“የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?”
“‘ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?’ እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።”—1 ቆሮ. 2:16
1, 2. (ሀ) ብዙ ሰዎች ምን ችግር ያጋጥማቸዋል? (ለ) የእኛን አስተሳሰብና የይሖዋን አስተሳሰብ በተመለከተ ልናስታውሰው የሚገባው እውነታ ምንድን ነው?
አንድ ሰው የሚያስብበትን መንገድ መረዳት አስቸጋሪ ሆኖብህ ያውቃል? ምናልባት ያገባኸው በቅርብ ጊዜ ሊሆን ይችላል፤ የትዳር ጓደኛህ የምታስብበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ መረዳት ከባድ እንደሆነ ይሰማሃል? ለነገሩ ወንዶችና ሴቶች የሚያስቡበት ሌላው ቀርቶ የሚናገሩበት መንገድ እንኳ የተለያየ ነው። እንዲያውም በአንዳንድ ባሕሎች ወንዶችና ሴቶች ቋንቋቸው አንድ ሆኖ እያለ በተለያየ ቀበሌኛ ይጠቀማሉ! ከዚህም በተጨማሪ የባሕልና የቋንቋ ልዩነት ሰዎች በሚያስቡበት መንገድና በባሕርያቸው ረገድ ልዩነት እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል። ይሁንና ሌሎች ሰዎችን ይበልጥ ባወቅሃቸው መጠን የሚያስቡበትን መንገድ ይበልጥ የመረዳት አጋጣሚ ይኖርሃል።
2 በመሆኑም አስተሳሰባችን ከይሖዋ አስተሳሰብ እጅግ የተለየ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ለእስራኤላውያን “ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣ መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለም” ብሏቸው ነበር። ከዚያም ይህን እውነታ በምሳሌ ለማስረዳት “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው” ብሏል።—ኢሳ. 55:8, 9
3. ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ‘ወዳጅነት’ ለመመሥረት የሚረዱን ሁለት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
3 እንዲህ ሲባል ታዲያ የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት መጣር የለብንም ማለት ነው? በፍጹም። የይሖዋን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ መረዳት ፈጽሞ የማንችለው ነገር ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ‘ወዳጅነት’ እንድንመሠርት ያበረታታናል። (ምሳሌ 3:32ን በ1954 ትርጉም እና መዝሙር 25:14ን አንብብ።) ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችልበት አንዱ መንገድ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ስለሚገኙት ሥራዎቹ ማሰብና ለእነዚህ ነገሮች ትኩረት መስጠት ነው። (መዝ. 28:5) ሌላው መንገድ ደግሞ “የማይታየው አምላክ አምሳል” የሆነውን ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማወቅ ነው። (1 ቆሮ. 2:16፤ ቆላ. 1:15) የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባዎች ለማጥናትና ባጠናነው ላይ ለማሰላሰል ጊዜ ከመደብን የይሖዋን ባሕርያትና የሚያስብበትን መንገድ መረዳት እንችላለን።
የተሳሳተ ዝንባሌ እንዳታዳብሩ ተጠንቀቁ
4, 5. (ሀ) የትኛውን የተሳሳተ ዝንባሌ እንዳናዳብር መጠንቀቅ አለብን? አብራራ። (ለ) እስራኤላውያን ምን ዓይነት የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው?
