ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሊያገኘው ከሚችለው ደስታ ሁሉ የሚልቀው የአምላክ የሥራ ባልደረባ በመሆን የሚያገኘው ደስታ ነው። በዛሬው ጊዜ የሚከናወነው የአምላክ ሥራ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ መሰብሰብን እንዲሁም እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያናዊ አኗኗር እንዲኖራቸውና ወደ አዲሱ ዓለም እንዲገቡ ማሠልጠንን ያጠቃልላል።—ሚክያስ 4:1-4፤ ማቴዎስ 28:19, 20፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
በላቲን አሜሪካ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከ1980 ወዲህ አንድ ሚልዮን ሰዎች ደቀ መዝሙር ሲሆኑ ማየታቸው በጣም አስደስቷቸዋል። አንዳንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገው በሚመለከቱበትና በመጽሐፉ ላይ እምነት በሚጥሉበት በዚህ ፍሬያማ ክልል ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ ረድተዋል። ካካበቱት ብዙ ተሞክሮ በመነሳት ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ስለሚገኘው ደስታ አንዳንድ ነገሮች ያካፍሉናል። የሚሰጧቸው ሐሳቦች በምትኖርበት ቦታ ከምታከናውነው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ደስታ እንድታገኝ ሊረዱህ ይችላሉ።
“በግ” ሊሆኑ የሚችሉትን ሰዎች ለይቶ ማወቅ
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት ሲልክ “በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 10:11) ሰዎችን ስታነጋግር በመንፈሳዊ ሊረዱ የሚችሉትን ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ50 ዓመታት በላይ ያሳለፈው ኤድዋርድ “በሚያቀርቧቸው ልባዊ የሆኑ ጥያቄዎችና ከቅዱሳን ጽሑፎች መልስ ሲሰጣቸው በሚኖራቸው እርካታ በግ መሰል ሰዎች መሆናቸውን ያሳያሉ” ብሏል። ካርል እንዲህ በማለት በዚህ ላይ አክላለች፦ “አንድ ሰው የግል ችግሮቹን ወይም የሚያስጨንቁትን ነገሮች የሚያካፍለኝ ከሆነ ከልቡ እርዳታ እየፈለገ ነው ማለት ነው። ችግሩን ለመወጣት የሚረዱትን ጠቃሚ ምክሮች ለማግኘት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን አገላብጣለሁ። እንዲህ ያለው የግል አሳቢነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደ መጀመር ያመራል።” ቢሆንም ልበ ቅን ሰዎች ሁልጊዜ በቀላሉ አይታወቁም። ሉዊስ ይህን በተመለከተ ሲናገር፦ “ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው የሚመስሉን ሰዎች ምንም ፍላጎት የሌላቸው ይሆናሉ፤ ቢሆንም መጀመሪያ ላይ ተቃዋሚዎች የሚመስሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ሲሰሙ ይለወጣሉ” ብሏል። አብዛኞቹ ላቲን አሜሪካውያን ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ስላላቸው “መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸውን ነገሮች ካሳየኋቸው በኋላ ወዲያውኑ ሲቀበሉ በመንፈሳዊ ሊረዱ የሚችሉ ሰዎች መሆናቸውን ለይቼ አውቃለሁ” በማለት አክሎ ተናግሯል። እንደነዚህ ያሉትን “የሚገባቸውን” ሰዎች በመንፈሳዊ እንዲያድጉ መርዳት እውነተኛ ደስታና እርካታ ያስገኛል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር
ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዲገነዘቡ ለመርዳት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለማስጠኛነት ባዘጋጃቸው ጽሑፎች መጠቀሙ ብዙውን ጊዜ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። (ማቴዎስ 24:45) ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲረዱ ተብለው የተዘጋጁትን እነዚህን ጽሑፎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ኤድዋርድ “የሰዎች ሁኔታ፣ ጠባይና አመለካከት በጣም ስለሚለያይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀምርበትን መንገድ እንደ ሁኔታው ለመለዋወጥ እሞክራለሁ” በማለት ተናግሯል። በእያንዳንዱ ሰው ላይ ተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም አትችልም።
ለአንዳንዶቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚያገለግሉ ጽሑፎችን ከማስተዋወቅህ በፊት ለረጅም ጊዜ መደበኛ ያልሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ቢሆንም አንድ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን “ብዙውን ጊዜ ሰዎችን መጀመሪያ ስናነጋግራቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ እንጋብዛቸዋለን” ብለዋል። በተመሳሳይም 55 ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የረዳች አንዲት የይሖዋ ምሥክር “ሰዎችን ገና በመጀመሪያ ሳነጋግራቸው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች እያወጣሁ አሳያቸዋለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የምጠቀምበት ዋነኛ ዘዴ ይህ ነው” በማለት ተናግራለች። አንዳንዶች ማጥናት የሚባለውን ነገር ባይወዱትም ሌሎች ግን ለሕይወቴ ይጠቅመኛል ብለው ያመኑበትን ነገር ለማጥናት ይጓጓሉ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እቤት ውስጥ ያለ ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ሲጋበዙ ደስ ይላቸዋል። አንዳንድ ሚስዮናውያን ይህን ግብዣ ካቀረቡ በኋላ “እንዴት እንደምናስጠና ባሳይዎ ደስ ይለኛል። ከወደዱት ሊቀጥሉ ይችላሉ። ካልፈለጉ ምርጫው የራስዎ ነው” በማለት ይናገራሉ። ሰዎች ግብዣው በዚህ መንገድ ከቀረበላቸው ለመቀበል አይፈሩም።
አነስተኛ ገቢና ዝቅተኛ ትምህርት ላላቸው ሰዎች መንፈሳዊ እርዳታ ያደረገ ሌላ የይሖዋ ምሥክር “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በማስጀመር ረገድ በተለይ ትራክቶች ጠቃሚ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ” ብሏል። የሙሉ ጊዜ አስተማሪዎች በየትኛውም ጽሑፍ ቢጠቀሙ ዋንኛ ትኩረታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማድረግ ይጥራሉ። ካሮላ “ዋናው ነጥብ ግልጽ ሆኖ እንዲታይና መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት አስቸጋሪ እንዳይመስል በመጀመሪያው ጥናት ወቅት በሥዕሎችና አምስት በሚያክሉ ጥቅሶች ብቻ እጠቀማለሁ” ብላለች።
ፍላጎታቸው ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ
ሰዎች እድገት የማድረግ ፍላጎት አላቸው። በዚህ የተነሳ ጄኒፈር እንዲህ በማለት ምክር ሰጥታለች፦ “ጥናቱን ሕያው አድርጉት። ወደ ፊት ግፉ።” ጥናቱን አንዳንድ ሳምንታት ሳትሰርዙ ዘወትር መምራቱ ወደ አንድ ቦታ እየተጓዙ እንዳሉ እንዲሰማቸው ያደርጋል። ገጠር ውስጥ ያደገ አንድ ልዩ አቅኚ ብዙም ያልተማሩ ሰዎች እድገት እንዲያደርጉ በግልጽ ማብራራትና በዋና ዋና ነጥቦች ላይ ማተኮር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲህ አለ፦ “በምኖርበት መንደር ውስጥ ዘር ከዘራን በኋላ መሬቱ ላይ ውኃ እናርከፈክፍ ነበር። ውኃውን አንዴ ከከለበስንበት መሬቱ ስለሚታጠብ የበቀሉት ዘሮች ማደግ ያቅታቸውና ይሞታሉ። ልክ እንደዚሁ ፍላጎት ያሳዩትን አዳዲስ ሰዎች ባንድ ጊዜ ብዙ ነገር የምትነግሯቸው ከሆነ በጣም ከባድ ሊመስላቸውና ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ።” አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንኳ ማስተዋላቸው እያደገ እንዲሄድ በአንድ ጊዜ አንድ ርዕስ ላይ ማተኮር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር አለባቸው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፣ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም” ብሏቸው ነበር።—ዮሐንስ 16:12
ፍላጎታቸው ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የሚቻልበት ሌላው መንገድ ያነጋገርካቸው ሰዎች አንተ ከሄድክ በኋላ ስለ አምላክ ቃል ማሰባቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታታት ነው። ዮላንዳ ምክር ስትሰጥ “አንድ ጥያቄ በይደር ትታችሁ ሂዱ። የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲያነቡ ወይም በአንድ የሚያሳስባቸው ርዕስ ላይ ምርምር እንዲያካሂዱ በማድረግ አንዳንድ የቤት ሥራዎችን ስጧቸው” ብላለች።
ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር ማሳደግ
ተማሪዎችህ ‘ቃሉን የሚሰሙ ብቻ ሳይሆን የሚያደርጉ’ እንዲሆኑ ስትረዳቸው ደስታህ እጥፍ ድርብ ይሆናል። (ያዕቆብ 1:22) እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሥራ የሚነሳሱት ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ነው። በሜክሲኮ የሚኖረው ፔዝሮ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሰዎች የማያውቁትን ሰው ሊወዱ አይችሉም። ስለዚህ ገና በጥናቱ መጀመሪያ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሜ የአምላክን ስም አስተምራቸዋለሁ፤ እንዲሁም የይሖዋን ባሕርያት ጎላ አድርጌ ለመግለጽ አጋጣሚዎች እፈልጋለሁ።” በውይይታችሁ ውስጥ ስለ ይሖዋ ያለህን አመለካከት በመግለጽ ለይሖዋ ያላቸውን አድናቆት ልትገነባ ትችላለህ። ኤልዛቤት እንዲህ ብላለች፦ “ሁልጊዜ የይሖዋን ደግነት ለመጥቀስ እሞክራለሁ። በጥናታችን ጊዜ የሚያምር አበባ፣ ውብ የሆነች ወፍ ወይም ተጫዋች የድመት ግልገል ካየሁ የይሖዋ ሥራ እንደሆኑ እጠቅሳለሁ።” ጄኒፈር “አምላክ ቃል የገባውን አዲስ ዓለም በተመለከተ እውን እንደሆነልህ በሚያሳይ ሁኔታ ተናገር። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ጠይቃቸው” በማለት ተናግራለች።
አንድ ሰው ስለ ይሖዋ የተማራቸውን ነገሮች በአድናቆት ሲያሰላስል ወደ ልቡ ጠልቆ ይገባና እርምጃ ለመውሰድ ያንቀሳቅሰዋል። ቢሆንም የተማረውን ነገር ካላስታወሰ ማሰላሰል አይችልም። ከእያንዳንዱ ጥናት በኋላ ሦስት ወይም አራት ዋና ዋና ነጥቦች አጠር አድርጎ መከለስ ለማስታወስ ይረዳል። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች አዳዲስ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ጀርባ ላይ ቁልፍ ጥቅሶችን ከማስታወሻ ጋር እንዲጽፉ ያደርጋሉ። በእንግሊዝ የምትኖር አንዲት ሚስዮናዊ ክለሳ ማድረግ ስለሚያስገኘው ሌላኛው ጥቅም ስትናገር “ትምህርቱ እንዴት እንደጠቀማቸው እጠይቃቸዋለሁ። ይህም ስለ ይሖዋ ጎዳናዎችና ሕጎች በአድናቆት እንዲያሰላስሉ ያደርጋቸዋል” ብላለች።
ከሦስተኛው የጊልያድ ኮርስ የተመረቀች አንዲት ታማኝ የይሖዋ ምሥክር “ቀናተኞች መሆን አለብን። ተማሪዎቻችን የምናስተምረውን ነገር እንደምናምንበት መገንዘብ አለባቸው” በማለት ተናግራለች። ደስተኛ ‘ሠራተኛ’ እንድትሆን ያደረገህን እምነት ለሰዎች ካካፈልክ ወደ ሌሎች ሊጋባ ይችላል።—ያዕቆብ 1:25
ብዙ ሰዎች ይሖዋን እንዲያመልኩ የረዳች አንዲት የይሖዋ ምሥክር “ሰዎች ለጸሎቶቻቸው የተሰጧቸውን መልሶች ለይተው እንዲያውቁ ስረዳቸው ወደ አምላክ ይበልጥ እንደቀረቡ ይሰማቸዋል። ራሴ ካጋጠመኝ መካከል እንደሚከተሉት ያሉ ምሳሌዎች እሰጣቸዋለሁ፦ እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ በአቅኚነት ወደምናገለግልበት ምድብ ቦታችን ስንደርስ የነበረን የሚበላ ነገር ጥቂት አትክልትና አንድ እሽግ ቅቤ ብቻ ሲሆን ገንዘብ የለንም ነበር። ምግቡን ራት ላይ ጨረስነውና ‘እንግዲህ ለነገ ምንም የለንም’ አልን። በነገሩ ላይ ጸለይንና ተኛን። በነጋታው አንዲት በአካባቢው የምትኖር የይሖዋ ምሥክር መጣችና እንዲህ በማለት ራሷን አስተዋወቀችን፦ ‘ይሖዋ አቅኚዎች እንዲልክ ጸልዬ ነበር። አሁን ቀኑን ሙሉ አብሬያችሁ ማሳለፍ እችላለሁ። ነገር ግን የምኖረው ከከተማው ውጪ በመሆኑ ምክንያት ምሳዬን አብሬያችሁ ስለምበላ ለሁላችንም ይህንን ምግብ ይዤ መጥቻለሁ።’ ብዛት ያለው ሥጋና አትክልት ነበር። መንግሥቱን አስቀድመን ከፈለግን ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወን ለተማሪዎቼ ሁልጊዜ እነግራቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 6:33
ተግባራዊ እርዳታ ስጥ
ሰዎችን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራት የበለጠ ነገር ይጠይቃል። በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ለብዙ ዓመታት ያገለገለ አንድ ሚስዮናዊ “ጊዜ ስጧቸው። ጥናቱ እንዳለቀ ሮጣችሁ አትሂዱ። አስፈላጊ ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ቆይታችሁ ተነጋገሩ” ብሏል። ኤልዛቤት “የሕይወት ጉዳይ ስለሆነ አሳቢነት አሳያቸዋለሁ። ልክ እንደ ልጆቼ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አስባለሁ” ብላለች። ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉትን ሐሳቦች አቅርበዋል፦ “ሲታመሙ ጠይቋቸው።” “ለምሳሌ አገልግሎት ላይ ሆነህ በቤታቸው አቅራቢያ ስታልፍ ጎራ ብለህ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አስተዋውቃቸው።” ኢቫ እንዲህ ብላለች፦ “የግለሰቡን የቀድሞ ሁኔታና ሕይወቱ ምን እንደሚመስል ለመረዳት ልብ ብለህ አዳምጥ። ይህ ሁኔታ ሰዎች ለእውነት በሚሰጡት ምላሽ ላይ ለውጥ ከማምጣቱም በተጨማሪ ለእድገታቸው ጋሬጣ ሊሆን ይችላል። ችግሮቻቸውን አውጥተው ለመናገር እንዳይፈሩ ጓደኛቸው ሁን።” በተጨማሪም ካርል እንዲህ ብላለች፦ “እውነት በሕይወቱ ላይ የሚያመጣቸው ለውጦች አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቡን ወይም ጓደኞቹን ሊያሳጣው ስለሚችል ለግለሰቡ ልባዊ አሳቢነት ማሳየት አስፈላጊ ነው። በጥቅሉ ሲታይ ተማሪው የት እንደምንኖር ማወቁና በማንኛውም ጊዜ ወደ እኛ ለመምጣት እንዳያመነታ ማድረጉ አስፈላጊ ነው።” ጉባኤውን አዲሱ ቤተሰቡ አድርጎ እንዲመለከት እርዳው።—ማቴዎስ 10:35፤ ማርቆስ 10:29, 30
ዮላንዳ ደግሞ “ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት ንቁ ሁኑ። በስብሰባዎች ላይ አብራችኋቸው ተቀመጡ ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን ነገር በማድረግ እርዷቸው” ብላለች። አዳዲስ ሰዎች ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚያሰለጥኑ፣ ንጽሕናቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዴት እንደሚጠብቁ፣ በስብሰባዎች ላይ መልስ ለመስጠት እንዴት እንደሚዘጋጁና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ንግግር እንዴት እንደሚያቀርቡ ማሳየት ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ ክፍል ነው። አንዲት ሌላ እህት እንዲህ በማለት ጨምራ ተናግራለች፦ “አዳዲሶችን ለአገልግሎት ማሠልጠኑ አስፈላጊ ነው። ይህ ሥልጠና ችላ ሲባል አንዳንዶች የስብከቱ ሥራ ያስፈራቸዋል፣ ይሖዋን በማገልገል የሚያገኙትን ደስታ ያጣሉ እንዲሁም ጸንተው አይቀጥሉም።” ስለዚህ ከቤት ወደ ቤት አገልግሎትን፣ ተመላልሶ መጠየቅንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መጀመርን በተመለከተ በደንብ አሠልጥናቸው። ተማሪህ በአንተ እርዳታና መሪነት እድገት ማድረጉን ስትመለከት ከፍተኛ ደስታ ታገኛለህ።
በጽናት እንዲቀጥሉ አበረታቷቸው
ሰዎችን ደቀ መዝሙር በማድረግ ተሞክሮ ያካበተች አንዲት እህት “ተማሪው ከተጠመቀ በኋላ ማስጠናት ችላ እየተባለ ነው” በማለት አስታውቃለች። አስተማሪውም ሆነ ተማሪው አዲስ የተጠመቀው ክርስቲያን ገና በመንፈሳዊ እንዳልጎለመሰ ማስታወስ አለባቸው። በእምነቱ፣ ለአምላክ ሕግ ባለው አድናቆትና ለይሖዋ ባለው ፍቅር ብዙ እድገት ማድረግ አለበት። እድገት እያደረገ ለመቀጠል እንዲረዳው ጥሩ የግል ጥናት ልምድ እንዲያዳብር ማበረታታት አስፈላጊ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:15
አንድ አዲስ ሰው እድገት አድርጎ የወንድማማች ማኀበሩ እንግዳ ተቀባይ አባል እንዲሆን እርዳታ ያስፈልገው ይሆናል። ወደፊት ከወንድሞች ጋር ሲቀራረብ የሚያይባቸውን ጉድለቶች እንዴት መመልከት እንዳለበት መመሪያ ሊያስፈልገው ይችላል። (ማቴዎስ 18:15-35) ጥሩ ችሎታ ያለው አስተማሪ እንዲሆንና ራሱን ችሎ ከልዩ ልዩ ጽሑፎች ሐሳብ ማፈላለግ እንዲችል እርዳታ ያስፈልገዋል። አንዲት ሚስዮናዊ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “አንዲት ተማሪ ከተጠመቀች በኋላ የአስተማሪነት ችሎታዋን ለማሻሻል ስለፈለገች እንዲህ አለችኝ፦ ‘በሚቀጥለው ሳምንት አዲስ ጥናት እመራለሁ፤ ቢሆንም ያጠናኋቸውን ምዕራፎች መከለስ ያስፈልገኛል። ጥቅሶቹና ምሳሌዎቹ እንዴት እንደተብራሩ ማስታወሻ ጽፌ ተማሪዬን ሳስጠና ለመጠቀም እንድችል እነዚህን ምዕራፎች እንደገና አንድ በአንድ ልትከልሺልኝ ትቺያለሽ?’ ከጊዜ በኋላ ጥሩ አስተማሪ የወጣት ሲሆን በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከተማሪዎቿ መካከል አራቱ ተጠመቁ።”
ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ጥረት ሊደረግለት የሚገባው ለምንድን ነው?
ፓምላ “ደቀ መዛሙርት ማድረግ ማለት ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎች መጨመር ማለት ነው። እውነትን ለተቀበሉት ሰዎች ሕይወት ማለት ነው” ስትል ተናግራለች። በመቀጠልም እንዲህ አለች፦ “እውነትን ለሰዎች ማስተማር እወዳለሁ። በጣም ደስ የሚል ነው! አንድ ሰው ተማሪዎቹ ቀስ በቀስ እድገት ሲያደርጉ፣ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ሲያደርጉና በይሖዋ መንፈስ ባይሆን ኖሮ ሊወጧቸው የማይችሏቸውን መሰናክሎች ሲወጡ ይመለከታል። ይሖዋን ማፍቀር ከጀመሩት ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ የቅርብ ጓደኞቼ ሆነዋል።”
አንዲት በጀርመን የምትገኝ ሚስዮናዊ እንዲህ ብላለች፦ “ደቀ መዝሙር እንዲሆኑ የረዳኋቸውን ሰዎች መለስ ብዬ ስመለከት በጣም ፈሪ የነበሩ ሰዎች የአምላክ አገልጋይ በመሆን ከፍተኛ እድገት አድርገው ስመለከት ማመን ያቅተኛል። የማይገፉ የሚመስሉ እንቅፋቶችን የተወጡ ሰዎችን አይቻለሁ፤ ይህን ያደረጉት በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ ግልጽ ነው። በፊት ተለያይተው የነበሩ አሁን ግን አንድ የሆኑ ደስተኛ ልጆችና ኃላፊነት የሚሰማቸው ወላጆች ያሏቸው ቤተሰቦች አይቻለሁ። ትርጉም ያለው ሕይወት የሚመሩና ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎች አይቻለሁ። ይህ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የሚያስገኘው ደስታ ነው።”
አዎን፣ ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ የይሖዋ አምላክ ባልደረባ መሆን ወደር የሌለው ደስታ ያስገኛል። የሚስዮናውያኑና የአቅኚዎቹ ተሞክሮ ይህ እውነት መሆኑን አሳይቷል። የተሰጡትን ምክሮች ከሠራህባቸውና በዚህ ሥራ በሙሉ ነፍስህ ከተካፈልክ ይህን የመሰለ ደስታና እርካታ ማግኘት ትችላለህ። የይሖዋ በረከት ሲታከልበት ደስታህ ሙሉ ይሆናል።—ምሳሌ 10:22፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58