ስለ ኢየሱስ መወለድ ከሚያወሳው ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
ከኢየሱስ መወለድ ጋር የተያያዙት ታሪካዊ ክንውኖች በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ ጉልህ ስፍራ ይሰጣቸዋል። ይህንንም በገና በዓል ሰሞን ከሚታየው ስፍር ቁጥር የሌለው ምስልና ድራማ መገንዘብ ይቻላል። ከኢየሱስ መወለድ ጋር ተያይዘው የተከናወኑት ነገሮች ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ቢሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት ሰዎችን ለማዝናናት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለማስተማርና ነገሮችን ለማቅናት ሲል በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው ቅዱስ ጽሑፍ ክፍል ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
አምላክ፣ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ልደት እንዲያከብሩት ቢፈልግ ኖሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትክክለኛውን ቀን ይገልጽላቸው ነበር። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛውን ቀን ይናገራልን? አልበርት ባርነስ የተባሉ አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ሃይማኖታዊ ምሁር ኢየሱስ የተወለደው እረኞች በማታ መንጋቸውን ይጠብቁ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ከገለጹ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ደምድመዋል:- “ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው መድኃኒታችን የተወለደው ከታኅሣሥ 25 በፊት ነው። . . . በዚህ ወቅት [ታኅሣሥ 25] በተለይ በቤተ ልሔም አቅራቢያ ባሉት ተራራማ ቦታዎች አየሩ ይበርዳል። አምላክ [ኢየሱስ] የተወለደበትን ቀን ሰውሮታል። . . . አሊያም ጊዜውን ማወቅ አያስፈልገንም። ቢያስፈልገን ኖሮ ቀኑ ተመዝግቦ እንዲቆይ ያደርግልን ነበር።”
ከዚህ በተቃራኒው ግን አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ የሞተበትን ቀን በግልጽ ይነግሩናል። ኢየሱስ የሞተው በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት የማለፍ በዓል በሚከበርበት ዕለት ማለትም ኒሳን 14 ጸደይ ወቅት ላይ ሲሆን ተከታዮቹም ይህንን የሞቱን መታሰቢያ በዓል እንዲያከብሩ ታዝዘዋል። (ሉቃስ 22:19) መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስንም ሆነ የሌላ የማንኛውንም ሰው ልደት እንድናከብር አያዝዘንም። የሚያሳዝነው ግን ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን በሚመለከት የተነሳው ውዝግብ በጊዜው የተከናወኑት ይበልጥ ትርጉም ያላቸው ነገሮች እንዳይስተዋሉ ሊያደርግ ይችላል።
በአምላክ የተመረጡ ወላጆች
አምላክ በእስራኤል ከሚገኙ በሺህዎች ከሚቆጠሩ ቤተሰቦች ውስጥ ልጁን እንዲያሳድጉለት የመረጠው ምን ዓይነት ወላጆችን ነው? የተመለከተው ሰዎቹ ታዋቂ መሆናቸውንና ሃብታቸውን ይሆን? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ያተኮረው ወላጆቹ ባላቸው መንፈሳዊ ባሕርያት ላይ ነው። ማርያም የመሲሑ እናት የመሆን መብት እንዳገኘች ካወቀች በኋላ የዘመረችውን በሉቃስ 1:46-55 ላይ የሚገኝ የውዳሴ መዝሙር ልብ በል። በዚህ መዝሙር ውስጥ “ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብራለች፤ . . . እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቶአልና” የሚሉት ቃላት ይገኙበታል። [የ1980 ትርጉም ] ማርያም ራሷን ‘ዝቅተኛ ቦታ እንዳላት’ የይሖዋ ባርያ አድርጋ ቆጥራለች። ከሁሉም በላይ ግን ባቀረበችው መዝሙር ውስጥ የሚገኙት ውብ የውዳሴ ቃላት ጥሩ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ያላት መንፈሳዊ ሰው መሆኗን ያመለክታል። ኃጢአተኛ የአዳም ዘር ብትሆንም የአምላክ ልጅ እናት ሆና ለመመረጥ በቅታለች።
የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ስለሆነው ስለ ማርያም ባልስ ምን ለማለት ይቻላል? ዮሴፍ ጥሩ ችሎታ ያለው አናጢ ነበር። ጠንክሮ በመሥራት አምስት ወንዶችንና ቢያንስ ሁለት ሴቶችን ያቀፈውን ትልቅ ቤተሰብ ያስተዳድር ነበር። (ማቴዎስ 13:55, 56) ዮሴፍ ሃብታም አልነበረም። ማርያም የመጀመሪያ ልጅዋን በአምላክ ቤተ መቅደስ የምታቀርብበት ጊዜ ሲደርስ ዮሴፍ ለመሥዋዕት የሚያቀርበው ጠቦት በማጣቱ አዝኖ መሆን አለበት። በጠቦት ምትክ ለድሆች የተደረገውን ዝግጅት መጠቀም ግድ ሆኖባቸው ነበር። የአምላክ ሕግ ወንድ ልጅ የወለደችን አንዲት እናት አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ጠቦት ለማምጣት ገንዘብዋ ያልበቃት እንደ ሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፣ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባለች፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፣ እርስዋም ትነጻለች።”—ዘሌዋውያን 12:8፤ ሉቃስ 2:22-24
መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ “ጻድቅ” እንደነበረ ይገልጻል። (ማቴዎስ 1:19) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እስከተወለደበት ጊዜ ድረስ ድንግል ከነበረችው ሚስቱ ጋር ምንም ዓይነት የጾታ ግንኙነት አልፈጸመም። ይህም የኢየሱስን ትክክለኛ አባት በተመለከተ ሊፈጠር የሚችለውን ግራ መጋባት አስቀርቷል። ገና አዲስ ለተጋቡ ባልና ሚስት በአንድ ጣሪያ ሥር እየኖሩ ከጾታ ግንኙነት መታቀብ ከባድ ሊሆንባቸው እንደሚችል እሙን ነው። ሆኖም ይህ ሁለቱም የአምላክን ልጅ የማሳደግ መብታቸውን ከፍ አድርገው እንደተመለከቱት የሚያሳይ ነው።—ማቴዎስ 1:24, 25
ዮሴፍም ልክ እንደ ማርያም መንፈሳዊ ሰው ነበር። ዓመታዊውን የማለፍ በዓል ለማክበር ሲል በየዓመቱ ሥራውን ያቆምና ቤተሰቡን ይዞ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ሦስት ቀን የሚፈጅ ጉዞ ያደርግ ነበር። (ሉቃስ 2:41) በተጨማሪም ኢየሱስ ወጣት ሳለ በየሳምንቱ በምኩራብ ተገኝቶ የአምላክ ቃል ሲነበብና ሲብራራ እንዲያዳምጥ ብሎም ተሳትፎ እንዲያደርግ ሳያሰለጥነው አይቀርም። (ሉቃስ 2:51፤ 4:16) በመሆኑም አምላክ ልጁን እንዲያሳድጉለት ትክክለኛ ምድራዊ እናትና አሳዳጊ አባት እንደመረጠ ምንም አያጠራጥርም።
ትሑት እረኞች ያገኙት ታላቅ በረከት
ሁኔታው ዘጠኝ ወር ለሞላት ለማርያም ከባድ የነበረ ቢሆንም ዮሴፍ ቄሣር ባወጣው ሕግ መሠረት ለመመዝገብ ወደ አባቶቹ ከተማ ተጓዘ። ባልና ሚስቱ ቤተ ልሔም ሲደርሱ ከሰዉ ብዛት የተነሳ በከተማው ውስጥ ማደሪያ ማግኘት አልቻሉም። በዚህ ምክንያት ጋጣ ውስጥ ለማደር ተገደዱ። እዚያም ማርያም ኢየሱስን ወልዳ ግርግም ውስጥ አስተኛችው። ይሖዋ ትሁት የነበሩትን የኢየሱስ ወላጆች እምነት ለማጠንከር ሲል ልጁ የተወለደው በእርሱ ፈቃድ መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ሰጣቸው። ይሖዋ አምላክ ይህን ያደረገው ታዋቂነት ያላቸውን የቤተ ልሔም ሽማግሌዎችን በመላክ ነበርን? አይደለም። ከዚህ ይልቅ መንጎቻቸውን ለመጠበቅ ሌሊቱን ውጪ ላደሩ ትጉህ እረኞች የመሲሑን መወለድ አበሰራቸው።
የአምላክ መልአክ ለእነዚህ እረኞች ተገለጠላቸውና ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄዱና እዚያም መሲሑን ‘በግርግም ውስጥ ተኝቶ’ እንደሚያገኙ ገለጸላቸው። እነዚህ ትሑት እረኞች መሲሑን በአንድ ጋጣ ውስጥ እንደሚያገኙት ሲነገራቸው ተደናግጠው ወይም እፍረት ተሰምቷቸው ይሆን? በፍጹም! መንጎቻቸውን እዚያው ትተው ጊዜ ሳያጠፉ ወደ ቤተ ልሔም አቀኑ። ኢየሱስን ሲያገኙት የአምላክ መልአክ የነገራቸውን ሁሉ ለዮሴፍና ለማርያም አወሩላቸው። ይህ መሆኑ ሁሉም ነገር አምላክ ባሰበው መንገድ እየተከናወነ እንዳለ እንዲሰማቸው በማድረግ እምነታቸውን አጠንክሮላቸው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ‘እረኞቹም’ በበኩላቸው “ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።” (ሉቃስ 2:8-20) አዎን፣ ይሖዋ የኢየሱስን መወለድ ፈሪሃ አምላክ ላላቸው እረኞች በማብሰር ረገድ ትክክለኛውን ምርጫ አድርጓል።
ከላይ ካለው ታሪክ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ከፈለግን ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለብን እንማራለን። ታዋቂ የመሆንም ሆነ ሃብትን የማሳደድ ፍላጎት ሊያድርብን አይገባም። ከዚህ ይልቅ ዮሴፍ፣ ማርያምና እረኞቹ እንዳደረጉት አምላክን በመታዘዝና ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች የመጀመሪያውን ሥፍራ በመስጠት ለእርሱ ያለንን ፍቅር ማረጋገጥ ይኖርብናል። በእርግጥም ከኢየሱስ መወለድ ጋር በተያያዙት ታሪካዊ ክንውኖች ላይ በማሰላሰል ብዙ ትምህርት ማግኘት ይቻላል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማርያም ሁለት እርግቦችን መሥዋዕት አድርጋ ማቅረቧ ምን ያሳያል?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የኢየሱስን መወለድ ያበሰረው ትሑት ለሆኑ ጥቂት እረኞች ነበር