4 በይሖዋ ሥራዎች ላይ ስናሰላስል ይሖዋን በሰዎች መሥፈርት እንዳንለካው መጠንቀቅ አለብን። ይሖዋ እንዲህ ስላለው ዝንባሌ ሲገልጽ በመዝሙር 50:21 ላይ “እንዳንተም የሆንሁ መሰለህ” ብሏል። ከ175 ዓመታት በፊት የኖሩ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ይህን ዝንባሌ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “የሰው ልጆች በራሳቸው መሥፈርት በአምላክ ላይ የመፍረድ ብሎም እነሱ ሊከተሏቸው እንደሚገቡ የሚያስቧቸውን ሕግጋት አምላክም ሊከተል እንደሚገባ የማሰብ ዝንባሌ አላቸው።”
5 የራሳችን መሥፈርትና ፍላጎታችን ለይሖዋ በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር መጠንቀቅ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ቅዱሳን መጻሕፍትን ስናጠና የምናገኛቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ፍጽምና በሚጎድለንና ነገሮችን ሙሉ በሙሉ መረዳት በማንችለው በእኛ አመለካከት በምንገመግምበት ጊዜ ይሖዋ የወሰደው እርምጃ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል። በጥንት ጊዜ የነበሩት እስራኤላውያን እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያዳበሩ ሲሆን ይሖዋ እነሱን የሚይዝበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ይሖዋ ምን እንዳላቸው እንመልከት፦ “እናንተ ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስማ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን?”—ሕዝ. 18:25
6. ኢዮብ ምን ትምህርት አግኝቷል? እኛስ ኢዮብ ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
6 ከራሳችን መሥፈርት አንጻር በይሖዋ ላይ የመፍረድን አዝማሚያ እንዳናዳብር የሚረዳን ቁልፍ፣ ነገሮችን በተሟላ መንገድ መረዳት እንደማንችል ብሎም አንዳንድ ጊዜ አመለካከታችን ሊዛባ እንደሚችል መገንዘብ ነው። ኢዮብ ይህን መማር አስፈልጎት ነበር። ኢዮብ መከራ በደረሰበት ወቅት በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠ ከመሆኑም ሌላ ስለ ራሱ ብቻ ማሰብ ጀምሮ ነበር። ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አልቻለም። ይሁንና ኢዮብ ሰፋ ያለ አመለካከት እንዲይዝ ይሖዋ በፍቅር ረድቶታል። ይሖዋ፣ ኢዮብ ሊመልሳቸው ያልቻላቸውን ከ70 የሚበልጡ ጥያቄዎች በማንሳት ኢዮብ መረዳት የማይችላቸው ነገሮች እንዳሉ እንዲገነዘብ ረድቶታል። ኢዮብም ትሑት በመሆን አመለካከቱን አስተካክሏል።—ኢዮብ 42:1-6ን አንብብ።
‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ መያዝ
7. ኢየሱስ ያደረጋቸውን ነገሮች መመርመራችን የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ያስችለናል የምንለው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም ኢየሱስ ያደረጋቸውን ነገሮች መመርመራችን የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ያስችለናል። (ሮም 15:5፤ ፊልጵ. 2:5) እስቲ ሁለት የወንጌል ዘገባዎችን እንመልከት።
8, 9. በዮሐንስ 6:1-5 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ኢየሱስ ለፊልጶስ ጥያቄ እንዲያቀርብለት ያነሳሳው ሁኔታ ምንድን ነው? ጥያቄ የጠየቀው ለምንድን ነው?
8 ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። ወቅቱ በ32 ዓ.ም. ከተከበረው የፋሲካ በዓል ትንሽ ቀደም ብሎ ነው። የኢየሱስ ሐዋርያት በመላው ገሊላ ግሩም የስብከት ሥራ አከናውነው መመለሳቸው ነበር። ደክሟቸው ስለነበር ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ በስተሰሜን ምሥራቅ ወደሚገኝ ገለል ያለ ስፍራ ወሰዳቸው። ይሁንና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተከተሏቸው። ኢየሱስ እነዚህን በርካታ ሰዎች ከፈወሰና ብዙ ነገር ካስተማራቸው በኋላ መፍትሔ የሚያሻው አንድ ችግር ተነሳ። ይህ ሁሉ ሕዝብ እንዲህ ባለው ገለልተኛ ስፍራ ምግብ ማግኘት እንዴት ይችላል? ኢየሱስ ይህን ችግር በመገንዘብ የዚያ አካባቢ ሰው የሆነውን ፊልጶስን “እነዚህ ሰዎች የሚበሉት ዳቦ ከየት ብንገዛ ይሻላል?” በማለት ጠየቀው።—ዮሐ. 6:1-5
9 ኢየሱስ፣ ፊልጶስን እንዲህ ብሎ የጠየቀው ለምን ነበር? ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገብቶት ይሆን? በጭራሽ። ታዲያ ይህን ያለው ምን አስቦ ነበር? በወቅቱ በቦታው የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ፣ “[ኢየሱስ] ይህን ያለው ሊፈትነው ብሎ እንጂ እሱ ራሱ ምን ሊያደርግ እንዳሰበ ያውቅ ነበር” በማለት ጽፏል። (ዮሐ. 6:6) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በመንፈሳዊ ምን ያህል እድገት እንዳደረጉ ለመፈተን ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ይህን ጥያቄ በመጠየቅ ስለ ጉዳዩ ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት ለመግለጽ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። እነሱ ግን ይህንን አጋጣሚ አልተጠቀሙበትም፤ እንዲሁም የእሱን አመለካከት ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማይችሉ አሳይተዋል። (ዮሐንስ 6:7-9ን አንብብ።) ሆኖም ኢየሱስ ጨርሶ ያላሰቡትን ነገር ሊያደርግ እንደሚችል አሳያቸው። በሺዎች የሚቆጠሩትን ሰዎች በተአምር መገበ።—ዮሐ. 6:10-13
10-12. (ሀ) ኢየሱስ ግሪካዊቷ ሴት የጠየቀችውን ነገር ወዲያውኑ ያልፈጸመላት ለምን ሊሆን ይችላል? አብራራ። (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?
