ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
ዐርብ ዕለት ተቀበረ፣ እሁድ ዕለት መቃብሩ ባዶ ሆኖ ተገኘ
አሁን ዐርብ ከሰዓት በኋላ ወደ ማብቂያው አካባቢ ነው። የኒሣን 15 ሰንበት ፀሐይ ስትጠልቅ ሊጀምር ነው። የኢየሱስ ሬሣ በመከራው እንጨት ላይ እንደተሰቀለ ዝልፍልፍ ብሎ ይታያል። ከጐኑ የተሰቀሉት ቀማኞች ግን ገና አልሞቱም። ዐርብ ከሰዓት በኋላ የማዘጋጀት ጊዜ ይባላል፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ምግባቸውን የሚያዘጋጁበትና እስከ ሰንበት ማግስት ሊቆይ የማይችል ማንኛውም ሥራቸውን የሚያጠናቅቁበት ዕለት ስለሆነ ነው።
አሁን ሊጀምር ያለው ሰንበት የተለመደው ሰንበት (ማለትም የሳምንቱ ሰባተኛ ቀን) ብቻ ሳይሆን እጥፍ ወይም “ታላቅ” ሰንበት ነው። እንዲህ ሊባል የቻለውም ከሳምንቱ በማንኛውም ቀን ላይ ቢያርፍ ሰንበት ሆኖ የሚቆጠረው የሰባቱ ቀን የቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን የሆነው ኒሣን 15 ከተለመደው ሰንበት ጋር አንድ ላይ ሊውል በመሆኑ ነው።
በአምላክ ሕግ መሠረት ሬሣ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ አያድርም። ስለዚህ አይሁድ እነዚያ ሞት የተፈረደባቸው (የተሰቀሉት) ሰዎች ጭናቸውን በመስበር ሞታቸው ይቀላጠፍ ዘንድ ለመኑት። ስለዚህ ወታደሮቹ የሁለቱን ቀማኞች ጭኖች ሰበሩ። ኢየሱስ ግን እንደሞተ ሲታይ ጭኖቹ አልተሰበሩም። ይህም “ከእርሱ አጥንት አይሰበርም” የሚለው ትንቢት ፍጻሜ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ በእውነት መሞቱን ለማረጋገጥ ከወታደሮቹ አንዱ ጦሩን በጐኑ ላይ ሰካው። ጦሩ የልቡን አካባቢ በስቶ ገባና ወዲያው ደምና ውሃ ወጣ። የዐይን ምሥክር የሆነው ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ሁኔታ “የወጉትም ያዩታል” የሚለው ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ይገልጽልናል።
የአይሁድ ሳንሄድሪን ሸንጎ ስመጥር አባል የሆነው ዮሴፍ ከአርማትያ ከተማ መጥቶ የሞት ቅጣቱ ሲፈጸም ተገኝቶ ነበረ። በኢየሱስ ላይ ለተበየነው ፍርድ ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ጋር ተስማምቶ ድምጽ አልሰጠም ነበር። ዮሴፍ ከኢየሱስ ደቀመዛሙርት አንዱ መሆኑን መግለጥ ፈርቶ የነበረ ቢሆንም ራሱም የኢየሱስ ደቀመዝሙር ነበር። ይሁን እንጂ አሁን በድፍረት ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነ። ጲላጦስም ተረኛ የሆነውን የጦር ሠራዊት መኮንን አዘዘና መኮንኑ ኢየሱስ መሞቱን ካረጋገጠ በኋላ ሬሳው ተሰጠ።
ዮሴፍም ሥጋውን ወስዶ በንጹሕ በፍታ (ለከፈን በተዘጋጀ አንሶላ) ከፈነው። ሌላው የሸንጐ አባል የነበረው ኒቆዲሞስም ረዳው። ኒቆዲሞስም ሥልጣኑን እንዳያጣ ፈርቶ የኢየሱስ ደቀመዝሙር መሆኑን አልገለጠም። አሁን ግን በሮማ የገንዘብ አቆጣጠር መቶ ፓውንድ የሚያወጣ የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። የኢየሱስ ሥጋ እነዚህን ቅመሞች በያዘ ከተልባ እግር በተሠራ መጠቅለያ ልብስ እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ተገነዘ።
ከዚያም ሥጋው በአቅራቢያው ባለ የአትክልት ሥፍራ ከአለት በተወቀረ አዲስ የዮሴፍ መቃብር ተቀመጠ። በመጨረሻ የመቃብሩ በር በትልቅ ድንጋይ ተከደነ። ከሰንበት በፊት የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለማከናወን ሬሳውን ማዘጋጀት አስቸኳይ ነበር። ስለዚህ መግደላዊት ማርያምና የትንሹ የያዕቆብ እናት ማርያምም (ሬሣውን በማዘጋጀቱ የረዱ ሳይሆን አይቀርም) ተጨማሪ ቅመምና ሽቱ ለማምጣት ወደ ቤታቸው ተቻኮሉ። የኢየሱስ ሥጋ ረዘም ላለ ጊዜ ሳይበሰብስ እንዲቆይ ለማድረግ ከሰንበት በኋላ በተጨማሪ በሽቶው ሊያሹት ዕቅድ አወጡ።
በማግስቱ ቅዳሜ (ሰንበት) የካህናት አለቆችና ፈሪሣውያን ወደ ጲላጦስ ሄደው “ጌታ ሆይ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝብም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ የኋለኛይቱ ስህተት ከፊተኛይቱ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ” አሉት።
ጲላጦስም “ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ሄዱና ድንጋዩን አትመው የሮማ ወታደሮችን በጠባቂነት አቆሙ።
እሁድ ዕለት በማለዳ መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብ እናት ማርያም ከሰሎሜና ከዮሃና እንዲሁም ሌሎች ሴቶች ጋር የኢየሱስን ሥጋ ለማሸት ቅመማ ቅመም ይዘው ወደ መቃብሩ መጡ። በመንገድ ላይ “ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?” ይባባሉ ነበር። ሲደርሱ የምድር መናወጥ ደርሶ እንደነበርና የይሖዋ መልአክ ድንጋዩን አንከባሎት ያገኙታል። ጠባቆቹ የሉም። መቃብሩም ባዶ ነው! ማቴዎስ 27:57 እስከ 28:2፤ ማርቆስ 15:42 እስከ 16:4፤ ሉቃስ 23:50 እስከ 24:3, 10፤ ዮሐንስ 19:31 እስከ 20:1፤ 19:14፤ 12:42፤ ዘሌዋውያን 23:5-7፤ ዘዳግም 21:22, 23፤ መዝሙር 34:20፤ ዘካርያስ 12:10
◆ ዐርብ የማዘጋጀት ቀን ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? ታላቁ ሰንበትስ ምንድን ነው?
◆ ከኢየሱስ ሥጋ ጋር በተያያዘ ምን ትንቢቶች ተፈጸሙ?
◆ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የኢየሱስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በተመለከተ ምን አደረጉ? ከኢየሱስ ጋርስ ዝምድናቸው ምን ነበር?
◆ ካህናት ለጲላጦስ ምን ጥያቄ አቀረቡ? እሱስ ምን መልስ ሰጠ?
◆ እሁድ ዕለት ጧት በማለዳ ምን ሆነ?