መለኮታዊ ትምህርት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ቅመሱ
“እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ አምላክህ ይሖዋ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17 አዓት
1. መለኮታዊውን ትምህርት በሕይወታችን ውስጥ ሥራ ላይ ብናውል እንዴት እንጠቀማለን?
ይሖዋ አምላክ ከማንም የበለጠ ዕውቀት አለው። እርሱን በአስተሳሰብም ሆነ በአነጋገር ወይም በድርጊት የሚበልጠው የለም። ፈጣሪያችን እንደ መሆኑ መጠን ስለሚያስፈልጉን ነገር ያውቃል፣ አትረፍርፎም ይሰጠናል። እንዴት እንደሚያስተምረንም አሳምሮ ያውቃል። መለኮታዊውን ትምህርት ሥራ ላይ ካዋልን ደግሞ ራሳችንን እንጠቅማለን፤ እውነተኛ ደስታም እናገኛለን።
2, 3. (ሀ) በጥንት ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ትእዛዛዙትን ጠብቀው ቢሆን ኖሮ ራሳቸውን እንዴት ሊጠቅሙ ይችሉ ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ መለኮታዊውን ትምህርት ሥራ ላይ ብናውል ውጤቱ ምን ይሆናል?
2 መለኮታዊ ትምህርት አምላክ አገልጋዮቹ ከጉዳት እንዲጠበቁና ከሕጎቹና ከመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር ተስማምተው በመኖር እንዲደሰቱ ያለውን ጥልቅ ምኞት በግልጽ ያሳያል። በጥንት ዘመን የነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች አምላክ የነገራቸውን ቢሰሙ ኖሮ ይህ ነው የማይባል በረከት ማግኘት ይችሉ ነበር። ምክንያቱም እርሱ “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር በሆነ ነበር” ብሏቸዋል።—ኢሳይያስ 48:17, 18
3 የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች ትእዛዞቹንና ትምህርቶቹን ከልብ ቢከተሉ ኖሮ ራሳቸውን ሊጠቅሙ ይችሉ ነበር። በባቢሎናውያን እጅ ወድቀው ሥቃይ ከማየት ይልቅ እንደ ወንዝ የሞላ፣ ጥልቀት ያለውና የማያቋርጥ ሰላምና ብልጽግና ማግኘት ይችሉ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የጽድቅ ሥራቸው እንደማይቆጠረው የባሕር ሞገድ ይበዛላቸው ነበር። እኛም በተመሳሳይ መለኮታዊውን ትምህርት በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ብናውል ከሚያስገኛቸው ብዙ ጥቅሞች ልንካፈል እንችላለን። ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
4. መለኮታዊው ትምህርት የብዙ ሰዎችን ሕይወት የነካው እንዴት ነው?
4 መለኮታዊ ትምህርት በሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ለውጥ በማምጣት ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። የይሖዋን መመሪያ በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች እንደ መዳራት፣ ጣኦት አምልኮ፣ ምዋርት፣ ክርክርና ቅንዓት የመሰሉትን “የሥጋ ሥራዎች” ከመፈጸም ይልቅ የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት ያሳያሉ። (ገላትያ 5:19–23) በተጨማሪም በኤፌሶን 4:17–24 ላይ የሚገኙትን የጳውሎስ ቃላት ይከተላሉ። ጳውሎስ በዚህ ቦታ ላይ የእምነት ባልደረቦቹን እንደ አሕዛብ በከንቱ አሳብና፣ በአእምሮ ጨለማ እንዳይመላለሱ እንዲሁም ከአምላክ ሕይወት እንዳይርቁ መክሯል። አሕዛብ ልባቸው ደንዝዞ የሥነ ምግባር ስሜታቸው በሙሉ ጠፍቶባቸዋል። ክርስቶስን የሚመስሉ ሰዎች ግን ከቀድሞ አኗኗራቸው ጋር የሚስማማውን አሮጌ ሰው አውልቀው ጥለው አእምሮአቸውን በሚያንቀሳቅሰው ኃይል ይታደሳሉ። በእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን አዲስ ሰው ይለብሳሉ።
5. መለኮታዊው ትምህርት ሰዎች በሚመላለሱበት መንገድ ላይ ለውጥ የሚስከትለው እንዴት ነው?
