በዚያ ዘመን ኖረህ ቢሆን ኖሮ መሲሑን ትቀበለው ነበርን?
ኢየሱስ ክርስቶስ በእስራኤላውያን መካከል የአምላክን ቃል በመስበክ ሦስት ዓመት ተኩል አሳልፏል። ይሁን እንጂ በምድራዊ አገልግሎቱ መደምደሚያ ላይ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ መሲሕ ወይም አምላክ እንደሚመጣ የተናገረለት “ቅቡዕ” መሆኑን ለመቀበል አሻፈረኝ ብለው ነበር። ለምን?
መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው ያልተቀበሉበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ሦስቱ ዛሬም ቢሆን ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የጨበጠውን መሲሐዊ ንግሥና ከመቀበል ወደ ኋላ እንዲሉ አድርገዋቸዋል።
‘ምልክት ማየት እንፈልጋለን’
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን መሲሑን ያልተቀበሉበት አንዱ ምክንያት ስለ እርሱ መሲሕነት የሚናገሩትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምልክቶች ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች ከአምላክ የተላከ መሆኑን ለማረጋገጥ ምልክት እንዲያሳያቸው ይፈልጉ ነበር። ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ 12:38 ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ፣ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን” እንዳሉ ይናገራል። ኢየሱስ ከዚያ ቀደም ምልክት አሳይቷቸው አልነበረምን? አዎን! አሳይቷቸዋል።
ይህን ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት ኢየሱስ ብዙ ተዓምራት አድርጎ ነበር። ውኃ ወደ ወይን ለውጧል፣ በጠና ታሞ የነበረ አንድ ብላቴና ፈውሷል፣ ታምማ የነበረችውን የጴጥሮስን አማት ፈውሷል፣ የሥጋ ደዌ የነበረበትን ሰው ከደዌ አንጽቶታል፣ ሽባ የነበረው ሰውዬ በእግሮቹ እንዲራመድ አድርጓል፣ ለ38 ዓመታት ታምሞ ሲሰቃይ የነበረው ሰው ጤንነቱ እንዲመለስለት አድርጓል፣ እጁ የሰለለችበትን ሰው ፈውሷል፣ ብዙ ሰዎችን ከሚማቅቁበት በሽታ አላቅቋል፣ የአንድን የጦር መኮንን አገልጋይ ፈውሷል፣ የአንዲትን መበለት ልጅ ከሞት አስነሥቷል እንዲሁም ዓይነ ስውርና ድዳ የነበረውንም ሰው አድኗል። እነዚህ ተዓምራት የተደረጉት በቃና፣ በቅፍርናሆም፣ በኢየሩሳሌምና በናይን ነበር። ከዚህም በላይ ስለ እነዚህ ተዓምራት ዜናው በይሁዳና በአካባቢው አገሮች ሁሉ ተሠራጭቶ ነበር።—ዮሐንስ 2:1-12፤ 4:46-54፤ ማቴዎስ 8:14-17፤ 8:1-4፤ 9:1-8፤ ዮሐንስ 5:1-9፤ ማቴዎስ 12:9-14፤ ማርቆስ 3:7-12፤ ሉቃስ 7:1-10፤ 7:11-17፤ ማቴዎስ 12:22
በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ምልክቶች አላነሱም። በሕዝቡ ፊት ይህን ያህል ብዙ ምልክቶችን ቢያደርግም በእርሱ አላመኑም። ኢየሱስ ከአምላክ እንደተላከ የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች እያዩ መሲሕ መሆኑን ያልተቀበሉት በመንፈሳዊ የታወሩ ሰዎች ነበሩ። ልባቸው ለእውነት የጠጠረና ደንዳና ነበር።—ዮሐንስ 12:37-41
ዛሬስ? አንዳንድ ሰዎች “እኔ የማምነው በዓይኔ ያየሁትን ነገር ብቻ ነው” ይላሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጋቸው በእርግጥ ጥበብ ነውን? ኢየሱስ በአሁኑ ወቅት ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በመሲሐዊ መንግሥቱ መንበረ ሥልጣኑን እንደጨበጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያመለክታሉ። እርሱ በዓይን የማይታይ በመሆኑ በመግዛት ላይ እንደሚገኝ እንድናስተውል የሚረዳ ምልክት ያስፈልገናል፤ ይህ ምልክት የዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀን መጀመሩን የሚያመለክት ይሆናል። ምልክቱ በመታየት ላይ መሆኑን ታምናለህን?—ማቴዎስ 24:3 አዓት
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ክርስቶስ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ተለይቶ የሚታወቀው በወቅቱ በሚኖረው ጦርነት፣ የምድር መናወጥ፣ የምግብ እጥረትና ታይቶ በማይታወቅ መጠን በሚከሰት ቸነፈር ነው። ‘በመጨረሻው ቀን’ ሰዎች እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት ራስ ወዳዶች፣ ስግብግቦች እና ራሳቸውን የማይገዙ ይሆናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:6, 7፤ ሉቃስ 21:10, 11) ከዘመን ስሌት በተጨማሪ የመሲሑ ግዛት በ1914 መጀመሩን የሚጠቁሙ ከ20 የሚበልጡ የተለያዩ የመጨረሻው ቀን ገጽታዎች አሉ።—የመጋቢት 1, 1993ን መጠበቂያ ግንብ ገጽ 5ን ተመልከት።
“ገንዘብንም የሚወዱ”
አይሁዳውያን ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው ሳይቀበሉ የቀሩበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ፍቅረ ነዋይ ነበር። ብዙዎቹ ለሃብት ከፍተኛ ቦታ መስጠታቸው ኢየሱስን እንዳይከተሉ እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ፈሪሳውያን ‘በገንዘብ ወዳድነታቸው’ የታወቁ ነበሩ። (ሉቃስ 16:14) ወደ ኢየሱስ መጥቶ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የጠየቀውን የአንድ ወጣት ባለጠጋ መኮንን ሁኔታ ተመልከት። የኢየሱስ ምላሽ “ትእዛዛትን ጠብቅ” የሚል ነበር። ወጣቱ ሰው አንዳንድ ሕጎችን ከመጠበቅ በተጨማሪ ሌላም ነገር እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ ሳይሆን አይቀርም “ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፣ ደግሞስ የሚጎድለኝ ምንድር ነው?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስ “ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፣ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ” አለው። የመሲሑ ደቀ መዝሙር የመሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት አግኝቶ ነበር! ይሁንና መኮንኑ እያዘነ ሄደ። ለምን? ምክንያቱም ለእርሱ ከሰማያዊ መዝገብ ይልቅ በምድር ያለው መዝገብ ይበልጥበት ነበር።—ማቴዎስ 19:16-22 አዓት
ዛሬም ሁኔታው አልተለወጠም። የመሲሐዊው ንጉሥ እውነተኛ ተከታይ መሆን ምድራዊ ንብረትን ጨምሮ ከማንኛውም ነገር በፊት ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትን ይጠይቃል። ፍቅረ ነዋይ የተጠናወተው አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች ይህ በጣም ፈታኝ ነው። ለምሳሌ በአንድ ምሥራቃዊ አገር የሚያገለግሉ ሚስዮናዊ ባልና ሚስት ከአንዲት ሴት ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይወያያሉ። እነዚህ ባልና ሚስት ሴትዮዋ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተጨማሪ ነገሮችን ለመማር ትፈልጋለች ብለው ስላሰቡ የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት እንድትወስድ ጋበዟት። የሰጠችው ምላሽ ምን ነበር? “እነዚህ መጽሔቶች ብዙ ገንዘብ እንዳገኝ ይረዱኛል?” ስትል ጠየቀች። ሴትዮዋ ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ይበልጥ ወደ ቁሳዊ ነገሮች አዘንብላ ነበር።
እነዚሁ ባልና ሚስት በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረን አንድ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑ ነበር። ወላጆቹ ግን “ጊዜህን እያጠፋህ ነው። ማታ ማታ ሌላ ሥራ ይዘህ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት አለብህ” ይሉታል። ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ መሲሐዊው ንጉሥ ከመማር ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን እንዲያስቀድሙ ሲያበረታቱ ማየት በጣም ያሳዝናል! አንድ የቻይናውያን ብሂል “ንጉሡ ምን ሀብታም ቢሆኑ የአሥር ሺህ ዓመት ዕድሜ አይገዙ” ይላል።
ብዙዎች ስለ መሲሐዊው ንጉሥ መማርና እርሱን መከተል ለፍቅረ ነዋይ ቦታ እንደሌለው ተገንዝበዋል። ብዙ ብር የሚያስገኝ የራሷ ንግድ የነበራት አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ገንዘብ ማግኘት በጣም የሚያስደስት ቢሆንም የግድ አስፈላጊ አይደለም። አንድን ሰው ደስተኛ የሚያደርገው ገንዘብ አይደለም።” በአሁኑ ጊዜ ይህች ምሥክር በአውሮፓ በሚገኝ አንድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆና በማገልገል ላይ ነች።
