የኢየሱስ ትምህርቶች በጸሎትህ ይዘት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ?
“ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ።”—ማቴ. 7:28
1, 2. ሕዝቡ በኢየሱስ ትምህርት አሰጣጥ እጅግ የተደነቁት ለምን ነበር?
የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸውን ትምህርቶች አምነን መቀበልና በተግባር ማዋል ይገባናል። እንደ ኢየሱስ ያስተማረ ማንም ሰው እንደሌለ ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ያስተማረበት መንገድ ሰዎቹን አስደንቋቸው ነበር!—ማቴዎስ 7:28, 29ን አንብብ።
2 የይሖዋ ልጅ ያስተማረበት መንገድ፣ ፍጹማን ባልሆኑ የሰው ልጆች ትምህርቶች ላይ ተመርኩዘው የተንዛዛ ንግግር ይሰጡ ከነበሩት ጸሐፍት የተለየ ነበር። ክርስቶስ ያስተማረው የአምላክን ቃል በመሆኑ የሚናገረው “እንደ ባለሥልጣን” ነበር። (ዮሐ. 12:50) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የሰጣቸው ሌሎች ትምህርቶች በምናቀርበው ጸሎት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ቀጥለን እንመረምራለን፤ እነዚህ ትምህርቶች በጸሎታችን ይዘት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባል የምንለው ለምን እንደሆነም እንመለከታለን።
እንደ ግብዞች አትጸልዩ
3. በማቴዎስ 6:5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ ምክር ጠቅለል አድርገህ ተናገር።
3 ጸሎት የእውነተኛው አምልኮ አስፈላጊ ገጽታ ሲሆን አዘውትረን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የሰጣቸው ትምህርቶች በጸሎታችን ይዘት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ምክንያቱም እነሱ ሰዎች እንዲያዩአቸው በምኩራቦችና በጎዳና ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።”—ማቴ. 6:5
4-6. (ሀ) ፈሪሳውያን “በምኩራቦችና በጎዳና ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ” የሚፈልጉት ለምን ነበር? (ለ) እንደነዚህ ያሉት ግብዝ ሰዎች “ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል” ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
4 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሚጸልዩበት ጊዜ፣ በሰዎች ፊት ሃይማኖተኛ መስለው ለመታየት እንደሚሞክሩት ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ‘ግብዝ’ ፈሪሳውያን መሆን የለባቸውም። (ማቴ. 23:13-32) ግብዝ የሆኑት እነዚህ ሰዎች “በምኩራቦችና በጎዳና ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ” ይወዱ ነበር። እንዲህ የሚያደርጉት “ሰዎች እንዲያዩአቸው” ስለሚፈልጉ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ (ጠዋት ሦስት ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ) አንድ ላይ ተሰብስበው የመጸለይ ልማድ ነበራቸው። በርካታ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ከሚጸልዩት የይሖዋ አምላኪዎች ጋር አብረው ይጸልዩ ነበር። ከኢየሩሳሌም ውጪ የሚኖሩ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን ደግሞ ብዙውን ጊዜ በቀን ሁለቴ “በምኩራቦች” ይጸልዩ ነበር።—ከሉቃስ 18:11, 13 ጋር አወዳድር።
5 አብዛኞቹ ሰዎች ማለዳና ከሰዓት በኋላ ጸሎት በሚቀርብበት ጊዜ በቤተ መቅደሱ ወይም በምኩራብ አቅራቢያ ስለማይገኙ ባሉበት ቦታ ሆነው ሊጸልዩ ይችሉ ነበር። አንዳንዶች ጸሎት በሚቀርብበት ጊዜ “በጎዳና ማዕዘኖች” ላይ ለመገኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። ይህን የሚያደርጉት በዚያ የሚያልፉ “ሰዎች እንዲያዩአቸው” ስለሚፈልጉ ነው። ሃይማኖተኛ መስለው ለመታየት የሚጥሩት እነዚህ ግብዞች፣ ሰዎች እንዲያደንቋቸው ሲሉ ‘ለታይታ ጸሎታቸውን ያስረዝማሉ።’ (ሉቃስ 20:47) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖረን አይገባም።
