ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ራእይ እውን ሆነ
“በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም [ለትንቢታዊው] ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ።”—2 ጴጥሮስ 1:19
1. በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ምን ተቃራኒ የሆኑ ሁኔታዎች ይታያሉ?
የዚህ ዓለም ችግር ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚባለው ሆኗል። ተፈጥሮ ከሚያስከትለው አደጋ አንስቶ እስከ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ድረስ በሰው ዘር ላይ የሚፈራረቁት ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ይመስላል። የዓለም ሃይማኖቶች እንኳ ያስገኙት አንዳች መፍትሄ የለም። እንዲያውም ጭፍን አስተሳሰብን፣ ጥላቻንና ብሔራዊ ስሜትን በማራገብ አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታዎች እንዲባባሱ ያደርጋሉ። አዎ፣ በትንቢት እንደተነገረው ‘ድቅድቅ ጨለማ ሕዝቦችን’ ሸፍኗል። (ኢሳይያስ 60:2) በአንጻሩ ደግሞ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት የሚጠባበቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው? “በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት” የሚጠነቀቁትን ያህል ትንቢታዊውን ቃል በትኩረት በመከታተላቸው ነው። እነዚህ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ “ቃል” ወይም መልእክት አካሄዳቸውን እንዲመራላቸው ይፈቅዳሉ።—2 ጴጥሮስ 1:19
2. ዳንኤል ስለ “ፍጻሜው ዘመን” በተናገረው ትንቢት መሠረት መንፈሳዊ ማስተዋል የሚያገኙት እነማን ብቻ ናቸው?
2 ነቢዩ ዳንኤል ‘የፍጻሜውን ዘመን’ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል። ብዙዎች ይነጻሉ፤ ይጠራሉ፤ እንከን አልባም ይሆናሉ፤ ክፉዎች ግን በክፋታቸው ይጸናሉ፤ ከክፉዎች አንዳቸውም አያስተውሉም፤ ጠቢባን ግን ያስተውላሉ።” (ዳንኤል 12:4, 10) መንፈሳዊ ማስተዋል ማግኘት የሚችሉት ከልባቸው ‘ወዲያ ወዲህ የሚራወጡ’ ወይም የአምላክን ቃል በትጋት የሚያጠኑ፣ መመሪያውን የሚያከብሩና ፈቃዱን ለማድረግ የሚጣጣሩ ሰዎች ብቻ ናቸው።—ማቴዎስ 13:11-15፤ 1 ዮሐንስ 5:20
3. በ1870ዎቹ ዓመታት የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተገነዘቡት ዓቢይ ጉዳይ ምን ነበር?
3 ‘የመጨረሻው ዘመን’ ከመጀመሩ በፊት በ1870ዎቹ ዓመታት እንኳ ይሖዋ አምላክ ‘በመንግሥተ ሰማይ ምስጢር’ ላይ ተጨማሪ ብርሃን መፈንጠቅ ጀምሮ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ ማቴዎስ 13:11) በዚያን ጊዜ የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ብዙዎች ከነበራቸው አመለካከት በተለየ የክርስቶስ መመለስ በዓይን እንደማይታይ ተገንዝበው ነበር። ኢየሱስ ወደ ምድር ተመልሷል የሚባለው በሰማይ ንግሥና ከያዘ በኋላ ትኩረቱን ወደ ምድር ሲያደርግ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በግልጽ የሚታዩትን በርካታ ምልክቶች በማስተዋል በዓይን የማይታየው የክርስቶስ መገኘት መጀመሩን ማወቅ ይችላሉ።—ማቴዎስ 24:3-14
ትንቢታዊው ራእይ እውን ሆነ
4. ይሖዋ በዚህ ዘመን ያሉ አገልጋዮቹን እምነት ያጠናከረው እንዴት ነው?
4 የክርስቶስ ተአምራዊ ለውጥ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሲሆን የሚጎናጸፈውን ክብር በሚገባ የሚያሳይ ራእይ ነበር። (ማቴዎስ 17:1-9) ብዙዎች የጠበቁት ነገር ሳይሆን በመቅረቱ ኢየሱስን ጥለው በሄዱበት ወቅት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ራእይ መመልከታቸው እምነታቸውን አጠናክሮላቸዋል። በተመሳሳይ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ይሖዋ ይህ አስደናቂ ራእይም ሆነ ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች በርካታ ትንቢቶች ባገኙት ፍጻሜ ላይ ተጨማሪ ብርሃን በመፈንጠቅ በዛሬው ጊዜ ያሉ አገልጋዮቹን እምነት አጠናክሯል። እስቲ ከእነዚህ እምነት የሚያጠናክሩ መንፈሳዊ ክንውኖች መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።
5. የንጋት ኮከብ ማን ነው? ‘የበራውስ’ መቼና እንዴት ነው?
