የጥናት ርዕስ 31
ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነህ?
“በትዕግሥት እጠብቃለሁ።”—ሚክ. 7:7
መዝሙር 128 እስከ መጨረሻው መጽናት
ማስተዋወቂያa
1-2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
በጣም የሚያስፈልግህ ዕቃ ተልኮልህ ዕቃው ባሰብከው ጊዜ ባይደርስ ምን ይሰማሃል? ታዝናለህ? ምሳሌ 13:12 “የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል” ይላል፤ አንተም እንዲህ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም ዕቃው በጠበቅከው ጊዜ ያልደረሰበት አጥጋቢ ምክንያት እንዳለ ብታውቅስ? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደምትሆን ግልጽ ነው።
2 “በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ” ለማዳበርና ይህን ዝንባሌ ይዘን ለመቀጠል የሚረዱንን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። (ሚክ. 7:7 ግርጌ) ከዚያም ይሖዋ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ያለብን በየትኞቹ ሁለት ሁኔታዎች ውስጥ እንደሆነ እናያለን። በመጨረሻም ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የሚያገኟቸውን በረከቶች እንመለከታለን።
ትዕግሥት የሚያስተምሩን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች
3. ምሳሌ 13:11 ምን ያስተምረናል?
3 የትዕግሥትን አስፈላጊነት የሚያጎላ አንድ ምሳሌ በምሳሌ 13:11 ላይ እናገኛለን። እንዲህ ይላል፦ “በፍጥነት የተገኘ ሀብት ይመናመናል፤ ጥቂት በጥቂት የሚያጠራቅም ሰው ግን ሀብቱ ይጨምራል።” ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን? ቀስ በቀስ ነገሮችን በትዕግሥት ማከናወን የጥበብ እርምጃ ነው።
4. በምሳሌ 4:18 ላይ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ምን ያስተምረናል?
4 ምሳሌ 4:18 እንዲህ ይላል፦ “የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።” ይህ ሐሳብ ይሖዋ ዓላማውን ለሕዝቡ የሚገልጸው ቀስ በቀስ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ይሁንና ጥቅሱን አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ መንፈሳዊ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ ለመግለጽም ልንጠቀምበት እንችላለን። መንፈሳዊ እድገት ጊዜ የሚወስድ ነገር ስለሆነ ልናጣድፈው አንችልም። ከአምላክ ቃልና ከድርጅቱ የምናገኘውን ምክር በትጋት የምናጠናና በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ ቀስ በቀስ የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ ማዳበር እንችላለን። ስለ አምላክ ያለን እውቀትም እያደገ ይሄዳል። ኢየሱስ ይህን ለማብራራት የተጠቀመበትን ምሳሌ እንመልከት።
5. ኢየሱስ አንድ ሰው እድገት የሚያደርገው ቀስ በቀስ እንደሆነ ለማሳየት ምን ምሳሌ ተጠቅሟል?
5 ኢየሱስ የምንሰብከው የመንግሥቱ መልእክት ከትንሽ ዘር ጋር እንደሚመሳሰልና ቅን በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ ቀስ በቀስ እንደሚያድግ የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “[ዘሪው] እንዴት እንደሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅልና ያድጋል። መሬቱም ራሱ ቀስ በቀስ ፍሬ ያፈራል፤ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ከዚያም ዛላውን በመጨረሻም በዛላው ላይ የጎመራ ፍሬ ይሰጣል።” (ማር. 4:27, 28) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ አንድ ተክል የሚያድገው ቀስ በቀስ እንደሆነ ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበል ሰውም በመንፈሳዊ የሚያድገው ቀስ በቀስ እንደሆነ መግለጹ ነበር። ለምሳሌ ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ወደ ይሖዋ በቀረቡ መጠን በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ መልካም ለውጦች ሲያደርጉ እንመለከታለን። (ኤፌ. 4:22-24) ያንን ትንሽ ዘር የሚያሳድገው ግን ይሖዋ እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብንም።—1 ቆሮ. 3:7
6-7. ይሖዋ ምድርን ከፈጠረበት መንገድ ምን እንማራለን?
