ከጥፋት ድኖ ጽድቅ ወደ ሰፈነበት አዲስ ዓለም መግባት
“በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”— መዝሙር 37:11
1, 2. (ሀ) ይሖዋ በዘመናችን የሚወስደው የማዳን እርምጃ በጥንት ዘመን ከወሰዳቸው የማዳን እርምጃዎች የተለየ የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ሕዝቦቹን ምን ዓይነት ሁኔታ ወደሰፈነበት ዓለም ያስገባቸዋል?
ይሖዋ አዳኝ አምላክ ነው። በጥንት ዘመን ሕዝቦቹን ብዙ ጊዜ አድኗቸዋል። ይሖዋ ጥንት በወሰዳቸው የማዳን እርምጃዎች በመላው የሰይጣን ዓለም ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የቅጣት ፍርዱን ስላልፈጸመ የማዳን እርምጃዎቹ ጊዜያዊ ብቻ ነበሩ። ሆኖም በቅርቡ ይሖዋ ከዚህ ቀደም አገልጋዮቹን ለማዳን ከወሰዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የላቀ የማዳን እርምጃ ይወስዳል። በዚያን ጊዜ ይሖዋ ማንኛውንም የሰይጣን ሥርዓት ርዝራዥ ከምድር ገጽ ጠራርጎ ካጠፋ በኋላ አገልጋዮቹን ጽድቅ ወደ ሰፈነበት ዘላለማዊ አዲስ ዓለም ያስገባቸዋል።— 2 ጴጥሮስ 2:9፤ 3:10-13
2 ይሖዋ አንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:10, 11) ለምን ያህል ጊዜ? “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 5:5) ሆኖም ይህ ከመፈጸሙ አስቀድሞ በዚህ ዓለም ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይከሰታል።
“ታላቁ መከራ”
3. ኢየሱስ “ታላቁን መከራ” የገለጸው እንዴት ነው?
3 ይህ ዓለም ከ1914 ጀምሮ ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ውስጥ ይገኛል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) እነዚህ ቀኖች ከጀመሩ እነሆ 83 ዓመታት የቆጠሩ ሲሆን ወደ ፍጻሜያቸው በመገስገስ ላይ ናቸው፤ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ወደፊት “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:21) አዎን፣ ወደ 50 ሚልዮን የሚጠጋ ሕይወት ካጠፋው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንኳ የከፋ መከራ ይመጣል። ዓለምን የሚያናውጥ ጊዜ በፍጥነት በመቅረብ ላይ ነው!
4. “ታላቂቱ ባቢሎን” የአምላክን ፍርድ የምትቀበለው ለምንድን ነው?
4 “ታላቁ መከራ” ሳይታሰብ “በአንድ ሰዓት” ከተፍ ይላል። (ራእይ 18:10) ታላቁ መከራ የሚጀምረው አምላክ በሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ በሚወስደው የቅጣት እርምጃ ይሆናል፤ የአምላክ ቃል እነዚህን ሃይማኖቶች በአጠቃላይ “ታላቂቱ ባቢሎን” ብሎ ይጠራቸዋል። (ራእይ 17:1-6, 15) የጥንቷ ባቢሎን በይበልጥ የምትታወቀው በሐሰት ሃይማኖት ነበር። ዘመናዊቷ ባቢሎንም ልክ እንደ ጥንት አምሳያዋ ስትሆን ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛትን ትወክላለች። አቋሟን በማላላት ከፖለቲካ ኃይላት ጋር ግልሙትና በመፈጸም ላይ ትገኛለች። ጦርነቶቻቸውን በመደገፍና በሁለቱም ጎራ የተሰለፉ የጦር ሠራዊቶችን በመባረክ የአንድ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲጨፋጨፉ አድርጋለች። (ማቴዎስ 26:51, 52፤ 1 ዮሐንስ 4:20, 21) ተከታዮቿ የሚፈጽሙትን የረከሰ ተግባር በዝምታ ከማለፏም በላይ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ታሳድዳለች።— ራእይ 18:5, 24
5. “ታላቁ መከራ” የሚጀምረው እንዴት ነው?
