ወደ አምላክ መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?
አንድ ደቀ መዝሙር ጸሎት እንዲያስተምራቸው ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ ፈቃደኛ ሆኗል። ሉቃስ 11:2-4 (የ1980 ትርጉም) ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል፦ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ አላቸው፦ [‘በሰማይ የምትኖር] አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ፣ መንግሥትህ ትምጣ፤ የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን፤ እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በልልን፣ ወደ ፈተናም አታግባን።’” ይህ ጸሎት የጌታ ጸሎት በመባል ይታወቃል። ጸሎቱ ብዙ ነገሮችን አካትቷል።
ገና ከመነሻው የጸሎቱ የመጀመሪያ ቃላት ጸሎታችን ለማን መቅረብ እንዳለበት ማለትም በሰማይ ወዳለው አባታችን መጸለይ እንዳለብን ይነግሩናል። ኢየሱስ ለሌላ አካል፣ ምስል፣ “ቅዱስ” ወይም ለራሱ እንኳ ጸሎት እንዲቀርብ ምንም ዓይነት ሐሳብ እንዳላቀረበ ልብ በል። ከዚህም በላይ አምላክ “ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” ብሏል። (ኢሳይያስ 42:8) ጸሎቱን የሚያቀርበው ሰው የቱንም ያህል ከልቡ ቢጸልይም ሰማያዊ አባታችን ከእርሱ ሌላ ለማንኛውም ነገር ወይም ለየትኛውም አካል የሚቀርበውን ጸሎት አይሰማም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ጸሎት ሰሚ’ የተባለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው።—መዝሙር 65:2
አንዳንድ ሰዎች “ቅዱሳን” የሚያገለግሉት ከአምላክ ጋር ለማማለድ ብቻ ነው ይሉ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ራሱ እንዲህ በማለት አዝዟል፦ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።” (ዮሐንስ 14:6, 13) ኢየሱስ ቅዱስ የተባለ ሁሉ ያማልዳል አላለም። ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ምን ብሎ እንደተናገረ ተመልከት፦ “የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”—ሮሜ 8:34፤ ዕብራውያን 7:25
መቀደስ ያለበት ስም
ኢየሱስ በጸሎቱ ውስጥ ቀጥሎ የጠቀሳቸው ቃላት “ስምህ ይቀደስ” ይላሉ። አንድ ሰው የአምላክን ስም ሳያውቀውና ሳይጠቀምበት ሊቀድሰው ማለትም ከስድብ ሊያነጻው ወይም የተለየ አድርጎ ሊይዘው እንዴት ይችላል? አምላክ “በብሉይ ኪዳን” ውስጥ ከ6,000 ጊዜ በላይ ይሖዋ በሚለው የግል ስም ተጠርቷል።
በካቶሊክ ዱዌይ ቨርሽን ላይ ለዘጸአት 6:3 የተሰጠው የግርጌ ማስታወሻ የአምላክን ስም በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ዘመናውያን ይሖዋ የሚለውን ስም ፈጥረዋል። . . . በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ ያለው [የአምላክ] ስም ለረጅም ጊዜ ሳይሠራበት ስለቆየ በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛ አነባበቡ አይታወቅም።” በዚህ የተነሳ የካቶሊኩ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል ያህዌህ በሚለው ስም ይጠቀማል። አንዳንድ ምሁራን ይህን አነባበብ ቢመርጡም በእንግሊዝኛ “ጅሆቫ” ብሎ መጥራቱ ተቀባይነት ያለውና ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲሠራበት የቆየ ነው። ሌሎች ቋንቋዎች መለኮታዊውን ስም የሚጠሩበት የየራሳቸው መንገድ አላቸው። ዋናው ቁም ነገር ስሙን ለመቀደስ እንድንችል በስሙ መጠቀሙ ላይ ነው። ቤተ ክርስቲያንህ ስትጸልይ ይሖዋ በሚለው ስም እንድትጠቀም አስተምሮሃልን?
በጸሎት ላይ የሚጠቀሱ ተገቢ ጉዳዮች
ኢየሱስ በመቀጠል ደቀ መዛሙርቱ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተማራቸው። የማቴዎስ ወንጌል “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ፣ እንዲሁም በምድር ይሁን” የሚሉትን ቃላት ይጨምራል። (ማቴዎስ 6:10 የ1980 ትርጉም) የአምላክ መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ መስተዳድር ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚተነብየው ይህ መንግሥት በቅርቡ ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት አጥፍቶ ዓለም አቀፋዊ ሰላም ያሰፍናል። (መዝሙር 72:1-7፤ ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 21:3-5) በዚህ የተነሳ እውነተኛ ክርስቲያኖች በጸሎታቸው ውስጥ ሁልጊዜ ስለመጪው መንግሥት ይጠቅሳሉ። ቤተ ክርስቲያንህ እንዲህ እንድታደርግ አስተምሮሃልን?