10 ይህ ዘገባ ከአንድ ሌላ ክንውን ጋር በተያያዘ የኢየሱስን አስተሳሰብ እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል። ኢየሱስ ሕዝቡን ከመገበ ብዙም ሳይቆይ ከሐዋርያቱ ጋር በስተሰሜን የእስራኤልን ድንበር ተሻግረው ወደ ጢሮስና ሲዶና ክልል ሄዱ። በዚያ እያሉ አንዲት ግሪካዊት ሴት፣ ልጇን እንዲፈውስላት ኢየሱስን ለመነችው። መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ ለሴትየዋ ምንም ምላሽ አልሰጣትም። ሆኖም ሴትየዋ ደጋግማ ስትወተውተው ኢየሱስ “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ ስላልሆነ መጀመሪያ ልጆቹ ይጥገቡ” አላት።—ማር. 7:24-27
11 መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ ሴትየዋን ለመርዳት ፈቃደኛ ያልሆነው ለምን ነበር? እምነቷን እንድታሳይ አጋጣሚ በመስጠት እንደ ፊልጶስ ሊፈትናት አስቦ ይሆን? ኢየሱስ ይህን ሲላት ምን ዓይነት የድምፅ ቃና እንደነበረው በጽሑፍ ከሰፈረው ዘገባ ማወቅ ባይቻልም ንግግሩ ተስፋ አላስቆረጣትም። “ቡችሎች” የሚለውን ቃል መጠቀሙ ንጽጽሩን ያለዝበዋል። ኢየሱስ በዚህ ወቅት የወሰደውን እርምጃ አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ከሚያደርጉት ነገር ጋር ማመሳሰል ይቻላል። አንድ ወላጅ ልጁ የጠየቀውን ነገር ለመስጠት ቢያስብም ይህን የሚጠቁም ምንም ምልክት ላያሳይ ይችላል፤ ይህን የሚያደርገው ልጁ የጠየቀውን ነገር ምን ያህል እንደሚፈልገው ለመፈተን ሲል ይሆናል። የኢየሱስ ምክንያት ምንም ይሁን ምን ሴትየዋ እምነት እንዳላት ባሳየች ጊዜ የፈለገችውን ነገር በደስታ ፈጽሞላታል።—ማርቆስ 7:28-30ን አንብብ።
12 እነዚህ ሁለት የወንጌል ዘገባዎች ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ለመረዳት ያስችሉናል። እስቲ አሁን ደግሞ እነዚህ ዘገባዎች የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ለማወቅ እንዴት ሊረዱን እንደሚችሉ እንመልከት።
ይሖዋ ሙሴን የያዘበት መንገድ
13. ኢየሱስ የሚያስብበትን መንገድ ማወቃችን የሚረዳን እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ የሚያስብበትን መንገድ ማወቃችን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ለመረዳት ሊከብዱን የሚችሉ ታሪኮችን እንድንረዳ ያስችሉናል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ ሠርተው ካመለኩ በኋላ ይሖዋ ለሙሴ ምን እንዳለው እንመልከት። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ አንገተ ደንዳናዎችም ናቸው፤ አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”—ዘፀ. 32:9, 10
14. ሙሴ ይሖዋ ለተናገረው ሐሳብ ምን ምላሽ ሰጠ?