5 የፖለቲካ ኃይላት ድንገት “በታላቂቱ ባቢሎን” ላይ በሚወስዱት እርምጃ “ታላቁ መከራ” ይጀምራል። የፖለቲካ ኃይላት “ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” (ራእይ 17:16) ከዚያም የቀድሞ ደጋፊዎቿ “ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ።” (ራእይ 18:9-19) ሆኖም የይሖዋ አገልጋዮች ከረጅም ጊዜ በፊት በጉጉት ሲጠብቁት የነበረ ነገር ስለሆነ በደስታ እንዲህ ይላሉ:- “ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፣ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለተበቀለ።”— ራእይ 19:1, 2
በአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት
6, 7. የይሖዋ አገልጋዮች “በታላቁ መከራ” ወቅት ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም ትምክኽት ሊኖራቸው የሚችለው ለምንድን ነው?
6 የፖለቲካ ኃይላት የሐሰት ሃይማኖትን ካጠፉ በኋላ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ይነሳሉ። ‘የማጎጉ ጎግ’ ሰይጣን “ተዘልለው ወደሚኖሩ፣ ሁላቸው ሳይፈሩ . . . ወደሚቀመጡ እገባለሁ” እንደሚል በትንቢት ተነግሯል። የይሖዋ አገልጋዮች በቀላሉ ለጥቃቱ የተጋለጡ እንደሆኑ በማሰብ ‘ምድርን እንደሚሸፍን ደመና በብርቱ የጦር ሠራዊት’ ጥቃት ይሰነዝርባቸዋል። (ሕዝቅኤል 38:2, 10-16) የይሖዋ ሕዝቦች በይሖዋ ስለሚታመኑ ይህ ጥቃት እንደሚከሽፍ ያውቃሉ።
7 ፈርዖንና ሠራዊቱ ቀይ ባሕር አጠገብ የአምላክ ሕዝቦች መዳፋቸው ውስጥ እንደገቡላቸው አድርገው ሲያስቡ ይሖዋ በተዓምራታዊ ሁኔታ ሕዝቦቹን በማዳን የግብፅን ሠራዊት አጠፋ። (ዘጸአት 14:26-28) “በታላቁ መከራ” ወቅት መንግሥታት የይሖዋ ሕዝቦች መዳፋችን ውስጥ ገብተውልናል ብለው በሚያስቡበት ጊዜም ይሖዋ ሕዝቦቹን በተዓምራዊ ሁኔታ ያድናቸዋል። “በዚያም ቀን . . . መቅሰፍቴ በመዓቴ ይመጣል፤ . . . በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ።” (ሕዝቅኤል 38:18, 19) ይህም “የታላቁ መከራ” መደምደሚያ ይሆናል!
8. ይሖዋ በክፉዎች ላይ የቅጣት ፍርዱን ከማስፈጸሙ በፊት ምን የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ የሆኑ ክስተቶች ይታያሉ? ውጤቱስ ምን ይሆናል?
8 “ታላቁ መከራ” ከጀመረ በኋላ፣ ነገር ግን ይሖዋ በቀሪው የዚህ ዓለም ክፍል ላይ የቅጣት ፍርዱን ከማስፈጸሙ ቀደም ብሎ በሆነ ወቅት ላይ የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ የሆኑ ክስተቶች ይታያሉ። እነዚህ ክስተቶች ምን ውጤት እንደሚያስከትሉ ልብ በል። “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።” (ማቴዎስ 24:29, 30) “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል . . . ሰዎችም በፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ።”— ሉቃስ 21:25, 26
“መዳናችሁ ቀርቧል”
9. የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ የሆኑት ክስተቶች በሚታዩበት ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ‘ራሳቸውን ቀና አድርገው’ የሚመለከቱት ለምንድን ነው?
9 በዚያን ጊዜ የሉቃስ 21:28 ትንቢት በቀጥታ ፍጻሜ ያገኛል። ኢየሱስ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ [“መዳናችሁ፣” NW ] ቀርቧልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” ብሏል። የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ የሆኑት ክስተቶች ከይሖዋ የመጡ መሆናቸውን ስለሚያውቁ የአምላክ ጠላቶች በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ። የይሖዋ አገልጋዮች ግን መዳናቸው እንደቀረበ ስለሚያውቁ በጣም ይደሰታሉ።
10. የአምላክ ቃል “የታላቁን መከራ” መደምደሚያ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?
10 ይሖዋ የሰይጣንን ሥርዓት ድባቅ ይመታዋል። “[ጎግን] በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። . . . እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW ] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” (ሕዝቅኤል 38:22, 23) የሰይጣን ሥርዓት ድምጥማጡ ይጠፋል። አምላክን ለመቀበል እምቢተኛ የሆነው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ተጠራርጎ ይወድማል። ያን ጊዜ “የታላቁ መከራ” ክፍል የሆነው አርማጌዶን መደምደሚያ ይሆናል።— ኤርምያስ 25:31-33፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-8፤ ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-21
11. የይሖዋ አገልጋዮች “ከታላቁ መከራ” የሚድኑት ለምንድን ነው?
11 “ከታላቁ መከራ” የሚድኑት በምድር ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ አምላኪዎች ይሆናሉ። እነዚህም “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ናቸው። እንዲህ በአስደናቂ ሁኔታ መዳን የሚያገኙት ለምንድን ነው? ‘ሌሊትና ቀን ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት’ ስለሚያቀርቡ ነው። ስለዚህ ከዚህ ዓለም የመጨረሻ ዕጣ በሕይወት ተርፈው ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም ይገባሉ። (ራእይ 7:9-15) “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ” ሲል ይሖዋ የገባው ቃል በዚህ መንገድ ሲፈጸም ያያሉ።— መዝሙር 37:34
አዲሱ ዓለም
12. ከአርማጌዶን የተረፉት ምን ነገር በጉጉት ሊጠባበቁ ይችላሉ?
12 ክፋት ጠፍቶ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ ክብራማ ዘመን ሲጠባ ማየት እንዴት የሚያስደስት ይሆናል! (ራእይ 20:1-4) የአርማጌዶን ተራፊዎች ወደ ገነትነት በሚለወጥ ምድር ላይ አምላክ ወደ አዘጋጀው ብሩህና ንጹህ አዲስ ዓለም ሲገቡ ይሖዋን ምንኛ ያመሰግኑታል! (ሉቃስ 23:43) ሞትን ሳይቀምሱ ለዘላለም ይኖራሉ! (ዮሐንስ 11:26) አዎን፣ ከዚያም ይሖዋ ዘላለማዊ እንደሆነ ሁሉ እነሱም ለዘላለም በሕይወት የመኖር አስደናቂ ተስፋ ይኖራቸዋል!
13. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የጀመረውን የመፈወስ ተግባር እንደገና የሚቀጥለው እንዴት ነው?
13 ከጥፋት የዳኑት ሰዎች የሚያገኙትን ተአምራታዊ በረከት በበላይነት የሚቆጣጠረው ይሖዋ በሰማይ ንጉሥ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ነው። ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የዕውሮች ዓይን እንዲያይ፣ የደንቆሮዎች ጆሮ እንዲሰማ አድርጓል፤ እንዲሁም ‘ማንኛውንም ደዌና ሕመም’ ፈውሷል። (ማቴዎስ 9:35፤ 15:30, 31) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይህን ታላቅ የመፈወስ ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደገና ይቀጥላል። የአምላክ ወኪል እንደመሆኑ መጠን “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” የሚለው ተስፋ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ራእይ 21:4) ከዚያም በኋላ የሕክምና ባለሙያዎች ወይም መቃብር ቆፋሪዎች ጨርሶ አያስፈልጉም።— ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24
14. ቀደም ሲል የሞቱት የይሖዋ አገልጋዮች ምን መዳን ያገኛሉ?