5 ሐዋርያው ጴጥሮስ የኢየሱስን ተአምራዊ ለውጥ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲያስ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ።” (2 ጴጥሮስ 1:19) ይህ ምሳሌያዊ የንጋት ኮከብ ወይም ‘የሚያበራ የንጋት ኮከብ’ ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ራእይ 22:16) ኮከቡ በ1914 የአምላክ መንግሥት በሰማይ በተወለደበት ጊዜ ‘የበራ’ ሲሆን ይህም አዲስ ዘመን መጥባቱን አብስሯል። (ራእይ 11:15) ኢየሱስ በተአምር በተለወጠበት ወቅት ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታይተው ነበር። እነርሱስ ማንን ያመለክታሉ?
6, 7. ኢየሱስ በተአምር በተለወጠበት ወቅት አብረውት የነበሩት ሙሴና ኤልያስ ማንን ያመለክታሉ? እነርሱን በተመለከተ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ጠቃሚ ማብራሪያ ይዘዋል?
6 ሙሴና ኤልያስ ከክርስቶስ ጋር በንጉሣዊ ክብሩ ስለታዩ እነዚህ ሁለት ታማኝ ምሥክሮች ከኢየሱስ ጋር የሚገዙትን ሰዎች የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው። ከኢየሱስ ጋር የሚገዙ ሰዎች እንዳሉ የሚገልጸው ሐሳብ ነቢዩ ዳንኤል ንጉሣዊ ሥልጣን ስለተሰጠው መሲሕ ያየው ራእይ ካለው ትርጉም ጋር ይስማማል። ዳንኤል “የሰው ልጅ የሚመስል” “ወደ ጥንታዌ ጥንቱ” ማለትም ወደ ይሖዋ አምላክ ቀርቦ ‘ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት’ ሲቀበል ተመልክቷል። ይሁንና ዳንኤል ቀጥሎ ምን እንደተመለከተ ልብ እንበል። “ከሰማይ በታች ያሉ መንግሥታት ልዕልና፣ ሥልጣንና ታላቅነት ለልዑሉ ሕዝብ፣ ለቅዱሳን ይሰጣል” ሲል ጽፏል። (ዳንኤል 7:13, 14, 27) አዎ፣ ኢየሱስ በተአምር ከመለወጡ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት አምላክ የክርስቶስን ንጉሣዊ ልዕልና የሚጋሩ ‘ቅዱሳን’ እንደሚኖሩ አሳውቆ ነበር።
7 ዳንኤል በራእይ ያያቸው ቅዱሳን እነማን ናቸው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለው እነዚህን ግለሰቦች በማስመልከት ነበር:- “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በእርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8:16, 17) ቅዱሳኑ በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ ግልጽ ነው። በራእይ መጽሐፍ ላይ ኢየሱስ “እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ” ብሏል። ቁጥራቸው 144,000 የሆነው ከሞት የተነሱት እነዚህ ‘ድል አድራጊዎች’ ከኢየሱስ ጋር ሆነው መላውን ምድር ይገዛሉ።—ራእይ 3:21፤ 5:9, 10፤ 14:1, 3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:53
8. በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሙሴና የኤልያስ ዓይነት ሥራ ያከናወኑት እንዴት ነው? ምንስ ውጤት አግኝተዋል?
8 ይሁንና ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሴና በኤልያስ የተመሰሉት ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህ ክርስቲያኖች ሰው ሆነው በምድር ላይ ሲኖሩ ሙሴና ኤልያስ ያከናወኑት ዓይነት ሥራ ስለሚሠሩ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ስደት እየደረሰባቸውም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው አገልግለዋል። (ኢሳይያስ 43:10፤ የሐዋርያት ሥራ 8:1-8፤ ራእይ 11:2-12) እንደ ሙሴና እንደ ኤልያስ በአንድ በኩል ሐሰት ሃይማኖትን በድፍረት ያጋልጣሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልበ ቅን ሰዎች አምላክን ብቻ እንዲያመልኩ ያሳስባሉ። (ዘፀአት 32:19, 20፤ ዘዳግም 4:22-24፤ 1 ነገሥት 18:18-40) ሥራቸው ፍሬ አፍርቶ ይሆን? እንዴታ! ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ እንዲሰበሰቡ ድጋፍ የሰጡ ከመሆኑም ሌላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” ለኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃደኝነት እንዲገዙ አስችለዋል።—ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:4
ክርስቶስ ድሉን አጠናቀቀ
9. ራእይ 6:2 ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያለውን ሁኔታ የሚገልጸው እንዴት ነው?
