ለቤተሰባችሁ መዳን ጠንክራችሁ ሥሩ
“ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው።”—ኤፌሶን 6:4
1, 2. በዛሬው ጊዜ ወላጆች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?
አንድ የታወቀ መጽሔት አብዮት በማለት ጠርቶታል። ይህ አባባል የሰፈረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤተሰብ ላይ እየታዩ ያሉትን ያልተጠበቁ ለውጦች በሚገልጽ አንድ ጽሑፍ ላይ ነው። እነዚህ ለውጦች “እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋው ፍቺ፣ ፈቶ ሌላ ማግባት፣ እንደገና መፋታት፣ ከጋብቻ በፊት ልጅ መውለድና ባልተፋቱ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉ አዳዲስ ውጥረቶች ውጤት ናቸው” ተብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን” እንደሚጋረጥባቸው አስቀድሞ ስለተናገረ እንዲህ ዓይነቶቹ ጫናዎችና ውጥረቶች እንግዳ ሊሆኑብን አይገባም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1–5
2 ስለዚህም በዛሬው ጊዜ ወላጆች ቀደም ሲል የነበሩት ትውልዶች የማያውቋቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ተደቅነውባቸዋል። ምንም እንኳ በመካከላችን ካሉት ወላጆች መካከል አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን ‘ከሕፃንነታቸው ጀምረው’ በአምላካዊ መንገዶች ኮትኩተው ያሳደጓቸው ቢሆንም ብዙዎቹ ቤተሰቦች ‘በእውነት መመላለስ’ የጀመሩት በቅርብ ጊዜ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:15፤ 3 ዮሐንስ 4) ወላጆቹ የአምላክን መንገዶች ለልጆቻቸው ማስተማር በጀመሩበት ወቅት ልጆቹ አድገው ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችና የእንጀራ አባት ወይም እናት ያለባቸው ቤተሰቦች በመካከላችን ይገኛሉ። ያላችሁበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው ምክር እናንተንም ይመለከታል።—ኤፌሶን 6:4
ክርስቲያን ወላጆችና የሚያበረክቱት ድርሻ
3, 4. (ሀ) አባቶች የሚያበረክቱት ድርሻ እየተዳከመ እንዲመጣ ያደረጉት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ክርስቲያን አባቶች የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎቶች ከማሟላት አልፈው መሄድ ያለባቸው ለምንድን ነው?
3 ጳውሎስ በመሠረቱ በኤፌሶን 6:4 ላይ የሚገኙትን ቃላቱን የተናገረው ‘ለአባቶች’ እንደሆነ ልብ በሉ። አንድ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ ቀደም ሲል በነበሩት ትውልዶች “አባቶች ልጆቻቸውን በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ አንጸው የማሳደግ ኃላፊነት ነበረባቸው። አባቶች ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት ነበረባቸው። . . . ይሁን እንጂ የኢንዱስትሪው አብዮት በመካከላቸው የነበረውን ይህን ቅርርብ አከሰመው። አባቶች በፋብሪካዎችና በኋላም በቢሮዎች ውስጥ ለመሥራት የእርሻ መሬታቸውንና የንግድ መደብራቸውን እንዲሁም ቤታቸውን ለቀው ሄዱ። በአንድ ወቅት የአባቶች ኃላፊነት የነበሩ ብዙ የሥራ ግዴታዎች በእናቶች ጫንቃ ላይ ወደቁ። ከጊዜ ወደ ጊዜ አባትነት የስም አባትነት ብቻ እየሆነ መጣ።”
4 ክርስቲያን ወንዶች፦ ልጆቻችሁን የማሠልጠኑንና የመንከባከቡን ሥራ በሙሉ ለሚስቶቻችሁ በመተው እንዲሁ የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎቶች በማሟላት ብቻ የምትረኩ አትሁኑ። ምሳሌ 24:27 “በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፣ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ” በማለት በጥንት ዘመን የነበሩትን አባቶች አሳስቧቸዋል። ዛሬም በተመሳሳይ ሠርታችሁ የምታድሩ ወንዶች እንደመሆናችሁ መጠን ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ስትሉ ለረጅም ሰዓት ደፋ ቀና ማለት ያስፈልጋችሁ ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከዚያ በኋላ ግን ጊዜ ወስዳችሁ በስሜታዊና በመንፈሳዊ ‘ቤታችሁን ገንቡ።’
