በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በታማኝነት መደገፍ
“የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኰል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም።”—2 ቆሮንቶስ 4:2
1. (ሀ) በማቴዎስ 24:14 እንዲሁም 28:19, 20 ላይ የተጠቀሰውን ሥራ ማከናወን ምን የሚጠይቅ ሆኗል? (ለ) የመጨረሻዎቹ ቀናት ሲጀምሩ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች ምን ያህል ተሠራጭቶ ነበር?
ኢየሱስ ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ የሚገኝበትን ጊዜና የአሮጌውን የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ አስመልክቶ በተናገረው ታላቅ ትንቢት ውስጥ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። ለተከታዮቹም “አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) የእነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎምና ማሳተም፣ መልእክቱን ለሌሎች ሰዎች ማስተማርና በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርጉት መርዳትን የሚጨምር ሰፊ ሥራ ይጠይቃል። በእንዲህ ዓይነቱ ሥራ መካፈል እንዴት ያለ መብት ነው! በ1914 መላው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የተወሰኑት ክፍሎቹ በ570 ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ቋንቋዎችና በርካታ ቀበሌኛዎች የተጨመሩ ሲሆን በብዙዎቹ ቋንቋዎች ከአንድ በላይ ትርጉሞች ይገኛሉ።a
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችና አሳታሚዎችን ለሥራው ያነሳሷቸው የተለያዩ ዓላማዎች ምንድን ናቸው?
2 ለማንኛውም ተርጓሚ በአንድ ቋንቋ የተዘጋጀን ጽሑፍ ሌላ ቋንቋ የሚያነቡና የሚሰሙ ሰዎች በሚረዱት መንገድ ማቅረብ ፈታኝ ሥራ ነው። አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የሚተረጉሙት የአምላክን ቃል መሆኑን ከልብ በመገንዘብ ሥራቸውን አከናውነዋል። ሌሎቹን ደግሞ የማረካቸው ሥራው ምሁራዊ ችሎታን የሚፈታተን መሆኑ ነው። ምናልባት የመጽሐፉን ይዘት ውድ ከሆነ ባሕላዊ ቅርስ አስበልጠው አላዩት ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ ሃይማኖትን የገንዘብ ማግኛ መስክ አድርገውታል፤ በተርጓሚነት ወይም በአሳታሚነት ስማቸው የሰፈረበትን መጽሐፍ ማሳተም ለእነርሱ የእንጀራ ጉዳይ ነው። ለሥራው ያነሳሳቸው ነገር በትርጉም ሥራቸውም ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።
3. የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ ለሥራው የነበረው አመለካከት ምንድን ነው?
3 የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ የሰጠው የሚከተለው ሐሳብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው:- “ቅዱሳን ጽሑፎችን መተርጎም ማለት ይሖዋ አምላክ ያሰበውንና የተናገረውን ነገር በሌላ ቋንቋ ማስቀመጥ ማለት ነው . . . ይህ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። የቅዱሳን ጽሑፎች ባለቤት የሆነውን መለኮት የሚፈሩትና የሚያፈቅሩት የዚህ ጽሑፍ ተርጓሚዎች የእርሱን ሐሳብና መግለጫዎች የተቻለውን ያህል በትክክል የማስተላለፍ ልዩ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እንዲሁም በልዑሉ አምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃል በመመርመር የዘላለም መዳንን ለማግኘት ለሚጥሩ አንባቢዎች ትክክለኛ ትርጉም የማዘጋጀት ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወንዶችን ያቀፈው ይህ ኮሚቴ የበርካታ ዓመታት ሥራ ውጤት የሆነውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ያዘጋጀው በዚህ ዓይነት ከባድ የኃላፊነት ስሜት ነው።” የኮሚቴው ዓላማ የመጀመሪያውን የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፍ በጥብቅ የተከተለና በትክክለኛ እውቀት እያደጉ ለመሄድ የሚያስችል መሠረት የሚጥል ግልጽና የሚገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት ነበር።
የአምላክ ስም ምን ደርሶበታል?
4. የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መገለጹ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
4 ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ዓላማዎች አንዱ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እንዲያውቁ መርዳት ነው። (ዘጸአት 20:2-7፤ 34:1-7፤ ኢሳይያስ 52:6) ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ ስለ አባቱ ስም ‘መቀደስ’ ማለትም ስሙ በክብርና በቅድስና ስለ መያዙ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) አምላክ የግል መጠሪያ ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ እንዲጠቀስ አድርጓል። ሰዎች ይህንን ስምና የስሙ ባለቤት ያሉትን ባሕርያት እንዲያውቁ ይፈልጋል።—ሚልክያስ 1:11
5. የተለያዩ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም እንዴት አድርገው ገልጸውታል?
5 ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ለመለኮታዊው ስም ልባዊ አክብሮት በማሳየት በትርጉም ሥራቸው ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅመውበታል። አንዳንድ ተርጓሚዎች ያህዌህ የሚለውን መጠሪያ መጠቀም መርጠዋል። ሌሎች ደግሞ በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ቢሆንም በቋንቋቸው የተለመደውን ምናልባትም ረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት በሰፊው የሚታወቅን መለኮታዊ ስም ለመጠቀም መርጠዋል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ጅሆቫ የሚለውን ስም በጥቅሶቹ ውስጥ 7,210 ጊዜ ተጠቅሞበታል።
6. (ሀ) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም በሚመለከት ምን አድርገዋል? (ለ) ይህስ ድርጊት ምን ያህል ተስፋፍቷል?
6 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች እንደ በኣልና ሞሎክ ያሉትን የአረማውያን ጣዖት አማልክት ስም ጠብቀው ሲያቆዩ የእውነተኛውን አምላክ የግል መጠሪያ ስም ግን በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው የቃሉ ትርጉሞች ውስጥ ማውጣቱን በስፋት ተያይዘውታል። (ዘጸአት 3:15፤ ኤርምያስ 32:35) አንድ በሰፊው የሚሠራበት በአልባንያ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደ ማቴዎስ 6:9 እና ዮሐንስ 17:6, 26 ያሉት ጥቅሶች ስለ ስም የሚጠቅሱት ምንም ነገር እንደሌለ በማስመሰል “ስምህ” (የአምላክ ስም ማለት ነው) የሚለውን የግሪክኛ ቃል “አንተ” በማለት ብቻ አስቀምጦታል። ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እና ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን በመዝሙር 83:18 ላይ የሚገኘውን የአምላክ የግል መጠሪያ ስምም ሆነ አምላክ ስም እንዳለው የሚጠቁመውን ሐሳብ አጥፍተውታል። መለኮታዊው ስም ቀደም ባሉት ጊዜያት በአብዛኞቹ ቋንቋዎች በተዘጋጁት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሞች ውስጥ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተዘጋጁ ትርጉሞች ግን ብዙውን ጊዜ ጭራሽ ያወጡታል ወይም በግርጌ ማስታወሻዎቻቸው ላይ ብቻ ጠቅሰውት ያልፋሉ። ይህ ሁኔታ በእንግሊዝኛ እንዲሁም በብዙ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የሕንድና የፓስፊክ ደሴት ቋንቋዎች በተዘጋጁ ትርጉሞች ላይ ታይቷል።
7. (ሀ) በአፍሪካ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችን የተረጎሙት አንዳንድ ሰዎች መለኮታዊውን ስም በሚመለከት ምን አድርገዋል? (ለ) አንተ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?
