የሕይወትን ዳቦ ቀምሰኸዋል?
አገር ጎብኚዎቹ ርቧቸዋል። በጥንታዊቷ የቤተልሔም ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን ሲጎበኙ የቆዩ ሲሆን በአካባቢው የተለመደውን ምግብ መብላት ፈልገዋል። ከመካከላቸው አንዱ፣ ፈላፍል የሚዘጋጅበት ምግብ ቤት ተመለከተ፤ ፈላፍል የሚባለው የተፈጨ ሽንብራ ከቲማቲም፣ ከቀይ ሽንኩርትና ከሌሎችም አትክልቶች ጋር ሆኖ ፒታ ከሚባል ዳቦ ጋር አብሮ የሚቀርብ ጣፋጭ ምግብ ነው። ጎብኚዎቹ ጣት የሚያስቆረጥመውን ይህን ምግብ መመገባቸው ጉብኝታቸውን ለመቀጠል የሚያስችል ኃይል ሰጣቸው።
እነዚህ ጎብኚዎች አይወቁት እንጂ ፒታ የተባለው ዳቦ በቤተልሔም ከጥንት ጀምሮ ይዘጋጅ ነበር፤ ምናልባትም በዚያ ዕለት ከጎበኟቸው ነገሮች ሁሉ በፊት የነበረው ይህ ዳቦ ሳይሆን አይቀርም። ቤተልሔም የሚለው ስም “የዳቦ ቤት” ማለት ሲሆን በዚያ አካባቢ በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ዳቦ ሲጋገር ኖሯል። (ሩት 1:22፤ 2:14a) በዛሬው ጊዜ ፒታ፣ በቤተልሔም በጣም ከተለመዱት ዳቦዎች አንዱ ነው።
ወደ አራት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ከቤተልሔም በስተ ደቡብ በሚገኝ ቦታ ላይ የአብርሃም ሚስት ሣራ፣ ድንገት ለመጡባቸው ሦስት እንግዶች ትኩስ “ቂጣ” ጋግራ አቅርባ ነበር። (ዘፍጥረት 18:6) ሣራ የተጠቀመችበት “ስልቅ ዱቄት” ኤመር ከተባለው ስንዴ ወይም ከገብስ የተዘጋጀ ሊሆን ይችላል። ሣራ ይህን ቂጣ በፍጥነት ማዘጋጀት ነበረባት፤ ቂጣውን የጋገረችው በፍም ወይም በጋለ ድንጋይ ላይ ሊሆን ይችላል።—1 ነገሥት 19:6
ይህ ዘገባ እንደሚያመለክተው የአብርሃም ቤተሰብ የሚበሉትን ዳቦ ወይም ቂጣ የሚያዘጋጁት ራሳቸው ነበሩ። ቤተሰቡ ከቦታ ቦታ ይጓዝ ስለነበር ሣራም ሆነች አገልጋዮቿ በትውልድ ከተማዋ በዑር ይጠቀሙባቸው የነበሩት ዓይነት የዳቦ መጋገሪያ ምድጃዎች አይኖሯቸው ይሆናል። ሣራ ስልቅ ዱቄቱን የምታዘጋጀው በአካባቢው ከሚገኝ እህል ነበር። ዱቄቱ የሚዘጋጀው በሄዱበት ሁሉ ይዘውት በሚጓዙት የእጅ ወፍጮ እንዲሁም በሙቀጫና ዘነዘና ሊሆን ስለሚችል ሥራው አድካሚ ነበር።
አብርሃም ከኖረ ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ ለእስራኤላውያን በተሰጠው የሙሴ ሕግ ላይ ወፍጮና መጅን ለብድር በመያዣነት መውሰድ የተከለከለ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ “የሰውን ነፍስ” ወይም መተዳደሪያ እንደመውሰድ ይሆናል። (ዘዳግም 24:6) አንድ ቤተሰብ ወፍጮ ከሌለው የዕለት ምግቡን ማዘጋጀት ስለማይችል አምላክ ወፍጮን በጣም አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል።—“በጥንት ዘመን በየዕለቱ መፍጨትና መጋገር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
የሰውን ልብ የሚያበረታ ዳቦ
ዳቦ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት የተጠቀሰ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ዳቦ የሚለውን ቃል ብዙውን ጊዜ ምግብን ለማመልከት ተጠቅመውበታል። ኢየሱስ፣ የአምላክ አገልጋዮች በእሱ በመተማመን “የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:11) እዚህ ላይ “ምግብ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዳቦ” ማለት ቢሆንም ቃሉ ምግብን በአጠቃላይ ያመለክታል፤ በመሆኑም ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሲናገር አምላክ በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ምግብ እንደሚሰጠን መተማመን እንደምንችል መግለጹ ነበር።—መዝሙር 37:25
ይሁን እንጂ ከዳቦ ወይም ከምግብ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። ኢየሱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” ብሏል። (ማቴዎስ 4:4) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ፣ እስራኤላውያን የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሙሉ በሙሉ ከአምላክ ያገኙ በነበረበት ወቅት የተጻፈ ነው። ይህ የሆነው ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆዩ ነበር። ወደ ሲና ምድረ በዳ ከገቡ አንድ ወር ገደማ ስለሆናቸው የያዙት ቀለብ እያለቀ ነበር። በዚያ ደረቅ ምድረ በዳ ውስጥ በረሃብ ሊያልቁ እንደሆነ ስላሰቡ በግብፅ ‘የፈለጉትን ያህል ምግብ መመገብ’ ይችሉ እንደነበር በመግለጽ ክፉኛ አጉረመረሙ።—ዘፀአት 16:1-3
