መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’—እንዴት?
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ነፃ እንደሆኑ ይሰማቸዋል፤ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች በአጉል እምነት ተተብትበዋል። ሌሎች ደግሞ ሙታንን ስለሚፈሩ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ ሥርዓቶችን በመፈጸም እነሱን ለማስደሰት ይጥራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሰው ሲሞት ምን እንደሚሆን ስለማያውቁ ሞትን ከመጠን በላይ ይፈራሉ። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሰዎች በአእምሯቸውና በስሜታቸው አልፎ ተርፎም በኢኮኖሚያቸው ላይ ጫና ከሚያሳድሩ ነገሮች ነፃ መውጣት ይችላሉ? አዎን፣ ይችላሉ! ቀደም ሲል ከተጠቀሰውና ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገረው ሐሳብ መመልከት እንደሚቻለው ነፃነት ሊገኝ የሚችለው እውነትን በማወቅ ብቻ ነው። ግን የትኛውን እውነት? በአጠቃላይ እውነት የሆነን ነገር ወይስ መንፈሳዊ እውነትን?
ኢየሱስ የዚህን ጥያቄ መልስ በግልጽ ተናግሯል።“በቃሌ ብትኖሩ . . . እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:31, 32) የኢየሱስ ‘ቃል’ ማለትም ያስተማራቸው ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ።
ኢየሱስ “እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ሲል በዋነኝነት እየተናገረ የነበረው ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ስለመውጣት ነው። ያም ሆኖ ስለ አምላክ ቃል እውነቱን ማወቅ ከአጉል እምነት፣ ሙታንን ከመፍራት እንዲሁም ሞትን ከመጠን በላይ ከመፍራትና እነዚህን ከመሳሰሉ ነገሮችም ነፃ ያወጣናል። ታዲያ እውነት ነፃ የሚያወጣን እንዴት ነው?
1. ከአጉል እምነት ነፃ መውጣት። ብዙ ሰዎች፣ አንዳንድ ዕቃዎች ወይም ቁጥሮች መጥፎ ነገር ያስከትላሉ ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ የጥሩ ገድ ምልክት ካላዩ አሊያም ኮከብ ቆጣሪዎችን ወይም መናፍስት ጠሪዎችን ካላማከሩ ከባድ የሆኑ ውሳኔዎችን አያደርጉም።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነፃ የሚያወጣው እንዴት ነው? በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በአጉል እምነት ከመጠላለፋቸው የተነሳ “ዕድል” እና “ዕጣ ፈንታ” የተባሉ አማልክትን እስከ ማምለክ ደርሰው ነበር! ታዲያ ይሖዋ ይህን ጉዳይ እንዴት ተመለከተው? “በፊቴ ክፉ ነገር [አደረጋችሁ]” ብሏቸዋል። (ኢሳይያስ 65:11, 12) አምላክ፣ በሕይወት ውስጥ መመሪያ ለማግኘት መናፍስት ጠሪዎችን ስለሚጠይቁ ሰዎችም ቢሆን ያለው አመለካከት ተመሳሳይ ነው፤ ምክንያቱም “መናፍስት ጠሪ . . . ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።”—ዘዳግም 18:11, 12
አጉል እምነቶችም ሆኑ መናፍስት ጠሪዎች ኢየሱስ “የውሸት አባት” ብሎ የጠራው “ዲያብሎስ” የሚጠቀምባቸው “መሠሪ ዘዴዎች” ናቸው፤ በመሆኑም ጉዳት ያስከትላሉ። (ዮሐንስ 8:44፤ ኤፌሶን 6:11) ስለ አንድ ወሳኝ ጉዳይ ምክር ለማግኘት ብትፈልግ ውሸታም የሆነን ሰው ታማክራለህ? እንደዚያ እንደማታደርግ የተረጋገጠ ነው! በመሆኑም ‘ከውሸት አባት’ ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር መራቅህ ብልህነት ነው።
በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዳን ዋነኛው ነገር ጥበብ ነው፤ ይህን ጥበብ ለማዳበር ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሰፈሩት መመሪያዎችና አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ያስፈልገናል። ምሳሌ 2:6 “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል” በማለት ይናገራል።
2. ሙታንን ከመፍራት ነፃ መውጣት። ብዙ ሰዎች የሞቱ ዘመዶቻቸው “መናፍስት” በመሆን በሕይወት ባሉት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚችሉ ያምናሉ። እንዲሁም የተለያዩ መሥዋዕቶችን በማቅረብ ካልተለማመኑ እነዚህ “መናፍስት” እንደሚቆጡ ይሰማቸዋል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች መሥዋዕቶችን ለማቅረብና ሌሎች ሥነ ሥርዓቶችን ለማካሄድ ብዙ ገንዘብ ስለሚያወጡ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ይዘፈቃሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነፃ የሚያወጣው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ ይሰጣል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ ሙታን ‘እንደተኙ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 11:11, 14) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? መልሱ በመክብብ 9:5 ላይ የሚገኝ ሲሆን ጥቅሱ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ይላል። አዎን፣ ሙታን ከባድ እንቅልፍ ላይ እንዳለ ሰው ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። እንዲያውም ከሕልውና ውጪ ስለሆኑ ሊጠቅሙንም ሆነ ሊጎዱን አይችሉም።
ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ከሞቱ ሰዎች ጋር እንደተገናኙ ይናገራሉ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የአምላክ ቃል ለዚህ ጥያቄም ቢሆን መልስ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጆች ከተፈጠሩ ብዙም ሳይቆይ በርካታ መላእክት በአምላክ ላይ እንዳመጹ ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 2:4) አጋንንት ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ክፉ መናፍስት የሰው ልጆችን ለማሳሳት ጥረት ያደርጋሉ። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ይህን የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ ደግሞ የሞቱ ሰዎችን መስለው በመቅረብ ነው፤ በዚህ መንገድ ‘ሙታን የተለየ አካል ይዘው በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ናቸው’ የሚለውን ውሸት ያስፋፋሉ።
3. ሞትን ከመጠን በላይ ከመፍራት ነፃ መውጣት። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በእርግጥም ሞት የሰው ልጆች ዋነኛ ጠላት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:26) በመሆኑም ሞትን መፍራታችን ወይም መሞት አለመፈለጋችን የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ያም ቢሆን ሞትን ከመጠን በላይ መፍራት አይኖርብንም።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነፃ የሚያወጣው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ በትክክል የሚናገር ከመሆኑም በላይ አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት ሙታንን የማስነሳት ዓላማ እንዳለውም ይገልጻል። ኢየሱስ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት እንደሚመጣ’ እና ሙታን ከመቃብር ‘እንደሚወጡ’ ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15
ሙታን ‘የሚወጡት’ ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው? ኢየሱስ ጥቂት ሰዎችን ከሞት ባስነሳ ጊዜ የሆነው ነገር የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ የሚረዳ ፍንጭ ይሰጠናል። ኢየሱስ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች በሙሉ ሕያው የሆኑት ቀድሞ የነበራቸውን ሰብዓዊ አካል ይዘው ነው። (ማርቆስ 5:35-42፤ ሉቃስ 7:11-17፤ ዮሐንስ 11:43, 44) ይህ ሐቅ “መነሳት” የሚል ትርጉም ካለው “ትንሣኤ” ከሚለው ቃል ጋር ይስማማል። አምላክ እሱን ያገለግል ለነበረውና በዕድሜ ለገፋው ለዳንኤል እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ ታርፋለህ፤ በቀኖቹ መጨረሻም ተነሥተህ የተመደበልህን ርስት ትቀበላለህ።” (ዳንኤል 12:13) ይህ ሐሳብ ዳንኤል ሞትን በድፍረትና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጋፈጥ ረድቶት መሆን አለበት!
ኢየሱስ የተሰጠው ተልእኮ “ለተማረኩት ነፃነትን” መስበክን ይኸውም በሐሰት እምነት ባርነት ሥር የወደቁ ሰዎችን ነፃ ማውጣትን ይጨምራል። (ሉቃስ 4:18) ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው አሁንም ድረስ ሰዎች ነፃ እንዲወጡ እየረዱ ነው። አንተም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው እውነት አማካኝነት ዘላቂ ነፃነት እንድታገኝ ልባዊ ምኞታችን ነው።
ይህን አስተውለኸዋል?
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቀጥሎ ከተዘረዘሩት ነገሮች ነፃ የሚያወጣን እንዴት ነው?
● ከአጉል እምነት?—ኢሳይያስ 8:19, 20፤ 65:11, 12
● ሙታንን ከመፍራት?—መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11, 14
● ሞትን ከመጠን በላይ ከመፍራት?—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሰዎችን ከአጉል እምነት፣ ሙታንን ከመፍራት እንዲሁም ሞትን ከመጠን በላይ ከመፍራት ነፃ ያወጣል