7 መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አንዳንድ የአፍሪካ ቋንቋዎች የተረጎሙት ሰዎች ከዚህም አልፈው ሄደዋል። መለኮታዊውን ስም የተኩት እንደ አምላክ እና ጌታ በሚሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ የማዕረግ ስሞች ሳይሆን ከአካባቢው ሃይማኖታዊ እምነቶች በተወሰዱ ስሞች ነው። በዙሉ ቋንቋ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኤንድ ሳልምስ (1986 እትም) የተባለው ትርጉም አምላክ (ንኩሉንኩሉ) የሚለውን የማዕረግ ስምና የዙሉ ተወላጆች ‘በጥንት ሰብዓዊ አባቶች በኩል አምልኮ የሚቀርብለትን ታላቅ የጥንት አባት’ ለማመልከት የሚጠቀሙበትን የተፀውኦ ስም (ምቬሊንጋንጊ) በተወራራሽነት ተጠቅሞባቸዋል። ዘ ባይብል ትራንስሌተር በተባለው መጽሔት የጥቅምት 1992 እትም ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደዘገበው ቡኩ ሎዬራ በመባል የሚታወቀው በቺቻዋ ቋንቋ የተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ሲዘጋጅ ተርጓሚዎቹ ጅሆቫ በሚለው ስም ፋንታ ቻውታ የሚለውን የተፀውኦ ስም ተጠቅመዋል። ጽሑፉ “ቻውታ ከረዥም ዘመናት በፊት የሚያውቁትና ሲያመልኩት የኖሩት አምላክ ነው” ብሏል። ይሁንና ከዚህ ሕዝብ መካከል ብዙዎቹ የሙታን መናፍስት ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውንም ያመልካሉ። ሰዎች አንድን “ከሁሉ በላይ የሆነ አካል” ስለተለማመኑ ብቻ አምልኳቸው ምንም ዓይነት ይሁን ምን ይህን “ከሁሉ በላይ የሆነ አካል” ለመጥራት የሚጠቀሙበት ስም ይሖዋ የሚለውን የግል መጠሪያ ሊተካ ይችላልን? በፍጹም አይችልም! (ኢሳይያስ 42:8፤ 1 ቆሮንቶስ 10:20) የአምላክን የግል ስም ሰዎች በወግ ላይ የተመሠረቱት እምነቶቻቸው ትክክል እንደሆኑ እንዲሰማቸው በሚያደርጉ ቃላት መተካት እነዚህ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምላክ እንዲቀርቡ አይረዳቸውም።
8. አምላክ ስሙን ለማስታወቅ ያለው ዓላማ ያልተኮላሸው ለምንድን ነው?
8 ይህ ሁሉ ግን ይሖዋ ስሙ እንዲታወቅ ያለውን ዓላማ አልለወጠውም ወይም አላኮላሸውም። ዛሬም ቢሆን በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በአሜሪካ አገሮች፣ በሩቅ ምሥራቅና በባሕር ደሴቶች ላይ በሚነገሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መለኮታዊውን ስም የያዙ መጽሐፍ ቅዱሶች ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ በ233 አገሮችና ክልሎች ውስጥ ስለ እውነተኛው አምላክ ስምና ዓላማ በመናገር በድምሩ ከአንድ ቢልዮን ሰዓት በላይ የሚያሳልፉ ከ5,400,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። የእንግሊዝኛ፣ የቻይንኛ፣ የሩሲያኛ፣ የስፓንኛ፣ የፖርቹጋል፣ የፈረንሳይኛና የደች ቋንቋዎችን ጨምሮ 3,600,000,000 የምድር ነዋሪዎች በሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች የተዘጋጁና የአምላክን ስም የያዙ መጽሐፍ ቅዱሶችን እያተሙ ያሠራጫሉ። በአብዛኛው የምድር ነዋሪ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችንም ያሳትማሉ። አምላክ፣ አሕዛብ “ይሖዋ እንደሆንኩ ማወቅ ይገባቸዋል” ሲል የተናገራቸው ቃላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል።—ሕዝቅኤል 38:23 NW
የግል እምነቶች በትርጉም ሥራው ላይ ተጽዕኖ ሲያሳድሩ
9. መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ቃል በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ የተጣለውን ከባድ ኃላፊነት የሚጠቁመው እንዴት ነው?
9 የአምላክን ቃል በሚተረጉሙና በሚያስተምሩ ሰዎች ላይ ከባድ ኃላፊነት ወድቋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እርሱም ሆነ አጋሮቹ የሚያከናውኑትን አገልግሎት በሚመለከት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኰል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።” (2 ቆሮንቶስ 4:2) መቀላቀል ማለት ባዕድ የሆነ ወይም ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ነገር በመጨመር መበረዝ ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ ያለውን ትተው የራሳቸውን ሐሳብ በማስተላለፋቸው ምክንያት ይሖዋ እንደገሰጻቸው በኤርምያስ ዘመን እንደ ነበሩት እምነት አጉዳይ የእስራኤል እረኞች አልነበረም። (ኤርምያስ 23:16, 22) ይሁን እንጂ በዘመናችንስ ምን ተፈጽሟል?
