አለመግባባትን የምትፈቱት እንዴት ነው?
በእንቅስቃሴ ላይ ጥንቃቄ ባለመደረጉ በተርታ ከተደረደሩት ከሸክላ የተሠሩ የዝሆን ቅርፅ ያላቸው አምስት ጌጦች መካከል ሦስተኛዋ ከመደርደሪያው ላይ ወደቀች። የበፊቱን ቅርፅ በምትይዝበት ሁኔታ መጠገን አለባት። አለበለዚያ አንድ ላይ ተቀናጅተው የፈጠሩት መስህብነት ያለው ቅርፅ መልኩን ማጣቱ ነው። ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው፤ አንተ ደግሞ ብቃቱ እንደሌለህ ሆኖ ተሰምቶሃል። ምክር መጠየቅ ሊኖርብህ ነው፤ ወይም ባለሙያ የሆነ ሰው ሥራውን እንዲያከናውንልህ እስከመጠየቅ ሊያደርስህ ይችላል።
በመንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች መካከል ሊኖር የሚገባው ስምምነት ከጌጣጌጦች ቅንጅት እጅግ የላቀ ነገር ነው። መዝሙራዊው እንዲህ በማለት መዘመሩ ተገቢ ነው፦ “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው።” (መዝሙር 133:1) ከአንድ መሰል ክርስቲያን ጋር የተፈጠረን አለመግባባት መፍታት አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶች ችግሩን ለመፍታት መከተል ያለባቸውን ትክክለኛ መንገድ አይከተሉም። ብዙውን ጊዜ ግንኙነታቸውን “ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ” የሚደረገው ጥረት ሳያስፈልግ የሚያስጨንቅ ወይም እጅግም የማያስደ ስትና አነስተኛ ጠባሳን ጥሎ የሚያልፍ ይሆናል።
አንዳንድ ክርስቲያኖች እነርሱ ሊፈቷቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች ሳያስፈልግ የተሾሙ ሽማግሌዎች እንዲመለከቱ ይፈልጋሉ። ይህ የሚሆነው ምን ማድረግ እንዳለባቸው በትክክል ስለማያውቁ ሊሆን ይችላል። “ብዙዎቹ ወንድሞቻችን በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አያውቁም” ሲል የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመለገስ ልምድ ያካበተ አንድ ወንድም አስተያየቱን ሰጥቷል። አስተያየቱን በመቀጠል “አብዛኞቹ ኢየሱስ የገለጸውን መንገድ አይከተሉም።” ታዲያ ኢየሱስ አንድ ክርስቲያን ከወንድሙ ጋር ያለውን አለመግባባት እንዴት መፍታት አለበት ብሏል? ይህን ምክር በደንብ ማወቅና እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል መረዳት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ቀላል የሆነ አለመግባባት
“እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።”—ማቴዎስ 5:23, 24
ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረበት ጊዜ አይሁዶች ኢየሩሳሌም በሚገኘው የቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ መሥዋዕቶች ወይም መባ የማቅረብ ልማድ ነበራቸው። አንድ አይሁዳዊ መሰሉን እስራኤላዊ ቢበድለው በዳዩ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የኃጢአት መሥዋዕት እንዲያቀርብ ሊደረግ ይችላል። ኢየሱስ ባቀረበው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ይገልጻል። ሰውዬው በመሠዊያው ፊት ቆሞ መባውን ለአምላክ ሊያቀርብ ሲል ወንድሙ በእርሱ ላይ የሆነ ቅያሜ እንዳለው አስታውሷል። አዎን፣ እስራኤላዊው እንዲህ ዓይነቱን ሃይማኖታዊ ግዴታ ከመፈጸሙ በፊት ከወንድሙ ጋር ዕርቅ መፍጠር እንዳለበት መገንዘብ ነበረበት።
እንዲህ ዓይነቶቹ መሥዋዕቶች በሙሴ ሕግ የታዘዙ ቢሆኑም በራሳቸው በአምላክ ዓይን ዋነኞቹ አስፈላጊ ነገሮች አልነበሩም። ነቢዩ ሳሙኤል ታማኝ ላልነበረው ንጉሥ ሳኦል እንዲህ ብሎታል፦ “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።”—1 ሳሙኤል 15:22