6 ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉት ግብዝ ሰዎች “ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል” ሲል ተናግሯል። እነዚህ ግለሰቦች የሰዎችን አድናቆትና ውዳሴ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን የሚያገኙትም ይህንኑ ብቻ ነው። ይሖዋ፣ እነዚህ ግብዞች ለሚያቀርቡት ጸሎት ምላሽ ስለማይሰጥ ሙሉ ብድራታቸው ከሰዎች የሚያገኙት ሙገሳ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ጸሎትን አስመልክቶ ቀጥሎ ከተናገረው ሐሳብ ለመገንዘብ እንደምንችለው የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች የሚያቀርቡትን ጸሎት አምላክ ይሰማል።
7. ኢየሱስ ‘ክፍላችን’ ውስጥ ገብተን መጸለይ እንዳለብን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
7 “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።” (ማቴ. 6:6) ኢየሱስ፣ ወደ ክፍላችን ገብተን በሩን ከዘጋን በኋላ እንድንጸልይ የሰጠው ምክር አንድ ሰው ጉባኤውን ወክሎ መጸለይ እንደሌለበት የሚያሳይ አይደለም። ኢየሱስ ይህን ምክር የሰጠው አንድ ሰው በሕዝብ ፊት በሚጸልይበት ጊዜ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብና አድናቆት ለማትረፍ መሞከር እንደማይገባው ለማስገንዘብ ሲል ነው። የአምላክን ሕዝቦች ወክለን በሰዎች ፊት የመጸለይ መብት ስናገኝ ይህን ምክር ልናስታውስ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ጸሎትን አስመልክቶ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር መታዘዝ ይኖርብናል።
8. በማቴዎስ 6:7 ላይ እንደተገለጸው ከጸሎት ጋር በተያያዘ የትኛውን ልማድ ልናስወግድ ይገባል?
8 “በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ተሰሚነት የሚያገኙ ይመስላቸዋል።” (ማቴ. 6:7) ኢየሱስ ጸሎት በምናቀርብበት ጊዜ ልናስወግደው የሚገባን ሌላው ልማድ መደጋገም እንደሆነ ገልጿል። ይህን ሲል ግን ከልብ የመነጨ ልመና እንዲሁም ምስጋና ስናቀርብ ፈጽሞ መደጋገም እንደሌለብን መናገሩ አልነበረም። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ያንኑ ቃል” ደጋግሞ ጸልዮአል።—ማር. 14:32-39
9, 10. ጸሎታችን ተደጋጋሚ መሆን የለበትም ሲባል ምን ማለት ነው?
9 በምንጸልይበት ጊዜ “አሕዛብ” እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግመን ማነብነብ አይኖርብንም። አሕዛብ በቃላቸው የሸመደዷቸውን አስፈላጊ ያልሆኑ ሐረጎች ‘ደጋግመው’ ያነበንባሉ። የበኣል አምላኪዎች “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ “ከጧት እስከ እኩለ ቀን” ድረስ የዚህን የሐሰት አምላክ ስም መጥራታቸው ምንም አልፈየደላቸውም። (1 ነገ. 18:26) በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ተሰሚነት የሚያገኙ” እየመሰላቸው የተንዛዙና ተደጋጋሚ የሆኑ ቃላትን የያዙ ጸሎቶችን ያቀርባሉ። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው “ቃላት በማብዛት” ረጅምና ተደጋጋሚ የሆነ ጸሎት ማቅረብ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ኢየሱስ የተናገረው ሌላም ነጥብ አለ፦
10 “ስለዚህ እንደ እነሱ አትሁኑ፤ ምክንያቱም አባታችሁ የሆነው አምላክ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።” (ማቴ. 6:8) በርካታ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ጸሎት በሚያቀርቡበት ወቅት እንደ አሕዛብ ቃላት ያበዙ ነበር። ውዳሴን፣ ምስጋናን እንዲሁም ልመናን ያካተተ ከልብ የመነጨ ጸሎት የእውነተኛው አምልኮ አስፈላጊ ገጽታ ነው። (ፊልጵ. 4:6) ሆኖም አምላክ ይረሳ ይመስል የሚያስፈልጉንን ነገሮች መላልሰን ልንነግረው እንደሚገባ በማሰብ ስለ አንድ ነገር ደጋግመን መጸለይ ስሕተት ነው። ጸሎት የምናቀርበው ‘ገና ሳንለምነው ምን እንደሚያስፈልገን ለሚያውቀው’ አምላክ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል።
11. በሕዝብ ፊት ጸሎት የማቅረብ መብት ሲሰጠን የትኞቹን ነጥቦች ማስታወስ ይኖርብናል?