‘አይሁዳውያንን መፍራት’
አይሁዳውያን ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው ያልተቀበሉበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ሰውን መፍራት ነበር። የእርሱን መሲሕነት በግልጽ መናገር ማለት በሌሎች ዘንድ የነበራቸውን ግምት የሚያሳጣ ነበር። አንዳንዶች ይህ ሊከፈል የማይገባው ትልቅ መሥዋዕትነት እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ሳንሄድሪን በመባል የሚታወቀው የአይሁዳውያን ከፍተኛ ሸንጎ አባል የነበረውን የኒቆዲሞስን ሁኔታ ተመልከት። ኢየሱስ ባደረጋቸው ምልክቶችና ባስተማራቸው ትምህርቶች በጣም ተነክቶ ስለ ነበር እንዲህ ብሏል፦ “መምህር ሆይ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን።” ይሁን እንጂ ኒቆዲሞስ ወደ ኢየሱስ ይመጣ የነበረው ጨለማን ተገን አድርጎ ነበር፤ ምናልባት በጨለማ የሚመጣው ሌሎች አይሁዳውያን ማንነቱን እንዳያዩት ብሎ ሳይሆን አይቀርም።—ዮሐንስ 3:1, 2
ኢየሱስ ሲናገር ከሰሙት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት ይልቅ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትን ያስበልጡ ነበር። (ዮሐንስ 5:44) ኢየሱስ በ32 እዘአ ለዳስ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ “ሕዝቡም ስለ እርሱ በሹክሹክታ ይነጋገሩ ነበረ።” ይሁን እንጂ “አይሁዳውያን ባለ ሥልጣኖችን በመፍራት ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አልተናገረም።” (ዮሐንስ 7:10-13 የ1980 ትርጉም፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን። ) ኢየሱስ ዓይኑን ያበራለት ሰው ወላጆች እንኳ ተዓምሩን ያደረገው የአምላክ ወኪል መሆኑን ለመናገር አልፈቀዱም። እነርሱም ቢሆኑ ‘አይሁዳውያንን ፈርተው’ ነበር።—ዮሐንስ 9:13-23
ዛሬም አንዳንዶች ኢየሱስ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በሰማይ በመግዛት ላይ እንዳለ ቢያውቁም ይህንን በይፋ ለመናገር ይፈራሉ። ለእነርሱ በሌሎች ዘንድ ያላቸውን ግምት ማጣት ሊከፍሉት የማይፈልጉት ትልቅ መሥዋዕት ነው። ለምሳሌ ያህል በጀርመን ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከአንድ ሰው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ሲያደርግ ሰውዬው እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምትሰብኩት ነገር እውነት ነው። ግን እኔ ዛሬ የይሖዋ ምሥክር ብሆን ነገ ሁሉም ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ይሰማል። የሥራ ባልደረቦቼ፣ ጎረቤቶቼ እንዲሁም እኔና ቤተሰቤ ያለንበት ማኅበር አባላት ምን ይሉኛል? ይህን ልቋቋመው አልችልም።”
ሰውን የመፍራት መንስኤ ምንድን ነው? ኩራት፣ በቤተሰብና በወዳጆች ዘንድ ተወዳጅ የመሆን ፍላጎት፣ የሌሎችን ፌዝና ማላገጥ መፍራት፣ ከአብዛኛው ሰው የተለዩ መሆንን መፍራት ነው። በተለይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ለጀመሩ ሰዎች እንደነዚህ ያሉት ስሜቶች ፈተና ይሆኑባቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሴት መሲሐዊው መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ አማካኝነት በምድር ላይ ገነትን እንደሚያቋቁም ስትሰማ በጣም ደስ አላት። ይሁን እንጂ ዋነኛ የዲስኮ ክለብ አሳዳጅ ስለነበረች ሰውን መፍራት ስለዚህ ተስፋ ለሌሎች እንዳትናገር ጋሬጣ ሆኖባት ነበር። በመጨረሻ በግልጽ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመናገር የሚያስችል ድፍረት አገኘች። የዲስኮ ክለብ ጓደኞቿ ቢያገልሏትም ባሏና ወላጆቿ ስለ እውነት ለማወቅ ፍላጎት አሳዩ። በመጨረሻ እርሷና እናቷ ሲጠመቁ ባሏና አባቷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። የነበረባትን ሰውን የመፍራት ዝንባሌ በማሸነፏ ምንኛ ተክሳለች!
