ፍጻሜው ቀርቧል፤ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ
“ የነገሮች ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤ ለጸሎትም ሁልጊዜ ንቁዎች ሁኑ።” — 1 ጴጥሮስ 4:7 አዓት
1. (ሀ) አንድ የሃማኖት መሪና ተከታዮቻቸው ምን የሚያሳዝን ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር? (ለ) ይፈጸማሉ ተብለው የሚጠበቁ አንዳንድ ነገሮ ሳይፈጸሙ ስለሚቀሩ ምን ጥያቄዎች ይጠየቁ ይሆናል?
“በዛሬዋ ምሽት የመጨረሻዋን ጸሎቴን እያቀረብኩ ሳለ ከአምላክ አንድ ተልእኮ ተሰጠኝ። 116,000 ሰዎች ወደ ሰማይ ያርጋሉ፤ እንዲሁም አማኞች የነበሩ 3. 7 ሚልዮን ሙታን ወደ ሰማይ እንዲሄዱ መቃብራቸው ይከፈታል አለኝ።” ይህን ያሉት ሚሽን ፎር ዘ ካሚንግ ዴይስ የተባለው ድርጅት መሪ ሲሆኑ ይህንንም የመዓት ቀን ነው ብለው በተነበዩለት ቀን ዋዜማ ማለትም በጥቅምት 28, 1992 ነበር። መድረሱ አልቀረም ጥቅምት 29 ደረሰ። ሆኖም ወደ ሰማይ የወጣ አንድም ሰው አልነበረም፤ አንድም የሙታን መቃብር አልተከፈተም። መዓት ይመጣል ብለው የሚያምኑት ኮርያውያን ወደ ሰማይ ከመነጠቅ ይልቅ ያ ቀን እንደማንኛውም ቀን በሰላም ሲነጋ ተመለከቱ። መዓት ይመጣል የተባለበት የመጨረሻው ቀን መጣና አለፈ፤ ይሁን እንጂ የመዓት ቀን ይመጣል እያሉ የሚናገሩት ሰዎች ከአቋማቸው ፍንክች አላሉም። ታዲያ ክርስቲያኖች ማድረግ ያለባቸው ምንድን ነው? መጨረሻው በጣም እየቀረበ እንዳለ ማመናቸውን ማቆም ይኖርባቸዋልን?
2. ወደፊት ስለሚመጣው የፍርድ ቀን ለሐዋርያቱ የነገራቸው ማን ነው? እነሱስ ይህንን ያወቁት በምን ሁኔታዎች ሥር ሆነው ነው?
2 ይህን ጥያቄ ለመመለስ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የግል ውይይት ያደረገበትን ወቅት መለስ ብለን እናስታውስ። ኢየሱስ በፊሊጶስ ቂሳሪያ ወረዳ ከገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ምሥራቅ በሚገኘው በአስደናቂ ሁኔታ ግርማ ሞገሱን ተላብሶ ከጀርባቸው ጉብ ባለው የአርሞንዔም ተራራ አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደሚገደል በግልጽ ነገራቸው። (ማቴዎስ 16:21) ቀጥሎ በጥሞና እንዲያስቡ በሚያደርጓቸው ቃሎች አነጋገራቸው። ኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ዘወትር የራስን ጥቅም መሥዋዕት እያደረጉ መኖር ማለት መሆኑን ካብራራላቸው በኋላ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል” ሲል አስጠነቀቀ። (ማቴዎስ 16:27) ኢየሱስ ወደፊት ስለመምጣቱ ተናገረ። ሆኖም ዳግመኛ በሚመጣበት ወቅት ፈራጅ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ማንኛውም ሰው ፍርድ የሚሰጠው ግለሰቡ ኢየሱስን በታማኝነት የሚከተል በመሆኑ ወይም ባለመሆኑ ነው። የኢየሱስ ፍርድ የተመሠረተው አንድ ሰው በሚያደርገው ድርጊት ላይ ነው እንጂ አንድ ሰው በሚኖረው ዓለማዊ ንብረቶች ላይ አይደለም። ደቀ መዛሙርቱ በአዕምሮአቸው መያዝ የነበረባቸው ይህንን ሐቅ ነው። (ማቴዎስ 16:25, 26) እንግዲያው ተከታዮቹ በክብር ለፍርድ የሚመጣበትን ጊዜ እንዲጠብቁ የነገራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው።