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ይህን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሥርዓት ደግሞታል። ደቀ መዛሙርቱም መሥዋዕታቸውን ከማቅረባቸው በፊት በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት መፍታት እንዳለባቸው አስረድቷቸዋል። ዛሬ ከክርስቲያኖች የሚፈለገው መሥዋዕት መንፈሳዊ ነው፤ “የምስጋና መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮች ፍሬ” ነው። (ዕብራውያን 13:15) የሆነ ሆኖ መሠረታዊ ሥርዓቱ አሁንም ይሠራል። ሐዋርያው ዮሐንስም በተመሳሳይ አንድ ሰው ወንድሙን እየጠላ አምላክን እወዳለሁ ቢል ከንቱ እንደሆነ ገልጿል።—1 ዮሐንስ 4:20, 21
የመጀመሪያውን እርምጃ የሚወስደው ወንድሙ በእሱ ላይ አንዳች ነገር እንዳለው ያስታወሰው ሰው ነው። በዚህ መንገድ የሚያሳየው ትሕትና ጥሩ ውጤቶችን ያስገኝ ይሆናል። የተበደለው ሰው ስህተቱን አምኖ ወደ እርሱ በመጣው ሰው ላይ ፊቱን ያዞራል ብሎ መገመት ያስቸግራል። የሙሴ ሕግ በስህተት የተወሰደ ነገር ሙሉ በሙሉ መመለስ እንዳለበትና ሌላ አንድ አምስተኛ እጅ መጨመር እንዳለበት ይገልጻል። (ዘሌዋውያን 6:5) ልክ እንደዚሁም በደሉን የፈጸመው ሰው ከሚያስፈልገው በላይ ለማድረግና በቃሉ መሠረታዊ ትርጉም መሠረት እሱ ያስከተለውን ማንኛውንም ጉዳት ለመጠገን መፈለጉን ካሳየ ሰላማቸውንና መልካም ግንኙነታቸውን መመለስ በጣም ቀላል ይሆናል።
ይሁን እንጂ ሰላማዊ ግንኙነቶችን መልሶ ለማምጣት የሚደረጉት ጥረቶች ሁልጊዜ አይሰምሩም። አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ከከበደው ሰው ጋር የተፈጠረን አለመግባባት መፍታት አስቸጋሪ እንደሆነ የምሳሌ መጽሐፍ ያስታውሰናል። ምሳሌ 18:19 እንዲህ ይላል፦ “የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ ነው፤ ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረት ነው።” ሌላ ትርጉም እንዲህ ይነበባል፦ “የተበደለን ወንድም ይቅር እንዲል ከማድረግ የተመሸገን ከተማ ድል ማድረግ ይቀላል፤ ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረቶች የጠነከረ ነው።” (ዘ ኢንግሊሽማንስ ባይብል) ይሁን እንጂ ልባዊና ትሕትና የተሞላባቸው ጥረቶች አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ መሰል አማኞች በመጨረሻ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ከባድ ኃጢአት ተፈጽሟል ከተባለ ግን በማቴዎስ 18 ላይ የተመዘገበውን የኢየሱስን ምክር መጠቀም ያስፈልጋል።
ከባድ አለመግባባትን መፍታት
“ወንድምህም ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው ባይሰማህ ግን፣ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፣ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፣ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፣ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።—ማቴዎስ 18:15–17
አንድ አይሁዳዊ (ወይም አንድ ክርስቲያን) ከአንድ መሰል የይሖዋ አምላኪ ጋር የሚያጋጩ ከባድ ችግሮች ቢያጋጥሙትስ? በደል እንደተፈጸመበት የተሰማው ሰው የመጀመሪያውን እርምጃ ይወስዳል። ከበደለው ሰው ጋር በግል ሁኔታዎቹን አንሥቶ ይወያያል። ደጋፊዎችን ለመሰብሰብ ባለመሞከሩ ከወንድሙ ጋር ዕርቅ መመሥረት እንደሚችል አያጠራጥርም። በተለይም የነበረው ችግር ነገሮችን በትክክል ካለመረዳት የመጣ ከሆነ ችግሩ ወዲያውኑ ሊቃለል ይችላል። ስለጉዳዩ የሚያውቁት በቀጥታ በነገሩ ውስጥ ያሉበት ሰዎች ብቻ ከሆኑ ሁሉም ነገር ይበልጥ በቀላሉ ሊፈታ ይችላል።