በግብፅ ጥሩ ዳቦ ይዘጋጅ እንደነበር ጥርጥር የለውም። በሙሴ ዘመን፣ ለግብፃውያን የተለያዩ ዳቦዎችንና ጣፋጭ ብስኩቶችን የሚያቀርቡ የሠለጠኑ ጋጋሪዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅትም ይሖዋ የሚበሉት እንደማያሳጣቸው ግልጽ ነው። ይሖዋ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ” በማለት ቃል ገባላቸው። እንዳለውም ማለዳ ላይ ከሰማይ ምግብ ሰጣቸው፤ ምግቡ “ስስ የሆነ አመዳይ” ወይም ጤዛ ይመስል ነበር። እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩት “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። ሙሴም “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው” አላቸው። እነሱም “መና”b ብለው የጠሩት ሲሆን ለቀጣዮቹ 40 ዓመታት የተመገቡት ይህን ምግብ ነበር።—ዘፀአት 16:4, 13-15, 31
እስራኤላውያን በተአምር የተሰጣቸውን መና መጀመሪያ ሲያዩ በጣም ተገርመው መሆን አለበት። ጣዕሙ “ከማር እንደ ተጋገረ ቂጣ” ሲሆን ሁሉም ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ማግኘት ይችል ነበረ። (ዘፀአት 16:18) ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሕዝቡ በግብፅ ይበሉት የነበረውን የተለያየ ምግብ መናፈቅ ጀመሩ። “ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!” በማለት አጉረመረሙ። (ዘኍልቍ 11:6) ቆየት ብለውም “ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” በማለት አማረሩ። (ዘኍልቍ 21:5) ‘ከሰማይ የመጣው እንጀራ’ ወይም ምግብ፣ ውሎ አድሮ የሚያስጠላና አስጸያፊ ነገር ሆኖ ታያቸው።—መዝሙር 105:40
የሕይወት ዳቦ
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ እንደ ሌሎች ብዙ ነገሮች ሁሉ ዳቦ ወይም ምግብም ሊሰለች ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አቅልለን ልንመለከተው የማይገባ ልዩ ዳቦ እንዳለ ይናገራል። ኢየሱስ እስራኤላውያን በንቀት ካጣጣሉት መና ጋር ያነጻጸረው ይህ ዳቦ፣ ዘላለማዊ ጥቅሞች የሚያስገኝ ነው።
ኢየሱስ ለሚያዳምጡት ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ የሕይወት ዳቦ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። ከሰማይ የወረደውን ዳቦ የሚበላ ሁሉ ግን አይሞትም። ከሰማይ የወረደው ሕያው ዳቦ እኔ ነኝ፤ ከዚህ ዳቦ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ዳቦው ደግሞ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”—ዮሐንስ 6:48-51
ከኢየሱስ አድማጮች መካከል ብዙዎቹ ኢየሱስ የጠቀሳቸው “ዳቦ” እና “ሥጋ” የሚሉት ቃላት ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳላቸው አልተረዱም ነበር። ሆኖም ምሳሌው በጣም ተስማሚ ነበር። መናው እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ባሳለፏቸው 40 ዓመታት በሕይወት እንዳቆያቸው ሁሉ ዳቦም አይሁዳውያን በየዕለቱ የሚጠቀሙበት ምግባቸው ነበር። መና ከአምላክ የተሰጠ ስጦታ ቢሆንም የዘላለም ሕይወት አላስገኘም። በሌላ በኩል ግን የኢየሱስ መሥዋዕት በእሱ ለሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያስገኛል። በእርግጥም ኢየሱስ “የሕይወት ዳቦ” ነው።
ሲርብህ ቁራሽ ዳቦ አንስተህ ትበላ ይሆናል። እንዲሁም ‘የዕለት ምግብህን’ ስለሰጠህ አምላክን እንደምታመሰግነው ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 6:11) እንዲህ ዓይነት ጣፋጭ ምግብ ማግኘታችንን የምናደንቅ ቢሆንም ‘ከሕይወት ዳቦ’ ማለትም ከኢየሱስ ክርስቶስ የምናገኘውን ጥቅም ፈጽሞ መርሳት የለብንም።
በሙሴ ዘመን ከነበሩት ምሥጋና ቢስ እስራኤላውያን በተለየ መልኩ እኛ ይህን በዋጋ ሊተመን የማይችል ዳቦ አቅልለን እንደማንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዛቴን ትጠብቃላችሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 14:15) የኢየሱስን ትእዛዛት የምንጠብቅና የሕይወትን ዳቦ የምንበላ ከሆነ የተትረፈረፈ ምግብ እያገኘን ለዘላለም የመኖር አስደሳች ተስፋ ይኖረናል።—ዘዳግም 12:7
a በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “እንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ዳቦን” ያመለክታል።
b “መና” የሚለው ስያሜ “ይህ ነገር ምንድን ነው? የሚል ትርጉም ካለው “ማን ሁ?” ከሚለው የዕብራይስጥ አገላለጽ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም።