የልቡ ምኞት ተፈጸመለት
መሲሐዊቷ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ ስትገዛ ለማየት ልብህ ይናፍቃልን? እንግዲያው የሰማያዊቷ መንግሥት በረከቶች እንዲመጡ ትጓጓለህ፣ ትጸልያለህ። ግን ታገሥ፤ ‘የተገኘች ፈቃድ የሕይወት ዛፍ ናትና።’—ምሳሌ 13:12፤ ያዕቆብ 5:7, 8
ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት በኢየሩሳሌም የሚኖር ስምዖን የሚባል ‘ጻድቅና ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው’ ነበረ። ስለ መሲሑ በሚናገሩት ትንቢቶች ያምን ስለነበር “የእስራኤልን መጽናናት” በትዕግሥት “ይጠባበቅ” ነበር።—ሉቃስ 2:25
መሲሐዊ ትንቢቶች ተስፋ ይሰጣሉ
ስለ መሲሑ የሚገልጸውን የመጀመሪያ ትንቢት የተናገረው ይሖዋ ነበር። ይህ ትንቢት ኃጢአተኛና ሟች ለሆኑት የሰው ልጆች ተስፋ የሚሰጥ ነው። አምላክ ‘የሴቲቱ’ ማለትም የጽንፈ ዓለማዊ ድርጅቱ ዘር እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር።—ዘፍጥረት 3:15
ይህ ዘር ከአብርሃም ዘር እንደሚመጣ ታወቀ። ያዕቆብም ስለዚህ ዘር አመጣጥ ተንብዮአል። (ዘፍጥረት 22:17, 18፤ 49:10) የመሲሐዊቷ መንግሥት ግርማ በመዝሙራት ውስጥ ተነግሯል። (መዝሙር 72:1–20) ኢሳይያስ ይህ ዘር ከድንግል እንደሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፤ ሚክያስም የሚወለደው በቤተልሔም መሆኑን ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 7:14፤ ሚክያስ 5:2) እነዚህ ስለ መሲሑ ከሚናገሩት ብዙ ትንቢቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
መሲሑ አሁንም አልመጣም!
እስቲ ጥንት ስለነበረው ሁኔታ እናስብ። የመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ እየተቃረበ ሳለ የሚኖረውን ሁኔታ እንገምት። አምላክ ስለ መሲሑ የሚናገረውን የመጀመሪያ ትንቢት ከተናገረ 4,000 ዓመታት አልፈዋል። አይሁዳውያን የይሖዋ ቤተ መቅደስ ሲጠፋ እንዲሁም የትውልድ አገራቸው ስትፈራርስ ተመልክተዋል። ለ70 ዓመት በባቢሎን በግዞት ከመቆየታቸውም በላይ 500 ዓመት ለሚያክል ጊዜ በአሕዛብ ገዥዎች ተገዝተዋል። ይሁን እንጂ አሁንም መሲሑ አልመጣም!
ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አይሁዳውያን የመሲሑን መምጣት ለማየት በጣም ጓጉተዋል። መሲሑ ለነሱና ለአሕዛብ ሁሉ በረከትን ያፈሳል።
ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው
የመሲሑን መምጣት በጉጉት ይጠባበቁና እንዲመጣ ይጸልዩ ከነበሩት ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው አይሁዳውያን መካከል በይሁዳ ዋና ከተማ የሚኖር ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የነበረው አረጋዊው ስምዖን አንዱ ነበር። ስምዖን አንድ ልዩ ነገር አጋጠመው።
አምላክ መንፈስ ቅዱሱን በስምዖን ላይ በማድረግ አንድ ራእይ አሳይቶት ነበር። ስምዖን መሲሕ የሚሆነውን ሳያይ አይሞትም። ግን ቀናትና ወራት እያለፉ ሄዱ። ስምዖን እያረጀ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ ብዙ እኖራለሁ ብሎ ሊያስብ አይችልም። አምላክ የሰጠው ተስፋ ይፈጸም ይሆን?
