ትንቢት የሚያተኩረው በክርስቶስ ላይ ነው
“የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነው።”—ራእይ 19:10
1, 2. (ሀ) እስራኤላውያን ከ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጀምሮ ውሳኔ የሚጠይቅ ምን ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
ጊዜው 29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን እስራኤል ውስጥ ወሬው ሁሉ ተስፋ ስለተደረገበት መሲሕ ሆኗል። የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት መሲሑን ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት ጨምሮታል። (ሉቃስ 3:15) ዮሐንስ እርሱ ክርስቶስ አለመሆኑን በግልጽ ነገራቸው። እንዲያውም ወደ ናዝሬቱ ኢየሱስ እያመለከተ “እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ” አለ። (ዮሐንስ 1:20, 34) ብዙም ሳይቆይ ሰዎች ትምህርቱን ለማዳመጥና ፈውስ ለማግኘት ኢየሱስን ይከተሉት ጀመር።
2 ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ወራት ይሖዋ ልጁን በተመለከተ እጅግ በርካታ ማስረጃ አቀረበ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ሲያጠኑ የነበሩና ኢየሱስ ያከናወናቸውን ሥራዎች የተመለከቱ ሰዎች በእርሱ ላይ እምነት እንዲጥሉ የሚያደርግ አሳማኝ ምክንያት አላቸው። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ እምነት እንደሚጎድለው አሳየ። ኢየሱስ በመንፈስ የተቀባ የአምላክ ልጅ መሆኑን የተቀበሉት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ በጣም ጥቂቶች ናቸው። (ዮሐንስ 6:60-69) በዚያን ዘመን ብትኖር ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ተቀብለህ የእርሱ ታማኝ ተከታይ ትሆን ነበር? ኢየሱስ የሰንበትን ሕግ ጥሰሃል ተብሎ በተከሰሰበት ወቅት ማንነቱን በሚመለከት የሰጠውን መልስና በሌላ ጊዜ ደግሞ የታማኝ ደቀ መዛሙርቱን እምነት ለማጠናከር ሲል ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ተመልከት።
ኢየሱስ ራሱ ማስረጃ አቀረበ
3. ኢየሱስ ስለ ራሱ ማንነት ማስረጃ እንዲያቀርብ የገፋፋው ምንድን ነው?
3 ጊዜው 31 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የማለፍ በዓል የሚከበርበት ወቅት ሲሆን ኢየሱስ ያለው በኢየሩሳሌም ነው። ለ38 ዓመታት በበሽታ ሲማቅቅ የነበረን ሰው በሰንበት ዕለት ስለፈወሰ አይሁዳውያን ያሳድዱት ጀመር። አምላክን ተሳድቧል ብለው የወነጀሉት ከመሆኑም ሌላ ‘አምላክ አባቴ ነው’ ብሏል በሚል ሊገድሉት ፈለጉ። (ዮሐንስ 5:1-9, 16-18) ኢየሱስ ስለ ራሱ ያቀረበው የመከላከያ ሐሳብ ማንኛውም ልበ ቅን አይሁዳዊ የኢየሱስን ትክክለኛ ማንነት እንዲቀበል የሚያስችል ሦስት ጠንካራ ማስረጃዎች ይዟል።
4, 5. የዮሐንስ አገልግሎት ዓላማ ምን ነበር? ሥራውንስ ምን ያህል በሚገባ አከናውኗል?
4 በመጀመሪያ ኢየሱስ ከእርሱ በፊት መንገድ ጠራጊ ሆኖ የመጣው መጥምቁ ዮሐንስ የሰጠውን ምሥክርነት በማመልከት እንዲህ አለ:- “ወደ ዮሐንስ ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል፤ ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሰኙ ወደዳችሁ።”—ዮሐንስ 5:33, 35
5 መጥምቁ ዮሐንስ “እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት” ሊባል የቻለው ሄሮድስ እርሱን ያለ ጥፋቱ ከማሳሰሩ በፊት ለመሲሑ መንገድ እንዲያዘጋጅ የተሰጠውን መለኮታዊ ተልእኮ የተወጣ በመሆኑ ነው። ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም [መሲሑ] በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው። . . . መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።”a (ዮሐንስ 1:26-37) ዮሐንስ፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በግልጽ በመናገር ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን አሳውቋል። ዮሐንስ የሰጠው ምሥክርነት ምንም የማያሻማ ከመሆኑ የተነሳ ከሞተ ከስምንት ወር ገደማ በኋላ ልበ ቅን የሆኑ በርካታ አይሁዳውያን “ዮሐንስ . . . ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” ብለዋል።—ዮሐንስ 10:41, 42
6. ኢየሱስ ያከናወናቸው ሥራዎች የአምላክ ድጋፍ እንዳለው ሰዎችን እንዲያምኑ የሚያስችላቸው እንዴት ነው?
6 በመቀጠል ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላም ማስረጃ አቀረበ። የሚያከናውናቸው መልካም ሥራዎች የአምላክ ድጋፍ እንዳለው እንደሚያረጋግጡ ጠቀሰ። “እኔ . . . ከዮሐንስ ምስክርነት የላቀ ምስክር አለኝ፤ እንድፈጽመው አብ የሰጠኝ፣ እኔም የምሠራው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል” አለ። (ዮሐንስ 5:36) በርካታ ተአምራትን የሚያጠቃልለውን ይህን ማስረጃ ጠላቶቹ እንኳ ሊክዱ አልቻሉም። ከጊዜ በኋላ አንዳንዶች “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለ ሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል። (ዮሐንስ 11:47) አንዳንዶች ግን በጎ ምላሽ በመስጠት “ታዲያ፣ ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ሰው ከሚሠራቸው ታምራዊ ምልክቶች የበለጠ ያደርጋል?” አሉ። (ዮሐንስ 7:31) ኢየሱስን የሚያዳምጡ ሰዎች በልጁ ላይ የሚንጸባረቀውን የአብን ባሕርይ ማስተዋል የሚችሉበት ግሩም አጋጣሚ አግኝተዋል።—ዮሐንስ 14:9
7. የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ኢየሱስ የሚመሠክሩት እንዴት ነው?
7 በመጨረሻ ኢየሱስ ማንም ሊክደው የማይችል ማስረጃ አቀረበ። ኢየሱስ “መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው” ካለ በኋላ “ሙሴን ብታምኑ ኖሮ፣ እኔን ባመናችሁ ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ የጻፈው ስለ እኔ ነው” አላቸው። (ዮሐንስ 5:39, 46) እርግጥ ከክርስትና በፊት ከሙሴ ሌላ ስለ ክርስቶስ የጻፉ ሌሎች በርካታ ምሥክሮች አሉ። እነዚህ ምሥክሮች ከጻፏቸው ነገሮች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶችና በዝርዝር የሠፈሩ የትውልድ ሐረጎች የሚገኙበት ሲሆን ሁሉም መሲሑን ለማወቅ ይረዳሉ። (ሉቃስ 3:23–38፤ 24:44-46፤ የሐዋርያት ሥራ 10:43) ስለ ሙሴስ ሕግ ምን ለማለት ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰን ሞግዚታችን ሆነ” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 3:24) አዎ፣ “የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና፤” ይህም ማለት ትንቢት የሚነገርበት ዋና ዓላማና ምክንያት ስለ ኢየሱስ ለመመሥከር ነው።—ራእይ 19:10
8. ብዙ አይሁዳውያን በመሲሑ ሳያምኑ የቀሩት ለምን ነበር?
8 እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች ማለትም ዮሐንስ የሰጠው የማያሻማ ምሥክርነት፣ ኢየሱስ ራሱ ያከናወነው ተአምራዊ ሥራና ያንጸባረቀው አምላካዊ ባሕርይ እንዲሁም ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙት እጅግ በርካታ ማስረጃ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አምነህ እንድትቀበል አያደርግህም? አምላክንና ቃሉን ከልብ የሚወድድ ማንኛውም ሰው ይህን በቀላሉ ከማስተዋሉም ሌላ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን አምኖ ይቀበላል። አብዛኞቹ እስራኤላውያን ግን እንዲህ ዓይነት ፍቅር አልነበራቸውም። ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን “የእግዚአብሔርም ፍቅር በልባችሁ እንደሌለ ዐውቃለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 5:42) “ከአንዱ አምላክ የሚመጣውን ክብር” ከመፈለግ ይልቅ ‘እርስ በርሳቸው ክብር ይሰጣጡ’ ነበር። በመሆኑም ልክ እንደ አባቱ እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ የሚጠላውን ኢየሱስን መቃወማቸው ምንም አያስገርምም።—ዮሐንስ 5:43, 44፤ የሐዋርያት ሥራ 12:21-23
እምነት የሚያጠናክር ትንቢታዊ ራእይ
9, 10. (ሀ) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምልክት ያሳየው በአስፈላጊው ጊዜ ነው የሚባለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ቃል የገባላቸው አስደናቂ ነገር ምንድን ነው?
9 ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጠውን ከላይ የተጠቀሰውን ማስረጃ ካቀረበ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። በ32 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተከበረውም የቂጣ በዓል አልፏል። በኢየሱስ አምነው የነበሩ ብዙ ሰዎች በስደት፣ በፍቅረ ነዋይ ወይም በኑሮ ጭንቀቶች የተነሳ ሳይሆን አይቀርም እርሱን መከተል አቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ ሰዎች ሊያነግሡት ሲሞክሩ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ግራ የተጋቡና ተስፋ የቆረጡ ይመስላል። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተአምር እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ ራሱን ለማስከበር ሲል ከሰማይ ምልክት ለማሳየት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። (ማቴዎስ 12:38, 39) ይህን ጥያቄያቸውን አለማስተናገዱ አንዳንዶቹን ግራ ሳያጋባቸው አልቀረም። ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ፣ በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በኦሪት ሕግ መምህራን እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ” እንዳለው ሲነግራቸው ጉዳዩን መረዳት በጣም ከበዳቸው።—ማቴዎስ 16:21-23
10 ከዘጠኝ እስከ አሥር ወር በሚያህል ጊዜ ውስጥ ‘ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ’ ይደርሳል። (ዮሐንስ 13:1) የታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ሁኔታ በጣም ስላሳሰበው ለእምነት የለሾቹ አይሁዳውያን ነፍጓቸው የነበረውን ያንኑ ነገር ማለትም ከሰማይ የመጣ ምልክት ለአንዳንዶቹ ለማሳየት ተስፋ ሰጣቸው። ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት ሰዎች መካከል የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ” አላቸው። (ማቴዎስ 16:28) ኢየሱስ መሲሐዊው መንግሥት በ1914 እስከሚቋቋምበት ጊዜ ድረስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዶቹ በሕይወት ይኖራሉ ማለቱ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ኢየሱስ በጣም ለሚቀርቡት ሦስት ደቀ መዛሙርቱ በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ ሲቀመጥ የሚኖረውን አስደናቂ ክብር በትንሹ ለማሳየት አስቧል። ክብሩን የገለጠበት ይህ ራእይ የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ ይባላል።
11. ስለ ኢየሱስ መለወጥ የሚገልጸውን ራእይ ተናገር።
11 ይህ ከሆነ ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። ቦታው የአርሞንዔም ተራራ ሸንተረር ሳይሆን አይቀርም። በዚያም ኢየሱስ “በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።” እንዲሁም ነቢዩ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩዋቸው። ይህ አስደናቂ ክንውን የተፈጸመው በምሽት ሳይሆን ስለማይቀር ለራእዩ የበለጠ ድምቀት ሰጥቶታል። እንዲያውም ራእዩ በጣም ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ ጴጥሮስ ለኢየሱስ፣ ለሙሴና ለኤልያስ ሦስት ድንኳን ለመትከል ሐሳብ አቀረበ። ጴጥሮስ ገና ተናግሮ ሳያበቃ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።—ማቴዎስ 17:1-6
12, 13. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ማየታቸው ምን ስሜት አሳድሮባቸዋል? ለምንስ?
12 እርግጥ ጴጥሮስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ፣ “ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” መሆኑን ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 16:16) ይሁንና አምላክ ራሱ በመንፈስ የተቀባውን የልጁን ማንነትና የሚያከናውነውን ሥራ በተመለከተ ማረጋገጫ በመስጠት የምሥክርነት ቃሉን ሲናገር መስማታቸው ምን ዓይነት ስሜት እንደሚያሳድርባቸው ገምት! ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስ ሲለወጥ በራእይ መመልከታቸው እምነታቸውን በጣም አጠናክሮላቸዋል! በዚህ መንገድ እምነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ በመጠናከሩ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ጊዜና ወደፊት በሚቋቋመው ጉባኤ ውስጥ ለሚያበረክቱት ጠቃሚ ድርሻ በተሻለ ሁኔታ ዝግጁ ሆነዋል።
13 የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ በደቀ መዛሙርቱ አእምሮ ላይ የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸው አልፏል። ከ30 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ኢየሱስ] ከግርማዊው ክብር ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርና ሞገስ ተቀብሎአል፤ እኛም ከእርሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል።” (2 ጴጥሮስ 1:17, 18) ዮሐንስም ቢሆን ባየው ነገር የዚያኑ ያህል ስሜቱ በጥልቅ ተነክቶ ነበር። ሁኔታው ከተፈጸመ ከ60 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ የተመለከተውን ራእይ አስታውሶ “ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:14) ይሁንና ተአምራዊ ለውጡ ለኢየሱስ ተከታዮች የተገለጠላቸው የመጨረሻው ራእይ አልነበረም።
የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የተገለጠላቸው ተጨማሪ እውቀት
14, 15. ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስ እስኪመለስ ድረስ በሕይወት የሚኖረው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። እዚያም ጴጥሮስን “[ዮሐንስ] እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው። (ዮሐንስ 21:1, 20-22, 24) ይህ አባባል ሐዋርያው ዮሐንስ ከሌሎቹ ሐዋርያት የበለጠ ዕድሜ እንደሚኖር ያሳያል? ዮሐንስ ለተጨማሪ 70 ዓመታት ያህል ይሖዋን በታማኝነት ስለሚያገለግል እንደዚያ ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የኢየሱስ አባባል ከዚያም የበለጠ ትርጉም አለው።
15 “እስክመለስ ድረስ” የሚሉት ቃላት “የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ” የሚለውን የኢየሱስን አባባል ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 16:28) ዮሐንስ፣ ኢየሱስ እስኪመለስ ድረስ ይኖራል ሲባል ከጊዜ በኋላ ኢየሱስን በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ ተቀምጦ በራእይ ይመለከታል ማለት ነው። ዮሐንስ በሕይወቱ ማብቂያ ገደማ በፍጥሞ ደሴት በስደት ላይ እያለ “በጌታ ቀን” የሚፈጸሙትን ነገሮች የሚገልጹ አስደናቂ ትንቢታዊ ምልክቶች በራእይ ተመለከተ። ዮሐንስ በእነዚህ አስደናቂ ራእዮች ስሜቱ በጥልቅ በመነካቱ ኢየሱስ “አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ” ሲል እርሱ ደግሞ “አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና” በማለት መልሷል።—ራእይ 1:1, 10፤ 22:20
16. እምነታችንን ዘወትር ማጠናከራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ልበ ቅን ሰዎች ኢየሱስን መሲሕ አድርገው የተቀበሉ ከመሆኑም ሌላ በእርሱ አምነዋል። በኢየሱስ ያመኑ ሰዎች በአካባቢያቸው የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች እምነት የለሽ ከመሆናቸው፣ ማከናወን ካለባቸው ሥራ እንዲሁም ከፊት ለፊታቸው ከሚጠብቃቸው ፈተና አንጻር ማበረታቻ ማግኘት አስፈልጓቸው ነበር። ኢየሱስ ታማኝ ተከታዮቹን ለማበረታታት ሲል መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ አቅርቧል፤ እንዲሁም እውቀት የሚጨምሩ ትንቢታዊ ራእዮች ገልጦላቸዋል። በአሁኑ ጊዜ “በጌታ ቀን” መገባደጃ ላይ እንገኛለን። በቅርቡ ክርስቶስ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት በአጠቃላይ ደምስሶ የአምላክን ሕዝቦች ነፃ ያወጣል። እኛም ይሖዋ ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን ባዘጋጀልን ነገሮች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም እምነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል።
በጨለማና በመከራ ወቅት ጥበቃ ማግኘት
17, 18. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሱስ ተከታዮችና የአምላክን ዓላማ ይቃወሙ በነበሩ ሰዎች መካከል ምን የጎላ ልዩነት ይታይ ነበር? የሁለቱ መጨረሻስ ምን ነበር?
17 ከኢየሱስ ሞት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ “በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” ስለ እርሱ እንዲመሠክሩ የሰጣቸውን ትእዛዝ በድፍረት ፈጽመዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ከተመሠረተ ጥቂት ጊዜ የሆነው የክርስቲያን ጉባኤ በተደጋጋሚ ጊዜያት በስደት ማዕበል ቢመታም ይሖዋ መንፈሳዊ እውቀትና ተጨማሪ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በመስጠት ባርኮታል።—የሐዋርያት ሥራ 2:47፤ 4:1-31፤ 8:1-8
18 በሌላ በኩል ደግሞ ምሥራቹን የሚቃወሙ ሰዎች ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊ እየሆነ ሄደ። ምሳሌ 4:19 “የክፉዎች መንገድ ግን እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነው፤ ምን እንደሚያሰናክላቸውም አያውቁም” ይላል። የሮም ወታደሮች በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምን በሚከቡበት ጊዜ ‘ጨለማው’ የከፋ ይሆናል። ሮማውያኑ ባልታወቀ ምክንያት ለጊዜው አፈግፍገው ከቆዩ በኋላ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ተመልሰው በመምጣት ከተማዋን እንዳልነበረች አደረጓት። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንዳለው ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዳውያን ሕይወታቸውን አጡ። ታማኝ ክርስቲያኖች ግን ከጥፋቱ አመለጡ። እንዴት? የሮም ወታደሮች ባፈገፈጉበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን መመሪያ ታዝዘው በመሸሻቸው ነው።—ሉቃስ 21:20-22
19, 20. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲሄድ መፍራት የሌለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ይሖዋ ሕዝቦቹ ምን ነገር እንዲገነዘቡ አድርጓል?
19 የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ከፊታችን የሚጠብቀን ታላቅ መከራ የሰይጣን ሥርዓት በአጠቃላይ የሚያከትምበት ጊዜ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚል ተስፋ ስለሰጠ የአምላክ ሕዝቦች መሸበር አይኖርባቸውም። (ማቴዎስ 28:20) ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ደቀ መዛሙርቱን እምነት ለማጠናከርና ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ጊዜ ለማዘጋጀት መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በሰማይ የሚኖረውን ክብር በራእይ አሳይቷቸዋል። በዚህ ዘመንስ ምን አድርጓል? በ1914 ትንቢታዊው ራእይ በእውን ተፈጸመ። ይህም የአምላክን ሕዝቦች እምነት በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክሯል! ራእዩ ወደፊት አስደሳች ጊዜ እንደሚመጣ አመላካች ሆኗል፤ እንዲሁም የይሖዋ ሕዝቦች ስለ መሲሐዊው መንግሥት ደረጃ በደረጃ ተጨማሪ ማስተዋል አግኝተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨለመ በሚሄደው በዚህ ዓለም ውስጥ “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው።”—ምሳሌ 4:18
20 ከ1914 በፊት እንኳ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ጌታ መመለስ የሚገልጹ መሠረታዊ እውነቶችን መረዳት ችለው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጡላቸው ሁለት መላእክት እንዳመለከቱት ጌታ የሚመለሰው በማይታይ ሁኔታ እንደሚሆን ተረድተው ነበር። ኢየሱስን ደመና ከዓይናቸው ከሰወረው በኋላ ሁለቱ መላእክት “ይህ ከእናንተ ዘንድ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፣ ልክ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል” አሏቸው።—የሐዋርያት ሥራ 1:9-11
21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
21 በተአምር በተለወጠበት ወቅት እንደሆነው ሁሉ ኢየሱስ ሲያርግ ከታማኝ ተከታዮቹ በስተቀር ብዙ ሕዝብ አላየውም። እንዲያውም መላው ዓለም ስለተፈጸመው ሁኔታ የሚያውቀው አንዳች ነገር አልነበረም። ክርስቶስ የመንግሥቱን ሥልጣን ይዞ በሚመለስበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ይሆናል። (ዮሐንስ 14:19) ንጉሣዊ ሥልጣን ይዞ መገኘቱን ማስተዋል የሚችሉት በመንፈስ የተቀቡ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ብቻ ይሆናሉ። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን ግንዛቤ ማግኘታቸው በእነርሱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርና የኢየሱስ ምድራዊ ተገዥዎች የሚሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲሰበስቡ እንደሚያስችላቸው እንመለከታለን።—ራእይ 7:9, 14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት የአምላክን ድምፅ የሰማው ዮሐንስ ብቻ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ ያነጋገራቸው አይሁዶች ግን ‘ከቶ ድምፁን አልሰሙም፤ መልኩንም አላዩም።’—ዮሐንስ 5:37
ታስታውሳለህ?
• ኢየሱስ ሰንበትን ጥሰሃል እንዲሁም አምላክን ሰድበሃል የሚል ክስ በቀረበበት ጊዜ መሲሕ መሆኑን ለማሳየት ያቀረበው ማስረጃ ምን ነበር?
• የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ማየታቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው?
• ኢየሱስ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ዮሐንስ በሕይወት እንደሚኖር ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
• በ1914 ፍጻሜውን ያገኘው ራእይ የትኛው ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አቅርቧል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በራእይ የታየው የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ እምነት የሚያጠናክር ነበር
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ‘እስኪመለስ’ ድረስ በሕይወት እንደሚኖር ተነግሮ ነበር