የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 41—ማርቆስ
ጸሐፊው:- ማርቆስ
የተጻፈበት ቦታ:- ሮም
ተጽፎ ያለቀው:- ከ60–65 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ29–33 ከክ.ል.በኋላ
ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ሲያዝ ሐዋርያት በሸሹበት ወቅት “ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ያገለደመ አንድ ወጣት” ይከተለው ነበር። ሰዎቹ ሊይዙት ሲሞክሩ ግን ወጣቱ “ግልድሙን ጥሎ ዕራቊቱን ሸሸ።” ይህ ወጣት ማርቆስ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ‘ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ’ በማለት ይጠራዋል፤ የማርቆስ ቤተሰቦች የራሳቸው ቤትና አገልጋዮች እንዳሏቸው ስለተገለጸ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተደላደለ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ማርያም የተባለችው እናቱም ክርስቲያን የነበረች ሲሆን የጥንቱ ጉባኤ ቤቷን ለመሰብሰቢያነት ይጠቀምበት ነበር። ጴጥሮስ በአንድ መልአክ አማካኝነት ከእስር በተፈታበት ወቅት ወደዚህ ቤት ሲሄድ ወንድሞችን ተሰብስበው አግኝቷቸዋል።— ማር. 14:51, 52፤ ሥራ 12:12, 13
2 የቆጵሮስ ተወላጅና ሌዋዊ የሆነው ሚስዮናዊው በርናባስ ለማርቆስ የአክስቱ ልጅ ነበር። (ሥራ 4:36፤ ቈላ. 4:10) በራብ ለተጠቁት ወንድሞች ከሚደረገው እርዳታ ጋር በተያያዘ በርናባስ ከጳውሎስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ወቅት ማርቆስ ከጳውሎስ ጋር ተዋወቀ። ማርቆስ በጉባኤው ውስጥ ከእነዚህ ወንድሞችና ቀናተኛ ከሆኑ ጎብኚ አገልጋዮች ጋር መገናኘቱ በሚስዮናዊነት አገልግሎት እንዲካፈል ፍላጎት እንዳሳደረበት አያጠራጥርም። በዚህም የተነሳ ጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያውን የሚስዮናዊነት ጉዟቸውን ሲያካሂዱ የጉዞ ጓደኛቸውና ረዳታቸው በመሆን አብሯቸው ተጉዟል። ሆኖም ጳውሎስና በርናባስ በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌን ሲሄዱ ማርቆስ ከእነሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። (ሥራ 11:29, 30፤ 12:25፤ 13:5, 13) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዟቸው ወቅት ማርቆስ ከእነሱ ጋር እንዲሄድ አልፈለገም፤ ይህ ደግሞ በጳውሎስና በበርናባስ መካከል መለያየት ፈጠረ። ጳውሎስ ሲላስን ይዞ ሲሄድ በርናባስ ግን የአክስቱን ልጅ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ።— ሥራ 15:36-41
3 ማርቆስ በአገልግሎት ብቁ መሆኑን በማሥመስከሩ ለበርናባስ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ በኋላ ለሐዋርያው ጴጥሮስና ጳውሎስም ጠቃሚ እርዳታ አበርክቷል። ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም በታሰረበት ወቅት (ከ60-61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) ማርቆስ ከእሱ ጋር ነበር። (ፊል. 1, 24) ከዚያም ከ62 እስከ 64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባሉት ዓመታት ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር በባቢሎን እንደነበረ ተገልጿል። (1 ጴጥ. 5:13) ጳውሎስ እንደገና በሮም በታሰረበት ወቅት (በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሳይሆን አይቀርም) ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ማርቆስ ‘በአገልግሎቱ ስለሚረዳው’ ይዞት እንዲመጣ ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 1:8፤ 4:11) ማርቆስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ቦታ ላይ ነው።