14 ዘገባው ቀጥሎ እንዲህ ይላል፦ “ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነዳል? ግብፃውያን፣ “በተራራዎቹ ላይ ሊገድላቸው ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው” ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ። ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለእስራኤል፣ “ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች” በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።’ ከዚያም እግዚአብሔር ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።”—ዘፀ. 32:11-14a
15, 16. (ሀ) ይሖዋ የተናገረው ነገር ሙሴ ምን እንዲያደርግ አጋጣሚ ሰጥቶታል? (ለ) ይሖዋስ ምን አደረገ?
15 ይሖዋ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ሙሴ ሐሳብ ማቅረቡ የግድ አስፈላጊ ነበር? በጭራሽ! ይሖዋ ምን ሊያደርግ እንደፈለገ ቢናገርም ይህ የመጨረሻ ውሳኔው አልነበረም። ኢየሱስ ፊልጶስንና ግሪካዊቷን ሴት እንደፈተናቸው ሁሉ ይሖዋም ሙሴን እየፈተነው ነበር ማለት ይቻላል። ሙሴ አመለካከቱን እንዲገልጽ አጋጣሚ ተሰጥቶት ነበር።b ይሖዋ፣ ሙሴን በእሱና በእስራኤል ሕዝብ መካከል አስታራቂ እንዲሆን የሾመው ሲሆን ሙሴ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት የሚጫወተውን ሚናም አክብሮለታል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለማወቅ የፈለገው ነገር ነበር፦ ሙሴ በነገሩ መበሳጨቱ በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተጽዕኖ ያሳድር ይሆን? ሙሴ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን ትቶ የእሱን ዘሮች ታላቅ ሕዝብ እንዲያደርጋቸው ያበረታታው ይሆን?
16 ሙሴ የሰጠው ምላሽ ይሖዋ ፍትሐዊ እርምጃ እንደሚወስድ ያለውን እምነት ያሳያል። በተጨማሪም የሰጠው ምላሽ የራሱን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ ለይሖዋ ስም እንደሚቆረቆር የሚያሳይ ነበር። የይሖዋ ስም እንዲነቀፍ አልፈለገም። ሙሴ ይህን ማድረጉ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ “የይሖዋን አስተሳሰብ” እንዳወቀ የሚያሳይ ነው። (1 ቆሮ. 2:16) ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው ዘገባ መገንዘብ እንደሚቻለው ይሖዋ የተወሰነ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ ስላላደረገ “በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።” ይሖዋ በመላው ብሔር ላይ ሊወስድ የፈለገውን እርምጃ አልወሰደም።
ይሖዋ አብርሃምን የያዘበት መንገድ
17. አብርሃም ያሳሰበውን ነገር ሲጠይቀው ይሖዋ ታላቅ ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው?
17 አብርሃም ከሰዶም ጋር በተያያዘ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ እምነታቸውን ለማሳየትና በእሱ እንደሚተማመኑ ለመግለጽ አጋጣሚ እንደሚሰጥ የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው። ከዚህ ዘገባ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ አብርሃም በተደጋጋሚ ያቀረበለትን ጥያቄ በማዳመጥ ታላቅ ትዕግሥት አሳይቷል። በውይይታቸው መሃል አብርሃም የሚከተለውን ጥያቄ አንስቶ ነበር፦ “እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር እንዴት ትገድለዋለህ? ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?”—ዘፍ. 18:22-33
18. ይሖዋ አብርሃምን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?
18 ከዚህ ዘገባ ስለ ይሖዋ አስተሳሰብ ምን እንማራለን? ይሖዋ ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርግ አብርሃም የሚሰጠው አስተያየት ያስፈልገው ነበር? በፍጹም! በእርግጥም ይሖዋ፣ ላደረገው ውሳኔ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ገና ከመጀመሪያው መግለጽ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አብርሃም እነዚህን ጥያቄዎች እንዲያቀርብ ይሖዋ ስለፈቀደለት አብርሃም የይሖዋን ውሳኔ ለመቀበልና የእሱን አስተሳሰብ ለመረዳት አጋጣሚ አግኝቷል። ከዚህም በተጨማሪ አብርሃም የይሖዋ ርኅራኄና ፍትሕ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ለመረዳት ችሏል። በእርግጥም ይሖዋ አብርሃምን እንደ ወዳጁ ተመልክቶታል።—ኢሳ. 41:8፤ ያዕ. 2:23
ምን ትምህርት እናገኛለን?