10. (ሀ) በዘመናችን አንዳንድ ተርጓሚዎች ለአምላክ ታማኞች ሆነው ሳይሆን ሌላ ዓላማ ይዘው የተነሱት እንዴት ነው? (ለ) ያለቦታቸው ምን ሆነው ተገኝተዋል?
10 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሃይማኖታዊ ምሁራንና ፓስተሮች የተውጣጣ አንድ ኮሚቴ የአይሁዳውያንን በጎ ጎን የሚጠቅሱ ቦታዎችንና ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁድ የመጣ መሆኑም የሚጠቁሙ ማስረጃዎች በማጥፋት አንድ የ“አዲስ ኪዳን” እትም ለማዘጋጀት ከጀርመን የናዚ አስተዳደር ጋር ተባብረው ነበር። አሁን በቅርቡ ደግሞ ዘ ኒው ቴስታመንት ኤንድ ሳልምስ:- አን ኢንክሉሲቭ ቨርሽን የተባለው ትርጉም አዘጋጆች ለክርስቶስ ሞት አይሁዳውያንን ተጠያቂ የሚያደርጉ ማስረጃዎችን ለማጥፋት በመሞከር ወደ ሌላኛው አቅጣጫ አድልተው ተገኝተዋል። እነዚሁ ተርጓሚዎች አምላክ አባት ተብሎ ከሚጠራ ይልቅ አባት-እናት ቢባል ኢየሱስም የአምላክ ወንድ ልጅ እንደሆነ ተደርጎ ከሚገለጽ ይልቅ ልጁ ቢባል የሴቶች መብት ተከራካሪዎች እንደሚደሰቱ ተሰምቷቸዋል። (ማቴዎስ 11:27) በመሆኑም ሚስቶች ለባሎቻቸው ስለመገዛታቸው ልጆችም ለወላጆቻቸው ስለመታዘዛቸው የሚገልጸውን መሠረታዊ ሥርዓት አጥፍተውታል። (ቆላስይስ 3:18, 20) እነዚህን ትርጉሞች ያዘጋጁት ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የአምላክን ቃል ላለመቀላቀል’ የነበረው ዓይነት ቁርጥ አቋም እንዳልነበራቸው ግልጽ ነው። እነዚህ ሰዎች ተርጓሚዎች መሆናቸውን ዘንግተው በመጽሐፍ ቅዱስ ስም የራሳቸውን ሐሳብ የሚያስፋፉ መጽሐፎችን ያወጡ ደራሲዎች ሆነዋል።
11. የሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስና ስለ ሞት ከሚናገረው ነገር ጋር የሚቃረኑት እንዴት ነው?
11 የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ባጠቃላይ የሰው ልጅ ነፍስ ሰው ሲሞት ከአካሉ ወጥታ የምትሄድ የማትሞት መንፈስ ናት ብለው ያስተምራሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን በአብዛኞቹ ቋንቋዎች የተዘጋጁት ቀደም ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሰዎች ራሳቸው ነፍሳት እንደሆኑ፣ እንስሳትም ነፍሳት መሆናቸውንና ነፍስ እንደምትሞት በግልጽ ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 12:5፤ 36:6 NW፤ ዘኁልቁ 31:28 የ1879 ትርጉም፤ ያዕቆብ 5:20) ይህ ለቀሳውስቱ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።
12. በቅርቡ የተሠሩ አንዳንድ ትርጉሞች መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ያድበሰበሱት እንዴት ነው?