5 መለኮታዊውን ትምህርት ሥራ ላይ ማዋል ከሚያስገኛቸው መልካም ውጤቶች አንዱ ሰዎች እንዴት አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሳየቱ ነው። ልክ ኖህ እንዳደረገው አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር ብናደርግ ታላቁ መምህራችን የሚያሳየንን የአኗኗር መንገድ ተከትለናል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 6:9፤ ኢሳይያስ 30:20, 21) አሕዛብ ግን ጳውሎስ እንደተናገረው “በአእምሮአቸው ከንቱነት” ይመላለሳሉ። ስለዚህ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች አእምሮ የሚመነጩት አንዳንድ ጽሑፎች ምንኛ ከንቱ ናቸው! አንድ ታዛቢ በፖምፔ በሚገኝ አንድ ግድግዳ ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን ካስተዋለ በኋላ “አንተ ግድግዳ፣ በላይህ ላይ የተጻፉት ከንቱ ሐሳቦች ተጭነውህ አለመውደቅህ በጣም የሚያስደንቅ ነው” ሲል ጽፏል። ‘ከይሖዋ በሚገኘው ትምህርት’ እና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ ግን ምንም ዓይነት ከንቱነት አይገኝም። (ሥራ 13:12) በዚህ ሥራ አማካኝነት እውነት ወዳድ የሆኑ ሰዎች ጤናማ ወደ ሆነ አስተሳሰብ ሊመለሱ ችለዋል። ለአምላክ ዓላማዎች ደንቆሮ ሆነው በኃጢአት መመላለሳቸውን እንዴት እንደሚያቆሙ ተምረዋል። ከአእምሮ ጨለማ ወጥተዋል። ትርፍ የማያስገኙ ግቦችን በሚያሳድድ የደነዘዘ ልብ መመራታቸውን አቁመዋል።
6. ለይሖዋ ትምህርት በመታዘዛችንና በደስተኝነታችን መካከል ምን ዓይነት ዝምድና አለ?
6 በተጨማሪም መለኮታዊው ትምህርት ለአምላክ ያለንን ፍቅርና እርሱን ለመታዘዝ ያለንን ፍላጎት ስለሚጨምርልን ጠቃሚያችን ነው። እንደዚህ ያለው እውቀት ወደ አምላክ ያቀርበናል፣ ለእርሱ ያለንንም ፍቅር ይጨምርልናል እንዲሁም እርሱን ለመታዘዝ ያለንን ፍላጐት ከፍ ያደርግልናል። 1 ዮሐንስ 5:3 “ትዕዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፣ ትዕዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” ይላል። በተጨማሪም የኢየሱስ ትምህርቶች ከአምላክ የተገኙ እንደሆኑ ስለምናውቅ ከኢየሱስ ትዕዛዛት ጋር ተስማምተን እንኖራለን። (ዮሐንስ 7:16–18) እንደዚህ ያለው ታዛዥነት ከመንፈሳዊ ጉዳት ይጠብቀናል እንዲሁም የደስታ ምንጭ ይሆንልናል።
እውነተኛ የሕይወት ዓላማ
7, 8. (ሀ) መዝሙር 90:12ን ልንረዳው የሚገባን እንዴት ነው? (ለ) ጥበብ የተሞላበት ልብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
7 ከይሖዋ የሚገኘው ትምህርት ሕይወታችንን ዓላማ ባለው መንገድ እንዴት መምራት እንደምንችል በማሳየት ይጠቅመናል። እንዲያውም መለኮታዊው ትምህርት የምንኖርባቸውን ቀኖች ልዩ በሆነ መንገድ እንዴት ልንቆጥር እንደምንችል ያስተምረናል። እርግጥ ነው የ70 ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው በጠቅላላ 25,550 ቀኖች ሊኖር ይችላል። 50 ዓመት ዕድሜ ላይ ለደረሰ ሰው ደግሞ 18,250 ቀናት ስለኖረ የሚቀሩት 7,300 ቀናት በእርግጥም በጣም ጥቂት ናቸው። በተለይ በዚህ ዕድሜው ነቢዩ ሙሴ በመዝሙር 90 ቁጥር 12 ላይ “ጥበበኞች ለመሆን እንድንችል ዕድሜአችን ምን ያህል አጭር እንደሆነ አስተምረን” ሲል የጸለየበትን ምክንያት በይበልጥ ሊረዳ ይችላል። (የ1980 ትርጉም።) ሙሴ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