4 ከወንጌሎች ሁሉ አጭር የሆነውን ይህን ወንጌል የጻፈው ማርቆስ እንደሆነ ይነገራል። ማርቆስ የኢየሱስ ሐዋርያት የሥራ ባልደረባ ከመሆኑም በላይ ሕይወቱን ለወንጌሉ ሥራ ያዋለ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ማርቆስ ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ አይደለም፤ ከኢየሱስ ጋርም የቅርብ ግንኙነት አልነበረውም። ታዲያ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት ያቀረበው ዘገባ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ሕያው እንዲሆን ያደረጉትን ዝርዝር ሐሳቦች ከየት አገኛቸው? የጥንቶቹ ፓፒየስ፣ ኦሪጀንና ተርቱሊያን እንደሚሉት ከሆነ ማርቆስ ይህን መረጃ ያገኘው በጣም ይቀርበው ከነበረው ከጴጥሮስ ነው።a ጴጥሮስ፣ ማርቆስን “ልጄ” በማለት ጠርቶታል። (1 ጴጥ. 5:13) ጴጥሮስ፣ ማርቆስ የመዘገበውን ታሪክ በሙሉ በዓይኑ ተመልክቷል፤ በመሆኑም በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ የማይገኙ በርካታ ዝርዝር ሐሳቦችን ለማርቆስ ነግሮት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ማርቆስ፣ ዘብዴዎስ ‘ቅጥር ሠራተኞች’ እንደነበሩት፣ የሥጋ ደዌ የነበረበት ሰው በኢየሱስ ፊት “በመንበርከክ” እንደለመነው፣ አጋንንት የያዙት ሰው “ሰውነቱን በድንጋይ ይቈራርጥ” እንደነበረ እንዲሁም ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ “በቤተ መቅደሱ ትይዩ” ተቀምጦ “የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ” እንደሚመጣ ትንቢት መናገሩን ገልጿል።— ማር. 1:20, 40፤ 5:5፤ 13:3, 26
5 ጴጥሮስ ራሱ ስሜቱ በጥልቅ የሚነካ ሰው ስለነበረ የኢየሱስን ስሜት ሊረዳና ለማርቆስ ሊነግረው ይችላል። በመሆኑም በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ኢየሱስ ምን እንደተሰማውና ምን እንዳደረገ በአብዛኛው የዘገበው ማርቆስ ነው፤ ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “አዝኖ በዙሪያው የቆሙትን በቍጣ ተመለከታቸው”፣ “ቃተተ” እንዲሁም “በመንፈሱ እጅግ በመቃተት” የሚሉትን አገላለጾች ተጠቅሟል። (3:5፤ 7:34፤ 8:12) ኢየሱስ ሀብታሙን ወጣት “ወደደው” በማለት የኢየሱስን ስሜት የገለጸልን ማርቆስ ነው። (10:21) በተጨማሪም ኢየሱስ በሐዋርያት መካከል አንድ ትንሽ ልጅ እንዳቆመ ብቻ ሳይሆን ልጁን ‘እንዳቀፈው’ በሌላ ጊዜም ‘ሕፃናትን እንዳቀፋቸው’ የሚገልጸው ዘገባ ፍቅርን የሚያንጸባርቅ ነው!— 9:36፤ 10:13-16
6 እንደ ችኩልነት፣ ቅልጥፍና፣ ኃይለኝነት፣ ንቁነትና ግልጽነት የመሳሰሉት አንዳንድ የጴጥሮስ ባሕርያት በማርቆስ የአጻጻፍ ስልት ላይ ተንጸባርቀዋል። ማርቆስ ታሪኮቹን ለማስፈር ከመቸኮሉ የተነሳ ስለ አንድ ክንውን ብዙም ማብራሪያ ሳይሰጥ ወደሚቀጥለው ክንውን የሚያልፍ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል፣ “ወዲያው” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት የተጠቀሰ ሲሆን ይህም ዘገባው የድራማ አጻጻፍ ስልት የተከተለ እንዲሆን አድርጎታል።
7 ማርቆስ፣ የማቴዎስ ወንጌልን ሊያገኝ ይችል የነበረ ከመሆኑም በላይ እሱ ከጻፈው ዘገባ ውስጥ በሌሎች ወንጌሎች ላይ የማይገኘው 7 በመቶው ብቻ ነው፤ ያም ቢሆን ግን ማርቆስ፣ የማቴዎስ ወንጌልን አጠር ባለ መልኩ ካዘጋጀ በኋላ አንዳንድ ለየት ያሉ ነጥቦችን አክሎበት እንዳቀረበው ማሰብ ስሕተት ነው። ማቴዎስ፣ ኢየሱስን ተስፋ እንደተሰጠበት መሲሕና ንጉሥ አድርጎ የገለጸው ሲሆን ማርቆስ ደግሞ የኢየሱስን ሕይወትና ሥራዎች ከሌላ አቅጣጫ አቅርቧል። ማርቆስ፣ ኢየሱስን የገለጸው ተአምር እንደሚሠራ የአምላክ ልጅና ድል አድራጊ አዳኝ አድርጎ ነው። ከዚህም ሌላ በክርስቶስ ስብከትና ትምህርት ላይ ሳይሆን ባከናወናቸው ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጓል። ማርቆስ፣ ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች ውስጥ የተወሰኑትን፣ ረጅም ከሆኑት ንግግሮቹ መካከል ደግሞ አንዱን ብቻ የዘገበ ሲሆን ስለ ተራራው ስብከት ጭራሽ አልጻፈም። የማርቆስ ወንጌል ከሌሎቹ ወንጌሎች ይልቅ አጭር የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፤ ያም ቢሆን ግን ኢየሱስ ያከናወናቸውን ነገሮች በተመለከተ ከሌሎቹ ወንጌሎች ያላነሰ ዘገባ ይዟል። በወንጌሉ ውስጥ ቢያንስ 19 ተአምራት ተለይተው ተጠቅሰዋል።
8 ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁዳውያን ሲሆን ማርቆስ ደግሞ በዋነኝነት የጻፈው ለሮማውያን መሆኑ ግልጽ ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? በመጽሐፉ ውስጥ የሙሴ ሕግ የተገለጸው ሕጉን የሚጠቅስ ሐሳብ በሚኖርበት ጊዜ ብቻ ሲሆን የኢየሱስ የዘር ሐረግም በወንጌሉ ውስጥ አልተካተተም። የክርስቶስ ወንጌል ለሁሉም ሰው ጠቃሚ እንደሆነ ተገልጿል። አይሁዳውያን ላልሆኑ አንባቢያን አዲስ ሊሆኑ የሚችሉትን የአይሁዳውያን ልማዶችና ትምህርቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል። (2:18፤ 7:3, 4፤ 14:12፤ 15:42) በአረማይክ ቋንቋ የተገለጹ አነጋገሮች ፍቺ ተቀምጧል። (3:17፤ 5:41፤ 7:11, 34፤ 14:36፤ 15:22, 34) የፓለስቲናን መልክአ ምድራዊ ስሞችና ዕፅዋትን በተመለከተ ማብራሪያ ቀርቧል። (1:5, 13፤ 11:13፤ 13:3) የአይሁዳውያን ሳንቲሞች ወደ ሮማውያን ገንዘብ ሲለወጡ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ተገልጿል። (12:42፣ የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) እንዲሁም ማርቆስ ከሌሎቹ የወንጌል ጸሐፊዎች በበለጠ በላቲን ቃላት ተጠቅሟል፤ ስፐኩላቶር (ወታደር)፣ ፕራይቶሪዮን (የገዢው ቤተ መንግሥት) እና ሴንቱሪዮ (የጦር አዛዥ) የሚሉትን ቃላት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።— 6:27፤ 15:16, 39
9 ማርቆስ ወንጌሉን በዋነኝነት የጻፈው ለሮማውያን በመሆኑ የጻፈው በሮም ሳይሆን አይቀርም። ከጥንታዊ አፈ ታሪክም ሆነ ከመጽሐፉ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው መጽሐፉ የተጠናቀረው ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ አሊያም ለሁለተኛ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ነው፤ ይህም ከ60-65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባሉት ዓመታት ውስጥ ማለት ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ማርቆስ ቢያንስ አንድ ጊዜ ምናልባትም ሁለት ጊዜ ወደ ሮም ሳይሄድ አይቀርም። በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበሩ ታዋቂ ምሑራን በሙሉ የወንጌሉ ጸሐፊ ማርቆስ መሆኑን ያረጋግጣሉ። በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ወንጌሉ በክርስቲያኖች መካከል ተሰራጭቶ ነበር። የማርቆስ ወንጌል በሁሉም ጥንታዊ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝሮች ውስጥ መገኘቱ የመጽሐፉን እውነተኝነት ያረጋግጣል።
