የክርስቶስ መለወጥ እንዴት እንደሚነካህ
አራት ሰዎች ወደ አንድ ረጅም ተራራ ላይ ገና መውጣታቸው ነበር። በእነዚያ ከፍታዎች ላይ አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጸመ። ሦስቱ የተደናገጡ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ሲመለከቱት ሳሉ በዓይናቸው ፊት ተለወጠ። የወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ ይህን አስደናቂ ሁኔታ ሲዘግብ አዳምጥ፦
“ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረዥም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፣ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን መምህር ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው። እጅግም ስለፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፣ ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ። ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም።”—ማርቆስ 9:2-8
እስቲ አስበው! የኢየሱስ ፊት እንደ ጸሐይ ያበራ ነበር። (ማቴዎስ 17:2) ልብሶቹም ያንጸባርቁ ነበር። “አጣቢ በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል ነጭ ሆነ።” የአምላክ የራሱ ኃይለኛ ድምጽ ስለልጁ ተናገረ። ምን ዓይነት አስደናቂ ሁኔታ ነበር!
እዚህ ላይ “ተለወጠ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል “ወደሌላ መልክ መለወጥ” ማለት ነው። ክርስቲያኖች “በልባቸው መታደስ እንዲለወጡ” በተመከሩበት በሮሜ 12:2 ላይም ይህ ግስ ተሠርቶበታል።—እንደ ኤክስፖሲተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ በደብልዩ ኢ ቫይን የተጻፈ ጥራዝ 9 ገጽ 148
አዎን በ32 እዘአ የማለፍ በዓል ከተከበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሲለወጥ አንድ አስደናቂ ሁኔታ ተፈጸመ። ወደዚህ ተአምር የመራው ምን ነበር? ልዩ ዓላማ አለውን? ሙሴና ኤልያስ ጣልቃ የገቡትስ ለምን ነበር? የክርስቶስ መለወጥ አንተን የሚነካህስ እንዴት ነው?
ከዚያ በፊት የተፈጸሙ ሁኔታዎች
ወደ ተራራው ከመውጣታቸው በፊት ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ በቂሣርያ ፊሊጶስ አቅራቢያ ነበሩ። ይህች ከተማ ከሄርሞን (አርሞንኤም) ተራራ ወደ ደቡብ ምሥራቅ 24 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ስለምትገኝ መለወጡ የተፈጸመው ምናልባት በጣም ረጅም በሆነው በሄርሞን ተራራ ከፍታ ላይ ሊሆን ይችላል።
ወደ ረጅሙ ተራራ ሲወጡ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን “ሰዎች እኔ ማን እንደሆንሁ ይላሉ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነሱም “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ” ብለው መለሱ። ከዚያም ኢየሱስ “እናንተስ እኔ ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ያኔ ኢየሱስ ይህን “ለማንም እንዳይነግሩ በጥብቅ አዘዛቸው። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንደሚገባው ያስተምራቸው ጀመር።”—ማርቆስ 8:27-31
ኢየሱስ ቀጥሎ ይህን ተስፋ ሰጠ፦ “በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ።” (ማርቆስ 9:1፤ ማቴዎስ 16:28) ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ሲጸልይ ሳለና በጴጥሮስ፣ በያዕቆብና በዮሐንስ ፊት በተለወጠ ጊዜ ይህ ተስፋ ተፈጸመ። ሉቃስ ይህ የሆነው “ስምንት ቀን ያህል ቆይቶ” ነው ይላል። በግልጽ እንደሚታየውም ተስፋው የተሰጠበትንና የተፈጸመበትን ቀን ጨምሮ ስለነበረ ነው።—ማቴዎስ 17:1, 2፤ ማርቆስ 9:2፤ ሉቃስ 9:28
