የጥናት ርዕስ 15
መስኩን የምትመለከቱት እንዴት ነው?
“ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ።”—ዮሐ. 4:35
መዝሙር 64 በመከሩ ሥራ በደስታ መካፈል
ማስተዋወቂያa
1-2. ኢየሱስ በዮሐንስ 4:35, 36 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው ለምን ሊሆን ይችላል?
ኢየሱስ በእህል ማሳ ውስጥ እያለፈ ነው፤ ማሳው የገብስ ቡቃያ ያለበት ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 4:3-6) ይህ አዝመራ ከአራት ወር ገደማ በኋላ ለአጨዳ ይደርሳል። ኢየሱስ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” በማለት ለሰሚዎቹ እንግዳ ሊሆን የሚችል ነገር ተናገረ። (ዮሐንስ 4:35, 36ን አንብብ።) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?
2 ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው በምሳሌያዊ ሁኔታ ሰዎችን ስለ መሰብሰብ ሳይሆን አይቀርም። እስቲ ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ በፊት ምን እንደተከናወነ አስብ። አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት ባይኖራቸውም ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት የሰበከ ሲሆን እሷም መልእክቱን ተቀበለች! እንዲያውም ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ” በተናገረበት ወቅት ብዙ ሳምራውያን ወደ እሱ እየመጡ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ከሳምራዊቷ ሴት ስለ ኢየሱስ ሰምተው ስለነበር ከእሱ መማር ፈልገው ነበር። (ዮሐ. 4:9, 39-42) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ ስለዚህ ዘገባ ሲገልጽ “ሰዎቹ ጉጉት ስለነበራቸው ለአጨዳ እንደደረሰ አዝመራ ነበሩ” ብሏል።
3. ለሰዎች የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት መያዛችሁ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥቅሞች ያስገኝላችኋል?
3 እናንተስ ምሥራቹን ለምትሰብኩላቸው ሰዎች ምን አመለካከት አላችሁ? ለአጨዳ እንደደረሰ አዝመራ አድርጋችሁ ትመለከቷቸዋላችሁ? እንዲህ ያለ አመለካከት መያዛችሁ በሦስት መንገዶች ይጠቅማችኋል። አንደኛ፣ በጥድፊያ ስሜት ትሰብካላችሁ። የመከር ወቅት የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ስለሆነ ሥራው ቶሎ መከናወን አለበት። ሁለተኛ፣ ሰዎች ምሥራቹን ሲቀበሉ በማየት ትደሰታላችሁ። ደግሞም ሰዎች “መከር በሚሰበሰብበት ጊዜ ሐሴት እንደሚያደርጉ” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳ. 9:3) ሦስተኛ፣ የምትሰብኩለት እያንዳንዱ ሰው ደቀ መዝሙር ሊሆን እንደሚችል ስለምታስቡ በግለሰብ ደረጃ የእሱን ትኩረት የሚስብ አቀራረብ ለመጠቀም ጥረት ታደርጋላችሁ።
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ከሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንማራለን?
4 አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች፣ ሳምራውያን የእሱ ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደማይችሉ አስበው ይሆናል፤ ኢየሱስ ግን እንዲህ ያለ አመለካከት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ ወደፊት ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደሚችሉ አስቧል። እኛም በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ወደፊት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሚሆኑ አድርገን ማሰብ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። እሱ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን? በዚህ ርዕስ ውስጥ ጳውሎስ (1) የሚሰብክላቸው ሰዎች የሚያምኑባቸውን ነገሮች በማወቅ፣ (2) ትኩረታቸውን የሚስቡትን ነገሮች በማስተዋል፣ (3) ወደፊት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሚሆኑ በማሰብ ረገድ ምን ምሳሌ እንደተወ እንመለከታለን።
የሚያምኑበት ነገር ምንድን ነው?
5. ጳውሎስ በምኩራብ ውስጥ መስበክ ይቀለው የነበረው ለምን ሊሆን ይችላል?
5 ጳውሎስ ብዙ ጊዜ በአይሁዳውያን ምኩራቦች ውስጥ ይሰብክ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በተሰሎንቄ ባለ ምኩራብ ውስጥ ‘ለሦስት ሰንበት ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከአይሁዳውያን ጋር ተወያይቶ’ ነበር። (ሥራ 17:1, 2) ጳውሎስ በምኩራብ ውስጥ መስበክ ይቀለው የነበረ ይመስላል። ምክንያቱም አይሁዳዊ ነበር። (ሥራ 26:4, 5) ጳውሎስ አይሁዳውያን የሚያምኑበትን ነገር በሚገባ ስለሚያውቅ ለእነሱ የሚሰብከው በልበ ሙሉነት ነበር።—ፊልጵ. 3:4, 5
6. ጳውሎስ በአቴንስ የገበያ ስፍራ የሰበከላቸው ሰዎች በምኩራብ ካገኛቸው ሰዎች ጋር ምን ልዩነት አላቸው?
6 ጳውሎስ አሳዳጆቹ ባደረሱበት ጥቃት የተነሳ በመጀመሪያ ከተሰሎንቄ ከዚያም ከቤርያ ከወጣ በኋላ ወደ አቴንስ ሄደ። በዚያም “በምኩራብ ከአይሁዳውያንና አምላክን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች ጋር” መወያየት ጀመረ። (ሥራ 17:17) በገበያ ስፍራ በሚሰብክበት ወቅት ግን የተለየ እምነት ያላቸው ሰዎች አገኘ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል የጳውሎስ መልእክት “አዲስ ትምህርት” የሆነባቸው ፈላስፎችና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል። እነሱም “ለጆሯችን እንግዳ የሆነ ነገር እያሰማኸን ነው” አሉት።—ሥራ 17:18-20
7. የሐዋርያት ሥራ 17:22, 23 እንደሚናገረው ጳውሎስ በሚሰብክበት መንገድ ላይ ምን ማስተካከያ አድርጓል?
7 የሐዋርያት ሥራ 17:22, 23ን አንብብ። ጳውሎስ በአቴንስ ላገኛቸው አሕዛብ መልእክቱን የተናገረው፣ በምኩራብ ውስጥ ላገኛቸው አይሁዳውያን በሰበከበት መንገድ አይደለም። ጳውሎስ ‘እነዚህ የአቴንስ ነዋሪዎች የሚያምኑበት ነገር ምንድን ነው?’ ብሎ ራሱን ጠይቆ ሊሆን ይችላል። በአካባቢው ያሉትን ነገሮችና ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውን በሚገባ አስተውሏል። ከዚያም ጳውሎስ እነሱ አምልኳቸውን የሚያካሂዱበትን መንገድና በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን እውነት በጋራ የሚያስማማ ነገር ለማግኘት ጥረት አድርጓል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ እንዲህ ብለዋል፦ “[ጳውሎስ] ከአይሁድ እምነት የመጣ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን አይሁዳውያንና ክርስቲያኖች ‘እውነተኛ’ ብለው የሚያመልኩትን አምላክ አረማዊ የሆኑት ግሪካውያን እንደማያመልኩት ተገንዝቦ ነበር፤ ሆኖም እሱ የሚሰብክላቸው አምላክ ለአቴናውያኑ በእርግጥ እንግዳ እንዳልሆነ ሊያስረዳቸው ጥረት አድርጓል።” ይህም ጳውሎስ አቀራረቡን እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ፈቃደኛ እንደነበር ያሳያል። እሱ የሚሰብከው መልእክት የመጣው እነሱ ‘የማይታወቅ አምላክ’ በማለት ከሚያመልኩት አምላክ እንደሆነ ለአቴናውያኑ ነግሯቸዋል። እነዚህ አሕዛብ ቅዱሳን መጻሕፍትን ባያውቁም ጳውሎስ ክርስቲያን የመሆን ተስፋ እንደሌላቸው አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ለአጨዳ እንደደረሰ አዝመራ አድርጎ የተመለከታቸው ሲሆን ለእነሱ ሲል ምሥራቹን በሚሰብክበት መንገድ ላይ ማስተካከያ አድርጓል።
8. (ሀ) በክልላችሁ ያሉ ሰዎች ሃይማኖታቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? (ለ) አንድ ሰው የራሱ ሃይማኖት እንዳለው ከነገራችሁ ምን ብላችሁ መልስ መስጠት ትችላላችሁ?
8 እናንተም እንደ ጳውሎስ አስተዋይ ሁኑ። በክልላችሁ ያሉ ሰዎች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች የሚጠቁሙ ምልክቶችን ፈልጉ። የቤቱ ባለቤት ቤቱ ወይም መኪናው ላይ ምን ዓይነት ጌጥ አድርጓል? የግለሰቡ ስም፣ አለባበስ፣ ፀጉር፣ ጢም ሌላው ቀርቶ የሚጠቀምባቸው ቃላት ስለ ሃይማኖቱ ምን ይጠቁማሉ? ወይም ደግሞ ግለሰቡ የራሱ ሃይማኖት እንዳለው በቀጥታ ነግሯችሁ ሊሆን ይችላል። ፍሉቱራ የተባለች አንዲት ልዩ አቅኚ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማት ‘የመጣሁት እምነቴን እንድትቀበል ለመጫን ሳይሆን ከአንተ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ነው’ ብላ መልስ ትሰጣለች።
9. ሃይማኖተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር የሚያስማሟችሁ ምን ርዕሰ ጉዳዮች አሉ?
9 ሃይማኖተኛ ከሆነ ሰው ጋር የትኞቹን ጉዳዮች አንስታችሁ መወያየት ትችላላችሁ? በጋራ የሚያስማማችሁን ነገር ፈልጉ። ለምሳሌ፣ ግለሰቡ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ያምን ይሆናል፤ ኢየሱስን የሰው ዘር አዳኝ አድርጎ ሊቀበል ይችላል፤ ወይም ደግሞ የምንኖርበት የክፋት ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ ያምን ይሆናል። በጋራ የሚያስማማችሁን ነገር መሠረት በማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ግለሰቡን በሚማርክ መንገድ ለመናገር ጥረት አድርጉ።
10. ምን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል? ለምንስ?
10 ሰዎች ሃይማኖታቸው የሚያስተምራቸውን እያንዳንዱን ነገር አምነው ላይቀበሉ እንደሚችሉ አስታውሱ። በመሆኑም የአንድን ሰው ሃይማኖት ካወቃችሁ በኋላም እንኳ እሱ በግሉ የሚያምንበትን ነገር ለማወቅ ሞክሩ። ዴቪድ የተባለ በአውስትራሊያ የሚኖር አንድ ልዩ አቅኚ “በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸው የሚያስተምራቸውን ነገር ከፍልስፍና ጋር ይቀላቅላሉ” ብሏል። በአልባኒያ የምትኖረው ዶናልታ “አገልግሎት ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሰዎች ሃይማኖት እንዳላቸው ቢገልጹም በአምላክ እንደማያምኑ በኋላ ላይ ይናገራሉ” ብላለች። በአርጀንቲና የሚኖር አንድ ሚስዮናዊ እንዳስተዋለው ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በሥላሴ እንደሚያምኑ ቢናገሩም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ናቸው ብለው አያምኑም። ሚስዮናዊው “ይህን ማወቃችን ከግለሰቡ ጋር የሚያስማማንን ነገር ማግኘት ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል” ብሏል። ከዚህ አንጻር ሰዎች በእርግጥ የሚያምኑበትን ነገር ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ይህን ካደረጋችሁ እንደ ጳውሎስ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” መሆን ትችላላችሁ።—1 ቆሮ. 9:19-23
ትኩረታቸውን የሚስበው ነገር ምንድን ነው?
11. በሐዋርያት ሥራ 14:14-17 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ጳውሎስ ምሥራቹን በልስጥራ ያሉ ሰዎችን በሚማርክ መንገድ የሰበከው እንዴት ነው?
11 የሐዋርያት ሥራ 14:14-17ን አንብብ። ጳውሎስ የአድማጮቹን ትኩረት የሚስበውን ነገር ካስተዋለ በኋላ የሚሰብክበትን መንገድ እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ጥረት ያደርግ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በልስጥራ የመሠከረላቸው ሰዎች ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ቢያውቁ እንኳ እውቀታቸው በጣም ውስን ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ እነሱን ለማሳመን የተጠቀመባቸው ነጥቦች ሰዎቹ በሚያውቋቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። ለምሳሌ፣ ፍሬያማ ምርት ስለ ማግኘትና ደስተኛ ስለ መሆን ተናግሯል። የተጠቀመባቸው ቃላትና ምሳሌዎች አድማጮቹ በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ ነበሩ።
12. የአንድን ሰው ትኩረት የሚስበውን ነገር ማወቅና አቀራረባችሁን እንደ ሁኔታው ማስተካከል የምትችሉት እንዴት ነው?
12 በክልላችሁ ያሉ ሰዎችን ትኩረት የሚስበውን ነገር ለማስተዋልና አቀራረባችሁን እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ጥረት አድርጉ። ታዲያ አንድን ሰው ከማነጋገራችሁ ወይም አንድን ቤት ከማንኳኳታችሁ በፊት የግለሰቡን ትኩረት የሚስበው ምን እንደሆነ ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? አሁንም ቁልፉ፣ አስተዋይ መሆን ነው። ግለሰቡ አትክልት እየተንከባከበ፣ መጽሐፍ እያነበበ፣ መኪና እየጠገነ ወይም ሌላ ሥራ እየሠራ ሊሆን ይችላል። ታዲያ በሚሠራው ነገር ላይ ተመሥርታችሁ ውይይት መጀመር ትችሉ ይሆን? (ዮሐ. 4:7) ግለሰቡ የለበሰው ልብስ እንኳ ስለ እሱ ለምሳሌ ስለ አገሩ፣ ስለ ሥራው ወይም ስለሚወደው የስፖርት ቡድን የሚጠቁመው ነገር ሊኖር ይችላል። ጉስታቮ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የአንድ ታዋቂ ዘፋኝ ምስል ያለበትን ቲሸርት ከለበሰ የ19 ዓመት ወጣት ጋር ውይይት ጀመርኩ። ስለ ቲሸርቱ ስጠይቀው ወጣቱ ይህን ዘፋኝ የሚወደው ለምን እንደሆነ ነገረኝ። በዚህ መንገድ የጀመርነው ጭውውት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና በር ከፈተ፤ ይህ ወጣት በአሁኑ ወቅት ወንድማችን ሆኗል።”
13. አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ስንጋብዝ ጉጉት እንዲያድርበት በሚያደርግ መንገድ ግብዣውን ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?
13 አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ስትጋብዙ ግብዣውን የምታቀርቡበት መንገድ ጉጉት እንዲያድርበት የሚያደርግ ይሁን፤ ማጥናቱ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝለት ግለጹለት። (ዮሐ. 4:13-15) ለምሳሌ ያህል፣ ፍላጎት ያሳየች አንዲት ሴት ፖፒ የተባለችን አንዲት እህት ወደ ቤቷ እንድትገባ ጋበዘቻት። ፖፒ፣ ሴትየዋ ስለ ትምህርት አሰጣጥ ያጠናች ፕሮፌሰር እንደሆነች የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ግድግዳ ላይ ተለጥፎ አየች፤ በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮችም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራምና በስብሰባዎች አማካኝነት ሰዎችን እንደሚያስተምሩ ጎላ አድርጋ ገለጸችላት። ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች፤ በቀጣዩ ቀን ወደ ስብሰባ የሄደች ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በወረዳ ስብሰባ ላይ ተገኘች። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ተጠመቀች። እንግዲያው ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ተመላልሶ መጠየቅ የማደርግላቸውን ሰዎች ትኩረት የሚስበው ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲጓጉ በሚያደርግ መንገድ ግብዣውን ላቀርብላቸው የምችለውስ እንዴት ነው?’
14. መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠኑ፣ ለእያንዳንዱ ተማሪ በሚስማማ መንገድ ጥናቱን መምራት የምትችሉት እንዴት ነው?
14 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመራችሁ በኋላ ለእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ተዘጋጁ፤ በምትዘጋጁበት ወቅት የተማሪውን አስተዳደግ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ያሳለፈውን ሕይወትና ትኩረቱን የሚስቡትን ነገሮች ግምት ውስጥ አስገቡ። ለተማሪው የትኞቹን ጥቅሶች እንደምታነብቡ፣ የትኞቹን ቪዲዮዎች እንደምታሳዩ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማብራራት የትኞቹን ምሳሌዎች እንደምትጠቀሙ አስቀድማችሁ ወስኑ። ‘ጥናቴን የሚማርከውና ልቡን የሚነካው ምንድን ነው?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። (ምሳሌ 16:23) ፍሎራ ከተባለች አቅኚ ጋር የምታጠና በአልባኒያ የምትኖር አንዲት ሴት “የትንሣኤን ትምህርት መቀበል ይከብደኛል” በማለት ለአስጠኚዋ አቋሟን ጠንከር አድርጋ ነግራት ነበር። ፍሎራ፣ ጥናቷ ይህን ትምህርት እንድትቀበል አልተጫነቻትም። ፍሎራ “በመጀመሪያ፣ የትንሣኤን ተስፋ ስለሰጠው አምላክ የበለጠ ማወቋ የተሻለ እንደሆነ ተሰማኝ” ብላለች። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ፍሎራ በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ስለ ይሖዋ ፍቅር፣ ጥበብና ኃይል ጎላ አድርጋ ለጥናቷ ትነግራት ጀመር። በኋላ ላይ ጥናቷ የትንሣኤን ትምህርት ተቀበለች። ይህች ሴት በአሁኑ ወቅት ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።
ወደፊት ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደሚችሉ አስቡ
15. በሐዋርያት ሥራ 17:16-18 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ በየትኞቹ የግሪካውያን ልማዶች ተረብሾ ነበር? ሆኖም አቴናውያኑ እንደማይለወጡ ያላሰበው ለምንድን ነው?
15 የሐዋርያት ሥራ 17:16-18ን አንብብ። የአቴንስ ከተማ በጣዖት አምልኮ፣ በፆታ ብልግናና በአረማዊ ፍልስፍና የተሞላች ብትሆንም ጳውሎስ፣ አቴናውያኑ ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደማይችሉ አላሰበም፤ የሰዎቹ ስድብም ቢሆን ተስፋ እንዲያስቆርጠው አልፈቀደም። ጳውሎስ ራሱ ‘አምላክን የሚሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበረ’ ቢሆንም በኋላ ላይ ክርስቲያን ሊሆን ችሏል። (1 ጢሞ. 1:13) ኢየሱስ፣ ጳውሎስ ወደፊት የእሱ ተከታይ ሊሆን እንደሚችል እንደተሰማው ሁሉ ጳውሎስም ለአቴናውያኑ ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው። ደግሞም ውጤቱ እንደሚያሳየው ጳውሎስ በእነሱ ላይ እንዲህ ያለ እምነት መጣሉ ተገቢ ነበር።—ሥራ 9:13-15፤ 17:34
16-17. ሁሉም ዓይነት ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳየው ምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉም ዓይነት ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ነበር። ጳውሎስ የግሪካውያን ከተማ በሆነችው በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አንዳንድ የጉባኤው አባላት ቀደም ሲል ወንጀለኞች እንደነበሩ ወይም በሥነ ምግባር ረገድ ያዘቀጠ ሕይወት እንደነበራቸው ገልጿል። ከዚያም “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም . . . ታጥባችሁ ነጽታችኋል” ብሏቸዋል። (1 ቆሮ. 6:9-11) እናንተ ብትሆኑ ኖሮ እነዚህ ሰዎች ተለውጠው ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ይችላሉ ብላችሁ ታስቡ ነበር?
17 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ሲሉ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል። በአውስትራሊያ የምትኖር ዩኪና የተባለች ልዩ አቅኚ፣ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ካጋጠማት ሁኔታ ተምራለች። ዩኪና ሰውነቷ ላይ የተለያዩ ንቅሳቶች ካሏትና በጣም ሰፋፊ የሆኑ ልብሶች ከለበሰች ወጣት ጋር በአንድ የሽያጭ ቢሮ ውስጥ ተገናኘች። ዩኪና እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ልጅቷን ለማነጋገር አመንትቼ ነበር፤ በኋላ ግን አነጋገርኳት። በዚህ ወቅት ልጅቷ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዳላት እንዲያውም አንዳንዶቹ ንቅሳቶቿ ከመዝሙር መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ እንደሆኑ አስተዋልኩ።” ይህች ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች።b
18. በሰዎች ላይ መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው?
18 ኢየሱስ አዝመራው ለአጨዳ እንደደረሰ የተናገረው ብዙ ሰዎች የእሱ ተከታይ እንደሚሆኑ ይጠብቅ ስለነበረ ነው? በፍጹም! በእሱ የሚያምኑት ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቁጥራቸው ጥቂት እንደሚሆን ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው ተናግረው ነበር። (ዮሐ. 12:37, 38) በተጨማሪም ኢየሱስ የሰዎችን ልብ የማንበብ ተአምራዊ ችሎታ ነበረው። (ማቴ. 9:4) ኢየሱስ እሱን ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ጥቂት ሰዎችን በመርዳት ላይ ትኩረት ቢያደርግም ለሁሉም ሰው በቅንዓት ሰብኳል። የሰዎችን ልብ የማንበብ ችሎታ የሌለን እኛማ በአንድ ክልል ወይም በአንድ ግለሰብ ላይ እንዳንፈርድ መጠንቀቅ እንዳለብን የታወቀ ነው! ከዚህ ይልቅ ሰዎች ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰብ አለብን። በቡርኪና ፋሶ ሚስዮናዊ ሆኖ የሚያገለግለው ማርክ እንዲህ ብሏል፦ “እድገት እንደሚያደርጉ የማስባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ማጥናታቸውን ያቆማሉ። ብዙም አይገፉም ብዬ ያሰብኳቸው ሰዎች ደግሞ ጥሩ እድገት ሲያደርጉ አይቻለሁ። ስለዚህ የይሖዋ መንፈስ ወደመራን አቅጣጫ መጓዝ የተሻለ እንደሆነ ተምሬያለሁ።”
19. በክልላችን ውስጥ ላሉ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
19 የክልላችንን ሁኔታ በጥቅሉ ስናየው ብዙዎቹ ሰዎች ለአጨዳ እንደደረሰ አዝመራ እንዳልሆኑ ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን አስታውሱ። አዝመራው ነጥቷል ማለትም ለአጨዳ ደርሷል። ሰዎች ለውጥ አድርገው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ይችላሉ። ይሖዋ ደቀ መዝሙር የመሆን ተስፋ ያላቸውን እነዚህን ሰዎች ‘እንደከበሩ ነገሮች’ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሐጌ 2:7) ለሰዎች የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት ካለን አስተዳደጋቸውንና ትኩረታቸውን የሚስቡትን ነገሮች ለማወቅ ጥረት እናደርጋለን። እነሱን እንደ ባዕድ ሰው ሳይሆን የወደፊት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን።
መዝሙር 57 ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መስበክ
a ኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ ለአድማጮቻቸው ምን አመለካከት እንደነበራቸው እናያለን፤ እኛም ሰዎች የሚያምኑባቸውንና ትኩረታቸውን የሚስቡትን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ወደፊት ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ ረገድ የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
b ሰዎች ለውጥ ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ተጨማሪ ምሳሌዎች “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው ተከታታይ ርዕስ ሥር ይገኛሉ። ይህ ተከታታይ ርዕስ እስከ 2017 ድረስ መጠበቂያ ግንብ ላይ ይወጣ ነበር። አሁን ግን የሚገኘው jw.org® ላይ ነው። ስለ እኛ > ተሞክሮዎች በሚለው ሥር ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት ከቤት ወደ ቤት እያገለገሉ ሳለ የሚከተሉትን ነገሮች አስተዋሉ፦ (1) አበቦች ያሉበትና የሚያምር ቤት፣ (2) ትናንሽ ልጆች ያሉበት ቤት፣ (3) ውስጡም ሆነ ውጩ የተዝረከረከ ቤት፣ (4) ሃይማኖተኛ ሰው ያለበት ቤት። ደቀ መዝሙር የመሆን አጋጣሚው ከፍተኛ የሆነው የቤት ባለቤት የትኛው ይመስላችኋል?