ይሖዋ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ያመጣል
“ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፣ . . . ለእርሱ [ለአምላክ] ተገብቶታልና።”—ዕብራውያን 2:10
1. ይሖዋ ለሰው ዘር ያለው ዓላማ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ምድርን ሲፈጥር የነበረው ዓላማ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ቤተሰብ ፍጻሜ በሌለው ሕይወት ተደስቶ እንዲኖርባት ነበር። (መክብብ 1:4፤ ኢሳይያስ 45:12, 18) እርግጥ አባታችን አዳም ኃጢአት በመሥራቱ ለልጆቹ ኃጢአትንና ሞትን አውርሷል። ይሁን እንጂ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ተስፋ በተሰጠበት ዘር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ፍጻሜውን ያገኛል። (ዘፍጥረት 3:15፤ 22:18፤ ሮሜ 5:12-21፤ ገላትያ 3:16) ይሖዋ ለሰው ዘር ዓለም ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስም እንዲሁ በፍቅር ተገፋፍቶ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ’ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ይህ “ተመጣጣኝ ቤዛ” አዳም ያሳጣንን መብትና ተስፋ ሁሉ እንድናገኝ በማድረግ ለዘላለም ሕይወት ያበቃናል።—1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6 NW፤ ዮሐንስ 17:3
2. የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያከናውነው ነገር በእስራኤላውያን ዓመታዊ የስርየት ቀን በምሳሌያዊ ሁኔታ የተገለጸው እንዴት ነው?
2 የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያከናውነው ተግባር በዓመታዊው የስርየት ቀን በምሳሌያዊ ሁኔታ ተገልጿል። በዚያ ዕለት የእስራኤል ሊቀ ካህናት ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ይሠዋና ደሙን በመገናኛው ድንኳን (ከጊዜ በኋላም በቤተ መቅደሱ) ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ባለው ቅዱስ ታቦት ፊት ያቀርበዋል። ይህን የሚያደርገው ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለሌዊ ነገድ ነበር። በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስ የደሙን ዋጋ ለአምላክ ያቀረበው በመጀመሪያ የመንፈሳዊ ‘ወንድሞቹን’ ኃጢአት ለመሸፈን ነው። (ዕብራውያን 2:12፤ 10:19-22፤ ዘሌዋውያን 16:6, 11-14) ከዚህም በተጨማሪ በስርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ ፍየል ይሠዋና በክህነት የማያገለግሉትን የቀሩትን 12 የእስራኤል ነገዶች ኃጢአት ለማስተሰረይ ደሙን ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይዞ ይገባ ነበር። በተመሳሳይም ሊቀ ካህኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የሚያምኑ የሰው ዘሮችን ኃጢአት ለመደምሰስ ደመ ሕይወቱን አፍስሷል።—ዘሌዋውያን 16:15
ወደ ክብር መጥተዋል
3. በዕብራውያን 2:9, 10 መሠረት አምላክ ለ1,900 ዓመታት ምን ሲያደርግ ቆይቷል?
3 አምላክ 1,900 ለሚያክሉ ዓመታት ከኢየሱስ ‘ወንድሞች’ ጋር የተያያዘ አስገራሚ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። ይህን ጉዳይ በሚመለከት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፣ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን። ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፣ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ [ለይሖዋ አምላክ]፣ ለእርሱ ተገብቶታልና።” (ዕብራውያን 2:9, 10) በምድር ላይ ሰው ሆኖ ሲኖር ሳለ ከደረሰበት መከራ ፍጹም ታዛዥነትን የተማረው የመዳን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዕብራውያን 5:7-10) የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ በመንፈስ የተወለደው የመጀመሪያው አካል ኢየሱስ ነው።
4. ኢየሱስ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ የተወለደው መቼና እንዴት ነበር?
4 ኢየሱስን ወደ ሰማያዊ ክብር ለማምጣት ሲል ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ ወይም በአንቀሳቃሽ ኃይሉ አማካኝነት መንፈሳዊ ልጁ ሆኖ እንዲወለድ አድርጓል። ኢየሱስና አጥማቂው ዮሐንስ ብቻቸውን ሳሉ ራሱን ለአምላክ ማቅረቡን ለማሳየት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ተጠመቀ። የሉቃስ የወንጌል ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፣ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።” (ሉቃስ 3:21, 22) ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ ሲወርድ ከማየቱም ሌላ ይሖዋ የምወደው ልጄ በማለት እንደተቀበለው በግልጽ ሲናገር ሰምቷል። ይሖዋ ‘ወደ ክብር ከሚያመጣቸው ብዙ ልጆች’ መካከል ኢየሱስ የመጀመሪያው መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ እንዲወለድ ያደረገው በዚህ ጊዜ ነበር።
5. የኢየሱስ መሥዋዕት የመጀመሪያ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ቁጥራቸውስ ስንት ነው?
