በምድር ላይ ለዘላለም መኖር—ክርስቶስ ስለዚህ ተስፋ አስተምሯል?
“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም።”—ራእይ 21:4
1, 2. በአንደኛው መቶ ዘመን የኖሩ በርካታ አይሁዳውያን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንደነበራቸው እንዴት ማወቅ እንችላለን?
ሀብታምና ታዋቂ የሆነ አንድ ወጣት ወደ ኢየሱስ እየሮጠ መጣ፤ ከዚያም በኢየሱስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው። (ማር. 10:17) ይህ ወጣት የዘላለም ሕይወት መውረስ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እየጠየቀ ነበር። ይሁንና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የፈለገው በሰማይ ነው ወይስ በምድር? ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አምላክ ከዘመናት በፊት ለአይሁዳውያን የትንሣኤና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። በአንደኛው መቶ ዘመን የኖሩ አብዛኞቹ አይሁዳውያንም ተመሳሳይ ተስፋ ነበራቸው።
2 የኢየሱስ ወዳጅ የነበረችው ማርታ የሞተውን ወንድሟን በተመለከተ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” ማለቷ ሙታን ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ እንደሚኖሩ ያላትን እምነት መግለጿ ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 11:24) እርግጥ ነው፣ በወቅቱ የነበሩት ሰዱቃውያን በትንሣኤ ተስፋ አያምኑም ነበር። (ማር. 12:18) ጆርጅ ፉት ሙር፣ ጁዳይዝም ኢን ዘ ፈርስት ሴንቸሪስ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ኢራ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በሁለተኛው ወይም በአንደኛው መቶ ዘመን ዓመተ ዓለም የተጻፉ . . . ጽሑፎች፣ በቀድሞ ዘመን የኖሩ ሰዎች ወደፊት አንድ ወቅት ላይ ከሞት ተነስተው እንደገና በምድር ላይ በሕይወት እንደሚኖሩ የሚናገረው እምነት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንደነበረው ያሳያሉ።” ኢየሱስን ቀርቦ ያነጋገረው ሀብታሙ ሰው በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ፈልጎ ነበር።
3. በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሃይማኖቶችና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር ማስተማሩን አይቀበሉም። በርካታ ሰዎች፣ ከሞቱ በኋላ በመንፈሳዊው ዓለም እንደሚኖሩ ተስፋ ያደርጋሉ። በመሆኑም ብዙ ሰዎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲያነቡ ‘የዘላለም ሕይወት’ የሚለውን ሐረግ ባገኙ ቁጥር ይህ አባባል የሚያመለክተው በሰማይ የሚኖረውን ሕይወት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ በእርግጥ እውነት ነው? ኢየሱስ ስለ ዘላለም ሕይወት ሲናገር ለማመልከት የፈለገው ነገር ምንድን ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን እምነት ነበራቸው? የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደፊት በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደሚቻል ያስተምራሉ?
“በዳግም ፍጥረት” ጊዜ የሚገኝ የዘላለም ሕይወት
4. “በዳግም ፍጥረት” ጊዜ ምን ነገር ይከናወናል?
4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ሆነው ምድርን ለመግዛት ትንሣኤ እንደሚያገኙ ያስተምራል። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-3) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለ ዘላለም ሕይወት በተናገረ ቁጥር እየጠቀሰ ያለው ይህ ቡድን ስለሚያገኘው ሕይወት ብቻ አልነበረም። ሀብታም የነበረው ወጣት ያለውን ሁሉ ትቶ የክርስቶስ ተከታይ እንዲሆን የቀረበለትን ግብዣ ሳይቀበል በመቅረት እያዘነ በሄደ ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን እንዳላቸው እንመልከት። (ማቴዎስ 19:28, 29ን አንብብ።) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ” ማለትም በሰማይ እንዲገዙ ከተመረጡት ውጪ ባለው የሰው ዘር ላይ ነገሥታትና ፈራጆች እንዲሆኑ ከሚሾሙት መካከል እንደሚሆኑ ነግሯቸዋል። (1 ቆሮ. 6:2) ኢየሱስ እሱን የሚከተሉ “ሁሉ” ስለሚያገኙት ሽልማትም ተናግሯል። እነዚህም ‘የዘላለም ሕይወት ይወርሳሉ።’ ይህ ሁሉ የሚከናወነው “በዳግም ፍጥረት” ጊዜ ነው።
5. “ዳግም ፍጥረት” ሲባል ምን ማለት ነው?