6 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው ሳይጣደፍ በቂ ጊዜ ወስዶ ነው። እንዲህ የሚያደርገው ለስሙ ክብር እንዲሁም ለሌሎች ጥቅም ሲል ነው። ለምሳሌ ይሖዋ ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን ቀስ በቀስ ያዘጋጃት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
7 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ምድርን ስለፈጠረበት መንገድ ሲናገር ‘መለኪያዎቿን እንደወሰነ፣’ ‘ምሰሶዎቿን እንደተከለ’ እንዲሁም ‘የማዕዘኗን ድንጋይ እንዳኖረ’ ይገልጻል። (ኢዮብ 38:5, 6) ይሖዋ የሠራውን ሥራ መለስ ብሎ ለማየትም ጊዜ ወስዷል። (ዘፍ. 1:10, 12) መላእክት የይሖዋ የፍጥረት ሥራ ቀስ በቀስ መልክ እየያዘ ሲሄድ ሲያዩ ምን ተሰምቷቸው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? በጣም ተደንቀው መሆን አለበት! እንዲያውም ‘በደስታ እንደጮኹ’ ተገልጿል። (ኢዮብ 38:7) ከዚህ ምን እንማራለን? ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ለማከናወን ብዙ ሺህ ዓመታት ወስዶበታል፤ ደግሞም በጥንቃቄ የፈጠረውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሯል።—ዘፍ. 1:31
8. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?
8 ከላይ በተጠቀሱት ምሳሌዎች ላይ እንደተመለከትነው የትዕግሥትን አስፈላጊነት የሚያጎሉ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በአምላክ ቃል ውስጥ ማግኘት እንችላለን። ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆን ያለብን በየትኞቹ ሁለት ሁኔታዎች ውስጥ እንደሆነ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።
ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅ የሚያስፈልገን መቼ ነው?
9. ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅ የሚያስፈልገን መቼ ሊሆን ይችላል?
9 ጸሎታችን መልስ እስኪያገኝ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ሊያስፈልገን ይችላል። አንድን ፈተና ለመቋቋም ወይም አንድን ድክመት ለማሸነፍ ኃይል እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ ከጸለይን በኋላ የምንፈልገው መፍትሔ እንደዘገየብን ሊሰማን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችንን ቶሎ የማይመልስልን ለምንድን ነው?
10. ከጸሎት ጋር በተያያዘ ታጋሾች መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
10 ይሖዋ ጸሎታችንን በትኩረት ያዳምጣል። (መዝ. 65:2) የምናቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት በእሱ ላይ እምነት እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዕብ. 11:6) ይሖዋ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድና ፈቃዱን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነትም ማየት ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 3:22) ስለዚህ አንድን መጥፎ ልማድ ወይም ድክመት ለማሸነፍ እንዲረዳን ይሖዋን ከጠየቅነው በኋላ ታጋሽ መሆንና ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ሊኖርብን ይችላል። ኢየሱስ አንዳንዶቹ ጸሎቶቻችን ወዲያውኑ ምላሽ ላያገኙ እንደሚችሉ ጠቁሟል። እንዲህ ብሏል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።” (ማቴ. 7:7, 8) ይህን ምክር በመከተል ‘በጽናት ከጸለይን’ የሰማዩ አባታችን እንደሚሰማንና ጸሎታችንን እንደሚመልስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ቆላ. 4:2
11. የጸሎታችን መልስ እንደዘገየ ከተሰማን ዕብራውያን 4:16 የሚረዳን እንዴት ነው?
11 የጸሎታችን መልስ የዘገየ ሆኖ ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ ልክ “በሚያስፈልገን ጊዜ” ጸሎታችንን እንደሚመልስልን ቃል ገብቶልናል። (ዕብራውያን 4:16ን አንብብ።) አንድ ነገር እኛ በጠበቅነው ጊዜ ሳይፈጸም ቢቀር ይሖዋን ፈጽሞ መውቀስ የሌለብን ለዚህ ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙዎች የአምላክ መንግሥት መጥቶ ይህን ሥርዓት እንዲያጠፋ ለዓመታት ሲጸልዩ ቆይተዋል። ኢየሱስም ቢሆን ስለዚህ ጉዳይ መጸለይ እንዳለብን አስተምሯል። (ማቴ. 6:10) ሆኖም አንድ ሰው መጨረሻው ሰዎች በጠበቁት ጊዜ ባለመምጣቱ የተነሳ በአምላክ ላይ ያለው እምነት እንዲዳከም ቢፈቅድ ይህ ምንኛ ሞኝነት ይሆናል! (ዕን. 2:3፤ ማቴ. 24:44) ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቃችንና ወደ እሱ በእምነት መጸለያችን የጥበብ እርምጃ ነው። መጨረሻው ልክ በትክክለኛው ጊዜ ይመጣል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ‘ቀኑንና ሰዓቱን’ አስቀድሞ ወስኗል። ያ ቀን ሲመጣ፣ ይሖዋ የመረጠው ጊዜ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ይረጋገጣል።—ማቴ. 24:36፤ 2 ጴጥ. 3:15
12. በትዕግሥት መጠበቅ ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉት ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
12 ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ቢፈጸም ነገሩ እስኪስተካከል ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ሰዎች በፆታቸው፣ በዘራቸው፣ በብሔራቸው ወይም በዜግነታቸው የተነሳ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። ሌሎች ደግሞ የአካል ጉዳተኛ ወይም የአእምሮ ሕመምተኛ በመሆናቸው የተነሳ የፍትሕ መጓደል ይደርስባቸዋል። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው እምነታቸው የተነሳ ከባድ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው የጸና . . . ይድናል” ብሏል። (ማቴ. 24:13) በሌላ በኩል ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብታውቅስ? ሽማግሌዎች ስለ ጉዳዩ ከሰሙ በኋላ ጉዳዩን ለእነሱ ትተወዋለህ? ጉዳዩን በይሖዋ መንገድ እንደሚይዙት በመተማመን በትዕግሥት ትጠብቃለህ? እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሽማግሌዎች ምን ነገሮችን ያከናውናሉ?