3. ኢየሱስ የወደፊት መምጣቱን እርግጠኝነት በሚገባ ያብራራው እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት መምጣቱ የማይቀር መሆኑን በግልጽ ያስረዳሉ። እንዲህ ሲል በእርግጠኝነት ተናገረ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።” (ማቴዎስ 16:28) እነዚህ ቃላት ከስድስት ቀን በኋላ ተፈጽመዋል። ኢየሱስ በሚያንጸባርቅ ሁኔታ ተለውጦ መታየቱ በጣም የሚቀርቡትን ደቀ መዛሙርቱን አስደነቃቸው። የኢየሱስ ፊት እንደ ፀሐይ ሲያበራና ልብሱ ነጭ ሆኖ ሲያንጸባርቅ ተመልክተዋል። የክርስቶስ መለወጥ የወደፊቱን ክብሩንና መንግሥቱን የሚያመለክት ነበር። የመንግሥቱ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ የሚያሳይ እንዴት ያለ ጠንካራ ማረጋገጫ ነው! ደቀ መዛሙርቱ ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንዴት ያለ ኃይለኛ ማበረታቻ ነው! — 2 ጴጥሮስ 1:16–19
ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
4. ክርስቲያኖች ስለእሱ መምጣት በመንፈሳዊ ንቁዎች መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
4 ከአንድ ዓመት ከሚያንስ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ በድጋሚ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በግል ሲወያይ እናገኘዋለን። የኢየሩሳሌምን ከተማ ትኩር ብለው እየተመለከቱ ሳሉ የእሱ የወደፊት መገኘት ምልክቶች ምን እንደሆኑ ከገለጸላቸው በኋላ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ሲል አስጠነቀቃቸው። የሚመጣበት ጊዜ ስለማይታወቅ ተከታዮቹ ምንጊዜም ንቁዎችና ዝግጁዎች መሆን አለባቸው። — ማቴዎስ 24:42
5. ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
5 ጌታ የሚመጣበት ሁኔታ ከሌባ ጋር ይመሳሰላል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ያን ግን እወቁ፣ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወም ነበር።” (ማቴዎስ 24:43) አንድ ሌባ የሚመጣበትን ጊዜ ለቤቱ ባለቤት አይናገርም። ዋና የማጥቂያ መሣሪያውም ሳይታሰብ መምጣት ነው። ስለዚህ የቤቱ ባለቤት ሁልጊዜ ንቁ ሆኖ መጠበቅ አለበት። ሆኖም ታማኝ ክርስቲያኖች ያለማቋረጥ ንቁዎች ሆነው የሚጠብቁት አንድ አደጋ ይደርስብናል ብለው በመስጋት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ክርስቶስ አንድ ሺህ የሰላም ዓመት ይዞ በክብር የሚመጣበትን ጊዜ የሚጠባበቁት በጉጉት ተገፋፍተው ነው።
6. በአስተሳሰብ ጤናሞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
6 ምንም እንኳን አንድ ሰው ነቅቶ ቢጠብቅም ኢየሱስ የሚመጣበትን ትክክለኛ ቀን በቅድሚያ ሊገምት አይችልም። ኢየሱስ እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” (ማቴዎስ 24:44) እንግዲያው ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ አስፈላጊ ነው። አንድ ክርስቲያን በአንድ የተወሰነ ቀን ላይ ክርስቶስ አይመጣም ብሎ ቢያስብ ክርስቶስ የሚመጣው በዚያው አይመጣም ብሎ ባሰበበት ቀን ሊሆን ይችላል! እርግጥ ቅን ልብ ያላቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ባለፉት ጊዜያት መጨረሻው የሚመጣበትን ጊዜ በቅንነት ለመተንበይ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” የሚለው የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ እውነት መሆኑ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። — ማቴዎስ 24:36
7. የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን እንዴት ዓይነት አኗኗር መኖር አለብን?
