እውነተኛ የሆነውን ሀብት መፈለግ
“በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ።”—ሉቃስ 16:9
1, 2. በዚህ ሥርዓት ውስጥ ምንጊዜም ድሆች የሚኖሩት ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት አስቸጋሪና ኢፍትሐዊ ነው። ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ቢንከራተቱም ያሰቡት አይሳካላቸውም። ብዙዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ወደ በለጸጉ አገሮች ይሰደዳሉ። ሆኖም በበለጸጉት አገሮችም ጭምር ድህነት ተንሰራፍቷል። በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ ነው። በቅርብ የወጡ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከምድራችን ነዋሪዎች መካከል 1 በመቶ የሚሆኑት ባለጸጋ ሰዎች ያላቸው ሀብት የቀሩት የምድር ነዋሪዎች በሙሉ ካላቸው ሀብት ጋር እኩል እንደሆነ ይገመታል። የእነዚህን አኃዞች ትክክለኛነት ማረጋገጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዶች ለልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ሀብት ሲኖራቸው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ግን በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ የማይካድ ሐቅ ነው። ኢየሱስ “ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው” በማለት ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ገልጾታል። (ማር. 14:7) እንዲህ ያለ ልዩነት የኖረው ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ፣ አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚጠፋው የአምላክ መንግሥት ሲመጣ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በራእይ 18:3 ላይ የተገለጹት “ነጋዴዎች” የሚያመለክቱት ስግብግብነት የተሞላበትን የንግድ ሥርዓት ነው፤ የሰይጣን ዓለም የንግዱንና የፖለቲካውን ሥርዓት እንዲሁም ሃይማኖትን ያቀፈ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ከፖለቲካና ከሐሰት ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ ርቀዋል፤ ይሁንና ከአምላክ ሕዝቦች መካከል አብዛኞቹ ከሰይጣን ዓለም የንግድ ሥርዓት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖራቸው ማድረግ አይችሉም።
3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዛሬው ጊዜ ላለው የንግድ ሥርዓት ያለንን አመለካከት ለመመርመር እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ማጤናችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ያለኝን ቁሳዊ ሀብት ለአምላክ ታማኝ እንደሆንኩ በሚያሳይ መንገድ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው? በንግዱ ዓለም ውስጥ ከሚገባው በላይ ላለመጠላለፍ መጠንቀቅ የምችለው እንዴት ነው? በዚህ አስቸጋሪ ሥርዓት ውስጥም እንኳ የአምላክ ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንደሚታመኑ የሚያሳዩት የትኞቹ ተሞክሮዎች ናቸው?’
የዓመፀኛው መጋቢ ምሳሌ
4, 5. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው መጋቢ ምን አጋጥሞት ነበር? (ለ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ምክር ሰጥቷቸዋል?
4 ሉቃስ 16:1-9ን አንብብ። ኢየሱስ ስለ ዓመፀኛው መጋቢ የተናገረው ምሳሌ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ መጋቢ፣ የጌታውን ንብረት እያባከነ ነው ተብሎ እንደተከሰሰ ሰማ፤ በመሆኑም የመጋቢነት ሥራውን ሲያጣ የሚረዱት “ወዳጆች” ለማፍራት ሲል ‘አርቆ አሳቢነት’ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ወስዷል።a ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው፣ ተከታዮቹ በዚህ ዓለም ውስጥ ለመኖር ሲሉ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ለማበረታታት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። መጋቢው የወሰደው እርምጃ “የዚህ ሥርዓት ልጆች” የሚያደርጉት ነገር እንደሆነ ኢየሱስ ገልጿል፤ ሆኖም ይህን ምሳሌ አንድ ትምህርት ለማስተላለፍ ተጠቅሞበታል።
5 ኢየሱስ፣ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳጋጠመው መጋቢ ሁሉ አብዛኞቹ ተከታዮቹም ፍትሕ የጎደለው የንግድ ሥርዓት ባለበት በዚህ ዘመን መተዳደሪያ ማግኘት ከባድ ሊሆንባቸው እንደሚችል ያውቃል። በመሆኑም እንደሚከተለው በማለት አሳስቧቸዋል፦ “በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ፤ እነሱም [ይሖዋና ኢየሱስ] የዓመፅ ሀብት ሲያልቅ በዘላለማዊ መኖሪያ ይቀበሏችኋል።” ኢየሱስ ከሰጠው ምክር ምን ትምህርት እናገኛለን?
