ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
“በእውነትም የአምላክ ልጅ ነበር”
ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ተሰቅሎ ብዙ ሳይቆይ እኩለ ቀን ላይ ሶስት ሰዓት የቆየ ምሥጢራዊ ጨለማ ሆነ። የፀሐይ ግርዶሽ ነበር ለማለት አይቻልም ምክንያቱም የፀሐይ ግርዶሽ የሚፈጠረው አዲስ ጨረቃ በምትኖርበት ጊዜ ባ ነው። የማለፍ በዓል በሚከበርበት ጊዜ ደግሞ ጨረቃ ሙሉ ነች። ከዚህም በላይ የፀሐይ ግርዶሽ የሚቆየው ለጥቂት ደቂቃ ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ጨለማ አምላክ ያመጣው መሆን ይኖርበታል። በኢየሱስ ላይ ይዘብቱ የነበሩትን ሰዎች ስድባቸውን እንዲያቆሙና ዝም እንዲሉ ሳያደርጋቸው አልቀረም።
ይህ አስፈሪ ሁኔታ የተፈጠረው ክፉ አድራጊው ጓደኛውን ገስጾ ኢየሱስን እንዲያስበው ከመጠየቁ በፊት ከሆነ ንሥሐ እንዲገባ የገፋፋው ይህ ጨለማ ሊሆን ይችላል። አራቱ ሴቶች ማለትም የኢየሱስ እናትና እህትዋ ሰሎሜ፣ መግደላዊት ማርያምና የታናሹ የሐዋርያው ያዕቆብ እናት ማርያም ወደ መከራው እንጨት የቀረቡት በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ በጣም ይወደው የነበረው ሐዋርያ ዮሐንስም ከእነርሱ ጋር ነበር።
ያጠባችውና ተንከባክባ ያሳደገችው ልጅ ተሰቅሎ ሲሰቃይ ስታይ የኢየሱስ እናት ምን ያህል ‘ልቧ እንደተወጋ’ መገመት ይቻላል። ኢየሱስ ግን ያስብ የነበረው ስለራሱ ሥቃይ ሳይሆን ስለ እርስዋ ደህንነት ነበር። በብዙ ችግር ዮሐንስን ጠቀሰና ለእናቱ “አንቺ ሴት፣ እነሆ ልጅሽ” አላት። ከዚያም ወደ ማርያም እያመለከተ “እናትህ እነኋት” አለው።
ስለዚህ ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ባልዋ ሞቶባት መበለት ሆና የምትኖረውን እናቱን እንዲጠብቅ በጣም ለሚወደው ሐዋርያው አደራ ሰጠ። ይህን ያደረገው ሌሎቹ የማርያም ልጆች ገና ስላላመኑበት ነበር። ስለዚህም ለእናቱ ሥጋዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳዊ ፍላጎትዋ በማሰቡ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል።
ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ያህል ሲሆን ኢየሱስ “ተጠማሁ” አለ። ከዚያም አባቱ ንጹሕ አቋሙ እስከ መጨረሻው እንዲፈተን ሲል ከእርሱ እንደራቀ ስለተሰማው ጮክ ብሎ “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ” አለ። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ “ይህስ ኤልያስን ይጠራል” አሉ። በዚህ ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ ሄደና የኮመጠጠ ወይን ጠጅ የተነከረ ስፖንጅ በሂሶጵ መቃ ላይ አድርጎ አቀረበለት። ሌሎቹ ግን “ተው፣ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ።
ኢየሱስ ኮምጣጣውን ወይን ጠጅ ከተቀበለ በኋላ “ተፈጸመ” አለ። አዎ፣ ሰማያዊ አባቱ እንዲፈጽም ወደ ምድር የላከውን ሥራ ሁሉ ፈጸመ። በመጨረሻም “አባት ሆይ፣ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” አለ። ኢየሱስ ይህን በማለት አምላክ የሕይወት ኃይሉን መልሶ እንደሚሰጠው እርግጠኛ በመሆን ነፍሱን አደራ ሰጠው። ከዚያም ራሱን ዘንበል አደረገና ሞተ።
የኢየሱስ ትንፋሽ ቀጥ እንዳለ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነና ታላላቅ ድንጋዮች ተሰንጥቀው ተከፈቱ። የምድር መናወጡ በጣም ኃይለኛ ስለነበረ ከኢየሩሳሌም ውጭ የነበሩ የመታሰቢያ መቃብሮች ተከፈቱና በመቃብሮቹ ውስጥ የነበሩ አስከሬኖች ወጡ። አስከሬኖቹን የተመለከቱ መንገደኞች ወደ ከተማው ገቡና የተመለከቱትን አወሩ።
ከዚህም በላይ ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ በአምላክ ቤተመቅደስ ውስጥ ቅድስቲቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየው ትልቅ መጋረጃ ከላይ ወደ ታች ተተረተረ። ይህ ብዙ ጌጣ ጌጦች የተጠለፉበት መጋረጃ በጣም ከባድ ከመሆኑም በላይ 60 ጫማ የሚያክል ቁመት ነበረው። ይህ አስደናቂ ተአምር አምላክ ልጁን የገደሉበትን ሰዎች መቆጣቱን ብቻ ሳይሆን አሁን ኢየሱስ ስለሞተ በሰማይ ወደሚገኘው ቅዱሰ ቅዱሳን መግባት መቻሉን ጭምር ያመለክት ነበር።
ሰዎች የምድር መናወጡንና የሆነውን ነገር በሙሉ ሲመለከቱ በጣም ፈሩ። የግድያውን ሥፍራ ይጠብቅ የነበረው የጦር ሠራዊት መኮንን አምላክን አከበረ። “ይህ ሰው በእውነት የአምላክ ልጅ ነበር” አለ። ይህ መኮንን ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት ተከስሶ በቀረበበትና በአምላክ ልጅነቱ ላይ ክርክር በተደረገበት ጊዜ በቦታው ሳይገኝ አልቀረም። አሁን ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነና በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች በሙሉ የበለጠ ታላቅ ሰው መሆኑን አመነ።
ሌሎችም እነዚህን ተአምራዊ ሁኔታዎች ሲመለከቱ ልባቸው ተነክቶ በጣም ማዘናቸውንና በተፈጸመው ነገር ሁሉ ማፈራቸውን ለማሳየት ደረታቸውን እየመቱ ወደ ቤታቸው መመለስ ጀመሩ። ሁኔታውን ከሩቅ ቆመው ይመለከቱ የነበሩ የኢየሱስ ሴት ደቀመዛሙርት ባዩአቸው ታላላቅ ሁኔታዎች በጣም ተደንቀው ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስም በዚያ ነበር። ማቴዎስ 27:45-56፤ ማርቆስ 15:33-41፤ ሉቃስ 23:44-49፤ 2:34, 35፤ ዮሐንስ 19:25-30
◆ ለሦስት ሰዓት ያህል ጨለማ የሆነው በፀሐይ ግርዶሽ ምክንያት ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
◆ ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት አረጋዊ ወላጆች ላሉአቸው ሰዎች ምን ጥሩ ምሳሌ ተወላቸው?
◆ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የተናገራቸው አራት ነገሮች ምን ነበሩ?
◆ የምድር መናወጡ ምን ውጤት አስከተለ? የቤተመቅደሱ መጋረጃ ተተርትሮ ለሁለት መከፈሉ ምን ትርጉም አለው?
◆ የመግደያውን ሥፍራ ይጠብቅ የነበረው የጦር ሠራዊት መኮንን በተአምራቶቹ የተነካው እንዴት ነው?