አንድ ቀን (በ2 ከዘአበ) አንድ ሕፃን የያዙ ወጣት ባልና ሚስት ከቤተ ልሔም ወደ ቤተ መቅደሱ መጡ። መንፈስ ቅዱስም ለስምዖን ለረጅም ጊዜ ሲጠብቀው የቆየው ዕለት ይህ እንደሆነ ገለጠለት። ነቢያት ስለ እርሱ የጻፉትን ልጅ ለማየት ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደ። በእርጅና የተዳከመው አካሉ የፈቀደለትን ያህል እየተቻኮለ ሄዶ ዮሴፍን፣ ማርያምንና ሕፃኑን አያቸው።
ስምዖን ሕፃኑን ኢየሱስን ሲያቅፈው ምን ያህል ደስ ብሎት ይሆን! ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንዲሁም ‘የይሖዋ ክርስቶስ’ የሚሆነው ይህ ሕፃን ነው። ስምዖን በጣም ስላረጀ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበትን ተልዕኰ ሲፈጽም አያለሁ ብሎ ተስፋ ሊያደርግ አይችልም። ቢሆንም በሕፃንነቱ እንኳን ሊያየው መቻሉ በጣም አስደስቶታል። ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች መፈጸም ሊጀምሩ ነው። ስምዖን ምን ያህል ተደስቶ ይሆን! ይህን ከተመለከተ መንፈሱ ረክቶ ትንሣኤ እስኪያገኝ ድረስ በሞት ሊያሸልብ ይችላል።—ሉቃስ 2:25–28
የስምዖን ትንቢታዊ ቃላት
ስምዖን ጮክ ብሎ ይሖዋን በማወደስ እንዲህ ሲል እንሰማዋለን፦ “ጌታ ሆይ፣ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” የኢየሱስ አሳዳጊ አባት የሆነው ዮሴፍና እናቱ ማርያም በዚህ አነጋገሩ ተገረሙ።—ሉቃስ 2:29–33
ስምዖን ዮሴፍንና ማሪያምን ሲመርቃቸው ፊቱ ብሩህ ሆኖ ነበር። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ልጁን እንዲያሳድጉ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ይሖዋ እንዲባርካቸው ያለውን ምኞት ገልጾላቸዋል። ከዚያም አረጋዊው ሰው ፊቱን ኮስተር አድርጎ ማሪያምን “እነሆ፣ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፣ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፣ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል” አላት።—ሉቃስ 2:34, 35
ስምዖን ለማርያም የነገራት ቃል
ማርያም ምን እንደተሰማት ገምት። ስምዖን ምን ማለቱ ነበር? አንዳንዶች ክርስቶስን ተቀብለው ከነበሩበት ውድቀት ይነሣሉ። ሌሎች ደግሞ ስለማይቀበሉት ተሰናክለውበት ይወድቃሉ። አስቀድሞ እንደተነገረው ኢየሱስ ለብዙ አይሁዶች የመሰናከያ ድንጋይ ሆኗል። (ኢሳይያስ 8:14፤ 28:16) የስምዖን አነጋገር እስራኤላውያን ግለሰቦች በመጀመሪያ እርሱን ባለማመናቸው ይወድቁና ከዚያ ደግሞ ኢየሱስን አምነው በመቀበል ይነሣሉ ማለት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የተለያዩ ግለሰቦች ለኢየሱስ የሚያሳዩት ስሜት የተለያየ እንደሚሆን፣ ይህም የብዙዎችን የልብ አሳብ የሚገልጥና አምላክ እንዲፈርድላቸው አለዚያም እንዲፈርድባቸው እንደሚያደርግ የሚገልጽ ነው። እርሱ ላላመኑት ምልክት ይሆናል። ሌሎች በእርሱ በማመናቸው በበደላቸውና በኃጢአታቸው ከመሞት ድነው በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ያገኛሉ። ሰዎች መሲሑን መቀበላቸውና አለመቀበላቸው በልባቸው ውስጥ ምን እንዳለ ያሳያል።
“በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል” የሚለው የስምዖን አነጋገርስ ምን ማለት ነው? በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ማርያም ቃል በቃል በሰይፍ እንደተወጋች የሚያመለክት ቦታ የለም። ሆኖም አብዛኛው ሕዝብ ኢየሱስን አለመቀበሉ ያሳዝናታል። ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተቸንክሮ ማየቷ ማሪያምን ምን ያህል አስጨንቋት ይሆን! ይህ ለሷ ልክ በሰይፍ እንደመወጋት ያህል ነበር።
ስምዖን ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች በኢየሱስ እንደሚፈጸሙ አመልክቷል
ስምዖን ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች በኢየሱስ ላይ እንደሚፈጸሙ እንዲገልጽ በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቷል። ስምዖን ‘ዓይኑ በሰዎች ሁሉ ፊት አምላክ ያዘጋጀውን ማዳኑንና ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጠውን ብርሃን ለሕዝቡም ለእስራኤል ክብር የሆነውን ስላዩ’ በሰላም ወይም በጸጥታ ይሞታል። (ሉቃስ 2:30–32) በዚህ አነጋገሩ የኢሳይያስን ትንቢታዊ ቃላት በሚገባ ተጠቅሞባቸዋል።
ነቢዩ እንዲህ በማለት ተንብዮ ነበር፦ “የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፣ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል።” “[እኔ ይሖዋ አንተን መሲሑን] እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ።” (ኢሳይያስ 40:5፤ 42:6፤ 49:6፤ 52:10) ለአሕዛብ ሁሉ እውነተኛ ብርሃን የሆነው፣ በመንፈሳዊ ጨለማ የጋረዳቸውን መሸፈኛ የሚገልጠውና ለሕዝብ ሁሉ ደኅንነት የሚያመጣው መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችና የተፈጸሙት ሁኔታዎች ይመሰክራሉ።
የአምላክ ቃል ስለ አረጋዊው ስምዖን ከዚህ ሌላ ምንም ተጨማሪ ነገር አይናገርም። ስምዖን የሞተው ክርስቶስ ለሰማያዊ ሕይወት የሚያበቃውን መንገድ ከመክፈቱ በፊት እንደሆነ ከሁኔታዎቹ መረዳት እንችላለን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስምዖን ትንሣኤ አግኝቶ በምድር ላይ ይኖራል። እርሱም ሆነ አንተ በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ሥር በሚገዛው በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ መኖር ምን ያህል ያስደስታችሁ ይሆን!