8 ሙሴ ለእያንዳንዱ እስራኤላዊ የሚኖርበትን ዕድሜ ትክክለኛ መጠን እንዲያሳውቅ አምላክን መጠየቁ አልነበረም። መዝሙር 90 ቁጥር 9 እና 10 እንደሚያመለክተው ይህ ዕብራዊ ነቢይ የአንድ ሰው ዕድሜ ከ70 ወይም ከ80 ዓመት እንደማያልፍ ተገንዝቦ ነበር። በእርግጥም በጣም አጭር ዘመን ነው። ስለዚህ የመዝሙር 90 ቁጥር 12 ቃላት ይሖዋ ለእርሱም ሆነ ለሕዝቦቹ ዕድሜአቸውን እንደ ውድ ነገር ለመቁጠርና አምላክ በሚፈቅደው መንገድ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ጥበብ እንዲያሳያቸው ወይም እንዲያስተምራቸው መለመኑ እንደሆነ ያመለክታሉ። እኛስ፣ እያንዳንዱ ቀን ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንገነዘባለንን? እያንዳንዱን ቀን ለታላቁ መምህራችን ለይሖዋ አምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ ለመጠቀም በመፈለግ ጥበበኞች መሆናችንን እናሳያለንን? መለኮታዊው ትምህርት እንዲህ እንድናደርግ ይረዳናል።
9. ዘመኖቻችንን ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ መቁጠርን ብንማር ምን ነገር ለማግኘት ተስፋ ልናደርግ እንችላለን?
9 ዕድሜያችን ለይሖዋ ክብር ማስገኘቱን እንዴት እንደምንቆጥር ከተማርን መለኮታዊው ትምህርት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ እውቀት በመስጠት ድል ስለሚያደርግ ዕድሜያችንን ለዘላለም እየቆጠርን ለመኖር እንችላለን። ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም) እርግጥ ነው፣ በዓለም ውስጥ ያለውን ዕውቀት በሙሉ ለማግኘት ብንችል እንኳን የዘላለም ሕይወት አያስገኝልንም። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት ሁሉ የሚበልጡትን ይሖዋንና ኢየሱስ ክርስቶስን በትክክል አውቀን ያወቅነውን በሥራ ላይ ብናውልና ብናምን ግን የዘላለም ሕይወት እናገኛለን።
10. አንድ ኢንሳይክሎፔዲያ ስለ ትምህርት ምን አለ? ይህስ መለኮታዊ ትምህርት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ጋር እንዴት ሊወዳደር ይችላል?
10 ምንም ያህል ዕድሜ የኖርን ብንሆን ልንረሳው የማይገባ አንድ ነገር አለ። እርሱም መለኮታዊውን ትምህርት የሚቀበሉ ሁሉ እውነተኛ የሆነ የሕይወት ዓላማ እንዲኖራቸው ማስቻሉ ነው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “ትምህርት ሰዎች ጠቃሚ የሆኑ የማኅበረሰብ አባላት እንዲሆኑ መርዳት መቻል ይኖርበታል። በተጨማሪም ባሕላዊ ቅርሶቻቸውን እንዲያውቁና እንዲያደንቁ እንዲሁም ይበልጥ አርኪ የሆነ ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻል ይኖርበታል።” መለኮታዊው ትምህርት እርካታ የሚገኝበት ሕይወት እንድንኖር ያስችለናል። የአምላክ ሕዝቦች እንደ መሆናችን መጠን ላገኘነው መንፈሳዊ ቅርስ ያለንን አድናቆት ያዳብርልናል። በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን ችግር በመፍታት ረገድ በጣም ከፍተኛ ሚና እንድንጫወት ስለሚያስችለን ጠቃሚ የሆንን የማኅበረሰብ አባሎች እንድንሆን አስችሎናል። እንደዚህ ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
ዓለም አቀፍ የትምህርት ፕሮግራም
11. ቶማስ ጀፈርሰን ስለ ትክክለኛው ትምህርት አስፈላጊነት ያጎሉት እንዴት ነበር?
11 ከሌላው የትምህርት ፕሮግራም ይበልጥ መለኮታዊ ትምህርት ሰዎች ለትምህርት ያላቸውን ጥማት ያረካላቸዋል። ሕዝቦችን ማስተማር ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑ የዩናይትድ ስቴትስ ሦስተኛ ፕሬዚደንት በሆኑት በቶማስ ጀፈርሰን ተገልጿል። ጀፈርሰን ወዳጃቸውና የነፃነቱን አዋጅ አብረዋቸው ከፈረሙት ሰዎች አንዱ ለሆኑት ለጆርጅ ዊዝ ነሐሴ 13, 1786 በፃፉት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በሕገ መንግሥታችን ውስጥ ከሚገኙት ሕጎች ሁሉ በአስፈላጊነቱ ብልጫ ያለው ዕውቀትን ለሕዝብ ስለማሰራጨት የወጣው ሕግ ይመስለኛል። ነፃነትንና ደስታን ጠብቆ ለማኖር ከዚህ የተሻለ መሠረት ሊኖር አይችልም። . . . የተከበርክ ወዳጄ ሆይ፣ በድንቁርና ላይ ጠንካራ ዘመቻ እንዲደረግ አጥብቀህ ስበክ። ተራውን ሕዝብ ለማስተማር የሚያስችሉ ሕጎች እንዲወጡና የወጡትም እንዲሻሻሉ አድርግ። የአገራችን ዜጎች . . . ለትምህርት የሚከፍሉት ግብር ሕዝቦቻችን በድንቁርና እንዲኖሩ ብናደርግ በመካከላችን ለሚነሡት ነገሥታት፣ ካህናትና ባላባቶች የሚከፈለውን ገንዘብ አንድ ሺኛ እንኳን እንደማይሆን ይወቁ።”
12. መለኮታዊው ትምህርት ከማንኛውም ዓይነት ትምህርት የበለጠ የተሳካና ጠቃሚ ውጤት የሚያስገኝ ዓለም አቀፍ የትምህርት ፕሮግራም ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
12 መለኮታዊው ትምህርት የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በድንቁርና እንዲኖሩ ከማድረግ ይልቅ ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎችን የሚጠቅም ምድር አቀፍ የትምህርት ፕሮግራም በማካሄድ ድል በማድረግ ላይ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የትምህርት ተሐድሶ ኮሚቴ በአስቸኳይ ምድር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የተገነዘበው ከ50 ዓመታት በፊት ሁለተኛው ዓለም ጦርነት በተፋፋመበት ጊዜ ነበር። አሁንም ቢሆን የዚህ ትምህርት አስፈላጊነት አልቀነሰም። ይሁን እንጂ የተሳካ ውጤት ያስገኘ ምድር አቀፍ የትምህርት ፕሮግራም መለኮታዊ ትምህርት ብቻ ነው። ይህ ትምህርት ሰዎችን ከፍርሐት ያወጣል፣ ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ ብርታት ይሰጣል፣ ከዓለም ኩራትና መሠረተ ቢስ ጥላቻ ያድናል፣ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ዕውቀት ይሰጣል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ሰዎችን የማስተማር ፕሮግራም በየትም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ታላቁን መምህር ይሖዋ አምላክን እንዲያገለግሉት በማስተማር ላይ ነው።
13. ኢሳይያስ 2:2–4 በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
13 በጣም ብዙ ሰዎች እውነትን እየተማሩ የይሖዋ አምላኪዎች በመሆን ላይ ስለሚገኙ የመለኮታዊው ትምህርት ጠቃሚነት በግልጽ ይታያል። እነዚህ ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ፍላጎታቸው ማሰብ ጀምረዋል። የይሖዋ ቀን ቅርብ መሆኑንም አውቀዋል። (ማቴዎስ 5:3፤ 1 ተሰሎንቄ 5:1–6) በአሁኑ “የፍጻሜ ዘመን” እነዚህ ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ወደ ይሖዋ ቤት ተራራ ማለትም ወደ ንጹሕ አምልኮቱ በመጉረፍ ላይ ናቸው። ይህ አምልኮት በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም በላይ የአምላክ ፈቃድ ተጻራሪ ከሆኑ አምልኮቶች ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ብሏል። (ኢሳይያስ 2:2–4) ቁጥሩ እየጨመረ ከሄደው ከዚህ የይሖዋ አምላኪና የመለኮታዊ ትምህርት ተጠቃሚ የሆነ ሠራዊት መካከል በመገኘታችሁ በጣም አልተደሰታችሁምን? በድል አድራጊነት “እናንት ሕዝቦች ይሖዋን አመስግኑ” ከሚሉ ሕዝቦች ጋር ለመሆን መቻል በጣም ግሩም ነገር ነው።—መዝሙር 150:6 አዓት
በመንፈሳችን ላይ የሚያስከትለው ጠቃሚ ውጤት
14. በ1 ቆሮንቶስ 14:20 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስ ምክር መከተል ምን ጥቅም አለው?
14 መለኮታዊ ትምህርት ከሚያስገኛቸው ብዙ ጥቅሞች መካከል አንዱ በአስተሳሰባችንና በመንፈሳችን ላይ የሚያስከትለው ጥሩ ውጤት ነው። ጽድቅን፣ ንጹሕ፣ በጎ የሆኑ እና የሚያስመሰግኑ ነገሮችን እንድናስብ ያንቀሳቅሰናል። (ፊልጵስዩስ 4:8) የይሖዋ ትምህርት “በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር እንድንከተል ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 14:20) ይህንን ማሳሰቢያ በሥራ ላይ ካዋልን ስለ ክፋት እውቀት ለማግኘት አንፈልግም። በተጨማሪም ጳውሎስ “መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 4:31) እንደዚህ ያለውን ምክር መከተል ከብልግና እና ከሌሎች ከባድ ኃጢአቶች እንድንርቅ ይረዳናል። ይህም ለአካላችንም ሆነ ለአእምሮአችን ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ አምላክን በማስደሰት ላይ መሆናችንን ከማወቅ የሚገኘውን ደስታ ያመጣልናል።
15. በአስተሳሰባችን በጎዎች ሆነን እንድንኖር ምን ሊረዳን ይችላል?
15 በአስተሳሰባችን በጎዎች ሆነን እንድንኖር ከሚረዱን ነገሮች አንዱ ‘መልካሙን ዓመል ከሚያበላሽ መጥፎ ባልንጀርነት’ መራቅ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን ከአመንዝሮች፣ ከሴሰኞች እና ከሌሎች መጥፎ ድርጊት ፈጻሚዎች ጋር ጓደኝነት አንመሠርትም። ስለዚህ እንደነዚህ ስላሉ ሰዎች የተፃፉ መጻሕፍትን በማንበብ ወይም እነርሱን በቴሌቪዥንም ሆነ በፊልሞች በማየት ወዳጆቻቸው መሆን አይገባንም። ልብ ሸፋጭ ስለሆነ መጥፎ ነገር የማድረግ ምኞት በቀላሉ ሊያድርበትና ሊፈተን ይችላል። (ኤርምያስ 17:9) እንግዲያው መለኮታዊውን ትምህርት አጥብቀን በመከተል እንደነዚህ የመሳሰሉትን ፈተናዎች እናርቅ። ይህ ትምህርት ‘ይሖዋን ለሚወዱ ሰዎች’ ‘ክፋትን እስከ መጥላት’ የሚያደርስ ለውጥ በአእምሮአቸው ላይ ስለሚያስከትል ትልቅ ጥቅም ያመጣላቸዋል።—መዝሙር 97:10
16. የአምላክ ትምህርት የምናሳየውን መንፈስ ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
16 ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው ለነበረው ለጢሞቴዎስ “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን” ብሎት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:22) ሐዋርያው አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ጢሞቴዎስንና ሌሎቹን ክርስቲያኖች የሚያንቀሳቅሰውን የአእምሮ ኃይል እንዲቀበል ተመኝቶ ነበር። የአምላክ ትምህርት የፍቅር፣ የደግነት እና የየዋህነት መንፈስ እንድናሳይ ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:9–14) ይህ ደግሞ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ከሚኖሩት ከብዙዎቹ ሰዎች ምንኛ የተለየ መንፈስ ነው! እነዚህ ሰዎች ትዕቢተኞች፣ የማያመሰግኑ፣ የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው፣ እርቅን የማይሰሙ፣ ሐሳበ ግትሮች፣ ተድላን የሚወዱ እና እውነተኛው ለአምላክ የማደር ባሕርይ የሌላቸው ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) መለኮታዊው ትምህርት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ማዋላችንን በቀጠልን መጠን በአምላክም ሆነ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ሊያደርገን የሚችለውን መንፈስ እናሳያለን።
በሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ረገድ ጠቃሚ ነው
17. በትሕትና መተባበር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 የይሖዋ ትምህርት ይሖዋን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በትሕትና መተባበር የሚያስገኘውን ጥቅም እንድናስተውል ይረዳናል። (መዝሙር 138:6) እርስ በርሳችን ተግባብተን የምንኖር ብንሆንም በዘመናችን እንዳሉት ብዙ ሰዎች የጽድቅን መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጥስም። ለምሳሌ ያህል በሽማግሌዎች ስብሰባ ወቅት በተሾሙ የበላይ ተመልካቾች መካከል የመግባባት መንፈስ ስለሚኖር ብዙ ጠቃሚ ውጤቶች ሊገኙ ችለዋል። እነዚህ ሰዎች የግል ስሜታቸው ምክንያታዊ አስተሳሰብን እንዳይጋርድ ወይም መከፋፈል እንዳያስከትል እየተጠነቀቁ እውነተኛውን ነገር በዝግታ ይናገራሉ። የጉባኤው አባላት በሙሉ መለኮታዊውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋላቸውን ቢቀጥሉበት ሁላችንም ከሚገኘው የአንድነት መንፈስ ጥቅም እናገኛለን።—መዝሙር 133:1–3
18. መለኮታዊ ትምህርት ለአማኝ ባልንጀሮቻችን ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል?
18 በተጨማሪም መለኮታዊ ትምህርት ለእምነት ባልንጀሮቻችን ተገቢ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ስለሚረዳ ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 6:44) ይሖዋ በተለይ ከ1919 ወዲህ አገልጋዮቹ የፍርዱን መልእክት እንዲያውጁ አድርጓል። ከዚህም የተነሣ የሰይጣን ዓለም የነገሮች ሥርዓት በዚህ ዓለም አቀፍ ማስጠንቀቂያ ተነቃንቆ እየተናጋ ነው። በዚሁ ጊዜ ውስጥ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ማለትም “የተመረጠው ዕቃ” በአምላክ ተስበው ከአሕዛብ ራሳቸውን ለይተዋል፤ እንዲሁም ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር የይሖዋን የአምልኮ ቤት በክብር በመሙላቱ ሥራ እየተካፈሉ ነው። (ሐጌ 2:7) በእርግጥም እነዚህን አምላክ የሳባቸውን የተመረጡ ዕቃዎች ተወዳጅ ባልንጀሮች አድርገን ልንመለከታቸው ይገባናል።
19. የአምላክ ትምህርት ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር የሚፈጠረውን አለመግባባት ስለ መፍታት ምን ያስተምራል?
