ከልባችሁ ይቅር በሉ
“ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፣ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።”—ማቴዎስ 18:35
1, 2. (ሀ) አንዲት የታወቀች ኃጢአተኛ ለኢየሱስ ያላትን አድናቆት የገለጸችው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ በምላሹ ምን ትምህርት አስጨበጠ?
ሴትዬዋ ዝሙት አዳሪ ሳትሆን አትቀርም። እንዲህ ያለች ሴት በአንድ ሃይማኖተኛ ሰው ቤት ትገኛለች ብለህ አትጠብቅም። እዚያ በመገኘቷ የተገረሙ ሰዎች ቢኖሩ እያደረገች ያለችውን ነገር ሲመለከቱ ደግሞ ይበልጥ ይገረማሉ። ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም ወዳለው ሰው ዘንድ ቀረብ አለችና እግሮቹን በእንባዎቿ እያራሰች በጠጉሯ በማበስ ለሚያከናውናቸው ሥራዎቹ ያላትን አድናቆት ገለጸች።
2 ሴትዬዋ ‘በከተማው የታወቀች ኃጢአተኛ’ ብትሆንም እንኳ ይህ ሰው ማለትም ኢየሱስ አልተጸየፋትም። ሆኖም የቤቱ ባለቤት ስምዖን የተባለው ፈሪሳዊ የሴትዬዋን ኃጢአተኝነት አክብዶ ተመልክቶት ነበር። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ በመበደራቸው ምክንያት ዕዳ ውስጥ ስለገቡ ሁለት ሰዎች ተናገረ። አንደኛው ከፍተኛ ዕዳ ነበረበት። ይህ ሰው የነበረበት ዕዳ አንድ የቀን ሠራተኛ ሁለት ዓመት ሙሉ ላቡን አንጠፍጥፎ በመሥራት ሊያገኝ ከሚችለው ደሞዝ ጋር የሚተካከል ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የመጀመሪያውን አንድ አሥረኛ ማለትም በሦስት ወር ውስጥ ሊገኝ ከሚችለው ደሞዝ የሚያንስ ዕዳ ነበረበት። ሁለቱም የነበረባቸውን ዕዳ መክፈል ባቃታቸው ጊዜ አበዳሪው “ዕዳቸውን [“በነፃ፣” NW] ተወላቸው።” ከፍተኛ ዕዳ የተሰረዘለት ግለሰብ ፍቅሩን ለመግለጽ ይበልጥ እንደሚገፋፋ ግልጽ ነው። ኢየሱስ የተናገረውን ይህን ምሳሌ ከሴትዬዋ የደግነት ድርጊት ጋር ካዛመደ በኋላ “ኃጢአቱ በጥቂቱ ይቅር የሚባልለት . . . የሚወድደውም በጥቂቱ ነው” የሚል መሠረታዊ ሥርዓት አክሎ ተናገረ። ከዚያም ሴትዬዋን “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል” አላት።—ሉቃስ 7:36-48 የ1980 ትርጉም
3. ራሳችንን ምን እያልን መመርመር ይኖርብናል?
3 እስቲ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘ያቺ ሴት እኔ ብሆን ኖሮ ወይም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የምገኝ ብሆን ኖሮና ምሕረት ቢደረግልኝ ሌሎችን ይቅር ለማለት እምቢተኛ እሆን ነበር?’ ‘ኧረ በጭራሽ’ ብለህ እንደምትመልስ የታወቀ ነው። የሆነ ሆኖ እኔ ይቅር ባይ ነኝ ብለህ አፍህን ሞልተህ መናገር ትችላለህ? ይቅር ባይነት ጉልህ ባሕርይህ ነውን? ብዙውን ጊዜ ቶሎ ይቅር የምትልና በሌሎችም ዘንድ በዚህ ባሕርይህ የምትታወቅ ነህን? ሁላችንም እንዲህ እያልን ራሳችንን በግልጽ መመርመር የሚገባን ለምን እንደሆነ ቀጥለን እንመልከት።
ይቅር ማለት አስፈላጊ ነው —ለእኛም ይቅርታ ተደርጎልናል
4. ራሳችንን በሚመለከት የትኛውን ሐቅ አምነን መቀበል ይኖርብናል?
