በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የገለልተኝነት አቋማችሁን ጠብቁ
“የአምላክ የሆነውን . . . ለአምላክ ስጡ።”—ማቴ. 22:21
1. አምላክንም ሆነ ሰብዓዊ መንግሥታትን መታዘዝ የምንችለው እንዴት ነው?
የአምላክ ቃል ለሰብዓዊ መንግሥታት እንድንታዘዝ ያስተምረናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሰው ይልቅ አምላክን መታዘዝ እንዳለብን ይገልጻል። (ሥራ 5:29፤ ቲቶ 3:1) ታዲያ እነዚህ ሐሳቦች እርስ በርስ ይጋጫሉ? በጭራሽ! በአንጻራዊ ሁኔታ ስለመገዛት የሚገልጸው መሠረታዊ ሥርዓት እነዚህን ትእዛዛት ለመረዳትና ለመፈጸም ያስችለናል። ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” ብሎ ሲናገር ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል።[1] (ማቴ. 22:21) ኢየሱስ የሰጠንን ይህን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የምንኖርበት አገር መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎች በመታዘዝ፣ ባለሥልጣናቱን በማክበር እንዲሁም ቀረጥ በመክፈል ለመንግሥት ሥልጣን እንገዛለን። (ሮም 13:7) ይሁንና የመንግሥት ባለሥልጣናት የአምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ ቢያዙን ይህን እንደማናደርግ በአክብሮት እንገልጻለን።
2. በዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ የትኛውንም ወገን እንደማንደግፍ የምናሳየው እንዴት ነው?
2 ለአምላክ የሚገባውን ለአምላክ የምንሰጥበት አንዱ መንገድ፣ በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ የገለልተኝነት አቋም በመያዝ ነው። (ኢሳ. 2:4) ሰብዓዊ መንግሥታት ሥልጣን እንዲይዙ የፈቀደላቸው ይሖዋ ስለሆነ አንቃወማቸውም፤ ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው እንቅስቃሴዎችንም አናካሂድም። (ሮም 13:1, 2) በፖለቲካ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር አንሞክርም፤ በምርጫ አንካፈልም ወይም ፖለቲካዊ ሥልጣን አንይዝም፤ አሊያም ደግሞ መንግሥት ለመለወጥ ጥረት አናደርግም።
3. የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?
3 አምላክ የገለልተኝነት አቋም እንድንይዝ መመሪያ የሰጠን በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ነው። አንደኛ ነገር፣ በዚህ ዓለም ፖለቲካና ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ‘የዓለም ክፍል አለመሆናችንን’ ስናሳይ የአምላክ ልጅ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርትና ምሳሌ እንከተላለን። (ዮሐ. 6:15፤ 17:16) ለአምላክ መንግሥት በታማኝነት ለመገዛት የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ የማናደርግ ከሆነ ለሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ የሚገልጸውን ምሥራች በንጹሕ ሕሊና መስበክ እንዴት እንችላለን? በሌላ በኩል ደግሞ በፖለቲካ ውስጥ በመግባት ምዕመኖቻቸው እንዲከፋፈሉ ከሚያደርጉት የሐሰት ሃይማኖቶች በተለየ፣ እውነተኛው አምልኮ የገለልተኝነት አቋማችንን እንድንጠብቅ በመርዳት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር እንዲኖረን ያደርጋል።—1 ጴጥ. 2:17
4. (ሀ) ወደፊት ገለልተኛ መሆን ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን እንዴት እናውቃለን? (ለ) ገለልተኝነታችንን ለመጠበቅ አሁኑኑ መዘጋጀት ያለብን ለምንድን ነው?
4 በምንኖርበት አገር ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የተረጋጋና ለእውነተኛው አምልኮ አመቺ ይመስል ይሆናል። ያም ሆኖ የሰይጣን ሥርዓት ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ሲሄድ የገለልተኝነት አቋምን መጠበቅ ይበልጥ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል እንጠብቃለን። የምንኖረው “ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ” እንዲሁም ‘ግትር’ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህ ዓለም ይበልጥ እየተከፋፈለ መሄዱ አይቀርም። (2 ጢሞ. 3:3, 4) በአንዳንድ አገሮች ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በፍጥነት በመለዋወጣቸው፣ ወንድሞቻችን ከገለልተኝነት ጋር የተያያዙ ያልተጠበቁ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል። እንግዲያው ገለልተኝነታችንን ለመጠበቅ አሁኑኑ አቋማችንን ማጠናከር እንዳለብን አስተዋላችሁ? ፈታኝ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ እጃችንን አጣጥፈን የምንጠብቅ ከሆነ አቋማችንን ልናላላና ገለልተኛ ሳንሆን ልንቀር እንችላለን። ታዲያ በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ገለልተኝነታችንን ለመጠበቅ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ የሚረዱን አራት ቁልፍ ነጥቦችን እንመልከት።
ለሰብዓዊ መንግሥታት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ
5. ይሖዋ ለሰብዓዊ መንግሥታት ምን አመለካከት አለው?