19. የኢዮብን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
19 “የይሖዋን አስተሳሰብ” በተመለከተ ምን ትምህርት አግኝተናል? በዚህ ረገድ ትክክለኛውን ግንዛቤ ለማግኘት የአምላክን ቃል መጠቀም ይኖርብናል። ነገሮችን ሙሉ በሙሉ መረዳት ስለማንችል በእኛ አመለካከት፣ መሥፈርትና አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዘን በይሖዋ ላይ ፈጽሞ መፍረድ አይኖርብንም። ኢዮብ “መልስ እሰጠው ዘንድ፣ እሟገተውም ዘንድ፣ [አምላክ] እንደ እኔ ሰው አይደለም” ብሏል። (ኢዮብ 9:32) ልክ እንደ ኢዮብ እኛም የይሖዋን አስተሳሰብ ስንረዳ እንደሚከተለው ለማለት እንነሳሳለን፦ “እነዚህ የሥራው ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እርሱ የሰማነው ምንኛ አነስተኛ ነው! የኀይሉንስ ነጐድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል?”—ኢዮብ 26:14
20. ቅዱሳን መጻሕፍትን ስናነብ ለመረዳት የሚከብደን ሐሳብ ብናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
20 ቅዱሳን መጻሕፍትን ስናነብ በተለይ ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ለመረዳት የሚከብደን ሐሳብ ብናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በጉዳዩ ላይ ምርምር አድርገንም እንኳ ግልጽ መልስ ማግኘት ባንችል ይህ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት የሚፈትን አጋጣሚ እንደሆነ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ በይሖዋ ባሕርያት ላይ ያለንን እምነት ለመግለጽ አጋጣሚ እንደሚሰጡን አስታውስ። ይሖዋ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማንችል በትሕትና አምነን እንቀበል። (መክ. 11:5) እንዲህ ማድረጋችን ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ የተናገረውን ሐሳብ እንድናስተጋባ ያነሳሳናል፦ “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው! ምክንያቱም ‘የይሖዋን ሐሳብ ማወቅ የቻለ ማን ነው? አማካሪውስ የሆነ ማን ነው?’ ወይስ ‘መልሶ ይከፍለው ዘንድ ለእሱ ያበደረ ማን ነው?’ ምክንያቱም ሁሉም ነገር የተገኘው ከእሱ፣ በእሱና ለእሱ ነው። ለዘላለም ክብር ለእሱ ይሁን። አሜን።”—ሮም 11:33-36
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተመሳሳይ ዘገባ በዘኍልቍ 14:11-20 ላይ ይገኛል።
b አንዳንድ ምሑራን እንደሚሉት ከሆነ በዘፀአት 32:10 ላይ የሚገኘው “ተወኝ” የሚለው የዕብራይስጥ አገላለጽ ሙሴ ይሖዋንና እስራኤልን እንዲያስታርቅ ወይም ‘በመካከላቸው እንዲገባ’ የቀረበ ግብዣ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። (መዝ. 106:23፤ ሕዝ. 22:30 የታረመው የ1980 ትርጉም) ይህ አስተያየት ትክክል ሆነም አልሆነ፣ ሙሴ አመለካከቱን ለይሖዋ ለመግለጽ ነፃነት እንደተሰማው መመልከት ይቻላል።
ታስታውሳለህ?
• በራሳችን መሥፈርት መሠረት በይሖዋ ላይ የመፍረድ ዝንባሌ እንዳናዳብር ምን ሊረዳን ይችላል?
• ኢየሱስ አንዳንድ ነገሮችን ያደረገበትን ምክንያት መረዳታችን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ‘ወዳጅነት’ ለመመሥረት የሚረዳን እንዴት ነው?
• ይሖዋ ከሙሴና ከአብርሃም ጋር ካደረገው ውይይት ምን ትምህርት አግኝተሃል?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ሙሴንና አብርሃምን ከያዘበት መንገድ የእሱን አስተሳሰብ በተመለከተ ምን ትምህርት እናገኛለን?