍጻሜ ተመልከት። ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት ወጥተው እውነተኛውን ሃይማኖት እንዲይዙ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ስናሳስብ ቆይተናል። (ራእይ 18:4, 5) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን እርምጃ ወስደዋል። የኢየሱስ ትንቢት ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንደሚመጡ አያመለክትም፤ በ66 እዘአ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ክርስትና እንዳልተለወጡ የተረጋገጠ ነው። ይሁንና እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲነሳሱ ትልቅ ማበረታቻ ይሆናቸዋል።
22. ኢየሱስ ወደ ተራራዎች እንድንሸሽ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ምንን የሚጨምር ሊሆን ይችላል?
22 በአሁኑ ጊዜ ታላቁን መከራ የሚመለከት ሙሉ ማብራሪያ ሊኖረን ባይችልም ኢየሱስ የተናገረለት ሽሽት በእኛ ሁኔታ ከአንድ አካባቢ ለቆ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድን አያመለክትም ወደሚል መደምደሚያ ብንደርስ ምክንያታዊ ነው። የአምላክ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያና በማንኛውም ቦታ ይገኛሉ። መሸሽ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ግን ክርስቲያኖች በእነሱና በሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጅቶች መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት መኖሩን በሚያሳይ መንገድ በመመላለስ መቀጠል እንደሚገባቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በተጨማሪም አንድ ሰው ልብሱን ወይም ሌሎች እቃዎቹን ለመሰብሰብ ወደ ቤቱ ተመልሶ እንዳይሄድ ኢየሱስ የሰጠው ማስጠንቀቂያም ትኩረት የሚያሻው ነው። (ማቴዎስ 24:17, 18) ስለዚህ ለቁሳዊ ነገሮች ባለን አመለካከት ረገድ ወደፊት የሚመጡ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በጣም አስፈላጊ የሆኑት ያሉን ቁሳዊ ነገሮች ናቸው ወይስ ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነው በአምላክ ጎን ለቆሙ ሰዎች የሚመጣው መዳን ነው? አዎን፣ ሽሽታችን አንዳንድ ችግሮችን ወይም እጦትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። ከይሁዳ ተነሥተው የዮርዳኖስን ወንዝ በማቋረጥ ወደ ፍርግያ እንደ ሸሹት እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁዎች መሆን አለብን።
23, 24. (ሀ) ጥበቃ የምናገኘው የት ብቻ ነው? (ለ) ኢየሱስ ‘በተቀደሰ ስፍራ ስለሚቆመው ርኩሰት’ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
23 ይሖዋንና ተራራ መሰል ድርጅቱን መጠጊያችን ማድረጋችንን መቀጠል አለብን። (2 ሳሙኤል 22:2, 3፤ መዝሙር 18:2፤ ዳንኤል 2:35, 44) ጥበቃ የምናገኘው እዚህ ነው! ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ ለጥቂት ጊዜ ብቻ በሚቆዩት ‘በዋሻዎችና በተራራ ዓለቶች’ በተመሰሉት ሰብዓዊ ድርጅቶችና ተቋሞች ውስጥ ከለላ ለማግኘት የሚሸሹትን ሰዎች አንመስልም። (ራእይ 6:15፤ 18:9-11) እርግጥ ጊዜያቱ በ66 እዘአ ይሁዳን ጥለው ለወጡት ርጉዝ ሴቶች ወይም ቀዝቃዛና ዝናባማ በሆነ ወቅት መጓዝ ለነበረበት ለማንኛውም ሰው አስቸጋሪ እንደነበሩ ሁሉ ወደፊትም ሁኔታዎች እየከበዱ ሊመጡ ይችላሉ። ሆኖም አምላክ በሕይወት እንድንተርፍ የሚያስችለንን ዝግጅት እንደሚያደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ እንኳ ሳይቀር በይሖዋና የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ባለው በልጁ ላይ ያለንን እምነት እናጠንክር።
24 ደግሞ ምን ይመጣ ይሆን ብለን በመስጋት በፍርሃት የምንኖርበት ምንም ምክንያት የለም። ኢየሱስ በዚያን ጊዜ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት እንዲዋጡ ፍላጎቱ አልነበረም፤ እኛም አሁንም ሆነ ወደፊት በፍርሃት እንድንዋጥ አይፈልግም። ልባችንንና አእምሯችንን እንድናዘጋጅ ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። ምንም ቢሆን ታዛዥ ክርስቲያኖች በሐሰት ሃይማኖትም ሆነ በተቀረው ክፉ ሥርዓት ላይ በሚመጣው ጥፋት አይቀጡም። ‘በተቀደሰው ስፍራ ላይ ስለሚቆመው ርኩሰት’ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ያስተውላሉ። እንዲሁም በማይናወጠው እምነታቸው ተጠቅመው እርምጃ ይወስዳሉ። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ሲል የገባውን ቃል ፈጽሞ አንዘንጋ።—ማርቆስ 13:13
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “የሮማውያኑ አርማዎች አምልኮታዊ ክብር ተሰጥቷቸው በሮም በሚገኙ ቤተ መቅደሶች ውስጥ ይቀመጡ ነበር፤ ሕዝቡ ለእነዚህ አርማዎች የነበረው የጠለቀ አክብሮት በሌሎች ብሔራት ላይ ከሚያገኘው የበላይነት የሚመነጭ ነበር። . . . [ወታደሮቹ] በምድር ላይ ከሚገኝ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ቅዱስ አድርገው የሚመለከቷቸው ነገሮች ሳይሆኑ አይቀሩም። ሮማውያን ወታደሮች የሚምሉት በራሳቸው አርማ ነበር።”—ዚ ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ 11ኛ እትም።
b የኢየሱስ ቃላት ከ66-70 እዘአ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው በታላቁ መከራ ወቅት እንዴት እንደሚፈጸሙ እንድናስተውል የሚረዳን ቢሆንም ፍጻሜዎቹ በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች ላይ የሚከናወኑ በመሆናቸው ሁለቱም ፍጻሜዎች ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይነት ይኖራቸዋል ማለት እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባል።
ታስታውሳለህ?
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን “የጥፋት ርኩሰት” ራሱን ያሳወቀው እንዴት ነበር?
◻ ዘመናዊው “ርኩሰት” በተቀደሰ ስፍራ ላይ የሚቆምበት ጊዜ ወደፊት ይመጣል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ በራእይ መጽሐፍ ላይ ‘ርኩሰቱ’ ስለሚሰነዝረው ጥቃት ምን ተተንብዮአል?
◻ በእኛ በኩል ምን ዓይነት “ሽሽት” ገና ይጠብቀን ይሆናል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታላቂቱ ባቢሎን ‘የጋለሞቶች እናት’ ተብላ ተጠርታለች
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተጠቀሰው ቀይ አውሬ ኢየሱስ የተናገረለት “ርኩሰት” ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀዩ አውሬ በሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ጥቃት ይሰነዝራል