የበጎቹና የፍየሎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
“እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል።” —ማቴዎስ 25:32
1, 2. የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ለማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አስተማሪ ነበር። (ዮሐንስ 7:46) ከማስተማሪያ ዘዴዎቹ አንዱ በምሳሌዎች መጠቀም ነበር። (ማቴዎስ 13:34, 35) እነዚህ ምሳሌዎች ቀላል ቢሆኑም ጥልቅ መንፈሳዊና ትንቢታዊ እውነቶችን በማስተላለፍ ረገድ ኃይለኛ ናቸው።
2 ኢየሱስ በሰጠው የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ላይ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ” በማለት አንድ የተለየ ሥልጣን ይዞ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ ጠቁሟል። (ማቴዎስ 25:31) ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠውን መልስ የደመደመው በዚህ ምሳሌ ስለሆነ ይህ ነገር የማወቅ ፍላጎት ሊያሳድርብን ይገባል። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ይሁን እንጂ ይህ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
3. ኢየሱስ ቀደም ሲል ባቀረበው ንግግሩ ላይ ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ወዲያውኑ ምን ይሆናል ብሎ ነበር?
3 ኢየሱስ ታላቁ መከራ ከፈነዳ “በኋላ ወዲያው” እንደሚከሰቱ የምንጠብቃቸውን አስደንጋጭ ሁኔታዎች አስቀድሞ ተናግሯል። በዚያን ጊዜ “የሰው ልጅ ምልክት” ይታያል ብሏል። ይህ ሁኔታ “የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ” የሚያዩትን “የምድር ወገኖች” በከፍተኛ ደረጃ ይነካል። የሰው ልጅ “ከመላእክቱ” ጋር ይመጣል። (ማቴዎስ 24:21, 29–31)a የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚፈጸመው እንዴት ነው? ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች በምዕራፍ 25 ውስጥ ያስቀምጡት እንጂ ይህ ምሳሌ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ ክፍል ሲሆን በክብሩ ስለሚመጣበት ጊዜ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚገኝበትና “በአሕዛብ ላይ” በመፍረድ ሥራው ላይ የሚያተኩር ነው።—ማቴዎስ 25:32
በምሳሌው ውስጥ የተገለጹት
4. በበጎቹና በፍየሎቹ ምሳሌ መጀመሪያ ላይ ስለ ኢየሱስ የተጠቀሰው ምንድን ነው? ሌሎችስ እነማን ተጠቅሰዋል?
4 ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው ‘የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ’ በማለት ነው። “የሰው ልጅ” ማን እንደሆነ ሳታውቅ አትቀርም። የወንጌል ጸሐፊዎች ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ የሚለውን አጠራር ኢየሱስን ለመግለጽ ይጠቀሙበታል። ኢየሱስ ራሱ እንኳ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የጠራው “የሰው ልጅ የሚመስል” “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ለመቀበል በዘመናት ወደ ሸመገለው እንደ ቀረበ የሚገልጸውን የዳንኤል ራእይ በአእምሮው ይዞ እንደ ነበረ አያጠራጥርም። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 26:63, 64፤ ማርቆስ 14:61, 62) በዚህ ምሳሌ ውስጥ በዋነኛነት የተጠቀሰው ኢየሱስ ቢሆንም ሌሎችም አሉ። በማቴዎስ 24:30, 31 ላይ እንደ ተገለጸው ቀደም ሲል በዚህ ንግግሩ ውስጥ የሰው ልጅ ‘በኃይልና በብዙ ክብር ሲመጣ’ መላእክት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግሮ ነበር። በተመሳሳይም የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ኢየሱስ ‘በክብሩ ዙፋን ላይ’ ለፍርድ ‘ሲቀመጥ’ መላእክት ከእሱ ጋር እንደሚኖሩ ያሳያል። (ከማቴዎስ 16:27 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ዳኛውና መላእክቱ በሰማይ ስለሆኑ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች በሰማይ ናቸውን?