7 እንግዲያው ምን ብለን መደምደም ይኖርብናል? የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን ምንጊዜም የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በቅርቡ እንደሚከሰት በማመን መኖር አለብን።
8. ከጥንት የክርስትና ዘመን ጀምሮ የክርስቲያኖች መለያ ምልክት የሆነው ምንድን ነው?
8 ዓለማዊ ታሪክ ጸሐፊዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደተገነዘቡት እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ከጥንት ጀምሮ የክርስቲያኖች መለያ ምልክት ሆኖ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል ዘ ትራንስሌተርስ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ አዘጋጂዎች በቃላት መፍቻቸው ውስጥ “ቀን” (“ዴይ”) በሚለው ቃል ሥር የሚከተለውን ይገልጻሉ:- “የአዲስ ኪዳን ዘመን ክርስቲያኖች የአሁኑ ዓለም ከመጥፎ ድርጊቱና ከክፋቱ ጋር ወደ ፍጻሜው የሚመጣበትንና ኢየሱስ በሰው ዘሮች ሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ አዲስ የሰላም ዘመን ለመክፈትና በጠቅላላው ዓለም ላይ ጌታ ለመሆን ወደ ምድር የሚመለስበትን ቀን (ማለትም ጊዜውን) ሲጠባበቁ ቆይተዋል።” ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ልዩ የሆነው ዓለም አቀፉ የክርስትና መስፋፋት ክርስቲያኖች የፍጻሜውን ዘመን ከመጠበቃቸው ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስን በቅርብ ጊዜ መመለስ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው። አንድ ክርስቲያን የፍጻሜውን ዘመን ሲጠባበቅ እንዲሁ ያለምንም እንቅስቃሴ ይናፍቃታል ማለት አይደለም።”
ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ ምን ማለት ነው?
9. ምንም እንኳን ጴጥሮስ ስለ መሲሑ የነበሩት አንዳንድ ግምቶች ትክክል ባይሆኑም በትምክህት ለመቆየት የቻለው ለምንድን ነው?
9 ኢየሱስ ከቅርብ ደቀ መዛሙርቱ ጋር የወዳጅነት ውይይት ካደረገ ከ30 ዓመት በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚመጣውን የፍጻሜ ዘመን መጠበቅ አልሰለቸውም። ምንም እንኳ እሱና መሰል ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያ መሲሁን የጠበቁበት መንገድ ትክክል ባይሆንም ተስፋቸው እንደሚፈጸም የይሖዋ ፍቅርና ኃይል ዋስትና ሆኖት በትምክህት መጠባበቁን ቀጥሏል። (ሉቃስ 19:11፤ 24:21፤ ሥራ 1:6፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 10) “ዳሩ ግን የነገሮች ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል” ሲል በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ጎልቶ የተገለጸ አንድ ነጥብ ተናግሯል። ከዚያም “ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤ ለጸሎትም ሁልጊዜ ንቁዎች ሁኑ” በማለት መሰል ክርስቲያኖችን አጥብቆ አሳስቧል። — 1 ጴጥሮስ 4:7
10. (ሀ) ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ ምን ማለት ነው? (ለ) ነገሮችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ካላቸው ተገቢ ግንኙነት አኳያ መመልከት ምን ማድረግን ይጨምራል?
10 “ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ” ማለት ከዓለማዊ አመለካከት አንጻር ብልጥ መሆን ማለት አይደለም። ይሖዋ “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 1:19) ጴጥሮስ የተጠቀመበት ቃል “በአስተሳሰብ አስተዋይ መሆን” ማለት ሊሆን ይችላል። ይህ መንፈሳዊ አስተዋይነት ከአምልኮታችን ጋር የተያያዘ ነው። ስለዚህ በአስተሳሰብ ረጋ ያልን መሆናችን ነገሮችን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ባላቸው ትክክለኛ ግንኙነት እንድናያቸው ያደርገናል፤ የትኞቹ ነገሮች በጣም አስፈላጊ እንደሆኑና የትኞቹ ደግሞ አስፈላጊ እንዳልሆኑ እንለያለን። (ማቴዎስ 6:33, 34) ምንም እንኳን መጨረሻው በቅርቡ የሚመጣ ቢሆንም መረን በለቀቀ የአኗኗር ዘይቤ ተጠርገን አንወሰድም፤ ወይም ደግሞ በምንኖርበት ዘመን ውስጥ ስላለው የጊዜ ሁኔታ ግድየለሾች አንሆንም። (ከማቴዎስ 24:37–39 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በጠባያችን የምናሳየው ልከኝነትና ሚዛናዊነት በመጀመሪያ ለአምላክ (‘ለጸሎትም ሁልጊዜ ንቁዎች በመሆን’) ከዚያም (‘እርስ በርሳችሁ የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ’ በሚለው መሠረት) ለጎረቤቶቻችን መገለጽ አለበት። — 1 ጴጥሮስ 4:7, 8
11. (ሀ) “[የእኛን] አእምሮ በሚያንቀሳቅሰው ኃይል አማካኝነት አዲስ መሆን” ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) አዲስ የአእምሮ ኃይል ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?
