ምዕራፍ 42
ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ገሠጻቸው
ማቴዎስ 12:33-50 ማርቆስ 3:31-35 ሉቃስ 8:19-21
ኢየሱስ ስለ “ዮናስ ምልክት” ተናገረ
ደቀ መዛሙርቱን ከቤተሰቡ ይበልጥ ያቀርባቸዋል
አንዳንድ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስ አጋንንትን ያስወጣው በአምላክ ኃይል መሆኑን መቀበል አለመፈለጋቸው መንፈስ ቅዱስን እንደ መሳደብ ነው። ታዲያ ከማን ወገን ይቆሙ ይሆን? ከአምላክ ወይስ ከሰይጣን? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “መልካም ዛፍ ካላችሁ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ካላችሁ ደግሞ የበሰበሰ ፍሬ ያፈራል፤ ዛፍ የሚታወቀው በፍሬው ነውና።”—ማቴዎስ 12:33
ኢየሱስ አጋንንትን በማስወጣት መልካም ፍሬ ማፍራት የቻለው ሰይጣንን ስለሚያገለግል ነው ብሎ መወንጀል ሞኝነት ነው። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ በግልጽ እንደተናገረው መልካም ፍሬ የሚገኘው ከመልካም እንጂ ከበሰበሰ ዛፍ አይደለም። ታዲያ ፈሪሳውያን ያፈሩት ፍሬ ይኸውም በኢየሱስ ላይ የሰነዘሩት መሠረተ ቢስ ክስ ምን ያሳያል? የበሰበሱ እንደሆኑ ይጠቁማል። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ እንዴት መልካም ነገር ልትናገሩ ትችላላችሁ? አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነውና።”—ማቴዎስ 7:16, 17፤ 12:34
በእርግጥም የምንናገራቸው ቃላት የልባችንን ሁኔታ የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ፍርድ ለመስጠት መሠረት ይሆናሉ። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፣ ሰዎች ለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል፤ ከቃልህ የተነሳ ጻድቅ ትባላለህና፤ ከቃልህም የተነሳ ትኮነናለህ።”—ማቴዎስ 12:36, 37
ኢየሱስ ብዙ ተአምራዊ ሥራዎችን ያከናወነ ቢሆንም ጸሐፍትና ፈሪሳውያን “መምህር፣ ምልክት እንድታሳየን እንፈልጋለን” በማለት ተጨማሪ ነገር እንዲያሳያቸው ጠየቁት። ኢየሱስ ተአምራቱን ሲፈጽም እነዚህ ሰዎች አዩም አላዩ፣ ያከናወናቸውን ነገሮች የተመለከቱ ብዙ የዓይን ምሥክሮች አሉ። በመሆኑም ኢየሱስ እነዚህን የአይሁድ መሪዎች እንዲህ አላቸው፦ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም።”—ማቴዎስ 12:38, 39
ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ ሲያብራራ “ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ ሁሉ የሰው ልጅም በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል” አለ። ዮናስን አንድ ትልቅ ዓሣ የዋጠው ሲሆን ከዓሣው ሆድ ሲወጣ ከሞት የተነሳ ያህል ነበር። ኢየሱስ ይህን ሲል እሱ ራሱ እንደሚሞትና በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ አስቀድሞ መናገሩ ነው። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ፣ የአይሁድ መሪዎች ንስሐ ለመግባትና ለመለወጥ ፈቃደኞች ባለመሆን ‘የዮናስን ምልክት’ እንደማይቀበሉ አሳይተዋል። (ማቴዎስ 27:63-66፤ 28:12-15) በአንጻሩ ግን “የነነዌ ሰዎች” ዮናስ ከሰበከላቸው በኋላ ንስሐ ገብተዋል። በመሆኑም ይህን ትውልድ ይኮንኑታል። ኢየሱስ፣ የሳባ ንግሥት የተወችው ምሳሌም እነዚህን ሰዎች እንደሚኮንናቸው ተናግሯል። የሳባ ንግሥት፣ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ፍላጎት ያሳየች ከመሆኑም ሌላ በጥበቡ ተደንቃለች። ኢየሱስ “ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ” በማለት ተናገረ።—ማቴዎስ 12:40-42
ኢየሱስ የዚህን ትውልድ ሁኔታ ርኩስ መንፈስ ከወጣለት ሰው ጋር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 12:45) ሰውየው ባዶውን ቦታ በመልካም ነገሮች ስላልሞላው ክፉው መንፈስ ከእሱ የባሱ ሌሎች ሰባት መናፍስትን ይዞ መጣና ሰውየው ላይ አብረው ሰፈሩበት። ርኩሱ መንፈስ እንደወጣለት ሰው ሁሉ፣ የእስራኤል ብሔርም ጸድቶና አንዳንድ ለውጦችን አድርጎ ነበር። ሆኖም ብሔሩ የአምላክን ነቢያት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፤ በመጨረሻም የአምላክ መንፈስ እንዳለበት በግልጽ የሚታየውን ኢየሱስን ተቃወመ። ይህም ብሔሩ መጀመሪያ ከነበረው የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ነው።
ኢየሱስ እየተናገረ ሳለ እናቱና ወንድሞቹ መጥተው በተሰበሰበው ሕዝብ ዳር ቆሙ። አጠገቡ ከተቀመጡት አንዳንዶቹ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያገኙህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንደ ወንድሞቹ፣ እህቶቹና እናቶቹ የሆኑትን ደቀ መዛሙርቱን ምን ያህል እንደሚቀርባቸው አሳየ። እጁን ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ “እናቴና ወንድሞቼ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው” አለ። (ሉቃስ 8:20, 21) ይህን በማለት ኢየሱስ ከቤተሰቡ ጋር ያለው ቅርበት ምንም ያህል የጠበቀ ቢሆን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ላለው ግንኙነት የበለጠ ቦታ እንደሚሰጥ አሳይቷል። እኛም በተለይ ሌሎች ሲጠራጠሩን ወይም እኛንም ሆነ መልካም ሥራችንን ሲነቅፉ ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ጋር እንዲህ ያለ ቅርበት ካለን ምንኛ እንበረታታለን!