6. በዛሬው ጊዜ ያለው የንግድ ሥርዓት በአምላክ ዓላማ ውስጥ እንዳልነበረ እንዴት ማወቅ እንችላለን?
6 ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮችን “የዓመፅ ሀብት” ብሎ የጠራቸው ለምን እንደሆነ ባይናገርም፣ ስግብግብነት የሚንጸባረቅበት የንግድ ሥርዓት በአምላክ ዓላማ ውስጥ እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን በኤደን እያሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አትረፍርፎ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 2:15, 16) ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቅዱስ መንፈሱን ከሰጣቸው በኋላ የነበረውን ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አንዳቸውም ቢሆኑ ያላቸው ማንኛውም ንብረት የግላቸው እንደሆነ አድርገው አይቆጥሩም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ያላቸው ነገር ሁሉ የጋራ ነበር።” (ሥራ 4:32) ነቢዩ ኢሳይያስም የሰው ልጆች በሙሉ የምድርን ሀብት በነፃ መጠቀም የሚችሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ተንብዮአል። (ኢሳ. 25:6-9፤ 65:21, 22) እስከዚያው ድረስ ግን የኢየሱስ ተከታዮች በዛሬው ጊዜ ያለውን “የዓመፅ ሀብት” በመጠቀም መተዳደሪያ ለማግኘት፣ ‘አርቀው ማሰብ’ ወይም “ብልሆች” መሆን ያስፈልጋቸዋል፤ በእርግጥ ይህን ሲያደርጉ አምላክን ማስደሰት እንዳለባቸውም አይዘነጉም።
የዓመፅ ሀብትን በጥበብ መጠቀም
7. በሉቃስ 16:10-13 ላይ ምን ምክር ተሰጥቶናል?
7 ሉቃስ 16:10-13ን አንብብ። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው መጋቢ ወዳጆችን ያፈራው ለግል ጥቅሙ ሲል ነው። ኢየሱስ በሰማይ ወዳጆች እንዲያፈሩ ተከታዮቹን ሲያሳስባቸው ግን ይህን በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንዲያደርጉት ማበረታታቱ አልነበረም። ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ ቀጥሎ ባሉት ቁጥሮች ላይ፣ “በዓመፅ ሀብት” መጠቀም ለአምላክ ታማኝ ከመሆን ጋር ተያይዞ ተገልጿል። ኢየሱስ ሊያጎላ የፈለገው ነጥብ፣ ያለንን የዓመፅ ሀብት ለአምላክ ‘ታማኝ መሆናችንን’ በሚያሳይ መንገድ ልንጠቀምበት የሚገባ መሆኑን ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
8, 9. አንዳንዶች የዓመፅ ሀብትን ታማኝ እንደሆኑ በሚያሳይ መንገድ እንዴት እንደተጠቀሙበት የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።
8 ከቁሳዊ ንብረታችን ጋር በተያያዘ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረውን ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ በገንዘብ መደገፍ ነው። (ማቴ. 24:14) በሕንድ የምትኖር አንዲት ትንሽ ልጅ፣ በአነስተኛ ሣጥን ውስጥ ሳንቲም ማጠራቀም ጀመረች፤ ይህች ልጅ ገንዘቡን መጫወቻ ለመግዛት እንኳ አላዋለችውም። ሣጥኑ ሲሞላላት ገንዘቡን በሙሉ አውጥታ ለስብከቱ ሥራ እንዲውል መዋጮ አደረገችው። በዚያው በሕንድ የሚኖር የኮኮናት እርሻ ያለው ወንድም ደግሞ ለማላያላም የርቀት የትርጉም ቢሮ ብዛት ያለው ኮኮናት ይሰጣል፤ ምክንያቱም የርቀት የትርጉም ቢሮው ኮኮናት መግዛት ያስፈልገዋል፤ በመሆኑም ኮኮናት በመሸጥ የሚተዳደረው ይህ ወንድም፣ ለቢሮው ገንዘብ ከሚሰጥ ይልቅ ኮኮናቱን ቢሰጥ እንደሚሻል ተሰምቶታል። ይህ አርቆ አሳቢነት ነው። በተመሳሳይም በግሪክ የሚኖሩ ወንድሞች የወይራ ዘይት፣ አይብ እና ሌሎች ምግቦችን ለቤቴል ቤተሰብ አዘውትረው ይሰጣሉ።
9 በሌላ አገር የሚኖር አንድ ስሪ ላንካዊ ወንድም፣ በአገሩ በሚገኘው የግል ይዞታው ላይ የጉባኤ እንዲሁ ትላልቅ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ እንዲሁም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንዲኖሩበት ፈቅዷል። ወንድም ይህን በማድረጉ የሚያጣው ገንዘብ እንዳለ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ይህ ዝግጅት በስሪ ላንካ ያሉትን አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወንድሞች በጣም ይጠቅማቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት መስበክ በማይችሉበት አገር፣ ወንድሞች ቤታቸው እንደ መንግሥት አዳራሽ እንዲያገለግል ይፈቅዳሉ፤ ይህም በርካታ አቅኚዎችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሌሎች ወንድሞች ጨምሮ ሁሉም አስፋፊዎች ብዙ ወጪ የማያስወጣ መሰብሰቢያ ቦታ እንዲያገኙ ያደርጋል።
10. በልግስና ስንሰጥ ከምናገኛቸው በረከቶች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
10 ቀደም ሲል ያየናቸው ምሳሌዎች፣ የአምላክ ሕዝቦች “በትንሽ ነገር” ይኸውም ቁሳዊ ሀብታቸውን በሚጠቀሙበት መንገድ “ታማኝ” መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይጠቁማሉ፤ ቁሳዊ ሀብት “ትንሽ ነገር” የተባለው ከመንፈሳዊ ሀብት ጋር ሲነጻጸር ዋጋው እዚህ ግባ የሚባል ስላልሆነ ነው። (ሉቃስ 16:10) እነዚህ የይሖዋ ወዳጆች እንዲህ ያለ መሥዋዕት በመክፈላቸው ምን ይሰማቸዋል? ለጋስ መሆን “እውነተኛውን ሀብት” እንደሚያስገኝ ተገንዝበዋል። (ሉቃስ 16:11) ለመንግሥቱ ሥራ አዘውትራ መዋጮ የምታደርግ አንዲት እህት ያገኘችውን በረከት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ ‘በቁሳዊ ነገሮች ለጋስ መሆኔ፣ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በሕይወቴ ውስጥ አስገራሚ ለውጦችን እንድመለከት አድርጎኛል። ለጋስ መሆኔ ከሌሎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ይበልጥ ይቅር ባይና ታጋሽ እንድሆን አስችሎኛል፤ እንዲሁም ቅር የሚያሰኙ ነገሮች ሲያጋጥሙኝ ችሎ ማለፍና የሚሰጠኝን ምክር መቀበል ይበልጥ ቀላል ሆኖልኛል።’ ብዙዎች ለጋስ መሆናቸው መንፈሳዊ ብልጽግና እንዳስገኘላቸው ተገንዝበዋል።—መዝ. 112:5፤ ምሳሌ 22:9
11. (ሀ) በልግስና መስጠታችን ‘አርቆ አሳቢዎች’ መሆናችንን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች ዘንድ ምን እየተከናወነ ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
11 ቁሳዊ ንብረቶችን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ በመጠቀም ‘አርቀን እንደምናስብ’ ማሳየት የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። ንብረታችንን ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት እንችላለን። የዚህ ዓለም ሀብት ያላቸውና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ወይም ወደ ሌላ አገር ተዛውረው ማገልገል ያልቻሉ ክርስቲያኖች፣ የሚያዋጡት ገንዘብ ሌሎችን በአገልግሎታቸው ለመደገፍ እንደሚውል ማወቃቸው ያስደስታቸዋል። (ምሳሌ 19:17) በፈቃደኝነት የሚደረጉት መዋጮዎች፣ መንፈሳዊ ጽሑፎችን ለማቅረብ እንዲሁም ድህነት ባጠላባቸው ሆኖም ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት ባለባቸው አካባቢዎች የሚደረገውን የስብከት ሥራ ለመደገፍ ያስችላሉ። ለበርካታ ዓመታት እንደ ማዳጋስካር፣ ሩዋንዳና ኮንጎ ባሉት አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች፣ ለቤተሰባቸው የሚሆነውን ምግብ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከመግዛት አንዱን ለመመረጥ ይገደዱ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት ከአንድ ሳምንት ወይም ከአንድ ወር ደሞዛቸው ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን የይሖዋ ድርጅት ብዙዎች የሚያደርጉትን መዋጮ በመጠቀምና ‘የአንዱ ትርፍ የሌላውን ጉድለት እንዲሸፍን’ በማድረግ መጽሐፍ ቅዱሶች ወደተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጎሙና እንዲሰራጩ አድርጓል፤ ይህም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንዲሁም መንፈሳዊ ጥማት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲያገኙ አስችሏል። (2 ቆሮንቶስ 8:13-15ን አንብብ።) በዚህም ምክንያት ሰጪዎቹም ሆኑ ተቀባዮቹ የይሖዋ ወዳጆች መሆን ችለዋል።
“በንግድ ሥራ” ላለመጠላለፍ መጠንቀቅ
12. አብርሃም በአምላክ እንደሚታመን ያሳየው እንዴት ነው?
12 ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ፤ ይህም በንግዱ ዓለም ውስጥ ከሚገባው በላይ ላለመጠላለፍ በመጠንቀቅ እንዲሁም “እውነተኛውን ሀብት” ለመፈለግ በመጣር ነው። በጥንት ዘመን የኖረውና የእምነት ሰው የነበረው አብርሃም፣ የበለጸገችውን ዑርን ለቆ በመውጣት በድንኳን ውስጥ መኖር የጀመረው የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን ስለፈለገ ነው። (ዕብ. 11:8-10) አብርሃም እውነተኛ ብልጽግና የሚገኘው ከይሖዋ እንደሆነ ይተማመን ስለነበር ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት አልጣረም፤ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌለው የሚያሳይ ይሆን ነበር። (ዘፍ. 14:22, 23) ኢየሱስ ሌሎችም እንዲህ ያለ እምነት እንዲያዳብሩ አበረታቷል፤ ሀብታም ለሆነ አንድ ወጣት እንዲህ ብሎታል፦ “ፍጹም መሆን ከፈለግክ ሂድና ንብረትህን ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን።” (ማቴ. 19:21) ይህ ወጣት እንደ አብርሃም ያለ እምነት አልነበረውም፤ ሌሎች ግን በአምላክ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመኑ አሳይተዋል።
13. (ሀ) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ምን ምክር ሰጥቶታል? (ለ) በዛሬው ጊዜ የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
13 ጢሞቴዎስ የእምነት ሰው ነበር። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን “የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር” ብሎ ከጠራው በኋላ “ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ አያጠላልፍም” ብሎታል። (2 ጢሞ. 2:3, 4) በዛሬው ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ጨምሮ በምድር ላይ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮች በሙሉ፣ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ይጥራሉ። የማስታወቂያው ኢንዱስትሪና በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ነገሮች የሚያሳድሩባቸውን ጫና ይቋቋማሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ተበዳሪ የአበዳሪው ባሪያ ነው’ የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት አይዘነጉም። (ምሳሌ 22:7) ሰይጣን፣ እሱ ለሚቆጣጠረው የንግድ ሥርዓት ባሪያ ሆነን ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን በሙሉ ስናባክን የማየትን ያህል የሚያስደስተው ነገር የለም። የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ለዓመታት ዕዳ ውስጥ እንድንዘፈቅ ሊያደርጉን ይችላሉ። አንዳንዶች ቤት ወይም መኪና ለመግዛት፣ ከፍተኛ ትምህርት ለመማር ሌላው ቀርቶ ድል ያለ ሠርግ ለመደገስ ሲሉ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ይገባሉ። አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ፣ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ባለመግባት እንዲሁም ወጪዎቻችንን በመቀነስ አርቆ አሳቢ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን፤ ይህን ስናደርግ ለዚህ ዓለም የንግድ ሥርዓት ሳይሆን ለይሖዋ ባሪያ መሆን እንችላለን።—1 ጢሞ. 6:10
14. ቁርጥ አቋማችን ምን ሊሆን ይገባል? በዚህ ረገድ የትኞቹን ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል?
14 አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች መለየት ይኖርብናል። አንድ ባልና ሚስት፣ አትራፊ የሆነ ድርጅት ነበራቸው። ይሁንና እንደገና ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት ስለፈለጉ ድርጅታቸውን፣ ጀልባቸውንና ሌሎች ንብረቶቻቸውን ሸጡ። ከዚያም በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤት በመገንባቱ ሥራ እገዛ ለማበርከት ራሳቸውን አቀረቡ። ይህን በማድረጋቸው ካገኟቸው በረከቶች አንዱ፣ ከሴት ልጃቸውና ከባሏ ጋር በቤቴል ማገልገል መቻላቸው ነው፤ በተጨማሪም ይህ ወንድምና ባለቤቱ በዎርዊክ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ይሠሩ ከነበሩት ወላጆቹ ጋር ለተወሰኑ ሳምንታት አብረው መሥራት ችለዋል። በኮሎራዶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምታገለግል አንዲት አቅኚ ደግሞ በአንድ ባንክ ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ትሠራ ነበር። የባንኩ ኃላፊዎች በሥራዋ በጣም ስለተደሰቱ ደሞዟን በሦስት እጥፍ በማሳደግ ሙሉ ቀን እንድትሠራ ግብዣ አቀረቡላት። ሆኖም ሥራው በአገልግሎቷ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳታተኩር ስለሚያደርጋት፣ ዳጎስ ያለ ገቢ የሚያስገኘውን ይህን ሥራ አልተቀበለችም። እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት ከከፈሉ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ስንል እንዲህ ያለ ቁርጥ አቋም መውሰዳችን፣ ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ያሳያል፤ በተጨማሪም ይህን ስናደርግ፣ በዛሬው ጊዜ የንግዱ ዓለም ከሚያቀርበው ማንኛውም ነገር ይልቅ ለመንፈሳዊ ሀብት ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ እናሳያለን።
ቁሳዊ ሀብት ሲያልቅ
15. ከሁሉ የላቀ እርካታ የሚያስገኘው የትኛው ሀብት ነው?
15 ቁሳዊ ሀብት ማግኘት አምላክ እንደባረከን የሚያሳይ ምልክት ላይሆን ይችላል። ይሖዋ የሚባርከው “በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ” የሆኑትን ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19ን አንብብ።) ሉቺያንb እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በአልባኒያ የምሥራቹ ሰባኪዎች እንደሚያስፈልጉ ስትገነዘብ በ1993 ከጣሊያን ወደ አልባኒያ ሄደች፤ ይህን ስታደርግ ራሷን የምታስተዳድርበት ሥራ ባይኖራትም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ተማምና ነበር። አልባኒያኛን በደንብ የቻለች ሲሆን ከ60 የሚበልጡ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ ረድታለች። በእርግጥ አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች የሚሰብኩት እንዲህ ባሉ ፍሬያማ ክልሎች አይደለም፤ ያም ቢሆን ሰዎች ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ እንዲያገኙና በዚያ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ለመርዳት የምናደርገው ማንኛውም ነገር፣ እኛም ሆንን እነሱ ለዘላለም ከፍ አድርገን የምንመለከተው ውድ ሀብት ያስገኝልናል።—ማቴ. 6:20
16. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያለው የንግድ ሥርዓት ምን ይጠብቀዋል? (ለ) ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለን እውቀት ለቁሳዊ ንብረት ባለን አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?
16 ኢየሱስ “የዓመፅ ሀብት ሲያልቅ” እንጂ ‘የዓመፅ ሀብት ቢያልቅ’ እንዳላለ ልብ እንበል። (ሉቃስ 16:9) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ባንኮች ያጋጠማቸው ችግርና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚከሰተው ነገር አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። ፖለቲካን፣ ሃይማኖትንና የንግዱን ዓለም ያቀፈው መላው የሰይጣን ሥርዓት ድምጥማጡ ይጠፋል። ነቢዩ ሕዝቅኤል እና ነቢዩ ሶፎንያስ፣ በንግዱ ዓለም ውስጥ ለዘመናት ትልቅ ቦታ ሲሰጣቸው የኖሩት ወርቅና ብር በዚያን ጊዜ ዋጋ ቢስ እንደሚሆኑ ተንብየዋል። (ሕዝ. 7:19፤ ሶፎ. 1:18) በሕይወታችን ማብቂያ ላይ ስንደርስ፣ የዚህን ዓለም “የዓመፅ ሀብት” በብዛት ለማካበት ስንል እውነተኛ የሆነውን ሀብት መሥዋዕት እንዳደረግን ብንገነዘብ ምን ይሰማናል? ሁኔታው፣ ብዛት ያለው ገንዘብ ለማከማቸት ሕይወቱን ሙሉ ሲለፋ ቆይቶ፣ ያከማቸው ነገር የሐሰት ገንዘብ እንደሆነ ከተገነዘበ ሰው ጋር ይመሳሰላል። (ምሳሌ 18:11) በእርግጥም የዓመፅ ሀብት ውሎ አድሮ ማለቁ አይቀርም፤ ስለዚህ በዚህ ሀብት ተጠቅመን በሰማይ ‘ወዳጆች የማፍራት’ አጋጣሚ አያምልጠን። የይሖዋን መንግሥት ለመደገፍ የምናደርገው ማንኛውም ነገር መንፈሳዊ ሀብት ያስገኝልናል።
17, 18. የአምላክ ወዳጅ የሆኑ ሰዎች ምን ተዘጋጅቶላቸዋል?
17 የአምላክ መንግሥት ሲመጣ፣ የመኖሪያ ቤት ዕዳና ኪራይ አይኖርም፤ የተትረፈረፈ ምግብ በነፃ እናገኛለን፤ የሕክምና ወጪም አያሳስበንም። በምድር ላይ የሚኖረው የይሖዋ ቤተሰብ የምድራችንን ምርጥ ነገሮች ያገኛል። እንደ ወርቅ፣ ብርና የከበረ ድንጋይ ያሉትን ነገሮች የምንጠቀምባቸው ለጌጣጌጥነት እንጂ ለንግድ ወይም ሀብት ለማከማቸት አይሆንም። የሚያማምሩ ቤቶችን ለመሥራት የሚያገለግሉ ውድ ዋጋ ያላቸው የእንጨት ዓይነቶች እንዲሁም የድንጋይና የብረት ማዕድናት በነፃ ይገኛሉ። ወዳጆቻችን አብረውን የሚሠሩት፣ ገንዘብ ለማግኘት ብለው ሳይሆን ሊረዱን ስለሚፈልጉ ነው። የምድርን የተትረፈረፈ ሀብት በጋራ መጠቀም እንጀምራለን።
18 በሰማይ ወዳጆች የሚያፈሩ ሰዎች የሚያገኙት በዋጋ የማይገመት ሀብት በዚህ ብቻ አያበቃም። በምድር ላይ ያሉት የይሖዋ አምላኪዎች፣ ኢየሱስ “እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ሲላቸው የሚሰማቸው ደስታ ወደር አይኖረውም።—ማቴ. 25:34
a ኢየሱስ በመጋቢው ላይ የቀረበው ክስ ትክክል መሆን አለመሆኑን አልተናገረም። በሉቃስ 16:1 ላይ “ክስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ መጋቢው የተወነጀለው በሐሰት እንደሆነ የሚጠቁምም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው መጋቢው ከሥራው በተባረረበት ምክንያት ላይ ሳይሆን በወሰደው እርምጃ ላይ ነው።
b የሉቺያ ሙሳኔት የሕይወት ታሪክ በመስከረም 2003 ንቁ! ከገጽ 12-16 ላይ ወጥቷል።