10 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ከምዕራፍ 16 ቁጥር 8 በኋላ የሚጨመሩት ረዥምና አጭር መደምደሚያዎች እውነተኛ የቅዱስ ጽሑፉ ክፍል እንደሆኑ ተደርገው አይታዩም። እነዚህ ጥቅሶች እንደ ሳይናይቲክ እና ቫቲካን ቁጥር 1209 ባሉት አብዛኞቹ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ አይገኙም። የአራተኛው መቶ ዘመን ምሑራን የነበሩት ዩሲቢየስና ጀሮም ትክክለኛው የወንጌል ዘገባ የሚደመደመው “ፈርተው ስለ ነበር ለማንም አንዳች አልተናገሩም” በሚለው ሐሳብ እንደሆነ ይስማማሉ። ምናልባት ከዚህ ሐሳብ በኋላ ያለው መደምደሚያ የተጨመረው ወንጌሉ በድንገት ስለተደመደመ ይህን ለማስቀረት ተብሎ ሊሆን ይችላል።
11 የማርቆስ ዘገባ ከሌሎች ወንጌሎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ካሉት ከሁሉም ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማማ መሆኑ የመጽሐፉን ትክክለኛነት ያሳያል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ሥልጣን እንዳለው በመጽሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተገልጿል፤ ይህም በተናገራቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ኃይሎች፣ በሰይጣንና በአጋንንቱ፣ በሕመምና በበሽታ እንዲያውም በሞት ላይ እንኳ ሳይቀር ባሳየው ኃይል ታይቷል። በመሆኑም ማርቆስ ትረካውን የሚጀምረው “የእግዚአብሔር ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ” በሚል ስሜት ቀስቃሽ መግቢያ ነው። የኢየሱስ መምጣትና ያከናወነው አገልግሎት “ምሥራች” ነው፤ በመሆኑም ሁሉም አንባቢያን የማርቆስ ወንጌልን በማጥናት ሊጠቀሙ ይችላሉ። ማርቆስ የተረካቸው ክንውኖች ከ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጸደይ ወራት እስከ 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጸደይ ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ናቸው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
31 በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበው ሕያው መግለጫ፣ ክርስትና ከተቋቋመበት ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይህን ወንጌል የሚያነቡ ሰዎች መሲሑን በተመለከተ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ለማወቅ አስችሏቸዋል። “እነሆ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ” ከሚለው መግቢያው ላይ ከሚገኘው ሐረግ ጀምሮ ኢየሱስ “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውኸኝ” በማለት ተሰቅሎ እያለ በሥቃይ እስከተናገረው ሐሳብ ድረስ ያለው በቅንዓት ስላከናወነው አገልግሎት የሚገልጸው ሙሉው የማርቆስ ዘገባ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው ከተናገሯቸው ትንቢቶች ጋር የሚስማማ ነው። (ማር. 1:2፤ 15:34፤ ሚል. 3:1፤ መዝ. 22:1) ከዚህም በላይ ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራትና ያከናወናቸው አስገራሚ ነገሮች፣ የሰጠው ጠቃሚ ትምህርት፣ የሐሰት ትምህርቶችን ማጋለጡ፣ በይሖዋ ቃልና መንፈስ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመኑ እንዲሁም በጎቹን በርኅራኄ መጠበቁ የአምላክ ልጅ እንደሆነና ሥልጣን ተሰጥቶት እንደመጣ የሚያረጋግጡ ናቸው። ከይሖዋ ባገኘው ሥልጣን “እንደ ባለ ሥልጣን” አስተምሯል፤ እዚህ ምድር ላይ ሳለ ዋነኛ ሥራው “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” እያለ ‘የእግዚአብሔርን ወንጌል መስበክ’ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። የኢየሱስን ትምህርት በሥራ ላይ ያዋሉ ሁሉ ይህ ነው የማይባል ጥቅም አግኝተዋል።— ማር. 1:22, 14, 15
