ዘፍጥረት
6 ሰዎች በምድር ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሄድ ሴቶች ልጆችን ወለዱ፤ 2 የእውነተኛው አምላክ ልጆችም*+ የሰዎች ሴቶች ልጆች ውብ እንደሆኑ አስተዋሉ። በመሆኑም የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው ወሰዱ። 3 ከዚያም ይሖዋ “ሰው ሥጋ ስለሆነ* መንፈሴ ሰውን ለዘላለም አይታገሥም።+ በመሆኑም ዘመኑ 120 ዓመት ይሆናል”+ አለ።
4 በዚያ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ኔፍሊም* በምድር ላይ ነበሩ። በዚያ ጊዜም የእውነተኛው አምላክ ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር ግንኙነት ፈጸሙ፤ ሴቶቹም ወንዶች ልጆችን ወለዱላቸው። እነሱም በጥንት ዘመን በኃያልነታቸው ዝና ያተረፉ ሰዎች ነበሩ።
5 በዚህም የተነሳ ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛና የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ+ እንደሆነ ተመለከተ። 6 ይሖዋም ሰዎችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤* ልቡም አዘነ።+ 7 በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “የፈጠርኳቸውን ሰዎች ከምድር ገጽ ጠራርጌ አጠፋለሁ፤ ሰውን ጨምሮ የቤት እንስሳትን እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትን አጠፋለሁ፤ ምክንያቱም እነሱን በመፍጠሬ ተጸጽቻለሁ።” 8 ኖኅ ግን በይሖዋ ፊት ሞገስ አገኘ።
9 የኖኅ ታሪክ ይህ ነው።
ኖኅ ጻድቅ ሰው ነበር።+ በዘመኑ* ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን* የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።+ 10 ኖኅ ከጊዜ በኋላ ሴም፣ ካምና ያፌት+ የተባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። 11 ይሁንና ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። 12 አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር፤+ ሰው* ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር።+
13 ከዚህ በኋላ አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በእነሱ የተነሳ ምድር በዓመፅ ስለተሞላች ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ስለሆነም እነሱን ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።+ 14 አንተ ከጎፈር እንጨት ለራስህ መርከብ* ሥራ።+ በመርከቡም ውስጥ የተለያዩ ክፍሎችን ሥራ፤ እንዲሁም መርከቡን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ቅጥራን*+ ለቅልቀው። 15 መርከቡንም የምትሠራው እንደሚከተለው ነው፦ የመርከቡ ርዝመት 300 ክንድ፣* ወርዱ 50 ክንድ እንዲሁም ከፍታው 30 ክንድ ይሁን። 16 በመርከቡም ላይ ከጣሪያው ሥር አንድ ክንድ ቁመት ያለው ብርሃን ማስገቢያ የሚሆን መስኮት* ሥራ፤ የመርከቡንም በር በጎኑ በኩል አድርግ፤+ መርከቡም ምድር ቤት እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ይኑረው።
17 “እኔ ደግሞ ከሰማያት በታች የሕይወት እስትንፋስ* ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃ+ አመጣለሁ። በምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይጠፋል።+ 18 እኔም ከአንተ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ አንተም ወደ መርከቡ መግባት አለብህ፤ አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ወደ መርከቡ መግባት ይኖርባችኋል።+ 19 ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲተርፉ ከሁሉም ዓይነት ሕያው ፍጡር+ ተባዕትና እንስት እያደረግክ ሁለት ሁለት ወደ መርከቡ አስገባ፤+ 20 በሕይወት እንዲተርፉ የሚበርሩ ፍጥረታት እንደየወገናቸው፣ የቤት እንስሳት እንደየወገናቸው እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳት ሁሉ እንደየወገናቸው ሁለት ሁለት እየሆኑ ከአንተ ጋር ይግቡ።+ 21 ለአንተም ሆነ ለእንስሳቱ ምግብ እንዲሆን ማንኛውንም ዓይነት ምግብ+ ሰብስበህ ይዘህ ትገባለህ።”