5. ክርስቲያን ሚስቶች ለቤተሰባቸው መዳን መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ክርስቲያን ሚስቶች፦ እናንተም ለቤተሰባችሁ መዳን ጠንክራችሁ መሥራት አለባችሁ። ምሳሌ 14:1 “ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች” ይላል። የትዳር ጓደኛሞች እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁን የማሠልጠኑን ኃላፊነት ከባልሽ ጋር ትጋራላችሁ። (ምሳሌ 22:6፤ ሚልክያስ 2:14) ይህም ልጆቻችሁን መገሠጽ፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለመስክ አገልግሎት ማዘጋጀት፣ አልፎ ተርፎም ባልሽ በማይችልበት ጊዜ የቤተሰቡን ጥናት መምራትን ሊያካትት ይችላል። በተጨማሪም ልጆቻችሁን የቤት ውስጥ ሙያዎችን፣ አንዳንድ ሥነ ሥርዓቶችን፣ የአካልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅንንና ሌሎች ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን በማስተማር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችያለሽ። (ቲቶ 2:5) ባሎችና ሚስቶች በዚህ መንገድ በጋራ ሲሠሩ ልጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በተሻለ መንገድ ማሟላት ይችላሉ። ልጆች ከሚያስፈልጓቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
የሚያስፈልጓቸውን ስሜታዊ ነገሮች ማሟላት
6. እናቶችና አባቶች ልጆቻቸው በስሜት እየበሰሉ እንዲሄዱ በማድረግ ረገድ ምን ሚና ይጫወታሉ?
6 “ሞግዚት የራስዋን ልጆች” ስትንከባከብ ልጆችዋ ደህንነት፣ አስተማማኝ ሁኔታና የመፈቀር ስሜት ይሰማቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:7፤ መዝሙር 22:9) ለልጆቻቸው በፍቅር የማይንገበገቡ እናቶች አሉ ብሎ መናገር ያዳግታል። ነቢዩ ኢሳይያስ “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን?” ሲል ጠይቋል። (ኢሳይያስ 49:15) ስለዚህ እናቶች ልጆች በስሜት እንዲበስሉ በመርዳት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። አባቶችም ቢሆኑ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። የቤተሰብ አማካሪ የሆኑት ፖል ሌዊስ እንዲህ አሉ፦ “[ወጣት ጥፋተኞች] የሆኑ ልጆች ከአባታቸው ጋር ጤናማ ግንኙነት እንደነበራቸው ሲናገሩ የሰማ አንድም የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ አጋጥሞኝ አያውቅም። ከመቶዎች አንድ ልጅ እንኳ አይገኝም።”
7, 8. (ሀ) በይሖዋ አምላክና በልጁ መካከል ጠንካራ የአንድነት ማሠሪያ እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የፍቅር ማሠሪያ ማበጀት የሚችሉት እንዴት ነው?
7 ስለዚህ ክርስቲያን አባቶች ቀስ በቀስ ከልጆቻቸው ጋር የፍቅር ማሰሪያቸውን እያጠበቁ መሄዳቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን እንውሰድ። ኢየሱስ ሲጠመቅ ይሖዋ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 3:22) በእነዚህ ጥቂት ቃላት ብዙ ነገር ተገልጿል! ይሖዋ (1) ኢየሱስ ልጁ መሆኑን አረጋግጧል፤ (2) ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር በግልጽ ተናግሯል፤ እንዲሁም (3) በኢየሱስ ደስ የሚለው መሆኑን አሳውቋል። ይሖዋ ለልጁ ያለውን ፍቅር የገለጸው ግን በዚህ ጊዜ ብቻ አይደለም። ይህ ከሆነ በኋላ ኢየሱስ ‘ዓለም ሳይፈጠር ወደድኸኝ’ በማለት ለአባቱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:24) ታዲያ አባቶች ታዛዥ ለሆኑት ልጆቻቸው በሙሉ እንደሚደሰቱባቸው፣ እንደሚያፈቅሯቸውና እንደሚያደንቋቸው ሊገልጹላቸው አይገባምን?