ሕልም ወይም እውን ያልሆነ ነገር አልነበረም
የኢየሱስ መለወጥ ሕልም አልነበረም። ሦስቱም ሐዋርያት አንድ ዓይነት ሕልም ሊያልሙ አይችሉም። ኢየሱስ “ራእይ” ብሎ ጠርቶታል። ይህ ደግሞ ሊሆን የማይችል ነገር የሚያመለክት ቃል አይደለም። ምክንያቱም በማቴዎስ 17:9 ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል በሌላ ቦታ “ትርኢት” ተብሎ ተተርጉሟል። (ሥራ 7:31) ስለዚህ ተመልካቾቹ ሙሉ በሙሉ ንቁዎች ነበሩ፤ ወይም እንቅልፍ አልወሰዳቸውም ነበር። እየተፈጸመ የነበረውንም ነገር በዓይኖቻቸውና በጆሮዎቻቸው አይተዋል፣ ሰምተዋል።—ሉቃስ 9:32
ሙሉ በሙሉ ንቁ ቢሆንም የሚናገረው ጠፍቶት የነበረው ጴጥሮስ ሦስት ዳሶች ማለት ለኢየሱስ፣ ለሙሴና ለኤልያስ ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ ዳስ እንዲሠሩ ሐሳብ አቀረበ። (ሉቃስ 9:33) ጴጥሮስ ሲናገር የጋረደው ዳመና እሥራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ በመገናኛው ድንኳን ላይ ይታይ እንደነበረው የአምላክን መገኘት የሚያመለክት ነበር። (ዘፀአት 40:34-38፤ ሉቃስ 9:34) በእርግጥም ሐዋርያቱ “እግዚአብሔር አብ” “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፣ እሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር ተኝተው ሊሆን አይችልም ነበር።—2 ጴጥሮስ 1:17, 18፤ ሉቃስ 9:35
ሙሴ ለምን እንደታየ
መለወጡ በሆነበት ጊዜ ሙሴ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ሞቶ ስለነበር “ምንም አያውቅም” ነበር። (መክብብ 9:5, 10) እንደ ዳዊት እሱም ገና ትንሣኤ አላገኘም ነበርና በአካል ሊገኝ አይችልም ነበር። (ሥራ 2:29-31) ታዲያ በራእይ ላይ ሙሴ ከክርስቶስ ጋር የታየው ለምን ነበር?
አምላክ ለሙሴ “ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሳላቸዋለሁ። ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ። ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል” ብሎ ነግሮት ነበር። (ዘዳግም 18:18) ጴጥሮስ ይህንኑ ትንቢት ጠቅሶ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አውሎታል። (ሥራ 3:20-23) ከኢየሱስ ሌላ ወደ እሥራኤል ሕዝብ ከተላኩት ነቢያት ሁሉ የበለጠ ታላቅ ነቢይ የነበረው ሙሴ ነበር።
በሙሴና ታላቁ ሙሴ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ መሃል ተመሳሳይነት አለ። ለምሳሌ ያህል ገና ጨቅላ ሕፃናት ሳሉ የሁለቱም ሕይወት በአምባ ገነን ገዥዎች አደጋ ላይ ወድቆ ነበር፤ አምላክ ግን ሕፃናቱ እንዲድኑ አድርጎአል። (ዘፀአት 1:20–2:10፤ ማቴዎስ 2:7-23) ሁለቱም የይሖዋ ልዩ አገልጋዮች የመሆን ሥራቸውን ሊጀምሩ ሲሉ አርባ ቀናት ጾመዋል። (ዘፀአት 24:18፤ 34:28፤ ዘዳግም 9:18, 25፤ ማቴዎስ 4:1, 2) ሁለቱም ሙሴና ኢየሱስ በአምላክ ኃይል ተአምራትን አድርገዋል።—ዘፀአት 14:21-31፤ 16:11-36፤ መዝሙር 78:12-54፤ ማርቆስ 4:41፤ ሉቃስ 7:18-23፤ ዮሐንስ 14:11
አምላክ ሙሴን እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ እንዲያወጣ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስም መንፈሳዊ ነፃነት የሚያመጣ ሆኖአል። (ዘፀአት 12:37–14:31፤ ዮሐንስ 8:31, 32) ሙሴ በአምላክና በእሥራኤል መካከል ለነበረው የሕግ ቃል ኪዳን መካከለኛ የመሆን መብት ያገኘ ሲሆን ኢየሱስ የአዲሱ ኪዳን መካከለኛ ነው። (ዘፀአት 19:3-9፤ 34:3-7፤ ኤርምያስ 31:31-34፤ ሉቃስ 22:20፤ ዕብራውያን 8:3-6፤ 9:15) ኢየሱስ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ እንዳደረገው ሁሉ ሙሴንም አምላክ በእሥራኤላውያን፣ በግብጻውያንና በሌሎች ፊት ለራሱ ስም ያደርግ ዘንድ ተጠቅሞበታል። (ዘፀአት 9:13-17፤ 1 ሳሙኤል 6:6፤ ዮሐንስ 12:28-30፤ 17:5, 6, 25, 26) ሙሴ ከተለወጠው ኢየሱስ ጋር እንዲታይ በማድረግ ኢየሱስ በጣም ከፍ ባለ መጠን በዚህ ሥልጣንም እንደሚያገለግል አምላክ ማሳየቱ ነበር።
ኤልያስ ለምን እንደታየ
የሞተው ነቢይ ኤልያስ ከሙታን ያልተነሣ ቢሆንም በመለወጡ ራእይ ላይ መታየቱ ተገቢ ነበር። ኤልያስ ንጹሕ አምልኰን በመመለስና በእሥራኤላውያን መካከል የይሖዋን ስም በማስቀደስ ታላቅ ሥራ ሠርቷል። ኢየሱስ ክርስቶስም በምድር ሳለ እንደዚያው አድርጓል፤ ለወደፊቱም በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ንጹሕ አምልኰን ለመመለስና ሰማያዊ አባቱን ለመደገፍ ገና የበለጠ ያደርጋል።
ነቢዩ ሚልክያስ የኤልያስ ሥራ ወደፊት ለሚመጣ ሥራ ጥላ የነበረ መሆኑን ገልጿል። በሚልክያስ በኩል አምላክ እንዲህ አለ፦ “እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው [የይሖዋ (አዓት)] ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።”—ሚልክያስ 4:5, 6
ይህ ትንቢት አነስተኛ ፍጻሜውን በዮሐንስ መጥምቁ ሥራ አግኝቷል። ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስን ከመለወጡ በኋላ ጸሐፍት መሲሕ ከመምጣቱ በፊት ኤልያስ መምጣት አለበት ለምን እንዳሉ ሲጠይቁት ኤልያስን በሚመለከት የተናገረው ትንቢት እንደተፈጸመ አመልክቷል። እንዲህ አለ፦ “ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያቀናል። ነገር ግን እላችኋለሁ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ስለ ዮሐንስ መጥምቁ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ።”—ማቴዎስ 17:10-13
ዮሐንስ በሕጉ ቃል ኪዳን ላይ በሠሩት ኃጢአት ንስሐ የገቡትን አይሁድ ባጠመቀ ጊዜ የኤልያስ ዓይነት ሥራ ሠርቷል። ከሁሉ በላይ ዮሐንስ የመሲሑ ቀደምት በመሆን ኢየሱስን አስተዋውቋል። (ማቴዎስ 11:11-15፤ ሉቃስ 1:11-17፤ ዮሐንስ 1:29) ነገር ግን የዮሐንስ ሥራ የሚልክያስ ትንቢት አነስተኛ ፍጻሜ የሆነው ለምንድነው?
በዚህ ራእይ ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገር ታይቷል። ይህም የሆነው ከዮሐንስ መጥምቁ ሞት በኋላ ስለሆነ የኤልያስ ዓይነቱ ሥራ ለወደፊቱም እንደሚሠራ ያመለክታል። ከዚህም በላይ ይህ ሥራ የሚከናወነው “ታላቁና የሚያስፈራው [የይሖዋ (አዓት)] ቀን ሳይመጣ” በፊቱ እንደሚሆን ትንቢቱ አመልክቷል። ያ በፍጥነት እየቀረበ ያለው ሁኔታ በአርማጌዶን የሚሆነውን “ታላቁንና ሁሉን በሚችለው በእግዚአብሔር ቀን የሚሆነውን ጦርነት” ያጠቃልላል። (ራእይ 16:14-16) ይህ ማለት በዚያ ጊዜ ገና ወደፊት የሚመጣ የነበረው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት መቋቋም ከመፈጸሙ በፊት ከኤልያስና ከተተኪው ከኤልያስ ጋር በሚመሳሰል ሥራ ይቀድማል ማለት ነው። በመሆኑም የይሖዋ ዘመናዊ ምሥክሮች ንጹሕ አምልኰ መመለስንና የአምላክን ስም ከፍ ማድረግን የሚጨምር ሥራ ሲካሄድ ይኸውና ከመቶ ዓመት በላይ ሆኗል።—መዝሙር 145:9-13፤ ማቴዎስ 24:14
ዓላማው
መለወጡ ኢየሱስ ሊቀበለው ለነበረው ስቃይና ሞት አጠንክሮት መሆን አለበት። ሰማያዊ አባቱ የመረጠው (የወደደው) ልጁ እንደሆነ ስለሱ ሲናገር መስማቱ የኢየሱስን እምነት አጠንክሮት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ለውጡ ለሌሎች ምን አድርጎላቸዋል?