4 መቼም ፍጹም አለመሆንህን በሚገባ ታውቃለህ። ጥያቄ ቢቀርብልህ ምናልባትም በ1 ዮሐንስ 1:8 ላይ የሚገኙትን “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” የሚሉትን ቃላት በመጥቀስ ኃጢአተኛ መሆንህን አላንዳች ማመንታት አምነህ ትቀበላለህ። (ሮሜ 3:23፤ 5:12) አንዳንዶች ከባድና አስጸያፊ ኃጢአቶችን በመፈጸማቸው ኃጢአተኝነታቸው በገሃድ ይታያል። ምንም እንኳ አንተ እንደነዚህ ያሉ ኃጢአቶችን ባትሠራም በተለያየ መንገድና በተደጋጋሚ ጊዜያት የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ሳታሟላ የቀረህባቸው ወይም በሌላ አነጋገር ኃጢአት የሠራህባቸው ጊዜያት እንዳሉ የታወቀ ነው። ይህ እውነት አይደለም?
5. አምላክን ስለ ምን ነገር ልናመሰግነው ይገባል?
5 ስለዚህ ሁኔታህ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሰጠው መግለጫ ጋር የሚስማማ ሊሆን ይችላል:- “እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፣ ከእርሱ [ከኢየሱስ] ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ።” (ቆላስይስ 2:13፤ ኤፌሶን 2:1-3) ‘በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ’ የሚለውን ሐረግ ልብ በል። ይህ ብዙ ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው። ሁላችንም እንደ ዳዊት “አቤቱ፣ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ” ብለን እንድንማጸን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን።—መዝሙር 25:11፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
6. ይሖዋንና ይቅር ባይነትን በተመለከተ ምን ነገር እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
6 አንተ ወይም ማናችንም ይቅርታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ ቁልፍ የሆነው ነገር ይሖዋ አምላክ ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑ ነው። ይቅር ባይነት የይሖዋ አምላክ ባሕርይ አብይ ገጽታ ነው። (ዘጸአት 34:6, 7፤ መዝሙር 86:5) አምላክ በጸሎት ወደ እርሱ ቀርበን ምሕረት እንዲያደርግልን በሌላ አባባል ይቅር እንዲለን እንድንጠይቀው እንደሚጠብቅብን የታወቀ ነው። (2 ዜና መዋዕል 6:21፤ መዝሙር 103:3, 10, 14) ይቅር ለማለት የሚያስችለውን ሕጋዊ መሠረት ለመጣልም የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት አዘጋጅቷል።—ሮሜ 3:24፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 14
7. በምን ረገድ ይሖዋን ለመምሰል መፈለግ ይኖርብሃል?
7 አንተም ሌሎችን ይቅር ማለት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትችል ዘንድ አምላክ ይቅር በማለት ረገድ ያሳየውን የፈቃደኝነት ምሳሌ መመልከት ይኖርብሃል። ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ [“በነፃ፣” NW] ይቅር እንዳላችሁ [“በነፃ፣” NW] ይቅር ተባባሉ” ብሎ በመጻፍ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶታል። (ኤፌሶን 4:32) ጳውሎስ በመቀጠል “እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ [“የምትመስሉ፣” NW] ሁኑ” ብሎ ሲናገር አምላክ ከተወው ምሳሌ ትምህርት መቅሰም እንዳለብን መግለጹ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ኤፌሶን 5:1) በሁለቱ መካከል ያለውን ዝምድና አስተዋልክ? ይሖዋ አምላክ ይቅር ብሎሃል። ስለዚህ ጳውሎስ በግልጽ ለማስገንዘብ እንደፈለገው አንተም የአምላክን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች ‘ርኅራኄ ማሳየትና በነፃ ይቅር’ ማለት ይኖርብሃል። ይሁን እንጂ እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ ‘ታዲያ እኔ ይህን እያደረኩ ነኝን? በተፈጥሮዬ ይቅር ለማለት የሚከብደኝ እንኳን ብሆን ይቅር ባይ በመሆን ረገድ አምላክን ለመምሰል እየተጣጣርኩኝ ነውን?’
