ዘካርያስ
12 የፍርድ መልእክት፦
2 “እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ የምታንገዳግድ ጽዋ* አደርጋታለሁ፤ ጠላት ይሁዳንም ሆነ ኢየሩሳሌምን ይከባል።+ 3 በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን ለሕዝቦች ሁሉ ከባድ* ድንጋይ አደርጋታለሁ። ድንጋዩን የሚያነሱት ሁሉ ክፉኛ መጎዳታቸው የማይቀር ነው፤+ የምድር ብሔራትም ሁሉ በእሷ ላይ ይሰበሰባሉ።+ 4 በዚያ ቀን” ይላል ይሖዋ፣ “እያንዳንዱን ፈረስ በድንጋጤ፣ ጋላቢውንም በእብደት እመታለሁ። ዓይኖቼን በይሁዳ ቤት ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቦቹን ፈረሶች ሁሉ ግን አሳውራለሁ። 5 የይሁዳም አለቆች* በልባቸው ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ አምላካቸው ስለሆነ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ብርታታችን ናቸው’ ይላሉ።+ 6 በዚያን ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ የሚነድ ምድጃና በታጨደ እህል መካከል እንዳለ የሚነድ ችቦ አደርጋቸዋለሁ፤+ እነሱም በስተ ቀኝም ሆነ በስተ ግራ፣ በዙሪያቸው ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ይበላሉ፤+ ኢየሩሳሌምም በገዛ ስፍራዋ* ይኸውም በኢየሩሳሌም ዳግመኛ የሰዎች መኖሪያ ትሆናለች።+
7 “የዳዊት ቤት ውበትና* የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ውበት* ከይሁዳ እጅግ የበለጠ እንዳይሆን ይሖዋ በመጀመሪያ የይሁዳን ድንኳኖች ያድናል። 8 በዚያ ቀን ይሖዋ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ዙሪያ መከታ ይሆናል፤+ በዚያም ቀን ከእነሱ መካከል የሚሰናከለው* እንደ ዳዊት ይሆናል፤ የዳዊትም ቤት እንደ አምላክ፣ በፊታቸውም እንደሚሄደው የይሖዋ መልአክ ይሆናል።+ 9 ደግሞም በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጡትን ብሔራት ሁሉ ለማጥፋት ቆርጬ እነሳለሁ።+
10 “በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የሞገስንና የምልጃን መንፈስ አፈሳለሁ፤ እነሱም የወጉትን ያዩታል፤+ ለአንድያ ልጅም እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኩር ልጅ እንደሚለቀሰው ያለ መራራ ለቅሶም ያለቅሱለታል። 11 በዚያን ቀን በኢየሩሳሌም የሚለቀሰው ለቅሶ በመጊዶ ሜዳ፣ በሃዳድሪሞን እንደተለቀሰው ለቅሶ ታላቅ ይሆናል።+ 12 ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ እያንዳንዱም ቤተሰብ ለየብቻው ያለቅሳል፤ የዳዊት ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የናታን+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 13 የሌዊ+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የሺምአይ+ ቤት ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 14 የቀሩትም ቤተሰቦች በሙሉ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለብቻው፣ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።