13. የፍርድ ጉዳዮችን በይሖዋ መንገድ መያዝ የትኞቹን ነገሮች ይጨምራል?
13 ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ ሲያውቁ ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ይጸልያሉ፤ ይህም ጉዳዩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለማየት ይረዳቸዋል። (ያዕ. 3:17) ዓላማቸው፣ የሚቻል ከሆነ ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ‘ከስህተት ጎዳናው እንዲመለስ’ መርዳት ነው። (ያዕ. 5:19, 20) በተጨማሪም ጉባኤውን ለመጠበቅና በተፈጸመው ድርጊት የተጎዱትን ወንድሞችና እህቶች ለማጽናናት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይፈልጋሉ። (2 ቆሮ. 1:3, 4) ሽማግሌዎች አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ሲሰሙ በመጀመሪያ ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ከዚያም ኃጢአት ለፈጸመው ግለሰብ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተመሥርተው ምክር ይሰጣሉ፤ እንዲሁም “በተገቢው መጠን” እርማት ይሰጡታል። (ኤር. 30:11) ሽማግሌዎች ጉዳዩን ሳያስፈልግ ባያጓትቱም ፍርድ ለማሳለፍ አይቸኩሉም። ጉዳዩ በተገቢው መንገድ ሲያዝ መላው ጉባኤ ይጠቀማል። ሆኖም ጉዳዩ በዚህ መንገድ ቢያዝም እንኳ ተበዳዩ ወገን ስሜቱ ሊጎዳ ይችላል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ሥቃዩን ለማቅለል ምን ማድረግ ትችላለህ?
14. አንድ የእምነት ባልንጀራህ ከባድ በደል አድርሶብህ ከሆነ ሁኔታውን ለመቋቋም የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ሊረዳህ ይችላል?
14 አንድ ሰው ምናልባትም የእምነት ባልንጀራህ ከባድ በደል ፈጽሞብህ ያውቃል? ይሖዋ ነገሮችን እስኪያስተካክል ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ግሩም ምሳሌዎችን በአምላክ ቃል ውስጥ ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሴፍ የገዛ ወንድሞቹ ግፍ ቢፈጽሙበትም እንኳ የእነሱ ድርጊት በምሬት እንዲዋጥ አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ትኩረት ያደረገው ለይሖዋ በሚያቀርበው አገልግሎት ላይ ነበር፤ ዮሴፍ በትዕግሥት በመጽናቱ ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኮታል። (ዘፍ. 39:21) ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ግፍ የፈጸሙበትን ሰዎች ይቅር ማለት እንዲሁም የይሖዋ በረከት እንዳልተለየው ማየት ችሏል። (ዘፍ. 45:5) እንደ ዮሴፍ ሁሉ እኛም ወደ ይሖዋ ስንቀርብና ነገሮችን ለእሱ ስንተው እንጽናናለን።—መዝ. 7:17፤ 73:28
15. አንዲት እህታችን የደረሰባትን በደል በትዕግሥት ለማለፍ የረዳት ምንድን ነው?