5 ኢየሱስ “ዳግም ፍጥረት” ሲል ምን ማለቱ ነበር? አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህን አባባል “አዲስ ዓለም” በማለት ተርጉሞታል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል “ሁሉም አዲስ የሚሆንበት ጊዜ” ሲል የተረጎመው ሲሆን ዘ ሆሊ ባይብል—ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ደግሞ “የሁሉ ነገር መታደስ” በማለት ተርጉሞታል። ኢየሱስ “ዳግም ፍጥረት” የሚለውን አባባል ማብራራት ያላስፈለገው መሆኑ አይሁዳውያን ለዘመናት ሲያምኑበት የኖሩትን ተስፋ እየጠቀሰ እንደነበር የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት በኤደን ገነት የነበረውን ሁኔታ እንደገና መልሶ ለማምጣት በምድር ላይ ያሉት ነገሮች ዳግም መፈጠር ይኖርባቸዋል። አምላክ “አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ” በማለት የገባው ቃል በዳግም ፍጥረት ጊዜ ፍጻሜውን ያገኛል።—ኢሳ. 65:17
6. ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች የሚናገረው ምሳሌ የዘላለም ሕይወት ተስፋን በተመለከተ ምን ያስተምረናል?
6 ኢየሱስ የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ አስመልክቶ በሰጠው ንግግር ላይም ስለ ዘላለም ሕይወት ተናግሯል። (ማቴ. 24:1-3) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። ሕዝቦችም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እሱም እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል።” የቅጣት ፍርድ የሚቀበሉት “ወደ ዘላለም ጥፋት ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት “ጻድቃን” የሚያመለክቱት በመንፈስ የተቀቡትን የክርስቶስ ‘ወንድሞች’ በታማኝነት የሚደገፉ ሰዎችን ነው። (ማቴ. 25:31-34, 40, 41, 45, 46) ቅቡዓኑ በሰማይ ባለው መንግሥት እንዲገዙ የተመረጡ በመሆናቸው “ጻድቃን” የተባሉት ሰዎች የዚያ መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች መሆን ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል፦ “[ይሖዋ የሾመው ንጉሥ] ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከታላቁም ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ” ድረስ ተገዢዎች ይኖሩታል። (መዝ. 72:8) ይህ ንጉሥ የሚገዛቸው እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።
የዮሐንስ ወንጌል ምን ይነግረናል?
7, 8. ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ስለ የትኞቹ ሁለት የተለያዩ ተስፋዎች ነግሮታል?
7 በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌሎች ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ላይ ‘የዘላለም ሕይወት’ የሚለውን ሐረግ ተጠቅሟል። ዮሐንስ ደግሞ ኢየሱስ ስለ ዘላለም መኖር የተናገረውን ሐሳብ ወደ 17 ለሚጠጉ ጊዜያት በወንጌል ዘገባው ላይ አስፍሯል። ኢየሱስ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት መውረስን አስመልክቶ ከተናገረባቸው ከእነዚህ አጋጣሚዎች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።
8 እንደ ዮሐንስ ዘገባ ከሆነ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወትን አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ኒቆዲሞስ ከተባለው ፈሪሳዊ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ነው። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ “ማንም ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሎታል። ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡ ሁሉ ‘ዳግመኛ መወለድ’ አለባቸው። (ዮሐ. 3:3-5) ኢየሱስ ስለ ሰማያዊው ሕይወት በመናገር ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ በመላው ዓለም ለሚኖሩት የሰው ልጆች ስለተዘረጋው ተስፋም ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።) ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ቅቡዓን ተከታዮቹ በሰማይ፣ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በምድር ላይ ስለሚያገኙት የዘላለም ሕይወት ነበር።
9. ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር የተነጋገረው ስለ የትኛው ተስፋ ነው?