11 ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ስለሌላቸው ጸሎቶች የተናገረው ሐሳብ፣ የተራቀቁ ቃላትን በመጠቀም አላስፈላጊ ድግግሞሽ የበዛበት ጸሎት ማቅረብ ይሖዋን እንደማያስደስተው ሊያስገነዝበን ይገባል። ከዚህም ሌላ አንድ ሰው በሕዝብ ፊት ጸሎት በሚያቀርብበት ጊዜ አድማጮቹን ለማስደመም መሞከር ወይም “አሜን” ለማለት እስኪናፍቁ ድረስ ጸሎቱን ማርዘም እንደሌለበት መገንዘብ ይኖርበታል። በተጨማሪም በጸሎት ላይ ለአድማጮች ምክር መስጠት ወይም ማስታወቂያ መናገር ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ከሰጠው ትምህርት ጋር ይጋጫል።
ኢየሱስ እንዴት መጸለይ እንዳለብን አስተምሮናል
12. “ስምህ ይቀደስ” የሚለው ልመና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ኢየሱስ፣ ውድ ከሆነው የጸሎት መብት ጋር በተያያዘ ሊወገዱ የሚገባቸውን ልማዶች በመግለጽ ብቻ ሳይወሰን ደቀ መዛሙርቱ እንዴት መጸለይ እንዳለባቸውም አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9-13ን አንብብ።) ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን የሰጠን በቃላችን ሸምድደን እንድንደግመው ሳይሆን እንዴት መጸለይ እንዳለብን ለማስተማር ሲል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በጸሎቱ መክፈቻ ላይ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት በቅድሚያ ስለ አምላክ ጠቅሷል። (ማቴ. 6:9) ከምድር ርቆ ‘በሰማያት የሚኖረው’ ይሖዋ ፈጣሪያችን በመሆኑ እሱን “አባታችን” ብለን መጥራታችን ተገቢ ነው። (ዘዳ. 32:6፤ 2 ዜና 6:21፤ ሥራ 17:24, 28) ‘አባቴ’ ከማለት ይልቅ “አባታችን” በሚለው ቃል መጠቀማችን ሌሎች የእምነት አጋሮቻችንም ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዳላቸው ያስታውሰናል። “ስምህ ይቀደስ” የሚለው ሐረግ፣ ይሖዋ በኤደን ዓመፅ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በስሙ ላይ የተቆለለውን ስድብ በሙሉ በማስወገድ ስሙን ለማስቀደስ እርምጃ እንዲወስድ የቀረበ ልመና ነው። ይሖዋ ክፋትን ከምድር ላይ ጠራርጎ በማጥፋት ለዚህ ጸሎት ምላሽ ይሰጣል፤ በዚህ መንገድ ስሙን ያስቀድሳል።—ሕዝ. 36:23
13. (ሀ) “መንግሥትህ ይምጣ” የሚለው ልመና ምላሽ የሚያገኘው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሲፈጸም ምን ነገሮች ይከናወናሉ?
13 “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” (ማቴ. 6:10) ኢየሱስ በሰጠው የናሙና ጸሎት ላይ የተጠቀሰው “መንግሥት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በሰማይ ያለውን መሲሐዊ መስተዳድር ሲሆን ይህ መንግሥት የሚመራው በክርስቶስና ከሞት ተነስተው አብረውት በሚገዙት “ቅዱሳን” ነው። (ዳን. 7:13, 14, 18፤ ኢሳ. 9:6, 7) ይህ መንግሥት ‘እንዲመጣ’ ስንጸልይ የአምላክ መንግሥት መለኮታዊውን አገዛዝ የሚቃወሙ በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ እንዲያጠፋቸው ልመና ማቅረባችን ነው። አምላክ በቅርቡ እንዲህ የሚያደርግ ሲሆን ይህ ደግሞ መላዋ ምድር ጽድቅ፣ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነባት ገነት እንድትሆን መንገድ ይከፍታል። (መዝ. 72:1-15፤ ዳን. 2:44፤ 2 ጴጥ. 3:13) የይሖዋ ፈቃድ በሰማይ እየተፈጸመ ነው። ፈቃዱ በምድር ላይ እንዲሆን ልመና ስናቀርብ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ እንዲፈጽም መጠየቃችን ነው፤ ይህም በጥንት ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተቃዋሚዎቹን ማጥፋትንም ይጨምራል።—መዝሙር 83:1, 2, 13-18ን አንብብ።
14. “የዕለቱን ምግባችንን” ለማግኘት መጸለያችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
14 “የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን።” (ማቴ. 6:11፤ ሉቃስ 11:3) በጸሎታችን ላይ እንዲህ ዓይነት ልመና ስናቀርብ አምላክ ‘የዕለት’ ጉርሳችንን እንዲሰጠን መጠየቃችን ነው። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በየዕለቱ እንደሚያሟላልን እምነት እንዳለን ያሳያል። ይህን ስንል ይሖዋ የተትረፈረፈ ነገር እንዲሰጠን መጠየቃችን አይደለም። በየዕለቱ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት የምናቀርበው ጸሎት አምላክ፣ እስራኤላውያን “ለዕለት የሚበቃቸውን” መና እንዲሰበስቡ እንዳዘዛቸው እንድናስታውስ ያደርገን ይሆናል።—ዘፀ. 16:4
15. ይሖዋ በደላችንን ይቅር እንዲለን መጠበቅ የምንችለው ምን ካደረግን ነው?