9 በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ የሚጋልብ ሥጋ ለባሽ ሳይሆን ኃያል ንጉሥ ነው። ደግሞም ፈረስ በመጋለብ ላይ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን ፈረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጦርነትን ያመለክታል። (ምሳሌ 21:31) ራእይ 6:2 “እነሆ፤ ነጭ ፈረስ ቆሞ ነበር፤ ተቀምጦበት የነበረውም ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም እንደ ድል አድራጊ ድል ለመንሣት ወጣ” ይላል። ከዚህ በተጨማሪ መዝሙራዊው ዳዊት ኢየሱስን በተመለከተ “እግዚአብሔር ብርቱ በትርህን ከጽዮን ወደ ውጭ ይሰዳል፤ አንተም በጠላቶችህ መካከል ሆነህ ትገዛለህ” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 110:2
10. (ሀ) ኢየሱስ ድል ለመንሳት የሚያደርገውን ግልቢያ በአስደናቂ ሁኔታ የጀመረው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቶስ በመጀመሪያ የተቀዳጀው ድል በመላው ዓለም ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?
10 ኢየሱስ በመጀመሪያ ድል የተቀዳጀው በኃይለኛ ጠላቶቹ ማለትም በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ነበር። ከሰማይ አባርሮ ወደ ምድር ጣላቸው። እነዚህ ክፉ መናፍስት የቀራቸው ጊዜ አጭር መሆኑን ስለሚያውቁ በሰው ዘር ላይ መራራ ቁጣቸውን በመግለጽ ታላቅ ወዮታ አምጥተዋል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ይህ ወዮታ በሌሎች ሦስት ፈረስ ጋላቢዎች ተገልጿል። (ራእይ 6:3-8፤ 12:7-12) ኢየሱስ ‘የመምጣቱንና የዓለምን መጨረሻ ምልክት’ በተመለከተ ከተናገረው ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ የሦስቱ ፈረሰኞች ግልቢያ ጦርነት፣ ረሃብና ቀሳፊ ወረርሽኝ አስከትሏል። (ማቴዎስ 24:3, 7፤ ሉቃስ 21:7-11) እንደ ማንኛውም ምጥ ሁሉ ይህ ‘የምጥ’ ጣርም ክርስቶስ የሰይጣንን ምድራዊ ድርጅት ርዝራዥ በሙሉ ደምስሶ ‘ድሉን’ እስኪያጠናቅቅ ድረስ እየተባባሰ መሄዱን እንደሚቀጥል ግልጽ ነው።a—ማቴዎስ 24:8
11. የክርስቲያን ጉባኤ ታሪክ ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣን መያዙን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣን መያዙን በግልጽ የሚያሳይ ሌላም ማስረጃ አለ። ይህም የክርስቲያን ጉባኤ የመንግሥቱን ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንዲሰብክ የተሰጠውን ተልእኮ መፈጸም እንዲችል እስካሁን ድረስ መቆየቱ ነው። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎንና በጥላቻ ከተሞሉ መንግሥታት አስከፊ ተቃውሞ ቢሰነዘርም የስብከቱ ሥራ ወደፊት ከመግፋትም አልፎ በታሪክ ዘመን ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሷል። (ራእይ 17:5, 6) በእርግጥም ይህ ክርስቶስ ለመንገሡ ታላቅ ምሥክር ነው!—መዝሙር 110:3
12. አብዛኞቹ ሰዎች በዓይን የማይታየውን የክርስቶስን መገኘት ያላስተዋሉት ለምንድን ነው?