9 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ከኒቆዲሞስ ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ በስተ ሰሜን ወደምትገኘው ወደ ገሊላ ተጓዘ። በጉዞው ላይ ሳለ ሲካር በተባለች የሰማርያ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት አንዲት ሴት እንዲህ አላት፦ “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ፈጽሞ አይጠማም፤ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።” (ዮሐ. 4:5, 6, 14) ይህ ውኃ፣ አምላክ ወደፊት በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩትን ሰዎች ጨምሮ መላው የሰው ዘር የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ለማስቻል ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ያመለክታል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ እንደምናገኘው አምላክ ራሱ “ለተጠማ ሁሉ ከሕይወት ውኃ ምንጭ በነፃ እሰጣለሁ” በማለት ተናግሯል። (ራእይ 21:5, 6፤ 22:17) በመሆኑም ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት የዘላለም ሕይወት ስለሚያገኙ ሰዎች ሲናገር እያመለከተ የነበረው የተቀቡትን የመንግሥቱ ወራሾች ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን በአምላክ የሚያምኑ ሰዎች ጭምር ነው።
10. ኢየሱስ በቤተዛታ የውኃ ገንዳ አጠገብ ያገኘውን አንድ ሰው ከፈወሰው በኋላ ይቃወሙት ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የዘላለም ሕይወትን አስመልክቶ ምን አላቸው?
10 ኢየሱስ በቀጣዩ ዓመት ላይ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ መጣ። በዚያም ሳለ ቤተዛታ በተባለው የውኃ ገንዳ አጠገብ ያገኘውን አንድ በሽተኛ ፈወሰ። ኢየሱስ፣ እንዲህ በማድረጉ ይነቅፉት ለነበሩት አይሁዳውያን እንደሚከተለው ብሏቸዋል፦ “ወልድ አብ ሲያደርግ ያየውን ብቻ እንጂ በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ አይችልም።” ኢየሱስ፣ አብ “የመፍረዱን ሥልጣን ሁሉ ለወልድ [እንደሰጠው]” ከገለጸ በኋላ “ቃሌን የሚሰማና የላከኝን የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” በማለት ነገራቸው። አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን [ይኸውም የሰውን ልጅ ድምፅ] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ ነገር የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” (ዮሐ. 5:1-9, 19, 22, 24-29) ኢየሱስ ያሳድዱት ለነበሩት አይሁድ እንዲህ ብሎ ሲናገር አይሁዳውያን በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ያላቸውን ተስፋ እንዲፈጽምላቸው አምላክ የሾመው እሱን እንደሆነና ይህንንም ከፍጻሜ የሚያደርሰው የሞቱትን ሰዎች በማስነሳት እንደሆነ መግለጹ ነበር።
11. በዮሐንስ 6:48-51 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋን የሚያካትት መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
11 ኢየሱስ በገሊላ በነበረበት ጊዜ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ዳቦ እንዲሰጣቸው ይፈልጉ የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እሱን መከተል ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ለእነዚህ ሰዎች ስለ ሌላ ዓይነት ዳቦ ማለትም ስለ “ሕይወት ዳቦ” ነገራቸው። (ዮሐንስ 6:40, 48-51ን አንብብ።) ኢየሱስ ‘ዳቦው ስለ ዓለም የምሰጠው ሥጋዬ ነው’ ብሏቸዋል። ኢየሱስ ሕይወቱን የሰጠው በሰማያዊ መንግሥቱ ከእሱ ጋር ለሚገዙት ብቻ ሳይሆን “ስለ ዓለም ሕይወት” ይኸውም ከኃጢአት ነፃ መውጣት ለሚያስፈልገው የሰው ዘር ጭምር ነው። “ከዚህ ዳቦ የሚበላ ሁሉ” ማለትም የኢየሱስ መሥዋዕት ባለው የመቤዠት ኃይል ላይ እምነት እንዳለው በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖረዋል። በእርግጥም ኢየሱስ ‘ለዘላለም ስለ መኖር’ ሲጠቅስ አይሁዶች ለረጅም ጊዜ ሲጠባበቁት የኖሩትንና በመሲሑ አገዛዝ ወቅት በምድር ላይ የሚያገኙትን ለዘላለም የመኖር ተስፋ ጭምር እያመለከተ ነበር።
12. ኢየሱስ ‘ለበጎቹ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው’ ለተቃዋሚዎቹ ሲናገር የትኛውን ተስፋ መጥቀሱ ነበር?