5. የኢየሱስን “ወንድሞች” ለይተን ልናውቃቸው የምንችለው እንዴት ነው?
5 ምሳሌውን ስንመለከት ለይተን ልናውቃቸው የሚገቡን ሦስት ቡድኖች እንዳሉ እንረዳለን። ከበጎችና ከፍየሎች በተጨማሪ የሰው ልጅ በጎቹንና ፍየሎቹን ለማወቅ ወሳኝ የሆነውን ሦስተኛውን ቡድን አክሏል። ኢየሱስ የዚህ ሦስተኛ ቡድን አባላት መንፈሳዊ ወንድሞቹ እንደሆኑ ገልጿል። (ማቴዎስ 25:40, 45) ኢየሱስ “የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነው” ስላለ እነዚህ ሰዎች የእሱ እውነተኛ ተከታዮች መሆን ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 12:50፤ ዮሐንስ 20:17) ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ በማድረግ ጳውሎስ “የአብርሃም ዘር” ክፍልና የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ ክርስቲያኖች ጽፏል። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች የኢየሱስ “ወንድሞች” እና ‘የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች’ በማለት ጠርቷቸዋል።—ዕብራውያን 2:9 እስከ 3:1፤ ገላትያ 3:26, 29
6. ከኢየሱስ ወንድሞች ውስጥ “ከሁሉ የሚያንሱ” የተባሉት እነማን ናቸው?
6 ኢየሱስ ከእነዚህ ወንድሞቹ ውስጥ ‘ከሁሉ የሚያንሱትን’ የጠቀሰው ለምንድን ነው? እነዚህ ቃላት ሐዋርያት ቀደም ሲል እሱ ሲናገር የሰሙትን ነገር ያስተጋባሉ። ኢየሱስ ከእሱ በፊት በመሞቱ ምክንያት ምድራዊ ተስፋ ያለውን መጥምቁ ዮሐንስን ሰማያዊ ሕይወት ከሚያገኙት ሰዎች ጋር ሲያነጻጽር “ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:11) ወደ ሰማይ ከሚሄዱት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ሐዋርያት በጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ ሲኖራቸው ሌሎቹ ደግሞ አነስተኛ ቦታ ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ሁሉም የኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች ናቸው። (ሉቃስ 16:10፤ 1 ቆሮንቶስ 15:9፤ ኤፌሶን 3:8፤ ዕብራውያን 8:11) ስለዚህ አንዳንዶቹ በምድር ላይ ሳሉ ከቁጥር የማይገቡ ቢመስሉም እንኳ ወንድሞቹ ስለ ነበሩ በጥሩ ሁኔታ መያዝ ነበረባቸው።
በጎቹና ፍየሎቹ እነማን ናቸው?
7, 8. ኢየሱስ በጎቹን በተመለከተ ምን ብሏል? በመሆኑም እነሱን በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን?
7 በበጎች ላይ የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “[ኢየሱስም] በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፦ ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።”—ማቴዎስ 25:34–40
8 ክብርና ሞገስ አግኝተው በኢየሱስ ቀኝ ለመቆም ብቁ እንደሆኑ የተፈረደላቸው በጎች አንድን የሰዎች ቡድን እንደሚያመለክቱ ግልጽ ነው። (ኤፌሶን 1:20 የ1980 ትርጉም፤ ዕብራውያን 1:3) ለዚህ የበቁት ምን ስላደረጉ ነው? ይህን ያደረጉትስ መቼ ነው? ኢየሱስ በታመመበትም ሆነ በታሰረበት ወቅት እሱን በመርዳት በደግነት፣ በአክብሮትና በልግስና ምግብ፣ መጠጥ እንዲሁም ልብስ እንደ ሰጡት ተናግሯል። በጎቹ እነዚህን ነገሮች ለኢየሱስ እንዳላደረጉለት ሲናገሩ መንፈሳዊ ወንድሞቹ የሆኑትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች መርዳታቸው እሱን የረዱት ያህል እንደሚቆጠር ኢየሱስ ገለጸላቸው።
9. ምሳሌው በሺው ዓመት ውስጥ የማይፈጸመው ለምንድን ነው?