12 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተዘጋጁ አንዳንድ ትርጉሞች እነዚህን እውነቶች አድበስብሰዋል። እንዴት? በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ ነፈሽ (ነፍስ) የሚለውን የዕብራይስጥ ስም በቀጥታ ሳይተረጉሙት ያልፋሉ። በዘፍጥረት 2:7 ላይ የመጀመሪያው ሰው (“ሕያው ነፍስ ሆነ” ከማለት ይልቅ) “መኖር ጀመረ” ይሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ የእንስሳትን ሕይወት በሚመለከት “ነፍስ” ከማለት ይልቅ “ፍጡር” ይሉ ይሆናል። (ዘፍጥረት 1:21 NW) እንደ ሕዝቅኤል 18:4, 20 ባሉት ጥቅሶች ላይ የሚሞተው (“ነፍስ” እንደሆነ ከመጥቀስ ይልቅ) “ሰውዬው” ወይም “ግለሰቡ” እንደሆነ አድርገው ያስቀምጡታል። እንዲህ ያለው አተረጓጎም ምናልባት ለተርጓሚው ትክክል መስሎ ሊታየው ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ አስተሳሰባቸው በሕዝበ ክርስትና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት ለታጠረ በቅንነት እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች ይህ ምን ያህል ይጠቅማቸዋል?b
13. አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ የደበቁት እንዴት ነው?
13 ተርጓሚዎች ወይም በእነርሱ የትርጉም ሥራ ላይ ሂስ የሚሰነዝሩ ሃይማኖታዊ ምሁራን ሁሉም ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለውን እምነታቸውን ለመደገፍ ሲሉ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውንም ነገር ለመሰወር ይሞክሩ ይሆናል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መዝሙር 37:11ን ትሑታን “መሬት” ይወርሳሉ ብለው ተርጉመዋል። “መሬት” የሚለው ቃል በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ ከተሠራበት ቃል (ኢሬትስ) የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ (ወደ ሌሎች ብዙ ቋንቋዎች ለመተርጎም መነሻ ሆኖ ያገለገለው) ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን በዚህ ብቻ አላበቃም። ይኸው ትርጉም ጌ የሚለውን የግሪክኛ ቃል በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ 17 ጊዜ “ምድር” እያለ የተረጎመው ቢሆንም በማቴዎስ 5:5 ላይ “ምድር” የሚለውን ቃል “አምላክ የሰጣቸውን ተስፋ” በሚለው ሐረግ ተክቶታል። የቤተ ክርስቲያን አባላት ይህንን ውርሻ ከሰማይ ጋር እንደሚያያይዙት የታወቀ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ወቅት የዋሆች፣ ገሮች ወይም ትሑታን “ምድርን ይወርሳሉ” እንዳለ በሐቀኝነት አልተነገራቸውም።
14. በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ምን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ተንጸባርቋል?
14 አንዳንዶቹ የቅዱስ ጽሑፉ ትርጉሞች ደግሞ ሰባኪዎች ጥሩ ደሞዝ እንዲያገኙ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” እንደሚል አይካድም። (1 ጢሞቴዎስ 5:18) ይሁን እንጂ 1 ጢሞቴዎስ 5:17 በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች “እጥፍ ድርብ ክብር” እንደሚገባቸው ሲናገር አንዳንዶቹ ከገንዘብ ሌላ ዋጋ ያለው ክብር ሊኖር አይችልም የሚል አስተሳሰብ አድሮባቸዋል። (ከ1 ጴጥሮስ 5:2 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እነዚህ ሽማግሌዎች “እጥፍ ደመወዝ እንደሚገባቸው ሊቆጠሩ ይገባል” ሲል ኮንቴምፖረሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን ደግሞ “እጥፍ ደመወዝ ሊከፈላቸው ይገባል” ብሏል።
የአምላክን ቃል በታማኝነት መደገፍ
15. የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደምንጠቀም እንዴት መወሰን እንችላለን?
15 ይህ ሁሉ ነገር በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያነቡትም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ሌሎችን ለሚያስተምሩት ሰዎች የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? በሰፊው በሚሠራባቸው በአብዛኞቹ ቋንቋዎች ለማማረጥ የሚያስችሉ ከአንድ በላይ ትርጉሞች ይገኛሉ። የምትጠቀሙበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በመምረጥ ረገድ አስተዋዮች ሁኑ። (ምሳሌ 19:8) አንድ የትርጉም ሥራ ያቀረበው ማሳበቢያ ምንም ይሁን ምን የአምላክን ስም በመንፈስ አነሳሽነት ካጻፈው ቃሉ ውስጥ በማውጣት የአምላክን ማንነት ለመግለጽ ሐቀኛ ሆኖ ካልተገኘ ተርጓሚዎቹ ሌሎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችስ እንዲሁ አጣምመው ሊሆን አይችልምን? የትርጉሙን ትክክለኛነት በሚመለከት ጥርጣሬ ካደረባችሁ ቀደም ብለው ከተዘጋጁ ትርጉሞች ጋር አወዳድራችሁ ለማየት ሞክሩ። የአምላክን ቃል የምታስተምሩ ከሆነ የመጀመሪያዎቹን የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች መልእክት በጥብቅ የሚከተሉ ትርጉሞችን ተጠቀሙ።
16. በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በመጠቀም ረገድ በግለሰብ ደረጃ ታማኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
16 ሁላችንም በግለሰብ ደረጃ ለአምላክ ቃል ታማኞች መሆን ይገባናል። መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የያዘውን ነገር በቁም ነገር በመመልከት በየቀኑ የተወሰነ ጊዜ መድበን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ታማኝነታችንን ልናሳይ እንችላለን። (መዝሙር 1:1-3) መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በሕይወታችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ በማዋልና መሠረታዊ ሥርዓቶቹንና ምሳሌዎቹን ለምናደርጋቸው ውሳኔዎች እንደ መመሪያ በመጠቀም ታማኝነታችንን ልናሳይ እንችላለን። (ሮሜ 12:2፤ ዕብራውያን 5:14) የአምላክን ቃል ለሌሎች ሰዎች በቅንዓት በመስበክ የአምላክ ቃል ታማኝ ጠበቆች መሆናችንን እናሳያለን። እንዲሁም በአስተማሪነት ሥራችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር ከግል አስተሳሰባችን ጋር እንዲስማማ ለማድረግ ሳናጣምመው ወይም ሳንለጥጠው በጥንቃቄ ስንጠቀምበት ታማኝነታችንን እናሳያለን። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) አምላክ የተናገረው ነገር በትክክል መፈጸሙ አይቀርም። ይሖዋ ቃሉን በመፈጸም ረገድ ታማኝ ነው። እኛም ቃሉን በመደገፍ ታማኞች ሆነን እንገኝ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ድርጅት በ1997 መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል የተተረጎመባቸው 2,167 የሚያክሉ ቋንቋዎችንና ቀበሌኛዎች መዝግቧል። ይህ ቁጥር የአንዳንድ ቋንቋዎችን ብዙ ቀበሌኛዎች የሚያካትት ነው።
b ይህ ማብራሪያ ያተኮረው ቋንቋው ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ የሚያስችል ሆኖ ሳለ በዚህ መንገድ ለመተርጎም ባልፈለጉ ተርጓሚዎች ላይ ነው። አንዳንድ ቋንቋዎች ያሏቸው ቃላት ውስን በመሆናቸው ተርጓሚዎቹ ሐሳቡን በግልጽ ለማስቀመጥ ሊቸገሩ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲኖር ሐቀኛ ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች ተርጓሚው የተለያዩ መግለጫዎችን ወይም ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ ቃና የሌለው አንድ ቃል ተጠቅሞ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እዚህ ላይ የገባው ቃል ነፈሽ የሚለው ቃል እንደሆነና ቃሉ ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን ለማመልከት እንደሚያገለግል እንዲሁም እስትንፋስ ያለውን፣ የሚመገብንና ሊሞት የሚችልን ፍጡር እንደሚያመለክት ያብራራሉ።
ታስታውሳለህን?
◻ ዛሬ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ሥራ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት አንዳንድ ዝንባሌዎች ምንድን ናቸው?
◻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተዘጋጁት ትርጉሞች የተከተሉት አቅጣጫ አምላክ ስሙን በሚመለከት ያለውን ዓላማ የማያጨናግፈው ለምንድን ነው?
◻ አንዳንድ ትርጉሞች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ፣ ስለ ሞትና ስለ ምድር የሚናገረውን እውነት የሚያድበሰብሱት እንዴት ነው?
◻ የአምላክን ቃል በታማኝነት እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው በምን በምን መንገዶች ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጠቀም የሚኖርብህ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው?