የጥናት ርዕስ 5
ከእናንተ ጋር እንሄዳለን
“አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን።”—ዘካ. 8:23
መዝሙር 26 ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል
ማስተዋወቂያa
1. ይሖዋ ስለ ዘመናችን ምን ትንቢት ተናግሯል?
ይሖዋ ስለ ዘመናችን የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’ ይላሉ።” (ዘካ. 8:23) እዚህ ላይ የተጠቀሰው “አይሁዳዊ” አምላክ በመንፈስ ቅዱስ የቀባቸውን ሰዎች ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብለውም ተጠርተዋል። (ገላ. 6:16) ‘አሥሩ ሰዎች’ ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች፣ ይሖዋ ቅቡዓኑን እየባረካቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ ከእነሱ ጋር ሆነው ይሖዋን ማምለካቸውን እንደ መብት ይቆጥሩታል።
2. ‘አሥሩ ሰዎች’ ከቅቡዓኑ ጋር ‘የሚሄዱት’ እንዴት ነው?
2 በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያለውን የእያንዳንዱን ቅቡዕ ስም ማወቅ ባይቻልም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከቅቡዓኑ ጋር ‘መሄድ’ ይችላሉ።b እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ “አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’” እንደሚሉ ይናገራል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው አይሁዳዊ አንድ ነው። ያም ሆኖ “ከእናንተ” ከሚለው ቃል ማየት እንደሚቻለው ሐሳቡ የሚያመለክተው ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን ነው። እንግዲያው እዚህ ላይ የተገለጸው አይሁዳዊ አንድን ሰው ሳይሆን ሁሉንም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያመለክት ነው! በመንፈስ ቅዱስ ያልተቀቡ ክርስቲያኖች ከቅቡዓኑ ጋር ሆነው ይሖዋን ያገለግላሉ። ይሁንና መሪያቸው ኢየሱስ እንደሆነ ስለሚገነዘቡ ቅቡዓኑን እንደ መሪዎቻቸው አድርገው አይመለከቷቸውም።—ማቴ. 23:10
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?
3 በዛሬው ጊዜ ከአምላክ ሕዝቦች መካከል የተወሰኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመሆናቸው አንዳንዶች የሚከተሉት ጥያቄዎች ይፈጠሩባቸው ይሆናል፦ (1) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? (2) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ ለሚወስዱት ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (3) ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱት ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ሊያሳስበን ይገባል? ይህ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
ቅቡዓን ስለ ራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
4. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1 ቆሮንቶስ 11:27-29 ላይ የሚገኘውን የትኛውን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል? ለምንስ?
4 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1 ቆሮንቶስ 11:27-29 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል። (ጥቅሱን አንብብ።) አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን “የማይገባው ሆኖ ሳለ” በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚኖረው ቂጣና የወይን ጠጅ ሊወስድ የሚችለው እንዴት ነው? አኗኗሩ ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የማይስማማ ሆኖ ሳለ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ከወሰደ ነው። (ዕብ. 6:4-6፤ 10:26-29) ቅቡዓን ክርስቲያኖች “አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሰጠውን የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” ማግኘት ከፈለጉ በታማኝነት መጽናት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።—ፊልጵ. 3:13-16
5. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
5 የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ፣ ትዕቢተኛ ከመሆን ይልቅ ትሑታን እንዲሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን ይረዳቸዋል። (ኤፌ. 4:1-3፤ ቆላ. 3:10, 12) በመሆኑም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ አይሰማቸውም። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ በመንፈስ ስለተቀቡ ብቻ ይሖዋ ለሌሎች አገልጋዮቹ ከሚሰጠው የበለጠ መንፈስ ቅዱስ እንደሰጣቸው አድርገው አያስቡም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ከሌሎች የበለጠ ጥልቅ እውቀት እንዳላቸውም አይሰማቸውም። በተጨማሪም ለማንም ሰው፣ በመንፈስ እንደተቀባና በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መውሰድ እንደሚገባው የሚገልጽ ሐሳብ ፈጽሞ አይሰነዝሩም። ከዚህ ይልቅ ወደ ሰማይ የሚሄዱትን የሚጋብዘው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ በትሕትና አምነው ይቀበላሉ።
6. በ1 ቆሮንቶስ 4:7, 8 መሠረት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል?