8 አባት ከሆንክ አዘውትረህ በቃልና በተግባር ተገቢ የፍቅር መግለጫዎችን በማሳየት ከልጆችህ ጋር በፍቅር ለመተሳሰር የሚበጅ ነገር ማድረግ ትችላለህ። እውነት ነው፣ አንዳንድ አባቶች በተለይም የራሳቸው አባቶች ፍቅራቸውን በግልጽ ሳያሳዩአቸው ያደጉ ከሆኑ እነርሱም ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር በቃላት መግለጽ ሊያስቸግራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ተጨንቀህ የምታደርገው ቢሆንም እንኳ ለልጆችህ ያለህን ፍቅር ለመግለጽ የምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። “ፍቅር . . . ያንጻል።” (1 ቆሮንቶስ 8:1) አንተ በምታሳያቸው አባታዊ ፍቅር ልጆችህ ያለ ስጋት ተማምነው የሚኖሩ ከሆነ ‘እውነተኛ የልጅነት ስሜት’ ያድርባቸዋል፤ ምሥጢራቸውን ለአንተ ለመግለጽም ሙሉ ነጻነት ይሰማቸዋል።—ምሳሌ 4:3 አዓት
የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ማሟላት
9. (ሀ) አምላክን የሚፈሩ እስራኤላውያን ወላጆች ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ያሟሉ የነበሩት እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ልጆቻቸውን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለማስተማር ምን አጋጣሚዎች አሏቸው?
9 ልጆች የሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮችም አሉ። (ማቴዎስ 5:3) ሙሴ እስራኤላውያን ወላጆችን እንዲህ ሲል አሳስቧቸው ነበር፦ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳግም 6:6, 7) ክርስቲያን ወላጅ ከሆንክ “በመንገድ ስትሄድ” መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለማስተማር በምታደርገው ጥረት ብዙ ነገር ማከናወን ትችላለህ። ቤት ውስጥ ተቀምጣችሁ በምትጫወቱበት ጊዜ፣ ዕቃ ለመግዛት ስትወጡ፣ ወይም ከልጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ከቤት ወደ ቤት ስትሄዱ ልጆቻችሁ ተዝንናተው እያሉ መመሪያዎችን በልባቸው ውስጥ ለመትከል ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላችኋል። በተለይ የመመገቢያ ሰዓቶች ቤተሰቦች መጨዋወት የሚችሉባቸው ጥሩ ጊዜያት ናቸው። “ምግብ የምንመገብበትን ሰዓት በቀኑ ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች አንስተን ለመወያየት እንጠቀምበታለን” በማለት አንዲት ወላጅ ተናግራለች።
10. አንዳንድ ጊዜ የቤተሰብ ጥናት አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ወላጆች ምን ዓይነት ቆራጥ አቋም ሊኖራቸው ይገባል?
10 ይሁን እንጂ ቋሚ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ለልጆቻችሁ መደበኛ መመሪያ መስጠትም በጣም አስፈላጊ ነው። ‘ስንፍና በልጆች ልብ ውስጥ የታሰረ መሆኑ’ የማይካድ ነው። (ምሳሌ 22:15) አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ሆን ብለው የቤተሰቡን ጥናት ማደናቀፍ እንደሚችሉ ይናገራሉ። እንዴት? በመቁነጥነጥና አሥር ጊዜ በማዛጋት እንዲሁም ሐሳብን የሚበታትኑ ነገሮችን (እርስ በእርስ መጣላትን የመሰሉ) በመፈጸም ወላጆቻቸው እንዲበሳጩ በማድረግ ወይም መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ገብተዋቸው እያሉ እንዳልገቧቸው በማስመሰል ነው። ይህ ሁኔታ የማንኛቸው ፈቃድ መፈጸም እንደሚገባው ወደሚለይበት ሁኔታ ላይ ከደረሰ ወላጅ ያለው ነገር የግድ መፈጸም ይኖርበታል። ክርስቲያን ወላጆች እጃቸውን መስጠትና ቤተሰቡን ልጆቹ እንዲሠለጥኑበት መፍቀድ የለባቸውም።—ከገላትያ 6:9 ጋር አወዳድር።
11. የቤተሰብ ጥናትን አስደሳች ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