11 ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ “[የእኛን] አእምሮ በሚያንቀሳቅሰው ኃይል አማካኝነት አዲስ” መሆናችንን ይጨምራል። (ኤፌሶን 4:23 አዓት) አዲስ የምንሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አለፍጽምናን ስለወረስንና ኃጢአተኛ በሆነ አካባቢ ውስጥ ስለምንኖር አእምሮአችን ከመንፈሳዊነት ጋር በሚቃረኑ ዝንባሌዎች ተጽዕኖ ስለሚደርስበት ነው። ይህ ኃይል አስተሳሰባችንንና ዝንባሌያችንን በፍቅረ ንዋይ እንዲጠመድና ራስወዳድ እንዲሆን በሚያደርገው አቅጣጫ እንዲጓዝ ያለማቋረጥ ይገፋዋል። ስለሆነም አንድ ሰው ክርስቲያን ሲሆን አስተሳሰቡን በትክክለኛው አቅጣጫ ማለትም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ዝግጁ ወደሆነ መንፈሳዊ አቅጣጫ የሚገፋ አዲስ ኃይል ወይም ኃይለኛ የአእምሮ ዝንባሌ ያስፈልገዋል። በዚህ መንገድ ለምሳሌ ትምህርትን፣ በአንድ ዓይነት ሥራ ባለሞያ ለመሆን የሚስችል ሥልጠናን፣ ተቀጥሮ መሥራትን፣ መዝናኛን፣ የጊዜ ማሳለፊያን የአለባበስ ፋሽንን ወይም ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ምርጫ ሲቀርብለት የመጀመሪያ ዝንባሌው ጉዳዩን ሥጋዊና ራስወዳድ በሆነ አመለካከት ከማየት ይልቅ በመንፈሳዊ አመለካከት ያየዋል። ይህ አዲስ የአእምሮ ዝንባሌ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝና መጨረሻው ቅርብ መሆኑን ባለመዘንጋት የሚያጋጥሙትን ነገሮች ለመወሰን ቀላል ያደርግለታል።
12. ‘በእምነት ጤናሞች’ ሆነን ለመቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
12 በአስተሳሰብ ጤናማ መሆን በጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት ላይ እንደምንገኝ ያሳያል። ‘በእምነት ጤናሞች’ ሆነን ለመቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? (ቲቶ 2:2) አእምሮአችንን ትክክለኛውን ዓይነት ምግብ መመገብ አለብን። (ኤርምያስ 3:15) ያለማቋረጥ የአምላክን ቃል እውነት መመገቡ ቅዱስ መንፈሱ በሚሠራው ሥራ ሲታገዝ መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። እንግዲያው በግል ጥናት እንዲሁም በመስክ አገልግሎት፣ በጸሎትና በክርስቲያናዊ ስብሰባ አዘውታሪ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው።
ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ የሚጠብቀን እንዴት ነው?
13. ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ የቂልነት ስህተቶችን ከመፈጸም ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?