12 ይሁንና ክርስቲያን ነን የሚሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ ሰዎች በምድር ላይ እየተከሰቱ ካሉት ታላላቅ ክንውኖች በስተጀርባ በዓይን የማይታዩትን ሐቆች ማስተዋል አለመቻላቸው ያሳዝናል። ይባስ ብሎም የአምላክን መንግሥት በሚያውጁ ሰዎች ላይ ያፌዛሉ። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) ለምን? ሰይጣን አእምሯቸውን ስላሳወረው ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) እንዲያውም ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችን በመንፈሳዊ ጨለማ ካሳወራቸው በርካታ መቶ ዓመታት ያለፉ ሲሆን ድንቅ የሆነው የመንግሥቱ ተስፋ ከአእምሯቸው እንዲጠፋ አድርጓል።
የመንግሥቱ ተስፋ ተረሳ
13. ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በመንፈሳዊ ጨለማ መዋጣቸው ወዴት አመራቸው?
13 ኢየሱስ በስንዴ መካከል እንደተዘራ እንክርዳድ ከሃዲዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሾልከው እንደሚገቡና ብዙዎችን እንደሚያስቱ ተንብዮ ነበር። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29-31፤ ይሁዳ 4) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ እነዚህ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች አረማዊ በዓላትን፣ ልማዶችንና ትምህርቶችን ከመቀበልም አልፈው “የክርስትና” መልክ ሰጧቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የገና በዓል ጣኦት አማልክት ለሆኑት ለሚትረ እና ለሳተርን ከሚቀርብ የአምልኮ ሥርዓት የመጣ ነው። ይሁንና እነዚህ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች እነዚህን አረማዊ በዓላት እንዲቀበሉ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1974) “የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚከበርበት የገና በዓል የተቋቋመው ክርስቶስ በቶሎ ይመለሳል የሚለው ተስፋ እየከሰመ በመሄዱ ነው” ይላል።
14. ኦሪገንና አውጉስቲን ያመነጩት ትምህርት የመንግሥቱን እውነት ያዛባው እንዴት ነው?
14 “መንግሥት” የሚለው ቃል ያለው ትርጉም እንዴት እንደተዛባም ተመልከት። ዘ ኪንግደም ኦቭ ጎድ ኢን ትዌንቲዝ ሴንቸሪ ኢንተርፕሪቴሽን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በክርስትና እምነት ‘መንግሥት’ የሚለው ቃል የነበረው ትርጉም ተቀይሮ በልብ ውስጥ የሚሰፍን የአምላክ አገዛዝ የሚል ትርጉም እንዲይዝ ያደረገው ኦሪገን [በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረ የሃይማኖት ምሑር] ነው።” ይህ የኦሪገን ትምህርት የተመሠረተው በምን ላይ ነበር? በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሳይሆን “ኢየሱስና የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከነበራቸው አስተሳሰብ ፈጽሞ በተለየ መልኩ በፍልስፍናና በዓለም አመለካከት” ላይ ነበር። የሂፖው አውጉስቲን (ከ354-430 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ዴ ኪቪታቲ ዴኢ (የአምላክ ከተማ) በተባለው መጽሐፉ ላይ ቤተ ክርስቲያን ራሷ የአምላክ መንግሥት ነች ሲል ገልጿል። እንዲህ ዓይነቱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አስተሳሰብ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የፖለቲካ ሥልጣን እንዲይዙ የሚያስችል የሃይማኖታዊ ትምህርት ድጋፍ እንዲያገኙ አስቻላቸው። ደግሞም ለብዙ መቶ ዓመታት በአብዛኛው ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የፖለቲካ ሥልጣን ይዘው ቆይተዋል።—ራእይ 17:5, 18
15. ገላትያ 6:7 በአብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ፍጻሜ ያገኘው እንዴት ነው?
15 በዛሬው ጊዜ ግን አብያተ ክርስቲያናት የዘሩትን እያጨዱ ነው። (ገላትያ 6:7) ብዙዎች ሥልጣናቸውንም ሆነ ምዕመናኖቻቸውን እያጡ ያሉ ይመስላል። እንዲህ ዓይነቱ አዝማሚያ አውሮፓ ውስጥ በጉልህ ይታያል። ክርስቲያኒቲ ቱዴይ የተባለው መጽሔት “በአውሮፓ ያሉት ታላላቅ ካቴድራሎች በአሁኑ ጊዜ ከቱሪስቶች በስተቀር ማንም ዝር የማይልባቸው ሙዚየሞች እንጂ የአምልኮ ቤት መሆናቸው አክትሟል” በማለት ዘግቧል። በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ተመሳሳይ አዝማሚያ ይታያል። ይህ ሁኔታ ለሐሰት ሃይማኖት ምን መልእክት ይዟል? የገንዘብም ሆነ የአባላት ድጋፍ በማጣት ከስማ ትጠፋ ይሆን? ይህስ በእውነተኛው አምልኮ ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?