14 በተጨማሪም ቀደም ባሉ ጊዜያት የሞቱ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ መዳን ያገኛሉ። ከተቀበሩበት መቃብር መዳፍ ተላቅቀው ወደ አዲሱ ዓለም ይመጣሉ። ይሖዋ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን እንደሚነሱ’ ዋስትና ሰጥቷል። (ሥራ 24:15) “ጻድቃን” ቀደም ብለው ትንሣኤ በማግኘት ገነትን በማስፋፋቱ ሥራ እገዛ ሳያደርጉ አይቀርም። ከረጅም ዘመን በፊት ሞተው የነበሩ ታማኞች ወደ ሕይወት ተመልሰው ተሞክሯቸውን ሲናገሩ መስማት ከአርማጌዶን ለተረፉት ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል!— ዮሐንስ 5:28, 29
15. በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖሩትን አንዳንድ ሁኔታዎች ግለጽ።
15 ከዚያም በሕይወት ያሉ ሁሉ መዝሙራዊው “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” በማለት ስለ ይሖዋ የተናገረው ሲፈጸም ይመለከታሉ። (መዝሙር 145:16) ፈጽሞ ረሃብ አይኖርም፤ ምድር ከባቢያዊ ሚዛኗ ተስተካክሎ የተትረፈረፈ ምርት ትሰጣለች። (መዝሙር 72:16) የመኖሪያ ቤት እጦት ፈጽሞ ይወገዳል፤ “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤” እንዲሁም እያንዳንዱ “ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።” (ኢሳይያስ 65:21, 22፤ ሚክያስ 4:4) ጦርነት፣ ዓመፅ ወይም ወንጀል ስለማይኖር ፍርሃት የሚባል ነገር ፈጽሞ አይኖርም። (መዝሙር 46:8, 9፤ ምሳሌ 2:22) “ዓለም ሁሉ የሰላም ዕረፍት ያገኛል፤ ሁሉም በደስታ ይዘምራል።”— ኢሳይያስ 14:7 የ1980 ትርጉም
16. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ጽድቅ የሚሰፍነው ለምንድን ነው?
16 ሰይጣን ፕሮፓጋንዳውን የሚያሰራጭበት የመገናኛ ብዙሃን ይወገዳል። በዚያ ፋንታ “በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉ።” (ኢሳይያስ 26:9፤ 54:13) ከዓመት ዓመት የሚተላለፈው ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ መመሪያ ስለሆነ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:9) ገንቢ አስተሳሰብና ተግባር በሰዎች ውስጥ ይሰርጻል። (ፊልጵስዩስ 4:8) እስቲ አስቡት፣ ከወንጀል፣ ከራስ ወዳድነትና ከቅናት ነፃ የሆነ ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ማለትም እያንዳንዳቸው የአምላክን መንፈስ ፍሬ የሚያፈሩ አባላት ያሉት አንድ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ይመሠረታል። እጅግ ብዙ ሰዎች አሁንም እንኳ እንደዚህ የመሰሉትን ባሕርያት በመኮትኮት ላይ ናቸው።— ገላትያ 5:22, 23
ይህን ያህል የዘገየው ለምንድን ነው?
17. ይሖዋ ክፋትን ሳያጠፋ እስከ አሁን ድረስ የቆየው ለምንድን ነው?
17 ሆኖም ይሖዋ ክፋትን በማስወገድና ሕዝቦቹን በማዳን ወደ አዲስ ዓለም ለማስገባት ይህን ያህል የዘገየው ለምንድን ነው? ምን መከናወን እንደነበረበት ልብ በሉ። ከሁሉ አስቀድሞ የይሖዋ ሉዓላዊነት ማለትም የመግዛት መብቱ መረጋገጥ ነበረበት። ይሖዋ በቂ ጊዜ በመፍቀድ ከእሱ ሉዓላዊ ገዥነት ውጭ ያለ ሰብዓዊ አገዛዝ ሁሉ ትልቅ ውድቀት እንደሚያስከትል በማያሻማ ሁኔታ እንዲረጋገጥ አድርጓል። (ኤርምያስ 10:23) ስለዚህ ይሖዋ አሁን ሰብዓዊ አገዛዝን በክርስቶስ በሚመራው ሰማያዊ መንግሥቱ ለመተካት በቂ ምክንያት አለው።— ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10
18. የአብርሃም ዝርያዎች የከነዓንን ምድር የሚወርሱት መቼ ነበር?