5 ከኢየሱስ መሥዋዕት የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሆኑት ‘ወንድሞቹ’ ናቸው። (ዕብራውያን 2:12-18) ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ፣ በሰማያዊው የጽዮን ተራራ ከበጉ ማለትም ከሞት ከተነሣው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ክብር ተቀዳጅተው ተመልክቷል። ዮሐንስ ስለ ቁጥራቸውም እንዲህ ሲል ገልጿል:- “አየሁም፣ እነሆም፣ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። . . . ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።” (ራእይ 14:1-5) በመሆኑም በሰማይ ‘ወደ ክብር የሚመጡት ብዙ ልጆች’ ጠቅላላ ቁጥር 144,001 ብቻ ነው፤ እነርሱም ኢየሱስና መንፈሳዊ ወንድሞቹ ናቸው።
“ከእግዚአብሔር የተወለደ”
6, 7. ‘ከአምላክ የተወለዱት’ እነማን ናቸው? ይህስ ለእነርሱ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
6 በመንፈስ የተወለዱት የይሖዋ ልጆች ‘ከአምላክ የተወለዱ ናቸው።’ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ስላሉት ግለሰቦች ሲጽፍ እንደሚከተለው ብሏል:- “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፣ ዘሩ [የይሖዋ ዘር] በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።” (1 ዮሐንስ 3:9) ይህ ‘ዘሩ’ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። ይህ ቅዱስ መንፈስ ከአምላክ ቃል ጋር ተዳምሮ 144,000ዎቹ እያንዳንዳቸው ለሰማያዊ ተስፋ ‘ሁለተኛ እንዲወለዱ’ አስችሏቸዋል።—1 ጴጥሮስ 1:3-5, 23
7 ፍጹም የነበረው አዳም “የእግዚአብሔር ልጅ” እንደነበር ሁሉ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ሲወለድም የአምላክ ልጅ ነበር። (ሉቃስ 1:35፤ 3:38) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ይሖዋ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል” ማለቱ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር ነበር። (ማርቆስ 1:11) አምላክ ከዚህ መግለጫ ጋር በማያያዝ መንፈስ ቅዱስን ማፍሰሱ ኢየሱስን መንፈሳዊ ልጁ አድርጎ እንደተቀበለው በግልጽ የሚያሳይ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በሰማይ ዳግም የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ የመሆንን መብት እንዲያገኝ ‘ሁለተኛ የተወለደ’ ያክል ነበር። 144,000 ወንድሞቹም እንዲሁ ‘ዳግም ተወልደዋል።’ (ዮሐንስ 3:1-8፤ መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 15, 1992 ገጽ 3-6ን ተመልከት።) እንዲሁም ልክ እንደ ኢየሱስ በአምላክ ተቀብተው ምሥራቹን የማወጅ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል።—ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:16-21፤ 1 ዮሐንስ 2:20
የመንፈሳዊ ልጅነት ማረጋገጫ
8. (ሀ) ኢየሱስ (ለ) የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ እንደተወለዱ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ነበር?
8 ኢየሱስ በመንፈስ መወለዱን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነበር። አጥማቂው ዮሐንስ በኢየሱስ ላይ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ ከመመልከቱም ሌላ አምላክ አዲስ ስለተቀባው መሲሕ መንፈሳዊ ልጅነት ሲናገር ሰምቷል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ መወለዳቸውን እንዴት ያውቃሉ? ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገበት ዕለት “ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሥራ 1:5) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ‘በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀዋል።’ መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰ ጊዜ ‘እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ’ የመጣ ሲሆን ‘እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖችም’ በእያንዳንዳቸው ላይ ታይተዋል። እጅግ የሚያስገርመው ደግሞ “መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች” መናገር መጀመራቸው ነበር። በመሆኑም የክርስቶስ ተከታዮች የአምላክ ልጆች በመሆን ወደ ሰማያዊ ክብር የሚሄዱበት በር እንደተከፈተላቸው የሚያረጋግጥ በዓይን የሚታይም ሆነ በጆሮ የሚደመጥ ማስረጃ ነበር።—ሥራ 2:1-4, 14-21፤ ኢዩኤል 2:28, 29
9. የሰማርያ ሰዎች፣ ቆርኔሌዎስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሌሎችም በመንፈስ እንደተወለዱ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ነበር?