የአምላክን ታላቅ ቀን ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ
16. ታላቂቱ ባቢሎን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተጠላች መምጣቷ ምን ከፍተኛ መልእክት አለው?
16 ጭስና አመድ የሚተፋ ዋልጌ እሳተ ጎሞራ ድንገተኛ ፍንዳታ ሊከሰት እንደሚችል እንደሚያመላክት ሁሉ በበርካታ የዓለም ክፍሎች የሚታየው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሃይማኖት ጥላቻም ሐሰት ሃይማኖት የቀራት ጊዜ በጣም ጥቂት መሆኑን ይጠቁማል። በቅርቡ ይሖዋ የዓለም የፖለቲካ ኃይሎች ግንባር ፈጥረው በመንፈሳዊ ጋለሞታ የሆነችውን ታላቂቱ ባቢሎንን እንዲያጋልጧትና እንዲያጠፏት ያነሳሳቸዋል። (ራእይ 17:15-17፤ 18:21) እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን ክስተትና ከዚያ ተከትለው የሚመጡትን ‘የታላቁን መከራ’ ሌሎች ገጽታዎች መፍራት ይኖርባቸዋል? (ማቴዎስ 24:21) በፍጹም! እንዲያውም አምላክ በክፉዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ የሚያስደስታቸው ነገር ይሆናል። (ራእይ 18:20፤ 19:1, 2) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሩሳሌምንና በከተማዋ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን ሁኔታ ተመልከት።
17. ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የሚችሉት ለምንድን ነው?
17 በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በከበበበት ወቅት በመንፈሳዊ ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች ድንጋጤም ሆነ ፍርሃት አልተሰማቸውም። የአምላክ ቃል ትጉ ተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን “ጥፋቷ መቃረቡን” አውቀው ነበር። (ሉቃስ 21:20) በተጨማሪም ከአደጋው ማምለጥ እንዲችሉ አምላክ መንገዱን እንደሚከፍትላቸው ያውቁ ነበር። መውጫ መንገድ ሲያገኙ ክርስቲያኖች አካባቢውን ጥለው ሸሹ። (ዳንኤል 9:26፤ ማቴዎስ 24:15-19፤ ሉቃስ 21:21) ዛሬም በተመሳሳይ አምላክን የሚያውቁና ልጁን የሚታዘዙ ሰዎች የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ ይችላሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) እንዲያውም ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ‘መዳናቸው ስለ ተቃረበ፣ ቀጥ ብለው ይቆማሉ እንዲሁም [በደስታ] ራሳቸውን ወደ ላይ ቀና ያደርጋሉ።’—ሉቃስ 21:28
18. ጎግ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ አጠቃላይ ጥቃት ሲሰነዝር ውጤቱ ምን ይሆናል?
18 ከታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት በኋላ የማጎጉ ጎግ በመሆን የሚነሳው ሰይጣን በይሖዋ ሰላማዊ ምሥክሮች ላይ ባለ በሌለ ኃይሉ ጥቃት ይሰነዝራል። የጎግ ሠራዊት “ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነው” ስለሚመጡ ድል በእጃቸው ያለ ይመስላቸዋል። ሆኖም ከባድ ዱብ ዕዳ ይጠብቃቸዋል! (ሕዝቅኤል 38:14-16, 18-23) ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ ‘ታማኝና እውነተኛ’ የሚባል ተቀምጦ ነበር . . . ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ወጣ።” ይህ የማይበገር “የነገሥታት ንጉሥ” የይሖዋን ታማኝ አምላኪዎች አድኖ ጠላቶቻቸውን በሙሉ ይደመስሳል። (ራእይ 19:11-21) ኢየሱስ በተአምር ሲለወጥ የታየው ራእይ በዚህ መንገድ በአስደናቂ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኛል!
19. ክርስቶስ የሚቀዳጀው የተሟላ ድል በታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል? በአሁኑ ጊዜስ ምን ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል?