9 በሺው ዓመት ውስጥ ቅቡዓን የሚራቡ፣ የሚጠሙ፣ የሚታመሙ ወይም የሚታሰሩ ሰብዓዊ ፍጥረታት ስለማይሆኑ ይህ ምሳሌ በዚያን ጊዜ የሚፈጸም አይደለም። ሆኖም ብዙዎቹ በዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ወቅት እነዚህ ችግሮች ደርሰውባቸዋል። ሰይጣን ወደ ምድር ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በእነሱ ላይ ትችት፣ ሥቃይና ሞት በማምጣት ቀሪዎቹን የቁጣው ልዩ ኢላማ አድርጓቸዋል።—ራእይ 12:17
10, 11. (ሀ) በጎቹ ለኢየሱስ ወንድሞች አንድ ዓይነት ደግነት ያደረጉ ሰዎችን በሙሉ ያካትታሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በጎቹ እነማንን ያመለክታሉ?
10 ኢየሱስ ከወንድሞቹ ለአንዱ ትንሽ ቁራሽ ወይም አንድ ብርጭቆ ውኃ በመስጠት አነስተኛ ደግነት ያሳየ ሰው ሁሉ ከበጎቹ እንደ አንዱ ለመሆን ይበቃል ማለቱ ነበርን? እንዲህ ዓይነቱ የደግነት ተግባር ሰብዓዊ ደግነት ሊሆን እንደሚችል አሌ ባይባልም በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱትን በጎች የሚመለከት ሌላ ነገር ያለ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ከወንድሞቹ ለአንዱ አንድ ዓይነት የደግነት ተግባር የፈጸሙ አምላክ የለም ባዮችን ወይም ቀሳውስትን መጥቀሱ እንዳልነበር የተረጋገጠ ነው። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ በጎቹን ሁለት ጊዜ “ጻድቃን” በማለት ጠርቷቸዋል። (ማቴዎስ 25:37, 46) ስለዚህ በጎቹ በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ የክርስቶስ ወንድሞችን በትጋት የረዷቸውንና በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ለማግኘት የሚያስፈልገውን እምነት ያሳዩ ሰዎችን ማመልከት ይኖርባቸዋል።
11 ለበርካታ መቶ ዘመናት እንደ አብርሃም የመሳሰሉ ብዙ ሰዎች በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም አግኝተዋል። (ያዕቆብ 2:21–23) ኖኅ፣ አብርሃምና ሌሎች ታማኝ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ሥር በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ከሚወርሱት “ሌሎች በጎች” መካከል ናቸው። በቅርቡ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ የሌሎች በጎች አባላት ከቅቡዓን ጋር “አንድ መንጋ” በመሆን እውነተኛውን አምልኮ ይዘዋል። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9) እነዚህ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች የክርስቶስ ወንድሞች የመንግሥቱ አምባሳደሮች እንደሆኑ ስለሚገነዘቡ በሰብዓዊም ይሁን በመንፈሳዊ መንገድ ይረዷቸዋል። ኢየሱስ ሌሎች በጎች በምድር ላይ ላሉት ወንድሞቹ የሚያደርጉትን ነገር ለእሱ እንዳደረጉለት አድርጎ ይቆጥረዋል። ከእነዚህ መካከል ኢየሱስ በአሕዛብ ላይ ለመፍረድ በሚመጣበት ወቅት በሕይወት የሚኖሩት በጎች እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል።
12. በጎቹ ለኢየሱስ ደግነት ስለማድረጋቸው ጥያቄ ያቀረቡት ለምን ሊሆን ይችላል?
12 ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ከቅቡዓን ጋር ሆነው ምሥራቹን የሚሰብኩትና እነሱን የሚረዷቸው ሌሎች በጎች ከሆኑ “ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህስ?” ብለው የሚጠይቁት ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 25:37) ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ምሳሌ ነው። ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ አማካኝነት ለመንፈሳዊ ወንድሞቹ ያለውን ጥልቅ አሳቢነት፣ ለእነሱ እንደሚያዝንና የእነሱን መከራ እንደሚካፈል አሳይቷል። ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ሲል “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፣ እኔን የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 10:40) ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ላይ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተጠቅሞ አንድ ሰው ለወንድሞቹ የሚደረገው ነገር (ጥሩም ይሁን መጥፎ) ወደ ሰማይ እንደሚደርስ አሳይቷል፤ ነገሩ በሰማይ ለእሱ የተደረገለት ያህል ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ እዚህ ላይ በሚፈረድላቸውም ሆነ በሚፈረድባቸው ሰዎች ላይ አምላክ የሚሰጠውን ፍርድ ተገቢና ፍትሐዊ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ በማስቀመጥ የይሖዋ የፍርድ መመዘኛ አጉልቷል። ፍየሎቹ ‘በዓይናችን ብናይህ ኖሮ እንረዳህ ነበር’ የሚል ሰበብ ማቅረብ አይችሉም።
13. ፍየል መሰሎቹ ሰዎች ኢየሱስን “ጌታ” ብለው የጠሩት ለምን ሊሆን ይችላል?
13 በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ ከተረዳን የፍየሎቹ ማንነት ግልጽ ይሆንልናል። ይህ የሚሆነው “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር . . . ሲመጣ ያዩታል” የሚለው ትንቢት በሚፈጸምበት ወቅት ነው። (ማቴዎስ 24:29, 30፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ከሚመጣው መከራ በሕይወት የሚተርፉ የንጉሡን ወንድሞች ይጠሉ የነበሩ ሰዎች ዳኛው እንዲያድናቸው “ጌታ ሆይ” በማለት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ይጠሩታል።—ማቴዎስ 7:22, 23፤ ከራእይ 6:15–17 ጋር አወዳድር።
14. ኢየሱስ በጎቹንና ፍየሎቹን የሚፈርድባቸው በምን መሠረት ነው?
14 ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚሰጠው ፍርድ የቀድሞ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች፣ አምላክ የለም ባዮች ወይም ሌሎች ሰዎች በተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚናገሩት ነገር ላይ የተመሠረተ አይሆንም። (2 ተሰሎንቄ 1:8) ከዚህ ይልቅ ዳኛው የልብን ሁኔታና ሰዎች “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ [ወንድሞቹ] ለአንዱ” እንኳ ያደረጓቸውን የቀድሞ ተግባራት ይመረምራል። በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ እሙን ነው። ይሁን እንጂ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሆኑት ቅቡዓን መንፈሳዊ ምግብና መመሪያ ማቅረባቸውን እስከቀጠሉ ድረስ “ከሕዝብ፣ ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡት “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንዳደረጉት ሁሉ ወደፊት በግ ሊሆኑ የሚችሉት ሰዎች ለባሪያው ክፍል መልካም የማድረግ አጋጣሚ አላቸው።—ራእይ 7:9, 14
15. (ሀ) ብዙዎች ፍየል መሰል ሰዎች እንደሆኑ ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሰው በግ ነው ወይም ፍየል ነው ብለን መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው?
15 ሰዎች የክርስቶስን ወንድሞችና ከእነሱ ጋር እንደ አንድ መንጋ ሆነው የተባበሩትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች በጎች የያዟቸው በምን መንገድ ነው? ብዙ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ በክርስቶስ ወኪሎች ላይ ጥቃት ባይፈጽሙም ሕዝቦቹን በፍቅር አልያዟቸውም። ፍየል መሰሎቹ ሰዎች ክፉውን ዓለም በመምረጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የመንግሥቱን መልእክት ሲሰሙ አልተቀበሉትም። (1 ዮሐንስ 2:15–17) እርግጥ በመጨረሻ ፍርድ እንዲሰጥ የተሾመው ኢየሱስ ነው። እኛ ማን በግ እንደሆነና ፍየል እንደሆነ የመፍረድ መብት አልተሰጠንም።—ማርቆስ 2:8፤ ሉቃስ 5:22፤ ዮሐንስ 2:24, 25፤ ሮሜ 14:10–12፤ 1 ቆሮንቶስ 4:5
የእያንዳንዱ ቡድን የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
16, 17. የበጎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?