11 ልጆችህ በቤተሰቡ ጥናት የማይደሰቱ ከሆነ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይቻል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ጥናቱን ልጆቻችሁ በቅርብ የሠሯቸውን ስህተቶች በማንሣት እንደገና ለመውቀስ ትጠቀሙበታላችሁን? እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች በግል መወያየቱ የተሻለ ይሆናል። ጥናታችሁ በቋሚነት ይካሄዳልን? በጣም የምትወዱትን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ወይም የስፖርት ጨዋታ ለመመልከት ብላችሁ የቤተሰብ ጥናቱን የምትሰርዙት ከሆነ ልጆቻችሁ ጥናቱን በቁም ነገር አክብደው ይመለከቱታል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። ጥናቱን የምትመሩት ከልብ በመነጨና በጋለ ስሜት ነውን? (ሮሜ 12:8) አዎን፣ ጥናት አስደሳች መሆን ይኖርበታል። ልጆቹ በሙሉ እንዲሳተፉ ለማድረግ ጣሩ። አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። የምታንጹ ሁኑ። ልጆቻችሁ ለሚያደርጉት ተሳትፎ ሞቅ ያለ ምስጋና አቅርቡላቸው። እንዲሁ ትምህርቱን ለመሸፈን ብቻ ሳይሆን ልባቸውን ለመንካት ሞክሩ።—ምሳሌ 23:15
በጽድቅ መገሠጽ
12. ተግሣጽ ሁልጊዜ በመግረፍ የማይሰጠው ለምንድን ነው?
12 ልጆች ተግሣጽ ማግኘትም በጣም ያስፈልጋቸዋል። ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ገደብ ልታበጁላቸው ይገባል። ምሳሌ 13:24 “በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድ ግን ተግቶ ይገሥጸዋል” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲል ግን ተግሣጽ ሁልጊዜ የሚሰጠው በመግረፍ ነው ማለቱ አይደለም። ምሳሌ 8:33 “ተግሣጽን አዳምጡ” ይላል። [አዓት] በተጨማሪም “መቶ ግርፋት በሰነፍ ጠልቆ ከሚገባ ይልቅ ተግሣጽ በአስተዋይ ሰው ጠልቆ ወደ ልቡ ይገባል” ተብሏል።—ምሳሌ 17:10
13. ለልጅ ተግሣጽ ሊሰጥ የሚገባው እንዴት ነው?
13 አንዳንድ ጊዜ በመግረፍ ተግሣጽ መስጠት ሊያስፈልግ ይችላል። ንዴት የታከለበት ከሆነ ግን ከልክ ያለፈና ግቡን የማይመታ መሆኑ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶች ሆይ፣ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” ሲል ያስጠነቅቃል። (ቆላስይስ 3:21) “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” መባሉ ትክክል ነው። (መክብብ 7:7) አንድ የተመረረ ወጣት ሌላው ቀርቶ በጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ላይ እንኳ ሊያምጽ ይችላል። ስለዚህ ወላጆች በጽድቅ ላይ የተመሠረተ ጠበቅ ያለ ነገር ግን ሚዛኑን የጠበቀ ተግሣጽ ለመስጠት ቅዱሳን ጽሑፎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አምላካዊ ተግሣጽ የሚሰጠው በፍቅርና በየዋህነት ነው።—ከ2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25 ጋር አወዳድር።a
14. ወላጆች ቁጣ እንደሚቀናቸው ከተሰማቸው ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
14 እርግጥ “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን።” (ያዕቆብ 3:2) ሌላው ቀርቶ አፍቃሪ የሆነ ወላጅ እንኳ በወቅቱ ያለው ሁኔታ ባሳደረበት ግፊት ተሸንፎ መጥፎ ቃል ሊወረውር ወይም ቁጣውን ሊገልጽ ይችላል። (ቆላስይስ 3:8) ይህ ሁኔታ ከተከሰተ ልጅህ ምሬት ተሰምቶት ወይም አንተም ራስህ ተበሳጭተህ እንዳለህ ጸሐይ እንድትጠልቅ አትፍቀድ። (ኤፌሶን 4:26, 27) ተገቢ ሆኖ ከተገኘ ይቅርታ በመጠየቅ ከልጅህ ጋር ለችግሩ እልባት አብጁለት። (ከማቴዎስ 5:23, 24 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ዓይነት ትሕትና ማሳየት አንተና ልጅህ በጣም እንድትቀራረቡ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ገንፍሎ የወጣውን ቁጣህን መቆጣጠር እንደማትችል ሆኖ ከተሰማህና ለንዴት እጅህን መስጠት የሚቀናህ ከሆነ ከተሾሙ የጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ ጠይቅ።
በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችና የእንጀራ አባት ወይም እናት ያለባቸው ቤተሰቦች
15. በነጠላ ወላጅ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኙ ልጆች እርዳታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?