32 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቶአችኋል” ብሏቸዋል። ማርቆስ “የእግዚአብሔር መንግሥት” የሚለውን አገላለጽ 14 ጊዜ የተጠቀመበት ሲሆን በመንግሥቱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች መመሪያ የሚሆኑ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ገልጿል። ኢየሱስ “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ . . . ያድናታል” ብሏል። ሕይወት እንዳናገኝ እንቅፋት የሚሆን ማንኛውም ነገር መወገድ ይኖርበታል:- “ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል።” ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም” እንዲሁም “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!” በማለት ተናግሯል። ሁለቱን ታላላቅ ትእዛዛት መጠበቅ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች እንደሚበልጥ ያስተዋለውን ሰው “ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” ብሎታል። በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የሚገኙት እነዚህና ሌሎች ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ትምህርቶች በዕለታዊ ሕይወታችን በሥራ ላይ ልናውላቸው የምንችላቸው በጣም ጠቃሚ የሆኑ ምክሮች ይዘዋል።— 4:11፤ 8:35፤ 9:43-48፤ 10:13-15, 23-25፤ 12:28-34
33 ሙሉው “የማርቆስ ወንጌል” በአንድ ወይም በሁለት ሰዓት ውስጥ ሊነበብ ይችል ይሆናል፤ አንባቢው እንዲህ በማድረግ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት አስደሳች፣ ፈጣንና ሕያው የሆነ ክለሳ ማድረግ ይችላል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ይህን ወንጌል በዚህ መልኩ በአንድ ጊዜ መውጣት እንዲሁም በጥልቀት ማጥናትና በዘገባው ላይ ማሰላሰል ምንጊዜም ቢሆን ጠቃሚ ነው። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዛሬው ጊዜም የማርቆስ ወንጌል በስደት ላይ ላሉ ክርስቲያኖች ጠቃሚ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ስለሚኖሩ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደሚገኘው ዘገባ ያለ ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክቶ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። የማርቆስን ወንጌል በማንበብ በዚህ ትኩረት የሚስብ ዘገባ እንድትደሰት እንዲሁም የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነው ኢየሱስ ያገኘው ዓይነት የማይጠፋ ደስታ አግኝተህ የእሱን ፈለግ እንድትከተል እናበረታታሃለን። (2 ጢሞ. 3:1፤ ዕብ. 12:2) አዎን፣ ኢየሱስ የተግባር ሰው መሆኑን አስተውል፤ የእሱ ዓይነት ቅንዓት ይኑርህ፤ እንዲሁም በፈተና እና በተቃውሞ ወቅት ያሳየውን የማያወላውል የአቋም ጽናትና ድፍረት ኮርጅ። በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከዚህ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መጽናናት አግኝ። የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ይህን ወንጌል ተጠቀምበት!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 337