12 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ የመታደስ በዓል በኢየሩሳሌም በተከበረበት ወቅት ለተቃዋሚዎቹ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ከበጎቼ መካከል ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል። የዘላለም ሕይወትም እሰጣቸዋለሁ።” (ዮሐ. 10:26-28) ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በሰማይ ስለሚገኘው ሕይወት ብቻ ነበር? ወይስ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖራቸውን የዘላለም ሕይወት ተስፋም በአእምሮው ይዞ ነበር? ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ ከጥቂት ጊዜ በፊት “አንተ ትንሽ መንጋ፣ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ስለፈቀደ አትፍሩ” በማለት ተከታዮቹን አበረታቷቸው ነበር። (ሉቃስ 12:32) ይሁንና በዚሁ የመታደስ በዓል ወቅት ኢየሱስ “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐ. 10:16) በመሆኑም ኢየሱስ ለተቃዋሚዎቹ የሰጠው መልስ፣ “ትንሽ መንጋ” የተባሉት ሰዎች ስለሚያገኙት ሰማያዊ ሕይወትም ሆነ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” ስለተዘረጋላቸው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ የሚጠቁም ሐሳብ ይዟል።
ማብራሪያ ያላስፈለገው ተስፋ
13. ኢየሱስ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
13 ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሳለ የተናገረው ሐሳብ የሰው ልጆች ተስፋ ምን እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል። ከጎኑ ተሰቅሎ የነበረው ወንጀለኛ “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” በማለት ተናገረ። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት ቃል ገባለት። (ሉቃስ 23:42, 43) ከሁኔታዎች መመልከት እንደሚቻለው ይህ ሰው አይሁዳዊ መሆን ይኖርበታል፤ በመሆኑም ኢየሱስ ለዚህ ሰው ገነትን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠት አላስፈለገውም። ይህ ወንጀለኛ ወደፊት በሚመጣው ዓለም ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ያውቅ ነበር።
14. (ሀ) ሐዋርያቱ ስለ ሰማያዊ ተስፋ የሚናገረውን ሐሳብ መረዳት እንደከበዳቸው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ተከታዮች ስለ ሰማያዊ ተስፋ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ያገኙት መቼ ነበር?
14 ኢየሱስ ሰማያዊ ተስፋን በተመለከተ የተናገረው ሐሳብ ግን ማብራሪያ ያስፈልገው ነበር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ቦታ ሊያዘጋጅላቸው ወደ ሰማይ እንደሚሄድ ሲነግራቸው ምን ለማለት እንደፈለገ አልገባቸውም ነበር። (ዮሐንስ 14:2-5ን አንብብ።) በኋላም እንዲህ አላቸው፦ “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። ይሁን እንጂ እሱ ይኸውም የእውነት መንፈስ ሲመጣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል።” (ዮሐ. 16:12, 13) የኢየሱስ ተከታዮች ዙፋናቸው በሰማይ እንደሆነ ያስተዋሉት በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ በኋላ ማለትም ወደፊት ነገሥታት እንዲሆኑ በአምላክ መንፈስ በተቀቡበት ጊዜ ነበር። (1 ቆሮ. 15:49፤ ቆላ. 1:5፤ 1 ጴጥ. 1:3, 4) ስለ ሰማያዊው ውርሻ የሚናገረው ተስፋ አዲስ እውቀት በመሆኑ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ደብዳቤዎች ትኩረት ያደረጉት በዚህ ተስፋ ላይ ነበር። ይሁንና እነዚህ ደብዳቤዎች በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረውን ተስፋ የሚያጠናክር ሐሳብ ይዘዋል?
በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ደብዳቤዎች ምን ይላሉ?
15, 16. ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ደብዳቤና ጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለ የሚጠቁሙት እንዴት ነው?
15 ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የእምነት ባልንጀሮቹን “የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች” ሲል ጠርቷቸዋል። በተጨማሪም ጳውሎስ፣ አምላክ “መጪውን ዓለም” ለኢየሱስ እንዳስገዛለት ገልጿል። (ዕብ. 2:3, 5፤ 3:1) በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ዓለም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ምንጊዜም ቢሆን የሚያመለክተው ሰዎች የሚኖሩባትን ምድር ነው። ስለዚህ ‘መጪው ዓለም’ የሚያመለክተው በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ሥር የሚተዳደረውንና ሰዎች በሚኖሩባት ምድር ላይ ወደፊት የሚቋቋመውን ሥርዓት ነው። በዚያን ወቅት ኢየሱስ፣ አምላክ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት የገባውን ቃል ያስፈጽማል።—መዝ. 37:29
16 ሐዋርያው ጴጥሮስም በመንፈስ ተመርቶ ስለ ሰው ዘር የወደፊት ሁኔታ ጽፏል። እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።” (2 ጴጥ. 3:7) በአሁኑ ጊዜ ያሉት በሰማይ የተመሰሉት መንግሥታት እንዲሁም ዓመፀኛ የሆነው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ የሚተኩት በምንድን ነው? (2 ጴጥሮስ 3:13ን አንብብ።) ‘በአዲስ ሰማያት’ ማለትም በአምላክ መሲሐዊ መንግሥትና ‘በአዲስ ምድር’ ይኸውም የይሖዋን እውነተኛ አምላኪዎች ባቀፈው ጻድቅ የሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይተካሉ።
17. የሰው ልጆች የወደፊት ተስፋ በራእይ 21:1-4 ላይ የተገለጸው እንዴት ነው?
17 በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የሚገኘውና የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንደሚደርሱ የሚገልጸው ራእይ ልባችን በአድናቆት ስሜት እንዲሞላ የሚያደርግ ነው። (ራእይ 21:1-4ን አንብብ።) አዳም በኤደን ገነት ኃጢአት ከሠራበት ጊዜ አንስቶ በአምላክና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ወደ ፍጽምና የሚደርሱበትን ጊዜ በተስፋ ይጠባበቁ ነበር። ጻድቅ የሆኑ ሰዎች ከእርጅና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ሳይኖሩ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጻሜ ለሌለው ጊዜ በሕይወት ይኖራሉ። ይህ ተስፋ በዕብራይስጥና በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሚገኙት ጠንካራ ማስረጃዎች የተደገፈ ከመሆኑም ሌላ ዛሬም ቢሆን ለይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የብርታት ምንጭ ሆኖላቸዋል።—ራእይ 22:1, 2
ልታብራራ ትችላለህ?
• ኢየሱስ “ዳግም ፍጥረት” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
• ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር የተነጋገረው ስለ ምን ጉዳይ ነበር?
• ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ ቃል የገባለት ምን በማለት ነበር?
• ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፈው ደብዳቤና ጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ መኖሩን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በግ መሰል ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ስለ ዘላለም ሕይወት ተናግሯል