የኢየሱስ መለወጥ የተመልካቾቹንም እምነት አጠንክሮላቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ መሆኑ በአእምሮአቸው እንዲሰርጽ አድርጐታል። በእርግጥም የይሖዋ ዋና ቃል አቀባይ የሆነው ቃል በመካከላቸው ስለነበረ የአምላክ የራሱ ድምጽ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲናገር ሰምተውታል። ኢየሱስ ሲጠመቅ ይሖዋ ይህንኑ የመሰለ ምሥክርነቱን የሰጠ ቢሆንም በመለወጡ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ልጁን መስማት እንደነበረባቸው አምላክ ጨምሮ ነገራቸው።—ማቴዎስ 3:13-17፤ 17:5፤ ዮሐንስ 1:1-3, 14
መለወጡ በሌላ መንገድም እምነት አጠንክሮአል። በራእዩ ወቅት ኢየሱስ “ሙሴ” እና “ኤልያስ” “(ክርስቶስ) በኢየሩሳሌም ሊፈጸም ስላለው ስለመውጣቱ (መሄዱ)” ተነጋግረዋል። (ሉቃስ 9:31) “መውጣት” ተብሎ የተተረጐመው ቃል በግሪክኛው ኤክሶደስ ነው። በግልጽ እንደሚታየው ይህ ኤክሶደስ ወይም መውጣት የኢየሱስን መሞትና ወደ መንፈሳዊ ሕይወት አምላክ የሚያስነሳው የመሆኑን ጉዳይ ያጠቃልላል። (1 ጴጥሮስ 3:18) ስለዚህ መለወጡ በክርስቶስ ትንሣኤ ማመንን አጠንክሯል። በተለይ ደግሞ ኢየሱስ የመሲሐዊት መንግሥት ንጉሥ እንደሚሆን አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ እምነትን ገንብቷል። ከዚህም በላይ ራእዩ መንግሥቲቱ ክብራማ እንደምትሆን አመልክቷል።
መገለጡ በቅዱስ ጽሑፋዊ ትንቢት ላይ የሚኖርን እምነትም አጠንክሯል። 32 ዓመታት ካለፉ በኋላ (64 እዘአ ገደማ) ጴጥሮስ ይህን ተሞክሮ አስታውሶ እንዲህ በማለት ጽፎአል፦ “የሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። ከገናናው ክብር፦ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ያ ድምጽ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአል። እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምጽ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኰከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ ሰው በጨለማ ሥፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠበቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።”—2 ጴጥሮስ 1:16-19
ለአንተ ያለው ትርጉም
አዎን፣ ጴጥሮስ የኢየሱስን መለወጥ ለአምላክ ትንቢታዊ ቃል ኃይለኛ ማረጋገጫ አድርጎ ተመልክቶታል። ሐዋርያው ዮሐንስም “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ። አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ብሎ ሲናገር ይህን ራእይ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 1:14) በተመሳሳይም መለወጡ በይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነትህን ሊገነባልህ ይችላል።
መለወጡና ከሱ ጋር የተያያዙት ሁኔታዎች ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅና ተስፋ የተገባው መሲሕ ለመሆኑ እምነትህን ሊያጠነክርልህ ይችላል። ኢየሱስ በመንፈሳዊ ሕላዌ በሰማይ ለመኖር ለመነሣቱ እምነትህን ሊያጠነክርልህ ይችላል። መለወጡ የክርስቶስ ክብርና መንግሥታዊ ኃይል ቅምሻ ስለሆነ ይህ አስደናቂ ራእይ በአምላክ መንግሥት ላይ ያለህን እምነት ሊጨምርልህ ይገባል።
የክርስቶስ መለወጥ በተለይ የኢየሱስ መገኘት እውን የሆነበትን ይህን የእኛን ዘመን የሚያመለክት መሆኑን ማወቅ እምነትን ያጠነክራል። (ማቴዎስ 24:3-14) ከ1914 ጀምሮ በሰማያት በአምላክ የተሾመው ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ነው። አምላክ የሰጠው ሥልጣንና ኃይል በሁሉም የመለኰታዊ አገዛዝ ጠላቶች ላይ በቅርቡ ይገለጣል። ይህም ለአዲስ ዓለም መንገድን ይከፍታል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በኢየሱስ ክርስቶስ መለወጥ በተገለጡት አስደናቂ ነገሮች ላይ እምነት ካሳየህ ዘላለማዊ በረከቱን ታገኛለህ።