ይሁን እንጂ የመጀመሪያው እርምጃ በቂ ላይሆን ይችላል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥም ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሲናገር “አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ” ብሏል። እነዚህ ሰዎች የዓይን ምሥክሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት ከግለሰቦቹ መካከል አንዱ የሌላኛውን ስም ሲያጠፋ ሰምተው ይሆናል፤ ወይም እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሰዎች መካከል አለመግባባትን የፈጠረው ነገር ቀደም ሲል ስምምነት ተደርጎበት በጽሑፍ ሲሰፍር ተመልክተው ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል እነዚህ ጉዳዩን እንዲመለከቱ የሚደረጉት ሰዎች ለችግሩ መንስኤ የሆነ ማንኛውም ነገር በሚመረመርበት ጊዜ ለሚነገሩት ነገሮች ወይም በጽሑፍ ለሚሰፍሩት ቃሎች ምሥክሮች ይሆናሉ። በዚህም ወቅት ቢሆን ስለጉዳዩ ማወቅ የሚኖርባቸው በተቻለ መጠን በጣም ጥቂት ሰዎች ይኸውም “አንድ ወይም ሁለት” ሰዎች ብቻ ናቸው። ይህም ጉዳዩ ካለመግባባት የመነጨ ከሆነ ሁኔታዎች እየከረሩ እንዳይመጡ ይከላከላል።
የተበደለው ሰው ምን ዓላማ ይዞ መነሣት ይገባዋል? መሰል ክርስቲያን ባልንጀራውን ለማዋረድ መሞከር ይኖርበታልን? ክርስቲያን ባልንጀራው ራሱን እንዲያቃልል ይፈልጋልን? ኢየሱስ በሰጠው ምክር መሠረት ክርስቲያኖች ወንድሞቻቸውን ለመኮነን ችኩሎች መሆን የለባቸውም። በደል የፈጸመው ሰው ስህተቱን ካመነ፣ ይቅርታ ከጠየቀና ችግሮቹን ለማስተካከል ከጣረ በደል የተፈጸመበት ሰው ‘ወንድሙን ገንዘቡ አድርጎታል።’—ማቴዎስ 18:15
ችግሩ ሊፈታ ካልቻለ ለጉባኤ ይቀርባል። በመጀመሪያ ይህ የሚያመለክተው የአይሁድ ሽማግሌዎችን ነበር፤ በኋላ ግን የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌዎችን የሚያመለክት ሆነ። ንስሐ የማይገባው ኃጢአተኛ ከጉባኤው መወገድ ሊያስፈልገው ይችላል። አይሁዳውያን ይርቋቸው እንደነበሩት ግለሰቦች ማለትም “እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ” ማለት ትርጉሙ ይህ ነበር። ይህ ከባድ እርምጃ እንዲሁ በማንኛውም ክርስቲያን በግለሰብ ደረጃ ሊወሰድ አይችልም። እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ያላቸው ጉባኤውን የሚወክሉ የተሾሙ ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው።—ከ1 ቆሮንቶስ 5:13 ጋር አወዳድር።
ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛ ሊወገድ የሚችል መሆኑ ማቴዎስ 18:15–17 ቀላል ስለሆነ አለመግባባት እንደማይናገር ያሳያል። ኢየሱስ ከባድ በደሎችን ማመልከቱ ነበር፤ ሆኖም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁለቱ ግለሰቦች ብቻ ሊፈቱት የሚችሉት ዓይነት ነው። ለምሳሌ ያህል በደሉ የተበደለውን ሰው ስም የሚያጠፋ ሐሜት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ቀጥሎ ያሉት ጥቅሶች ኢየሱስ ከፍተኛ ዕዳ ስለተሰረዘለት ጨካኝ ባሪያ ምሳሌ መናገሩን ስለሚገልጹ ጉዳዩ ገንዘብ ነክ ነገሮችን የሚመለከት ይሆናል። (ማቴዎስ 18:23–35) በተባለው ጊዜ ያልተከፈለ ብድር በሁለቱ ግለሰቦች መካከል በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ጊዜያዊ ችግር ብቻ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የተበደረው ሰው ዕዳውን አልከፍልም ብሎ ድርቅ ካለ ከባድ ኃጢአት ይኸውም ሌብነት ይሆናል።