13 ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ የዘላለም ሕይወት የሚያሳጣንን የቂልነት ስህተት ከመፈጸም ሊጠብቀን ይችላል። ይህ የሚቻለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የአእምሮ ሕግ’ በማለት ይናገራል። በእምነት ጤናማ የሆነ አንድ ሰው የአእምሮው ሕግ የሚመራው ደስ በሚሰኝበት ማለትም “በእግዚአብሔር ሕግ” ነው። እውነት ነው፣ ‘የኃጢአት ሕግ’ ከአእምሮ ሕግ ጋር ይዋጋል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን በይሖዋ እርዳታ ድል አድራጊ ሊሆን ይችላል። — ሮሜ 7:21–25
14, 15. (ሀ) አእምሮን ለመቆጣጠር የሚታገሉት የትኞቹ ሁለት ተጽዕኖዎች ናቸው? (ለ) በአእምሮአችን ውስጥ ያለውን ውጊያ ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ ራስን ብቻ በማስደሰት ላይ ትኩረት በሚያደርግ በኃጢአተኛ ሥጋ በሚገዛ አእምሮ ለይሖዋ አገልግሎት ሲል የራስን ጥቅም በመሠዋት አኗኗር ላይ ትኩረት በሚያደርግ በአምላክ መንፈስ በሚገዛ አእምሮ መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት ያነጻጽራል። ጳውሎስ በሮሜ 8:5–7 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፣ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፣ መገዛትም ተስኖታል።”
15 ከዚያም ጳውሎስ በቁጥር 11 ላይ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚተባበረው አእምሮ እንዴት በውጊያው እንደሚያሸንፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፣ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።”
16. ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ ከምን ማባበያዎች ይጠብናቀናል?
16 ስለዚህ በአስተሳሰብ ጤናማ በመሆን መረን በለቀቁት በሁሉም ዓይነት ተድላዎቹ፣ በቁሳዊ ነገሮቹና በጾታ ብልግናው ተለይቶ በሚታወቀው በየትም ሥፍራ በሚገኘው በዚህ ዓለም ማባበያ አንታለልም። ጤናማው አስተሳሰባችን ‘ከዝሙት እንድንሸሽና’ ከሚያስከትላቸው አስከፊ ውጤቶች እንድናመልጥ ይነግረናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ጤናማ የሆነው አእምሮ ዝንባሌያችን የመንግሥቱን ፍላጎት እንድናስቀድም ግድ ይለናል። እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያዳክምብን የሚችል ቋሚ የሆነ ሰብአዊ ሥራ እንድንይዝ በሚቀርብልን ግብዣ በምንፈተንበት ጊዜ አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል።
17. አንዲት አቅኚ እኅት ገንዘብ ነክ ግዴታ ባጋጠማት ጊዜ ጤናማ አስተሳሰብ እንዳላት ያሳየችው እንዴት ነበር?
17 ለምሳሌ ያህል በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ በምትገኝ አንዲት ሞቃት አገር ውስጥ የምትኖር የመንግሥቱን ፍላጎት በአእምሮዋ ውስጥ በአንደኛ ቦታ ላይ ያስቀመጥች አንዲት ወጣት እኅት አለች። ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ፍቅር ኮትኩታ ነበር። በዚያ አገር አብዛኞቹ ሥራዎች ስድስት ወይም ሰባት ቀን ሙሉ ጊዜ መሥራትን ይጠይቃሉ። የይሖዋ ምስክር ያልሆነው አባቷ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች በኋላ ለቤተሰቡ ከፍተኛ ገንዘብ ታመጣለች ብሎ ይጠብቅ ነበር። ይሁን እንጂ አቅኚ ለመሆን ጠንካራ ፍላጎት ስለነበራት የግማሽ ቀን ሥራ አገኘችና አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ይህም አባቷን በጣም አናደደው። ንብረትሽን ሁሉ አውጥቼ መንገድ ላይ እጥለዋለሁ ብሎ አስፈራራት። በቁማር ምክንያት ከባድ ዕዳ ውስጥ ስለተዘፈቀ ልጁ እዳውን ሁሉ እንደምትከፍልለት ይጠብቅ ነበር። ታናሽ ወንድሟ ዩኒቨርሲቲ እየተማረ ቢሆንም በእዳው ምክንያት የሚከፍለው የመማሪያ ገንዘብ አልነበረም። እርሷ ከረዳችው ታናሽ ወንድሟ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ሥራ ሲያገኝ ቤተሰቡን እንደሚረዳ ቃል ገባላት። ለወንድሟ ባላት ፍቅርና ለአቅኚነት አገልግሎት ባላት ፍቅር መካከል ልቧ ለሁለት ተከፈለ። ስለ ጉዳዩ በጥንቃቄ ካሰበችበት በኋላ በአቅኚነቱ ለመቀጠልና ሌላ ዓይነት ሥራ ለመፈለግ ወሰነች። ቤተሰቦቿንና ወንድሟን በገንዘብ ለመርዳት ብቻ ሳይሆን በጣም የምትወደውን የአቅኚነት አገልግሎት ለመቀጠል የሚያስችላት ጥሩ ሥራ በማግኘት ለጸሎቷ መልስ አገኘች።
ጤናማ አስተሳሰብን ይዛችሁ ለመቆየት የይሖዋን እርዳታ አጥብቃችሁ ፈልጉ
18. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ተስፋ የመቁረጥ ስሜት የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) እነዚህን የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚሰማቸውን ሰዎች የትኞቹ ጥቅሶች ሊያጽናኗቸው ይችላሉ ይሆናል?