15 እርግጥ ነው፣ ዮሴፍ እንደደረሰበት ያለ ከባድ ግፍ ላይደርስብን ይችላል፤ ሆኖም ሰዎች መጥፎ ነገር ሲያደርጉብን ስሜታችን መጎዳቱ አይቀርም። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ጨምሮ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ችግር ሲያጋጥመን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላችን ይጠቅመናል። (ፊልጵ. 2:3, 4) አንድ ተሞክሮ እንመልከት። አንዲት እህት የሥራ ባልደረባዋ ስለ እሷ የሐሰት ወሬ እያሰራጨች እንደሆነ ስትሰማ ስሜቷ በጥልቅ ተጎድቶ ነበር። ሆኖም እህታችን በችኮላ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጊዜ ወስዳ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ አሰላሰለች። ኢየሱስ፣ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። (1 ጴጥ. 2:21, 23) ይህን በአእምሮዋ በመያዝ ጉዳዩን ለመተው ወሰነች። ከጊዜ በኋላ እህታችን የሥራ ባልደረባዋ በከባድ የጤና ችግር የተነሳ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደነበረች ተረዳች። እህታችን የሥራ ባልደረባዋ ስለ እሷ መጥፎ ነገር የተናገረችው በክፋት ተነሳስታ ላይሆን እንደሚችል አሰበች። ስለዚህ እህታችን የተፈጸመባትን በደል በትዕግሥት በማለፏ በጣም ተደሰተች፤ ውስጣዊ ሰላምም አገኘች።
16. ግፍ ተፈጽሞብህ ከሆነ ምን ሊያጽናናህ ይችላል? (1 ጴጥሮስ 3:12)
16 በደረሰብህ ግፍ ወይም በሌላ ምክንያት ተጎድተህ ከሆነ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ” እንደሆነ አስታውስ። (መዝ. 34:18) ትዕግሥት በማሳየትህ እንዲሁም ሸክምህን በእሱ ላይ በመጣልህ ይወድሃል። (መዝ. 55:22) ይሖዋ የምድር ሁሉ ዳኛ ነው። ከእሱ እይታ የሚያመልጥ አንድም ነገር የለም። (1 ጴጥሮስ 3:12ን አንብብ።) አንተስ መፍታት የማትችለው ችግር ካጋጠመህ እሱን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነህ?
ይሖዋን በትዕግሥት የሚጠብቁ የሚያገኟቸው ዘላለማዊ በረከቶች
17. በኢሳይያስ 30:18 ላይ ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?
17 በቅርቡ የሰማዩ አባታችን በመንግሥቱ አማካኝነት አትረፍርፎ ይባርከናል። ኢሳይያስ 30:18 እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና። እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።” ይሖዋን የሚጠባበቁ ሁሉ አሁንም ሆነ በመጪው አዲስ ዓለም የተትረፈረፉ በረከቶች ያገኛሉ።
18. የትኞቹ በረከቶች ይጠብቁናል?
18 የአምላክ ሕዝቦች ወደ አዲሱ ዓለም ሲገቡ በዚህ ዓለም ውስጥ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮችና አስጨናቂ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ይገላገላሉ። የፍትሕ መጓደልም ሆነ ሥቃይ አይኖርም። (ራእይ 21:4) የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት አንጨነቅም፤ ምክንያቱም ሁሉ ነገር ይትረፈረፋል። (መዝ. 72:16፤ ኢሳ. 54:13) ያ ጊዜ ምንኛ አስደሳች ይሆን!
19. ይሖዋ ለየትኛው ጊዜ ቀስ በቀስ እያዘጋጀን ነው?
19 ያ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ይሖዋ መጥፎ ልማዶቻችንን እንድናስወግድና እሱን የሚያስደስቱ ባሕርያትን እንድናዳብር በመርዳት በእሱ አገዛዝ ሥር ለሚኖረው ሕይወት እያዘጋጀን ነው። አይዟችሁ፤ ተስፋ አትቁረጡ! አስደሳች ሕይወት ይጠብቃችኋል! ብሩህ ተስፋ ስለተዘረጋልን ይሖዋ ሥራውን እስኪፈጽም ድረስ እሱን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች እንሁን!
መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”
a ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገለ አንድ ክርስቲያን “ይህ ሥርዓት ይህን ያህል ይቆያል ብዬ አላሰብኩም ነበር” ሲል ሰምተህ ታውቃለህ? ያለንበት ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑ አንጻር ሁላችንም ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን። ያም ቢሆን ታጋሾች መሆን አለብን። በትዕግሥት እንድንጠብቅ የሚረዱንን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም በየትኞቹ ሁለት ሁኔታዎች ውስጥ ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለብን እንመረምራለን። በመጨረሻም በትዕግሥት የሚጠብቁ ሰዎች የሚያገኟቸውን በረከቶች እናያለን።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ከልጅነቷ አንስቶ አዘውትራ ወደ ይሖዋ ትጸልያለች። ትንሽ ልጅ ሳለች ወላጆቿ እንዴት መጸለይ እንዳለባት አስተምረዋታል። በወጣትነቷ አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች፤ ይሖዋ አገልግሎቷን እንዲባርክላት አዘውትራ ትጠይቀው ነበር። ከዓመታት በኋላ ባለቤቷ በጠና ሲታመም ይህን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችላትን ኃይል እንዲሰጣት ወደ ይሖዋ ምልጃ ስታቀርብ ይታያል። በአሁኑ ወቅት መበለት ናት፤ የሰማዩ አባቷ ከልጅነቷ ጀምሮ ሲያደርግላት እንደነበረው አሁንም ጸሎቷን እንደሚመልስላት በመተማመን በጽናት ትጸልያለች።