15 የሁለት ወላጆች ድጋፍ የሚያገኙት ሁሉም ልጆች አይደሉም። በዩናይትድ ስቴትስ ከአራት ልጆች መካከል አንዱ የሚያድገው በነጠላ ወላጅ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ‘አባት የሌላቸው ብዙ ልጆች’ ነበሩ፤ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ለእነዚህ ልጆች አሳቢነት ማሳየት እንደሚገባ በተደጋጋሚ ተገልጿል። (ዘጸአት 22:22) ልክ እንደዚሁም በዛሬው ጊዜ በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ክርስቲያን ቤተሰቦች ተጽዕኖዎችና ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፤ ነገር ግን ይሖዋ “ለድሀ አደጎች አባት፣ ለባልቴቶችም ዳኛ” መሆኑን በማወቅ ይጽናናሉ። (መዝሙር 68:5) ክርስቲያኖች “ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ” እንዳለባቸው ተመክረዋል። (ያዕቆብ 1:27) መሰል አማኞች በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን ለመርዳት ብዙ ማድረግ ይችላሉ።b
16. (ሀ) ነጠላ ወላጆች ለራሳቸው ቤተሰብ ሲሉ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? (ለ) ተግሣጽ መስጠት አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ሆኖም የግድ መሰጠት ያለበትስ ለምንድን ነው?
16 ነጠላ ወላጅ ከሆናችሁ ቤተሰባችሁን ለመጥቀም ራሳችሁ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን፣ በስብሰባዎች መገኘትንና የመስክ አገልግሎትን በተመለከተ ትጉዎች መሆን ያስፈልጋችኋል። ነገር ግን ተግሣጽ መስጠቱ ሊከብዳችሁ ይችላል። የምታፈቅሩት የትዳር ጓደኛችሁ በሞት ስለተለያችሁ ከደረሰባችሁ መሪር ሐዘን ገና አላገገማችሁ ይሆናል። ወይም ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በመለያየታችሁ ከጥፋተኝነት ስሜት ጋር አሊያም ከብስጭት ጋር እየታገላችሁ ሊሆን ይችላል። ፍርድ ቤት ልጆቹን የማሳደግ መብት ለሁለታችሁም ከሰጠ ልጃችሁ ከተለያችሁት ወይም ከተፋታችሁት የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ለመሆን ይመርጥ ይሆናል የሚል ፍርሃትም ሊያድርባችሁ ይችላል። እነዚህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ሚዛናዊ ተግሣጽ ለመስጠት ስሜታችሁ እንዳይታዘዝላችሁ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ያልተቀጣ ብላቴና ግን እናቱን ያሳፍራል” ሲል ይነግረናል። (ምሳሌ 29:15) ስለዚህ ቀደም ሲል በነበራችሁ የትዳር ጓደኛ ሳቢያ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጸጸት ወይም ስሜታዊ ተጽዕኖ አይደርባችሁ። ምክንያታዊና የማይለዋወጡ የአቋም ደረጃዎችን አውጡ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከመፈጸም ወደ ኋላ አትበሉ።—ምሳሌ 13:24
17. ነጠላ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ የቤተሰቡ አባላት ሚና ምን እንደሆነ ሊታወቅ የማይቻለው እንዴት ነው? ይህን ለማስቀረትስ ምን ማድረግ ይቻላል?