ይቅር ባይ ለመሆን መጣጣር ይኖርብናል
8. የጉባኤዎቻችንን ሁኔታ በተመለከተ ምን ነገር መገንዘብ ይኖርብናል?
8 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የይቅር ባይነትን አምላካዊ ጎዳና እንድንከተል የሚያደርጉ ሁኔታዎች ብዙም አያጋጥሙንም ብሎ ማሰቡ ጥሩ ነው። እውነታው ግን ከዚያ የተለየ ነው። ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ኢየሱስ የተወውን የፍቅር ምሳሌ ለመከተል እንደሚጣጣሩ የታወቀ ነው። (ዮሐንስ 13:35፤ 15:12, 13፤ ገላትያ 6:2) የዚህን ክፉ ዓለም አስተሳሰብ፣ አነጋገርና ድርጊት እርግፍ አድርገው ለመተው ረዥም ጊዜ የፈጀ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን አሁንም ጥረት ማድረጋቸውን አላቆሙም። የአዲሱን ሰው ባሕርያት ማንጸባረቅ ከልብ ይፈልጋሉ። (ቆላስይስ 3:9, 10) ሆኖም ዓለም አቀፉ ጉባኤም ሆነ እያንዳንዱ ጉባኤ ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች የተገነባ የመሆኑን ሃቅ መዘንጋት የለብንም። በጥቅሉ ሲታይ ቀድሞ ከነበሩበት ሁኔታ በእጅጉ እንደተሻሻሉ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ፍጹማን አይደሉም።
9, 10. በወንድሞች መካከል ችግሮች ቢነሱ መደነቅ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
9 በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍጽምናን መጠበቅ እንደማይገባን አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦልናል። ለምሳሌ ያህል በቆላስይስ 3:13 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የጳውሎስ ቃላት ልብ በል። “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ [“በነፃ፣” NW] ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ [“ይሖዋ፣” NW] ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።”
10 እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎችን ይቅር በማለትም ሆነ ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ያለብን ግዴታ አምላክ እኛን ይቅር ከማለቱ ጋር የተቆራኘ ነገር መሆኑን ያሳስበናል። ይህ ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጳውሎስ እንደገለጸው አንድ ሰው ሌላውን ‘እንዲነቅፍ የሚያደርግ’ ምክንያት ሊኖረው ስለሚችል ነው። ጳውሎስ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ተገንዝቦ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ‘በሰማይ የተጠበቀ ተስፋ’ በነበራቸው ‘ቅዱሳን’ ክርስቲያኖች መካከል እንኳ ሳይቀር አንዱ ሌላውን እንዲነቅፍ ምክንያት የሚሆኑ ሁኔታዎች ይፈጠሩ ነበር። (ቆላስይስ 1:2, 5) ‘የእግዚአብሔር ምርጦች፣ ቅዱሳን፣ የተወደዱ’ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በሌላቸው በዛሬው ጊዜ በሚኖሩ በአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ከዚያ የተለየ ነገር ይኖራል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? (ቆላስይስ 3:12) ስለዚህ በጉባኤያችን ውስጥ ለነቀፋ ምክንያት የሚሆኑ ማለትም በእርግጥ የተፈጸሙ ወይም ተፈጽመዋል ብለን የገመትናቸው ስሜት የሚጎዱ ስህተቶች ቢፈጠሩ መደነቅ አይኖርብንም።
11. ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ምንን በተመለከተ አሳስቦናል?
11 የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ያዕቆብ የተናገራቸው ቃላትም ወንድሞቻችንን በይቅርታ እንድናልፋቸው የሚያደርጉ ሁኔታዎች ቢያንስ አልፎ አልፎ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ መጠበቅ እንዳለብን ያሳያሉ። “ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፣ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።” (ያዕቆብ 3:13, 14) “መራራ ቅናትና አድመኛነት” በእውነተኛ ክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ? አዎን፣ ከያዕቆብ ቃላት በግልጽ ለመረዳት እንደምንችለው እነዚህ ባሕርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩ ጉባኤዎች ውስጥ ተከስተው ነበር፤ ዛሬም ሊከሰቱ ይችላሉ።
12. በጥንቷ ፊልጵስዩስ ጉባኤ ምን ችግር ተነስቶ ነበር?