5 ገለልተኝነታችንን ለመጠበቅ የሚረዳን የመጀመሪያው ቁልፍ፣ ለፖለቲካው ሥርዓት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ነው። አንዳንድ መንግሥታት ጥሩ ይመስሉ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የይሖዋ ዓላማ ሰው ሰውን እንዲገዛው አይደለም። (ኤር. 10:23) ሰብዓዊ መንግሥታት ብሔራዊ ስሜትን የሚያበረታቱ ሲሆን ይህ ደግሞ የሰው ልጆችን ይከፋፍላል። የተሻሉ የሚባሉት ሰብዓዊ ገዢዎችም እንኳ ሁሉንም ችግሮች ማስወገድ አይችሉም። ከዚህም በተጨማሪ ከ1914 ወዲህ ሰብዓዊ መንግሥታት የአምላክ መንግሥት ተቀናቃኝ ሆነዋል፤ ይህ መንግሥት በቅርቡ እነዚህን ብሔራት ያጠፋቸዋል።—መዝሙር 2:2, 7-9ን አንብብ።
6. ለመንግሥት ባለሥልጣናት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
6 አምላክ የዓለም የፖለቲካ መዋቅር እንዲቀጥል የፈቀደው፣ በተወሰነ መጠን መረጋጋት እንዲሰፍን ስለሚያደርግ ነው፤ ይህ ደግሞ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ያስችለናል። (ሮም 13:3, 4) አምላክ ለባለሥልጣናት እንድንጸልይ እንኳ አዞናል፤ በተለይ ደግሞ የሚያደርጉት ውሳኔ አምልኳችንን የሚነካ በሚሆንበት ጊዜ ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞ. 2:1, 2) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ፍትሕ እንዲያስፈጽሙልን ወደ መንግሥት ባለሥልጣናት ይግባኝ እንላለን። (ሥራ 25:11) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን፣ በፖለቲካው ሥርዓት ላይ ሥልጣን እንዳለው ቢናገርም ሰይጣን እያንዳንዱን መሪ ወይም ባለሥልጣን በቀጥታ እንደሚቆጣጠረው አይገልጽም። (ሉቃስ 4:5, 6) በመሆኑም አንድን ባለሥልጣን ለይተን በመጥቀስ በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ መናገር የለብንም። እንዲያውም ‘ከመንግሥታትና ከባለሥልጣናት’ ጋር በተያያዘ “ስለ ማንም ክፉ ነገር” አንናገርም።—ቲቶ 3:1, 2
7. የትኛውን አመለካከት ልናስወግድ ይገባል?
7 አምላክን የምንታዘዝበት አንዱ መንገድ፣ የትኛውንም ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ከሌሎች አስበልጠን ባለማየት ነው፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የእኛን ጥቅም የሚያስጠብቅ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይህን ማድረግ አይኖርብንም። በዚህ ረገድ የገለልተኝነት አቋማችን ሊፈተን የሚችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ በአምላክ ሕዝቦችም ላይ ጭምር መከራ ያደረሰን አንድ ጨቋኝ አገዛዝ ለማስወገድ የሚጥር አብዮታዊ እንቅስቃሴ አለ እንበል። ከተቃዋሚዎቹ ጋር አብረን ሰልፍ ባንወጣም የእነሱ ዓይነት መንፈስ በውስጣችን ይኖር ይሆን? (ኤፌ. 2:2) በንግግራችንና በድርጊታችን ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰባችንም ጭምር የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ ይኖርብናል።
“ጠንቃቆች” ሆኖም “የዋሆች ሁኑ”
8. የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ ፈታኝ በሚሆንበት ጊዜ “ጠንቃቆች” ሆኖም “የዋሆች” መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
8 የገለልተኝነት አቋማችንን እንድንጠብቅ የሚረዳን ሁለተኛው ቁልፍ፣ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን “እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች” መሆን ነው። (ማቴዎስ 10:16, 17ን አንብብ።) አደገኛ ሁኔታዎችን አስቀድመን በማስተዋል ጠንቃቆች መሆናችንን እናሳያለን፤ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የገለልተኝነት አቋማችንን በመጠበቅ ደግሞ የዋሆች መሆናችንን እናሳያለን። ሊያጋጥሙን የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችንና እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት መወጣት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።
9. ሰዎችን በምናነጋግርበት ጊዜ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል?
9 ንግግራችን። ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሲነሱ ስለምንናገረው ነገር ጠንቃቃ መሆን አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስንሰብክ የአንድን መሪ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ፖሊሲዎች፣ ከማወደስም ሆነ ከመንቀፍ መቆጠብ ይኖርብናል። ከሰዎች ጋር ስንነጋገር ትኩረት ማድረግ ያለብን መሠረታዊ በሆነው ችግር ላይ እንጂ በማንኛውም ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ ሊሆን አይገባም፤ በዚህ መንገድ የሚያግባቡንን ነጥቦች ለማንሳት ጥረት ማድረግ አለብን። ከዚያም የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆች ያሉባቸውን ችግሮች ለዘለቄታው ጠራርጎ የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እናሳያቸው። በውይይቱ መሃል፣ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ጋብቻ ወይም ፅንስ ማስወረድን የመሳሰሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች ከተነሱ የአምላክ መሥፈርቶች ምን እንደሆኑ እናስረዳቸው፤ እንዲሁም እነዚህን መሥፈርቶች በሕይወታችን ተግባራዊ ለማድረግ የምንጥረው እንዴት እንደሆነ ልንገልጽላቸው ይገባል። ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የየትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ አቋም ደግፈን መናገር አይኖርብንም። በተጨማሪም አንዳንድ ሕጎች ሊወጡ፣ ሊሻሩ ወይም ሊለወጡ እንደሚገባ የሚገልጽ ሐሳብ ቢሰነዘር እኛ ከየትኛውም ወገን ልንሆን አይገባም፤ ሌሎች የእኛን አመለካከት እንዲቀበሉም ጫና አናሳድርም።
10. በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርበውን ማንኛውም ነገር በምናይበት ወይም በምናነብበት ጊዜ የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
10 መገናኛ ብዙኃን። ብዙውን ጊዜ የዜና ዘገባዎች ተዛብተውና የአንድን ወገን ስሜት በሚያንጸባርቅ መልኩ ይቀርባሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ መገናኛ ብዙኃን ለፖለቲካው ሥርዓት እንደ መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። መንግሥት መገናኛ ብዙኃኑን በሚቆጣጠርባቸው አገሮች የዜና ዘገባዎች በእጅጉ ተዛብተው ሊቀርቡ ይችላሉ፤ ይሁንና ነፃነት አለ በሚባልባቸው አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖችም እንኳ የዜና ዘገባዎችን ሲያዳምጡ፣ የዘጋቢዎቹ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው መጠንቀቅ አለባቸው። ‘አንድ ዘጋቢ የሚያቀርበውን ዝግጅት መስማት የሚያስደስተኝ የእሱን ፖለቲካዊ አመለካከት ስለምደግፍ ነው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። መልሳችሁ አዎ ከሆነ፣ ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ የመረጃ ምንጭ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። ያም ሆነ ይህ፣ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን የዜና ዘገባዎች አዘውትረን ከማዳመጥ መቆጠብ የጥበብ አካሄድ ነው፤ እንዲሁም የምንሰማውን ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው “የትክክለኛ ትምህርት መሥፈርት” አንጻር መገምገም ይኖርብናል።—2 ጢሞ. 1:13
11. ላሉን ቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ፍቅር ማዳበራችን የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ ከባድ እንዲሆንብን ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው?
11 ፍቅረ ንዋይ። ላሉን ቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ፍቅር ካዳበርን ፈታኝ ሁኔታዎች ሲደርሱብን የገለልተኝነት አቋማችንን ልናላላ እንችላለን። በማላዊ የምትኖረው ሩት በ1970ዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ስደት በደረሰባቸው ወቅት አንዳንድ ወንድሞች ይህን ሲያደርጉ ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “የተመቻቸ ኑሯቸውን መተው ፈተና ሆነባቸው። አንዳንዶች ከእኛ ጋር ቢሰደዱም ከጊዜ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲውን በመቀላቀል ወደ ቤታቸው ተመለሱ፤ ይህን ያደረጉት በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያለው ያልተመቻቸ ሕይወት ስለከበዳቸው ነው።” ከዚህ በተለየ አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች፣ የገለልተኝነት አቋማቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት በኢኮኖሚ ቢቸገሩ አሊያም ንብረታቸውን በሙሉ ቢያጡም እንኳ አቋማቸውን አላላሉም።—ዕብ. 10:34
12, 13. (ሀ) ይሖዋ ስለ ሰው ልጆች ምን አመለካከት አለው? (ለ) ከአገራችን ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆነ ኩራት አድሮብን እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?
12 ተገቢ ያልሆነ ኩራት። ሰዎች ዘራቸውን፣ ብሔራቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ከተማቸውን ወይም አገራቸውን አስመልክተው በኩራት ሲናገሩ ብዙ ጊዜ እንሰማለን። ይሁንና ስለ ዘር፣ ባሕል ወይም አገር ተገቢ ያልሆነ ኩራት ማዳበር ይሖዋ ለሰብዓዊ አገዛዝና ለሰው ዘር ካለው አመለካከት ጋር እንደሚጋጭ እናውቃለን። እርግጥ ነው፣ አምላክ ያደግንበትን ባሕል እንድንተው አይጠብቅብንም። እንዲያውም የተለያዩ ባሕሎች መኖራቸው በሰብዓዊው ቤተሰብ መካከል ያለውን አስደናቂ ልዩነት ያጎላል። ያም ቢሆን በአምላክ ዓይን ሁሉም ሰው እኩል መሆኑን ማስታወስ ይገባናል።—ሮም 10:12
13 ከትውልድ ቦታችን ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆነ ኩራት ማዳበር ብሔራዊ ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ አቋማችንን ወደማላላት ሊመራን ይችላል። ክርስቲያኖችም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ኩራት ወጥመድ ሊሆንባቸው ይችላል፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ጉባኤ አንዳንድ አባላት እንኳ ከእነሱ የተለየ ዜግነት ባላቸው ወንድሞቻቸው ላይ አድልዎ ፈጽመዋል። (ሥራ 6:1) ተገቢ ያልሆነ ኩራት በልባችን ውስጥ እያቆጠቆጠ መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ለምሳሌ የሌላ አገር ዜጋ የሆነ ክርስቲያን አንድ ሐሳብ አቀረበልን እንበል። ‘እኛ ነገሮችን የምናከናውንበት መንገድ የተሻለ ነው’ በማለት ሐሳቡን ወዲያውኑ ውድቅ እናደርገዋለን? የተሻለው አካሄድ ሁላችንም፣ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ነው።—ፊልጵ. 2:3
ይሖዋ ኃይል እንዲሰጣችሁ ጠይቁ
14. ጸሎት የሚረዳን እንዴት ነው? ይህን የሚያሳየው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው?
14 የገለልተኝነት አቋማችንን እንድንጠብቅ የሚረዳን ሦስተኛው ቁልፍ፣ ይሖዋ ኃይል እንዲሰጠን መጠየቅ ነው። ይሖዋ እንደ ትዕግሥትና ራስን መግዛት ያሉ ባሕርያት ማዳበር እንድንችል ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን እንጸልይ፤ ምግባረ ብልሹ የሆነ ወይም ፍትሕ የሚያጓድል መንግሥት የሚያደርስብንን ጫና ተቋቁመን ለመኖር እነዚህ ባሕርያት ያስፈልጉናል። በተጨማሪም ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን እንድናላላ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማስተዋልና ማሸነፍ እንድንችል የሚያስፈልገውን ጥበብ እንዲሰጠን ይሖዋን እንጠይቅ። (ያዕ. 1:5) ለእውነተኛው አምልኮ ቆራጥ አቋም በመያዛችን ምክንያት ብንታሰር ወይም ሌላ ዓይነት ቅጣት ቢደርስብን ደግሞ እምነታችንን በድፍረት ለማስረዳትና የሚመጣብንን ማንኛውንም ስደት በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ እንጸልይ።—የሐዋርያት ሥራ 4:27-31ን አንብብ።
15. የገለልተኝነት አቋማችንን ለመጠበቅ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? (“የአምላክ ቃል በአቋማቸው እንዲጸኑ ረድቷቸዋል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
15 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ሊያበረታህ ይችላል። ፈተና ሲያጋጥምህ የገለልተኝነት አቋምህን ለመጠበቅ ሊረዱህ በሚችሉ ጥቅሶች ላይ አሰላስል። መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት የማትችልበት አጋጣሚ ቢፈጠር ከእነዚህ ጥቅሶች ማበረታቻ ማግኘት እንድትችል ጥቅሶቹን በቃልህ ለመያዝ ሞክር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት ወደፊት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ያለን ተስፋ እውን ሆኖ እንዲታየን ይረዳናል። ስደት ሲደርስብን መጽናት እንድንችል ይህ ተስፋ ያስፈልገናል። (ሮም 8:25) ስለምትጓጓላቸው በረከቶች በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ አሰላስል፤ በገነት ውስጥ እነዚህን በረከቶች ስታገኝ የሚኖረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር።
ንጹሕ አቋማቸውን ከጠበቁ ሰዎች ጥቅም ማግኘት
16, 17. የገለልተኝነት አቋማቸውን ከጠበቁ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
16 የገለልተኝነት አቋማችንን እንድንጠብቅ የሚረዳን አራተኛው ቁልፍ፣ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የተዉት ምሳሌ ነው። የእነሱ ምሳሌ ለመጽናት የሚያስፈልገንን ጥበብና ብርታት ይሰጠናል። ለምሳሌ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የባቢሎንን መንግሥት የሚወክለውን ምስል ለማምለክ ፈቃደኞች አልሆኑም። (ዳንኤል 3:16-18ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህ ወጣቶች ስለወሰዱት ቆራጥ እርምጃ በማንበባቸው፣ ለሚኖሩበት አገር ባንዲራ አምልኮ አናቀርብም ለማለት የሚያስችላቸውን ድፍረት አግኝተዋል። ኢየሱስም ቢሆን በዓለም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግጭቶች ውስጥ ፈጽሞ ጣልቃ አልገባም። የእሱ ምሳሌ ሌሎችን ሊጠቅም እንደሚችል ስለተገነዘበ ደቀ መዛሙርቱን “አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሏቸዋል።—ዮሐ. 16:33
17 በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋማቸውን ጠብቀዋል። አንዳንዶች አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ የታሰሩ አልፎ ተርፎም በእምነታቸው ምክንያት የተገደሉም አሉ። የእነሱ ምሳሌ በቱርክ የሚኖረውን ባሪሽን እንደጠቀመው ሁሉ አንተንም ሊጠቅምህ ይችላል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ፍራንትስ ራይተር፣ የሂትለርን ሠራዊት ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተገደለ ወጣት ወንድም ነው። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ለእናቱ የጻፈላት ደብዳቤ ታላቅ እምነት እንዳለውና በይሖዋ እንደሚተማመን ያሳያል፤ እኔም እንዲህ ዓይነት ፈተና ካጋጠመኝ የእሱን ምሳሌ ለመከተል እፈልጋለሁ።”[2]
18, 19. (ሀ) የጉባኤህ አባላት የገለልተኝነት አቋምህን እንድትጠብቅ ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
18 በጉባኤህ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም ድጋፍ ሊሰጡህ ይችላሉ። ከገለልተኝነት አቋም ጋር በተያያዘ የሚያጋጥምህን ፈተና ለሽማግሌዎች ንገራቸው፤ እነዚህ የጎለመሱ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሊሰጡህ ይችላሉ። የጉባኤው አባላት የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ካወቁ ሊያበረታቱህ ይችላሉ። ስለ አንተ እንዲጸልዩ ጠይቃቸው። እርግጥ ነው፣ ወንድሞቻችን እንዲያበረታቱንና እንዲጸልዩልን የምንፈልግ ከሆነ እኛም ለእነሱ እንዲሁ ልናደርግላቸው ይገባል። (ማቴ. 7:12) በjw.org ላይ ኒውስሩም > ሊጋል ዲቨሎፕመንትስ በሚለው ሥር የወጣው “ጀሆቫስ ዊትነስስ ኢምፕሪዝንድ ፎር ዜይር ፌይዝ—ባይ ሎኬሽን” የሚለው ርዕስ የወንድሞችህን ስም ጠቅሰህ ለመጸለይ ያስችልሃል። ይህ ርዕስ በእምነታቸው ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ዝርዝር ማግኘት የሚቻልባቸውን ሊንኮች ይዟል። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል የአንዳንዶቹን ስም በመጥቀስ፣ ደፋሮች ሆነው ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ጸልይላቸው።—ኤፌ. 6:19, 20
19 ሰብዓዊ መንግሥታት መጨረሻቸው እየቀረበ ሲመጣ፣ ለይሖዋና ለመንግሥቱ የምናሳየው ታማኝነት ይበልጥ እያስቆጣቸው ቢሄድ ልንገረም አይገባም። እንግዲያው በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የገለልተኝነት አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ከአሁኑ እናጠናክር።
^ [1] (አንቀጽ 1) እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ ቄሳር ሲል መንግሥታትን ማመልከቱ ነበር። በወቅቱ ትልቅ ሥልጣን ያለው ሰብዓዊ ገዢ ቄሳር ነበር።
^ [2] (አንቀጽ 17) የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 662 እንዲሁም የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ላይ የሚገኘውን “አምላክን ለማስከበር ሲል ሞቷል” የሚል ሣጥን ተመልከት።