15 ኢየሱስ በሰጠው የናሙና ጸሎት ላይ የተጠቀሰው ቀጣዩ ልመና ከእኛ የሚጠበቅ ነገር እንዳለ ይጠቁማል። ኢየሱስ “የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን” ብሏል። (ማቴ. 6:12) ይሖዋ በደላችንን ይቅር እንዲለን መጠበቅ የምንችለው መጀመሪያ እኛ ራሳችን የበደሉንን ‘ይቅር ካልን’ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 6:14, 15ን አንብብ።) የበደሉንን በነፃ ይቅር ማለት ይኖርብናል።—ኤፌ. 4:32፤ ቆላ. 3:13
16. ይሖዋ ወደ ፈተና እንዳያገባን እንዲሁም ከክፉው እንዲያድነን ስንጸልይ ምን ማለታችን ነው?
16 “ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።” (ማቴ. 6:13) ኢየሱስ ለናሙና በሰጠው ጸሎት ላይ የተጠቀሱት እነዚህ ተዛማጅነት ያላቸው ልመናዎች ምን ትርጉም አላቸው? ይሖዋ፣ ኃጢአት እንድንሠራ እንደማይፈትነን የታወቀ ነው። (ያዕቆብ 1:13ን አንብብ።) ዋነኛው የሰው ልጆች ‘ፈታኝ’ ‘ክፉው’ ሰይጣን ነው። (ማቴ. 4:3) ይሁንና አምላክ አንዳንድ ነገሮች እንዲፈጸሙ ስለፈቀደ ብቻ እሱ ራሱ እንዳከናወናቸው ተደርጎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። (ሩት 1:20, 21፤ መክ. 11:5) ስለሆነም “ወደ ፈተና አታግባን” ብለን ስንጸልይ የይሖዋን ትእዛዝ እንድንጥስ በምንፈተንበት ጊዜ በፈተናው እንድንሸነፍ ይሖዋ እንዳይፈቅድ መለመናችን ነው። “ከክፉው አድነን” የሚለውን ልመና ስናቀርብ ሰይጣን እንዲያሸንፈን ይሖዋ እንዳይፈቅድ መጠየቃችን ነው። ደግሞም አምላክ ‘ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ።
‘ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ደጋግማችሁ አንኳኩ’
17, 18. ‘ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ደጋግማችሁ አንኳኩ’ የሚለው መመሪያ ምን ትርጉም አለው?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “በጽናት ጸልዩ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 12:12) ኢየሱስም ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።” (ማቴ. 7:7, 8) ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም ነገር ‘ደጋግመን መለመናችን’ ተገቢ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስም ኢየሱስ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር በመስማማት የሚከተለውን ሐሳብ ጽፏል፦ “[በአምላክ] ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”—1 ዮሐ. 5:14
18 ‘ደጋግማችሁ ለምኑ እንዲሁም ሳታቋርጡ ፈልጉ’ የሚለው የኢየሱስ ምክር ለጸሎታችን ወዲያውኑ መልስ ባናገኝም እንኳ ተስፋ ሳንቆርጥ በትጋት መጸለይ እንዳለብን ያሳያል። ከዚህም በላይ ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት እንዲሁም ይህ መንግሥት ለሰው ልጆች ከሚያመጣቸው በረከቶች፣ ጥቅሞችና ሽልማቶች ተቋዳሽ ለመሆን እንድንችል ‘ደጋግመን ማንኳኳት’ ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ አምላክ ለምናቀርበው ጸሎት ምላሽ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ለይሖዋ ታማኝ ከሆንን ለጸሎታችን መልስ እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም ክርስቶስ “የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል” ብሏል። የይሖዋ አገልጋዮች ያጋጠሟቸው በርካታ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት አምላክ በእርግጥም ‘ጸሎትን ይሰማል።’—መዝ. 65:2
19, 20. በማቴዎስ 7:9-11 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ አንጻር ይሖዋ አፍቃሪ ከሆነ አባት ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው?
19 ኢየሱስ፣ አምላክን ለልጆቹ መልካም ነገሮችን ከሚሰጥ አፍቃሪ አባት ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን በሰጠበት ወቅት በቦታው ተገኝተህ የሚከተለውን ሐሳብ ሲናገር እንደሰማህ አድርገህ አስብ፦ “ከመካከላችሁ ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት መልካም ነገር አብልጦ አይሰጣቸውም!”—ማቴ. 7:9-11
20 አንድ ሰብዓዊ አባት ከአዳም በወረሰው ኃጢአት ምክንያት በአንጻራዊ ሁኔታ “ክፉ” ቢሆንም ለልጁ ፍቅር አለው። ለልጁ “መልካም ስጦታ” ለመስጠት ይጥራል እንጂ አያታልለውም። በሰማይ ያለው አፍቃሪ አባታችን እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለሚመለከተን እንደ መንፈስ ቅዱስ ያሉ ‘መልካም ነገሮችን’ ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:13) ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን በሚያስደስተው መንገድ ማገልገል እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ብርታት ይሰጠናል።—ያዕ. 1:17
ከኢየሱስ ትምህርቶች ጥቅም ማግኘታችሁን ቀጥሉ
21, 22. የተራራው ስብከት አስደናቂ ነው የምንለው ለምንድን ነው? አንተስ ኢየሱስ ስለሰጣቸው ትምህርቶች ምን ይሰማሃል?
21 በእርግጥም የተራራው ስብከት እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከተሰጡ ንግግሮች ሁሉ የላቀ ነው። መንፈሳዊ ቁም ነገሮችን ግልጽ በሆነ መንገድ በማቅረብ ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። በእነዚህ ተከታታይ የጥናት ርዕሶች ላይ ከተራራው ስብከት የተወሰዱ አንዳንድ ነጥቦችን ተመልክተናል፤ ይህም በተራራው ስብከት ላይ የቀረበውን ምክር በተግባር ማዋላችን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝልን አስገንዝቦናል። ኢየሱስ የሰጣቸው እነዚህ ትምህርቶች በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉን ከመሆኑም ሌላ ብሩህ ተስፋ ይፈነጥቁልናል።
22 በእነዚህ ተከታታይ የጥናት ርዕሶች ላይ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ካስተማራቸው ውድ የሆኑ መንፈሳዊ ሀብቶች መካከል የተመለከትነው ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ኢየሱስ ንግግሩን ሲሰጥ ያዳመጡት ሰዎች “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ [መደነቃቸው]” ምንም አያስገርምም! (ማቴ. 7:28) እኛም በእነዚህና ታላቅ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማራቸው በዋጋ የማይተመኑ ሌሎች ትምህርቶች አእምሯችንና ልባችን ሲሞላ በዚያ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች እንደሚሰማን ምንም ጥርጥር የለውም።
መልስህ ምንድን ነው?
• ኢየሱስ ግብዝ የሆኑ ሰዎች ስለሚያቀርቡት ጸሎት ምን ብሏል?
• በምንጸልይበት ጊዜ አንድ ዓይነት ነገር መደጋገም የሌለብን ለምንድን ነው?
• ኢየሱስ የሰጠው የናሙና ጸሎት የትኞቹን ልመናዎች አካትቷል?
• ‘ደጋግመን መለመን፣ ሳናቋርጥ መፈለግ እንዲሁም ደጋግመን ማንኳኳት’ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች እንዲያዩአቸውና እንዲሰሟቸው ብለው የሚጸልዩትን ግብዞች ኢየሱስ አውግዟቸዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዕለት ምግባችንን ለማግኘት መጸለያችን ተገቢ የሆነው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?