የማቴዎስ ወንጌል
24 ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ እየሄደ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እሱ ቀረቡ። 2 እሱም መልሶ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አላቸው።+
3 በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና*+ የዚህ ሥርዓት* መደምደሚያ+ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት።
4 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤+ 5 ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ።+ 6 ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። በዚህ ጊዜ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+
7 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና+ የምድር ነውጥ ይከሰታል።+ 8 እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
9 “በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣+ ይገድሏችኋል+ እንዲሁም በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።+ 10 በተጨማሪም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ። 11 ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤+ 12 ክፋት* እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል። 13 እስከ መጨረሻው የጸና* ግን ይድናል።+ 14 ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤+ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።
15 “ስለዚህ ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’ በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ስታዩ+ አንባቢው ያስተውል፤ 16 በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 17 በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለመውሰድ አይውረድ፤ 18 በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ አይመለስ። 19 በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! 20 ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት* ቀን እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 21 ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ ታላቅ መከራ+ ይከሰታል። 22 እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ሆኖም ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ።+
23 “በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’+ ወይም ‘ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 24 ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ።+ 25 እንግዲህ አስቀድሜ አስጠንቅቄያችኋለሁ። 26 ስለዚህ ሰዎች ‘እነሆ፣ በምድረ በዳ ነው’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘እነሆ፣ ቤት ውስጥ በውስጠኛው ክፍል ይገኛል’ ቢሏችሁ አትመኑ።+ 27 መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚያበራ ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም* እንዲሁ ይሆናል።+ 28 በድን ባለበት ሁሉ ንስሮች ይሰበሰባሉ።+
29 “በእነዚያ ቀናት ከሚኖረው መከራ በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤+ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ።+ 30 ከዚያም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ የምድር ወገኖችም ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ፤+ የሰው ልጅም+ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 31 እሱም መላእክቱን በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ እነሱም ከአራቱ ነፋሳት፣* ከአንዱ የሰማይ ዳርቻ እስከ ሌላው የሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።+
32 “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 33 በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 34 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም። 35 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+
36 “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣+ ማንም አያውቅም።+ 37 በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ+ የሰው ልጅ መገኘትም* እንደዚሁ ይሆናል።+ 38 ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን+ ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ 39 የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤+ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። 40 በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው እዚያው ይተዋል። 41 ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ እዚያው ትተዋለች።+ 42 ስለዚህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።+
43 “ነገር ግን ይህን እወቁ፦ አንድ ሰው ሌባ+ በየትኛው ክፍለ ሌሊት* እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር።+ 44 ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።+
45 “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም* ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?+ 46 ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው!+ 47 እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።
48 “ነገር ግን ያ ክፉ ባሪያ በልቡ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብ+ 49 ደግሞም ባልንጀሮቹ የሆኑትን ባሪያዎች መደብደብ ቢጀምር እንዲሁም ከሰካራሞች ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ 50 የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ይመጣል፤+ 51 ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል፤* ዕጣውንም ከግብዞች ጋር ያደርገዋል። በዚያም ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል።+