16 ኢየሱስ ለበጎቹ ሲፈርድላቸው “እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት [“ከተመሠረተበት” አዓት] ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ብሏቸዋል። “ኑ” የሚለው ግብዣ እንዴት ያለ ሞቅ ያለ ግብዣ ነው! የሚመጡት ወዴት ነው? ወደ ዘላላም ሕይወት ነው። ይህም “ጻድቃን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” በሚለው የማጠቃለያ ሐሳቡ ላይ ተገልጿል።—ማቴዎስ 25:34, 46
17 ኢየሱስ በመክሊቶቹ ምሳሌ ላይ ከእሱ ጋር በሰማይ የሚገዙት ሰዎች ምን እንደሚፈለግባቸው አሳይቷል፤ ሆኖም በዚህ ምሳሌ ላይ የገለጸው የመንግሥቱ ዜጎች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው። (ማቴዎስ 25:14–23) በጎቹ ለኢየሱስ ወንድሞች የሙሉ ልብ ድጋፍ በመስጠታቸው ምክንያት የመንግሥቱን ምድራዊ ግዛት ይወርሳሉ። አምላክ ሊቤዡ ለሚችሉ ሰዎች “ዓለም ከተመሠረተበት” ጊዜ ጀምሮ ያዘጋጀላቸውን በገነት ምድር ውስጥ የመኖር ተስፋ ያገኛሉ።—ሉቃስ 11:50, 51
18, 19. (ሀ) ኢየሱስ በፍየሎቹ ላይ ምን ፍርድ ይሰጣል? (ለ) ፍየሎቹ ዘላለማዊ ሥቃይ እንደማይደርስባቸው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
18 ይህ በፍየሎቹ ላይ ከሚሰጠው ፍርድ ምንኛ የተለየ ነው! “በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፣ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፣ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፣ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና፦ ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ፦ እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል።”—ማቴዎስ 25:41–45
19 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህ አነጋገር ፍየል መሰል የሆኑት ሰዎች የማይሞቱ ነፍሳት በመሆን በዘላለም እሳት ይሠቃያሉ ማለት እንዳልሆነ ያውቃሉ። ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሰዎች ነፍሳት ናቸው እንጂ በውስጣቸው የማይሞቱ ነፍሳት የላቸውም ። (ዘፍጥረት 2:7 አዓት ፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ዳኛው በፍየሎቹ ላይ “የዘላለም እሳት” በመበየኑ ወደፊት የመኖር ተስፋ የሌለው ጥፋት ይደርስባቸዋል። ይህ ፍርድ ለሰይጣንና ለአጋንንቱ ጭምር ዘላለማዊ ጥፋት ያስከትልባቸዋል። (ራእይ 20:10, 14) ስለዚህ ይሖዋ የሾመው ዳኛ ሁለት ተቃራኒ ፍርዶችን ይሰጣል። በጎቹን “ኑ” የሚላቸው ሲሆን ፍየሎቹን ደግሞ “ከእኔ ሂዱ” ይላቸዋል። በጎቹ “የዘላለም ሕይወት” ያገኛሉ። ፍየሎቹ “የዘላለም ቅጣት” ይቀበላሉ።—ማቴዎስ 25:46b
ይህ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
20, 21. (ሀ) ክርስቲያኖች ምን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ አላቸው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የመለያየት ሥራ የትኛው ነው? (ሐ) የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ መፈጸም ሲጀምር የሰዎች ሁኔታ ምን ይሆናል?