በተጨማሪም የሚያሳስቡንን የግል ጉዳዮች በጸሎታችን ውስጥ መጥቀስ እንደምንችል ኢየሱስ አሳይቷል። እንዲህ አለ፦ “የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን፤ እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በልልን፣ ወደ ፈተናም አታግባን።” (ሉቃስ 11:3, 4) የኢየሱስ ቃላት በዕለት ተዕለት ጉዳዮቻችን የአምላክን ፈቃድ መጠየቅ እንደምንችልና የሚያስጨንቀን ወይም የሚረብሸን ማንኛውም ነገር ሲያጋጥመን ወደ ይሖዋ መቅረብ እንደምንችል ያሳያሉ። በዚህ መንገድ አምላክን ዘወትር መለመናችን ሕይወታችን በእርሱ ላይ የተመካ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ስለዚህ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ ይበልጥ እያወቅን እንሄዳለን። አምላክ በደላችንን ይቅር እንዲለን በየዕለቱ መጠየቃችንም ቢሆን ጠቃሚ ነው። እንዲህ ስናደርግ ያለብንን ድካም ይበልጥ ከማወቃችንም በተጨማሪ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የሌሎችን ጉድለቶች ችለን እንድናልፍ ይረዳናል። በተለይ የዚህን ዓለም የሥነ ምግባር ዝቅጠት ስንመለከት ኢየሱስ ወደ ፈተና አታግባን ብለን እንድንጸልይ የሰጠን ምክር አስፈላጊ ነው። ከዚህ ጸሎት ጋር በመስማማት ወደ መጥፎ ድርጊት ሊመሩን ከሚችሉ ነገሮችና ሁኔታዎች መራቅ አለብን።
የጌታ ጸሎት አምላክን የሚያስደስቱ ጸሎቶች ስለማቅረብ ብዙ ትምህርት እንደሚሰጠን አያጠያይቅም። ሆኖም ኢየሱስ ይህን ጸሎት ዘወትር እንድንደጋግመው አስቦ ነበርን?
ስለ ጸሎት የተሰጠ ተጨማሪ ምክር
ኢየሱስ ጸሎትን በተመለከተ ተጨማሪ ትምህርት ሰጥቷል። ማቴዎስ 6:5, 6 እንዲህ ይላል፦ “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኵራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ . . . አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” እነዚህ ቃላት ጸሎት አንድን ሰው ለማስገረም ሲባል ለታይታ መቅረብ እንደሌለበት ያስተምሩናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያበረታታው በልብህ ውስጥ ያለውን ነገር በግልህ ለይሖዋ ታፈስለታለህን?—መዝሙር 62:8
ኢየሱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።” (ማቴዎስ 6:7) ኢየሱስ የተሸመደዱ ጸሎቶችን እንደማይደግፍ በግልጽ ለማየት ይቻላል። ጸሎቶችን ከመጽሐፍ ማንበብንም ቢሆን ከዚህ ለይቶ አይመለከተውም። በተጨማሪም በመቁጠሪያ ስለመጠቀም አልተናገረም።
አንድ የካቶሊክ የጸሎት መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት አምኗል፦ “በምናዝንበት ወይም በየዕለቱ ወደ እርሱ በምንጸልይበት ጊዜ ምስጋና ወይም ልመና ስናቀርብ ጸሎታችን ከሁሉ የተሻለ ሊሆንልን የሚችለው ከራሳችን የመነጨውን ነገር በራሳችን አባባል ስንናገር ነው።” የራሱ የኢየሱስ ጸሎቶች የተሸመደዱ ሳይሆኑ ከራሱ የመነጩ ነበሩ። ለምሳሌ በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ የተመዘገበውን የኢየሱስ ጸሎት አንብብ። ይህ ጸሎት ኢየሱስ የይሖዋ ስም ተቀድሶ ለማየት የነበረውን ፍላጎት ጠበቅ አድርጎ የሚገልጽና ከናሙና ጸሎቱ ጋር የሚስማማ ነበር። የኢየሱስ ጸሎት ከራሱ የመነጨና ልባዊ ነበር።
አምላክ የሚሰማቸው ጸሎቶች
የተሸመደዱ ጸሎቶች እንድታቀርብ፣ “ለቅዱሳን” ወይም ለምስሎች እንድትጸልይ አለዚያም እንደ መቁጠሪያ ባሉ ሃይማኖታዊ መሣሪያዎች እንድትጠቀም ተነግሮህ ከነበረ ኢየሱስ ባዘዘው መንገድ መጸለዩ መጀመሪያ ላይ አስፈሪ ይሆንብህ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ባዘዘው መንገድ ለመጸለይ ቁልፉ አምላክን ማወቅ ነው፤ ይህም ስሙን፣ ዓላማዎቹን፣ ባሕርያቱን ማወቅ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በማጥናት ይህን ማድረግ ትችላለህ። (ዮሐንስ 17:3) የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ዝግጁና ፈቃደኞች ናቸው። እስካሁንም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘እግዚአብሔር ቸር መሆኑን እንዲቀምሱ’ ረድተዋል! (መዝሙር 34:8) አምላክን ይበልጥ ባወቅከው መጠን ይበልጥ በጸሎት እርሱን ለማወደስ ትገፋፋለህ። አክብሮት በተሞላበት ጸሎት ወደ ይሖዋ ይበልጥ በቀረብክ መጠን ከእርሱ ጋር ያለህ ዝምድና እየጠበቀ ይሄዳል።
በዚህ የተነሳ ሁሉም እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ‘ሳያቋርጡ እንዲጸልዩ’ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ጸሎትህ የኢየሱስ ክርስቶስን መመሪያዎች ጨምሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስምም መሆኑን አረጋግጥ። በዚህ መንገድ አምላክ ጸሎትህን እንደሚቀበለው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን ይበልጥ ባወቅነው መጠን ወደ እርሱ ከልብ ለመጸለይ እንገፋፋለን