19 እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን አንዳንድ ጊዜ ችግር ማጋጠሙ አይቀርም። ጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ለመጀመር ሲነሣ በርናባስ ማርቆስን ይዞ ለመሄድ ቆርጦ ነበር። ጳውሎስ በዚህ አሳብ አልተስማማም ምክንያቱም ማርቆስ “ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበረና ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም።” በዚህ ጊዜ በመካከላቸው “መከፋፋት ሆነ።” በርናባስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ሲሄድ ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን ይዞ ወደ ሶርያና ኪልቅያ ሄደ። (ሥራ 15:36–41) ይህ ቅሬታ ከጊዜ በኋላ እንደ ተወገደ ምንም አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም ማርቆስ ከጳውሎስ ጋር በሮም የነበረ ሲሆን ሐዋርያውም ማርቆስን አመስግኖ ጽፏል። (ቆላስይስ 4:10) መለኮታዊ ትምህርት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዱ ክርስቲያኖች በማቴዎስ 5:23, 24 እና በማቴዎስ 18:15–17 ላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉትን የኢየሱስ ምክሮች በሥራ ላይ በማዋል የግል አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ማሳየቱ ነው።
ምንጊዜም ጠቃሚ እና ድል አድራጊ ነው
20, 21. ስለ መለኮታዊ ትምህርት አንዳንድ ነገሮችን መመርመራችን ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
20 መለኮታዊው ትምህርት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞችና ድሎች ባጭሩ መርምረን እንዳየነው ይህን ትምህርት ዘወትር በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ለማዋል መጣር የሚያስፈልገን መሆኑን ያለጥርጥር መመልከት እንችላለን። እንግዲያው በጸሎት የተጋ መንፈስ በመያዝ ከታላቁ አስተማሪያችን የሚገኘውን ትምህርት መማራችንን እንቀጥል። በቅርቡ መለኮታዊው ትምህርት ምንም ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ድል ያደርጋል። የዚህ ዓለም ጠቢባንና ምሁራን የመጨረሻ ትንፋሻቸውን ሲተነፍሱ ድል አድራጊነቱን ያረጋግጣል። (ከ1 ቆሮንቶስ 1:19 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ሲያውቁና ፈቃዱን ሲያደርጉ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር ይሖዋን በማወቅ ትሞላለች። (ኢሳይያስ 11:9) ይህም ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ መሆኑን በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ ያረጋግጣል። ለስሙ ቅድስና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
21 ምንጊዜም መለኮታዊው ትምህርት ድል አድራጊና ጠቃሚም ነው። ታዲያ እናንተ የአምላክን ታላቅ የማስተማሪያ መጽሐፍ በትጋት በማጥናት ከዚህ ትምህርት ተጠቃሚዎች ትሆናላችሁን? ከሚሰጣቸው መመሪያዎችና ምክሮች ጋር ተስማምታችሁ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርጋችኋልን? ለሌሎችስ የዚህን መጽሐፍ እውነት በቅንዓት ትናገራላችሁን? ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ሆናችሁ እነዚህን ለመሰሉ ጥያቄዎች የአዎንታ መልስ ከሰጣችሁ መለኮታዊው ትምህርት ለታላቁ መምህራችንና ለጽንፈ ዓለሙ ጌታ ይሖዋ ክብር ሙሉ በሙሉ ድል የሚነሳበትን ጊዜ በተስፋ ልትጠባበቁ ትችላላችሁ።
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
◻ መለኮታዊው ትምህርት በሕይወታችን ላይ ምን ለውጥ ያስከትላል?
◻ የይሖዋ ትምህርት ሰዎች ለትምህርት ያላቸውን ፍላጎት በማሟላት ላይ የሚገኘው እንዴት ነው?
◻ መለኮታዊ ትምህርት በአስተሳሰባችንና በዝንባሌያችን ላይ ምን ጠቃሚ ውጤት ያስከትላል?
◻ የአምላክ ትምህርት ከሰዎች ጋር ተግባብቶ በመኖር ረገድ ጠቃሚነቱ የተረጋገጠው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መለኮታዊ ትምህርት ኖኅ እንዳደረገው አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር እንዴት ማድረግ እንደምንችል ያሳየናል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሁሉም ብሔራት ሕዝቦች ወደ ይሖዋ ተራራ እየጎረፉ ናቸው