12 ከጳውሎስ ጋር አብረው በማገልገል ጥሩ ስም ባተረፉ ሁለት የተቀቡ ክርስቲያኖች መካከል የተፈጠረው ሁኔታ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል። የፊልጵስዩስ ጉባኤ አባል ስለነበሩት ስለ ኤዎድያን እና ሲንጤኪ የሚናገረውን ታሪክ ከዚህ ቀደም ሳታነብ አትቀርም። ምንም እንኳ ጉዳዩ በዝርዝር የሰፈረ ባይሆንም ፊልጵስዩስ 4:2, 3 እንደሚያሳየው በእነዚህ ሁለት ሴቶች መካከል አንድ ዓይነት አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። አለመግባባቱ የተፈጠረው በግዴለሽነትና ደግነት በጎደለው መንገድ በተነገሩ ቃላት፣ አንዳቸው ሌላውን ችላ በማለታቸው ወይም አንድ ዓይነት ቅናት የሚያሳድር የፉክክር መንፈስ በመፈጠሩ ይሆን? ብቻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በጣም ተካርረው ስለነበር ጳውሎስ እስከሚኖርበት እስከ ሮም እንኳ ሳይቀር ወሬው ደርሶ ነበር። እነዚህ መንፈሳዊ እህትማማቾች ተኮራርፈው ሊሆን ስለሚችል በስብሰባዎች ላይ አንዷ ሌላዋን እንዳላየች ሆና እንድታልፍ ወይም ለየጓደኞቻቸው አንዷ ስለ ሌላዋ ጥሩ ያልሆነ ወሬ እንድታወራ አድርጓት ሊሆን ይችላል።
13. ኤዎድያን እና ሲንጤኪ በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት የፈቱት እንዴት ሳይሆን አይቀርም? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 በጉባኤህ ውስጥ በአንዳንዶች መካከል እንዲህ ያለ ሁኔታ ተፈጥሮ ተመልክተህ ታውቃለህ? ወይም አንተ ራስህ እንዲህ ያለ ሁኔታ ገጥሞህ ያውቃል? ይህን የመሰለ ችግር በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በተወሰነ መጠን ሊከሰት ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ እነዚያን ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ እህቶች “በጌታ እንዲስማሙ” መክሯቸዋል። ችግሩን አንስተው ለመወያየት፣ ምንም ሳይደባበቁ ለመነጋገር፣ ይቅር ለመባባልና ከዚያም አልፈው የይሖዋን የይቅር ባይነት ባሕርይ ለመኮረጅ ተስማምተው ሊሆን ይችላል። ኤዎድያን እና ሲንጤኪ በመካከላቸው የነበረውን አለመግባባት አስወግደዋል ብለን ለማመን የሚያበቁን በቂ ምክንያቶች አሉን። እኛም ብንሆን በዚህ ረገድ ሊሳካልን ይችላል። ይህን የመሰለ የይቅር ባይነት ባሕርይ በዛሬውም ጊዜ ቢሆን ማንጸባረቅ ይቻላል።
ይቅር በማለት ሰላም ፍጠሩ
14. የግል አለመግባባቶች በሚነሱበት ወቅት በተቻለ መጠን ችላ ብሎ ማለፉ ጥሩና የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?
14 በአንተና በአንድ ሌላ ክርስቲያን መካከል ችግር ቢፈጠር ይቅር ለማለት ማድረግ የሚኖርብህ ነገር ምንድን ነው? ግልጹን ለመናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ጠቃሚ ምሳሌዎችና ምክሮች ከመከተል የተሻለ ሌላ አማራጭ ዘዴ የለም። ይህን ጠቃሚ ምክር ሰምቶ ተግባራዊ ማድረግ ቀላል አይደለም። ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጉዳዩን መርሳት ወይም መተው ነው። በኤዎድያን እና በሲንጤኪ ላይ እንደታየው ችግሮች በሚነሱበት ወቅት ስህተተኛው ወይም ጥፋተኛው ሌላኛው ወገን እንደሆነ አድርጎ መናገር የተለመደ ነው። አንተም እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚገጥምህ ጊዜ ጥፋተኛው ሌላኛው ክርስቲያን እንደሆነ ወይም በጣም እንደጎዳህ ትናገር ይሆናል። የሆነ ሆኖ ይቅር በማለት ጉዳዩን መዝጋት ትችል ይሆን? አንድ ክርስቲያን ቢጎዳህና ስህተቱ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የእሱ ቢሆን ይቅር በማለትና ጉዳዩን በማለፍ ትልቁን ሚና የምትጫወተው አንተ መሆንህን ማስታወስ ይኖርብሃል።
15, 16. (ሀ) ሚክያስ ይሖዋን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ‘ዓመፅን ያልፋል’ ሲባል ምን ማለት ነው?
15 ይቅር በማለት በኩል ምሳሌ የሚሆነን አምላክ መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ። (ኤፌሶን 4:32–5:1) አምላክ በደልን እንዴት እንደሚያልፍ ነቢዩ ሚክያስ ሲናገር “በደልን ይቅር የሚል፣ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ [“የሚያልፍ፣” NW] እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቁጣውን ለዘላለም አይጠብቅም” በማለት ጽፏል።—ሚክያስ 7:18
16 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘ዓመፅን ያልፋል’ ብሎ ሲናገር አምላክ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችን ዳግም ማስታወስ ስለሚሳነው ሊያስታውሳቸው አይችልም ማለቱ አይደለም። ከባድ ኃጢአት የፈጸሙትን የሳምሶንንና የዳዊትን ሁኔታ ተመልከት። አምላክ ብዙ ጊዜያት ካለፉ በኋላም እንኳ ቢሆን እነዚህ ሰዎች የፈጸሟቸውን ኃጢአቶች ለማስታወስ አልተቸገረም፤ እንዲያውም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኃጢአታቸው እንዲመዘገብ በማድረግ እኛም እንድናውቅ አድርጎናል። ሆኖም ይቅር ባይ የሆነው አምላካችን ለእነዚህ ሁለት ሰዎች ምሕረቱን አሳይቷቸዋል፤ እምነታቸውንም መኮረጅ እንችል ዘንድ እንደ ምሳሌ አድርጎ አስቀምጦልናል።—ዕብራውያን 11:32፤ 12:1
17. (ሀ) ሌሎች ሰዎች የፈጸሙብንን ስህተት ወይም በደል ለማለፍ የትኛው አቀራረብ ሊረዳን ይችላል? (ለ) እንዲህ ለማድረግ ከጣርን ይሖዋን የምንመስለው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
17 አዎን፣ ይሖዋ የተፈጸሙ በደሎችን ‘ያልፋል።’a ዳዊትም ይህን ሁኔታ ያውቅ ስለነበር ከአምላክ ምሕረት ለማግኘት በተደጋጋሚ ጸልዮአል። (2 ሳሙኤል 12:13፤ 24:10) የእምነት ባልደረቦቻችን ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት የሚፈጽሙብንን ጥቃቅን ስህተቶችና በደሎች ለማለፍ ፈቃደኛ በመሆን ረገድ አምላክን መምሰል እንችል ይሆን? ከመሬት ለመነሳት እያኮበኮበ ባለ አንድ አውሮፕላን ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ወደ ውጭ ስትመለከት ማኮብኮቢያው አቅራቢያ አንድ የምታውቀው ሰው እንደ ልጅ ምላሱን እያወጣ ሲሳደብ ትመለከታለህ። የተናደደበት ነገር እንደነበር ይገባሃል። አንተን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ ፈጽሞ አንተ ትዝ አላልከው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ አውሮፕላኑ ከፍታውን እየጨመረ ሲሄድ ግለሰቡ ትንሽ ጥቁር ነጥብ ሆኖ ይታይሃል። በአንድ ሰዓት ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀህ ስለምትሄድ የግለሰቡን ስድብ የዚያኑ ያህል ትተኸው መጥተሃል ማለት ነው። በተመሳሳይም ብዙውን ጊዜ ይሖዋን ለመምሰል መጣጣራችንና የተፈጸመብንን በደል በጥበብ ማለፋችን ይቅር እንድንል ሊረዳን ይችላል። (ምሳሌ 19:11) አንዲት ትንሽ ስህተት ከአሥር ዓመት በኋላ ወይም በሺህ ዓመቱ ጊዜ ውስጥ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ይበልጡኑ ኢምንት መስላ አትታይምን? ታዲያ በደሉን ለምን ችላ ብለን አናልፈውም?
18. የተፈጸመብንን በደል ወደ ጎን ለመተውና ለመርሳት እንደማንችል ሆኖ ቢሰማን የትኛውን ምክር ልንሠራበት እንችላለን?
18 ይሁንና ከስንት አንድ ጊዜ ሊያጋጥም እንደሚችለው ስለጉዳዩ ጸልየህና ይቅር ለማለት ሞክረህም እንደዚያ ማድረግ እንደማትችል ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ ምን ታደርጋለህ? ኢየሱስ ሰላም ለመፍጠርና ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለማግኘት ወደ ሌላኛው ወገን እንድትሄድና ለብቻችሁ ሆናችሁ እንድትነጋገሩ ምክር ሰጥቷል። “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።”—ማቴዎስ 5:23, 24
19. ከወንድማችን ጋር ሰላምን ለመፍጠር በምንሞክርበት ጊዜ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል? የትኛውንስ ዝንባሌ ማስወገድ ይኖርብናል?
19 ኢየሱስ አንተ ትክክል መሆንህን እርሱ ደግሞ ጥፋተኛ መሆኑን ለማሳመን ወደ ወንድምህ ዘንድ ሂድ እንዳላለ ግልጽ ነው። ጥፋተኛው ምናልባት እርሱ ሊሆን ይችላል። በአብዛኛው ግን በሁለታችሁም በኩል ጥፋት ይኖራል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በአንደኛ ደረጃ ግባችን ሊሆን የሚገባው ግለሰቡ ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ እግራችን ላይ እንዲወድቅ ማድረግ አይደለም። ወንድምህን የምታነጋግረው በዚህ መንፈስ ተነሳስተህ ከሆነ የተሳካ ውጤት የማግኘትህ አጋጣሚ በጣም የመነመነ ነው። በተጨማሪም ግባችን የተፈጸሙብንን ወይም ተፈጽመውብናል ብለን ያሰብናቸውን ጥቃቅን ስህተቶች ሁሉ አንድ በአንድ እያነሳን ለመነጋገርም መሆን የለበትም። ክርስቲያናዊ ፍቅር በሚያንጸባርቅ በረጋ መንፈስ ውይይት ስታደርጉ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ አለመግባባት እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ከተገነዘባችሁ ሁለታችሁም ችግሩን ለመፍታት ልትጥሩ ትችላላችሁ። ውይይት አድርጋችሁም ስምምነት ላይ ላትደርሱ ትችሉ ይሆናል። ሆኖም ውይይት ካደረጋችሁ በኋላ ስምምነት ላይ ባትደርሱ የግድ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባችሁ ሆኖ ይሰማችኋል? ሁለታችሁም ይቅር ባይ የሆነውን አምላካችንን ለማምለክ ከልብ የምትፈልጉ እንደሆናችሁ ተስማምታችሁ መለያየታችሁ የተሻለ አይሆንም? ይህን ሃቅ ከተቀበላችሁ “ፍጹም ባለመሆናችን የተነሳ እንዲህ ያለ አለመግባባት በመካከላችን በመፈጠሩ አዝናለሁ። እባክህ እንርሳው” ብላችሁ ከልባችሁ ለመናገር አይከብዳችሁም።
20. ሐዋርያት ከተዉት ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
20 ከሐዋርያት መካከል አንዳንዶች ከፍተኛ ክብር ማግኘት ፈልገው በነበረ ጊዜ በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውስ። (ማርቆስ 10:35-39፤ ሉቃስ 9:46፤ 22:24-26) ይህም ከፍተኛ ውጥረትን ምናልባትም የስሜት መጎዳትን ሌላው ቀርቶ ከፍተኛ ቅያሜን ፈጥሮ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሁሉም እንዲህ ያለውን አለመግባባት ችላ ብለው ማለፍና አብረው መሥራታቸውን መቀጠል ችለዋል። እንዲያውም አንዱ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ብሎ ለመጻፍ ችሏል:- “ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፣ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፣ መልካምንም ያድርግ፣ ሰላምን ይሻ ይከተለውም።”—1 ጴጥሮስ 3:10, 11
21. ኢየሱስ ይቅር ባይ መሆንን በሚመለከት ምን ጥልቅ ምክር ለግሷል?
21 እንደ ሰንሰለት የተያያዘውን ሂደት የመጀመሪያ ምዕራፍ ቀደም ሲል ተመልክተናል:- አምላክ ባለፉት ጊዜያት የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች በሙሉ ይቅር እንዳለን ሁሉ እኛም የእርሱን ምሳሌ በመኮረጅ ወንድሞቻችንን ይቅር ማለት ይኖርብናል። (መዝሙር 103:12፤ ኢሳይያስ 43:25) ሆኖም በዚህ ዑደት ላይ ሌላም ማከል እንችላለን። ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ከተናገረ በኋላ እንዲህ አለ:- “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋል።” ከአንድ ዓመት ጊዜ በኋላም ጉዳዩን እንደገና በማንሳት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብለው እንዲጸልዩ አስተማራቸው:- “ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፣ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና።” (ማቴዎስ 6:12, 14፤ ሉቃስ 11:4) ከዚያም ከመሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ እንዲህ በማለት አክሎ ተናገረ:- “ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፣ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፣ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት።”—ማርቆስ 11:25
22, 23. ይቅር ለማለት ያለን ፈቃደኝነት የወደፊት ሕይወታችንን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
22 አዎን፣ የአምላክን ያልተቋረጠ ይቅርታ ማግኘታችን በእጅጉ የተመካው ወንድሞቻችንን ይቅር ለማለት ባለን ፈቃደኝነት ላይ ነው። በሁለት ክርስቲያኖች መካከል አንድ ዓይነት ችግር በሚነሳበት ጊዜ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ትንሽ ቅር ቢያሰኙን፣ እዚህ ግባ የማይባል በደል ቢፈጽሙብን ወይም ከሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ቢጎዱን ስህተት መሥራታቸውን ለማሳመን ከመሞከር ይልቅ የአምላክን ይቅርታ ማግኘቱ ከሁሉ የተሻለ አይሆንምን?’ ፍርዱን አንተው ስጥ።
23 ይሁን እንጂ ጉዳዩ ከቀላል የግል አለመግባባቶች ወይም ችግሮች አልፎ የሚሄድ ቢሆንስ? በማቴዎስ 18:15-18 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ምክር ተግባራዊ የሚሆነው መቼ ነው? እስቲ በሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ቁም ነገሮች እንመርምር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ምሁር እንደተናገሩት ሚክያስ 7:18 ላይ የተሠራበት የዕብራይስጡ ምሳሌያዊ አነጋገር “በሚጓዝበት ጊዜ ትኩረት ሊሰጠው ያልፈለገውን ነገር ምንም ልብ ሳይል እያለፈ ከሚሄድ ተጓዥ ባሕርይ የተወሰደ ነው። እዚህ ላይ ለመግለጽ የተፈለገው አምላክ ኃጢአትን አያስተውልም ወይም አቃልሎ ይመለከታል ወይም ከቁብ አይቆጥርም ለማለት ሳይሆን ለመቅጣት ሲል ሆነ ብሎ በአእምሮው ውስጥ አይዝም ወይም በሌላ አባባል ከመቅጣት ይልቅ ይቅር የሚል መሆኑን የሚያመለክት ነው።”—መሳፍንት 3:26፤ 1 ሳሙኤል 16:8
ታስታውሳለህ?
◻ ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ይሖዋ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
◻ በጉባኤ ውስጥ ስላሉ ወንድሞች ምን ነገር ማስታወስ ይገባናል?
◻ ብዙውን ጊዜ ቅር የሚያሰኙ ድርጊቶችን ወይም ትናንሽ በደሎችን በተመለከተ ምን ለማድረግ መሞከር ይኖርብናል?
◻ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከወንድሞቻችን ጋር ሰላምን ለመፍጠር ምን ልናደርግ እንችላለን?
[በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአንድ ክርስቲያን ጋር አለመግባባት በሚፈጠርበት ወቅት ጉዳዩን ለማለፍ ሞክር፤ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ጉዳዩ ቀስ በቀስ እየከሰመ ይሄዳል