9 ከዚያ ጥቂት ቆይቶ ወንጌላዊው ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄዶ ሰበከ። የሰማርያ ሰዎች መልእክቱን ተቀብለው ቢጠመቁም አምላክ መንፈሳዊ ልጆቹ አድርጎ እንደተቀበላቸው የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አልነበረም። ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸለዩላቸውና በእነዚህ አማኞች ላይ እጃቸውን በጫኑባቸው ጊዜ ለተመልካች ግልጽ በሆነ መንገድ ‘መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።’ (ሥራ 8:4-25) ይህ፣ ያመኑት የሰማርያ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች መሆናቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነበር። በተመሳሳይም በ36 እዘአ ቆርኔሌዎስና ሌሎች አሕዛብ የአምላክን እውነት ተቀበሉ። ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት አይሁዳውያን አማኞች “በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።” (ሥራ 10:44-48) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች በልሳን እንደመናገር ያሉትን ‘የመንፈስ ስጦታዎች’ ተቀብለዋል። (1 ቆሮንቶስ 14:12, 32) በዚህ መንገድ እነዚህ ግለሰቦች በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች ስለመሆናቸው ግልጽ ማስረጃ አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የመጡት ክርስቲያኖች በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች መሆን አለመሆናቸውን እንዴት ያውቃሉ?
የመንፈሱ ምሥክርነት
10, 11. በሮሜ 8:15-17 መሠረት መንፈሱ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ወራሾች ለሚሆኑት ሰዎች የሚመሠክርላቸው በምን መንገድ ነው?
10 እነዚህ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ የአምላክ መንፈስ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ አላቸው። ጳውሎስ ይህን በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8:15-17) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሰማያዊ አባታቸው ልጆች እንደሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ኃይለኛ የልጅነት መንፈስ አላቸው። (ገላትያ 4:6, 7) ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት ወራሾች ለመሆን የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሆነው በመንፈስ ቅዱስ እንደተወለዱ ፍጹም እርግጠኛ ናቸው። በዚህ ረገድ የይሖዋ መንፈስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
11 በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ግፊት የቅቡዓኑን መንፈስ ወይም በውስጣቸው ያለው ብርቱ ስሜት የአምላክ ቃል ስለ ሰማያዊ ተስፋ ለሚናገረው ነገር አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ግድ ይላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች የሚናገረውን ነገር ሲያነቡ እነዚህ ቃላት ለእነርሱ እንደተነገሩ ሆኖ ይሰማቸዋል። (1 ዮሐንስ 3:2) ‘ወደ ኢየሱስ ክርስቶስና’ ወደ ሞቱ እንደተጠመቁ ያውቃሉ። (ሮሜ 6:3) ሞተው እንደ ኢየሱስ ለሰማያዊ ክብር ትንሣኤ የሚያገኙ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች እንደሆኑ የጸና እምነት አላቸው።
12. የአምላክ መንፈስ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ውስጥ ምን ተክሏል?
12 መንፈሳዊ ልጆች በመሆን በመንፈስ መወለድ ኮትኩተን የምናሳድገው ፍላጎት አይደለም። በመንፈስ የተወለዱት ሰዎች ወደ ሰማይ መሄድ የሚፈልጉት ዛሬ በምድር ላይ ያለው መከራ ስላስጨነቃቸው አይደለም። (ኢዮብ 14:1) ከዚህ ይልቅ የይሖዋ መንፈስ በእውነተኞቹ ቅቡዓን ውስጥ በአጠቃላይ፣ የሰው ልጆች በጋራ ከሚካፈሉት የተለየ ተስፋና ምኞት በውስጣቸው ተክሏል። እነዚህ በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ደስተኛ በሆኑ ቤተሰቦችና ወዳጆች ተከብቦና ሰብዓዊ ፍጽምናን ተላብሶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ድንቅ መብት እንደሆነ ይገነዘባሉ። ይሁን እንጂ የልባቸው ምኞት እንዲህ ዓይነት ሕይወት ማግኘት አይደለም። ቅቡዓን ያላቸው ሰማያዊ ተስፋ እጅግ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ ማንኛውንም ምድራዊ ተስፋና ዝምድና ሁሉ ለመሠዋት ፈቃደኛ ናቸው።—2 ጴጥሮስ 1:13, 14
13. በ2 ቆሮንቶስ 5:1-5 መሠረት የጳውሎስ ‘ናፍቆት’ ምን ነበር? ይህስ በመንፈስ የተወለዱትን ሰዎች በሚመለከት ምን ማለት ይሆናል?