18 በእነዚህ ሁሉ መቶ ዘመናት ውስጥ የተከናወነው ነገር በአብርሃም ዘመን ከተከናወነው ነገር ጋር የሚመሳሰል ነው። ዘሮቹ የከነዓንን ምድር እንደሚወርሱ ይሖዋ ለአብርሃም ነግሮት ነበር፤ ሆኖም ‘የአሞራውያን ኃጢአት ገና ስላልተፈጸመ’ አራት መቶ ዓመት መጠበቅ ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 12:1-5፤ 15:13-16) እዚህ ላይ የተጠቀሱት “አሞራውያን” (ትልቁ ነገድ) በከነዓን ምድር የሚኖሩትን ሕዝቦች በጠቅላላ ሳያመለክቱ አይቀሩም። ስለዚህ ይሖዋ ሕዝቦቹ የከነዓንን ምድር እንዲወርሱ ከማድረጉ በፊት ወደ አራት መቶ የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በከነዓን የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ኅብረተሰብ እንዲመሠርቱ ፈቅዶላቸዋል። ውጤቱ ምን ሆነ?
19, 20. ከነዓናውያን ምን ዓይነት ኅብረተሰብ ሆነው ነበር?
19 በሄንሪ ኤች ሃሊይ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ (በእንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ አርኪኦሎጂስቶች የበኣል ሚስት የሆነች አሽቶሬት የተባለችውን ሴት አምላክ ቤተ መቅደስ በመጊዶ ውስጥ እንዳገኙ ይገልጻል። እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ከዚህ ቤተ መቅደስ ጥቂት እርምጃዎች ራቅ ብሎ አንድ መካነ መቃብር ይገኛል፤ በመካነ መቃብሩ ውስጥ በዚህ ቤተ መቅደስ ለመሥዋዕትነት የቀረቡ ሕፃናትን አፅም የያዙ በርካታ ማሰሮዎች ተገኝተዋል። . . . የበኣልና የአሽቶሬት ነቢያት ሕፃናትን በመጨፍጨፍ የታወቁ ነበሩ።” “ሌላው ዘግናኝ ድርጊት ‘የመሠረት መሥዋዕት’ የሚሉት ነው። ቤት ሊሠሩ ሲሉ አንድ ልጅ ይሠዉና አካሉን ከግድግዳው ጋር ይገነቡታል።”
20 ሃሌይ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “የበኣል፣ የአሽቶሬትና የሌሎች ከነዓናውያን አማልክት አምልኮ በጣም የተንዛዙ ምስጢራዊ የአምልኮ ሥርዓቶችን ያቀፉ ነበሩ፤ ቤተ መቅደሶቻቸው አስነዋሪ ድርጊት የሚፈጸምባቸው ማዕከሎች ነበሩ። . . . ከነዓናውያን የአምልኮ ሥርዓታቸውን የሚያከናውኑት የጾታ ብልግና በመፈጸምና . . . ከዚያም የመጀመሪያ ልጆቻቸውን አርደው ለእነዚሁ አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ነበር። የከነዓን ምድር በጠቅላላ ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሆኖ ነበር። . . . እንዲህ ያለ አጸያፊ ድርጊትና የጭካኔ ተግባር ይፈጽም የነበረ ኅብረተሰብ እንዳለ የመቀጠል መብት ይኖረዋልን? . . . የከነዓናውያንን ከተሞች ፍርስራሽ ቆፍረው ጥናት ያደረጉ እርኪኦሎጂስቶች አምላክ ለምን ከዚያ ቀደም ብሎ እንዳላጠፋቸው በጣም ይገርማቸዋል።”— ከ1 ነገሥት 21:25, 26 ጋር አወዳድር።
21. በከነዓናውያን ሁኔታና በእኛ ዘመን መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
21 የአሞራውያን ኃጢአት “ተፈጸመ።” በመሆኑም ይሖዋ እነሱን ለማጥፋት በቂ ምክንያት ነበረው። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህ ዓለም በዓመፅ፣ በጾታ ብልግናና ለአምላክ ሕጎች ንቀት በማሳየት ተሞልቷል። በጥንቷ ከነዓን በተፈጸመው ሕፃናትን በጭካኔ መሥዋዕት የማድረግ ተግባር የምንዘገነን ከሆነ ዛሬ ይህ ዓለም በሚያደርጋቸው ጦርነቶች በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች መሥዋዕት መሆን በከነዓን ከተፈጸመው ይበልጥ የሚዘገንን አይደለምን? እንዴታ፣ አሁን ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ለማምጣት በቂ ምክንያት አለው።
አንድ ሌላ ነገር ማከናወን
22. ይሖዋ በመታገሡ በዘመናችን ምን ተከናውኗል?
22 የይሖዋ ትዕግሥት በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ውስጥ አንድ ሌላ ነገር በማከናወን ላይ ነው። እጅግ ብዙ ሰዎችን ለመሰብሰብና ለማስተማር ጊዜ የፈቀደ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከአምስት ሚልዮን በላይ ሆኗል። በይሖዋ አመራር ሥር በመሆን ወደፊት በመገስገስ ላይ ባለ አንድ ድርጅት ተደራጅተዋል። ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለሌሎች እንዲያስተምሩ ሰልጥነዋል። በስብሰባዎቻቸውና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸው አማካኝነት የአምላክን ፍቅራዊ መንገዶች ይማራሉ። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ ቆላስይስ 3:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ከዚህም በተጨማሪ ‘የምሥራቹን’ ስብከት ለመደገፍ ሲሉ በግንባታ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በኅትመት ሥራና በሌሎች መስኮች ችሎታዎቻቸውን በማዳበር ላይ ይገኛሉ። (ማቴዎስ 24:14) እንዲህ ዓይነቱ የማስተማርና የግንባታ ችሎታ በአዲሱ ዓለም ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ሳይውል አይቀርም።
23. በዚህ ዘመን በሕይወት መኖር ትልቅ መብት የሆነው ለምንድን ነው?
23 አዎን፣ “ታላቁን መከራ” አልፈው ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም እንዲገቡ ይሖዋ አገልጋዮቹን በማዘጋጀት ላይ ነው። በዚያን ጊዜ ከሰይጣንና እሱ ከሚቆጣጠረው ዓለም እንገላገላለን፤ በሽታ፣ ሐዘንና ሞት አይኖሩም። የአምላክ ሕዝቦች በጋለ ስሜትና በደስታ ገነትን የመገንባት አስደሳች ሥራቸውን ይቀጥላሉ፤ እያንዳንዱ ቀን ‘አስደሳች’ ይሆናል። በዚህ የፍጻሜ ዘመን ላይ መኖራችን፣ ይሖዋን ማወቃችንና ማገልገላችን እንዲሁም ‘መዳናችን በመቅረቡ ራሳችንን ቀና አድርገን ወደ ላይ የምንመለከትበት’ ጊዜ በጣም እንደቀረበ ማወቃችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!— ሉቃስ 21:28፤ መዝሙር 146:5
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ “ታላቁ መከራ” ምንድን ነው? እንዴትስ ይጀምራል?
◻ ጎግ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሚሠነዝረው ጥቃት የሚከሽፈው ለምንድን ነው?
◻ “ታላቁ መከራ” የሚደመደመው እንዴት ነው?
◻ አዲሱ ዓለም ምን ግሩም በረከቶችን ይዟል?
◻ ይሖዋ ይህን ሥርዓት ሳያጠፋ እስከ አሁን ድረስ የቆየው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መላዋ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች