ምዕራፍ 21
በናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ
ኢየሱስ ከኢሳይያስ ጥቅልል አነበበ
የናዝሬት ሰዎች ኢየሱስን ለመግደል ሞከሩ
የናዝሬት ሕዝብ በአድናቆት ተውጧል። ኢየሱስ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በዮሐንስ ለመጠመቅ ከናዝሬት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የሚታወቀው በአናጺነቱ ነበር። አሁን ግን ተአምር የመፈጸም ችሎታ እንዳለው በስፋት እየተወራ ነው። የከተማዋ ነዋሪዎች በመካከላቸው አንዳንድ ተአምራት ሲሠራ ለመመልከት ጓጉተዋል።
ኢየሱስ እንደ ልማዱ በከተማዋ ውስጥ ወደሚገኘው ምኩራብ ሲሄድ ጉጉታቸው ይበልጥ ጨመረ። በዚያ የሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት ጸሎትን እንዲሁም “በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች” እንደሚደረገው ከሙሴ መጻሕፍት ማንበብን ይጨምራል። (የሐዋርያት ሥራ 15:21) ከዚህም ሌላ ከነቢያት መጻሕፍት የተወሰኑ ክፍሎች ይነበባሉ። ኢየሱስ ለማንበብ ሲነሳ፣ ወደዚያ ምኩራብ ይመጣ በነበረባቸው ዓመታት የሚያውቃቸውን ብዙ ሰዎች ሳይመለከት አልቀረም። እዚያም የነቢዩ ኢሳይያስን ጥቅልል ሰጡት። እሱም በይሖዋ መንፈስ ስለተቀባው ሰው የሚናገረውን ቦታ አወጣ፤ ይህ ጥቅስ በዛሬው ጊዜ በኢሳይያስ 61:1, 2 ላይ ይገኛል።
ኢየሱስ፣ አስቀድሞ የተነገረለት ይህ ሰው ለተማረኩት ነፃነትና ለታወሩት ማየትን እንዲሁም የይሖዋ ሞገስ የሚገኝበትን ቀን መቅረብ እንደሚያውጅ የሚገልጸውን ሐሳብ አነበበ። ከዚያም ጥቅልሉን ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ። ሁሉም ትኩር ብለው እየተመለከቱት ነው። ኢየሱስ በዚህ ወቅት ረዘም ላለ ጊዜ ሳይናገር አልቀረም፤ ከተናገረው መካከል “ይህ አሁን የሰማችሁት የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ዛሬ ተፈጸመ” የሚለው ትልቅ ትርጉም ያለው ሐሳብ ይገኝበታል።—ሉቃስ 4:21
ሰዎቹ “ከአፉ በሚወጡት የሚማርኩ ቃላት” ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለም እንዴ?” ይባባሉ ጀመር። ሆኖም ኢየሱስ እንደፈጸመ የሰሟቸውን ዓይነት ተአምራት ሲያከናውን ለመመልከት ፈልገዋል፤ እሱም ይህን ስለተገነዘበ እንዲህ አለ፦ “‘አንተ ሐኪም፣ እስቲ ራስህን አድን’ የሚለውን አባባል እንደምትጠቅሱብኝ ጥርጥር የለውም። ‘በቅፍርናሆም እንደተደረገ የሰማነውን ነገር እዚህ በራስህ አገርም አድርግ’ ትሉኛላችሁ።” (ሉቃስ 4:22, 23) የኢየሱስ የቀድሞ ጎረቤቶች፣ ኢየሱስ ለአገሩ ሰዎች ቅድሚያ ሊሰጥ ስለሚገባ ሰዎችን መፈወስ መጀመር ያለበት ከአካባቢው እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስ የናቃቸው መስሏቸው ይሆናል።
ኢየሱስ አስተሳሰባቸው ስለገባው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ አንዳንድ ክንውኖችን ጠቀሰ። በኤልያስ ዘመን በእስራኤል ውስጥ ብዙ መበለቶች ቢኖሩም ኤልያስ ግን ከእነዚህ ወደ አንዳቸውም እንዳልተላከ ገለጸ። ኤልያስ የሄደው በሲዶና አቅራቢያ በምትገኝ ሰራፕታ በተባለች ከተማ ወደምትኖር እስራኤላዊት ያልሆነች መበለት ነው፤ በዚያ የፈጸመው ተአምርም የሴትየዋንና የልጇን ሕይወት አትርፏል። (1 ነገሥት 17:8-16) በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ የሥጋ ደዌ ሕመምተኞች ነበሩ፤ ሆኖም ነቢዩ ያነጻው ሶርያዊውን ንዕማንን ብቻ ነው።—2 ነገሥት 5:1, 8-14
ኢየሱስ ባደገበት ከተማ የነበሩት ሰዎች፣ ራስ ወዳድነታቸውንና እምነተ ቢስነታቸውን ለማጋለጥ ኢየሱስ እንዲህ ያለ ንጽጽር መጠቀሙ ተገቢ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ምን አደረጉ? በምኩራቡ የነበሩት ሰዎች እጅግ ስለተቆጡ ተነስተው ኢየሱስን እያጣደፉ ከከተማው አስወጡት። የናዝሬት ከተማ ወደምትገኝበት ተራራ አፋፍ በመውሰድ ቁልቁል ሊወረውሩት ሞከሩ። ሆኖም ኢየሱስ ከእጃቸው አምልጦ በሰላም ሄደ። ከዚያም በገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ምዕራብ ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ተጓዘ።