6 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ጥሪ ማግኘት ታላቅ መብት እንደሆነ ቢሰማቸውም ሌሎች የተለየ ክብር እንዲሰጧቸው አይጠብቁም። (ፊልጵ. 2:2, 3) ከዚህም ሌላ ይሖዋ እነሱን ሲቀባቸው፣ መመረጣቸውን ሰው ሁሉ እንዲያውቅ እንዳላደረገ ይገነዘባሉ። በመሆኑም አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን፣ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን አንዳንዶች ወዲያውኑ ባያምኑ ሊገረም አይገባም። እንዲያውም ይህ ክርስቲያን፣ ከአምላክ ልዩ ኃላፊነት እንዳገኘ የሚናገርን ሰው ቶሎ ማመንን መጽሐፍ ቅዱስ እንደማያበረታታ ይገነዘባል። (ራእይ 2:2) አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሱ መሳብ ስለማይፈልግ ከሰዎች ጋር ሲተዋወቅ ቅቡዕ መሆኑን አይናገርም። ሰማያዊ ሽልማቱን እያነሳም አይኩራራም።—1 ቆሮንቶስ 4:7, 8ን አንብብ።
7. ቅቡዓኑ ምን ከማድረግ ይቆጠባሉ? ለምንስ?
7 ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ቡድን አባላት እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ከሌሎች ቅቡዓን ጋር ብቻ ጊዜያቸውን ለማሳለፍ አይሞክሩም። በተጨማሪም ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በመፈለግ ከእነሱ ጋር ስለ ጥሪያቸው ለማውራት ወይም የራሳቸውን ቡድኖች አቋቁመው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥረት አያደርጉም። (ገላ. 1:15-17) ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ የጉባኤው አንድነት ይናጋል። እንዲህ ያለው አካሄድ፣ የአምላክ ሕዝቦች ሰላምና አንድነት እንዲኖራቸው ከሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ጋር ይጋጫል።—ሮም 16:17, 18
ሌሎች ለቅቡዓኑ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
8. በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚወስዱ ክርስቲያኖች ባለን አመለካከት ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
8 ለቅቡዓን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? አንድ ሰው የክርስቶስ ቅቡዕ ወንድም ቢሆንም እንኳ ለዚህ ግለሰብ ከልክ ያለፈ አክብሮት መስጠት ስህተት ነው። (ማቴ. 23:8-12) መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎችን ‘በእምነታቸው እንድንመስላቸው’ ቢያበረታታንም ማንኛውንም ሰው መሪያችን አድርገን መከተል እንዳለብን አይናገርም። (ዕብ. 13:7) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች “እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው” እንደሚገባ ይገልጻል። እንዲህ ያለ ክብር የሚሰጣቸው ግን በመንፈስ ስለተቀቡ ሳይሆን ‘በመልካም ሁኔታ ስለሚያስተዳድሩ’ እንዲሁም ‘በመናገርና በማስተማር ተግተው ስለሚሠሩ’ ነው። (1 ጢሞ. 5:17) የተቀቡ ክርስቲያኖችን ከልክ በላይ የምናደንቃቸው ወይም ትኩረት የምንሰጣቸው ከሆነ እንዲጨንቃቸው እናደርጋለን።c ከዚህ የባሰው ደግሞ እንዲህ ያለው ትኩረት፣ ኩሩ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። (ሮም 12:3) ማናችንም ብንሆን የክርስቶስ ቅቡዕ ወንድሞች እንዲህ ያለ ከባድ ስህተት እንዲሠሩ ምክንያት መሆን አንፈልግም!—ሉቃስ 17:2
9. ለቅቡዓን ክርስቲያኖች አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9 ታዲያ ይሖዋ በመንፈስ ለሚቀባቸው ሰዎች አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በመንፈስ መቀባታቸውን ያወቁት እንዴት እንደሆነ ልንጠይቃቸው አይገባም። ይህ እኛን የማይመለከተን የግል ጉዳይ ነው። (1 ተሰ. 4:11፤ 2 ተሰ. 3:11) ከዚህም ሌላ በመንፈስ የተቀባው ግለሰብ የትዳር ጓደኛ፣ ወላጆች ወይም ሌሎች የቤተሰብ አባላትም ቅቡዕ እንደሆኑ አድርገን ልናስብ አይገባም። ሰማያዊ ጥሪ ከቤተሰብ የሚወረስ ነገር አይደለም። እንዲህ ያለውን ግብዣ የሚያቀርበው አምላክ ነው። (1 ተሰ. 2:12) በተጨማሪም ሌሎች እንዲያዝኑ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥያቄዎች ከማንሳት መቆጠብ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ ቅቡዕ የሆነ ባል ያላትን አንዲት እህት፣ ወደፊት ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ ከባለቤቷ ጋር እንደማትኖር ስታስብ ምን እንደሚሰማት ልንጠይቃት አይገባም። ደግሞም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—መዝ. 145:16
10. ‘ሌሎችን ከመካብ’ መቆጠባችን ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?
10 ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሌሎች የበለጠ ቦታ አለመስጠታችን ለእኛም ጥበቃ ይሆንልናል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝነታቸውን ሊያጎድሉ እንደሚችሉ ይናገራል። (ማቴ. 25:10-12፤ 2 ጴጥ. 2:20, 21) ‘ሌሎችን ከመካብ’ የምንቆጠብ ከሆነ ቅቡዓንን ጨምሮ በሌሎች ዘንድ በስፋት የሚታወቅም ሆነ ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገለ የማንኛውም ሰው ተከታይ አንሆንም። (ይሁዳ 16) እንዲህ ማድረጋችን፣ ግለሰቡ ታማኝነቱን ቢያጎድል ወይም ከጉባኤ ቢርቅ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዳናጣ አሊያም እሱን ማገልገላችንን እንዳናቆም ጥበቃ ይሆንልናል።
በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱት ሰዎች ቁጥር ሊያሳስበን ይገባል?
11. በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ በሚወስዱት ሰዎች ቁጥር ላይ ምን ለውጥ ታይቷል?
11 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ለበርካታ ዓመታት እየቀነሰ ሲሄድ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ነው። ታዲያ ቁጥሩ መጨመሩ ሊያሳስበን ይገባል? አይገባም። በዚህ ረገድ በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።
12. በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ሊያሳስበን የማይገባው ለምንድን ነው?
12 “ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል።” (2 ጢሞ. 2:19) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎችን የሚቆጥሩት ወንድሞች ግን በእርግጥ በመንፈስ የተቀባው ማን እንደሆነ ማወቅ አይችሉም። በመሆኑም ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱት ሰዎች ቁጥር፣ ቅቡዓን ነን ብለው በስህተት የሚያስቡ ሰዎችንም ይጨምራል። ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ይወስዱ የነበሩ አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ ይህን ማድረጋቸውን አቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ አድርገው የሚያስቡት ከአእምሮ ወይም ከስሜት ጋር የተያያዘ ችግር ስላለባቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን ትክክለኛ ቁጥር አናውቅም።
13. ታላቁ መከራ ሲጀምር በምድር ላይ የሚኖሩት ቅቡዓን ቁጥር ምን ያህል እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል?
13 ኢየሱስ ቅቡዓኑን ወደ ሰማይ ለመውሰድ በሚመጣበት ጊዜ በብዙ የዓለም ክፍሎች ቅቡዓን ይኖራሉ። (ማቴ. 24:31) እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት በምድር ላይ የሚቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጥቂት እንደሚሆኑ ይናገራል። (ራእይ 12:17) ይሁንና ታላቁ መከራ ሲጀምር በምድር ላይ ምን ያህል ቅቡዓን እንደሚኖሩ አይናገርም።
14. በሮም 9:11, 16 መሠረት ቅቡዓን ከሚመረጡበት መንገድ ጋር በተያያዘ ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
14 ቅቡዓንን የሚመርጥበትን ጊዜ የሚወስነው ይሖዋ ነው። (ሮም 8:28-30) ይሖዋ ቅቡዓንን መምረጥ የጀመረው ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ቅቡዓን ሳይሆኑ አይቀሩም። ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት ውስጥ፣ ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች አልነበሩም። ያም ቢሆን በእነዚህ ዓመታት የነበሩትን ጥቂት እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ በመንፈስ ቀብቷቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ኢየሱስ እንደጠቀሰው በእንክርዳድ መካከል ያደገ ስንዴ ናቸው። (ማቴ. 13:24-30) በመጨረሻዎቹ ቀናትም ይሖዋ የ144,000ዎቹ አባላት የሚሆኑ ሰዎችን መምረጡን ቀጥሏል።d ይሖዋ ለዚህ መብት ብቁ የሚሆኑ አንዳንድ ሰዎችን መጨረሻው ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለመምረጥ ከፈለገ በእሱ ጥበብ ላይ ጥያቄ ለማንሳት እኛ ማን ነን? (ሮም 9:11, 16ን አንብብ።)e ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ እንደጠቀሳቸው ሠራተኞች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። እነዚህ ሠራተኞች፣ ጌታቸው በመጨረሻው ሰዓት ለተቀጠሩት ሰዎች ባደረገው ነገር አጉረምርመዋል።—ማቴ. 20:8-15
15. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በማቴዎስ 24:45-47 ላይ የተጠቀሰው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ክፍል ናቸው? አብራራ።
15 በሰማይ የመኖር ተስፋ ካላቸው መካከል ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ክፍል የሆኑት ሁሉም አይደሉም። (ማቴዎስ 24:45-47ን አንብብ።) እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዛሬው ጊዜም ይሖዋና ኢየሱስ በጥቂት ወንድሞች ተጠቅመው ብዙኃኑን እየመገቡ ወይም እያስተማሩ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማስጻፍ የተጠቀመው በጥቂት ቅቡዓን ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ ለአምላክ ሕዝብ “በተገቢው ጊዜ” መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት ያለባቸው ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው።
16. ከዚህ ርዕስ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
16 ከዚህ ርዕስ ምን ትምህርት አግኝተናል? ይሖዋ ለአብዛኞቹ የሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ ለጥቂቶች ደግሞ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ ‘በአይሁዳዊው’ ለተመሰሉትም ሆነ ‘በአሥሩ ሰዎች’ ለተመሰሉት አገልጋዮቹ ወሮታ ይከፍላል፤ ደግሞም ሁለቱንም ቡድኖች ተመሳሳይ ሕጎችን እንዲታዘዙና ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ይጠብቅባቸዋል። ሁሉም ምንጊዜም ትሑት መሆን አለባቸው። እንዲሁም ሁሉም በኅብረት ሊያገለግሉትና አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። በተጨማሪም ሁሉም በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ አለባቸው። ወደ መጨረሻው ይበልጥ እየተቃረብን ስንሄድ ሁላችንም እንደ “አንድ መንጋ” ሆነን ክርስቶስን መከተላችንን እና ይሖዋን ማገልገላችንን እንቀጥል።—ዮሐ. 10:16
a በዚህ ዓመት የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ የሚከበረው ማክሰኞ፣ መጋቢት 29, 2012 ዓ.ም. (ሚያዝያ 7, 2020) ነው። በዚያ ምሽት ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ ለሚወስዱት ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? የእነዚህ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድ ጉዳዩ ሊያሳስበን ይገባል? ይህ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ሲሆን የተመሠረተው በጥር 2016 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣ ትምህርት ላይ ነው።
b በመዝሙር 87:5, 6 መሠረት አምላክ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የሚገዙትን የሁሉንም ቅቡዓን ስም ወደፊት ሊገልጥ ይችላል።—ሮም 8:19
c በጥር 2016 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ፍቅር ‘ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
d የሐዋርያት ሥራ 2:33 መንፈስ ቅዱስ በቅቡዓኑ ላይ የሚፈሰው በኢየሱስ በኩል እንደሆነ ቢጠቁምም ለእያንዳንዱ ሰው ጥሪውን የሚያቀርበው ይሖዋ ነው።
e ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በግንቦት 1, 2007 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
መዝሙር 34 በንጹሕ አቋም መመላለስ
f የሥዕሉ መግለጫ፦ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኘን የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይና ባለቤቱን ፎቶግራፍ ለማንሳት ግርግር ሲፈጠር። ይህ ምንኛ አክብሮት የጎደለው ድርጊት ነው!