በሁለት ክርስቲያኖች ብቻ ሊፈቱ የማይችሉ ሌሎች ኃጢአቶች አሉ። በሙሴ ሕግ መሠረት ከባድ ኃጢአቶች መነገር ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 5:1፤ ምሳሌ 29:24) ልክ እንደዚሁም የጉባኤውን ንጽሕና የሚነኩ ከባድ ኃጢአቶች ለክርስቲያን ሽማግሌዎች መነገር አለባቸው።
ይሁን እንጂ በአብዛኛው በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ለዚህ የሚያደርስ አይደለም።
ይቅር ብለህ ልታልፈው ትችላለህን?
ኢየሱስ ከባድ አለመግባባትን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ከገለጸ በኋላ ወዲያው ሌላ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቷል። እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት [ሰባ ሰባት ጊዜ አዓት] እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።” (ማቴዎስ 18:21, 22) በሌላ ወቅት ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “በቀንም ሰባት ጊዜ” ይቅር እንዲሉ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 17:3, 4) እንግዲያው የክርስቶስ ተከታዮች እርስ በእርሳቸው በነጻ ይቅር በመባባል አለመግባባትን መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ግልጽ ነው።
ይህ ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው። “አንዳንድ ወንድሞች እንዴት ይቅር ማለት እንደሚችሉ እንኳ አያውቁም” ሲል በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ወንድም ተናግሯል። እንዲህ ሲል አክሎ ተናገረ፦ “አንድ ሰው ከሁሉም በላይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ሰላም እንደተጠበቀ እንዲቆይ በማሰብ ይቅር ማለት የተሻለ መሆኑን ሲገልጽላቸው አዲስ ነገር ይሆንባቸዋል።”
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እርስ በእርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላስይስ 3:13) እንግዲያው ወደ በደለን ወንድም ከመሄዳችን በፊት የሚከተሉትን ጥያቄዎች በጥሞና ብናስብባቸው ጥሩ ነው፦ በደሉ በእርግጥ ለእርሱ ሊቀርብ የሚገባ ነውን? አንዴ የሆነውን ነገር በእውነተኛ ክርስቲያናዊ መንፈስ ማለፍ ያቅተኛልን? እኔ በእሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ይቅር እንዲለኝ አልፈልግም ነበርን? ይቅር ላለማለት ከወሰንኩ አምላክ ጸሎቶቼን በመስማት በደሌን ይቅር ይለኛል ብዬ ልጠብቅ እችላለሁን? (ማቴዎስ 6:12, 14, 15) እንዲህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች በቀላሉ ይቅር ለማለት ሊረዱን ይችላሉ።
እንደ ክርስቲያኖች መጠን ከዋና ዋና ኃላፊነቶቻችን መካከል አንዱ በይሖዋ ሕዝብ ጉባኤ ውስጥ ሰላም እንደተጠበቀ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ስለዚህ የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ እናድርግ። ይህም በነጻ ይቅር እንድንል ይረዳናል። እንዲህ ዓይነቱ የይቅር ባይነት መንፈስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መለያ ምልክት ለሆነው የወንድማማችነት ፍቅር አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ዮሐንስ 13:34, 35
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምክር በመከተል አለመግባባትን መፍታት ይችላሉ