13 አምላክ የሰጠው ሰማያዊ ተስፋ በእነዚህ ሰዎች ውስጥ በጥልቀት የተተከለ ከመሆኑ የተነሣ እንደሚከተለው ሲል እንደጻፈው እንደ ጳውሎስ ይሰማቸዋል:- “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፣ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፣ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፣ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።” (2 ቆሮንቶስ 5:1-5) ጳውሎስ የማይሞት መንፈሳዊ ፍጥረት በመሆን ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ለመሄድ ‘ይናፍቅ’ ነበር። ሰብዓዊውን አካል ፈራሽ በሆነው ድንኳን መስሎታል፤ ድንኳን ከመኖሪያ ቤት ጋር ሲወዳደር ጥንካሬ የሌለውና ጊዜያዊ ማደሪያ ነው። መንፈሱ የመጪው ሰማያዊ ሕይወት መያዣ ሆኖ የተሰጣቸው ክርስቲያኖች ሟች የሆነ ሥጋዊ አካል ለብሰው በምድር ላይ ቢኖሩም ‘ከአምላክ የተሠራውን’ የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን መንፈሳዊ አካል ለማግኘት በጉጉት ይጠባበቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:50-53) እነርሱ ልክ እንደ ጳውሎስ “ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ [ከሰብዓዊው አካል] ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ [በሰማይ] ማደር ደስ ይለናል” በማለት በጉጉት ሊናገሩ ይችላሉ።—2 ቆሮንቶስ 5:8
ልዩ በሆነ ቃል ኪዳን ታቅፈዋል
14. ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም በመጀመሪያ የጠቀሰው ቃል ኪዳን የትኛው ነው? ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር በተያያዘ የሚጫወተውስ ሚና ምንድን ነው?
14 በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች በሁለት ልዩ ቃል ኪዳኖች ውስጥ እንደታቀፉ እርግጠኞች ናቸው። ኢየሱስ ያልቦካ ቂጣና ወይን ተጠቅሞ ከፊቱ ይጠብቀው የነበረውን ሞት የሚያስቡበትን በዓል ባቋቋመ ጊዜ አንደኛውን ቃል ኪዳን የጠቀሰ ሲሆን የወይኑን ጽዋ በሚመለከት “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” ብሏል። (ሉቃስ 22:20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:25) አዲሱ ቃል ኪዳን የተደረገው በእነማን መካከል ነው? በይሖዋ አምላክና በመንፈሳዊ እስራኤል አባላት መካከል ነው፤ ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ወደ ሰማያዊ ክብር ሊያመጣቸው ዓላማ አለው። (ኤርምያስ 31:31-34፤ ገላትያ 6:15, 16፤ ዕብራውያን 12:22-24) በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ የተመሠረተው ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ለይሖዋ ስም የሚሆኑ ሰዎችን ከብሔራት በማውጣጣት እነዚህን በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች የአብርሃም “ዘር” ክፍል እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። (ገላትያ 3:26-29፤ ሥራ 15:14) አዲሱ ቃል ኪዳን ሁሉም የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት አግኝተው ከሞት በመነሳት ወደ ክብር እንዲመጡ ያስችላቸዋል። ‘ዘላለማዊ ቃል ኪዳን’ እንደመሆኑ መጠን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ለዘላለም የሚዘልቁ ይሆናሉ። ይህ ቃል ኪዳን በሺው ዓመት ግዛትና ከዚያም በኋላ ባሉት ጊዜያት በሌሎች መንገዶችም የሚጫወተው ሚና ይኑር አይኑር ጊዜ የሚያሳየን ነገር ይሆናል።—ዕብራውያን 13:20
15. ከሉቃስ 22:28-30 ጋር በሚስማማ መንገድ የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች መታቀፍ የጀመሩት በየትኛው ሌላ ቃል ኪዳን ውስጥ ነው? ይህ የሆነውስ መቼ ነበር?
15 ይሖዋ ወደ ‘ክብር ሊያመጣ’ ያዘጋጃቸው “ብዙ ልጆቸ” በግለሰብ ደረጃም በአንድ ሰማያዊ መንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ ገብተዋል። ኢየሱስ በእርሱና ዱካውን በሚከተሉት ተከታዮቹ መካከል የተደረገውን ይህን ቃል ኪዳን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፣ በአሥራ ሁለቱም በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ።” (ሉቃስ 22:28-30) የመንግሥቱ ቃል ኪዳን ተግባራዊ የሆነው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ ነው። ያ ቃል ኪዳን በኢየሱስና በተባባሪ ነገሥታቱ መካከል ለዘላለም ይጸናል። (ራእይ 22:5) በመሆኑም በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች በአዲሱ ቃል ኪዳን እንዲሁም በመንግሥቱ ቃል ኪዳን ውስጥ ስለመግባታቸው እርግጠኞች ናቸው። ከዚህ የተነሣ የጌታ እራት ሲከበር የኢየሱስን ኃጢአት የለሽ ሰብዓዊ አካል ከሚያመለክተው ቂጣ እንዲሁም ሲሞት የፈሰሰውንና የአዲሱ ቃል ኪዳን መሠረት የሆነውን የኢየሱስን ፍጹም ደም ከሚወክለው ወይን የሚካፈሉት በምድር ላይ የቀሩትና በአንጻራዊ ሁኔታ ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት የሆነው ቅቡዓን ብቻ ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 11:23-26፤ መጠበቂያ ግንብ 3-110 ገጽ 17-20ን ተመልከት።
የተጠሩ፣ የተመረጡና የታመኑ
16, 17. (ሀ) ወደ ክብር ለመምጣት 144,000ዎቹ በሙሉ ምን ማድረግ ይፈለግባቸዋል? (ለ) ‘አሥሩ ነገሥታት’ እነማን ናቸው? በምድር ላይ ለቀሩት የክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ያላቸው አመለካከትስ ምንድን ነው?
16 የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በመጀመሪያ ደረጃ 144,000 ሰዎች ለሰማያዊ ሕይወት እንዲጠሩ እንዲሁም በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች በመሆን እንዲመረጡ አስችሏቸዋል። እርግጥ ነው ወደ ክብር መምጣት ይችሉ ዘንድ ‘መጠራታቸውንና መመረጣቸውን ለማጽናት መትጋትና’ እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:10፤ ኤፌሶን 1:3-7፤ ራእይ 2:10) በምድር ላይ የቀሩት ጥቂት ቅቡዓን ፖለቲካዊ ኃይሎችን በሙሉ ከሚያመለክቱት “አሥር ነገሥታት” ተቃውሞ ቢገጥማቸውም የጸና አቋማቸውን ጠብቀው ይገኛሉ። “እነዚህ በጉን ይዋጋሉ፤” ይሁን እንጂ አንዱ መልአክ እንደተናገረው “በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፣ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።”—ራእይ 17:12-14
17 ሰብዓዊ ገዥዎች “የነገሥታት ንጉሥ” በሆነው በኢየሱስ ላይ አንዳች ነገር ማድረግ አይቻላቸውም። ምክንያቱም እርሱ ያለው በሰማይ ነው። ይሁን እንጂ ምድራዊ ሕይወታቸውን ላልጨረሱት ‘ወንድሞቹ’ ጥላቻ ያሳያሉ። (ራእይ 12:17) በአምላክ የጦርነት ቀን ማለትም በአርማጌዶን ‘የነገሥታት ንጉሥ’ የሆነው ኢየሱስና አብረውት ያሉት ‘የተጠሩ፣ የተመረጡና የታመኑ’ ‘ወንድሞቹ’ ድል ሲቀዳጁ ይህ ጥላቻ ያከትማል። (ራእይ 16:14, 16) እስከዚያው ድረስ ግን በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች ብዙ ሥራ አላቸው። ይሖዋ ወደ ክብር እስኪያመጣቸው ድረስ ዛሬ ምን ነገር እያከናወኑ ነው?
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አምላክ ‘ወደ ሰማያዊ ክብር የሚያመጣቸው’ እነማንን ነው?
◻ ‘ከአምላክ መወለድ’ ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ለአንዳንድ ክርስቲያኖች ‘መንፈሱ የሚመሰክርላቸው’ እንዴት ነው?
◻ በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች በየትኞቹ ቃል ኪዳኖች ውስጥ ታቅፈዋል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ሰማያዊ ክብር ለማግኘት የሚያስችል በር እንደተከፈተ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ታይቷል