20 ኢየሱስ ስለ መገኘቱና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት የሚሆነውን ነገር ሲናገር የሰሙት አራቱ ሐዋርያት ብዙ የሚያስቡባቸው ጉዳዮች ነበሯቸው። ነቅተው መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:42) በተጨማሪም በማርቆስ 13:10 ላይ የተጠቀሰውን የምሥክርነቱን ሥራ ማከናወን ነበረባቸው። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥራ በትጋት እየተካፈሉ ነው።
21 ታዲያ ስለ በጎቹና ፍየሎቹ ምሳሌ ያገኘነው ይህ ተጨማሪ ማስተዋል ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል? በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ሚናቸውን እየለዩ ነው። አንዳንዶች ‘ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ’ ላይ ሲሆኑ ሌሎች ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ መንገድ’ ላይ ለመቆየት እየጣሩ ነው። (ማቴዎስ 7:13, 14) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ የሚሰጥበት በምሳሌው ውስጥ የተገለጸው ጊዜ ገና ወደፊት ይጠብቀናል። የሰው ልጅ የዳኝነት ተግባሩን ለማከናወን ሲመጣ ብዙ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑ ራሳቸውን የወሰኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘የታላቁ መከራን’ የመጨረሻ ክፍል አልፈው ወደ አዲሱ ዓለም ለመግባት ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ፍርድ ይሰጣል። ይህ ተስፋ በአሁኑ ጊዜ ሊያስደስታቸው ይገባል። (ራእይ 7:9, 14) በሌላ በኩል ከ“አሕዛብ ሁሉ” መካከል በጣም ብዙ ሰዎች እንደ ልበ ደንዳና ፍየሎች ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች “ወደ ዘላለም ቅጣት . . . ይሄዳሉ።” ይህ ለምድር እንዴት ያለ እፎይታ ያመጣል!
22, 23. ምሳሌው የሚፈጸመው ወደፊት ቢሆንም የስብከቱ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
22 በምሳሌው ውስጥ የተገለጸው ፍርድ ወደፊት በቅርብ ጊዜ የሚፈጸም ቢሆንም እንኳ አሁን አንድ በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር እየተከናወነ ነው። እኛ ክርስቲያኖች ሰዎች በሁለት ወገን እንዲለዩ የሚያደርገውን ሕይወት አድን መልእክት በማወጅ ላይ ነን። (ማቴዎስ 10:32–39) ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የጌታን [“የይሖዋን” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” (ሮሜ 10:13, 14) የአምላክን ስምና የመዳንን መልእክት በማሳወቅ ለሕዝብ የምንሰጠው አገልግሎት ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ ተዳርሷል። አሁንም ቢሆን ይህን ሥራ በግምባር ቀደምነት የሚመሩት ቅቡዓን የክርስቶስ ወንድሞች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ሌሎች በጎች ከእነሱ ጋር ተባብረዋል። በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች በኢየሱስ ወንድሞች ለሚታወጀው መልእክት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው።
23 ከቤት ወደ ቤት ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስለምንሰብክ ብዙዎች መልእክታችን ይደርሳቸዋል። ሌሎች በማናውቀው መንገድ ስለ ይሖዋ ምሥክሮችና እኛ ስለምንወክለው ነገር ሊሰሙ ይችላሉ። ኢየሱስ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ሲደርስ ማኅበረሰቡን ተጠያቂ የሚያደርገውና ቤተሰብን ግምት ውስጥ የሚያስገባው ምን ያህል ነው? ይህን ያህል ነው ብለን ለመናገር አንችልም፤ ስለ ጉዳዩ አስቀድሞ መገመትም ፋይዳ አይኖረውም። (ከ1 ቆሮንቶስ 7:14 ጋር አወዳድር።) በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል፣ የአምላክን ሕዝቦች ይተቻሉ ወይም በቀጥታ ያሳድዳሉ። ስለዚህ ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንደ ፍየሎች አድርጎ ከሚፈርድባቸው ሰዎች መካከል ሊሆኑ ይችላሉ።—ማቴዎስ 10:22፤ ዮሐንስ 15:20፤ 16:2, 3፤ ሮሜ 2:5, 6
24. (ሀ) ግለሰቦች ለስብከቱ ሥራችን አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ጥናት አንተ በግልህ ለአገልግሎት ምን ዓይነት ዝንባሌ እንድትይዝ ረድቶሃል?
24 ደስ የሚለው ግን በርካታ ሰዎች የአምላክን ቃል በማጥናትና የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። በአሁኑ ጊዜ ፍየሎች ከሚመስሉት አንዳንዶቹ ተለውጠው በግ መሰል ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ዋናው ነጥብ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡትና የክርስቶስን ወንድሞች በትጋት የሚረዱት ሰዎች ኢየሱስ ፍርድ ለመስጠት በዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በቀኙ ለመሰለፍ መሠረት የሚሆንላቸውን ነገር ካሁኑ በማሳየት ላይ መሆናቸው ነው። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት መባረካቸውን ይቀጥላሉ። ስለዚህ ይህ ምሳሌ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ይበልጥ በቅንዓት እንድናከናውን ሊገፋፋን ይገባል። ጊዜው ሳያልቅ የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ የምንችለውን ያህል ለመሥራት እንፈልጋለን። ይህን ካደረግን ሌሎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚችሉበትን አጋጣሚ እንፈጥርላቸዋለን። በዚያን ጊዜ ሰዎች እንዲጠፉም ሆነ እንዲድኑ ፍርድ የመስጠት ሥልጣን ያለው ኢየሱስ ነው።—ማቴዎስ 25:46
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b ኤል ኢቫንሄሊዮ ደ ማቴኦ የተባለ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “የዘላለም ሕይወት ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ነው፤ ከማያዳግም ቅጣት ጋር የሚቃረን ነገር ነው። አይኦንየስ የተባለው ግሪክኛ ቅጽል በአንደኛ ደረጃ የሚያመለክተው ጊዜን ሳይሆን የአንድን ነገር ባሕርይ ነው። ይህ የማያዳግም ጥፋት ዘላለማዊ ሞት ነው።”—ጡረታ የወጡት፣ ፕሮፌሰር ጅዋን ማቲዮስ (መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተቋም፣ ሮም) እና ፕሮፌሰር ፌርናንዶ ካማቾ፣ (መንፈሳዊ ተቋም፣ ሲቬሌ) ማድሪድ፣ ስፔይን 1981
ታስታውሳለህን?
◻ የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚፈጸመው ወደፊት እንደሆነ የሚያሳዩት በማቴዎስ 24:29–31 እና በማቴዎስ 25:31–33 ላይ ያሉት ተመሳሳይ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ይህ የሚፈጸመውስ መቼ ነው?
◻ ከኢየሱስ ወንድሞች ውስጥ “ከሁሉ የሚያንሱ” የተባሉት እነማን ናቸው?
◻ ኢየሱስ “ጻድቃን” የሚለውን ቃል መጠቀሙ እነዚህ ሰዎች እነማንን እንደሚወክሉና እንደማይወክሉ ለይቶ ለማወቅ የሚረዳው እንዴት ነው?
◻ ምሳሌው የሚፈጸመው ወደፊት ቢሆንም የስብከቱ ሥራችን በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊና አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ተመሳሳይነታቸውን አስተውሉ
ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የሰው ልጅ ይመጣል የሰው ልጅ ይመጣል
በታላቅ ክብር ይመጣል በክብር ከመጣ በኋላ
በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል
መላእክቱንም ይልካቸዋል ከመላእክት ጋር ይመጣል
የምድር ወገኖች ሁሉ ያዩታል አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ በመጨረሻም
ፍየሎች ይፈረድባቸዋል (ታላቁ
መከራ ያበቃል)
[ምንጭ]
Garo Nalbandian