በእርግጥ መሲሑን ትቀበላለህን?
ኢየሱስ በመከራ እንጨት ተሰቅሎ ሊሞት በሚያጣጥርበት ወቅት አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርት በቦታው ተገኝተው ነበር። በትንቢት የተነገረለት መሲሕ እርሱ መሆኑን ተቀብለው ነበር። ከእነርሱ ሌላ የአይሁድ መኳንንት ተገኝተው የነበረ ሲሆን በዚያን ጊዜም ቢሆን ምልክት ይፈልጉ የነበረ ይመስላል። “ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ [ወይም መሲሕ] ከሆነ፣ ራሱን ያድን።” (ሉቃስ 23:35) እነዚህ ሰዎች ምልክት መጠየቃቸውን አያቆሙምን? ኢየሱስ በርካታ ተዓምራትን አሳይቷል። ከዚህም በላይ በአወላለዱ፣ በአገልግሎቱ፣ በደረሰበት ፈተና፣ በሞቱና በትንሣኤው አማካኝነት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።—ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” የሚለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ገጽ 343-4ን ተመልከት።
ያለፉ ያገደሙት ሁሉ ያሳያቸውን መሲሕነቱን የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች ችላ ብለው ኢየሱስን ይሰድቡት ነበር። (ማቴዎስ 27:39, 40) ወታደሮቹ ቁሳዊ አስተሳሰብ ተጠናውቷቸው ስለነበር የኢየሱስን ልብስ እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቡም ላይ እጣ ተጣጣሉበት። (ዮሐንስ 19:23, 24) አንዳንዶቹ ደግሞ የሰው ፍርሃት እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የሳንሄድሪን አባል የነበረውን የአርማቲያሱን የዮሴፍን ሁኔታ ተመልከት። “አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር” ነበር። ከመሲሑ ሞት በኋላ ለኢየሱስ አስከሬን የሚያስፈልገውን ሁሉ ያደረጉለት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ናቸው። ስለዚህ ዮሴፍ የነበረበትን የሰው ፍርሃት አሸንፎ ነበር።—ዮሐንስ 19:38-40
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኖረህ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገህ ትቀበለው ነበርን? ይህን ማድረግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን መቀበልን፣ ፍቅረ ነዋይን ማሸነፍን እንዲሁም ለሰው ፍራቻ አለመንበርከክን ይጠይቅብህ ነበር። በዚህ የመጨረሻ ዘመንም እያንዳንዳችን እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ መሲሐዊ ንጉሥ እንደሆነ እቀበላለሁን?’ ምድርን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንደሆነ አድርገው ከልባቸው ከተቀበሉት ሰዎች መካከል ትገኝ ይሆን?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢየሱስ መሲሐዊ ንጉሥ መሆኑን የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች ቸል አትበል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ መሲሑ መማር ብዙውን ጊዜ ሰዎች ምን ይሉኝ ይሆን የሚለውን ፍራቻ ማሸነፍን ይጠይቃል