17 ነገር ግን አንዲት ነጠላ እናት ወንድ ልጅዋን የባለቤትዋ ምትክ ማለትም የቤቱ አባወራ አድርጋ የምትመለከተው ከሆነ ወይም ሴት ልጅዋን እንደ ምሥጢረኛዋ አድርጋ በማየት ከባድ የግል ችግሮቿን እየነገረች የምታስጨንቃት ከሆነ ችግሮች ሊነሡ ይችላሉ። እንዲህ ማድረግ ተገቢ ያልሆነና አንድን ልጅ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። የወላጅ ሚና ምን እንደሆነ የልጅ ሚና ደግሞ ምን እንደሆነ ማወቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ከተደረሰ ተግሣጽ የሚባል ነገር ደብዛው ሊጠፋ ይችላል። እናንተ ወላጅ መሆናችሁ ይታወቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ማግኘት የምትፈልጊ እናት ከሆንሽ ሽማግሌዎችን አለዚያም የጎለመሰችና በዕድሜ ጠና ያለችን እህት ልትጠይቂ ትችያለሽ።—ከቲቶ 2:3–5 ጋር አወዳድር።
18, 19. (ሀ) የእንጀራ አባት ወይም እናት ያለባቸው ቤተሰቦች የሚያጋጥሙአቸው አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) የእንጀራ አባት ወይም እናት ባሉባቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኙ ወላጆችና ልጆች ጥበብና ማስተዋል ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
18 የእንጀራ አባት ወይም እናት ያለባቸው ቤተሰቦችም ልክ እንደዚሁ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ብዙውን ጊዜ የእንጀራ አባት ወይም እናት “ወዲያውኑ አይፈቀሩም።” ለምሳሌ ያህል የእንጀራ ልጆች የአብራክ ክፋይ ለሆኑ ልጆች የሚደረገውን ማንኛውንም አድሎ የሚመስል ነገር ሲያዩ ወዲያው ሊሰማቸው ይችላል። (ከዘፍጥረት 37:3, 4 ጋር አወዳድር።) እንዲያውም የእንጀራ ልጆች ወላጃቸው በሞት ስለተለያቸው የተሰማቸውን መሪር ሐዘን ለመቋቋም እየታገሉ ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም የእንጀራ አባትን ወይም እናትን ማፍቀር ማለት ለወለዷቸው አባት ወይም እናት የነበራቸውን ታማኝነት በሆነ መንገድ ማጉደል ሆኖ ሊታያቸው ይችላል። አስፈላጊውን ተግሣጽ ለመስጠት በምትሞክሩበት ጊዜ “የወለድሺኝ መሰለሽ!” የሚል የሚጎመዝዝ ማሳሰቢያ ሊገጥማችሁ ይችላል።
19 ምሳሌ 24:3 “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል” ይላል። አዎን፣ የእንጀራ አባት ወይም እናት ያለበት አንድ ቤተሰብ ሳይደነቃቀፍ መቀጠል እንዲችል ሁሉም ጥበብና ማስተዋል ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ብዙውን ጊዜ ልጆች ሊዋጥላቸው የማይችል ሐቅ ቢሆንም እንኳ ሁኔታዎቹ መለወጣቸውን አምነው በጸጋ መቀበል አለባቸው። የእንጀራ አባቶች ወይም እናቶችም እንደዚሁ ተቃውሞ ሲገጥማቸው ወዲያውኑ ከመከፋት ይልቅ ታጋሾችና ርኅሩኆች መሆንን መማር ይገባቸዋል። (ምሳሌ 19:11፤ መክብብ 7:9) ተግሣጽ የመስጠትን ሃላፊነት ለመወጣት ከመነሣታችሁ በፊት ከእንጀራ ልጃችሁ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጣሩ። እንዲህ ዓይነቱ የአንድነት ማሠሪያ እስኪበጅ ድረስ አንዳንዶች ተግሣጹን ልጁን የወለደው ወላጅ እንዲሰጥ መተዉ የተሻለ ሆኖ ሊታያቸው ይችላል። ውጥረቶች ሲከሰቱ እርስ በእርስ ለመነጋገር ጥረቶች መደረግ አለባቸው። “አንድ ላይ ሆነው በሚመካከሩ ሰዎች ዘንድ ጥበብ አለ” በማለት ምሳሌ 13:10 [አዓት] ይናገራል።c
ለቤተሰባችሁ መዳን ጠንክራችሁ መሥራታችሁን ቀጥሉ!
20. የክርስቲያን ቤተሰብ ራስ የሆኑ ሁሉ ምን ማድረጋቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል?