18 አንዳንድ የክርስቶስ ተከታዮች ያገኙትን ጤናማ አስተሳሰብ ይዞ መቆየቱ አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል። ይህ የአሁኑ ክፉ ሥርዓት እነሱ ከጠበቁት በላይ በመዘግየቱ ትዕግሥታቸው እየቀነሰ ይሄድ ይሆናል። ተስፋ ሊቆርጡም ይችላሉ። ይሁን እንጂ መጨረሻው ይመጣል። ይሖዋ ቃል ገብቷል። (ቲቶ 1:2) እንዲሁም ቃል የገባልልን ምድራዊ ገነት ያመጣል። ለዚህም ይሖዋ ዋስትና ሰጥቷል። (ራእይ 21:1–5) አዲሱ ዓለም ሲመጣ ጤናማ አስተሳሰብ ለያዙት ሁሉ የሚሆን “የሕይወት ዛፍ” ይኖራል። — ምሳሌ 13:12
19. ጤናማ አስተሳሰብን ይዞ መቆየት የሚቻለው እንዴት ነው?
19 ጤናማ አስተሳሰብን ይዘን መቆየት የምንችለው እንዴት ነው? የይሖዋን እርዳታ አጥብቀን እንፈልግ። (መዝሙር 54:4) ወደ እሱ ተጠግተን እንኑር። ይሖዋ ከእኛ ጋር የቅርብ ወዳጅ ለመሆን እንደሚፈልግ ማወቃችን ምንኛ ያስደስተናል! ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 4:8) ጳውሎስ እንዲህ ይላል:- “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:4–7) የዚህ እየሞተ ያለው የነገሮች ሥርዓት ጫናዎችን መሸከም እንደማትችል ሆኖ ከተሰማህ ሸክሞቹን ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣላችው፤ እሱም ደግፎ ያቆምሃል። — መዝሙር 55:22
20. በ1 ጢሞቴዎስ 4:10 መሠረት ምን ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል?
20 አዎ፣ መጨረሻው ቅርብ ነው፤ ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ! ከ1,900 ዓመታት በፊት ይህ ምክር ግሩም ነበር፤ ዛሬም በጣም አስፈላጊ የሆነ ምክር ነው። ይሖዋ ወደ እሱ አዲስ ዓለም እየተንከባከበ መምራቱን በቀጠለ መጠን በጤናማ የማሰብ ኃይላችን ተጠቅመን እሱን ማመስገናችንን አናቋርጥ። — 1 ጢሞቴዎስ 4:10
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ጤናማ አስተሳሰብ ሲባል ምን ማለት ነው?
◻ በአስተሳሰብ ጤናማ መሆን በጣም አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ አእምሮአችንን በሚያንቀሳቅሰው ኃይል አዲስ ለመሆን የምንችለው እንዴት ነው?
◻ በአእምሮአችን ውስጥ ምን የማያቋርጥ ውጊያ ማድረግ አለብን?
◻ ጤናማ አስተሳሰብን ይዘን የምንቆየው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ መቅረብ ጤናማ አስተሳሰብን ይዘን ለመቆየት ይረዳናል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአስተሳሰብ ጤናሞች ከሆንን በዚህ ዓለም ማባበያዎች አንታለልም