19 ኢየሱስ በዚያ ቀን ‘በሚያምኑበት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ይመጣል።’ (2 ተሰሎንቄ 1:10) በድል አድራጊው የአምላክ ልጅ ፊት በታላቅ አክብሮታዊ ፍርሃት ከሚቆሙት ሰዎች መካከል መሆን ትፈልጋለህ? ከሆነ እምነትህን ማጠናከርህን ቀጥል፤ እንዲሁም ‘የሰው ልጅ ባላሰብክበት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁን።’—ማቴዎስ 24:43, 44
የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ
20. (ሀ) አምላክ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ስለሾመልን የሚሰማንን አመስጋኝነት መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
20 “ታማኝና ልባም ባሪያ” የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው እንዲኖሩና የማስተዋል ስሜታቸውን እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ይሰጣል። (ማቴዎስ 24:45, 46 የ1954 ትርጉም፤ 1 ተሰሎንቄ 5:6) ለእነዚህ ወቅታዊ ማሳሰቢያዎች አመስጋኝ ነህ? በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለማስቀደም ትጠቀምባቸዋለህ? እስቲ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘የአምላክ ልጅ በሰማይ እየገዛ መሆኑን ለማየት የሚያስችል የጠራ መንፈሳዊ እይታ አለኝ? በታላቂቱ ባቢሎንና በተቀረው የሰይጣን ሥርዓት ላይ መለኮታዊ ፍርድ ለመፈጸም ተዘጋጅቶ በመጠባበቅ ላይ እንዳለ ተገንዝቤያለሁ?’
21. አንዳንዶች መንፈሳዊ እይታቸው እንዲዳከም የፈቀዱት ለምን ሊሆን ይችላል? በአስቸኳይ ማድረግ ያለባቸውስ ነገር ምንድን ነው?
21 ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ መንፈሳዊ እይታቸው እንዲዳከም ፈቅደዋል። አንዳንድ የቀድሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዳጋጠማቸው ትዕግሥት ወይም ጽናት አንሷቸው ይሆን? ስለ ኑሮ መጨነቅ፣ ፍቅረ ነዋይ ወይም ስደት ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ይሆን? (ማቴዎስ 13:3-8, 18-23፤ ሉቃስ 21:34-36) አንዳንዶች ታማኝና ልባም ባሪያ በጽሑፍ የሚያወጣቸውን ትምህርቶች መረዳት ከብዷቸው ይሆናል። ከእነዚህ ሁኔታዎች መካከል አንዱ አጋጥሞህ ከሆነ እንደገና ከይሖዋ ጋር ጠንካራና የጠበቀ ዝምድና መመሥረት እንድትችል የአምላክን ቃል በትኩስ ቅንዓት እንድታጠናና ይሖዋን በጸሎት እንድትማጸን እናሳስብሃለን።—2 ጴጥሮስ 3:11-15
22. በራእይ የታየውን የኢየሱስን ተአምራዊ ለውጥና ተዛማጅ የሆኑ ትንቢቶችን መመርመርህ ምን ስሜት አሳድሮብሃል?
22 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተአምራዊ ለውጡን በራእይ እንዲያዩ የተደረጉት ማበረታቻ ባስፈለጋቸው ወቅት ነበር። በዛሬው ጊዜ እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከዚያ የበለጠ ነገር ያገኘን ሲሆን ይህም አስደናቂው ትንቢታዊ ራእይም ሆነ ከዚያ ጋር ዝምድና ያላቸው በርካታ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘታቸው ነው። በእነዚህ አስደናቂ ክንውኖችና ወደፊት በሚኖራቸው ፍጻሜ ላይ ስናሰላስል እኛም እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ “አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና” ብለን ከልብ በመነጨ ስሜት ለመናገር ያብቃን።—ራእይ 22:20
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ‘ምጥ’ የሚለው ቃል አንዲት ነፍሰ ጡር ልትወልድ ስትል ምጡ እየተፋፋመባት እንደሚሄደው ሁሉ በዓለም ላይ ያሉ ችግሮችም በታላቁ መከራ ወቅት መቋጫ እስኪበጅላቸው ድረስ በመጠንም ሆነ በአስከፊነታቸው እየተባባሱ እንደሚሄዱ ያሳያል።
ታስታውሳለህ?
• በ1870ዎቹ ዓመታት፣ ጥቂት ቁጥር የነበራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የክርስቶስን መመለስ በተመለከተ ምን ተገንዝበው ነበር?
• በራእይ የታየው የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
• የኢየሱስ የድል ግልቢያ በዓለምና በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?
• ኢየሱስ የድል ግልቢያውን ሲያጠናቅቅ በሕይወት ከሚተርፉት መካከል ለመገኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትንቢታዊው ራእይ እውን ሆነ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ የድል ግልቢያውን በጀመረበት ወቅት ምን እንደተፈጸመ ታውቃለህ?