20 ጠንካራ የሆኑ ክርስቲያን ቤተሰቦች እንዲሁ በአጋጣሚ የሚገኙ አይደሉም። የቤተሰብ ራስ የሆናችሁ ለቤተሰባችሁ መዳን ጠንክራችሁ መሥራታችሁን መቀጠል አለባችሁ። ጤናማ ያልሆኑ ባሕርያትን ወይም ዓለማዊ ዝንባሌዎችን ለይታችሁ በማወቅ ረገድ ንቁዎች ሁኑ። በአነጋገር፣ በጠባይ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። (1 ጢሞቴዎስ 4:12) የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በሥራ አሳዩ። (ገላትያ 5:22, 23) ትዕግሥት፣ አሳቢነት፣ ይቅር ባይነትና ርኅሩኅነት ልጆቻችሁን የአምላክን መንገዶች ለማስተማር የምታደርጋቸውን ጥረቶች የበለጠ ያጠናክራሉ።—ቆላስይስ 3:12–14
21. በአንድ ቤት ውስጥ ሞቅ ያለና አስደሳች የሆነ መንፈስ ለዘለቄታው እንዲሰፍን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
21 በአምላክ እርዳታ በመታገዝ በቤትህ ውስጥ ደስተኛና ሞቅ ያለ መንፈስ ለዘለቄታው እንዲሰፍን ለማድረግ ጣር። በየቀኑ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ጊዜ አብራችሁ ለመመገብ በመጣር ሁላችሁም አንድ ላይ ሆናችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ይኑራችሁ። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ የመስክ አገልግሎትና የቤተሰብ ጥናት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም “ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለመፈንጠዝም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1, 4 አዓት) አዎን፣ ገንቢ የሆኑ የመዝናኛ ጊዜዎችን መድቡ። ቤተ መዘክሮችን፣ የአራዊት መጠበቂያዎችንና እነዚህን የመሳሰሉ ቦታዎችን መጎብኘት ለመላው ቤተሰብ አስደሳች ነው። ወይም ቴሌቪዥኑን አጥፍታችሁ በመዘመር፣ ሙዚቃ በማዳመጥ፣ የተለያዩ ጨዋታዎችን በመጫወትና በመነጋገር የምታሳልፉት ጊዜ ሊኖራችሁ ይችላል። ይህ ቤተሰቡ እርስ በእርሱ እንዲቀራረብ ሊረዳ ይችላል።
22. ለቤተሰባችሁ መዳን ጠንክራችሁ መሥራት ያለባችሁ ለምንድን ነው?
22 ክርስቲያን ወላጆች የሆናችሁ ሁላችሁም “በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ” ስትሄዱ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ለማስደሰት መጣራችሁን ቀጥሉ። (ቆላስይስ 1:10) ቤተሰባችሁን ለአምላክ ቃል ታዛዥ በመሆን ረገድ ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው አድርጉ። (ማቴዎስ 7:24–27) “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ለማሳደግ የምታደርጓቸው ጥረቶች የይሖዋን ተቀባይነት እንደሚያገኙ ምንም አትጠራጠሩ።—ኤፌሶን 6:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመስከረም 8, 1992 የእንግሊዝኛ ንቁ! ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፦ ‘የተግሣጽ በትር’—ጊዜ ያለፈበት ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b መስከረም 15, 1980 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 15–26 ተመልከት።
c የጥቅምት 15, 1984 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 21–5 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ባልና ሚስት ቤተሰባቸውን በመገንባት ረገድ መተባበር የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ለልጆች የሚያስፈልጉ አንዳንድ ስሜታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህን ማሟላት የሚቻለውስ እንዴት ነው?
◻ የቤተሰብ ራሶች ልጆቻቸውን መደበኛ በሆነና ባልሆነ መንገድ ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ወላጆች ልጆቻቸውን በጽድቅ መገሠጽ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ በነጠላ ወላጅ ለሚተዳደሩ ቤተሰቦችና የእንጀራ አባት ወይም እናት ላለባቸው ቤተሰቦች ጥቅም ሲባል ምን ማድረግ ይቻላል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ልጅ በአባቱ ዘንድ መወደዱና ተቀባይነት ማግኘቱ ለስሜታዊ ብስለቱ ወሳኝ ነው